በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቤዛው የሚያድነን እንዴት ነው?

ቤዛው የሚያድነን እንዴት ነው?

ቤዛው የሚያድነን እንዴት ነው?

“በወልድ እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ የዘላለም ሕይወት አለው፤ ወልድን የማይታዘዝ ግን የአምላክ ቁጣ በላዩ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም።”—ዮሐ. 3:36

1, 2. የጽዮን መጠበቂያ ግንብ መታተም እንዲጀምር ምክንያት ከሆኑት ነገሮች አንዱ ምንድን ነው?

“መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት የሚያጠና ማንኛውም ሰው የክርስቶስ ሞት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ መገንዘቡ አይቀርም።” ይህ ሐሳብ የወጣው ጥቅምት 1879 በታተመው የዚህ መጽሔት አራተኛ እትም ላይ ነበር። ርዕሱ በመደምደሚያው ላይ የሚከተለውን በቁም ነገር ሊታሰብበት የሚገባ ሐሳብ ይዞ ነበር፦ “ክርስቶስ መሥዋዕት ሆኖ መቅረቡንና ሞቱ ለኃጢአት ማስተሰረያ መሆኑን የሚያቃልል ወይም እንዳልተቀበልነው የሚያሳይ ምንም ነገር እንዳናደርግ እንጠንቀቅ።”—1 ዮሐንስ 2:1, 2ን አንብብ።

2 የጽዮን መጠበቂያ ግንብ ለመጀመሪያ ጊዜ ሐምሌ 1879 እንዲታተም ምክንያት ከሆኑት ነገሮች አንዱ መጽሐፍ ቅዱስ ቤዛውን በተመለከተ ለሚያስተምረው ትምህርት ጥብቅና መቆም ነበር። በ1800ዎቹ መገባደጃ አካባቢ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች የኢየሱስ ሞት ለኃጢአታችን ቤዛ ሊሆን መቻሉን መጠራጠር በመጀመራቸው በመጽሔቱ ላይ የወጣው ትምህርት ‘በተገቢው ጊዜ የቀረበ ምግብ’ ነበር። (ማቴ. 24:45) በወቅቱ ብዙዎች፣ የሰው ልጅ ፍጽምናውን እንዳጣ ከሚገልጸው ሐቅ ጋር የሚጋጨውን የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ መቀበል ጀምረው ነበር። የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ አራማጆች ሰው በራሱ እየተሻሻለ የሚሄድ ስለሆነ ቤዛ አያስፈልገውም ብለው ያስተምራሉ። ከዚህ አንጻር ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በሰጠው ምክር ላይ ትኩረት ማድረጋችን የተገባ ነው፦ “ቅዱስ የሆነውን ነገር ከሚጻረሩ ከንቱ ንግግሮችና በውሸት ‘እውቀት’ ተብለው ከሚጠሩ እርስ በርሳቸው ከሚቃረኑ ሐሳቦች በመራቅ በአደራ የተሰጠህን ነገር ጠብቅ። ምክንያቱም አንዳንዶች እንዲህ ዓይነቱ እውቀት እንዲታይላቸው ለማድረግ ሲጣጣሩ ከእምነት ጎዳና ወጥተዋል።”—1 ጢሞ. 6:20, 21

3. ከዚህ በመቀጠል የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

3 አንተ ‘ከእምነት ጎዳና ላለመውጣት’ ቁርጥ ውሳኔ እንዳደረግህ ምንም ጥርጥር የለውም። እምነትህ ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል ከፈለግህ የሚከተሉትን ጥያቄዎች መመርመርህ ተገቢ ነው፦ ቤዛ ያስፈለገኝ ለምንድን ነው? ቤዛውን ለማዘጋጀት ምን መሥዋዕትነት መክፈል አስፈልጓል? ከአምላክ ቁጣ ሊያድነኝ ከሚችለው ከዚህ ውድ ዝግጅት ጥቅም ማግኘት የምችለው እንዴት ነው?

