በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልጆቻችሁ የንባብና የጥናት ፍቅር እንዲያድርባቸው እርዷቸው

ልጆቻችሁ የንባብና የጥናት ፍቅር እንዲያድርባቸው እርዷቸው

ልጆቻችሁ የንባብና የጥናት ፍቅር እንዲያድርባቸው እርዷቸው

ልጆቻችሁ የወደፊት ሕይወታቸው ጥሩ እንዲሆን ለመርዳት ልታደርጉ ከምትችሏቸው አስፈላጊ ነገሮች አንዱ የንባብና የጥናት ፍቅር እንዲያድርባቸው ጥረት ማድረግ ነው። ደግሞም ንባብና ጥናት ከፍተኛ ደስታ ያስገኛሉ! አንዳንድ ግለሰቦች ስለ ልጅነት ሕይወታቸው ሲያስቡ ካሏቸው ጥሩ ትዝታዎች መካከል ወላጆቻቸው ያነቡላቸው የነበረውን ጊዜ ያስታውሳሉ። ማንበብ በራሱ አስደሳች ከመሆኑም በላይ ብዙ ጥቅሞች ያስገኛል። መንፈሳዊ እድገት ለማድረግ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ትልቅ አስተዋጽኦ ስለሚያበረክት በተለይ ለአምላክ አገልጋዮች ማንበብ ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው። አንድ ክርስቲያን ወላጅ ያስተዋለውን ሲናገር “ትልቅ ቦታ የምንሰጠው በንባብና በጥናት ላወቅናቸው ነገሮች ነው” ብሏል።

ልጆቻችሁ ጥሩ የጥናት ልማድ ማዳበራቸው ከአምላክ ጋር የተቀራረበ ዝምድና እንዲመሠርቱ ሊረዳቸው ይችላል። (መዝ. 1:1-3, 6) የንባብ ችሎታ ለመዳን የሚያስፈልግ መሥፈርት ባይሆንም ማንበብ ብዙ መንፈሳዊ በረከቶችን እንደሚያስገኝ መጽሐፍ ቅዱስ ያሳያል። ለምሳሌ ያህል፣ ራእይ 1:3 “የዚህን ትንቢት ቃል ጮክ ብሎ የሚያነብ እንዲሁም ቃሉን የሚሰሙ . . . ደስተኞች ናቸው” ይላል። ከዚህም በላይ ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት ለጢሞቴዎስ በሰጠው ምክር ላይ ቁልፍ ከሆኑት የጥናት ክፍሎች አንዱ የሆነውን ነገር ይኸውም ትኩረት የመሰብሰብን አስፈላጊነት ጠቁሟል፤ ጳውሎስ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “በእነዚህ ነገሮች ላይ አሰላስል፤ እንዲሁም ትኩረትህ ሙሉ በሙሉ በእነዚህ ነገሮች ላይ ያረፈ ይሁን።” እንዲህ ያለው ለምን ነበር? “እድገትህ በሁሉም ሰዎች ዘንድ በግልጽ እንዲታይ” በማለት ምክንያቱን ገልጿል።—1 ጢሞ. 4:15

እርግጥ ነው፣ ማንበብና ማጥናት መቻል በራሱ ለአንድ ሰው ጥቅም ያስገኝለታል ማለት አይደለም። ብዙ ሰዎች እነዚህ ችሎታዎች ቢኖሯቸውም አይጠቀሙባቸውም፤ ከዚህ ይልቅ እምብዛም ጥቅም በሌላቸው ሥራዎች ይጠመዳሉ። ታዲያ ወላጆች፣ ልጆቻቸው ጠቃሚ ለሆነ እውቀት ጉጉት እንዲኖራቸው መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው?

