በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስ የአምላክ ጽድቅ ጎልቶ እንዲታይ ያደረገው እንዴት ነው?

ኢየሱስ የአምላክ ጽድቅ ጎልቶ እንዲታይ ያደረገው እንዴት ነው?

ኢየሱስ የአምላክ ጽድቅ ጎልቶ እንዲታይ ያደረገው እንዴት ነው?

“በኢየሱስ ደም የሚያምኑ ሁሉ ማስተሰረያ ያገኙ ዘንድ አምላክ እሱን መሥዋዕት አድርጎ አቅርቦታል። አምላክ ይህን ያደረገው . . . የራሱን ጽድቅ ለማሳየት ነው።”—ሮም 3:25

1, 2. (ሀ) የሰው ልጆች ስላሉበት ሁኔታ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምራል? (ለ) በዚህ የጥናት ርዕስ ውስጥ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

በኤደን ገነት ስለተካሄደው ዓመፅ የሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ በብዙዎች ዘንድ የሚታወቅ ነው። የአዳም ኃጢአት ያስከተለውን ውጤት ሁላችንም የቀመስነው ሲሆን ጳውሎስ ሁኔታውን እንዲህ ሲል ገልጾታል፦ “በአንድ ሰው አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ፤ ሁሉም ኃጢአት ስለሠሩም ሞት ለሰው ሁሉ ተዳረሰ።” (ሮም 5:12) ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ ምንም ያህል ብንጥር ስህተት መሥራታችን አይቀርም፤ በመሆኑም የአምላክን ይቅርታ ማግኘት ያስፈልገናል። ሐዋርያው ጳውሎስም እንኳ እንዲህ በማለት በምሬት ተናግሯል፦ “የምመኘውን መልካም ነገር አላደርግምና፤ የማልፈልገውን መጥፎ ነገር የማድረግ ልማድ ግን አለኝ። እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ!”—ሮም 7:19, 24

2 በዚህ የጥናት ርዕስ ላይ የሚከተሉትን አስፈላጊ ጥያቄዎች እንመለከታለን፦ ሁላችንም ኃጢአተኞች ሆነን ሳለ የናዝሬቱ ኢየሱስ ከአዳም ኃጢአት ነፃ ሆኖ ሊወለድ የቻለው እንዴት ነው? የተጠመቀው ለምንድን ነው? ኢየሱስ ያሳለፈው ሕይወት የይሖዋን ጽድቅ ያጎላው እንዴት ነው? ከሁሉ በላይ ደግሞ የክርስቶስ ሞት ያከናወነው ነገር ምንድን ነው?

የአምላክ ጽድቅ ጥያቄ ላይ ወደቀ

3. ሰይጣን ሔዋንን ያታለላት እንዴት ነው?

3 የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን አዳምና ሔዋን፣ የአምላክን ሉዓላዊነት ለመቀበል አሻፈረን ብለው “ዲያብሎስና ሰይጣን ተብሎ የሚጠራው የመጀመሪያው እባብ” እንዲገዛቸው መምረጣቸው ሞኝነት ነበር። (ራእይ 12:9) ይህን ያደረጉት እንዴት እንደሆነ እንመልከት። ሰይጣን የይሖዋ አምላክ አገዛዝ ጽድቅ የሰፈነበት መሆኑን በተመለከተ ጥያቄ አስነሳ። ይህን ያደረገው “በእርግጥ እግዚአብሔር፣ ‘በአትክልቱ ስፍራ ካሉ ዛፎች ከማናቸውም እንዳትበሉ’ ብሎአልን?” ብሎ ሔዋንን በመጠየቅ ነበር። ሔዋንም ከዛፎቹ መካከል አንደኛውን መንካት እንደሌለባቸው አለበለዚያ ግን እንደሚሞቱ አምላክ የሰጣቸውን ግልጽ ትእዛዝ ነገረችው። በዚህ ጊዜ ሰይጣን “መሞት እንኳ አትሞቱም” በማለት አምላክ የተናገረው ነገር ውሸት እንደሆነ ገለጸ። ሔዋን አምላክ አንድ የደበቃቸው መልካም ነገር እንዳለ እንዲሰማት በማድረግ ሰይጣን አታለላት፤ ፍሬውን ብትበላ እንደ አምላክ እንደምትሆን ብሎም መልካምና ክፉ የሆነውን ነገር በራሷ መወሰን እንደምትችል እንድታስብ አደረጋት።—ዘፍ. 3:1-5