ከአምላክ ቁጣ መዳን

4, 5. አምላክ በዚህ ክፉ ሥርዓት ላይ አሁንም ድረስ እንደተቆጣ የሚያሳየው ምንድን ነው?

4 መጽሐፍ ቅዱስና የሰው ዘር ታሪክ እንደሚያሳየው አዳም በኃጢአት ከወደቀበት ጊዜ አንስቶ የአምላክ ቁጣ በሰው ልጆች ላይ ነው። (ዮሐ. 3:36) ይዋል ይደር እንጂ ማንኛውም ሰው ከሞት ማምለጥ አለመቻሉ ይህ እውነት መሆኑን ያሳያል። የአምላክ ተቀናቃኝ የሆነው የሰይጣን አገዛዝ የሰው ልጆችን ከሚደርስባቸው ማቆሚያ የሌለው መከራ ፈጽሞ ሊታደጋቸው አልቻለም፤ እንዲሁም የሁሉንም ዜጎቹን መሠረታዊ ፍላጎት ማሟላት የቻለ አንድም ሰብዓዊ መንግሥት የለም። (1 ዮሐ. 5:19) በመሆኑም የሰው ልጅ ከጦርነት፣ ከወንጀልና ከድህነት መላቀቅ አልቻለም።

5 ከዚህ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ይህ ክፉ ሥርዓት የይሖዋ በረከት ርቆታል። ጳውሎስ ‘አምላክን የሚጻረር ድርጊት በሚፈጽሙ ላይ የአምላክ ቁጣ ከሰማይ እንደሚገለጥ’ ተናግሯል። (ሮም 1:18-20) ስለዚህ አምላክን የሚያሳዝን ጎዳና የሚከተሉና ንስሐ የማይገቡ ሰዎች በሙሉ አካሄዳቸው ከሚያስከትለው መዘዝ አያመልጡም። በዛሬው ጊዜ፣ በሰይጣን ዓለም ላይ ልክ እንደ መቅሰፍት እየፈሰሱ ባሉት የፍርድ መልእክቶች አማካኝነት የአምላክ ቁጣ እየተገለጠ ነው፤ እነዚህ የፍርድ መልእክቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመሠረቱ በርካታ ጽሑፎቻችን ላይ ወጥተዋል።—ራእይ 16:1

6, 7. ቅቡዓን ክርስቲያኖች የትኛውን ሥራ በግንባር ቀደምትነት እያከናወኑ ነው? የሰይጣን ዓለም ክፍል የሆኑ ሰዎች አሁንም ምን አጋጣሚ ተከፍቶላቸዋል?

6 ይህ ሲባል ታዲያ ሰዎች ከሰይጣን አገዛዝ ነፃ ወጥተው ከአምላክ ጋር እርቅ ለመፍጠር ጊዜው አልፎባቸዋል ማለት ነው? አይደለም፣ አንድ ሰው ከአምላክ ጋር እርቅ ለመፍጠር ከፈለገ አሁንም በሩ ክፍት ነው። ‘ክርስቶስን ተክተው የሚሠሩ አምባሳደሮች’ የሆኑት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ግንባር ቀደም ሆነው በሚያከናውኑት የስብከት ሥራ አማካኝነት በሁሉም ብሔራት ውስጥ የሚገኙ ሰዎች “ከአምላክ ጋር ታረቁ” የሚል ግብዣ እየቀረበላቸው ነው።—2 ቆሮ. 5:20, 21

7 ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ኢየሱስ “ከሚመጣው ቁጣ የሚያድነን” መሆኑን ተናግሯል። (1 ተሰ. 1:10) ይሖዋ ቁጣውን ለመጨረሻ ጊዜ በሚገልጥበት በዚያ ወቅት ንስሐ ያልገቡ ኃጢአተኞች ለዘላለም ይጠፋሉ። (2 ተሰ. 1:6-9) ታዲያ ከዚህ ቁጣ የሚያመልጡት እነማን ናቸው? መጽሐፍ ቅዱስ “በወልድ እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ የዘላለም ሕይወት አለው፤ ወልድን የማይታዘዝ ግን የአምላክ ቁጣ በላዩ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም” ይላል። (ዮሐ. 3:36) አዎን፣ የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ በሚመጣበት ጊዜ በሕይወት የሚኖሩ ሁሉ በኢየሱስ ብሎም በቤዛው ላይ እምነት እንዳላቸው በተግባር እስካሳዩ ድረስ መጨረሻ ከሚመጣው የአምላክ የቁጣ ቀን ይተርፋሉ።

ቤዛው ጥቅም የሚያስገኘው እንዴት ነው?

8. (ሀ) አዳምና ሔዋን ምን ግሩም ተስፋ ከፊታቸው ተዘርግቶላቸው ነበር? (ለ) ይሖዋ ፍትሑ ፍጹም እንደሆነ ያሳየው እንዴት ነው?

8 አዳምና ሔዋን የተፈጠሩት ፍጹም ሆነው ነው። ለአምላክ ታዛዥ ሆነው ቢቀጥሉ ኖሮ በአሁኑ ጊዜ ምድር ደስተኛ በሆኑ ዘሮቻቸው ትሞላ የነበረ ከመሆኑም በላይ እነሱም በገነት ውስጥ ከልጆቻቸው ጋር ሊኖሩ ይችሉ ነበር። የሚያሳዝነው ግን የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ሆን ብለው የአምላክን ትእዛዝ ጣሱ። በውጤቱም ዘላለማዊ ሞት የተፈረደባቸው ከመሆኑም በላይ ከገነት ተባረሩ። አዳምና ሔዋን ልጆች በወለዱበት ወቅት የሰው ዘር በኃጢአት ተጽዕኖ ሥር ወድቆ የነበረ ሲሆን የመጀመሪያዎቹ ወንድና ሴትም ከጊዜ በኋላ አርጅተው ሞቱ። ይህም ይሖዋ የተናገረው ነገር እውነት መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው። ከዚህም በላይ የአምላክ ፍትሕ ፍጹም መሆኑን ያሳያል። ይሖዋ አዳምን ከተከለከለው ፍሬ ከበላ እንደሚሞት አስጠንቅቆት ነበር፤ የሆነውም ይኸው ነው።

9, 10. (ሀ) የአዳም ዘሮች የሚሞቱት ለምንድን ነው? (ለ) ከዘላለማዊ ሞት ማምለጥ የምንችለው እንዴት ነው?

9 የአዳም ዘሮች እንደመሆናችን መጠን በወረስነው አለፍጽምና ምክንያት ኃጢአት የመሥራት ዝንባሌ አለን፤ ይዋል ይደር እንጂ መሞታችንም አይቀርም። አዳም ኃጢአት በሠራበት ወቅት በእሱ አብራክ ውስጥ የነበርን ያህል ነው። ስለዚህ በእሱ ላይ የተበየነው የሞት ፍርድ እኛንም ይጨምራል። ይሖዋ ቤዛ ሳይከፈል እርጅናና ሞት እንዲቀር ቢያደርግ ቃል አባይ ይሆናል። ጳውሎስ እንደሚከተለው ብሎ የተናገረው ሐሳብ ሁላችንም ያለንበትን ሁኔታ የሚገልጽ ነው፦ “ሕጉ መንፈሳዊ እንደሆነ እናውቃለን፤ እኔ ግን ለኃጢአት የተሸጥኩ ሥጋዊ ነኝ። እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ! እንዲህ ወዳለው ሞት ከሚመራኝ ሰውነት ማን ይታደገኛል?”—ሮም 7:14, 24

