በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጉባኤውን ማነጻችሁን ቀጥሉ

ጉባኤውን ማነጻችሁን ቀጥሉ

ጉባኤውን ማነጻችሁን ቀጥሉ

“እርስ በርሳችሁ መጽናናታችሁንና እርስ በርስ መተናነጻችሁን ቀጥሉ።”—1 ተሰ. 5:11

1. በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ መሆን ምን በረከቶች ያስገኛል? ያም ሆኖ የትኞቹ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሊያጋጥሙን ይችላሉ?

የክርስቲያን ጉባኤ አባል መሆንህ በእርግጥም ትልቅ በረከት ነው። ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና መሥርተሃል። ቃሉን እንደ መመሪያ አድርገህ መቀበልህ ክርስቲያናዊ ያልሆነ አኗኗር ከሚያመጣው ጣጣ ጠብቆሃል። ለአንተ በጎ በሚያስቡ እውነተኛ ጓደኞች ተከበሃል። አዎን፣ በረከቶቹ ብዙ ናቸው። ያም ሆኖ አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ከተለያዩ ችግሮች ጋር እየታገሉ ነው። አንዳንዶች በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን ጥልቅ ነገሮች ለማስተዋል የሌሎች እገዛ ያስፈልጋቸው ይሆናል። ሌሎች ደግሞ ሕመም አሊያም የመንፈስ ጭንቀት ይኖርባቸው ይሆናል፤ ወይም ጥበብ የጎደለው ውሳኔ ማድረጋቸው ባስከተለባቸው መጥፎ ውጤት እየተሠቃዩ ሊሆን ይችላል። ከዚህም በላይ ሁላችንም አምላካዊ ፍርሃት በሌለው ዓለም ውስጥ መኖራችን የግድ ነው።

2. ወንድሞቻችን ችግር ሲደርስባቸው ምን ማድረግ ይገባናል? ለምንስ?

2 ማንኛችንም ብንሆን የእምነት ባልንጀሮቻችን መከራ ወይም ሥቃይ ሲደርስባቸው መመልከት አንፈልግም። ሐዋርያው ጳውሎስ ጉባኤን ከአካል ጋር ያመሳሰለው ሲሆን “አንድ የአካል ክፍል ቢሠቃይ ሌሎቹ የአካል ክፍሎች በሙሉ አብረውት ይሠቃያሉ” በማለት ተናግሯል። (1 ቆሮ. 12:12, 26) ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አስቸጋሪ ሁኔታ ሲያጋጥማቸው እነሱን ለመደገፍ ጥረት ማድረግ ይገባናል። አንዳንዶች ከጉባኤ አባላት ባገኙት እርዳታ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን መጋፈጥ ብሎም ችግሩን በተሳካ ሁኔታ መወጣት እንደቻሉ የሚናገሩ በርካታ ቅዱስ ጽሑፋዊ ዘገባዎችን እናገኛለን። እነዚህን ዘገባዎች ስንመረምር አንተም በተመሳሳይ መንገድ ሌሎችን መርዳት የምትችለው እንዴት እንደሆነ ቆም ብለህ አስብ። ወንድሞችህን በመንፈሳዊ በመርዳት የይሖዋን ጉባኤ ማነጽ የምትችለው እንዴት ነው?

‘ይዘውት ሄዱ’

3, 4. አቂላና ጵርስቅላ አጵሎስን የረዱት በምን መንገድ ነው?

