በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“አትፍራ፤ እረዳሃለሁ”

“አትፍራ፤ እረዳሃለሁ”

“አትፍራ፤ እረዳሃለሁ”

ኢየሱስ “ሙሉ በሙሉ እንድትፈተኑ . . . ዲያብሎስ አንዳንዶቻችሁን እስር ቤት መክተቱን ይቀጥላል” በማለት ተከታዮቹን አስጠንቅቋቸው ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ይህንን ማስጠንቀቂያ ከመስጠቱ በፊት “ሊደርስብህ ያለውን መከራ አትፍራ” ብሎ ነበር። ሰይጣን የመንግሥቱን ስብከት ሥራ ለማስቆም እስርን እንደ ማስፈራሪያ መጠቀሙን ስለቀጠለ አንዳንድ መንግሥታት በእውነተኛ ክርስቲያኖች ላይ ስደት ማድረሳቸው የማይቀር ሐቅ ነው። (ራእይ 2:10፤ 12:17) ታዲያ ሰይጣን የሚጠቀምባቸውን ዘዴዎች ለመቋቋም ዝግጁ እንድንሆን እንዲሁም ኢየሱስ እንደመከረን ‘እንዳንፈራ’ ምን ሊረዳን ይችላል?

እርግጥ ነው፣ አብዛኞቻችን የፍርሃት ስሜት ያደረብን ጊዜ ይኖራል። ያም ቢሆን በፍርሃት እንዳንሸነፍ ይሖዋ ሊረዳን እንደሚችል የአምላክ ቃል ማረጋገጫ ይሰጠናል። ይሖዋ የሚረዳን እንዴት ነው? ይሖዋ የሚደርስብንን ተቃውሞ ለመጋፈጥ ዝግጁዎች እንድንሆን እኛን ከሚረዳባቸው መንገዶች አንዱ ሰይጣንና ወኪሎቹ የሚጠቀሙባቸውን ዘዴዎች ለይተን እንድናውቅ በማድረግ ነው። (2 ቆሮ. 2:11) ይህን በምሳሌ ለመመልከት እንድንችል በጥንት ዘመን የተከናወነ አንድ ታሪክ እንመርምር። በዘመናችን “የዲያብሎስን መሠሪ ዘዴዎች መቋቋም” የቻሉ አንዳንድ ታማኝ የእምነት ባልንጀሮቻችን የተዉትንም ምሳሌ እንመለከታለን።—ኤፌ. 6:11-13

አንድ ክፉ መሪ ፈሪሃ አምላክ ያለውን ንጉሥ ተገዳደረው

በስምንተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ክፉ የነበረው የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም ብዙ አገሮችን በተከታታይ ድል ማድረግ ችሎ ነበር። ይህ ሁኔታ የልብ ልብ ስለሰጠው በይሖዋ ሕዝቦችና አምላክን ይፈራ የነበረው ንጉሥ ሕዝቅያስ በሚኖርባት በዋና ከተማዋ ኢየሩሳሌም ላይ ዓይኑን ጣለ። (2 ነገ. 18:1-3, 13) ሰይጣን፣ እውነተኛው አምልኮ ከምድረ ገጽ እንዲጠፋ የማድረግ እቅዱን ለማሳካት በሰናክሬም እየተጠቀመ እንደነበረ ምንም ጥርጥር የለውም።—ዘፍ. 3:15

ሰናክሬም፣ መልእክተኞችን ወደ ኢየሩሳሌም በመላክ ነዋሪዎቿ እጃቸውን እንዲሰጡ ጠየቀ። ከሰናክሬም መልእክተኞች መካከል የንጉሡ ዋና አፈ ቀላጤ የሆነው የጦር መሪው ይገኝበታል። * (2 ነገ. 18:17) የዚህ የጦር መሪ ዓላማ የአይሁዳውያንን ወኔ ማኮላሸትና ያለምንም ውጊያ እጃቸውን እንዲሰጡ ማድረግ ነበር። ታዲያ የአይሁዳውያንን ልብ በፍርሃት ለማራድ ምን ዘዴዎች ተጠቀመ?

