በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በታላቁ መንፈሳዊ የመከር ሥራ የተሟላ ተሳትፎ ይኑራችሁ

በታላቁ መንፈሳዊ የመከር ሥራ የተሟላ ተሳትፎ ይኑራችሁ

በታላቁ መንፈሳዊ የመከር ሥራ የተሟላ ተሳትፎ ይኑራችሁ

“የጌታ ሥራ የበዛላችሁ ሁኑ።”—1 ቆሮ. 15:58

1. ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ምን ግብዣ አቅርቦላቸው ነበር?

ኢየሱስ በ30 ዓ.ም. መገባደጃ አካባቢ የሰማርያን ክልል አቋርጦ በሄደበት ወቅት ሲካር በተባለች ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ አንድ የውኃ ጉድጓድ አጠገብ አረፍ ብሎ ነበር። በዚያም ለደቀ መዛሙርቱ “ዓይናችሁን ወደ ማሳው አቅንታችሁ አዝመራው እንደነጣ ተመልከቱ” አላቸው። (ዮሐ. 4:35) ኢየሱስ እየተናገረ ያለው ሰብል ስለመሰብሰብ ሳይሆን የእሱ ተከታይ የሚሆኑ ልበ ቅን ሰዎችን ስለመሰብሰቡ መንፈሳዊ የመከር ሥራ ነበር። በሌላ አባባል ደቀ መዛሙርቱ በዚህ ሥራ እንዲካፈሉ እየጋበዛቸው ነበር። ሥራው በጣም ብዙ ቢሆንም ያለው ጊዜ ግን አጭር ነበር!

2, 3. (ሀ) የምንኖረው በመከር ወቅት መሆኑን የሚጠቁመው ምንድን ነው? (ለ) በዚህ ርዕስ ላይ ምን እንመረምራለን?

2 ኢየሱስ ስለ መከሩ ሥራ የተናገረው ሐሳብ በዘመናችን ልዩ ትርጉም አለው። የምንኖረው በእርሻ የተመሰለው ዓለም “እንደነጣ” በሌላ አባባል ለመከር እንደደረሰ በግልጽ በሚታይበት ዘመን ነው። በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት ሰጪ የሆነውን እውነት እንዲቀበሉ ግብዣ እየቀረበላቸው ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በመጠመቅ አዳዲስ ደቀ መዛሙርት ይሆናሉ። እኛም የመከሩ ሥራ ጌታ የሆነው ይሖዋ አምላክ የሚሰጠውን አመራር በመከተል ባለፉት ዘመናት ሁሉ ከተከናወኑት በሚበልጠው የመከር ሥራ የመካፈል መብት አግኝተናል። በዚህ የመከር ሥራ በመካፈል ረገድ ‘ሥራ የበዛልህ’ ነህ?—1 ቆሮ. 15:58

3 ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ባከናወነበት ሦስት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ደቀ መዛሙርቱን የመከሩ ሠራተኞች እንዲሆኑ አዘጋጅቷቸዋል። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ካስተማራቸው በርካታ ጠቃሚ ትምህርቶች መካከል ሦስቱ በዚህ የጥናት ርዕስ ላይ ይብራራሉ። እነዚህ ትምህርቶች በዘመናችን በሚካሄደው ደቀ መዛሙርትን የመሰብሰብ ሥራ አቅማችን የሚፈቅደውን ያህል ለመካፈል የሚያስችሉንን በጣም ጠቃሚ የሆኑ ባሕርያት ያጎላሉ። እስቲ እነዚህን ባሕርያት አንድ በአንድ እንመልከታቸው።

ትሕትና በጣም አስፈላጊ ነው

4. ኢየሱስ የትሕትናን አስፈላጊነት በምሳሌ ያስተማረው እንዴት ነው?

4 እስቲ የሚከተለውን ሁኔታ በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር፦ ደቀ መዛሙርቱ ከሁሉ የሚበልጠው ማን እንደሆነ እየተከራከሩ ነበር። እርስ በርስ በጎሪጥ ይተያዩ የነበረ ከመሆኑም ሌላ በመካከላቸው አለመተማመን እንደሰፈነ ያስታውቃል። በመሆኑም ኢየሱስ አንድ ትንሽ ልጅ ጠርቶ በመካከላቸው እንዲቆም አደረገ። ከዚያም ትኩረቱን በልጁ ላይ በማድረግ እንዲህ አለ፦ “በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚበልጠው እንደዚህ ትንሽ ልጅ ራሱን ዝቅ የሚያደርግ [ወይም “ራሱን ትንሽ የሚያደርግ፣” ባይንግተን] ነው።” (ማቴዎስ 18:1-4ን አንብብ።) ሰውን በሥልጣኑ፣ በሀብቱና በታዋቂነቱ ከሚመዝነው ከዚህ ዓለም በተለየ መልኩ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ታላቅ መሆናቸው የሚለካው በሌሎች ዘንድ ‘ራሳቸውን ትንሽ በማድረጋቸው’ መሆኑን መገንዘብ ነበረባቸው። ይሖዋ ሊባርካቸውና ሊጠቀምባቸው የሚችለው እውነተኛ ትሕትና ካሳዩ ብቻ ነው።

5, 6. በመከሩ ሥራ የተሟላ ተሳትፎ ለማድረግ ትሑት መሆን ያለብህ ለምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ።

5 ዛሬም ቢሆን በዓለም ላይ ያሉ ብዙ ሰዎች ሕይወታቸው ያተኮረው ሥልጣንን፣ ሀብትንና ዝናን በማሳደድ ላይ ነው። በዚህም የተነሳ ለመንፈሳዊ ነገሮች እምብዛም ቦታ አይሰጡም ወይም ጨርሶ ጊዜ የላቸውም። (ማቴ. 13:22) ከዚህ በተቃራኒ የይሖዋ ሕዝቦች የመከሩን ሥራ ጌታ ሞገስና በረከት ለማግኘት ስለሚፈልጉ በሌሎች ዘንድ ‘ራሳቸውን ትንሽ ለማድረግ’ ፈቃደኞች ናቸው።—ማቴ. 6:24፤ 2 ቆሮ. 11:7፤ ፊልጵ. 3:8

6 በደቡብ አሜሪካ ውስጥ የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ የሚያገለግለውን ፍራንሲስኮን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ወጣት እያለ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን በማቋረጥ አቅኚ ሆነ። እንዲህ ይላል፦ “ከጊዜ በኋላ ለማግባት ስወስን እኔና ባለቤቴ ጥሩ ኑሮ እንዲኖረን የሚያደርግ ሥራ ማግኘት እችል ነበር። ሆኖም ሕይወታችንን ቀላል ለማድረግና ሁለታችንም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመቀጠል ወሰንን። በኋላ ላይ ልጆች ስንወልድ ሁኔታዎች ይበልጥ እየከበዱ ሄዱ። ያም ሆኖ ይሖዋ በውሳኔያችን እንድንጸና ረድቶናል።” ፍራንሲስኮ ሐሳቡን ሲያጠቃልል እንዲህ ብሏል፦ “ካገኘኋቸው ልዩ የሆኑ በርካታ ኃላፊነቶች በተጨማሪ ከ30 ለሚበልጡ ዓመታት በሽምግልና የማገልገል መብት አግኝቻለሁ። ሕይወታችንን ቀላል በማድረጋችን አንድም ቀን ቆጭቶን አያውቅም።”

7. በ⁠ሮም 12:16 ላይ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ ምን ጥረት አድርገሃል?

