በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“የፍቅራዊ ደግነት ሕግ” አንደበታችሁን እንዲቆጣጠረው ፍቀዱ

“የፍቅራዊ ደግነት ሕግ” አንደበታችሁን እንዲቆጣጠረው ፍቀዱ

“የፍቅራዊ ደግነት ሕግ” አንደበታችሁን እንዲቆጣጠረው ፍቀዱ

“አፏን በጥበብ ትከፍታለች፣ የፍቅራዊ ደግነት ሕግም በአንደበቷ አለ።”—ምሳሌ 31:26 NW

1, 2. (ሀ) የይሖዋ አገልጋዮች ማበረታቻ የተሰጣቸው የትኛውን ባሕርይ እንዲያዳብሩ ነው? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ የትኞቹን ነጥቦች እንመረምራለን?

በጥንት ዘመን ንጉሥ ልሙኤል እናቱ ከሰጠችው ከፍተኛ ቁም ነገር ያዘሉ ምክሮች መካከል አንዲት ጥሩ ሚስት ልታሟላው ስለሚገባው ብቃት የተናገረችው ሐሳብ ይገኝበታል። “አፏን በጥበብ ትከፍታለች፣ የፍቅራዊ ደግነት ሕግም በአንደበቷ አለ” በማለት ነግራው ነበር። (ምሳሌ 31:1, 10, 26 NW) አንዲት ጥበበኛ ሴትም ሆነች ይሖዋን ማስደሰት የሚፈልጉ ሌሎች ሰዎች ሁሉ በአንደበት አጠቃቀማቸው ረገድ ፍቅራዊ ደግነት ማሳየት ይገባቸዋል። (ምሳሌ 19:22ን NWን አንብብ። *) ሁሉም እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች በአነጋገራቸው ፍቅራዊ ደግነት ሊያንጸባርቁ ይገባል።

2 ፍቅራዊ ደግነት ምንድን ነው? ይህን ባሕርይ ማሳየት የሚገባን ለእነማን ነው? ‘የፍቅራዊ ደግነት ሕግ’ በአንደበታችን እንዲኖር ለማድረግ የሚረዳን ምንድን ነው? እንዲህ ማድረጋችን ከቤተሰባችን አባላትና ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር ባለን ግንኙነት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድረው እንዴት ነው?

ከጽኑ ፍቅር የሚመነጭ ደግነት

3, 4. (ሀ) ፍቅራዊ ደግነት ምንድን ነው? (ለ) ፍቅራዊ ደግነት ከሰብዓዊ ደግነት የሚለየው እንዴት ነው?

3 ከቃሉ መረዳት እንደሚቻለው ፍቅራዊ ደግነት ፍቅርንና ደግነትን አጣምሮ የያዘ ባሕርይ ነው። ፍቅራዊ ደግነት ለሌሎች ሰዎች ከልብ አሳቢ መሆንንና አሳቢነታችንን በድርጊትና በቃል መግለጽን የሚጨምር የደግነት ባሕርይን የሚያካትት ነው። ፍቅርም የዚህ ባሕርይ አንዱ ገጽታ ስለሆነ ከፍቅር ተነሳስቶ ስለ ሌሎች ደኅንነት ማሰብን ይጨምራል። ይሁን እንጂ ፍቅራዊ ደግነት ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጡ ቃል ከፍቅር የመነጨ ደግነት ማሳየትን ብቻ የሚያመለክት አይደለም። ፍቅራዊ ደግነት ለአንድ ሰው ደግነት ለማሳየት የተነሳሳንበት ዓላማ ግቡን እስኪመታ ድረስ ከዚያ ሰው ጋር በፈቃደኝነትና በጽናት ተጣብቆ በመኖር የሚገለጽ የደግነት ባሕርይ ነው።

4 ፍቅራዊ ደግነት ከደግነት የሚለይበት ሌላም ዘርፍ አለ። ከሰብዓዊነት ተነሳስተን የምናደርገውን ደግነት ለማናውቀው ሰውም እንኳ ልናሳየው እንችላለን። ሐዋርያው ጳውሎስና 275 ሰዎች የመርከብ መሰበር አደጋ በደረሰባቸው ወቅት የማልታ ደሴት ነዋሪዎች ከዚያ በፊት ባያውቋቸውም እንኳ ለጳውሎስና ለሰዎቹ እንዲህ ዓይነቱን ደግነት አሳይተዋል። (ሥራ 27:37 እስከ 28:2) በሌላ በኩል ፍቅራዊ ደግነት ቀደም ሲል ወዳጅነት የመሠረቱ ሁለት ግለሰቦች አንዳቸው ከሌላው ጋር በጽናት በመጣበቅ የሚያሳዩት ባሕርይ ነው። * “እስራኤላውያን ከግብፅ ምድር በወጡ ጊዜ” ቄናውያን ያሳዩአቸው እንዲህ ያለውን ባሕርይ ነበር።—1 ሳሙ. 15:6 NW