የተገለሉ ቢሆንም ታማኝነታቸውን አላላሉም

የሰናክሬም የጦር መሪ የሕዝቅያስ ተወካዮችን እንዲህ አላቸው፦ “ታላቁ የአሦር ንጉሥ የሚለው ይህ ነው፤ ‘ለመሆኑ እንዲህ የልብ ልብ እንድታገኝ ያደረገህ ምንድነው? እነሆ፤ እንዲህ የምትመካባት ግብፅ፤ የሚደገፍባትን ሰው እጅ ወግታ የምታቈስል የተቀጠቀጠች ሸንበቆ ናት።’” (2 ነገ. 18:19, 21) የጦር መሪው ያቀረበው ክስ ሐሰት ነበር፤ ምክንያቱም ሕዝቅያስ ከግብፅ ጋር ሕብረት አልፈጠረም። ያም ቢሆን የጦር መሪው የሰነዘረው ክስ አይሁዳውያን እንዲገነዘቡት የፈለገውን ነጥብ የሚያጎላ ነበር፤ ‘ማንም አይደርስላችሁም። ብቻችሁን ስለሆናችሁ ምንም የምታመጡት ነገር የለም’ እንደማለት ነበር።

በቅርብ ዓመታት ውስጥ የእውነተኛው አምልኮ ተቃዋሚዎችም እውነተኛ ክርስቲያኖች ከሌሎች ተገልለው ለብቻቸው እንዲቀሩ በማድረግ እነሱን ለማስፈራራት ሞክረዋል። በእምነቷ ምክንያት ታስራና ከእምነት ባልንጀሮቿ ለበርካታ ዓመታት እንድትገለል ተደርጋ የነበረች አንዲት እህት በፍርሃት እንዳትሸነፍ የረዳት ምን እንደሆነ ከጊዜ በኋላ ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “ጸሎት ወደ ይሖዋ እንድቀርብ ረድቶኛል። . . . አምላክ ‘የተጎሳቆለውንና መንፈሱ የተሰበረውን’ እንደሚያይ የሚናገረውን በ⁠ኢሳይያስ 66:2 (NW) ላይ የሚገኘውን ማበረታቻ አስታውስ ነበር። ይህን ጥቅስ ሁልጊዜ ማስታወሴ የብርታት ምንጭ ሆኖልኛል፤ ይህ ነው የማይባል ማጽናኛም ሰጥቶኛል።” ለዓመታት ለብቻው ታስሮ የነበረ አንድ ወንድምም “ከአምላክ ጋር የቀረበ ዝምድና ያለው ሰው በአንዲት ጠባብ ክፍል ውስጥ መሆኑ ከይሖዋ ጋር ለመገናኘት እንደማያግደው ተገንዝቤያለሁ” ብሏል። አዎን፣ እነዚህ ሁለት ክርስቲያኖች ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና ስለነበራቸው ከሌሎች ተገልለው ብቻቸውን መታሰራቸው የፈጠረባቸውን ስሜት ለመቋቋም ችለዋል። (መዝ. 9:9, 10) ብቻቸውን የታሰሩት እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች፣ አሳዳጆቻቸው ከቤተሰቦቻቸው፣ ከወዳጆቻቸውና ከእምነት ባልንጀሮቻቸው ሊነጥሏቸው ቢችሉም ከይሖዋ ፈጽሞ ሊለዩዋቸው እንደማይችሉ ያውቁ ነበር።—ሮም 8:35-39