3 አጵሎስ በኤፌሶን መኖር በጀመረበት ጊዜ ቀናተኛ ወንጌላዊ ነበር። “በመንፈስ እየተቃጠለ ኢየሱስን ስለሚመለከቱ ጉዳዮች በትክክል ይናገርና ያስተምር ነበር፤ ይሁን እንጂ እሱ የሚያውቀው የዮሐንስን ጥምቀት ብቻ ነበር” በማለት የሐዋርያት ሥራ ዘገባ ይናገራል። አጵሎስ “በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም” ስለ መጠመቅ አለማወቁ፣ የሰበኩለት የአጥማቂው ዮሐንስ ደቀ መዛሙርት አሊያም በ33 ከዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት በፊት የነበሩ የኢየሱስ ተከታዮች ሊሆኑ እንደሚችሉ ይጠቁማል። አጵሎስ ቀናተኛ ሰባኪ ቢሆንም ገና ያልተረዳቸው ወሳኝ ጉዳዮች ነበሩ። ታዲያ ከእምነት ባልንጀሮቹ ጋር መቀራረቡ የረዳው እንዴት ነው?—ሥራ 1:4, 5፤ 18:25፤ ማቴ. 28:19

4 አቂላና ጵርስቅላ የተባሉት ክርስቲያን ባልና ሚስት አጵሎስ በምኩራብ ውስጥ በድፍረት ሲናገር በሰሙት ጊዜ ይዘውት በመሄድ የአምላክን መንገድ ይበልጥ አስተማሩት። (የሐዋርያት ሥራ 18:24-26ን አንብብ።) ይህ ለእሱ ያላቸውን ፍቅር የሚያሳይ ነው። እርግጥ ነው፣ አቂላና ጵርስቅላ አጵሎስን ያናገሩት እየተቹት እንዳለ በሚያስመስል መንገድ ሳይሆን በዘዴና አሳቢነት በሚንጸባረቅበት መንገድ መሆን አለበት። አጵሎስ የሚያስፈልገው ስለ ጥንቱ የክርስቲያን ጉባኤ ታሪክ ማወቅ ብቻ ነበር። አጵሎስ አዲሶቹ ወዳጆቹ እንደነዚህ ያሉ አስፈላጊ ነገሮችን ስላካፈሉት አመስጋኝ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። አጵሎስ እንዲህ ያለውን ትምህርት ማግኘቱ በአካይያ የነበሩትን ወንድሞቹን ‘በእጅጉ ለመርዳትና’ ጥሩ ምሥክርነት ለመስጠት አስችሎታል።—ሥራ 18:27, 28

5. በሺዎች የሚቆጠሩ የመንግሥቱ ሰባኪዎች በፍቅር ተነሳስተው ምን እርዳታ እያበረከቱ ነው? ይህስ ምን ውጤት አስገኝቷል?

5 በዛሬው ጊዜ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉ በርካታ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲረዱ እገዛ ላደረጉላቸው ግለሰቦች ከፍተኛ አድናቆት አላቸው። በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ከአስተማሪዎቻቸው ጋር ዘላቂ ወዳጅነት መሥርተዋል። አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች እውነትን እንዲረዱ ለማድረግ ለበርካታ ወራት ቋሚ ጊዜ መድቦ ማስጠናት ያስፈልጋል። ይሁን እንጂ የመንግሥቱ ሰባኪዎች እንዲህ ያለውን መሥዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኞች ናቸው፤ ምክንያቱም ይህ የሰዎችን ሕይወት የሚመለከት ጉዳይ መሆኑን ይገነዘባሉ። (ዮሐ. 17:3) ሰዎች እውነትን ሲቀበሉና በተማሩት መንገድ ሲኖሩ እንዲሁም ሕይወታቸውን የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ ሲጠቀሙበት መመልከት ምንኛ ደስ ያሰኛል!

“በመልካም ምግባሩ የተመሠከረለት ነበር”

6, 7. (ሀ) ጳውሎስ የጉዞ ጓደኛው እንዲሆን ጢሞቴዎስን የመረጠው ለምንድን ነው? (ለ) ጢሞቴዎስ ጥሩ እድገት ማድረግ እንዲችል የረዳው ምንድን ነው?

