በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የትዳር ጓደኛ ሲከዳ ሁኔታውን መቋቋም

የትዳር ጓደኛ ሲከዳ ሁኔታውን መቋቋም

የትዳር ጓደኛ ሲከዳ ሁኔታውን መቋቋም

ማርጋሪታና ባሏ ራውል ለብዙ ዓመታት የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ሆነው ይሖዋን አገልግለዋል። * ይሁን እንጂ የመጀመሪያ ልጃቸው ከተወለደ ብዙም ሳይቆይ ራውል ከይሖዋ መራቅ ጀመረ። ውሎ አድሮም ራውል ከሥነ ምግባር ውጪ የሆነ አኗኗር መከተል በመጀመሩ ከክርስቲያን ጉባኤ ተወገደ። ማርጋሪታ “ይህ ሁሉ ሲደርስብኝ የምሞት መስሎኝ ነበር” ትላለች። “ልቤ ተሰበረ፤ ምን እንደማደርግ ግራ ገብቶኝ ነበር።”

ጄን ደግሞ ባሏ የከዳት ከዚህ ለየት ባለ መንገድ ነበር፤ ታምነውና ትወደው የነበረው ባሏ እንደጠበቀችው ሳይሆን ቀረ። ከተጋቡ ብዙም ሳይቆይ አካላዊ ጥቃት ያደርስባት ጀመር። “ለመጀመሪያ ጊዜ በቡጢ ሲመታኝ ክው ብዬ ቀረሁ፤ በሃፍረት ተዋጥኩ እንዲሁም እንደተዋረድኩ ተሰማኝ” ትላለች ጄን። “በሌሎች ጊዜያትም ከመታኝ በኋላ ይቅርታ እንዳደርግለት ይለምነኝ ጀመር፤ እንዲህ ማድረግ አመል ሆነበት። እኔም ምንጊዜም ይቅርታ ማድረግና ጉዳዩን መርሳት ክርስቲያናዊ ግዴታዬ እንደሆነ አስብ ነበር። እንዲሁም ችግራችንን ለሌላ ሰው ሌላው ቀርቶ በጉባኤያችን ላሉ ሽማግሌዎች እንኳ መናገር ታማኝነት ማጉደል እንደሆነ ይሰማኝ ነበር። ባለቤቴ በእኔ ላይ አካላዊ ጥቃት ማድረሱንና ከዚያ በኋላ ይቅርታ መጠየቁን የቀጠለ ሲሆን በዚህ ሁኔታ ዓመታት አለፉ። በዚህ ሁሉ ጊዜ ባሌ እንዲወደኝ ለማድረግ ከእኔ የሚጠበቅ አንድ ነገር ያለ ይመስለኝ ነበር። በመጨረሻ እኔንና ሴት ልጃችንን ጥሎን ሲሄድ ጥፋተኛዋ እኔ እንደሆንኩና ትዳራችን እንዳይፈርስ ለማድረግ አነጋገሬም ሆነ ድርጊቴ የተሻለ ሊሆን ይገባ እንደነበር ተሰማኝ።”

አንቺም እንደ ማርጋሪታና ጄን ባልሽ ስለከዳሽ ስሜትሽ ተጎድቶ እንዲሁም የገንዘብ ችግር አጋጥሞሽና መንፈሳዊ አቋምሽ ተናግቶ ይሆናል። ባል ከሆንክ ደግሞ ሚስትህ ስለከዳችህ ስሜታዊ ሥቃይና ልዩ ልዩ ችግሮች እያጋጠሙህ ሊሆን ይችላል። የምንኖረው መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ እንደተናገረው “ለመቋቋም በሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን” ውስጥ ለመሆኑ ምንም ጥያቄ የለውም። ትንቢቱ እንደሚያመለክተው “በመጨረሻዎቹ ቀኖች” በአብዛኞቹ ቤተሰቦች ውስጥ ተፈጥሯዊ ፍቅር ሙሉ በሙሉ ስለሚጠፋ ቤተሰብ ችግር ላይ ይወድቃል። አንዳንዶች አምላክን እናገለግላለን ቢሉም ድርጊታቸው ይህ ውሸት መሆኑን ያሳያል። (2 ጢሞ. 3:1-5) እነዚህ ችግሮች በእውነተኛ ክርስቲያኖች ላይም ሊደርሱ ይችላሉ፤ ታዲያ የትዳር ጓደኛ ሲከዳ ሁኔታውን መቋቋም የሚቻለው እንዴት ነው? *