4. የሰው ዘር የአምላክ ተቀናቃኝ በሆነው በሰይጣን አገዛዝ ሥር የወደቀው እንዴት ነው?

4 ሰይጣን ያቀረበው ሐሳብ ጠቅለል ተደርጎ ሲታይ የሰው ልጆች ከአምላክ ርቀው በራሳቸው ቢመሩ ይበልጥ ደስተኞች እንደሚሆኑ የሚጠቁም ነበር። አዳም የአምላክ አገዛዝ ጽድቅ የሰፈነበት መሆኑን ከመደገፍ ይልቅ ሚስቱን በመስማት እሱም ከተከለከለው ፍሬ በላ። አዳም ይህን ሲያደርግ በይሖዋ ዘንድ የነበረውን የጽድቅ አቋም ያጣ ከመሆኑም ሌላ በኃጢአትና በሞት የጭቆና ቀንበር ሥር እንድንወድቅ አደረገን። ከዚህም በተጨማሪ የሰውን ዘር የአምላክ ተቀናቃኝና “የዚህ ዓለም አምላክ” በሆነው በሰይጣን አገዛዝ ሥር እንዲሆን አድርጎታል።—2 ቆሮ. 4:4 አ.መ.ት፤ ሮም 7:14

5. (ሀ) ይሖዋ ቃሉን የሚጠብቅ አምላክ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ ለአዳምና ለሔዋን ዘሮች ምን ተስፋ ሰጣቸው?

5 ይሖዋ በአዳምና ሔዋን ላይ የሞት ፍርድ መበየኑ የተናገረው ነገር ፈጽሞ መሬት ጠብ እንደማይል የሚያሳይ ነበር። (ዘፍ. 3:16-19) ታዲያ አዳምና ሔዋን መሞታቸው የአምላክን ዓላማ አያደናቅፈውም? በፍጹም አያደናቅፈውም! ይሖዋ በአዳምና በሔዋን ላይ የሞት ፍርድ ሲያስተላልፍ ለዘሮቻቸው ብሩሕ ተስፋ የሚፈነጥቅ ነገር ተናግሯል። ይሖዋ አንድ ‘ዘር’ የማስነሳት ዓላማ እንዳለውና ሰይጣን የዚህን ዘር ተረከዝ እንደሚቀጠቅጠው ገለጸ። ተስፋ የተደረገበት ይህ ዘር ተረከዙ ላይ ከደረሰበት ጉዳት በማገገም ‘የሰይጣንን ራስ ይቀጠቅጣል።’ (ዘፍ. 3:15) መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ሐሳብ ይበልጥ ሲያብራራ ኢየሱስ ክርስቶስን በተመለከተ እንዲህ ይላል፦ “የአምላክ ልጅ እንዲገለጥ የተደረገው ለዚህ ዓላማ ይኸውም የዲያብሎስን ሥራ ለማፍረስ ነው።” (1 ዮሐ. 3:8) ይሁን እንጂ የኢየሱስ አኗኗርም ሆነ ሞቱ የአምላክ ጽድቅ ጎልቶ እንዲታይ ያደረጉት እንዴት ነው?

የኢየሱስ ጥምቀት ያለው ትርጉም

6. ኢየሱስ የአዳምን ኃጢአት እንዳልወረሰ እንዴት እናውቃለን?

6 ኢየሱስ ሙሉ ሰው በሚሆንበት ጊዜ በአንድ ወቅት ፍጹም ከነበረው ከአዳም ጋር እኩል መሆን ነበረበት። (ሮም 5:14፤ 1 ቆሮ. 15:45) ይህ እንዲሆን ደግሞ ፍጹም ሆኖ መወለድ ነበረበት። ታዲያ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? መልአኩ ገብርኤል ለኢየሱስ እናት ለማርያም የሚከተለውን ግልጽ ማብራሪያ ሰጥቷታል፦ “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ የልዑሉም ኃይል በአንቺ ላይ ያርፋል። ስለሆነም የሚወለደው ልጅ ቅዱስ፣ የአምላክ ልጅ ይባላል።” (ሉቃስ 1:35) ኢየሱስ ልጅ እያለ ማርያም ስለተወለደበት መንገድ አንዳንድ ነገሮችን ሳትነግረው አልቀረችም። በመሆኑም በአንድ ወቅት ማርያምና አሳዳጊ አባቱ ዮሴፍ፣ ኢየሱስን በአምላክ ቤተ መቅደስ ውስጥ ባገኙት ጊዜ “በአባቴ ቤት መሆን እንደሚገባኝ አታውቁም?” ብሏቸው ነበር። (ሉቃስ 2:49) ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው ኢየሱስ የአምላክ ልጅ መሆኑን ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ያውቅ ነበር። በመሆኑም የአምላክ ጽድቅ ጎልቶ እንዲታይ ማድረግ ኢየሱስ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ነበር።

7. ኢየሱስ ምን ውድ ነገሮች ነበሩት?

7 ኢየሱስ ለአምልኮ በሚደረጉ ስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ በመገኘት ለመንፈሳዊ ነገሮች ከፍተኛ ጉጉት እንዳለው አሳይቷል። ፍጹም አእምሮ ስለነበረው ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ሲነበብ የሰማውንም ሆነ ያነበበውን ነገር ሁሉ በደንብ ተረድቶት ነበር። (ሉቃስ 4:16) ኢየሱስ ውድ የሆነ ሌላም ነገር ይኸውም ለሰው ልጆች መሥዋዕት አድርጎ ሊያቀርበው የሚችለው ፍጹም ሰብዓዊ አካል ነበረው። በተጠመቀበት ወቅት እየጸለየ የነበረ ሲሆን በመዝሙር 40:6-8 ላይ በሚገኘው ትንቢታዊ ሐሳብ ላይ አሰላስሎ ሊሆን ይችላል።—ሉቃስ 3:21፤ ዕብራውያን 10:5-10ን አንብብ። *

8. አጥማቂው ዮሐንስ ኢየሱስ እንዳይጠመቅ የተከላከለው ለምን ነበር?

8 አጥማቂው ዮሐንስ መጀመሪያ ላይ ኢየሱስ እንዳይጠመቅ ተከላክሎ ነበር። ይህን ያደረገው ለምንድን ነው? ዮሐንስ አይሁዳውያንን የሚያጠምቃቸው ሕጉን ባለመፈጸማቸው ምክንያት ከሠሩት ኃጢአት ንስሐ መግባታቸውን ሲያሳዩ ነበር። ዮሐንስ የኢየሱስ የቅርብ ዘመድ እንደመሆኑ መጠን ኢየሱስ ጻድቅ እንደሆነና ንስሐ መግባት እንደማያስፈልገው ሳያውቅ አይቀርም። ኢየሱስ መጠመቁ ተገቢ እንደሆነ ለዮሐንስ ነገረው። “በዚህ መንገድ ጽድቅ የሆነውን ሁሉ መፈጸማችን ተገቢ ነው” አለው።—ማቴ. 3:15

9. የኢየሱስ ጥምቀት ምን ያመለክት ነበር?