6 ሐዋርያቱ ጳውሎስና ሲላስ በሁለተኛው ሚስዮናዊ ጉዟቸው ወቅት ልስጥራን ሲጎበኙ ጢሞቴዎስ ከተባለ ወጣት ጋር ተገናኙ፤ በወቅቱ ጢሞቴዎስ በአሥራዎቹ ዕድሜ መገባደጃ ወይም በ20ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ አካባቢ ሳይሆን አይቀርም። ጢሞቴዎስ “በልስጥራና በኢቆንዮን ባሉ ወንድሞች ዘንድ በመልካም ምግባሩ የተመሠከረለት ነበር።” የጢሞቴዎስ እናት ኤውንቄ እና አያቱ ሎይድ ክርስቲያኖች ቢሆኑም አባቱ ግን አማኝ አልነበረም። (2 ጢሞ. 1:5) ጳውሎስ ከዚህ ቤተሰብ ጋር የተዋወቀው ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ ወደዚያ አካባቢ በሄደበት ወቅት ሳይሆን አይቀርም። አሁን ግን ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ለተለየ ዓላማ እንደሚፈልገው ገለጸ፤ ምክንያቱም ጢሞቴዎስ ከሌሎቹ ወጣቶች ለየት ያለ ነበር። በመሆኑም የጉባኤው የሽማግሌዎች አካል በሰጠው ድጋፍ መሠረት ጢሞቴዎስ ጳውሎስን በሚስዮናዊነት አገልግሎቱ እንዲያግዘው ተመረጠ።—የሐዋርያት ሥራ 16:1-3ን አንብብ።

7 ጢሞቴዎስ በዕድሜ ከሚበልጠው የሥራ ባልደረባው ብዙ የሚማረው ነገር ነበር። ደግሞም ከጳውሎስ ብዙ በመማር ትልቅ እድገት አድርጓል፤ በመሆኑም ከጊዜ በኋላ ጳውሎስ ስለተማመነበት ጉባኤዎችን እንዲጎበኝና እሱን ወክሎ እንዲሠራ ልኮታል። ተሞክሮ ያልነበረውና ምናልባትም ዓይናፋር የነበረው ጢሞቴዎስ ለ15 ዓመታት ያህል ከጳውሎስ ጋር አብሮ መሥራቱ እድገት በማድረግ ጎበዝ የበላይ ተመልካች ለመሆን አስችሎታል።—ፊልጵ. 2:19-22፤ 1 ጢሞ. 1:3

8, 9. የጉባኤ አባላት ወጣቶችን ለማበረታታት ምን ማድረግ ይችላሉ? ምሳሌ ስጥ።

8 በዛሬው ጊዜ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ወጣት ወንዶችና ሴቶች ብዙ መሥራት ይችላሉ። መንፈሳዊ የሆኑ የእምነት ባልንጀሮቻቸው እነዚህን ወጣቶች ካበረታቷቸውና ከረዷቸው ወጣቶቹ በይሖዋ ሕዝቦች መካከል ተጨማሪ ኃላፊነት ለመቀበል ጥረት ሊያደርጉና ወደዚህ ግብ ሊደርሱ ይችላሉ። እስቲ ጉባኤህን መለስ ብለህ ተመልከት! ጢሞቴዎስ እንዳደረገው ራሳቸውን ሊያቀርቡ የሚችሉ ወጣቶች አሉ? እርዳታና ማበረታቻ የምትሰጣቸው ከሆነ እነዚህ ወጣቶች አቅኚዎች፣ ቤቴላውያን፣ ሚስዮናውያን ወይም ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህ ግቦች ላይ ለመድረስ እንዲጣጣሩ ምን ዓይነት እርዳታ ልታደርግላቸው ትችላለህ?