ማሰላሰልና ጸሎት አስፈላጊ ናቸው

5. አንደበታችንን ለመግራት ምን ሊረዳን ይችላል?

5 ፍቅራዊ ደግነትን በንግግራችን ማሳየት ቀላል አይደለም። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ አንደበትን አስመልክቶ ሲጽፍ “ምላስን ግን ሊገራ የሚችል አንድም ሰው የለም። ምላስ ገዳይ መርዝ የሞላባት ለመቆጣጠር የምታስቸግር ጎጂ ነገር ናት” ብሏል። (ያዕ. 3:8) ለመቆጣጠር በጣም አስቸጋሪ የሆነውን ይህን የሰውነት ክፍል ለመግራት ምን ሊረዳን ይችላል? ኢየሱስ በዘመኑ ለነበሩት የሃይማኖት መሪዎች የተናገረው ሐሳብ ይህን በሚመለከት ጠለቅ ያለ ማስተዋል ይሰጠናል። “አንደበት የሚናገረው በልብ ውስጥ የሞላውን ነው” በማለት ተናግሯል። (ማቴ. 12:34) ፍቅራዊ ደግነት አንደበታችንን እንዲቆጣጠርልን የምንፈልግ ከሆነ ይህን ባሕርይ ልባችን ላይ መቅረጽ ማለትም በውስጣችን መትከል አለብን። ማሰላሰልና ጸሎት ይህን ለማድረግ የሚረዱን እንዴት እንደሆነ እንመልከት።

6. ይሖዋ በፍቅራዊ ደግነት ተነሳስቶ ባከናወናቸው ሥራዎች ላይ በአድናቆት ማሰላሰል ያለብን ለምንድን ነው?

6 ይሖዋ አምላክ ‘ፍቅራዊ ደግነቱ እጅግ ብዙ’ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ዘፀ. 34:6 NW) መዝሙራዊው “ይሖዋ ሆይ፣ ፍቅራዊ ደግነትህ ምድርን ሞላ” በማለት ዘምሯል። (መዝ. 119:64 NW) ቅዱሳን መጻሕፍት ይሖዋ ለአገልጋዮቹ እንዴት ፍቅራዊ ደግነት እንዳሳየ የሚናገሩ በርካታ ታሪኮችን ይዘዋል። ጊዜ ወስደን በይሖዋ ‘ሥራዎች’ ላይ በአድናቆት ማሰላሰላችን ይህን ባሕርይ የማዳበር ፍላጎት እንዲኖረን ይረዳናል።—መዝሙር 77:12ን አንብብ።

7, 8. (ሀ) ይሖዋ ለሎጥና ለቤተሰቡ ፍቅራዊ ደግነት የተንጸባረቀበት ምን እርምጃ ወስዷል? (ለ) ዳዊት አምላክ ስላደረገለት ፍቅራዊ ደግነት ምን ተሰምቶት ነበር?

7 ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ የአብርሃም የወንድም ልጅ የሆነው ሎጥ ይኖርባት በነበረችው በሰዶም ከተማ ላይ ጥፋት ባመጣ ጊዜ እሱንና ቤተሰቡን እንዴት እንዳዳነ አስብ። ጥፋቱ እየቀረበ ሲመጣ ወደ ሎጥ ተልከው የመጡት መላእክት ቤተሰቡን ይዞ በፍጥነት ከተማዋን ለቆ እንዲወጣ አሳሰቡት። ሎጥ ለመውጣት “ሲያመነታም፣ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ስለ ራራላቸው [መላእክቱ] የእርሱን፣ የሚስቱንና የሁለት ሴቶች ልጆቹን እጅ ይዘው ከከተማይቱ በደኅና አወጧቸው” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። አምላክ በወሰደው በዚህ የማዳን እርምጃ ላይ ስናሰላስል ልባችን በጥልቅ አልተነካም? ይህ እርምጃ በእርግጥ የአምላክ ፍቅራዊ ደግነት መገለጫ ነው ብለን ለማመን አልተነሳሳንም?—ዘፍ. 19:16, 19