9 ኢየሱስ ፍጹም ሰው እንደመሆኑ መጠን ልክ እንደ አዳም ፍጹም የሆኑ ልጆችን የመውለድ ችሎታውን ለመጠቀም ማሰብ ይችል ነበር። ሆኖም ኢየሱስ የይሖዋ ፈቃድ ይህ እንዳልሆነ ስለሚያውቅ እንዲህ ዓይነት ሕይወት ለመምራት ፈጽሞ አላሰበም። አምላክ ኢየሱስን ወደ ምድር የላከው ተስፋ የተደረገበት ዘር ወይም መሲሕ በመሆን የሚጫወተውን ሚና እንዲፈጽም ነበር። ይህም ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን መሥዋዕት ማድረግን ይጨምር ነበር። (ኢሳይያስ 53:5, 6, 12ን አንብብ።) እርግጥ ነው፣ የኢየሱስ ጥምቀት ያለው ትርጉም ከእኛ ጥምቀት የተለየ ነው። ኢየሱስ ቀድሞውንም ቢሆን ለአምላክ የተወሰነው የእስራኤል ብሔር አባል ስለነበር መጠመቁ ራሱን ለይሖዋ መወሰኑን የሚያመለክት አልነበረም። ከዚህ ይልቅ የኢየሱስ ጥምቀት ስለ መሲሑ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በተገለጸው መሠረት የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም ራሱን ማቅረቡን የሚያመለክት ነበር።

10. መሲሕ በመሆን የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ምን ነገሮችን ይጨምር ነበር? ኢየሱስስ እነዚህን ኃላፊነቶች በመቀበሉ ምን ተሰምቶት ነበር?

10 ይሖዋ ለኢየሱስ የነበረው ፈቃድ የአምላክን መንግሥት ምሥራች መስበክን፣ ደቀ መዛሙርት ማድረግንና ተከታዮቹን ወደፊት ለሚከናወነው ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ ማዘጋጀትን ይጨምር ነበር። ኢየሱስ የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም ራሱን ማቅረቡ የይሖዋ አምላክን የጽድቅ አገዛዝ ለመደገፍ ሲል መከራ ለመቀበልና በጭካኔ ለመገደል ፈቃደኛ መሆኑንም ጭምር ያመለክት ነበር። ኢየሱስ በሰማይ የሚኖረውን አባቱን ከልቡ ይወድ ነበር፤ በመሆኑም የእሱን ፈቃድ ለማድረግ ሲል አካሉን መሥዋዕት አድርጎ ማቅረቡ ጥልቅ እርካታ አስገኝቶለታል። (ዮሐ. 14:31) በተጨማሪም እኛን ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ነፃ ለማውጣት ሲል ፍጹም ሕይወቱ ያለውን ዋጋ ቤዛ አድርጎ ለአምላክ ማቅረብ እንደሚችል ማወቁ አስደስቶት ነበር። ኢየሱስ እነዚህን ከባድ ኃላፊነቶች ለመሸከም ራሱን በማቅረቡ አምላክ ተስማምቶ ነበር? እንዴታ!

11. ኢየሱስ ተስፋ የተሰጠበት መሲሕ ወይም ክርስቶስ አድርጎ ራሱን ባቀረበበት ወቅት ይሖዋ በድርጊቱ እንደተስማማ ያሳየው እንዴት ነው?

11 ኢየሱስ ከዮርዳኖስ ወንዝ ሲወጣ ይሖዋ አምላክ በድርጊቱ መስማማቱን በግልጽ እንደተናገረ አራቱም የወንጌል ጸሐፊዎች መሥክረዋል። አጥማቂው ዮሐንስ እንዲህ ብሏል፦ “መንፈስ ከሰማይ ወጥቶ እንደ ርግብ ሲወርድ አይቻለሁ፤ በእሱም ላይ አረፈ። . . . እኔም አይቻለሁ፤ እሱም የአምላክ ልጅ መሆኑን መሥክሬያለሁ።” (ዮሐ. 1:32-34) ከዚህ በተጨማሪ ይሖዋ ራሱ “በእሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” በማለት ተናግሯል።—ማቴ. 3:17፤ ማር. 1:11፤ ሉቃስ 3:22

እስከ ሞት ድረስ ታማኝ ሆኗል

12. ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ ባለው ሦስት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ምን አከናወነ?