ራስሽን ይሖዋ በሚያይሽ መንገድ ተመልከቺ

የምትወጂው ሰው ይህን ያህል ሊጎዳሽ መቻሉን ማመን መጀመሪያ ሊከብድሽ ይችላል። ሌላው ቀርቶ እሱ ለፈጸመው ኃጢአት ራስሽን መውቀስ ትጀምሪ ይሆናል።

ይሁንና ፍጹም ሰው የነበረው ኢየሱስም እንኳ ያምነውና ይወደው በነበረ ሰው እንደተከዳ አስታውሺ። ኢየሱስ የቅርብ ወዳጆቹ የነበሩትን ሐዋርያት የመረጣቸው ጉዳዩን በጸሎት ብዙ ካሰበበት በኋላ ነበር። መጀመሪያ ላይ 12ቱም ሐዋርያት ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ነበሩ። ስለዚህ ኢየሱስ፣ ይሁዳ “ከሃዲ” ሲሆን በጣም እንዳዘነ ጥርጥር የለውም። (ሉቃስ 6:12-16) ይሁን እንጂ ይሖዋ፣ ይሁዳ ለወሰደው እርምጃ ኢየሱስን ተጠያቂ አላደረገውም።

እርግጥ ነው፣ በአሁኑ ጊዜ ፍጹም የሆነ የትዳር ጓደኛ የለም። ሁለቱም የትዳር ጓደኛሞች ስህተት ይሠራሉ። አንድ መዝሙራዊ በመንፈስ ተመርቶ “እግዚአብሔር ሆይ፤ ኀጢአትን ብትቈጣጠር፣ ጌታ ሆይ፤ ማን ሊቆም ይችላል?” በማለት ሐቁን አስቀምጦታል። (መዝ. 130:3) ሁለቱም የትዳር ተጓዳኞች ይሖዋን በመምሰል አንዳቸው የሌላውን አለፍጽምና ችለው ለማለፍ ፈቃደኞች መሆን ይኖርባቸዋል።—1 ጴጥ. 4:8

ያም ቢሆን ግን “እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለአምላክ መልስ እንሰጣለን።” (ሮም 14:12) አንድ ሰው መጥፎ ቃላት በመናገር ወይም አካላዊ ጥቃት በመሰንዘር የትዳር ጓደኛውን መበደል አመል ከሆነበት ይሖዋ ተጠያቂ የሚያደርገው እንዲህ ያለውን ግለሰብ ነው። ይሖዋ በሌሎች ላይ አካላዊ ጥቃት በመሰንዘር ዓመፅ የሚፈጽሙና የሚሳደቡ ሰዎችን ያወግዛል፤ በመሆኑም አንድ ሰው ለትዳር ጓደኛው ፍቅርና አክብሮት እንደጎደለው በግልጽ የሚያሳይ እንዲህ ዓይነት ድርጊት ለመፈጸም ምንም ምክንያት ሊኖረው አይችልም። (መዝ. 11:5፤ ኤፌ. 5:33፤ ቆላ. 3:6-8) እንዲያውም አንድ ክርስቲያን በቁጣ የመገንፈል ልማድ ካለውና ንስሐ ገብቶ አካሄዱን የማያስተካክል ከሆነ ከክርስቲያን ጉባኤ መወገድ አለበት። (ገላ. 5:19-21፤ 2 ዮሐ. 9, 10) አንዲት ሚስት የትዳር ጓደኛዋ እንዲህ ዓይነቱን ክርስቲያናዊ ያልሆነ ድርጊት የሚፈጽም ከሆነ ጉዳዩን ለሽማግሌዎች በመናገሯ የጥፋተኝነት ስሜት ሊሰማት አይገባም። በእርግጥም ይሖዋ እንዲህ ያለ በደል ለደረሰባቸው ሰዎች በጣም ያዝናል።

አንድ የትዳር ጓደኛ ምንዝር ሲፈጽም ኃጢአት የሚሠራው ታማኝ በሆነው የትዳር ጓደኛ ላይ ብቻ ሳይሆን በይሖዋ ላይ ጭምር ነው። (ማቴ. 19:4-9፤ ዕብ. 13:4) ታማኝ የሆነው የትዳር ጓደኛ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት መሠረት ለመኖር የሚጥር እስከሆነ ድረስ ሌላኛው ወገን ኃጢአት በመፈጸሙ ጥፋተኛ እንደሆነ ሊሰማው አይገባም።