7 አንተም በዓለም ላይ የሚታየውን ‘ራስን ከፍ አድርጎ’ የመመልከት ዝንባሌ በማስወገድ “ትሕትና የሚንጸባረቅበት አስተሳሰብ” የምታዳብር ከሆነ በመከሩ ሥራ ብዙ በረከትና መብት እንደምታገኝ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ።—ሮም 12:16፤ ማቴ. 4:19, 20፤ ሉቃስ 18:28-30

ትጉ መሆን ጥሩ ውጤት ያስገኛል

8, 9. (ሀ) ኢየሱስ ስለ ታላንቱ የተናገረውን ታሪክ በአጭሩ ግለጽ። (ለ) ይህ ታሪክ በተለይ እነማንን ሊያበረታታ ይችላል?

8 በመከሩ ሥራ የተሟላ ተሳትፎ ለማድረግ የሚረዳን ሌላው ባሕርይ ትጋት ነው። ኢየሱስ ስለ ታላንት የተናገረው ታሪክ ለዚህ ምሳሌ ይሆነናል። * ታሪኩ ወደ ሌላ አገር ከመጓዙ በፊት ለሦስት ባሪያዎቹ ንብረቱን በአደራ ስለሰጠ ሰው የሚናገር ነው። ለመጀመሪያው አምስት ታላንት፣ ለሌላው ሁለት፣ ለሦስተኛው ደግሞ አንድ ሰጣቸው። የመጀመሪያዎቹ ሁለት ባሪያዎች ጌታቸው እንደሄደ በትጋት በመሥራት በተሰጣቸው ታላንት ‘ነገዱበት።’ ሦስተኛው ባሪያ ግን “ሰነፍ” ስለነበር ታላንቱን መሬት ውስጥ ቀበረው። ጌታቸው ሲመለስ የመጀመሪያዎቹን ሁለት ባሪያዎች “በብዙ ነገሮች ላይ” ላይ በመሾም ለሥራቸው ወሮታ ከፈላቸው። ከሦስተኛው ባሪያ ግን የሰጠውን ታላንት የወሰደበት ሲሆን ከቤቱም አባረረው።—ማቴ. 25:14-30

9 አንተም ኢየሱስ በተናገረው ታሪክ ላይ የተገለጹትን ትጉ ባሪያዎች ምሳሌ በመከተል ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በተቻለህ መጠን ሙሉ ተሳትፎ ማድረግ እንደምትፈልግ ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁንና ያለህበት ሁኔታ ብዙ መሥራት እንዳትችል አቅምህን ገድቦት ቢሆንስ? ለምሳሌ የኑሮ ውድነት በመኖሩ ለቤተሰብህ የሚያስፈልገውን ለማቅረብ ስትል ረጅም ሰዓት ለመሥራት ተገድደህ ይሆናል። ወይም ደግሞ በዕድሜ መግፋት ምክንያት ጉልበትና ጤና አጥተህ ይሆናል። ሁኔታህ እንደዚህ ከሆነ የታላንቱ ታሪክ ለአንተም ማበረታቻ ይዟል።

10. ኢየሱስ በተናገረው ታሪክ ላይ የተጠቀሰው ጌታ ምክንያታዊ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነበር? ይህስ አንተን በግልህ የሚያበረታታህ እንዴት ነው?

10 በታሪኩ ላይ የተገለጸው ጌታ እያንዳንዱ ባሪያ አቅሙ የተለያየ መሆኑን ተገንዝቦ እንደነበር ልብ በል። ታላንቱን “ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው” መስጠቱ ይህን ያሳያል። (ማቴ. 25:15) እንደተጠበቀው የመጀመሪያው ባሪያ ከሁለተኛው ባሪያ የበለጠ አትርፏል። ሆኖም ጌታው ሁለቱም ባሪያዎች “ጥሩና ታማኝ” እንደሆኑ መግለጹ እንዲሁም ለሁለቱም አንድ ዓይነት ሽልማት መስጠቱ ሁለቱም በትጋት መሥራታቸውን እንደተገነዘበ የሚያሳይ ነው። (ማቴ. 25:21, 23) በተመሳሳይም የመከሩ ሥራ ጌታ የሆነው ይሖዋ አምላክ ያለህበት ሁኔታ በእሱ አገልግሎት በሚኖርህ ተሳትፎ ላይ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ያውቃል። እሱን ለማገልገል በሙሉ ነፍስህ የምታደርገውን ጥረት ያስተውላል፤ እንዲሁም የሚገባህን ወሮታ ይከፍልሃል።—ማር. 14:3-9፤ ሉቃስ 21:1-4ን አንብብ።

11. አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ሥር እያሉም በትጋት መሥራት ብዙ በረከት የሚያስገኘው እንዴት እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ።

11 ሴልሚራ የምትባል በብራዚል የምትኖር አንዲት እህት ምሳሌ እንደሚያሳየው በአምላክ አገልግሎት ትጉ መሆን ኑሯችን የተመቻቸ በመሆኑ ላይ የተመካ አይደለም። ከሃያ ዓመታት በፊት የሴልሚራ ባለቤት በዘራፊዎች ስለተገደለ ሦስት ትንንሽ ልጆቿን ብቻዋን ለማሳደግ ተገደደች። የቤት ሠራተኛ ሆና ረጅም ሰዓታት ትሠራ የነበረ ሲሆን ጥቅጥቅ አድርገው በሚጭኑ የሕዝብ መጓጓዣዎች የምታደርገው ጉዞም በጣም አድካሚ ነበር። ሴልሚራ እነዚህ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢኖሩባትም ፕሮግራሟን አስተካክላ የዘወትር አቅኚ ሆነች። ከጊዜ በኋላ ሁለቱ ልጆቿ እንደ እሷ አቅኚ ሆኑ። “ባለፉት ዓመታት ውስጥ ከ20 የሚበልጡ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠናሁ ሲሆን አሁን ‘የቤተሰቤ’ አባላት ሆነዋል” ብላለች። “አሁንም ድረስ እነዚህ ሰዎች ወዳጆቼ ናቸው፤ በጣም እንዋደዳለን። ይህ ገንዘብ ሊገዛው የማይችል ውድ ሀብት ነው።” የመከሩ ሥራ ጌታ የሴልሚራን ትጋት የተሞላበት ጥረት እንደባረከው ምንም ጥርጥር የለውም!

12. በስብከቱ ሥራ ትጋት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

12 አሁን ያለህበት ሁኔታ በአገልግሎት የምታሳልፈውን ጊዜ የሚገድብብህ ቢሆንም እንኳ ይበልጥ ውጤታማ የሆነ አገልግሎት ለማከናወን ጥረት በማድረግ በመከሩ ሥራ ያለህን ተሳትፎ ማሳደግ ትችላለህ። በየሳምንቱ በአገልግሎት ስብሰባ ላይ የሚቀርቡትን ጠቃሚ ሐሳቦች በቁም ነገር ተግባራዊ የምታደርጋቸው ከሆነ የስብከት ችሎታህን እያሻሻልክ የምትሄድ ከመሆኑም ሌላ አዳዲስ የስብከት ዘዴዎችን መጠቀም ትችላለህ። (2 ጢሞ. 2:15) ከዚህም በተጨማሪ የምትችል ከሆነ በፕሮግራምህ ላይ ማስተካከያ በማድረግ ወይም እምብዛም አስፈላጊ ያልሆኑ ነገሮችን በመተው ጉባኤው ለመስክ አገልግሎት ያደረገውን ዝግጅት በቋሚነት መደገፍ ትችላለህ።—ቆላ. 4:5

13. ትጋትን ለማዳበርና ይህን ባሕርይ ይዘን ለመቀጠል ቁልፉ ምንድን ነው?