12 ከዚያ በኋላ በነበረው ሦስት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ኢየሱስ ስለ አባቱና የአምላክ አገዛዝ ጽድቅ የሰፈነበት ስለመሆኑ ለሰዎች በማስተማሩ ሥራ ራሱን ሙሉ በሙሉ አስጠምዶ ነበር። ተስፋይቱን ምድር ከዳር እስከ ዳር በእግሩ ማዳረስ ድካም ቢያስከትልበትም ስለ እውነት የተሟላ ምሥክርነት ከመስጠት ምንም ነገር እንዲያግደው አልፈቀደም። (ዮሐ. 4:6, 34፤ 18:37) ኢየሱስ ስለ አምላክ መንግሥት ለሌሎች አስተምሯል። ኢየሱስ የታመሙትን በመፈወስ፣ የተራቡትን በመመገብ ሌላው ቀርቶ የሞቱትን በማስነሳት የፈጸማቸው ተአምራት የአምላክ መንግሥት ለሰው ልጆች ምን እንደሚያከናውን አሳይተዋል።—ማቴ. 11:4, 5

13. ኢየሱስ ጸሎትን በተመለከተ ምን አስተምሯል?

13 ኢየሱስ ላስተማራቸው ትምህርቶችና ላከናወናቸው ፈውሶች ምስጋናውን ራሱ ከመውሰድ ይልቅ ለዚህ ሁሉ ሊወደስ የሚገባው ይሖዋ መሆኑን በመግለጽ በትሕትና ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቷል። (ዮሐ. 5:19፤ 11:41-44) ኢየሱስ ልንጸልይባቸው የሚገቡ ከሁሉ በላይ አስፈላጊ የሆኑ ጉዳዮች የትኞቹ እንደሆኑም አስተምሯል። የአምላክ ስም ‘እንዲቀደስ’ እንዲሁም የይሖዋ ፈቃድ “በሰማይ እየሆነ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ” መሆን እንዲችል ጽድቅ የሰፈነበት የአምላክ አገዛዝ ክፉ የሆነውን የሰይጣን አገዛዝ እንዲተካው በጸሎታችን ላይ መጠየቅ ይኖርብናል። (ማቴ. 6:9, 10) ኢየሱስ “የአምላክን መንግሥትና ጽድቅ [በመፈለግ]” ከጸሎታችን ጋር በሚስማማ መንገድ እንድንመላለስም መክሮናል።—ማቴ. 6:33

14. ኢየሱስ ፍጹም ሆኖ ሳለ በአምላክ ዓላማ ውስጥ የሚጫወተውን ሚና ለመፈጸም ጥረት ማድረግ ያስፈለገው ለምን ነበር?

14 ኢየሱስ መሥዋዕት ሆኖ የሚሞትበት ጊዜ እየተቃረበ ሲሄድ ኃላፊነቱ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ይበልጥ ተገነዘበ። የአባቱ ዓላማ መፈጸሙና ስሙ ከነቀፋ ነፃ መሆኑ የተመካው ኢየሱስ ግፍ ሲፈጸምበትና ጭካኔ በተሞላበት መንገድ ሲገደል እስከ መጨረሻው በመጽናቱ ላይ ነበር። ኢየሱስ ከመሞቱ ከአምስት ቀናት በፊት እንዲህ ሲል ጸልዮ ነበር፦ “አሁን ነፍሴ ተጨንቃለች፤ እንግዲህ ምን ማለት እችላለሁ? አባት ሆይ፣ ከዚህ ሰዓት አድነኝ። ይሁንና የመጣሁት ለዚህ ሰዓት ነው።” ኢየሱስ ሰው እንደመሆኑ መጠን እንዲህ የተሰማው መሆኑ አያስገርምም፤ ያም ሆኖ ስለ ራሱ ከማሰብ ይልቅ ይበልጥ አስፈላጊ ወደሆነው ነገር ትኩረቱን በማዞር “አባት ሆይ፣ ስምህን አክብረው” በማለት ጸልዮአል። ይሖዋም “ስሜን አክብሬዋለሁ፤ ደግሞም አከብረዋለሁ” በማለት ፈጣን ምላሽ ሰጠው። (ዮሐ. 12:27, 28) ኢየሱስ ማንኛውም ሰው ካጋጠመው የሚበልጠውን የታማኝነት ፈተና ለመጋፈጥ ዝግጁ ነበር። ሆኖም የሰማዩ አባቱ የተናገራቸውን እነዚያን ቃላት መስማቱ የአምላክ ጽድቅ ጎልቶ እንዲታይ በማድረግና የይሖዋን ሉዓላዊነት በመደገፍ ረገድ እንደሚሳካለት ሙሉ በሙሉ እንዲተማመን እንዳደረገው ምንም ጥርጥር የለውም። ደግሞም ተሳክቶለታል!