የትዳር ጓደኛሽ ከድቶሽ ከሆነ ይሖዋ ምን እንደሚሰማሽ የሚያውቅ መሆኑን አስታውሺ። ይሖዋ ራሱን የእስራኤል ብሔር ባል እንደሆነ አድርጎ የገለጸ ሲሆን ይህ ሕዝብ በፈጸመው መንፈሳዊ ምንዝር ምክንያት የተሰማውን ሐዘን የሚገልጹ ልብ የሚነኩ ሐሳቦችን በቃሉ ውስጥ አስፍሮልናል። (ኢሳ. 54:5, 6፤ ኤር. 3:1, 6-10) የትዳር ጓደኛሽ ከድቶሽ ከሆነ የምታፈሽውን እንባ ይሖዋ እንደሚመለከት እርግጠኛ መሆን ትችያለሽ። (ሚል. 2:13, 14) ይሖዋ ማጽናኛና ማበረታቻ እንደሚያስፈልግሽ ያውቃል።

ይሖዋ ማጽናኛ የሚሰጥበት መንገድ

ይሖዋ ማጽናኛ የሚሰጥበት አንዱ መንገድ በክርስቲያን ጉባኤ አማካኝነት ነው። ጄን እንዲህ ዓይነቱን ማጽናኛ አግኝታለች። “የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ጉባኤያችንን የጎበኘው ስሜቴ በጣም ተጎድቶ በነበረበት ወቅት ላይ ነበር” በማለት ጄን ታስታውሳለች። “ባለቤቴ ለመፋታት ጥያቄ በማቅረቡ ምክንያት ምን ያህል እንዳዘንኩ የወረዳ የበላይ ተመልካቹ አውቆ ነበር። ጊዜ ወስዶ ከእኔ ጋር በመወያየት እንደ 1 ቆሮንቶስ 7:15 ባሉት ጥቅሶች ላይ እንዳስብባቸው ረዳኝ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና እሱ የሰጠኝ ደግነት የተንጸባረቀበት ሐሳብ የነበረኝ የጥፋተኝነት ስሜት ቀለል እንዲልልኝ እንዲሁም በተወሰነ መጠን የአእምሮ ሰላም እንዳገኝ ረድቶኛል።” *

ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ማርጋሪታም ይሖዋ በክርስቲያን ጉባኤ አማካኝነት ተግባራዊ እርዳታ እንደሚሰጥ መገንዘብ ችላለች። እንዲህ ብላለች፦ “ባለቤቴ የንስሐ ዝንባሌ እንደሌለው ግልጽ በሆነ ጊዜ ልጆቼን ይዤ ወደ ሌላ ከተማ ሄድኩ። እዚያ ስደርስም ሁለት ክፍል ቤት ተከራየሁ። በቀጣዩ ቀን በሐዘን ተውጬ ዕቃዎቻችንን እያወጣሁ ሳለ በሩ ተንኳኳ። በሩን ያንኳኳችው አጠገባችን የምትኖረው የቤቱ ባለቤት እንደምትሆን ጠብቄ ነበር። የሚገርመው ነገር፣ የመጣችው እናቴን መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠናቻትና ቤተሰባችን እውነትን እንዲያውቅ የረዳችው እህት ነበረች። ይህች እህት እኛ ቤት የመጣችው እኔ እዚያ እንዳለሁ ስላወቀች ሳይሆን ቤቱን ያከራየችኝን ሴት መጽሐፍ ቅዱስ ታስጠናት ስለነበር ነው። እሷን ሳገኝ በጣም ከመደሰቴ የተነሳ ስሜቴን መቆጣጠር አልቻልኩም። ያለሁበትን ሁኔታ ስነግራት አብራኝ አለቀሰች። በዚያን ዕለት በሚደረገው ስብሰባ ላይ እንድንገኝ ወዲያውኑ ዝግጅት አደረገችልን። ጉባኤው ጥሩ አቀባበል ያደረገልን ሲሆን ሽማግሌዎቹም የቤተሰቤን መንፈሳዊ ፍላጎት ማሟላት እንድችል እኔን ለመርዳት ዝግጅት አደረጉ።”

ሌሎች ሊረዱ የሚችሉበት መንገድ

በእርግጥም የክርስቲያን ጉባኤ አባላት በብዙ መንገዶች ተግባራዊ ድጋፍ መስጠት ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ማርጋሪታ በወቅቱ ሥራ ማግኘት ነበረባት። በጉባኤ ውስጥ ያለ አንድ ቤተሰብ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ልጆቿን ከትምህርት ቤት ሲመለሱ በመንከባከብ ሊረዷት ፈቃደኛ መሆናቸውን ገለጹላት።

“ወንድሞችና እህቶች ከእኔና ከልጆቼ ጋር አብረውን ለማገልገል ሲጠይቁኝ ከምንም በላይ ደስ ይለኛል” ትላለች ማርጋሪታ። የጉባኤው አባላት እንዲህ ያለውን ተግባራዊ እርዳታ በመስጠት ‘አንዳቸው የሌላውን ሸክም ይሸከማሉ፤’ በዚህ መንገድ “የክርስቶስን ሕግ” ይፈጽማሉ።—ገላ. 6:2