በመሆኑም ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ለማጠናከር ያገኘነውን እያንዳንዱን አጋጣሚ መጠቀማችን ምንኛ አስፈላጊ ነው! (ያዕ. 4:8) በየጊዜው ራሳችንን እንዲህ እያልን መጠየቅ ይኖርብናል፦ ‘ይሖዋ ለእኔ ምን ያህል እውን ነው? በዕለታዊ ሕይወቴ ቀላልም ሆነ ከበድ ያሉ ውሳኔዎችን በማደርግበት ጊዜ በአምላክ ቃል እመራለሁ?’ (ሉቃስ 16:10) ከአምላክ ጋር ያለንን የተቀራረበ ግንኙነት ጠብቀን ለመመላለስ ጥረት የምናደርግ እስከሆነ ድረስ የምንፈራበት ምንም ምክንያት የለም። ነቢዩ ኤርምያስ፣ በመከራ ውስጥ የነበሩትን አይሁዳውያን በመወከል እንዲህ ብሎ ነበር፦ “በጥልቁ ጕድጓድ ውስጥ ሳለሁ፣ . . . [“ይሖዋ ሆይ፣” NW]፤ የአንተን ስም ጠራሁ። . . . በጠራሁህ ጊዜ ቀረብኸኝ፣ እንዲሁም፣ ‘አትፍራ’ አልኸኝ።”—ሰቆ. 3:55-57

ጥርጣሬን ለመዝራት የተደረገው ጥረት አልተሳካም

የሰናክሬም የጦር መሪ በሕዝቡ ዘንድ ጥርጣሬ ለመዝራት ሲል ተንኮል የተሞላበት ሐሳብ አቀረበ። “አንተ [ሕዝቅያስ] የእግዚአብሔርን የተቀደሱ ስፍራዎችንና መሠዊያዎችን [ደምስሰሃል።] . . . እግዚአብሔር ራሱ በዚህች አገር ላይ አደጋ እንድጥልባትና እንድደመስሳት አዝዞኛል” አለ። (2 ነገ. 18:22, 25 የ1980 ትርጉም) የጦር መሪው ይህን ሲል ይሖዋ በሕዝቡ ስላዘነ ለእነሱ እንደማይዋጋ መግለጹ ነበር። ይሁንና ነገሩ የተገላቢጦሽ ነበር። ይሖዋ በሕዝቅያስና ወደ እውነተኛው አምልኮ በተመለሱት አይሁዳውያን ተደስቶ ነበር።—2 ነገ. 18:3-7

በዛሬው ጊዜም ተንኮለኛ የሆኑ ተቃዋሚዎች የሚናገሩት ሐሳብ ተቀባይነት እንዲያገኝ ሲሉ ጥቂቱን እውነት በሐሰት ሸፋፍነው ያቀርቡ ይሆናል፤ ይህን የሚያደርጉት በልባችን ውስጥ ጥርጣሬ ለመዝራት ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ወህኒ ቤት ያሉ ወንድሞችና እህቶች በአገራቸው ውስጥ በአመራር ቦታ ላይ ያለ አንድ ወንድም አቋሙን እንዳላላና እነሱም እምነታቸውን ቢተዉ ምንም ችግር እንደሌለው የተነገራቸው ጊዜያት አሉ። ይሁንና አስተዋይ የሆኑ ክርስቲያኖች እንደዚህ ያለው ሐሳብ ጥርጣሬ እንዲያሳድርባቸው አይፈቅዱም።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት አንዲት እህት ምን እንዳጋጠማት እንመልከት። እስር ቤት እያለች መርማሪው፣ በኃላፊነት ቦታ ላይ ያለ አንድ ወንድም እምነቱን እንደካደ የሚገልጽ በጽሑፍ የሰፈረ ሐሳብ አሳያት። ከዚያም መርማሪው በዚህ የይሖዋ ምሥክር ትተማመን እንደሆነ ጠየቃት። እህትም “[እሱ] እንደማንኛውም ሰው ፍጽምና የጎደለው ነው” በማለት መለሰችለት። አክላም ይህ ወንድም የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች እስከተከተለ ድረስ አምላክ ይጠቀምበት እንደነበር ገለጸች። “ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጋጭ ነገር ሲናገር ግን ወንድሜ መሆኑ ይቀራል” አለች። ይህች ታማኝ እህት “በገዦች አትታመኑ፤ ማዳን በማይችሉ ሥጋ ለባሾችም አትመኩ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በመከተል ጥበበኛ መሆኗን አሳይታለች።—መዝ. 146:3

