በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ቀን ምን ይገልጣል?

የይሖዋ ቀን ምን ይገልጣል?

የይሖዋ ቀን ምን ይገልጣል?

“የይሖዋ ቀን እንደ ሌባ ይመጣል፤ . . . ምድርና በላይዋ የተሠሩ ነገሮችም ይጋለጣሉ።”—2 ጴጥ. 3:10

1, 2. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ያለው ክፉ ሥርዓት ወደ ፍጻሜው የሚመጣው እንዴት ነው? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

በዛሬ ጊዜ ያለው ክፉ ሥርዓት፣ ሰዎች ያለ ይሖዋ እርዳታ ምድርን በተሳካ ሁኔታ ማስተዳደር ይችላሉ በሚለው ውሸት ላይ የተመሠረተ ነው። (መዝ. 2:2, 3) ታዲያ በውሸት ላይ የተመሠረተ ነገር ሊጸና ይችላል? በፍጹም! ያም ቢሆን የሰይጣን ዓለም በራሱ እስኪጠፋ መጠበቅ አያስፈልገንም። አምላክ እሱ በወሰነው ጊዜና በራሱ መንገድ ይህን ሥርዓት ያጠፋዋል። አምላክ በዚህ ክፉ ዓለም ላይ የሚወስደው እርምጃ የእሱን ፍትሕና ፍቅር ፍጹም በሆነ መልኩ የሚያንጸባርቅ ይሆናል።—መዝ. 92:7፤ ምሳሌ 2:21, 22

2 ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የይሖዋ ቀን እንደ ሌባ ይመጣል፤ በዚያም ቀን ሰማያት በነጎድጓድ ድምፅ በቅጽበት ያልፋሉ፤ ሰማያትና ምድር የተሠሩባቸው ንጥረ ነገሮችም በኃይለኛ ሙቀት ይቀልጣሉ፤ ምድርና በላይዋ የተሠሩ ነገሮችም ይጋለጣሉ።” (2 ጴጥ. 3:10) እዚህ ላይ “ሰማያት” እና “ምድር” የተባሉት ምንድን ናቸው? የሚቀልጡት “ንጥረ ነገሮች” ምንድን ናቸው? ጴጥሮስ “ምድርና በላይዋ የተሠሩ ነገሮችም ይጋለጣሉ” ሲል ምን ማለቱ ነበር? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ማወቃችን በቅርቡ ለሚመጣው አስፈሪ ክስተት ራሳችንን እንድናዘጋጅ ይረዳናል።

የሚያልፉት ሰማያትና ምድር

3. በ⁠2 ጴጥሮስ 3:10 ላይ የተጠቀሱት “ሰማያት” ምንድን ናቸው? የሚያልፉትስ እንዴት ነው?

3 “ሰማያት” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ሲሠራበት በአብዛኛው የሚያመለክተው ከተገዥዎቻቸው በላይ ከፍ ብለው ያሉትን ገዥዎች ነው። (ኢሳ. 14:13, 14፤ ራእይ 21:1, 2) ‘የሚያልፉት ሰማያት’ ፈሪሃ አምላክ በሌለው ኅብረተሰብ ላይ የሚገዙትን ሰብዓዊ መንግሥታት የሚወክሉ ናቸው። እነዚህ ሰማያት “በነጎድጓድ ድምፅ” ወይም በሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም መሠረት “በታላቅ ድምፅ” የሚያልፉ መሆናቸው ጥፋታቸው ቅጽበታዊ እንደሚሆን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።

4. “ምድር” የሚለው ቃል የሚያመለክተው ምንድን ነው? የሚጠፋውስ እንዴት ነው?

4 “ምድር” የሚለው ቃል ከአምላክ የራቀውን የሰው ዘር ዓለም ይወክላል። በኖኅ ዘመን እንዲህ ያለ ዓለም ነበረ፤ ይህ ዓለም አምላክ ስለፈረደበት በውኃ ጠፍቷል። “በዚያው ቃል አሁን ያሉት ሰማያትም ሆኑ ምድር ለእሳትና ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎች ለሚጠፉበት የፍርድ ቀን ተጠብቀው ይቆያሉ።” (2 ጴጥ. 3:7) የጥፋት ውኃው ፈሪሃ አምላክ የሌላቸውን ሰዎች በሙሉ ጠራርጎ ያስወገዳቸው በአንድ ጊዜ ሲሆን ወደፊት ‘በታላቁ መከራ’ ወቅት የሚመጣው ጥፋት ግን የሚከሰተው ደረጃ በደረጃ ይሆናል። (ራእይ 7:14) በመጀመሪያ አምላክ፣ በዚህ ዓለም የፖለቲካ ገዥዎች በመጠቀም ‘ታላቂቱ ባቢሎንን’ ያጠፋታል፤ ለዚህች ሃይማኖታዊ ጋለሞታ ያለውን ጥላቻ በዚህ መንገድ ያሳያል። (ራእይ 17:5, 16፤ 18:8) ቀጥሎም በአርማጌዶን ጦርነት ይሖዋ ራሱ የተቀረውን የሰይጣን ዓለም ጠራርጎ ሲያጠፋው ታላቁ መከራ ይደመደማል።—ራእይ 16:14, 16፤ 19:19-21

‘ንጥረ ነገሮቹ ይቀልጣሉ’

5. “ንጥረ ነገሮች” የሚለው ምሳሌያዊ አነጋገር ምን ያመለክታል?

5 “ይቀልጣሉ” የተባሉት “ንጥረ ነገሮች” ምንድን ናቸው? አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት “ንጥረ ነገሮች” የሚለውን ሐረግ “መነሻ የሆኑ ነገሮች” ወይም “መሠረታዊ ነገሮች” በማለት ይፈታዋል። ይህ ሐረግ “የንግግር ንጥረ ነገር የሆኑትን ፊደላትን” ለማመልከት እንደተሠራበት መዝገበ ቃላቱ ይናገራል። በመሆኑም ጴጥሮስ የጠቀሳቸው “ንጥረ ነገሮች” ይህ ዓለም አምላካዊ ያልሆነ ባሕርይ፣ ዝንባሌ፣ አካሄድና ግብ እንዲኖረው ያደረጉትን መሠረታዊ ነገሮች ያመለክታሉ። እነዚህ “ንጥረ ነገሮች” “በማይታዘዙት ልጆች ላይ አሁን እየሠራ” ያለውን “የዓለምን መንፈስ” ይጨምራሉ። (1 ቆሮ. 2:12፤ ኤፌሶን 2:1-3ን አንብብ።) ይህ መንፈስ ወይም ‘አየር’ የሰይጣንን ዓለም ሞልቶታል። ይህ መንፈስ፣ ሰዎች ትዕቢተኛና ዓመፀኛ የሆነውን “የአየሩ ሥልጣን ገዥ” ይኸውም የሰይጣንን አመለካከት በሚያንጸባርቅ መንገድ እንዲያስቡ፣ እቅድ እንዲያወጡ፣ እንዲናገሩና እንዲያደርጉ ያነሳሳቸዋል።

6. የዓለም መንፈስ የሚገለጸው በምን መንገድ ነው?

6 የዓለም መንፈስ ተጽዕኖ ያደረገባቸው ሰዎች፣ አውቀውትም ይሁን ሳያውቁት ሰይጣን አእምሯቸውንና ልባቸውን እንዲቀርጸው ስለሚፈቅዱ የእሱን አስተሳሰብና አመለካከት ያንጸባርቃሉ። በዚህም የተነሳ የአምላክን ፈቃድ ችላ በማለት የፈለጉትን ያደርጋሉ። ለሚያጋጥሟቸው ሁኔታዎች ምላሽ የሚሰጡት ኩራት ወይም ራስ ወዳድነት በሚንጸባረቅበት መንገድ ነው፤ እንዲሁም በሥልጣን ላይ የማመፅ ዝንባሌ ያላቸው ከመሆኑም ሌላ ‘ለሥጋ ምኞትና ለዓይን አምሮት’ ያደሩ ናቸው።—1 ዮሐንስ 2:15-17ን አንብብ። *

7. ‘ልባችንን መጠበቅ’ ያለብን ለምንድን ነው?

7 እንግዲያው ከጓደኛ ምርጫ፣ ከምናነባቸው ነገሮች፣ ከመዝናኛ እንዲሁም ኢንተርኔት ላይ ከምንመለከታቸው ድረ ገጾች ጋር በተያያዘ ከአምላክ ቃል በተማርነው መሠረት ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ በማድረግ ‘ልባችንን መጠበቃችን’ ምንኛ አስፈላጊ ነው! (ምሳሌ 4:23) ሐዋርያው ጳውሎስ “በክርስቶስ ላይ ሳይሆን በዓለም መሠረታዊ ነገሮች እንዲሁም በሰው ወግ ላይ በተመሠረተ ፍልስፍናና ከንቱ ማታለያ ማንም አጥምዶ እንዳይወስዳችሁ ተጠንቀቁ” በማለት ጽፏል። (ቆላ. 2:8) የይሖዋ ቀን እየቀረበ በመሆኑ ይህን መመሪያ መከተላችን ይበልጥ አጣዳፊ ይሆናል፤ ምክንያቱም ይህ ቀን የሰይጣንን ሥርዓት “ንጥረ ነገሮች” በሙሉ በኃይለኛ ሙቀት በማቅለጥ የአምላክን ቁጣ ትኩሳት መቋቋም የማይችሉ መሆናቸውን ያጋልጣል። ይህም በ⁠ሚልክያስ 4:1 ላይ የሚገኘውን የሚከተለውን ጥቅስ ያስታውሰናል፦ “እንደ ምድጃ እሳት የሚነድ ቀን ይመጣል፤ ትዕቢተኞች ሁሉና ክፉ አድራጊዎች በሙሉ ገለባ ይሆናሉ፤ ያ የሚመጣው ቀንም ያቃጥላቸዋል።”

“ምድርና በላይዋ የተሠሩ ነገሮችም ይጋለጣሉ”

8. ምድርና በላይዋ የተሠሩ ነገሮች ‘የሚጋለጡት’ እንዴት ነው?

8 ጴጥሮስ “ምድርና በላይዋ የተሠሩ ነገሮችም ይጋለጣሉ” በማለት ሲጽፍ ምን ማለቱ ነበር? የሰይጣን ዓለም ይሖዋንና መንግሥቱን ስለሚቃወም ጥፋት የሚገባው መሆኑን አምላክ በታላቁ መከራ ወቅት እንደሚያጋልጥ መግለጹ ነበር። ይህንን ጊዜ በተመለከተ በ⁠ኢሳይያስ 26:21 ላይ እንዲህ የሚል ትንቢት ተነግሯል፦ “በምድር ላይ የሚኖረውን ሕዝብ ስለ ኀጢአቱ ለመቅጣት፣ እነሆ፤ እግዚአብሔር ከመኖሪያው ወጥቶ ይመጣል፤ ምድር በላይዋ የፈሰሰውን ደም ትገልጣለች፤ የተገደሉትንም ከእንግዲህ አትሸሽግም።”

9. (ሀ) ምን ነገሮችን ማስወገድ ይኖርብናል? ለምንስ? (ለ) የትኞቹን ባሕርያት ማዳበር ይኖርብናል? ለምንስ?

9 ዓለምና ክፉ የሆነው የዓለም መንፈስ ተጽዕኖ ያሳደረባቸው ሰዎች በይሖዋ ቀን እርስ በርስ በመገዳደል ጭምር እውነተኛ ማንነታቸውን ይገልጣሉ። እንዲያውም በዛሬው ጊዜ በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ የሆኑት ዓመፅ የሞላባቸው በርካታ መዝናኛዎች የብዙዎችን አእምሮ በመቅረጽ ‘አንዱ ሌላውን ለሚወጋበት’ ለዚያ ቀን እያዘጋጇቸው ያሉ ይመስላል። (ዘካ. 14:13) እንግዲያው አምላክ የሚጠላቸውን እንደ ኩራትና ዓመፅን መውደድ ያሉ ዝንባሌዎች እንድናዳብር ሊያደርጉን የሚችሉ ፊልሞችን፣ መጻሕፍትን፣ የቪዲዮ ጨዋታዎችንና እንደነዚህ ያሉ ሌሎች ነገሮችን በሙሉ ማስወገዳችን ምንኛ አስፈላጊ ነው! (2 ሳሙ. 22:28፤ መዝ. 11:5) ከዚህ በተቃራኒ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ፍሬ የሆኑትን ባሕርያት እናዳብር፤ ምክንያቱም እነዚህ ባሕርያት በይሖዋ ቀን የሚኖረውን ምሳሌያዊ ትኩሳት መቋቋም ይችላሉ።—ገላ. 5:22, 23

“አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር”

10, 11. “አዲስ ሰማያት” እና “አዲስ ምድር” የሚሉት አገላለጾች ምን ያመለክታሉ?