13 አንድ ሰው ትጉ የሚሆነው ለአምላክ ፍቅርና አድናቆት ሲኖረው መሆኑን አስታውስ። (መዝ. 40:8) ኢየሱስ በተናገረው ታሪክ ላይ የተጠቀሰው ሦስተኛው ባሪያ ጌታው ብዙ የሚጠብቅና ምክንያታዊነት የጎደለው ሰው እንደሆነ ስላሰበ ፈርቶት ነበር። በዚህም የተነሳ ይህ ባሪያ በታላንቱ ተጠቅሞ የጌታው ንብረት እየጨመረ እንዲሄድ ከማድረግ ይልቅ ታላንቱን ቀበረው። እኛም እንዲህ ዓይነት የስንፍና አዝማሚያ እንዳይጠናወተን የመከሩ ሥራ ጌታ ከሆነው ከይሖዋ ጋር የቀረበ ዝምድና መመሥረትና ይህንን ዝምድና ላለማጣት መጣር ይኖርብናል። እንደ ፍቅር፣ ትዕግሥትና ምሕረት ስላሉት ማራኪ ባሕርያቱ ለማጥናትና በእነዚህ ላይ ለማሰላሰል ጊዜ መድብ። ይህን ስታደርግ በእሱ አገልግሎት የተቻለህን ሁሉ ለማድረግ ከልብ ትነሳሳለህ።—ሉቃስ 6:45፤ ፊልጵ. 1:9-11

“ቅዱሳን ልትሆኑ ይገባል”

14. የመከሩ ሠራተኞች ለመሆን የሚፈልጉ ሁሉ የትኛውን አስፈላጊ ብቃት ማሟላት ይኖርባቸዋል?

14 ሐዋርያው ጴጥሮስ ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት በመጥቀስ አምላክ ለምድራዊ አገልጋዮቹ ያለውን ፈቃድ እንዲህ በማለት ገልጾታል፦ “የጠራችሁ ቅዱስ አምላክ፣ ቅዱስ እንደሆነ ሁሉ እናንተም ራሳችሁ በምግባራችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ፤ ምክንያቱም ‘እኔ ቅዱስ ስለሆንኩ እናንተም ቅዱሳን ልትሆኑ ይገባል’ ተብሎ ተጽፏል።” (1 ጴጥ. 1:15, 16፤ ዘሌ. 19:2፤ ዘዳ. 18:13) ይህ አባባል የመከሩ ሠራተኞች በመንፈሳዊና በሥነ ምግባራዊ ሁኔታ ንጽሕናቸውን መጠበቅ እንዳለባቸው አጉልቶ ያሳያል። በምሳሌያዊ አነጋገር ታጥበን ለመንጻት የሚያስችሉንን እርምጃዎች በመውሰድ ይህን አስፈላጊ ብቃት ማሟላት እንችላለን። ታዲያ ራሳችንን ማንጻት የምንችለው በምንድን ነው? እውነት በሆነው የአምላክ ቃል አማካኝነት ነው።

15. እውነት የሆነው የአምላክ ቃል እኛን ምን የማድረግ ኃይል አለው?

15 እውነት የሆነው የአምላክ ቃል፣ ለማንጻት ከሚያገለግል ውኃ ጋር ተመሳስሏል። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ የቅቡዓን ክርስቲያኖችን ጉባኤ የሚመለከተው ‘በቃሉ አማካኝነት በውኃ ታጥባ ቅዱስና እንከን የለሽ’ እንደሆነች የክርስቶስ ሙሽራ ንጹሕ አድርጎ መሆኑን ሐዋርያው ጳውሎስ ጽፏል። (ኤፌ. 5:25-27) ኢየሱስ ራሱ እሱ የሰበከው የአምላክ ቃል ስላለው የማንጻት ኃይል ቀደም ሲል ተናግሮ ነበር። ለደቀ መዛሙርቱ “እናንተ ከነገርኳችሁ ቃል የተነሳ አሁን ንጹሐን ናችሁ” ብሏቸው ነበር። (ዮሐ. 15:3) በመሆኑም እውነት የሆነው የአምላክ ቃል ሰዎችን በሥነ ምግባርና በመንፈሳዊ ንጹሕ እንዲሆኑ የማድረግ ኃይል አለው። አምልኮታችን በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት የሚኖረው የአምላክ እውነት በዚህ መንገድ እንዲያነጻን ከፈቀድንለት ብቻ ነው።

16. በመንፈሳዊና በሥነ ምግባራዊ ሁኔታ ንጽሕናችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?