የአምላክን ቃል ትክክለኛ እውቀት ማግኘታችንና ምክሩን ተግባራዊ ማድረጋችን ለመጽናት ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ በሚያዳክሙ አሳሳች ሐሳቦች እንዳንታለል ይጠብቀናል። (ኤፌ. 4:13, 14፤ ዕብ. 6:19) ተጽዕኖ በሚደረግብን ወቅት አጥርተን ማሰብ እንድንችል ራሳችንን ለማዘጋጀት ለግል ጥናትና በየዕለቱ ለሚደረግ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ቅድሚያ መስጠት ይኖርብናል። (ዕብ. 4:12) በእርግጥም እውቀታችን ጥልቀት ያለው እንዲሆንና እምነታችን እንዲጠናከር ለማድረግ ጊዜው አሁን ነው። ለበርካታ ዓመታት ብቻውን ቢታሰርም የጸና አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ሁሉም ሰው ለሚቀርብልን መንፈሳዊ ምግብ በሙሉ አድናቆት ቢያዳብር ደስ ይለኛል፤ ምክንያቱም ይህ ምግብ በሆነ ወቅት ላይ እንዴት እንደሚጠቅመን አናውቅም።” የአምላክን ቃልና በዛሬው ጊዜ በታማኝና ልባም ባሪያ አማካኝነት የሚቀርቡልንን ጽሑፎች በጥንቃቄ የምናጠና ከሆነ በሕይወታችን ውስጥ ከባድ ፈተና ሲያጋጥመን መንፈስ ቅዱስ የተማርናቸውን ነገሮች ‘እንድናስታውስ ያደርገናል።’—ዮሐ. 14:26

ዛቻ ቢሰነዘርባቸውም ጥበቃ አግኝተዋል

የሰናክሬም የጦር መሪ አይሁዳውያንን ለማስፈራራት ሲል እንዲህ አለ፦ “ከሆነልህ ከጌታዬ ከአሦር ንጉሥ ጋር ውርርድ ግጠም፤ የሚጋልቧቸው ሰዎች ማግኘት የምትችል ከሆነ፣ ሁለት ሺህ ፈረሶች እሰጥሃለሁ። የምትመካው በግብፅ ሠረገሎችና ፈረሶች ሆኖ ሳለ ከጌታዬ የበታች የጦር ሹማምንት እንኳ አንዱን እንዴት መመለስ ትችላለህ?” (2 ነገ. 18:23, 24) ከሰው አንጻር ካየነው ሕዝቅያስና ሕዝቡ ኃያሉን የአሦር ሠራዊት መቋቋም የሚችሉበት መንገድ አልነበረም።

በዛሬው ጊዜ ያሉ አሳዳጆቻችንም በተለይ የመንግሥት ሙሉ ድጋፍ ካላቸው እጅግ ኃያል መስለው ይታዩ ይሆናል። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የነበሩት የናዚ ደጋፊ የሆኑ አሳዳጆች ሁኔታ ከዚህ ጋር ይመሳሰላል። በርካታ የአምላክ አገልጋዮችን ለማስፈራራት ሞክረው ነበር። በወህኒ ቤት ብዙ ዓመታት ያሳለፈ አንድ ወንድማችን ምን ዓይነት ማስፈራሪያ እንደደረሰበት ከጊዜ በኋላ ተናግሯል። በአንድ ወቅት አንድ ባለሥልጣን “ወንድምህ በጥይት እንደተገደለ አይተሃል አይደል? ከዚህ ያገኘኸው ትምህርት አለ?” አለው። ወንድም “እኔ ምሥክር የሆንኩት ለይሖዋ ነው፤ ይህን አቋሜንም ፈጽሞ አልለውጥም” በማለት መለሰ። ባለሥልጣኑም “እንግዲያው አንተም የወንድምህ እጣ ይደርስሃል” በማለት ዛተበት። ያም ቢሆን ወንድማችን በአቋሙ የጸና ሲሆን ጠላቶቹም ማስፈራራታቸውን ተዉት። ይህ ወንድም እንዲህ ያለውን ዛቻ እንዲቋቋም የረዳው ምንድን ነው? “በይሖዋ ስም ላይ እምነት ነበረኝ” ብሏል።—ምሳሌ 18:10

