በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

ኢየሱስ በኃጢአተኝነቷ ለምትታወቅ ሴት ኃጢአቷ ይቅር እንደተባለላት ሊናገር የቻለው እንዴት ነው?—ሉቃስ 7:37, 48

ኢየሱስ፣ ስምዖን በተባለ ፈሪሳዊ ቤት በማዕድ ተቀምጦ ሳለ አንዲት ሴት ‘ከኢየሱስ በስተኋላ እግሩ አጠገብ ተቀመጠች።’ ሴትየዋ አጠገቡ ሆና እያለቀሰች በእንባዋ እግሩን ታርስ ጀመር፤ ከዚያም በፀጉሯ ታብሰው ነበር። በተጨማሪም እግሩን እየሳመች ሽቶ ቀባችው። ሴትየዋ “በከተማው ውስጥ በኃጢአተኝነቷ የምትታወቅ” እንደነበረች የወንጌል ዘገባው ይገልጻል። እርግጥ ነው፣ ማናችንም ብንሆን ፍጽምና የጎደለን እንደመሆናችን መጠን ኃጢአተኞች ነን፤ ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ‘ኃጢአተኛ’ የሚለውን አገላለጽ ብዙውን ጊዜ የሚጠቀመው በኃጢአት ድርጊታቸው የታወቁ ሰዎችን ለመግለጽ ነው። ሴትየዋ ዝሙት አዳሪ ሳትሆን አትቀርም። ኢየሱስ “ኃጢአትሽ ይቅር ተብሎልሻል” ያላት እንዲህ ላለች ሴት ነበር። (ሉቃስ 7:36-38, 48) ታዲያ ኢየሱስ ይህን ሲል ምን ማለቱ ነበር? የቤዛው መሥዋዕት ገና ስላልቀረበ ኃጢአቷ ይቅር ሊባል የሚችለው እንዴት ነው?

ኢየሱስ ሴትየዋ እግሩን ካጠበችና ሽቶ ከቀባችው በኋላ ኃጢአቷ ይቅር እንደተባለላት ከመናገሩ በፊት በእንግድነት ለተቀበለው ለስምዖን አንድ አስፈላጊ ነጥብ ለማብራራት ምሳሌ ተጠቀመ። ኢየሱስ ኃጢአትን፣ ለመክፈል አዳጋች ከሆነ ከባድ ዕዳ ጋር በማመሳሰል ለስምዖን እንዲህ አለው፦ “ከአንድ አበዳሪ ገንዘብ የተበደሩ ሁለት ሰዎች ነበሩ፤ አንዱ አምስት መቶ ሌላው ደግሞ ሃምሳ ዲናር ተበድረው ነበር። ሁለቱም የተበደሩትን መክፈል ባቃታቸው ጊዜ አበዳሪው ዕዳቸውን ሙሉ በሙሉ ተወላቸው። እንግዲህ ከሁለቱ ሰዎች አበዳሪውን አብልጦ የሚወደው የትኛው ነው?” ስምዖን “ብዙ ዕዳ የተተወለት ይመስለኛል” በማለት መለሰ። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “በትክክል ፈርደሃል” አለው። (ሉቃስ 7:41-43) ሁላችንም አምላክን የመታዘዝ ዕዳ አለብን፤ ስለዚህ እሱን ባለመታዘዝ ኃጢአት ስንሠራ ዕዳችንን ሳንከፍል ቀረን ማለት ነው። በዚህ መንገድ ዕዳችን እየተጠራቀመ ይሄዳል። ይሖዋ ግን ያለብንን ዕዳ በመተው ምሕረት ለማድረግ ፈቃደኛ እንደሆነ አበዳሪ ነው። ኢየሱስ “የሌሎችን ዕዳ ይቅር እንዳልን ዕዳችንን ይቅር በለን” ብለው እንዲጸልዩ ተከታዮቹን ያበረታታቸው ለዚህ ነው።—ማቴ. 6:12 የግርጌ ማስታወሻ

ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት አምላክ ሰዎችን ይቅር የሚለው ምን ነገርን መሠረት በማድረግ ነበር? ፍጹም በሆነው የይሖዋ ፍትሕ መሠረት ለኃጢአት የሚሰጠው ቅጣት ሞት ነው። በመሆኑም አዳም ኃጢአት በመሥራቱ ሕይወቱን አጥቷል። ይሁን እንጂ አምላክ ለእስራኤላውያን በሰጠው ሕግ መሠረት ሕግን የተላለፈ አንድ ሰው የእንስሳ መሥዋዕት ለይሖዋ በማቅረብ ኃጢአቱ ይቅር ሊባልለት ይችል ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ “በሕጉ መሠረት ሁሉም ነገር ለማለት ይቻላል፣ በደም ይነጻል፤ ደም ካልፈሰሰ በስተቀር ይቅርታ አይደረግም” በማለት ጽፏል። (ዕብ. 9:22) አይሁዳውያን ከዚህ ውጪ ከአምላክ ዘንድ ይቅርታን ማግኘት የሚቻልበት መንገድ እንዳለ አያውቁም ነበር። በመሆኑም በኢየሱስ ዘመን የነበሩት ሰዎች ክርስቶስ ለሴትየዋ የተናገረውን ነገር መቃወማቸው ምንም የሚያስገርም አይደለም። ከኢየሱስ ጋር አብረውት በማዕድ የተቀመጡት ሰዎች በልባቸው “ኃጢአትን እንኳ ሳይቀር ይቅር የሚል ይህ ሰው ማን ነው?” አሉ። (ሉቃስ 7:49) ታዲያ በጣም ኃጢአተኛ የሆነችው የዚህች ሴት መተላለፍ ይቅር ሊባል የሚችለው በምን መሠረት ነው?

የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ካመፁ በኋላ የተነገረው ትንቢት ይሖዋ አንድ ‘ዘር’ የማስነሳት ዓላማ እንዳለውና ሰይጣንና ‘ዘሮቹ’ የዚህን ዘር ተረከዝ እንደሚቀጠቅጡት ይገልጻል። (ዘፍ. 3:15) ኢየሱስ በአምላክ ጠላቶች ሲገደል ተረከዙ የተቀጠቀጠ ያህል ነበር። (ገላ. 3:13, 16) የፈሰሰው የክርስቶስ ደም የሰው ልጆችን ከኃጢአትና ከሞት ነፃ ለማውጣት የሚያስችል ቤዛ ሆኖ ያገለግላል። ይሖዋ ዓላማውን ከግቡ እንዳያደርስ የሚያግደው ምንም ነገር ስለሌለ በዘፍጥረት 3:15 ላይ የሚገኘውን ትንቢት ከተናገረበት ጊዜ ጀምሮ የቤዛውን ዋጋ እንደተከፈለ አድርጎ ሊቆጥረው ይችላል። በመሆኑም እሱ በገባው ቃል ላይ እምነት እንዳላቸው በተግባር የሚያሳዩ ሰዎችን ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ይቅር ማለት ይችላል።

በቅድመ ክርስትና ዘመን ይሖዋ እንደ ጻድቃን አድርጎ የቆጠራቸው በርካታ ግለሰቦች ነበሩ። ከእነዚህም መካከል ሄኖክ፣ ኖኅ፣ አብርሃም፣ ረዓብና ኢዮብ ይገኙበታል። አምላክ በሰጠው ተስፋ ላይ እምነት በማሳደር ቃሉ ፍጻሜ የሚያገኝበትን ጊዜ በጉጉት ይጠባበቁ ነበር። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “አብርሃም በይሖዋ አመነ፤ እንደ ጽድቅም ተቆጠረለት” በማለት ጽፏል። ረዓብን አስመልክቶ ደግሞ “በተመሳሳይም ጋለሞታይቱ ረዓብ . . . በሥራ ጻድቅ ተብላ አልተጠራችም?” ብሏል።—ያዕ. 2:21-25

የጥንቱ የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊት የተለያዩ ከባድ ኃጢአቶችን ፈጽሞ ነበር፤ ይሁንና በእውነተኛው አምላክ ላይ ጠንካራ እምነት የነበረው ከመሆኑም ሌላ ኃጢአት በሠራበት ጊዜ ሁሉ ከልቡ ንስሐ ገብቷል። በተጨማሪም ቅዱሳን መጻሕፍት እንዲህ ይላሉ፦ “በኢየሱስ ደም የሚያምኑ ሁሉ ማስተሰረያ ያገኙ ዘንድ አምላክ እሱን መሥዋዕት አድርጎ አቅርቦታል። አምላክ ይህን ያደረገው ትዕግሥቱን ባሳየባቸው በቀደሙት ዘመናት የተፈጸሙትን ኃጢአቶች ይቅር በማለት የራሱን ጽድቅ ለማሳየት ነው፤ በተጨማሪም በኢየሱስ ላይ እምነት ያለውን ሰው ጻድቅ ብሎ በመጥራት በዚህም ዘመን የራሱን ጽድቅ ለማሳየት ነው።” (ሮም 3:25, 26) ይሖዋ ወደፊት የሚቀርበውን የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት መሠረት በማድረግ ፍትሑ የሚጠይቀውን ነገር ሳያጓድል የዳዊትን መተላለፍ ይቅር ማለት ይችል ነበር።

ከዚህ ለመረዳት እንደሚቻለው የኢየሱስን እግር ሽቶ የቀባችው ሴት ሁኔታም ተመሳሳይ ነው። ሴትየዋ ሥነ ምግባር የጎደለው አኗኗር ትከተል የነበረ ቢሆንም ንስሐ ገብታለች። ከኃጢአት መዋጀት እንደሚያስፈልጋት የተገነዘበች ከመሆኑም በላይ ይሖዋ ሰዎችን ከኃጢአት ለመቤዠት ያዘጋጀውን ግለሰብ ከልቧ መቀበሏን በተግባር አሳይታለች። ይህ መሥዋዕት በወቅቱ ገና ያልቀረበ ቢሆንም መሥዋዕቱ መቅረቡ የተረጋገጠ በመሆኑ የመሥዋዕቱ ዋጋ እንደ እሷ ላሉ ሰዎች ሊሠራ ይችል ነበር። በመሆኑም ኢየሱስ “ኃጢአትሽ ይቅር ተብሎልሻል” ብሎ ሊናገራት ችሏል።

ከዚህ ዘገባ በግልጽ መመልከት እንደሚቻለው ኢየሱስ ኃጢአተኛ የሆኑ ሰዎችን አላገለላቸውም። መልካም ነገር አድርጎላቸዋል። ከዚህም በላይ ይሖዋ ንስሐ የገቡ ኃጢአተኞችን ይቅር ለማለት ፈቃደኛ ነው። ፍጽምና ለጎደለን የሰው ልጆች ይህን አስደናቂ ዝግጅት ማወቃችን እንዴት የሚያጽናና ነው!

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረላቸው