በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ለማስተማር የተቻለህን ሁሉ ጥረት ማድረግህን ቀጥል”

“ለማስተማር የተቻለህን ሁሉ ጥረት ማድረግህን ቀጥል”

“ለማስተማር የተቻለህን ሁሉ ጥረት ማድረግህን ቀጥል”

“እናንተ ‘መምህር’ እና ‘ጌታ’ ብላችሁ ትጠሩኛላችሁ፤ እንደዚያ ስለሆንኩም እንዲህ ብላችሁ መጥራታችሁ ትክክል ነው።” (ዮሐ. 13:13) ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ በተናገራቸው በእነዚህ ቃላት አማካኝነት አስተማሪ በመሆን የሚጫወተውን ሚና አጉልቷል። ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ ትንሽ ቀደም ብሎም ተከታዮቹን እንዲህ ሲል አዝዟቸው ነበር፦ “ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ ያዘዝኳችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው።” (ማቴ. 28:19, 20) ከጊዜ በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስም የአምላክ ቃል አስተማሪዎች የመሆንን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ገልጿል። ክርስቲያን ሽማግሌ ለነበረው ለጢሞቴዎስ የሚከተለውን ማሳሰቢያ ሰጥቶታል፦ “በሕዝብ ፊት ለማንበብ፣ አጥብቀህ ለመምከርና ለማስተማር የተቻለህን ሁሉ ጥረት ማድረግህን ቀጥል። . . . እድገትህ በሁሉም ሰዎች ዘንድ በግልጽ እንዲታይ በእነዚህ ነገሮች ላይ አሰላስል፤ እንዲሁም ትኩረትህ ሙሉ በሙሉ በእነዚህ ነገሮች ላይ ያረፈ ይሁን።”—1 ጢሞ. 4:13-15

ዛሬም ቢሆን የማስተማሩ ሥራ በመስክ አገልግሎታችንም ሆነ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን ላይ ጉልህ ስፍራ አለው። ለማስተማር የተቻለንን ሁሉ ጥረት ማድረጋችንን መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው? ይህስ የአምላክ ቃል አስተማሪዎች በመሆን ረገድ እድገት እንድናደርግ የሚረዳን በየትኞቹ መንገዶች ነው?

የታላቁን አስተማሪ አርዓያ ተከተል

ኢየሱስ ያስተማረበት መንገድ የብዙዎችን ትኩረት ይስብ ነበር። የተናገራቸው ቃላት ናዝሬት በሚገኘው ምኩራብ ውስጥ ተሰብስበው በነበሩት ሰዎች ላይ ምን ስሜት እንዳሳደሩ ልብ በል። የወንጌል ጸሐፊ የሆነው ሉቃስ “ሁሉም ስለ እሱ መልካም ነገር ይናገሩ ጀመር፤ ከአፉ በሚወጡት የሚማርኩ ቃላትም [ይደነቁ] . . . ነበር” በማለት ስለ ሁኔታው ዘግቧል። (ሉቃስ 4:22) የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በሚሰብኩበት ጊዜ ጌታቸው የተወውን ምሳሌ ተከትለዋል። ሐዋርያው ጳውሎስም ክርስቲያን ባልንጀሮቹን “እኔ የክርስቶስን አርዓያ እንደምከተል እናንተም የእኔን አርዓያ ተከተሉ” በማለት አበረታቷቸዋል። (1 ቆሮ. 11:1) ጳውሎስ የኢየሱስን ዘዴዎች ይከተል ስለነበር ‘በአደባባይና ከቤት ወደ ቤት በማስተማር’ ረገድ የተካነ ሊሆን ችሏል።—ሥራ 20:20

“በገበያ ስፍራ” ማስተማር

የጳውሎስን በሕዝብ ፊት የማስተማር ችሎታ ከሚያሳዩ ግሩም ምሳሌዎች አንዱ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 17 ላይ ይገኛል። ዘገባው ጳውሎስ ወደ አቴና፣ ግሪክ እንደሄደ ይናገራል። ጳውሎስ፣ በመንገድም ይሁን ሕዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች በከተማዋ ውስጥ በሄደበት ሁሉ ብዙ ጣዖታትን ተመለከተ። በሁኔታው እጅግ መበሳጨቱ ምንም አያስገርምም! ያም ሆኖ ጳውሎስ ስሜቱ ከቁጥጥሩ ውጪ እንዲሆን አልፈቀደም። ከዚህ ይልቅ “በምኩራብ . . . እንዲሁም በየዕለቱ በገበያ ስፍራ ከሚያገኛቸው ሰዎች ጋር ይወያይ ጀመር።” (ሥራ 17:16, 17) ይህ ለእኛ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው! በሰዎች ላይ ከመፍረድ ይልቅ ሁሉንም ዓይነት ሰዎች በአክብሮት ማናገራችን አንዳንዶች መልእክቱን እንዲያዳምጡና ውሎ አድሮ ከሐሰት ሃይማኖት ባርነት ነፃ እንዲወጡ መንገድ ሊጠርግ ይችላል።—ሥራ 10:34, 35፤ ራእይ 18:4

ጳውሎስ በገበያ ስፍራ ያገኛቸው በርካታ ሰዎች መልእክቱን ለመቀበል እንቢተኞች ነበሩ። ከአድማጮቹ አንዳንዶቹ ፈላስፎች ሲሆኑ እሱ ከሚሰብክላቸው እውነት ፈጽሞ የተለየ አመለካከት ነበራቸው። እነዚህ ሰዎች ክርክር በሚያስነሱበት ጊዜ ጳውሎስ የሚሰጡትን ሐሳብ ያዳምጥ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። አንዳንዶቹ “ጥሬ ለቃቃሚ” ብለው የጠሩት ሲሆን ይህ አገላለጽ “ለፍላፊ” የሆነን ሰው ለማመልከት የሚሠራበት ዘይቤያዊ አነጋገር ነው። ሌሎች ደግሞ “ስለ ባዕዳን አማልክት የሚሰብክ ይመስላል” ይሉ ነበር።—ሥራ 17:18

ይሁን እንጂ ጳውሎስ አድማጮቹ የሚሰነዝሩት ነቀፌታ ተስፋ አላስቆረጠውም። እንዲያውም እምነቱን እንዲያስረዳ በተጠየቀ ጊዜ አጋጣሚውን ተጠቅሞ የማስተማር ችሎታውን ጥሩ አድርጎ የሚያሳይ ማስተዋል የተሞላበት ንግግር ሰጠ። (ሥራ 17:19-22፤ 1 ጴጥ. 3:15) ጳውሎስ የሰጠውን ንግግር በዝርዝር በመከለስ የማስተማር ችሎታችንን እንድናሻሽል የሚረዳንን ትምህርት ለማግኘት እስቲ እንሞክር።

በጋራ የሚያስማማችሁን ነጥብ አንሳ

ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፦ “የአቴና ሰዎች ሆይ፣ በሁሉም መስክ ከሌሎች ሰዎች ይበልጥ እናንተ አማልክትን እንደምትፈሩ ማየት ችያለሁ። ለአብነት ያህል፣ . . . ሃይማኖታዊ አክብሮት የምትሰጧቸውን ነገሮች በትኩረት ስመለከት ‘ለማይታወቅ አምላክ’ የሚል ጽሑፍ የተቀረጸበት አንድ መሠዊያ አይቻለሁ። ስለዚህ ይህን ሳታውቁ አምልኮታዊ ክብር የምትሰጡትን እኔ አሳውቃችኋለሁ።”—ሥራ 17:22, 23

ጳውሎስ በዙሪያው ያሉትን ነገሮች ያስተውል ነበር። በአካባቢው ያሉትን ነገሮች በትኩረት መመልከቱ ስለሚያናግራቸው ሰዎች ብዙ ለማወቅ አስችሎታል። እኛም ትኩረት ሰጥተን የምንመለከት ከሆነ ስለ ቤቱ ባለቤት አንዳንድ ነገሮችን ማወቅ እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ በግቢው ውስጥ መጫወቻዎች መኖራቸው አሊያም በሩ ላይ ወይም ቤቱ ውስጥ አንዳንድ ምልክቶች መኖራቸው ስለ ግለሰቡ ብዙ የሚናገሩት ነገር አለ። የቤቱ ባለቤት ምን ዓይነት ሰው እንደሆነ የተወሰነ ግንዛቤ ማግኘታችን የምንናገረውን ብቻ ሳይሆን እንዴት እንደምንናገርም በጥንቃቄ እንድናስብ ያደርገናል።—ቆላ. 4:6

ጳውሎስ መልእክቱን ያቀረበው አዎንታዊ በሆነ መልኩ ነበር። ይሁንና የአቴና ሰዎች “አምልኮታዊ ክብር” ይሰጡ የነበረው በተሳሳተ እውቀት ላይ ተመሥርተው እንደነበር አስተዋለ። በመሆኑም ጳውሎስ እውነተኛውን አምላክ እንዴት ማምለክ እንደሚችሉ ግልጽ በሆነ መንገድ ጠቆማቸው። (1 ቆሮ. 14:8) እንግዲያው የመንግሥቱን ምሥራች ስናውጅ በግልጽና አዎንታዊ በሆነ መልኩ መናገራችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!

ዘዴኛ ሁን እንዲሁም አታዳላ

ጳውሎስ ንግግሩን ሲቀጥል እንዲህ አለ፦ “ዓለምንና በውስጡ ያለውን ነገር ሁሉ የፈጠረው አምላክ፣ እሱ የሰማይና የምድር ጌታ ስለሆነ በእጅ በተሠሩ ቤተ መቅደሶች ውስጥ አይኖርም፤ በተጨማሪም ሕይወትንና እስትንፋስንም ሆነ ማንኛውንም ነገር ለሰው ሁሉ የሚሰጠው እሱ ስለሆነ የሚጎድለው ነገር ያለ ይመስል በሰው እጅ አይገለገልም።”—ሥራ 17:24, 25

እዚህ ላይ ጳውሎስ ይሖዋን “የሰማይና የምድር ጌታ” ብሎ በመጥራት ሕይወት ሰጪያችን እሱ መሆኑን በዘዴ አሳውቋቸዋል። የተለያየ ሃይማኖትና ባሕል ያላቸውን ልበ ቅን ሰዎች የሕይወት ሁሉ ምንጭ ይሖዋ አምላክ መሆኑን እንዲያውቁ መርዳት እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው!—መዝ. 36:9

ጳውሎስ ቀጥሎ እንዲህ አለ፦ “የሰውን ወገኖች በሙሉ ከአንድ ሰው ፈጠረ፤ የተወሰኑትን ዘመናትና የሰው ልጆች የሚኖሩበትንም ድንበር ደነገገ፤ ይህንም ያደረገው ሰዎች አምላክን እንዲፈልጉትና አጥብቀው በመሻት እንዲያገኙት ብሎ ነው፤ እንዲህ ሲባል ግን እሱ ከእያንዳንዳችን የራቀ ነው ማለት አይደለም።”—ሥራ 17:26, 27

የምናስተምርበት መንገድ ስለምናመልከው አምላክ ማንነት ለሌሎች የሚያስተላልፈው መልእክት አለ። ይሖዋ ለማንም ሳያዳላ ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሰዎች እሱን “አጥብቀው በመሻት እንዲያገኙት” አጋጣሚ ሰጥቷል። እኛም በተመሳሳይ ሳናዳላ የምናገኛቸውን ሰዎች ሁሉ እናነጋግራለን። በፈጣሪ መኖር የሚያምኑ ሰዎች ወደ እሱ እንዲቀርቡና ዘላለማዊ በረከቶችን እንዲያገኙ ለመርዳት እንጥራለን። (ያዕ. 4:8) ይሁን እንጂ የአምላክን መኖር የሚጠራጠሩ ሰዎችን እንዴት መርዳት እንችላለን? የጳውሎስን ምሳሌ እንከተላለን። ሐዋርያው ቀጥሎ ምን እንዳለ እንመልከት።

“በእናንተ መካከል ያሉ አንዳንድ ባለቅኔዎች ‘እኛም የእሱ ልጆች ነንና’ ብለው እንደተናገሩት ሁሉ ሕይወት ያገኘነው፣ የምንንቀሳቀሰውና የምንኖረው በእሱ ነው። እንግዲህ እኛ የአምላክ ልጆች ከሆንን አምላክ . . . ከወርቅ ወይም ከብር ወይም ከድንጋይ የተቀረጸን ነገር ይመስላል ብለን ልናስብ አይገባም።”—ሥራ 17:28, 29

ጳውሎስ የአቴና ሰዎች የሚያውቋቸውና የሚቀበሏቸው ባለቅኔዎች የተናገሩትን በመጥቀስ የአድማጮቹን ትኩረት ለማግኘት ሞክሯል። እኛም በተመሳሳይ አድማጮቻችን እንደሚቀበሉት የምናውቀውን ነጥብ በማንሳት በጋራ የምንስማማበትን ነገር ለማግኘት ጥረት እናደርጋለን። ለአብነት ያህል፣ ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ የተጠቀመበት የሚከተለው ምሳሌ በዛሬው ጊዜ ላሉ ሰዎችም አሳማኝ ነው፦ “እያንዳንዱ ቤት የራሱ ሠሪ አለው፤ ሁሉን ነገር የሠራው ግን አምላክ ነው።” (ዕብ. 3:4) የቤቱ ባለቤት በዚህ ቀላል ምሳሌ ላይ እንዲያስብበት በማድረግ የምንናገረው ነገር እውነት መሆኑን እንዲቀበል ልንረዳው እንችላለን። ጳውሎስ ከሰጠው ንግግር ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማስተማር የሚረዳ ሌላም ነጥብ እናገኛለን፤ ይህም ለእርምጃ እንዲነሳሱ ማድረግ ነው።