8 አሁን ደግሞ ‘[ይሖዋ] ኀጢአትሽን ሁሉ ይቅር ይላል፣ ደዌሽንም ሁሉ ይፈውሳል’ በማለት የዘመረውንና የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረውን የዳዊትን ሁኔታ እንመልከት። ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር ለፈጸመው ኃጢአት የይሖዋን ይቅርታ በማግኘቱ ልቡ በአመስጋኝነት ስሜት ተሞልቶ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም! “ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፣ እንዲሁ ለሚፈሩት ምሕረቱ [‘ፍቅራዊ ደግነቱ፣’ NW] ታላቅ ናት” በማለት ይሖዋን አወድሶታል። (መዝ. 103:3, 11) በዚህም ሆነ በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ላይ ማሰላሰላችን ልባችን ለይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት ባለን አድናቆት እንዲሞላ እንዲሁም እሱን ለማወደስና ለማመስገን እንድንነሳሳ ያደርገናል። ልባችን በአድናቆት በተሞላ መጠን እውነተኛውን አምላክ ለመምሰል ያለን ፍላጎት የዚያኑ ያህል ይጨምራል።—ኤፌ. 5:1

9. የይሖዋ አገልጋዮች ፍቅራዊ ደግነትን በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ለማሳየት ምን ጠንካራ ምክንያት አላቸው?

9 ከእነዚህ ቅዱስ ጹሑፋዊ ምሳሌዎች መረዳት እንደሚቻለው ይሖዋ ፍቅራዊ ደግነቱን ወይም ጽኑ ፍቅሩን የሚያሳየው አስቀድመው ከእሱ ጋር ዝምድና ለመሠረቱ ሰዎች ነው። ሕያው ከሆነው አምላክ ጋር እንዲህ ያለ ዝምድና ያልመሠረቱ ሰዎችን በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? ይሖዋ ለእነዚህ ሰዎች ደግነት አያሳያቸውም? ያሳያቸዋል፤ ሉቃስ 6:35 “[አምላክ] ለማያመሰግኑም ሆነ ለክፉዎች ደግ ነው” ይላል። “እሱ በክፉና በጥሩ ሰዎች ላይ ፀሐዩን ያወጣል፤ ጻድቅ በሆኑና ጻድቅ ባልሆኑ ሰዎች ላይም ዝናብ ያዘንባል።” (ማቴ. 5:45) እውነትን ከማወቃችንና በሕይወታችን ተግባራዊ ከማድረጋችን በፊት የአምላክን ደግነት ቀምሰናል። አገልጋዮቹ ከሆንን በኋላ ግን የእሱን ጽኑ ፍቅር ወይም ጸንቶ የሚኖረውን ፍቅራዊ ደግነቱን ማግኘት ችለናል። (ኢሳይያስ 54:10ን አንብብ።) ለዚህ ምንኛ አመስጋኞች ነን! ይህን ማወቃችን በአነጋገራችንም ሆነ በሌሎች የሕይወታችን ዘርፎች ፍቅራዊ ደግነትን እንድናሳይ ጠንካራ ምክንያት ይሆነናል።

10. ፍቅራዊ ደግነትን ለማዳበር ጸሎት ከፍተኛ እገዛ ያበረክትልናል የምንለው ለምንድን ነው?

10 የጸሎት መብት ፍቅራዊ ደግነትን ለማዳበር ከፍተኛ እገዛ ያበረክትልናል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ፍቅራዊ ደግነት አጣምሮ የያዛቸው ፍቅርና ደግነት የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ፍሬ ገጽታዎች በመሆናቸው ነው። (ገላ. 5:22) ይህ መንፈስ እንዲመራን በመፍቀድ ፍቅራዊ ደግነትን በልባችን ውስጥ መትከል እንችላለን። የይሖዋን ቅዱስ መንፈስ ማግኘት የምንችልበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ጸሎት ነው። (ሉቃስ 11:13) የአምላክን መንፈስ ለማግኘት በተደጋጋሚ ጊዜ መጸለያችንና አመራሩን መቀበላችን ተገቢ ነው። አዎን፣ የፍቅራዊ ደግነት ሕግ በአንደበታችን እንዲኖር ማሰላሰልና ጸሎት አስፈላጊ ናቸው።

ባለትዳሮች በአንደበት አጠቃቀማችሁ ረገድ ፍቅራዊ ደግነትን አሳዩ

11. (ሀ) ባሎች ለሚስቶቻቸው ፍቅራዊ ደግነት እንዲያሳዩ ይሖዋ እንደሚጠብቅባቸው እንዴት እናውቃለን? (ለ) አንድ ባል የፍቅራዊ ደግነት ሕግ አንደበቱን እንዲገታ ሊረዳው የሚችለው እንዴት ነው?