9 ለ20 ዓመታት በቤቴል ያገለገለው ማርቲን ከ30 ዓመት በፊት አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች አብሮት ባገለገለ ጊዜ ትኩረት ሰጥቶ ስለረዳው በጣም አመስጋኝ ነው። የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ወጣት እያለ በቤቴል ሲያገለግል ስላሳለፈው ጊዜ ለማርቲን በአድናቆት ስሜት ነገረው። በተጨማሪም በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ለማገልገል ራሱን ማቅረብ ይችል እንደሆነ እንዲያስብበት ማርቲንን አበረታታው። ማርቲን ከወረዳ የበላይ ተመልካቹ ጋር ያደረገው የማይረሳ ውይይት ከጊዜ በኋላ ላደረገው ምርጫ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ይሰማዋል። ማን ያውቃል፣ አንተም ከወጣቶች ጋር ስለ ቲኦክራሲያዊ ግቦች ማውራትህ ጥሩ ውጤት ሊያስገኝ ይችላል።

“የተጨነቁትን ነፍሳት አጽናኗቸው”

10. አፍሮዲጡ ምን ተሰምቶት ነበር? ለምንስ?

10 አፍሮዲጡ በእምነቱ ምክንያት ታስሮ የነበረውን ሐዋርያው ጳውሎስን ለመጠየቅ ከፊልጵስዩስ ተነስቶ ሮም ለመድረስ ረጅምና አድካሚ ጉዞ አድርጎ ነበር። ይህ ክርስቲያን ወደ ጳውሎስ የሄደው የፊልጵስዩስ ክርስቲያኖችን ወክሎ ነበር። አፍሮዲጡ የፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች ለጳውሎስ የላኩለትን ስጦታ የወሰደለት ከመሆኑም በላይ ሐዋርያው ያለበትን አስቸጋሪ ሁኔታ መቋቋም እንዲችል በሚያስፈልገው ሁሉ ለመርዳት አብሮት ሊቆይ አቅዶ ነበር። ይሁን እንጂ አፍሮዲጡ ሮም እያለ “በጠና ታሞ ሞት አፋፍ ደርሶ ነበር።” ይህ ክርስቲያን የተሰጠውን ተልእኮ እንዳልተወጣ ስለተሰማው ተክዞ ወይም በጣም ተጨንቆ ነበር።—ፊልጵ. 2:25-27

11. (ሀ) በጉባኤ ያሉ አንዳንድ ወንድሞች የመንፈስ ጭንቀት ቢኖርባቸው መገረም የሌለብን ለምንድን ነው? (ለ) ጳውሎስ አፍሮዲጡን ለመርዳት ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች ምን ምክር ሰጥቷቸዋል?

11 በዛሬው ጊዜ ሰዎች የሚያጋጥሟቸው የተለያዩ ጫናዎች በመንፈስ ጭንቀት እንዲሠቃዩ ያደርጓቸዋል። የዓለም የጤና ድርጅት ያወጣው አኃዛዊ መረጃ እንደሚያሳየው ከ5 ሰዎች አንዱ በሕይወቱ ውስጥ በሆነ ወቅት ላይ የመንፈስ ጭንቀት ሊያጋጥመው ይችላል። የይሖዋ ሕዝቦችም ከዚህ ችግር ነፃ አይደሉም። አንድ ሰው ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ነገር ለማቅረብ ሲጥር የሚያጋጥሙት ችግሮች፣ የጤና መታወክ፣ በድክመቶቹ የተነሳ የሚያድርበት የተስፋ መቁረጥ ስሜት ወይም ሌሎች ነገሮች በጭንቀት እንዲዋጥ ሊያደርጉት ይችላሉ። የፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች አፍሮዲጡን ለመርዳት ምን ማድረግ ይችሉ ነበር? ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የጌታን ተከታዮች ወትሮ በምትቀበሉበት መንገድ በታላቅ ደስታ [አፍሮዲጡን] ተቀበሉት፤ እንዲሁም እንደ እሱ ያሉትን ሰዎች በአክብሮት ያዟቸው፤ ምክንያቱም እሱ እናንተ እዚህ ሆናችሁ በግል ልትሰጡኝ ያልቻላችሁትን አገልግሎት በሚገባ ለማሟላት ሲል ከጌታ ሥራ የተነሳ ነፍሱን ለአደጋ በማጋለጥ ለሞት ተቃርቦ ነበር።”—ፊልጵ. 2:29, 30

12. በመንፈስ ጭንቀት የተዋጡ ሰዎችን ምን ሊያጽናናቸው ይችላል?