10 ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ኃጢአታችንን ይቅር ለማለትና እኛን ከዘላለማዊ ሞት ቅጣት ነፃ ለማውጣት የሚያስችል ሕጋዊ መንገድ ማዘጋጀት የሚችለው ይሖዋ አምላክ ብቻ ነው። ይሖዋ ይህን ያደረገው የሚወደውን ልጁን ፍጹም ሰው ሆኖ እንዲወለድ ከሰማይ ወደ ምድር በመላክ ነው፤ ፍጹም ሰው ሆኖ የተወለደው የአምላክ ልጅ ሕይወቱን ለእኛ ቤዛ አድርጎ መስጠት ይችላል። ከአዳም በተለየ መልኩ ኢየሱስ ፍጽምናውን ጠብቆ ኖሯል። “ምንም ኃጢአት አልሠራም።” (1 ጴጥ. 2:22) በመሆኑም ኢየሱስ ፍጹማን የሆኑ ልጆችን መውለድ ይችል ነበር። እሱ ግን ኃጢአተኛ የሆኑትን የአዳም ዘሮች እንደ ልጆቹ አድርጎ ለመውሰድና በእሱ ላይ እምነት እንዳላቸው በተግባር የሚያሳዩ ሁሉ የዘላለም ሕይወት ማግኘት የሚችሉበትን መንገድ ለመክፈት ሲል በአምላክ ጠላቶች እጅ ለመሞት ፈቃደኛ ሆኗል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “አንድ አምላክ አለ፤ በአምላክና በሰው መካከል ደግሞ አንድ አስታራቂ አለ፤ እሱም ሰው የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤ ራሱን ለሁሉ ተመጣጣኝ ቤዛ አድርጎ የሰጠው እሱ ነው።”—1 ጢሞ. 2:5, 6

11. (ሀ) ቤዛው እንዴት እንደሚጠቅመን በምሳሌ ማስረዳት የሚቻለው እንዴት ነው? (ለ) እነማን እንኳ ከቤዛው ጥቅም ያገኛሉ?

11 ቤዛው የሚጠቅመን እንዴት እንደሆነ ለመረዳት እንድንችል በባንክ ያጠራቀሙትን ገንዘብ የተጭበረበሩና በዚህም ምክንያት ዕዳ ውስጥ የተዘፈቁ ሰዎችን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። የባንኩ ባለንብረቶች ሰዎቹን በማጭበርበራቸው ለረጅም ዓመታት እንዲታሰሩ ተፈረደባቸው፤ ይህ በእርግጥም ተገቢ ቅጣት ነው። ይሁንና ገንዘባቸውን የተጭበረበሩት ሰዎችስ ምን ይውጣቸዋል? ንብረታቸውን በማጣታቸው ለችግር የተጋለጡት እነዚህ ሰዎች አንድ ደግ የሆነ ሀብታም ሰው ባንኩን ተረክቦ ሰዎቹ ያጡትን ገንዘብ በሙሉ መልሶ በመስጠት ከዕዳቸው ነፃ ካላወጣቸው በቀር ካሉበት ሁኔታ የሚወጡበት ምንም መንገድ አይኖርም። በተመሳሳይም ይሖዋ አምላክና የሚወደው ልጁ የአዳምን ዘሮች በመዋጀት ያለባቸውን የኃጢአት ዕዳ በፈሰሰው የኢየሱስ ደም አማካኝነት ሰርዘውላቸዋል። አጥማቂው ዮሐንስ ስለ ኢየሱስ ሲናገር “የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግደው የአምላክ በግ ይኸውላችሁ!” ለማለት የቻለው ለዚህ ነው። (ዮሐ. 1:29) ኃጢአቱ እንደሚወገድለት የተነገረለት ዓለም በሕይወት ያሉትን ብቻ ሳይሆን የሞቱትንም ሰዎች ይጨምራል።

ቤዛው ምን ያህል መሥዋዕትነት ተከፍሎበታል?

12, 13. አብርሃም ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ ለማቅረብ ፈቃደኛ መሆኑ ምን ያስተምረናል?