11 ሐዋርያው ጳውሎስ ባሎችን “ክርስቶስ ጉባኤውን እንደወደደና ለእሱ ራሱን አሳልፎ እንደሰጠ ሁሉ እናንተም ሚስቶቻችሁን መውደዳችሁን ቀጥሉ” የሚል ማሳሰቢያ ሰጥቷቸዋል። (ኤፌ. 5:25) በተጨማሪም ጳውሎስ፣ ይሖዋ ለአዳምና ለሔዋን የነገራቸውን ነገር አስታውሷቸዋል። ሐዋርያው “ሰው ከአባቱና ከእናቱ ተለይቶ ከሚስቱ ጋር ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ” በማለት ጽፏል። (ኤፌ. 5:31) ከዚህ በግልጽ መመልከት እንደሚቻለው ይሖዋ፣ ባሎች ለሚስቶቻቸው ሁልጊዜ ፍቅራዊ ደግነት በማሳየት ከእነሱ ጋር በታማኝነት ተጣብቀው እንዲኖሩ ይጠብቅባቸዋል። በአንደበት አጠቃቀሙ ረገድ ጽኑ ፍቅርን የሚያሳይ ባል የባለቤቱን ስህተት በሰው ፊት አያወራም ወይም እሷን የሚያቃልል ነገር አይናገርም። እንዲያውም እሷን ማመስገን ያስደስተዋል። (ምሳሌ 31:28) በመካከላቸው አለመግባባት በሚፈጠርበት ጊዜ ባል ፍቅራዊ ደግነት የሚያሳይ መሆኑ ሚስቱን የሚያዋርድ ነገር ላለመናገር አንደበቱን እንዲገታ ያደርገዋል።

12. አንዲት ሚስት አንደበቷ በፍቅራዊ ደግነት ሕግ እንደሚገዛ በአነጋገሯ ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?

12 አንዲት ሚስትም አንደበቷ በፍቅራዊ ደግነት ሕግ እንደሚገዛ ማሳየት ይኖርባታል። የዚህ ዓለም መንፈስ በአነጋገሯ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድርባት አይገባም። ባሏን ‘በጥልቅ የምታከብረው’ ከሆነ በሰዎች ፊት ስለ እሱ ጥሩ ነገር ትናገራለች፤ ይህ ደግሞ ሰዎች ለእሱ ያላቸው አክብሮት እንዲጨምር ያደርጋል። (ኤፌ. 5:33) ልጆቻቸው ለአባታቸው ያላቸው አክብሮት እንዲቀንስ ስለማትፈልግ በእነሱ ፊት ከእሱ ጋር ከመጨቃጨቅ ወይም አመለካከቱን ከመቃወም ትቆጠባለች። እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን ለመፍታት በግል ታነጋግረዋለች። መጽሐፍ ቅዱስ “ጠቢብ ሴት ቤቷን ትሠራለች” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 14:1) ቤቷ ለሁሉም የቤተሰቡ አባል አስደሳችና እረፍት የሚያስገኝ እንዲሆን ታደርጋለች።

13. የፍቅራዊ ደግነት ሕግ በተለይ ተግባራዊ መሆን ያለበት መቼ ነው? እንዲህ ማድረግ የሚቻለውስ እንዴት ነው?

13 ባለትዳሮች ብቻቸውን በሚሆኑበት ጊዜም እንኳ አንደበታቸውን እርስ በርስ እንደሚከባበሩ በሚያሳይ መንገድ መጠቀም ይኖርባቸዋል። ጳውሎስ “ቁጣን፣ ንዴትን፣ ክፋትንና ስድብን የመሳሰሉትን ሁሉ ከእናንተ አስወግዱ” በማለት ጽፏል። አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ርኅራኄን፣ ደግነትን፣ ትሕትናን፣ ገርነትንና ትዕግሥትን ልበሱ። . . . በእነዚህ ነገሮች ሁሉ ላይ ፍቅርን ልበሱ፤ ምክንያቱም ፍቅር ፍጹም የሆነ የአንድነት ማሰሪያ ነው።” (ቆላ. 3:8, 12-14) ልጆች በቤት ውስጥ ሁልጊዜ ፍቅርና ደግነት የሚንጸባረቅበት ንግግር መስማታቸው በጥሩ ሁኔታ እንዲያድጉ የሚረዳቸው ከመሆኑም በላይ በአነጋገር ረገድ የወላጆቻቸውን ምሳሌ ይከተላሉ።

14. የቤተሰብ ራሶች አንደበታቸውን በእነሱ ሥር ያሉትን ለማበረታታት ሊጠቀሙበት የሚችሉት እንዴት ነው?

14 መዝሙራዊው “ምሕረትህ [“ፍቅራዊ ደግነትህ፣” NW] ለመጽናናት ትሁነኝ” በማለት ወደ ይሖዋ ጸልዮአል። (መዝ. 119:76) ይሖዋ ሕዝቡን የሚያጽናናበት ዋነኛው መንገድ ምክርና መመሪያ መስጠት ነው። (መዝ. 119:105) የቤተሰብ ራሶች በሰማይ የሚኖረውን አባታችን ምሳሌ በመከተል አንደበታቸውን በእነሱ ሥር የሚገኙትን ለማጽናናት ሊጠቀሙበት የሚችሉት እንዴት ነው? አስፈላጊውን መመሪያና ማበረታቻ በመስጠት ይህን ማድረግ ይችላሉ። የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራም እንዲህ ያለውን መንፈሳዊ ሀብት ለማግኘት የሚያስችል ግሩም አጋጣሚ ይከፍታል።—ምሳሌ 24:4

ለእምነት ባልንጀሮቻችሁ ጽኑ ፍቅር አሳዩ

15. ሽማግሌዎችም ሆኑ በመንፈሳዊ የጎለመሱ ክርስቲያኖች አንደበታቸውን ሌሎች የጉባኤውን አባላት ለመጠበቅ ሊጠቀሙበት የሚችሉት እንዴት ነው?

15 ንጉሥ ዳዊት “ቸርነትህና [“ፍቅራዊ ደግነትህና፣” NW] እውነትህ ዘወትር ይጠብቁኝ” በማለት ጸልዮአል። (መዝ. 40:11) ክርስቲያን ሽማግሌዎችና በጉባኤ ውስጥ ያሉ በመንፈሳዊ የጎለመሱ ሰዎች በዚህ ረገድ ይሖዋን መምሰል የሚችሉት እንዴት ነው? አንደበታችንን ቅዱስ ጽሑፋዊ ትምህርት ለማስተላለፍ የምንጠቀምበት ከሆነ ፍቅራዊ ደግነት እያሳየን ነው ማለት ይቻላል።—ምሳሌ 17:17

16, 17. አንደበታችን በፍቅራዊ ደግነት ሕግ እንደሚገዛ ማሳየት የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?

16 አንድ ክርስቲያን ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚጋጭ አካሄድ እየተከተለ እንደሆነ ካስተዋልን ምን ማድረግ ይኖርብናል? ፍቅራዊ ደግነት አንደበታችንን እሱን ለማረም እንድንጠቀምበት አያነሳሳንም? (መዝ. 141:5 NW) አንድ የእምነት ባልንጀራችን ከባድ ኃጢአት እንደፈጸመ ካወቅን ለግለሰቡ ያለን ጽኑ ፍቅር ‘የጉባኤ ሽማግሌዎችን ወደ እሱ እንዲጠራ’ እንድናበረታታው ያነሳሳናል፤ ‘እነሱም በይሖዋ ስም ዘይት ቀብተው ይጸልዩለታል።’ (ያዕ. 5:14) ስህተት የሠራው ሰው ወደ ሽማግሌዎች ካልሄደ ጉዳዩን ለእነሱ አለማሳወቃችን ፍቅርና ደግነት እንደጎደለን የሚያሳይ ይሆንብናል። ከመካከላችን አንዳንዶች ተስፋ ሊቆርጡ፣ ብቸኝነት ሊሰማቸው፣ የዋጋ ቢስነት ስሜት ሊያጠቃቸው ወይም ከመጠን በላይ ሊያዝኑ ይችላሉ። በዚህ ጊዜ በአንደበታችን ላይ የፍቅራዊ ደግነት ሕግ እንዳለ ማሳየት የምንችልበት የተሻለው መንገድ ‘የተጨነቁትን ነፍሳት ማጽናናት’ ነው።—1 ተሰ. 5:14