10 ሁለተኛ ጴጥሮስ 3:13ን አንብብ። “አዲስ ሰማያት” የሚለው አገላለጽ በሰማይ ያለውን የአምላክ መንግሥት የሚያመለክት ሲሆን ይህ መንግሥት የተቋቋመው “የተወሰኑት የአሕዛብ ዘመናት” በ1914 በተፈጸሙበት ወቅት ነው። (ሉቃስ 21:24) በንጉሥ የሚተዳደረው ይህ መንግሥት በክርስቶስ ኢየሱስና አብረውት በሚገዙት 144,000 ሰዎች የተዋቀረ ሲሆን ከእነዚህ ተባባሪ ገዥዎች አብዛኛዎቹ በአሁኑ ጊዜ ሰማያዊ ሽልማታቸውን አግኝተዋል። ዮሐንስ እነዚህን የተመረጡ ሰዎች በራእይ መጽሐፍ ላይ በሚከተለው መንገድ ገልጿቸዋል፦ “ቅድስቲቱ ከተማ፣ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ከሰማይ ከአምላክ ዘንድ ስትወርድ አየሁ፤ እሷም ለባሏ እንዳጌጠች ሙሽራ ተዘጋጅታ ነበር።” (ራእይ 21:1, 2, 22-24) ምድራዊቷ ኢየሩሳሌም ለጥንቱ የእስራኤል መንግሥት መቀመጫ እንደነበረች ሁሉ አዲሲቱ ኢየሩሳሌምና ባሏ በአዲሱ ሥርዓት ውስጥ የሚኖረውን መንግሥት ያስገኛሉ። ይህች ሰማያዊት ከተማ ‘ከሰማይ ትወርዳለች’ ሲባል ትኩረቷን ወደ ምድር ታዞራለች ማለት ነው።

11 “አዲስ ምድር” የሚለው አገላለጽ ለአምላክ መንግሥት ለመገዛት ፈቃደኛ መሆኑን የሚያሳይ በምድር ላይ የሚኖር አዲስ ሰብዓዊ ኅብረተሰብን ያመለክታል። የአምላክ ሕዝቦች በአሁኑ ጊዜም እንኳ በመንፈሳዊ ገነት ውስጥ ተደስተው የሚኖሩ ሲሆን ይህ ገነት ውብ በሆነው ‘መጪው ዓለም’ ፍጹም ወደሆነ ሁኔታ ይሻገራል። (ዕብ. 2:5) ታዲያ የዚህ አዲስ ሥርዓት ክፍል መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

ለይሖዋ ታላቅ ቀን ተዘጋጁ

12. የይሖዋ ቀን ለዓለም ዱብ እዳ የሚሆንበት ለምንድን ነው?

12 ጳውሎስም ሆነ ጴጥሮስ የይሖዋ ቀን የሚመጣው “እንደ ሌባ” ይኸውም ሳይታሰብ በድንገት እንደሆነ አስቀድመው ተናግረዋል። (1 ተሰሎንቄ 5:1, 2ን አንብብ።) ይህን ቀን ለሚጠብቁ እውነተኛ ክርስቲያኖች እንኳ ቀኑ ድንገተኛ ይሆናል። (ማቴ. 24:44) ለዚህ ዓለም ግን ቀኑ ድንገተኛ ከመሆን ባለፈ የሚያስከትለው ነገር አለ። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “[ከይሖዋ የራቁ ሰዎች] ‘ሰላምና ደኅንነት ሆነ!’ ሲሉ የምጥ ጣር እርጉዝ ሴትን እንደሚይዛት ያልታሰበ ጥፋት ድንገት ይመጣባቸዋል፤ ደግሞም በምንም ዓይነት አያመልጡም።”—1 ተሰ. 5:3

13. “ሰላምና ደኅንነት ሆነ!” የሚለው ልፈፋ እንዳያታልለን መጠንቀቅ የምንችለው እንዴት ነው?

13 “ሰላምና ደኅንነት ሆነ!” የሚለው ልፈፋ አጋንንት የሚያሰራጩት ሌላ ውሸት ከመሆን ያለፈ የሚያመጣው ለውጥ የለም፤ የአምላክ አገልጋዮች ግን እንዲህ ባለው ውሸት አይሞኙም። ጳውሎስ “በጨለማ ውስጥ ስላልሆናችሁ ሌሊቱ ድንገት እንደሚነጋበት ሌባ ያ ቀን ድንገት አይደርስባችሁም፤ ምክንያቱም እናንተ ሁላችሁ የብርሃን ልጆችና የቀን ልጆች ናችሁ” በማለት ጽፏል። (1 ተሰ. 5:4, 5) በመሆኑም በጨለማ ከተዋጠው የሰይጣን ዓለም በመራቅ በብርሃን ውስጥ እንመላለስ። ጴጥሮስ እንደሚከተለው በማለት ጽፏል፦ “የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ ይህን አስቀድማችሁ ስላወቃችሁ ሕግ የሚተላለፉ ሰዎች [ማለትም በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉ ሐሰተኛ አስተማሪዎች] በሚፈጽሙት ስህተት ከእነሱ ጋር ተታልላችሁ እንዳትወሰዱና ከጽኑ አቋማችሁ እንዳትወድቁ ተጠንቀቁ።”—2 ጴጥ. 3:17

14, 15. (ሀ) ይሖዋ ያከበረን እንዴት ነው? (ለ) በመንፈስ መሪነት የተጻፉትን የትኞቹን ማሳሰቢያዎች በቁም ነገር ልንመለከት ይገባል?

14 ይሖዋ ‘እንድንጠነቀቅ’ በመንገር ብቻ አልተወንም። ከዚህ ይልቅ ወደፊት ስለሚሆነው ነገር መሠረታዊ ነገሮችን ‘አስቀድመን እንድናውቅ’ በማድረግ አክብሮናል።

15 የሚያሳዝነው ግን አንዳንዶች ንቁ የመሆንን አስፈላጊነት በተመለከተ ለሚሰጡት ማሳሰቢያዎች ደንታ ቢስ ከመሆናቸውም በላይ ማስጠንቀቂያውን መስማት ሰልችቷቸዋል። ‘ይህን ማሳሰቢያ ለአሥርተ ዓመታት ስንሰማ ኖረናል’ በማለት ይናገሩ ይሆናል። ይሁንና እነዚህ ግለሰቦች እንዲህ ያለውን አስተያየት መሰንዘራቸው ታማኝና ልባም ባሪያን ብቻ ሳይሆን ይሖዋንና ልጁንም ጭምር እንደሚጠራጠሩ የሚያሳይ መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል። ይሖዋ ያንን ቀን ‘እንድንጠብቀው’ አዞናል። (ዕን. 2:3) ኢየሱስም በተመሳሳይ “ጌታችሁ በየትኛው ቀን እንደሚመጣ ስለማታውቁ ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ” ብሏል። (ማቴ. 24:42) ከዚህም በላይ ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ቅዱስ ሥነ ምግባር በመከተልና ለአምላክ ያደራችሁ መሆናችሁን የሚያሳዩ ተግባሮች በመፈጸም ምን ዓይነት ሰዎች መሆን እንዳለባችሁ ልታስቡበት ይገባል! . . . የይሖዋን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና በአእምሯችሁ አቅርባችሁ እየተመለከታችሁ ልትኖሩ ይገባል!” (2 ጴጥ. 3:11, 12) ታማኝና ልባም ባሪያም ሆነ የበላይ አካሉ እነዚህን ማሳሰቢያዎች ፈጽሞ አቅልለው አይመለከቷቸውም!

16. የትኛውን አመለካከት ልናስወግድ ይገባል? ለምንስ?

16 ‘ክፉው ባሪያ’ ግን ጌታው እንደሚዘገይ ይሰማዋል። (ማቴ. 24:48) ይህ ክፉ ባሪያ በ2 ጴጥሮስ 3:3, 4 ላይ የተጠቀሱት ሰዎች ዓይነት አመለካከት አለው። ጴጥሮስ የይሖዋን ቀን በአእምሯቸው አቅርበው በሚመለከቱ ታዛዥ ሰዎች ላይ የሚዘብቱና “የራሳቸውን ምኞት” የሚከተሉ “ፌዘኞች” “በመጨረሻው ዘመን” እንደሚመጡ ጽፎ ነበር። እነዚህ ፌዘኞች በመንግሥቱ ጉዳዮች ላይ ሳይሆን በራሳቸውና ራስ ወዳድነት በሚንጸባረቅበት ምኞታቸው ላይ ያተኩራሉ። እንዲህ ያለውን አደገኛ የሆነ የዓመፀኝነት መንፈስ ፈጽሞ እንዳናዳብር እንጠንቀቅ! ከዚህ ይልቅ ስለ አምላክ መንግሥት በመስበኩና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ራሳችንን በማስጠመድ እንዲሁም ይሖዋ አምላክ ስለወሰነው ጊዜ ከልክ በላይ ባለመጨነቅ “የጌታችንን ትዕግሥት እንደ መዳን” እንደምንቆጥረው እናሳይ።—2 ጴጥ. 3:15፤ የሐዋርያት ሥራ 1:6, 7ን አንብብ።

አዳኝ በሆነው አምላክ ታመኑ

17. ታማኝ የሆኑ ክርስቲያኖች ኢየሱስ ከኢየሩሳሌም እንዲሸሹ ለሰጣቸው ምክር ምን ምላሽ ሰጡ? ለምንስ?