16 በመሆኑም በአምላክ የመከር ሥራ ለመካፈል መጀመሪያ በሥነ ምግባርም ሆነ በመንፈሳዊ ሁኔታ የሚያረክሱንን ነገሮች በሙሉ ማስወገድ ይኖርብናል። አዎን፣ የመከሩ ሠራተኛ የመሆን መብታችንን ይዘን ለመቀጠል እንድንችል የይሖዋን የላቁ ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ መሥፈርቶች በመጠበቅ ረገድ ምሳሌ መሆን አለብን። (1 ጴጥሮስ 1:14-16ን አንብብ።) ለአካላዊ ንጽሕናችን ሁልጊዜ ትኩረት እንደምንሰጥ ሁሉ እውነት የሆነው የአምላክ ቃል እንዲያነጻን ሁልጊዜ ራሳችንን ማቅረብ አለብን። ይህም መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብንና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘትን ይጨምራል። ከዚህም ሌላ የአምላክን ማሳሰቢያዎች በሕይወታችን ውስጥ በተግባር ለማዋል ልባዊ ጥረት ማድረግ ያስፈልገናል። ይህን ማድረጋችን የኃጢአተኝነት ዝንባሌያችንን ለመዋጋትና ይህ ዓለም የሚያሳድርብንን በካይ ተጽዕኖ ለመቋቋም ያስችለናል። (መዝ. 119:9፤ ያዕ. 1:21-25) አዎን፣ ከባድ ኃጢአት ብንሠራም እንኳ እውነት በሆነው የአምላክ ቃል አማካኝነት ‘ታጥበን መንጻት’ እንደምንችል ማወቃችን እንዴት የሚያጽናና ነው!—1 ቆሮ. 6:9-11

17. ንጽሕናችንን ለመጠበቅ የትኞቹን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክሮች ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል?

17 እውነት የሆነው የአምላክ ቃል እንዲያነጻህ እየፈቀድክ ነው? ለምሳሌ፣ በዚህ ዓለም ላይ ስላሉት ወራዳ መዝናኛዎች ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ ምን ምላሽ ትሰጣለህ? (መዝ. 101:3) እምነትህን ከማይጋሩ አብረውህ የሚማሩ ልጆችና የሥራ ባልደረቦችህ ጋር አላስፈላጊ ቅርርብ ከመፍጠር ትቆጠባለህ? (1 ቆሮ. 15:33) በይሖዋ ፊት ያለህን ንጽሕና እንድታጣ ሊያደርጉህ የሚችሉ የግል ድክመቶችህን ለማሸነፍ ከልብህ ጥረት ታደርጋለህ? (ቆላ. 3:5) ከዚህ ዓለም የፖለቲካ ውዝግብ እንዲሁም ብሔራዊ ስሜት ከሚንጸባረቅባቸው የውድድር ስፖርቶች ትርቃለህ?—ያዕ. 4:4

18. በሥነ ምግባርና በመንፈሳዊ ንጹሕ መሆናችን ውጤታማ የመከሩ ሠራተኞች እንድንሆን የሚረዳን እንዴት ነው?

18 እንደነዚህ ባሉት ጉዳዮች ረገድ በታማኝነት መታዘዝህ ግሩም ውጤቶች ያስገኛል። ኢየሱስ ቅቡዓን ደቀ መዛሙርቱን ከወይን ቅርንጫፎች ጋር በማመሳሰል እንዲህ ብሏል፦ “በእኔ ላይ ያለውን ፍሬ የማያፈራውን ቅርንጫፍ ሁሉ [አባቴ] ቆርጦ ይጥለዋል፤ ፍሬ የሚያፈራውን ቅርንጫፍ ሁሉ ደግሞ ይበልጥ እንዲያፈራ ያጠራዋል።” (ዮሐ. 15:2) በውኃ የተመሰለው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት እንዲያጠራህ ራስህን ባቀረብክ መጠን ይበልጥ ታፈራለህ።

አሁንም ሆነ ወደፊት የምናገኛቸው በረከቶች

19. የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በመከሩ ሥራ ባደረጉት ጥረት ምን በረከት አግኝተዋል?