12 እኛም ተስፋ የቆረጡ ወይም በመንፈስ ጭንቀት የተዋጡ ወንድሞቻችንን መርዳት ይኖርብናል። ይሖዋን በማገልገል ስላከናወኑት ተግባር አንስተን ልንነግራቸው የምንችላቸው በጎ የሆኑ ነገሮች እንዳሉ ጥርጥር የለውም። ክርስቲያን ለመሆን አሊያም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመካፈል ሲሉ በሕይወታቸው ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ አድርገው ሊሆን ይችላል። ያደረጉትን ጥረት እንደምናደንቅና ይሖዋም ጥረታቸውን ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው ልንነግራቸው እንችላለን። አንዳንድ ታማኝ አገልጋዮች በዕድሜ መግፋት ወይም በሕመም ምክንያት እንደቀድሟቸው ማገልገል አቅቷቸው ቢሆንም እንኳ ለዓመታት ላከናወኑት አገልግሎት ልናከብራቸው ይገባል። በመንፈስ ጭንቀት እንዲዋጡ ያደረጋቸው ምክንያት ምንም ይሁን ምን ይሖዋ ለታማኝ አገልጋዮቹ በሙሉ የሚከተለውን ምክር ሰጥቷል፦ “የተጨነቁትን ነፍሳት አጽናኗቸው፤ ደካሞችን ደግፏቸው፤ ሁሉንም በትዕግሥት ያዙ።”—1 ተሰ. 5:14

“በደግነት ይቅር ልትሉትና ልታጽናኑት ይገባል”

13, 14. (ሀ) የቆሮንቶስ ጉባኤ ምን ጠንከር ያለ እርምጃ ወስዷል? ለምንስ? (ለ) የውገዳ እርምጃ መወሰዱ ምን ውጤት አስገኝቷል?

13 በመጀመሪያው መቶ ዘመን በቆሮንቶስ በነበረው ጉባኤ ውስጥ አንድ ሰው ዝሙት ይፈጽም የነበረ ሲሆን ንስሐ የመግባት አዝማሚያም አልነበረውም። የግለሰቡ አኗኗር የጉባኤውን ንጽሕና አደጋ ላይ የሚጥል ከመሆኑም ሌላ ድርጊቱ በማያምኑ ሰዎች ዘንድ እንኳ አሳፋሪ ነገር ነበር። በመሆኑም ጳውሎስ ግለሰቡ ከጉባኤ እንዲወገድ ማዘዙ ተገቢ ነበር።—1 ቆሮ. 5:1, 7, 11-13

14 እንዲህ ያለው ተግሣጽ ጥሩ ውጤት አስገኝቷል። ጉባኤው በካይ ከሆነ ተጽዕኖ የተጠበቀ ከመሆኑም ሌላ ኃጢአተኛው ወደ ልቡ ተመልሶ እውነተኛ ንስሐ ገባ። ግለሰቡ የንስሐ ፍሬ በማፍራቱ ጳውሎስ ለጉባኤው በጻፈው ሁለተኛ ደብዳቤ ላይ ይህ ሰው ውገዳው ሊነሳለት እንደሚገባ ገልጿል። ይሁን እንጂ ሌላም መደረግ ያለበት ነገር ነበር። ጳውሎስ ለጉባኤው እንዲህ የሚል መመሪያም ሰጥቷል፦ “አሁን ይህ ሰው [ንስሐ የገባው ኃጢአተኛ] ከልክ በላይ በሐዘን እንዳይዋጥ በደግነት ይቅር ልትሉትና ልታጽናኑት ይገባል።”—2 ቆሮንቶስ 2:5-8ን አንብብ።

15. ንስሐ ገብተው ወደ ጉባኤ ለተመለሱ ኃጢአተኞች ምን አመለካከት ሊኖረን ይገባል?