ፍቅራችሁና ምሳሌነታችሁ

ልጆች የጥናት ክፍለ ጊዜ አስደሳች እንዲሆንላቸው ጥናቱ ወላጆች ለልጆቻቸው ፍቅር እንዳላቸው በሚያሳይ መንገድ ሊከናወን ይገባዋል። ኦዌንና ክላውዲያ የሚባሉ ክርስቲያን ባልና ሚስት ሁለት ልጆቻቸው ትንሽ የነበሩበትን ጊዜ ሲያስታውሱ እንዲህ ይላሉ፦ “የጥናት ወቅት ለእነሱ ልዩ ጊዜ በመሆኑ በጉጉት ይጠብቁት ነበር፤ እንደምንወዳቸውና እንደምናስብላቸው ይሰማቸዋል። ጥናት ሲባል ወደ አእምሯቸው የሚመጣው ፍቅር የሰፈነበት አስደሳች ጊዜ ነበር።” ቤተሰብ ለጥናት የሚሰባሰብባቸው ጊዜያት ፍቅር የሰፈነባቸው መሆናቸው ልጆች አድገው ይበልጥ ተፈታታኝ ወደ ሆነው የአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ሲገቡም እንኳ ስለ ጥናት ጥሩ አመለካከት እንዲኖራቸው ያደርጋቸዋል። የኦዌንና የክላውዲያ ልጆች አሁን አቅኚዎች ሲሆኑ ወላጆቻቸው የንባብና የጥናት ፍቅር ስላሳደሩባቸው አሁንም ድረስ እየተጠቀሙ ነው።

ልጆች ንባብንና ጥናትን እንዲወዱ የሚረዳው ነገር የወላጆች ምሳሌነት ነው። ወላጆቻቸው ሲያነቡና ሲያጠኑ አዘውትረው የሚመለከቱ ልጆች እነሱም እነዚህን እንቅስቃሴዎች የሕይወታቸው ክፍል እንደሆኑ አድርገው መመልከታቸው አይቀርም። ይሁን እንጂ እናንተ የማንበብ ልማድ ከሌላችሁ ለልጆቻችሁ ጥሩ ምሳሌ ልትሆኑ የምትችሉት እንዴት ነው? ቅድሚያ በምትሰጧቸው ነገሮች ወይም ለንባብ ባላችሁ አመለካከት ረገድ ማስተካከያ ማድረግ ትችላላችሁ። (ሮም 2:21) ንባብ በሕይወታችሁ ውስጥ ትልቅ ቦታ ከምትሰጧቸው ነገሮች አንዱ ከሆነ ይህ በልጆቻችሁ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ያሳድራል። በተለይም መጽሐፍ ቅዱስ በማንበብ፣ ለስብሰባ በመዘጋጀትና የቤተሰብ ጥናት በማድረግ ረገድ ትጉ መሆናችሁ እነዚህ እንቅስቃሴዎች ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆኑ ለልጆቻችሁ ግልጽ መልእክት ያስተላልፋል።

በመሆኑም ፍቅራችሁና ምሳሌነታችሁ ልጆቻችሁ የማንበብ ፍላጎት እንዲያድርባቸው ለመርዳት ወሳኝ ነገሮች ናቸው። ይሁን እንጂ ልጆቻችሁን ለማበረታታት ምን ተግባራዊ እርምጃዎች ልትወስዱ ትችላላችሁ?