17 የሮም ሠራዊት በ66 ዓ.ም. ይሁዳን ከወረረ በኋላ ታማኝ የሆኑት ክርስቲያኖች ኢየሱስ የሰጣቸውን ምክር በመስማት ባገኙት አጋጣሚ ተጠቅመው ከኢየሩሳሌም ከተማ ወጡ። (ሉቃስ 21:20-23) እነዚህ ክርስቲያኖች ምንም ሳያመነቱ በፍጥነት እርምጃ የወሰዱት ለምን ነበር? የኢየሱስን ማስጠንቀቂያ ሁልጊዜ ያስቡት እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። ክርስቶስ አስቀድሞ ባስጠነቀቃቸው መሠረት እንዲህ ያለ ውሳኔ ማድረጋቸው አስቸጋሪ ሁኔታዎችን እንደሚያስከትልባቸው አውቀው መሆን አለበት። በሌላ በኩል ደግሞ ይሖዋ ታማኞቹን በፍጹም እንደማይጥል ያውቁ ነበር።—መዝ. 55:22

18. በ⁠ሉቃስ 21:25-28 ላይ የሚገኙት የኢየሱስ ቃላት ስለ መጪው ታላቅ መከራ ያለህን አመለካከት የሚነኩት እንዴት ነው?

18 በታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ታላቅ መከራ በዚህ ሥርዓት ላይ በሚመጣበት ወቅት ሊያድነን የሚችለው ይሖዋ ብቻ በመሆኑ በእሱ ላይ ሙሉ በሙሉ መታመን አለብን። ታላቁ መከራ ከጀመረ ብዙም ሳይቆይ ሆኖም ይሖዋ በቀረው ዓለም ላይ የፍርድ እርምጃ ከመውሰዱ በፊት “ሰዎች ከፍርሃትና በዓለም ላይ የሚመጡትን ነገሮች ከመጠበቅ የተነሳ ይዝለፈለፋሉ።” የአምላክ ጠላቶች በፍርሃት ሲርዱ የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች ግን ምንም ስጋት አያድርባቸውም። እንዲያውም መዳናቸው እየቀረበ መሆኑን ስለሚያውቁ ደስ ይላቸዋል።—ሉቃስ 21:25-28ን አንብብ።

19. በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የትኛውን ነጥብ እንመረምራለን?

19 ከዓለምና ‘ከንጥረ ነገሮቹ’ የተለዩ ሆነው የሚኖሩ ሰዎች እንዴት ያለ አስደሳች ተስፋ ይጠብቃቸዋል! ይሁን እንጂ የሚቀጥለው ርዕስ እንደሚያብራራው ሕይወት ማግኘት ከፈለግን ክፋትን በማስወገድ ብቻ መወሰን የለብንም። ይሖዋን የሚያስደስቱ ባሕርያትን ማዳበርና በእሱ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውን ሥራዎች ማከናወን ይኖርብናል።—2 ጴጥ. 3:11

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.6 የዓለም መንፈስ የሚገለጽባቸውን መንገዶች በተመለከተ የተሟላ ማብራሪያ ለማግኘት ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 388-391 ተመልከት።

ልታብራራ ትችላለህ?

• አሁን ያሉት ‘ሰማያትና ምድር’ ምን ያመለክታሉ?

• “ንጥረ ነገሮች” ሲባል ምን ማለት ነው?

• ‘አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር’ ምን ያመለክታሉ?

• በአምላክ ላይ ሙሉ በሙሉ መታመን ያለብን ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

‘ልብህን መጠበቅና’ ከዓለም መለየት የምትችለው እንዴት ነው?

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

‘የጌታችንን ትዕግሥት እንደ መዳን እንደምንቆጥረው’ እንዴት ማሳየት እንችላለን?