15 ከዚህ ዘገባ ምን ትምህርት እናገኛለን? አንዳንድ ክርስቲያኖች ንስሐ ባለመግባታቸው መወገዳቸው ያሳዝነናል። በአምላክ ስምና በጉባኤው ላይ ነቀፋ አምጥተው ሊሆን ይችላል። ከዚህም አልፎ በግለሰብ ደረጃ በድለውን ሊሆን ይችላል። ይሁንና ጉዳዩን እንዲመረምሩ የተመደቡት ሽማግሌዎች ነገሩን ይሖዋ ከሰጠው መመሪያ አንጻር ከተመለከቱ በኋላ ንስሐ የገባው ኃጢአተኛ ወደ ጉባኤው መመለስ እንዳለበት ከወሰኑ ይሖዋ ግለሰቡን ይቅር ብሎታል ማለት ነው። (ማቴ. 18:17-20) እኛም ይሖዋን ለመምሰል መጣር አይኖርብንም? በእርግጥም ግለሰቡን ይቅር ለማለት ፈቃደኛ አለመሆን ይሖዋን ከመቃወም ተለይቶ አይታይም። የአምላክ ጉባኤ ሰላምና አንድነት ተጠብቆ እንዲቆይ ለማድረግ እንዲሁም የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት ስንል እውነተኛ ንስሐ ገብተው ወደ ጉባኤው ለተመለሱ ኃጢአተኞች ‘ፍቅራችንን ልናረጋግጥላቸው’ አይገባም?—ማቴ. 6:14, 15፤ ሉቃስ 15:7

‘ይጠቅመኛል’

16. ጳውሎስ በማርቆስ ቅር የተሰኘው ለምን ነበር?

16 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኝ ሌላ ዘገባ ደግሞ ቅር ያሰኙንን ሰዎች ተቀይመን መቆየት እንደማይኖርብን ያሳያል። ለምሳሌ፣ ማርቆስ ተብሎ የሚጠራው ዮሐንስ በአንድ ወቅት ሐዋርያው ጳውሎስን በጣም አሳዝኖት ነበር። እንዴት? ጳውሎስና በርናባስ የመጀመሪያው የሚስዮናዊ ጉዟቸውን ባደረጉበት ጊዜ ማርቆስ እነሱን ለመርዳት አብሯቸው ሄዶ ነበር። ይሁን እንጂ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ማርቆስ ምክንያቱ ባይገለጽም ከእነሱ ተለይቶ ወደ ቤቱ ተመለሰ። ጳውሎስ፣ ማርቆስ ባደረገው ውሳኔ በጣም ቅር ተሰኝቶ ስለነበር ሁለተኛውን የሚስዮናዊ ጉዟቸውን ለማድረግ ሲነሱ ማርቆስን ይዞ በመሄዱ ጉዳይ ላይ ከበርናባስ ጋር ተጋጩ። ጳውሎስ በመጀመሪያው ጉዟቸው ላይ ከተከሰተው ሁኔታ አንጻር ማርቆስ አብሯቸው እንዲሄድ አልፈለገም።—የሐዋርያት ሥራ 13:1-5, 13⁠ን እና 15:37, 38ን አንብብ።

17, 18. በጳውሎስና በማርቆስ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት እንደ ተፈታ እንዴት እናውቃለን? ከዚህስ ምን ትምህርት እናገኛለን?

