በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ንቁ መሆን ጥሩ ውጤት ያስገኛል

ንቁ መሆን ጥሩ ውጤት ያስገኛል

ንቁ መሆን ጥሩ ውጤት ያስገኛል

በጉባኤህ የአገልግሎት ክልል ውስጥ ሊፈጠሩ የሚችሉ ለስብከት የሚያመቹ አጋጣሚዎችን በንቃት ትከታተላለህ? ፊንላንድ ውስጥ ቱርኩ በተባለች ታሪካዊ የወደብ ከተማ የሚኖሩ ክርስቲያን ወንድሞቻችን እንደነዚህ ያሉ አጋጣሚዎችን በንቃት የሚከታተሉ ሲሆን ይህም ጥሩ ውጤት አስገኝቶላቸዋል።

ከተወሰነ ጊዜ በፊት፣ የአንድን ትልቅ መርከብ የማጠናቀቂያ ሥራ ለማከናወን የእስያ ተወላጅ የሆኑ ሰዎች ወደ ቱርኩ ከተማ እንደመጡ የአካባቢው ወንድሞች አስተዋሉ። ከዚያም አንድ ወንድም እነዚህ የውጭ አገር ሠራተኞች የት ሆቴል እንዳረፉ አወቀ። ከዚህም በተጨማሪ እነዚህ ሠራተኞች ማለዳ ላይ መሃል ከተማ ከሚገኘው ሆቴላቸው በአውቶቡስ ተሳፍረው ወደ ወደቡ እንደሚሄዱ ተመለከተ። ይህ ወንድም ሁኔታውን ወዲያውኑ በቱርኩ ባለው የእንግሊዝኛ ጉባኤ ውስጥ ላሉ ወንድሞች አሳወቀ።

በዚያ ጉባኤ ውስጥ ያሉት ሽማግሌዎች ይህን ያህል ብዛት ያላቸው የውጭ አገር ዜጎች ወደ አካባቢው መምጣታቸው ለእነዚህ ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት ለማካፈል ጥሩ አጋጣሚ እንደሚከፍት በመገንዘብ በፍጥነት ልዩ ዘመቻ አዘጋጁ። በዚያው ሳምንት እሁድ ዕለት አሥር አስፋፊዎች ጠዋት አንድ ሰዓት ላይ በአውቶቡስ መቆሚያው አካባቢ ተሰባሰቡ። መጀመሪያ ላይ ዝር ያለ አንድም ሠራተኛ አልነበረም። ወንድሞች ‘ዘግይተን ይሆን እንዴ?’ ብለው አሰቡ። ‘ቱርኩን ለቀው ሄደው ይሆን?’ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን ቱታ የለበሰ አንድ ሠራተኛ ብቅ አለ። ከዚያም አንድ ሁለት እያሉ ብዙ ሠራተኞች ተሰባሰቡ። ብዙም ሳይቆይ ሠራተኞቹ የአውቶቡስ ማቆሚያውን አጥለቀለቁት። አስፋፊዎቹ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተዘጋጁ ጽሑፎችን በመጠቀም ለሠራተኞቹ መስበክ ጀመሩ። ሁሉም ሠራተኞች በአውቶቡሶቹ ውስጥ ቦታ ቦታቸውን እስኪይዙ አንድ ሰዓት ያህል ወሰደባቸው፤ ይህ ደግሞ ወንድሞች አብዛኞቹን ለማነጋገር እንዲችሉ ጊዜ ሰጣቸው። አውቶቡሶቹ ሲንቀሳቀሱ ለሠራተኞቹ 126 ቡክሌቶች እና 329 መጽሔቶች ተበርክተውላቸው ነበር!

ወንድሞች ባገኙት ጥሩ ውጤት በመበረታታታቸው በቀጣዩ ሳምንት በወረዳ የበላይ ተመልካቹ ጉብኝት ወቅትም ሌላ ዘመቻ ለማካሄድ አሰቡ። ቀኑ ዝናባማ ቢሆንም ከማለዳው አሥራ ሁለት ሰዓት ተኩል ላይ የወረዳ የበላይ ተመልካቹ የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባውን ከመራ በኋላ 24 አስፋፊዎች አውቶቡሶቹ ወደሚቆሙበት ቦታ አመሩ። አስፋፊዎቹ፣ አብዛኞቹ የውጭ ዜጎች ከፊሊፒንስ የመጡ መሆናቸውን ተገንዝበው ስለነበር በዚህ ወቅት በተጋሎግ ቋንቋ የተዘጋጁ ጽሑፎችንም ይዘው ነበር። የዚያን ዕለት አውቶቡሶቹ ወደ ወደቡ ጉዞ ከመጀመራቸው በፊት ለሠራተኞቹ 7 መጻሕፍት፣ 69 ቡክሌቶችና 479 መጽሔቶች ተበረከቱላቸው። በዚህ ዘመቻ የተካፈሉት ወንድሞችና እህቶች ምን ያህል ደስታና እርካታ እንደተሰማቸው መገመት ትችላለህ!

ሠራተኞቹ ወደየአገራቸው ከመመለሳቸው በፊት ወንድሞች ሠራተኞቹ ወዳረፉበት ሆቴል በመሄድ ለአብዛኞቹ የመንግሥቱን መልእክት በስፋት አብራርተውላቸዋል። አንዳንዶቹ ሠራተኞች በሌሎች አገሮች ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር እንደተገናኙ ገልጸዋል። ሠራተኞቹ በፊንላንድ በቆዩበት ወቅት ወንድሞች እነሱን ለማነጋገር ጥረት በማድረጋቸው የተሰማቸውን አድናቆት ገልጸዋል።

አንተስ በጉባኤህ የአገልግሎት ክልል ውስጥ ሊፈጠሩ የሚችሉ አጋጣሚዎችን በንቃት ትከታተላለህ? የተለያየ ባሕል ላላቸው ሰዎች ምሥራቹን ለመስበክ ጥረት ታደርጋለህ? ከሆነ አንተም በቱርኩ እንዳሉት ወንድሞቻችን አስደሳች ተሞክሮ ልታገኝ ትችላለህ።

[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ ካርታ/ሥዕል]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ፊንላንድ

ሄልሲንኪ

ቱርኩ

[ምንጭ]

STX Europe