የማንበብ ፍቅር እንዲያድርባቸው መርዳት

ልጆቻችሁ የንባብ ፍቅር እንዲያድርባቸው ለመርዳት ገና ከጅምሩ ልትወስዷቸው የምትችሏቸው አንዳንድ ጠቃሚ እርምጃዎች ምንድን ናቸው? ገና ከጨቅላነታቸው ጀምሮ መጻሕፍት ስጧቸው። ወላጆቹ የማንበብ ፍቅር ያሳደሩበት አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “ልጆቻችሁ መጻሕፍትን እንዴት መያዝና መጠቀም እንደሚችሉ አሠልጥኗቸው። በዚህ መንገድ መጻሕፍት ጓደኞቻቸውና የሕይወታቸው ክፍል ይሆናሉ።” ብዙ ልጆች ማንበብ ከመቻላቸው ከረጅም ጊዜ በፊት ከታላቁ አስተማሪ ተማር እና የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ እንደተባሉት ያሉት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ መጻሕፍት የቅርብ ጓደኞቻቸው ይሆናሉ። እንደዚህ ያሉ ጽሑፎችን ከልጆቻችሁ ጋር ስታነቡ ከቋንቋው ጋር ብቻ ሳይሆን ‘ከመንፈሳዊ ጉዳዮች’ እና “ከመንፈሳዊ ቃላት” ጋር እንዲተዋወቁ ታደርጋላችሁ።—1 ቆሮ. 2:13

ዘወትር ድምፃችሁን ከፍ አድርጋችሁ አንብቡ። በየቀኑ ከልጆቻችሁ ጋር የማንበብ ልማድ አዳብሩ። እንዲህ ማድረጋችሁ ትክክለኛውን አነባበብ የሚያስተምራቸው ከመሆኑም በላይ የማንበብን ልማድ ያዳብራል። የምታነቡበት መንገድም ቢሆን ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ሕያው በሆነ መንገድ አንብቡ፤ ልጆቹም እንዲሁ ያደርጋሉ። እንዲያውም ልጆቻችሁ አንድን ታሪክ ደጋግማችሁ እንድታነቡላቸው ይጠይቋችሁ ይሆናል። ሳትሰለቹ አንብቡላቸው! ከጊዜ በኋላ አዳዲስ ርዕሰ ጉዳዮችን እንድታነቡላቸው መጠየቃቸው አይቀርም። ይሁን እንጂ አብረዋችሁ እንዲያነቡ ለማስገደድ መሞከር የለባችሁም። ኢየሱስ አድማጮቹን “መረዳት በሚችሉት መጠን” ብቻ በማስተማር በዚህ ረገድ ምሳሌ ትቶልናል። (ማር. 4:33) ልጆቻችሁን አብረዋችሁ እንዲያነቡ የማታስገድዷቸው ከሆነ እያንዳንዱን የንባብ ወቅት በጉጉት ይጠባበቃሉ፤ እናንተም የማንበብ ፍቅር እንዲያዳብሩ በመርዳት ረገድ ይበልጥ እየተሳካላችሁ ትሄዳላችሁ።

ሐሳባቸውን እንዲገልጹ አበረታቷቸው፤ እንዲሁም የምታነቡትን ተወያዩበት። ትንንሽ ልጆቻችሁ በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ቃላትን መለየት፣ አጠራራቸውን ማወቅ እንዲሁም ትርጉማቸውን መረዳት ሲችሉ በጣም ትደሰታላችሁ። በምታነቡት ነገር ላይ መወያየት እድገታቸውን በእጅጉ ያፋጥነዋል። ልጆች ጥሩ አንባቢ እንዲሆኑ መርዳት የሚቻለው እንዴት እንደሆነ የሚገልጽ አንድ መጽሐፍ እንደሚጠቁመው መወያየታችሁ ልጆቹ “ቃላትን እንዲያውቁ ይረዳቸዋል፤ ይህም ወደፊት በሚያነቡበት ጊዜ እነዚያን ቃላት ለመለየትና ለመረዳት ያስችላቸዋል።” ይኸው መጽሐፍ አክሎ እንደገለጸው “የሕፃናት አእምሮ እውቀት ለመሰብሰብ ክፍት በመሆኑ [ከእነሱ ጋር] ማውራት እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው፤ በተለይ ወሬው ትርጉም ያለው . . . ሲሆን ይበልጥ ይጠቅማቸዋል።”