የትዳር ጓደኛቸው በፈጸመው ኃጢአት የተነሳ እየተሠቃዩ ያሉ ሰዎች እንዲህ ዓይነቱን ተግባራዊ እርዳታ ከልብ ያደንቃሉ። ባሏ 15,000 የአሜሪካ ዶላር ዕዳና አራት ልጆች ጥሎባት የሄደ ሞኒክ የምትባል እህት እንዲህ ብላለች፦ “መንፈሳዊ ወንድሞቼና እህቶቼ በጣም አፍቃሪዎች ነበሩ። እነሱ ድጋፍ ባያደርጉልኝ ኖሮ ምን እሆን እንደነበረ ማሰብ አልችልም። ይሖዋ በጣም ግሩም ወንድሞች እንደሰጠኝ ይሰማኛል፤ እነዚህ ወንድሞች ልጆቼን በጣም ረድተዋቸዋል። ልጆቼ እንዲህ ያለውን ድጋፍ በማግኘታቸው በመንፈሳዊ ሲጎለምሱ ማየት ችያለሁ፤ ይህም ታላቅ ደስታ አምጥቶልኛል። ምክር ሲያስፈልገኝ ሽማግሌዎች ይረዱኝ ነበር። የማወራው ሰው ባስፈለገኝ ጊዜም ያዳምጡኝ ነበር።”—ማር. 10:29, 30

እርግጥ ነው፣ አፍቃሪ የሆነ ወዳጅ አንድ ሰው ስላጋጠመው አሳዛኝ ሁኔታ ማውራት የማይፈልግበት ጊዜ ሊኖር እንደሚችል ይገነዘባል። (መክ. 3:7) ማርጋሪታ እንዲህ ትላለች፦ “ስላጋጠመኝ ችግር አይሁን እንጂ ስለ ሌላ ስለማንኛውም ነገር ማለትም ስለ ስብከቱ ሥራ፣ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችንና ስለ ልጆቻችን በአዲሱ ጉባኤያችን ውስጥ ካሉት እህቶች ጋር ማውራት አብዛኛውን ጊዜ ያስደስተኛል። ያጋጠመኝን ነገር ስለማያነሱብኝና ያለፈውን ወደኋላ ትቼ ሕይወትን እንደ አዲስ እንድጀምር ስለረዱኝ አመስጋኝ ነኝ።”

ብድር የመመለስን ስሜት አስወግጂ

የትዳር ጓደኛቸው ለፈጸመው ኃጢአት በሆነ መንገድ ተጠያቂ እንደሆኑ ከሚያስቡ ሰዎች በተቃራኒ አንቺ ደግሞ በእሱ ጥፋት ምክንያት እየተሠቃየሽ በመሆንሽ ቂም ትይዢ ይሆናል። እንዲህ ያለው ስሜት በውስጥሽ እንዲያድግ ከፈቀድሽለት ለይሖዋ ታማኝ ሆነሽ ለመቀጠል ያደረግሽውን ቁርጥ ውሳኔ ሊሸረሽረው ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ታማኝነቱን ያጎደለውን የትዳር ጓደኛሽን በሆነ መንገድ ለመበቀል ትፈተኚ ይሆናል።

እንደዚህ ያለ ስሜት በውስጥሽ ሥር እየሰደደ እንዳለ ከተሰማሽ ኢያሱና ካሌብ የተዉትን ምሳሌ መለስ ብለሽ ማሰቡ ጠቃሚ ነው። እነዚህ ታማኝ ሰዎች የተስፋይቱን ምድር ለመሰለል ሲሉ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ነበር። ሌሎቹ ሰላዮች እምነት ስለጎደላቸው ሕዝቡ ይሖዋን ከመታዘዝ ወደኋላ እንዲል አደረጉት። እንዲያውም ኢያሱና ካሌብ ሕዝቡ ለይሖዋ ታማኝ ሆነው እንዲቀጥሉ ለማበረታታት በሞከሩ ጊዜ አንዳንዶቹ በድንጋይ ሊወግሯቸው ፈልገው ነበር። (ዘኍ. 13:25 እስከ 14:10) እስራኤላውያን ባደረጉት ነገር የተነሳ ኢያሱና ካሌብ ያለ ጥፋታቸው ለ40 ዓመት በምድረ በዳ ለመንከራተት ተገደዋል።