17 የአምላክ ጠላቶች በእምነት ባልንጀሮቻችን ላይ መጥፎ ወሬ ቢያናፍሱ ምን ማድረግ ይኖርብናል? የወንድሞቻችንን ታማኝነት ከመጠራጠር ይልቅ እንዲህ ያለውን ወሬ በቸልታ ማለፍ ወይም ወሬውን የነገረን ሰው ምክንያታዊ እንደሆነ ከተሰማን ተጨባጭ ማስረጃ ይኖረው እንደሆነ ልንጠይቀው እንችላለን። የአምላክ ጠላቶች በክርስቲያን ወንድሞቻችን ላይ ጉዳት ለማድረስ አስበው ስለ እነሱ አንዳንድ መረጃ እንድንሰጣቸው ቢጠይቁን ለወንድሞቻችን ያለን ጽኑ ፍቅር ምንም ዓይነት መረጃ አሳልፈን እንዳንሰጥ ያደርገናል።—ምሳሌ 18:24 NW

‘ፍቅራዊ ደግነትን የሚከተል ሰው ሕይወትን’ ያገኛል

18, 19. ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ባለን ግንኙነት ረገድ የፍቅራዊ ደግነት ሕግ ከአንደበታችን ሊጠፋ የማይገባው ለምንድን ነው?

18 ጽኑ ፍቅር ከይሖዋ አገልጋዮች ጋር ባለን ግንኙነት ሁሉ በግልጽ መታየት ይኖርበታል። በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ በምንሆንበት ጊዜም እንኳ የፍቅራዊ ደግነት ሕግ ከአንደበታችን ሊጠፋ አይገባም። ይሖዋ፣ የእስራኤል ልጆች ፍቅራዊ ደግነት “እንደ ማለዳ ጉም” በንኖ በጠፋበት ጊዜ አዝኖ ነበር። (ሆሴዕ 6:4, 6) እሱ የሚደሰተው ፍቅራዊ ደግነትን አዘውትረው በሚያሳዩ ሰዎች ነው። ይሖዋ ፍቅራዊ ደግነትን የሚከታተሉ ሰዎችን እንዴት እንደሚባርክ እንመልከት።

19 ምሳሌ 21:21 “ጽድቅንና ፍቅርን [“ፍቅራዊ ደግነትን፣” NW] የሚከተል፤ ሕይወትን ብልጽግናንና ክብርን ያገኛል” ይላል። እንዲህ ዓይነት ሰው ከሚያገኛቸው በረከቶች መካከል ሕይወት ማለትም ዛሬ ታይቶ የሚጠፋ ሳይሆን የዘላለም ሕይወት ይገኝበታል። ይሖዋ እንዲህ ዓይነቱን ሰው ‘እውነተኛ የሆነውን ሕይወት አጥብቆ መያዝ’ እንዲችል ይረዳዋል። (1 ጢሞ. 6:12, 19) እንግዲያው ‘እርስ በርሳችን ምሕረትን [“ፍቅራዊ ደግነትን፣” NW]’ ለማሳየት የምንችለውን ሁሉ እናድርግ።—ዘካ. 7:9

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.1 ምሳሌ 19:22 (NW)፦ “ከሰው የሚፈለገው ነገር ፍቅራዊ ደግነት ነው፤ ከውሸታም ሰው ድሃ ይሻላል።”

^ አን.4 ፍቅራዊ ደግነት ከታማኝነት፣ ከፍቅርና ከደግነት የሚለየው እንዴት እንደሆነ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ግንቦት 15, 2002 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 12-13 እና 18-19 ተመልከት።

ልታብራራ ትችላለህ?

• ፍቅራዊ ደግነት ሲባል ምን ማለት ነው?

• በአንደበታችን ላይ የፍቅራዊ ደግነት ሕግ እንዲኖር ምን ሊረዳን ይችላል?

• ባለትዳሮች በአነጋገራቸው ጽኑ ፍቅር ሊያሳዩ የሚችሉት እንዴት ነው?

• ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ባለን ግንኙነት በአንደበታችን ላይ የፍቅራዊ ደግነት ሕግ እንዳለ የሚያሳየው ምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዳዊት ይሖዋን ስለ ፍቅራዊ ደግነቱ አወድሶታል

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቋሚ የሆነ የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራም አላችሁ?