ልጆቻችሁ እንዲያነቡላችሁ አድርጉ፤ ጥያቄም እንዲጠይቋችሁ አበረታቷቸው። እናንተ ራሳችሁ ጥያቄ ከጠየቃችሁ በኋላ መልስ ሊሆኑ የሚችሉ ሐሳቦችን መጠቆም ትፈልጉ ይሆናል። እንዲህ ማድረጋችሁ ልጆች፣ መጻሕፍት የእውቀት ምንጭ እንደሆኑና የሚያነቡት እያንዳንዱ ቃል ትርጉም እንዳለው እንዲማሩ ያስችላቸዋል። በተለይ የምታነቡት ነገር ከየትኛውም መጽሐፍ የበለጠ አስፈላጊ በሆነው በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ ከሆነ ይህ ዘዴ ጠቃሚ ነው።—ዕብ. 4:12

ይሁንና ማንበብ አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል ፈጽሞ አትርሱ። ጥሩ አንባቢ ለመሆን ጊዜና ልምምድ ይጠይቃል። * ስለዚህ ትንንሽ ልጆቻችሁ ለንባብ ፍቅር እያዳበሩ ሲሄዱ በየጊዜው አድናቆታችሁን ልትገልጹላቸው እንደሚገባ አትዘንጉ። ልጆቻችሁን ማድነቃችሁ ለንባብ ፍቅር እንዲኖራቸው ይረዳል።

ጠቃሚና አስደሳች

ልጆቻችሁን እንዴት እንደሚያጠኑ ስታስተምሯቸው ንባብ ትርጉም ያለው ይሆንላቸዋል። ጥናት፣ ስለተለያዩ ነገሮች ትክክለኛ እውቀት ማግኘትንና አንዱ ከሌላው ጋር እንዴት እንደሚዛመድ ማስተዋልን ይጠይቃል። እንዲሁም የተገኘውን መረጃ የማቀናበር፣ የማስታወስና በመረጃው የመጠቀም ችሎታ ያስፈልጋል። ልጃችሁ እንዴት እንደሚያጠና ከተማረና ማጥናት የሚያስገኘውን ጥቅም ከተገነዘበ ጥናት ጠቃሚና አስደሳች ይሆንለታል።—መክ. 10:10

ለጥናት አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ማሳወቅ። የቤተሰብ አምልኮ የምታደርጉበት ምሽት፣ በዕለት ጥቅሱ ላይ የምታደርጉት ውይይትና እንደነዚህ ያሉት እንቅስቃሴዎች ልጆቻችሁ የማጥናት ችሎታን እንዲያዳብሩ ለመርዳት ግሩም አጋጣሚዎች ይሰጧችኋል። አንድ ልጅ ለአጭር ጊዜም ቢሆን አርፎ ቁጭ ብሎ ሐሳቡ ሳይበታተን አንድን ነገር እንዲከታተል ማድረግ ትኩረቱን መሰብሰብን እንዲለማመድ ያደርገዋል፤ ይህ ደግሞ ትምህርት ለመቅሰም አስፈላጊ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ወንድ ልጅህ አሁን የተማረው ነገር ቀደም ሲል ከሚያውቀው ጋር እንዴት እንደሚዛመድ እንዲነግርህ ልትጠይቀው ትችላለህ። ይህ ልጁ ነገሮችን ማነጻጸርን እንዲለምድ ይረዳዋል። ሴት ልጅህ ደግሞ ያነበበችውን ነገር በራሷ አባባል ተጠቅማ ፍሬ ነገሩን በአጭሩ እንድታስቀምጥ ልትጠይቃት ትችላለህ። እንዲህ ማድረጓ ያነበበችው ነገር ምን ቁም ነገር እንደያዘ እንድታስተውልና ነጥቡን እንድታስታውስ ይረዳታል። ያነበቡትን ነገር ለማስታወስ የሚረዳው ሌላው ዘዴ ደግሞ መከለስ ሲሆን ይህ ዘዴ አንድን ርዕሰ ትምህርት ካነበቡ በኋላ ዋና ዋና ነጥቦቹን ደግሞ መናገር ማለት ነው። ትንንሽ ልጆችም እንኳ በጥናቱ ወቅት ወይም በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ አጭር ማስታወሻ መያዝ ሊማሩ ይችላሉ። ይህ ደግሞ ትኩረታቸውን እንዲሰበስቡ የሚረዳ በጣም ጠቃሚ ዘዴ ነው! እነዚህን ቀላል የሆኑ ዘዴዎች ተግባራዊ ማድረጋችሁ ለእናንተም ሆነ ለልጆቻችሁ የመማር ሂደቱን አስደሳችና ትርጉም ያለው ያደርግላችኋል።