የኢየሱስ ሞት ያከናወነው ነገር

15. ኢየሱስ ሊሞት ሲል “ተፈጸመ” ያለው ለምንድን ነው?

15 ኢየሱስ በመከራው እንጨት ላይ ተሰቅሎ ሊሞት እያጣጣረ ሳለ “ተፈጸመ!” አለ። (ዮሐ. 19:30) ኢየሱስ ከተጠመቀበት አንስቶ እስከ ሞተበት ባለው ሦስት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ በአምላክ እርዳታ በርካታ ታላላቅ ነገሮችን ማከናወን ችሏል! ኢየሱስ በሞተበት ወቅት ታላቅ የምድር መናወጥ ተከስቶ ነበር፤ እንዲሰቅሉት ከታዘዙት ወታደሮች አንዱ የሆነው ሮማዊ መቶ አለቃ ይህን ሲመለከት “ይህ በእርግጥ የአምላክ ልጅ ነበር” አለ። (ማቴ. 27:54) መቶ አለቃው፣ ኢየሱስ የአምላክ ልጅ እንደሆነ በመናገሩ ሲፌዝበት ሳይመለከት አልቀረም። ኢየሱስ ምንም ያህል ከባድ መከራ ቢደርስበትም ታማኝነቱን በመጠበቅ ሰይጣን የወጣለት ውሸታም መሆኑን አረጋግጧል። ሰይጣን የአምላክን ሉዓላዊነት የሚደግፉትን ሁሉ በተመለከተ “ሰው ለሕይወቱ ሲል ያለውን ሁሉ ይሰጣል” የሚል ግድድር አስነስቶ ነበር። (ኢዮብ 2:4) ኢየሱስ ታማኝ በመሆን አዳምና ሔዋን እሱ ከደረሰበት ጋር ሲነጻጸር በጣም ቀላል የሆነውን ፈተና በታማኝነት መወጣት ይችሉ እንደነበር አሳይቷል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ኢየሱስ ያሳለፈው ሕይወትም ሆነ ሞቱ የይሖዋ አገዛዝ ጽድቅ የሰፈነበት መሆኑ እንዲረጋገጥና ጎልቶ እንዲታይ አድርጓል። (ምሳሌ 27:11ን አንብብ።) የኢየሱስ ሞት ያከናወነው ሌላስ ነገር አለ? አዎን፣ አለ!

16, 17. (ሀ) በቅድመ ክርስትና ዘመን የነበሩ የይሖዋ ምሥክሮች በይሖዋ ፊት የጽድቅ አቋም ሊኖራቸው የቻለው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ ልጁ ላሳየው ታማኝነት ወሮታ የከፈለው እንዴት ነው? ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስስ ምን ማድረጉን ቀጥሏል?