12 በሰማይ ያለው አባታችንና የሚወደው ልጁ ቤዛውን ለማዘጋጀት ምን ያህል መሥዋዕትነት እንደከፈሉ ሙሉ በሙሉ መረዳት ለእኛ አስቸጋሪ ነው። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ለማሰላሰል የሚረዱንን ታሪኮች ይዟል። ለምሳሌ፣ አብርሃም የአምላክን ትእዛዝ በማክበር ወደ ሞሪያ ተራራ የሦስት ቀን ጉዞ ባደረገበት ወቅት ምን ተሰምቶት ሊሆን እንደሚችል ለማሰብ ሞክር፤ አምላክ እንዲህ ሲል አዞት ነበር፦ “የምትወደውን አንዱን ልጅህን፣ ይስሐቅን ይዘህ ወደ ሞሪያ ምድር ሂድ፤ እኔ በማመለክትህ በአንዱ ተራራ ላይ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገህ ሠዋው።”—ዘፍ. 22:2-4

13 በመጨረሻም አብርሃም ይሖዋ ወዳሳየው ቦታ ደረሰ። አብርሃም የይስሐቅን እጅና እግር በማሰር ራሱ በሠራው መሠዊያ ላይ ሲያጋድመው ምን ያህል ተጨንቆ ሊሆን እንደሚችል አስብ። ልጁን ለማረድ ቢላውን ሲያነሳ መንፈሱ በጣም እንደሚረበሽ የታወቀ ነው! በመሠዊያው ላይ የተጋደመው ይስሐቅም ቢላው ሲያርፍበት የሚሰማውን ኃይለኛ ሥቃይ እያሰበ ሞቱን ሲጠባበቅ ይታይህ። ሆኖም አብርሃም ይህን እርምጃ ከመውሰዱ በፊት የይሖዋ መልአክ አስቆመው። አብርሃምና ይስሐቅ በዚያ ወቅት ያደረጉት ነገር ይሖዋ የሰይጣን ወኪሎች ልጁን እንዲገድሉት ሲፈቅድ ምን ያህል መሥዋዕትነት እንደከፈለ ለመረዳት ያስችለናል። ይስሐቅ ከአብርሃም ጋር መተባበሩ ኢየሱስ ለእኛ ሲል ለመሠቃየትና ለመሞት ፈቃደኛ መሆኑን በደንብ እንድንረዳ ያስችለናል።—ዕብ. 11:17-19

14. ቤዛው ምን ያህል መሥዋዕትነት እንደጠየቀ ለመረዳት የሚያስችለን ያዕቆብ በሕይወቱ ውስጥ ያጋጠመው የትኛው ሁኔታ ነው?

14 ያዕቆብ በሕይወቱ ውስጥ ያጋጠመው አንድ ሁኔታም ቤዛው ምን ያህል መሥዋዕትነት እንደጠየቀ ለመረዳት ያስችለናል። ያዕቆብ ካሉት ልጆች ሁሉ አብልጦ የሚወደው ዮሴፍን ነበር። የሚያሳዝነው ግን የዮሴፍ ወንድሞች በእሱ ይቀኑበት የነበረ ከመሆኑም በላይ ይጠሉት ነበር። ያም ሆኖ ዮሴፍ የወንድሞቹን ሁኔታ ለማወቅ አባቱ ሲልከው ለመሄድ ፈቃደኛ ነበር። በወቅቱ ወንድሞቹ በኬብሮን ከሚገኘው ቤታቸው በስተሰሜን 100 ኪሎ ሜትር ርቀው የአባታቸውን መንጋ እየጠበቁ ነበር። የያዕቆብ ልጆች በደም የተሸፈነውን የዮሴፍን ልብስ ይዘው ሲመጡ ያዕቆብ ምን ተሰምቶት እንደሚሆን እስቲ አስበው! ያዕቆብ “ይህማ የልጄ እጀ ጠባብ ነው!፤ ክፉ አውሬ በልቶታል፣ በእርግጥም ዮሴፍ ተቦጫጭቈአል” አለ። ሁኔታው በያዕቆብ ላይ ከፍተኛ ሥቃይ አስከትሎበት ስለነበር ለብዙ ቀናት ለልጁ አለቀሰ። (ዘፍ. 37:33, 34) ይሖዋ እሱን የሚያሳዝኑት ሁኔታዎች ሲፈጸሙ ስሜቱን የሚገልጸው ፍጽምና እንደጎደላቸው የሰው ልጆች አይደለም። ያም ሆኖ በያዕቆብ ሕይወት ውስጥ በተከናወነው በዚህ ታሪክ ላይ ማሰላሰላችን አምላክ የሚወደው ልጁ በምድር ላይ እንግልት ሲደርስበትና ጭካኔ በተሞላበት መንገድ ሲገደል ምን ተሰምቶት ሊሆን እንደሚችል በተወሰነ መጠን ለመረዳት ያስችለናል።