ለማጥናት የሚጋብዙ ሁኔታዎች እንዲኖሩ አድርጉ። በምታጠኑበት ክፍል ውስጥ አየር በደንብ መንሸራሸር እንዲችልና በቂ ብርሃን እንዲኖር እንዲሁም ጸጥታ እንዲሰፍንና ምቹ ሁኔታ እንዲኖር ማድረጋችሁ ልጆቹ ትኩረታቸውን መሰብሰብ ቀላል እንዲሆንላቸው ይረዳል። እርግጥ ነው፣ ወላጆች ለጥናት ያላቸው አመለካከት ወሳኝ ነው። “ወላጆች ለንባብና ለጥናት የመደባችሁት ፕሮግራም ቋሚና የማይቋረጥ እንዲሆን ማድረጋችሁ በጣም አስፈላጊ ነው” በማለት አንዲት እናት ተናግራለች። “ይህም ልጆቻችሁ የተደራጁ እንዲሆኑ ይረዳቸዋል። ምን ነገር በምን ጊዜ መከናወን እንዳለበት እያወቁ ይሄዳሉ።” ብዙ ወላጆች በጥናት ወቅት ሌሎች እንቅስቃሴዎች ጣልቃ እንዲገቡ አይፈቅዱም። አንድ ባለሞያ እንደገለጹት ይህ ዘዴ ልጆች ጥሩ የጥናት ልማድ እንዲያዳብሩ በማስተማር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው።

የጥናት ጥቅም ጎልቶ እንዲታያቸው አድርጉ። በመጨረሻም ልጆቻችሁ ያጠኑት ነገር እንዴት እንደሚጠቅማቸው እንዲያስተውሉ እርዷቸው። በጥናት ያገኙትን መረጃ በሥራ ላይ ማዋላቸው ጥናቱ ዓላማ ያለው እንዲሆን ያደርግላቸዋል። አንድ ወጣት ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “የማጠናው ነገር ያለውን ጠቀሜታ ካልተረዳሁ ያንን ነገር ማጥናት ትግል ይሆንብኛል። በሕይወቴ ውስጥ ተግባራዊ ላደርገው የምችለው ከሆነ ግን ያንን ነገር ለመረዳት ፍላጎት ያድርብኛል።” ወጣቶች ጥናትን አንድ ጠቃሚ ግብ ላይ ለመድረስ እንደሚያስችል መንገድ አድርገው ካዩት ጥናቱን በተመስጦ ያከናውናሉ። ለማንበብ ፍቅር ማዳበር እንደቻሉት ሁሉ ለጥናትም ፍቅር እያደረባቸው ይሄዳል።

ከሁሉ የላቀው ጥቅም

ልጆቻችሁ የማንበብ ፍቅር እንዲያድርባቸው መርዳት የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች በሙሉ ዘርዝሮ መጨረስ አይቻልም። ማንበብና ማጥናት ከሚያስገኟቸው ጥቅሞች መካከል በትምህርት ቤትና በሥራ ቦታ ስኬታማ መሆን፣ ከሰዎች ጋር ጥሩ ግንኙነት መመሥረት፣ ስለምንኖርበት ዓለም በሚገባ ማወቅ እንዲሁም በወላጅና በልጅ መካከል ጠንካራ ፍቅር እንዲኖር ማድረግ ይገኙበታል፤ ማንበብና ማጥናት በራሱ የሚያስገኘው ጥልቅ እርካታም ሳይጠቀስ የሚታለፍ አይደለም።