በይሖዋ ላይ ሙሉ እምነት ካለን ሰይጣን እኛን በመንፈሳዊ ለመጉዳት ከሚጠቀምባቸው ነገሮች በሙሉ ሊከላከልልን የሚችል ትልቅ ጋሻ የያዝን ያህል ነው። (ኤፌ. 6:16) በመሆኑም እምነታችንን እንዲያጠናክርልን ይሖዋን በጸሎት መጠየቃችን በጣም አስፈላጊ ነው። (ሉቃስ 17:5) በተጨማሪም እምነታችንን ለማጠናከር በሚያስችሉን ታማኝና ልባም ባሪያ ባደረጋቸው ዝግጅቶች ጥሩ አድርገን መጠቀም ይኖርብናል። ማስፈራሪያ በሚሰነዘርብን ወቅት ልበ ደንዳና ለሆኑ ሕዝቦች ይሰብክ ለነበረው ለነቢዩ ሕዝቅኤል ይሖዋ የሰጠውን ማረጋገጫ ማስታወሳችን ያጠነክረናል። እንዲህ ብሎት ነበር፦ “እኔ በእነርሱ ፊት የማትበገር ጠንካራ አደርግሃለሁ። ግንባርህን ከባልጩት ይልቅ እንደሚጠነክር ድንጋይ አደርገዋለሁ።” (ሕዝ. 3:8, 9) አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ይሖዋ ለሕዝቅኤል እንዳደረገው እኛንም እንደ ባልጩት ሊያጠነክረን ይችላል።

ፈተናን መቋቋም

ተቃዋሚዎች የአንድን ሰው አቋም ለማላላት የሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች ሁሉ ካልሠሩላቸው አንዳንድ ጊዜ የሚያጓጓ ግብዣ በማቅረብ ግለሰቡ ታማኝነቱን እንዲያጎድል ማድረግ እንደሚቻል ያውቃሉ። የሰናክሬም የጦር መሪም ይህን ዘዴ ተጠቅሟል። ለኢየሩሳሌም ነዋሪዎች እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “የአሦር ንጉሥ የሚለው ይህ ነው፤ ‘ከእኔ ጋር ሰላም መሥርቱ፤ እጃችሁን ስጡ፤ . . . ይህም የሚሆነው የእናንተኑ ወደ ምትመስለው ምድር እህልና የወይን ጠጅ፣ ዳቦና የወይን ተክል፣ የወይራ ዛፍና ማር ወዳለበት እስካገባችሁ ድረስ ነው፤ እናንተም ሞትን ሳይሆን ሕይወትን ምረጡ።’” (2 ነገ. 18:31, 32) በተከበበችው ከተማ ውስጥ ያለው የአይሁድ ሕዝብ መውጣት መግባት ስለማይችል ትኩስ ዳቦ የመብላትና አዲስ የወይን ጠጅ የመጠጣት ሐሳብ በጣም ሳያጓጓው አልቀረም!

ወህኒ ቤት የነበረ አንድ ሚስዮናዊ አቋሙን እንዲያላላ ለማድረግ እንዲህ ያለ ግብዣ ቀርቦለት ነበር። በደንብ ማሰብ እንዲችል ለስድስት ወር ያህል የሚያምር የአትክልት ቦታ ወዳለበት ቆንጆ ቤት እንደሚዛወር ተነገረው። ወንድም ግን በመንፈሳዊ ንቁ ሆኖ የቀጠለ ሲሆን ክርስቲያናዊ አቋሙን አላላላም። ይህን እንዲያደርግ የረዳው ምንድን ነው? ከጊዜ በኋላ እንዲህ ብሏል፦ “የመንግሥቱ ተስፋ ለእኔ ሕያው ነበር። . . . ስለ አምላክ መንግሥት ያለኝ እውቀት እምነቴን ያጠናከረው ከመሆኑም ሌላ መንግሥቱ እውን መሆኑን እርግጠኛ መሆኔና ይህን ለቅጽበትም እንኳ አለመጠራጠሬ በአቋሜ እንድጸና ረድቶኛል።”