ከቤዛው ጥቅም ማግኘት

15, 16. (ሀ) ይሖዋ ቤዛውን እንደተቀበለ ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ከቤዛው ጥቅም ያገኘኸው እንዴት ነው?

15 ይሖዋ አምላክ ታማኝ የሆነውን ልጁን ክብር የተላበሰ መንፈሳዊ አካል አድርጎ ከሞት አስነስቶታል። (1 ጴጥ. 3:18) ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ለ40 ቀናት ለደቀ መዛሙርቱ በመገለጥ እምነታቸውን ያጠናከረላቸው ሲሆን ወደፊት ለሚጠብቃቸው ታላቅ የወንጌላዊነት ሥራም አዘጋጅቷቸዋል። ከዚያም ኢየሱስ በቤዛዊ መሥዋዕቱ ላይ እምነት እንዳላቸው በተግባር ላሳዩ እውነተኛ ተከታዮቹ ያፈሰሰውን የደሙን ዋጋ ወደ ሰማይ በመሄድ ለአምላክ አቀረበ። ይሖዋ አምላክ በ33 ዓ.ም. በጴንጤቆስጤ ዕለት በኢየሩሳሌም ተሰብስበው በነበሩት ደቀ መዛሙርት ላይ መንፈስ ቅዱስን እንዲያፈስ ለኢየሱስ ኃላፊነት በመስጠት የክርስቶስን ቤዛ እንደተቀበለው አሳይቷል።—ሥራ 2:33

16 ወዲያውኑ እነዚህ ቅቡዓን የክርስቶስ ተከታዮች፣ ሰዎች ለኃጢአታቸው ይቅርታ እንዲያገኙ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በመጠመቅ ከአምላክ ቁጣ እንዲያመልጡ ማሳሰብ ጀመሩ። (የሐዋርያት ሥራ 2:38-40ን አንብብ።) ከዚህ ታሪካዊ ዕለት አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ እምነት በማሳደራቸው አምላክ ከእሱ ጋር ዝምድና መመሥረት እንዲችሉ ወደ ራሱ ስቧቸዋል። (ዮሐ. 6:44) አሁን ደግሞ እስቲ ሌሎች ሁለት ጥያቄዎችን እንመርምር፦ ማንኛችንም ብንሆን የዘላለም ሕይወት ተስፋ ያገኘነው በራሳችን መልካም ሥራ ነው? ይህንን አስደናቂ ተስፋ አንዴ ካገኘን በኋላ ልናጣው እንችላለን?

17. የአምላክ ወዳጅ የመሆን ውድ መብትህን እንዴት ልትመለከተው ይገባል?

17 ቤዛው በራሳችን መልካም ሥራ ያገኘነው ነገር ሳይሆን የአምላክ ጸጋ መግለጫ ነው። ሆኖም በዛሬው ጊዜ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በቤዛው ላይ እምነት እንዳላቸው በተግባር በማሳየታቸው የአምላክ ወዳጆች መሆን ከመቻላቸውም በላይ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ አግኝተዋል። ይሁን እንጂ የይሖዋ ወዳጆች መሆናችን ይህን ወዳጅነት ምንጊዜም እንደማናጣው ማረጋገጫ አይሆንም። ወደፊት ከሚመጣው የአምላክ ቁጣ ለማምለጥ ‘ክርስቶስ ኢየሱስ ለከፈለው ቤዛ’ ልባዊ አድናቆት ማሳየታችንን መቀጠል ይኖርብናል።—ሮም 3:24፤ ፊልጵስዩስ 2:12ን አንብብ።

በቤዛው ላይ እምነት ማሳደራችሁን ቀጥሉ

18. በቤዛው ላይ እምነት እንዳለን በተግባር ማሳየት ምንን ይጨምራል?