17 ማርቆስ ከበርናባስ ጋር በሌላ ክልል በሚስዮናዊነት ማገልገሉን መቀጠሉ በእሱና በጳውሎስ መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ተስፋ አለመቁረጡን ያሳያል። (ሥራ 15:39) ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ጳውሎስ ስለ ማርቆስ ከጻፈው ነገር መመልከት እንደሚቻለው ማርቆስ ታማኝና እምነት የሚጣልበት ሰው መሆኑን አሳይቷል። ጳውሎስ በሮም በታሰረበት ጊዜ ወደ ጢሞቴዎስ ደብዳቤ በመጻፍ ወደ እሱ እንዲመጣ ጠየቀው። በዚሁ ደብዳቤ ላይ ጳውሎስ፣ “ማርቆስ ለአገልግሎት ስለሚጠቅመኝ ከአንተ ጋር ይዘኸው ና” በማለት ጽፎ ነበር። (2 ጢሞ. 4:11) አዎን፣ ማርቆስ ጥሩ እድገት በማድረጉ ጳውሎስ ለእሱ ያለው አመለካከት ተለውጧል።

18 ከዚህ ዘገባ የምናገኘው ትምህርት አለ። ማርቆስ ጥሩ ሚስዮናዊ ለመሆን የሚያስፈልጉትን ባሕርያት አዳብሯል። ጳውሎስ እሱን ይዞ ለመሄድ ፈቃደኛ ባለመሆኑ አልተሰናከለም። እሱም ሆነ ጳውሎስ መንፈሳዊ ሰዎች በመሆናቸው በመካከላቸው የተፈጠረው ቅራኔ ለረጅም ጊዜ እንዲዘልቅ አልፈቀዱም። እንዲያውም ጳውሎስ፣ ማርቆስ ጥሩ ረዳት እንደሆነ ከጊዜ በኋላ ገልጿል። ከዚህ ለመመልከት እንደምንችለው ወንድሞች በመካከላቸው የተፈጠረውን አለመግባባት ካስወገዱና ችግሩን ከፈቱት በኋላ ሊወስዱት የሚገባው ትክክለኛ እርምጃ በይሖዋ አገልግሎት ወደፊት መግፋትና ሌሎች መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ መርዳት ነው። አዎንታዊ አመለካከት መያዝ ጉባኤን ለማነጽ ይረዳል።

ጉባኤውና አንተ

19. የክርስቲያን ጉባኤ አባላት በሙሉ አንዳቸው ለሌላው ምን እርዳታ ማበርከት ይችላሉ?

19 “ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን” በተባለው በዚህ ወቅት አንተም ሆንክ በጉባኤ ውስጥ ያሉ ወንድሞችና እህቶች አንዳችሁ የሌላው እርዳታ ያስፈልጋችኋል። (2 ጢሞ. 3:1) አንዳንድ ክርስቲያኖች የሚያጋጥሟቸውን ሁኔታዎች ለመወጣት ምን እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው ሁልጊዜ ላያውቁ ቢችሉም ይሖዋ ግን ምን ማድረግ እንደሚገባቸው ያውቃል። በመሆኑም አንተን ጨምሮ የተለያዩ የጉባኤ አባላትን በመጠቀም እነዚህ ወንድሞች ትክክለኛውን እርምጃ እንዲወስዱ ሊረዳቸው ይችላል። (ኢሳ. 30:20, 21፤ 32:1, 2) እንግዲያው ሐዋርያው ጳውሎስ የሰጠውን የሚከተለውን ምክር ሁላችንም ተግባራዊ እናድርግ፦ “አሁን እያደረጋችሁት እንዳለው እርስ በርሳችሁ መጽናናታችሁንና እርስ በርስ መተናነጻችሁን ቀጥሉ።”—1 ተሰ. 5:11

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ወንድሞቻችንን ማነጽ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

• አንዳንዶች ምን ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታዎችን እንዲወጡ ልትረዳቸው ትችላለህ?

• በጉባኤያችን ውስጥ የሚገኙ ክርስቲያኖች እርዳታ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ ክርስቲያን ባልንጀራችን አስቸጋሪ ሁኔታ ሲያጋጥመው ልንረዳው እንችላለን

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዛሬው ጊዜ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ወጣት ወንዶችና ሴቶች ብዙ መሥራት ይችላሉ