የአምላክ መንግሥት ለእኛ ምን ያህል እውን ነው? አብርሃም፣ ሐዋርያው ጳውሎስና ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት እውን ስለሆነላቸው ከባድ ፈተናዎችን መቋቋም ችለዋል። (ፊልጵ. 3:13, 14፤ ዕብ. 11:8-10፤ 12:2) እኛም በሕይወታችን ውስጥ መንግሥቱን የምናስቀድምና የሚያመጣቸውን ዘላቂ በረከቶች ሁልጊዜ በአእምሯችን የምናስብ ከሆነ ከመከራ በመገላገል ጊዜያዊ እፎይታ እንድናገኝ የሚቀርብልንን ፈተና መቋቋም እንችላለን።—2 ቆሮ. 4:16-18

ይሖዋ ፈጽሞ አይተወንም

የሰናክሬም የጦር መሪ አይሁዳውያንን ለማስፈራራት ምንም ዓይነት ጥረት ቢያደርግም ሕዝቅያስና ሕዝቡ በይሖዋ ላይ የማይናወጥ እምነት ነበራቸው። (2 ነገ. 19:15, 19፤ ኢሳ. 37:5-7) ይሖዋም በምላሹ አንድ መልአክ ልኮ በአንድ ሌሊት ብቻ በአሦራውያን የጦር ሰፈር የነበሩትን 185,000 ወታደሮች በመግደል ለጸሎታቸው መልስ ሰጥቷቸዋል። የኀፍረት ማቅ የተከናነበው ሰናክሬም በማግሥቱ ከሠራዊቱ መሃል ከተረፉት ጥቂት ሰዎች ጋር በመሆን ወደ ዋና ከተማው ወደ ነነዌ እግሬ አውጪኝ አለ።—2 ነገ. 19:35, 36

በግልጽ ለመመልከት እንደሚቻለው ይሖዋ በእሱ የታመኑትን አልተዋቸውም። መከራ ሲያጋጥማቸው የጸኑ በዘመናችን የሚገኙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ምሳሌ እንደሚያሳየው ይሖዋ ዛሬም አልተለወጠም። በሰማይ የሚገኘው አባታችን “እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ‘አትፍራ፤ እረዳሃለሁ’ ብዬ ቀኝ እጅህን እይዛለሁና” የሚል ማረጋገጫ የሰጠን መሆኑ በእርግጥም የተገባ ነው።—ኢሳ 41:13

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.6 አንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሶች ይህን ግለሰብ “ራፋስቂስ” ብለው ይጠሩታል። ይህ መጠሪያ ከፍተኛ ቦታ ላለው የአሦር ባለሥልጣን የሚሰጥ የማዕረግ ስም ነው። የዚህ ባለሥልጣን የግል ስም በዘገባው ላይ አልተጠቀሰም።

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ይሖዋ ራሱ አገልጋዮቹ ‘እንዳይፈሩ’ ያበረታታባቸው ከ30 የሚበልጡ ሐሳቦች በቃሉ ውስጥ ይገኛሉ

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሰናክሬም የጦር መሪ የተጠቀመባቸው ዘዴዎች በዛሬው ጊዜ ያሉ የአምላክ ሕዝቦች ጠላቶች ከሚጠቀሙባቸው ጋር የሚመሳሰሉት እንዴት ነው?

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከይሖዋ ጋር የቀረበ ዝምድና መመሥረት በፈተና ወቅት በአቋማችን ለመጽናት ይረዳናል