18 ይህ የጥናት ርዕስ በተመሠረተበት በ⁠ዮሐንስ 3:36 ላይ የሚገኘው ጥቅስ በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እምነት እንዳለን በተግባር ማሳየት ለእሱ መታዘዝን እንደሚጨምር ይጠቁማል። ለቤዛው ያለን አድናቆት ኢየሱስ ሥነ ምግባርን ጨምሮ ካስተማራቸው ትምህርቶች ጋር በሚስማማ መንገድ እንድንኖር ሊያነሳሳን ይገባል። (ማር. 7:21-23) ዝሙት በሚፈጽሙ፣ ጸያፍ ቀልድ በሚናገሩ እንዲሁም የብልግና ምስሎችን የመመልከት ልማድን ጨምሮ ‘ማንኛውንም ዓይነት ርኩሰት’ በሚፈጽሙና ንስሐ በማይገቡ ሁሉ ላይ “የአምላክ ቁጣ” ይመጣል።—ኤፌ. 5:3-6

19. በቤዛው ላይ እምነት እንዳለን በየትኞቹ መንገዶች ማሳየት እንችላለን?

19 ለቤዛው ያለን አድናቆት ‘ለአምላክ ያደርን መሆናችንን በሚያሳዩ ተግባሮች’ እንድንጠመድ ሊያነሳሳን ይገባል። (2 ጴጥ. 3:11) ዘወትር ልባዊ ጸሎት ለማቅረብ፣ የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና የቤተሰብ አምልኮ ለማድረግ፣ በስብሰባ ላይ ለመገኘት እንዲሁም በመንግሥቱ የስብከት ሥራ በቅንዓት ለመካፈል የሚያስችል በቂ ጊዜ እንመድብ። ከዚህም በተጨማሪ “መልካም ማድረግንና ያላችሁን ነገር ለሌሎች ማካፈልን አትርሱ፤ ምክንያቱም አምላክ እንዲህ ባሉት መሥዋዕቶች እጅግ ይደሰታል” የሚለውን ምክር ተግባራዊ እናድርግ።—ዕብ. 13:15, 16

20. በቤዛው ላይ እምነት እንዳላቸው በተግባር ማሳየታቸውን የሚቀጥሉ ሁሉ ወደፊት ምን በረከት እንደሚያገኙ መጠበቅ ይችላሉ?

20 የይሖዋ ቁጣ በዚህ ክፉ ሥርዓት ላይ በሚወርድበት ጊዜ፣ በቤዛው ላይ እምነት እንዳለንና ቤዛውን ምንጊዜም እንደምናደንቀው በማሳየታችን በጣም እንደምንደሰት ምንም ጥርጥር የለውም! አምላክ ቃል በገባልን አዲስ ዓለም ውስጥ በምንኖርበት ጊዜ ደግሞ ከአምላክ ቁጣ እንድንድን ምክንያት ለሆነን ለዚህ ግሩም ዝግጅት ለዘላለም አመስጋኝ እንሆናለን።—ዮሐንስ 3:16ን እና ራእይ 7:9, 10, 13, 14ን አንብብ።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ቤዛው የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

• ቤዛው ምን ያህል መሥዋዕትነት ተከፍሎበታል?

• ቤዛው ምን ጥቅሞች ያስገኛል?

• በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ እምነት እንዳለን በተግባር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከአምላክ ጋር እርቅ ለመፍጠር በሩ ክፍት ነው

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ በሕይወታቸው ውስጥ ባጋጠሟቸው ነገሮች ላይ ማሰላሰላችን ቤዛው ምን ያህል ታላቅ መሥዋዕትነት እንደተከፈለበት ለመገንዘብ ይረዳናል