ኢያሱና ካሌብ በዚህ በጣም አዝነው ሊሆን እንደሚችል የታወቀ ነው፤ ያም ሆኖ የወንድሞቻቸው በደል እንዲያስመርራቸው አልፈቀዱም። ትኩረት ያደረጉት መንፈሳዊ ሚዛናቸውን በመጠበቅ ላይ ነበር። በምድረ በዳ ያሳለፉት 40 ዓመት ሲፈጸም ከሌዋውያን ጋር በመሆን በእነሱ ትውልድ ከነበሩት ሰዎች መካከል በሕይወት ተርፈው ወደ ተስፋይቱ ምድር የመግባት መብት በማግኘት ተክሰዋል።—ዘኍ. 14:28-30፤ ኢያሱ 14:6-12

ታማኝነቱን ያጎደለው የትዳር ጓደኛሽ በፈጸመው ድርጊት የተነሳ ለረጅም ጊዜ ትሠቃዪ ይሆናል። ትዳራችሁ ቢያከትምም አንቺ ግን ስሜትሽ ሊጎዳ እንዲሁም የገንዘብ ችግር ሊያጋጥምሽ ይችላል። ይሁን እንጂ አሉታዊ በሆኑ ሐሳቦች ላይ በማተኮር ከመቆዘም ይልቅ በምድረ በዳ በነበሩት እምነት የለሽ እስራኤላውያን ታሪክ እንደታየው ይሖዋ፣ ሆን ብለው መሥፈርቶቹን ችላ የሚሉ ሰዎችን እንዴት እንደሚቀጣ ከሁሉ በተሻለ መንገድ የሚያውቅ መሆኑን አስታውሺ።—ዕብ. 10:30, 31፤ 13:4

ሁኔታውን ልትቋቋሚው ትችያለሽ!

አፍራሽ የሆኑ ሐሳቦች ሸክም እንዲሆኑብሽ በመፍቀድ ፈንታ አእምሮሽን በመንፈሳዊ ነገሮች ሙይው። “በድምፅ የተቀረጹ የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! እትሞችን ማዳመጥ ሁኔታውን ለመቋቋም ረድቶኛል” ትላለች ጄን። “ስብሰባዎችም ከፍተኛ የብርታት ምንጭ ሆነውልኛል። በስብሰባዎች ላይ ንቁ ተሳትፎ ማድረጌ አእምሮዬ በችግሮቼ ላይ እንዳያተኩር ለማድረግ ረድቶኛል። የስብከቱ ሥራም በተመሳሳይ መንገድ ረድቶኛል። ሌሎች በይሖዋ ላይ እምነት እንዲያሳድሩ በመርዳት እኔም የራሴን እምነት አጠንክሬያለሁ። እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቼን መርዳት አእምሮዬ ይበልጥ አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩር ለማድረግ አስችሎኛል።”

ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ሞኒክ እንዲህ ትላለች፦ “በስብሰባዎች ላይ አዘውትሬ መገኘቴና የቻልኩትን ያህል ዘወትር በመስክ አገልግሎት መሳተፌ ችግሩን ለመቋቋም አስችሎኛል። ቤተሰቤ እርስ በርስም ሆነ ከጉባኤው ጋር ተቀራርቧል። የደረሰብኝ ከባድ መከራ የራሴን ድክመቶች እንዳውቅ ረድቶኛል። እምነቴ ቢፈተንም በይሖዋ እርዳታ ሁኔታውን መቋቋም ችያለሁ።”

አንቺም ተመሳሳይ መከራዎችን መቋቋም ትችያለሽ። መከዳት ስሜታዊ ሥቃይ የሚያስከትል ቢሆንም ጳውሎስ በመንፈስ አነሳሽነት የሰጠውን የሚከተለውን ምክር በተግባር ለማዋል ጥረት አድርጊ፦ “ካልታከትን ወቅቱ ሲደርስ ስለምናጭድ ተስፋ ቆርጠን መልካም ሥራ መሥራታችንን አንተው።”—ገላ. 6:9

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.2 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.4 ምንም እንኳ ይህ ትምህርት የተዘጋጀው ከሚስቶች አንጻር ቢሆንም የቀረቡት ሐሳቦች የትዳር ጓደኞቻቸው ለከዷቸው ባሎችም ይሠራሉ።

^ አን.13 መለያየትንና ፍቺን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ሰፊ ማብራሪያ ለማግኘት ‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’ የሚለውን መጽሐፍ ከገጽ 125-130, 219-221 ተመልከት።

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የትዳር ጓደኛቸው የከዳቸው ክርስቲያኖች ሌሎች በመስክ አገልግሎት ሲረዷቸው ደስ ይላቸዋል