16 ከኢየሱስ በፊት በርካታ የይሖዋ አገልጋዮች በዚህች ምድር ላይ ኖረዋል። እነዚህ ሰዎች በአምላክ ፊት የጽድቅ አቋም የነበራቸው ሲሆን ትንሣኤ እንደሚያገኙ ተስፋ ተሰጥቷቸዋል። (ኢሳ. 25:8፤ ዳን. 12:13) ይሁንና ቅዱስ አምላክ የሆነው ይሖዋ፣ ኃጢአተኛ ለሆኑ የሰው ልጆች እንዲህ ያለ አስደናቂ በረከት ለመስጠት የሚያስችል ምን ሕጋዊ መሠረት አለው? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሲል መልሱን ይሰጠናል፦ “በኢየሱስ ደም የሚያምኑ ሁሉ ማስተሰረያ ያገኙ ዘንድ አምላክ እሱን መሥዋዕት አድርጎ አቅርቦታል። አምላክ ይህን ያደረገው ትዕግሥቱን ባሳየባቸው በቀደሙት ዘመናት የተፈጸሙትን ኃጢአቶች ይቅር በማለት የራሱን ጽድቅ ለማሳየት ነው፤ በተጨማሪም በኢየሱስ ላይ እምነት ያለውን ሰው ጻድቅ ብሎ በመጥራት በዚህም ዘመን የራሱን ጽድቅ ለማሳየት ነው።”—ሮም 3:25, 26 *

17 ይሖዋ ኢየሱስን ከሞት በማስነሳትና ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ከነበረው የላቀ ቦታ በመስጠት ወሮታውን ከፍሎታል። ክብር የተላበሰ መንፈሳዊ ፍጥረት የሆነው ኢየሱስ በአሁኑ ጊዜ ያለመሞትን ባሕርይ ተላብሷል። (ዕብ. 1:3) ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ሊቀ ካህናትና ንጉሥ እንደመሆኑ መጠን ተከታዮቹ የአምላክን ጽድቅ አጉልተው እንዲያሳዩ መርዳቱን ቀጥሏል። በሰማይ ያለው አባታችን ይሖዋ፣ የልጁን ምሳሌ በመከተል ይህን ለሚያደርጉትና እሱን በታማኝነት ለሚያገለግሉት ሁሉ ወሮታ ከፋይ በመሆኑ ምንኛ አመስጋኞች ነን!—መዝሙር 34:3ን እና ዕብራውያን 11:6ን አንብብ።

18. የሚቀጥለው የጥናት ርዕስ ትኩረት የሚያደርገው በምን ላይ ነው?

18 ከአቤል ጀምሮ የነበሩ ታማኝ የሰው ልጆች፣ ተስፋ በተሰጠበት ዘር ላይ እምነት እንዳላቸው በተግባር በማሳየታቸው እንዲሁም ዘሩ መምጣቱ እንደማይቀርና በትንቢት የተነገሩትን ነገሮች በሙሉ እንደሚፈጽም እርግጠኞች በመሆናቸው ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና መመሥረት ችለዋል። ይሖዋ፣ ልጁ ታማኝነቱን እንደሚጠብቅና ሞቱም “የዓለምን ኃጢአት” ሙሉ በሙሉ እንደሚሸፍን ያውቅ ነበር። (ዮሐ. 1:29) የኢየሱስ ሞት በዛሬው ጊዜ ያሉ ሰዎችንም ይጠቅማል። (ሮም 3:26) ታዲያ የክርስቶስ ቤዛ ለአንተ ምን በረከቶችን ሊያመጣልህ ይችላል? የሚቀጥለው የጥናት ርዕስ በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት ያደርጋል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.7 ሐዋርያው ጳውሎስ ከ⁠መዝሙር 40:6-8 ላይ ሲጠቅስ የተጠቀመው የግሪክኛውን የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም ሲሆን እዚያ ላይ ጥቅሱ “አካል አዘጋጀህልኝ” ይላል። አሁን ባሉ የጥንቶቹ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች ላይ ይህ ሐሳብ አይገኝም።

^ አን.16 በገጽ 6 እና 7 ላይ የሚገኘውን “የአንባቢያን ጥያቄዎች” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• የአምላክ ጽድቅ ጥያቄ ላይ የወደቀው እንዴት ነው?

• የኢየሱስ ጥምቀት ምን ያመለክታል?

• የኢየሱስ ሞት ምን አከናውኗል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የኢየሱስ ጥምቀት ምን እንደሚያመለክት ታውቃለህ?