ከሁሉ በላይ ደግሞ ልጆቻችሁ ለጥናት ፍቅር ማዳበራቸው መንፈሳዊ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች እንዲሆኑ ሊረዳቸው ይችላል። የጥናት ፍቅር፣ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት “ስፋቱ፣ ርዝመቱ፣ ከፍታውና ጥልቀቱ ምን ያህል እንደሆነ” ለመረዳት እንዲችሉ አእምሯቸውንና ልባቸውን ለመክፈት የሚያስችል ቁልፍ ነው። (ኤፌ. 3:18) እርግጥ ነው፣ ክርስቲያን ወላጆች ለልጆቻቸው የሚያስተምሩት ብዙ ነገር አላቸው። ወላጆች ለልጆቻቸው ጊዜና ትኩረት ከሰጡ እንዲሁም ገና ከልጅነታቸው ጀምሮ ጥሩ መሠረት እንዲኖራቸው የሚችሉትን ሁሉ ካደረጉ ልጆቻቸው የኋላ ኋላ የይሖዋ አምላኪዎች ለመሆን እንደሚመርጡ ተስፋ ማድረጋቸው የተገባ ነው። ልጆቻችሁ ጥሩ የጥናት ልማድ እንዲኖራቸው ማሠልጠናችሁ ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና ለመመሥረትና ይህን ዝምድና ጠብቀው ለመኖር የሚያስችላቸውን መንገድ ይከፍትላቸዋል። እንግዲያው ልጆቻችሁ የንባብና የጥናት ፍቅር እንዲያድርባቸው ለመርዳት በምትጣጣሩበት ጊዜ የይሖዋ በረከት እንዳይለያችሁ በጸሎት መጠየቃችሁ የተገባ ነው።—ምሳሌ 22:6

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.14 ትምህርት የመቀበል ችግር ያለባቸው ልጆች ማንበብና ማጥናት ከሌሎች በተለየ ተፈታታኝ ይሆንባቸዋል። ወላጆች እንዲህ ዓይነት ችግር ያለባቸውን ልጆቻቸውን እንዴት መርዳት እንደሚችሉ ሐሳብ ለማግኘት የጥር 2009 ንቁ! ገጽ 10, 11⁠ን እንዲሁም የየካቲት 22, 1997 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ከገጽ 3-10 መመልከት ይችላሉ።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የንባብ ፍቅር እንዲያድርባቸው . . .

• ከጨቅላነታቸው ጀምሮ መጻሕፍት ስጧቸው

• ድምፃችሁን ከፍ አድርጋችሁ አንብቡላቸው

• ሐሳባቸውን እንዲገልጹ አበረታቷቸው

• የምታነቡትን ተወያዩበት

• ልጆቻችሁ እንዲያነቡላችሁ አድርጉ

• ጥያቄ እንዲጠይቋችሁ አበረታቷቸው

የጥናት ፍቅር እንዲያድርባቸው . . .

• ጥሩ ምሳሌ ሁኑላቸው

• ልጆቻችሁ የሚከተሉትን ነገሮች እንዲለምዱ አሠልጥኗቸው፦

○ ትኩረትን መሰብሰብ

○ ነገሮችን ማነጻጸር

○ ፍሬ ነገሩን በአጭሩ ማስቀመጥ

○ መከለስ

○ ማስታወሻ መያዝ

• ለማጥናት የሚጋብዙ ሁኔታዎች እንዲኖሩ አድርጉ

• የጥናት ጥቅም ጎልቶ እንዲታያቸው አድርጉ