የጊዜውን አጣዳፊነት ጎላ አድርገህ ግለጽ

ጳውሎስ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “እርግጥ አምላክ ሰዎች ባለማወቅ የኖሩበትን ጊዜ ቸል ብሎ አልፎታል፤ አሁን ግን የሰው ልጆች ሁሉ በያሉበት ቦታ ንስሐ መግባት አለባቸው ብሎ እየተናገረ ነው። ምክንያቱም በሾመው ሰው አማካኝነት በዓለም ሁሉ ላይ በጽድቅ ለመፍረድ ዓላማ ያለው ሲሆን ይህንንም ለማድረግ ቀን ወስኗል።”—ሥራ 17:30, 31

አምላክ ለተወሰነ ጊዜ ክፋት እንዲቀጥል መፍቀዱ ሁላችንም የልባችንን እውነተኛ ሁኔታ ለማሳየት አጋጣሚ ሰጥቶናል። ያለንበት ጊዜ አጣዳፊ መሆኑን ጎላ አድርገን መግለጻችንና በቅርቡ በሚመጣው የአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር የሚኖሩትን በረከቶች አሳማኝ በሆነ መንገድ መናገራችን በጣም አስፈላጊ ነው።—2 ጢሞ. 3:1-5

የተለያየ ምላሽ

“እነሱም ስለ ሙታን ትንሣኤ በሰሙ ጊዜ አንዳንዶቹ ያሾፉበት ጀመር፤ ሌሎች ግን ‘በሌላም ጊዜ ስለዚሁ ጉዳይ መስማት እንፈልጋለን’ አሉት። ከዚያም ጳውሎስ ከመካከላቸው ወጥቶ ሄደ፤ አንዳንድ ሰዎች ግን ከእሱ ጋር በመተባበር አማኞች ሆኑ።”—ሥራ 17:32-34

አንዳንዶች የምናስተምረውን ነገር ወዲያው የሚቀበሉ ሲሆን ሌሎች ግን ትምህርቱን አምነው ለመቀበል ጊዜ ሊወስድባቸው ይችላል። ሆኖም እውነትን ግልጽና ቀላል በሆነ መንገድ ማብራራታችን ቢያንስ አንድ ሰው ስለ ይሖዋ ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኝ ለመርዳት ያስችለናል፤ ሰዎችን ወደ ልጁ ለመሳብ አምላክ ስለተጠቀመብን ምንኛ አመስጋኞች ነን!—ዮሐ. 6:44

የምናገኘው ትምህርት

በጳውሎስ ንግግር ላይ ስናሰላስል የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ለሰዎች እንዴት ማብራራት እንደምንችል ብዙ ትምህርት እናገኛለን። በጉባኤ ውስጥ የሕዝብ ንግግር የማቅረብ መብት ካገኘን አንድ የማያምን ሰው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ለመረዳትና ለመቀበል እንዲችል ነጥቡን በዘዴ በማቅረብ ረገድ የጳውሎስን ምሳሌ ለመከተል ጥረት ማድረግ እንችላለን። እንዲህ ያሉ እውነቶችን ግልጽ በሆነ መንገድ ማቅረብ ብንፈልግም በስብሰባው ላይ የተገኘ የማያምን ሰው የሚከተለውን እምነት ላለመንቀፍ መጠንቀቅ ይኖርብናል። በሌላ በኩል ደግሞ በመስክ አገልግሎታችን ላይ ትምህርቱን አሳማኝ በሆነ መንገድና በዘዴ ለማቅረብ እንጥራለን። እንዲህ ስናደርግ ‘ለማስተማር የተቻለንን ሁሉ ጥረት እንድናደርግ’ ጳውሎስ የሰጠውን ምክር በትክክል እንደምንከተል እናሳያለን።

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጳውሎስ ያስተማረው ግልጽና ቀላል በሆነ እንዲሁም ዘዴ በታከለበት መንገድ ነበር

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የምንሰብክላቸውን ሰዎች ስሜት ከግምት በማስገባት የጳውሎስን ምሳሌ መከተል እንችላለን