19 የኢየሱስን ሥልጠና ተግባራዊ ላደረጉት ታማኝ ደቀ መዛሙርት በ33 ዓ.ም. በጴንጤቆስጤ ዕለት መንፈስ ቅዱስ ኃይል የሰጣቸው ሲሆን ይህም “እስከ ምድር ዳር ድረስ” ምሥክር እንዲሆኑ አስችሏቸዋል። (ሥራ 1:8) እነዚህ ደቀ መዛሙርት የበላይ አካል አባላት፣ ሚስዮናውያን እንዲሁም ተጓዥ ሽማግሌዎች ሆነው ያገለገሉ ከመሆኑም ሌላ ምሥራቹን “ከሰማይ በታች ባለ ፍጥረት ሁሉ” መካከል በመስበክ ረገድ ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል። (ቆላ. 1:23) በዚህም ብዙ በረከቶች ያጨዱ ሲሆን ለሌሎችም ታላቅ ደስታ ማምጣት ችለዋል!

20. (ሀ) በመንፈሳዊው የመከር ሥራ ሙሉ ተሳትፎ በማድረግህ ምን በረከቶች አግኝተሃል? (ለ) ምን ለማድረግ ቆርጠሃል?

20 አዎን፣ ትሕትና በማሳየትና በትጋት በመሥራት እንዲሁም በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን የላቁ መሥፈርቶች በመጠበቅ በአሁኑ ጊዜ እየተከናወነ ባለው ታላቅ መንፈሳዊ የመከር ሥራ የተሟላና ትርጉም ያለው ተሳትፎ ማድረጋችንን እንቀጥላለን። ብዙዎች ቁሳዊ ንብረትንና ተድላን በማሳደድ ላይ ያተኮረውን የዚህን ዓለም የአኗኗር ዘይቤ በመከተላቸው ለሥቃይና ለብስጭት የተዳረጉ ሲሆን እኛ ግን እውነተኛ ደስታና እርካታ አግኝተናል። (መዝ. 126:6) ከሁሉ በላይ ደግሞ “ከጌታ ጋር በተያያዘ በትጋት [የምናከናውነው] ሥራ ከንቱ አለመሆኑን” እናውቃለን። (1 ቆሮ. 15:58) የመከሩ ሥራ ጌታ የሆነው ይሖዋ አምላክ ‘ላከናወንነው ሥራ እንዲሁም ለስሙ ላሳየነው ፍቅር’ ለዘላለም ይባርከናል።—ዕብ. 6:10-12

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.8 ኢየሱስ ስለ ታላንት የተናገረው ታሪክ በዋነኝነት ከቅቡዓን ደቀ መዛሙርቱ ጋር ስላለው ግንኙነት የሚገልጽ ቢሆንም ለሁሉም ክርስቲያኖች የሚሆን መሠረታዊ ሥርዓት ይዟል።

ታስታውሳለህ?

በመከሩ ሥራ የተሟላ ተሳትፎ ለማድረግ ጥረት በምታደርግበት ጊዜ . . .

• ትሕትና ማሳየትህ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

• ትጋትን ማዳበርና ይህን ባሕርይ ይዘህ መቀጠል የምትችለው እንዴት ነው?

• በሥነ ምግባርና በመንፈሳዊ ንጹሕ ሆነህ መቀጠልህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ትሕትና ከመንግሥቱ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ቀላል ሕይወት እንድንመራ ይረዳናል