በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘መሪያችሁ አንድ እሱም ክርስቶስ ነው’

‘መሪያችሁ አንድ እሱም ክርስቶስ ነው’

‘መሪያችሁ አንድ እሱም ክርስቶስ ነው’

“መሪያችሁ አንድ እሱም ክርስቶስ ስለሆነ ‘መሪ’ ተብላችሁ አትጠሩ።”—ማቴ. 23:10

1. የይሖዋ ምሥክሮች እንደ መሪያቸው አድርገው የሚቀበሉት ማንን ነው? ለምንስ?

የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ሰብዓዊ መሪዎች አሏቸው፤ የሮም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳትን፣ የምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ፓትሪያርኮችንና የሌሎች ሃይማኖቶች መሪዎችን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። የይሖዋ ምሥክሮች እንደ መሪያቸው አድርገው የሚከተሉት አንድም ሰው የለም። የማንም ሰው ደቀ መዝሙር ወይም ተከታይ አይደሉም። ይህ አቋማቸው ይሖዋ “እነሆ፤ እርሱን ለሕዝቦች ምስክር፣ መሪ፣ የጦር አዝማችም አድርጌዋለሁ” በማለት ስለ ልጁ ከተናገረው ትንቢታዊ መልእክት ጋር የሚስማማ ነው። (ኢሳ. 55:4) ዓለም አቀፉ የቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤና የቅቡዓኑ አጋሮች የሆኑት “ሌሎች በጎች” ይሖዋ ከሰጣቸው ሌላ ማንንም መሪ አድርገው አይቀበሉም። (ዮሐ. 10:16) ይህ አቋማቸው ኢየሱስ “መሪያችሁ አንድ እሱም ክርስቶስ [ነው]” ሲል ከተናገረው ሐሳብ ጋር ይስማማል።—ማቴ. 23:10

የእስራኤላውያን መንፈሳዊ አለቃ

2, 3. የአምላክ ልጅ ከእስራኤላውያን ጋር በተያያዘ ምን ከፍተኛ ሚና ነበረው?

2 የክርስቲያን ጉባኤ ከመመሥረቱ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት ይሖዋ አንድ መልአክ ሕዝቡን እስራኤልን እንዲመራ አድርጎ ነበር። ይሖዋ እስራኤላውያንን ከግብፅ ካወጣቸው በኋላ እንዲህ አላቸው፦ “በጕዞ ላይ ሳለህ የሚጠብቅህንና ወዳዘጋጀሁልህ ስፍራ የሚያስገባህን መልአክ በፊትህ ልኬልሃለሁ። በጥንቃቄ ተከተለው፤ የሚናገረውንም ልብ ብለህ አድምጠው፤ አታምፅበት። ስሜ በርሱ ላይ ነው።” (ዘፀ. 23:20, 21) ይሖዋ “ስሜ በርሱ ላይ ነው” ብሎ የተናገረለት ይህ መልአክ የአምላክ የበኩር ልጅ ነው ብሎ ማመን ምክንያታዊ ነው።

3 የአምላክ አንድያ ልጅ ሰው ሆኖ ከመወለዱ በፊት ይጠራ የነበረው ሚካኤል በሚለው ስም ሳይሆን አይቀርም። በዳንኤል መጽሐፍ ላይ ሚካኤል ‘የዳንኤል ሕዝብ’ ማለትም የእስራኤላውያን “አለቃ” ተብሎ ተጠርቷል። (ዳን. 10:21፤ 12:1) ደቀ መዝሙሩ ይሁዳ፣ ዳንኤል ከኖረበት ከረጅም ዘመን በፊት ሚካኤልን ከእስራኤላውያን ጋር አያይዞ ጠቅሶት ነበር። ሙሴ ከሞተ በኋላ ሰይጣን የሙሴን አስከሬን በሆነ መንገድ ለራሱ ዓላማ ሊያውለው ምናልባትም እስራኤላውያን የጣዖት አምልኮ እንዲፈጽሙ ለማነሳሳት ሊጠቀምበት አስቦ የነበረ ይመስላል። ሚካኤል ግን እንዲህ ያለው ሁኔታ እንዳይከሰት ተከላክሏል። ይሁዳ እንዲህ ብሏል፦ “የመላእክት አለቃ ሚካኤል የሙሴን ሥጋ በተመለከተ ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ ኃይለ ቃል በመጠቀም ሊፈርድበት አልደፈረም፤ ከዚህ ይልቅ ‘ይሖዋ ይገሥጽህ’ አለው።” (ይሁዳ 9) ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ደግሞ ማለትም እስራኤላውያን ኢያሪኮን ከመውረራቸው በፊት ለኢያሱ ተገልጦ መለኮታዊ ድጋፍ እንደማይለየው ያረጋገጠለት ‘የይሖዋ ሠራዊት አለቃ’ የተባለው ሚካኤል መሆን ይኖርበታል። (ኢያሱ 5:13-15ን አንብብ።) አንድ መልአክ ለነቢዩ ዳንኤል አስፈላጊ መልእክት ለማድረስ በሄደበት ጊዜ ኃይለኛ የሆነ አንድ ጋኔን ሲከለክለው የመላእክት አለቃ የሆነው ሚካኤል ሊረዳው መጥቶ ነበር።—ዳን. 10:5-7, 12-14

አስቀድሞ የተነገረለት መሪ መጣ

4. የመሲሑን መምጣት አስመልክቶ ምን ትንቢት ተነግሮ ነበር?

4 ይህ ሁኔታ ከመከሰቱ ቀደም ብሎ ይሖዋ “ገዥው [“መሪው፣” NW] መሲሕ” እንደሚመጣ የሚገልጸውን ትንቢት ለዳንኤል እንዲነግረው መልአኩ ገብርኤልን ልኮት ነበር። (ዳን. 9:21-25) * ልክ በተባለው ጊዜ ይኸውም በ29 ዓ.ም. በመጸው ወቅት ላይ ኢየሱስ በዮሐንስ ተጠመቀ። ኢየሱስ በተጠመቀበት ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በእሱ ላይ የወረደ ሲሆን በዚህ ወቅት ቅቡዕ ማለትም ክርስቶስ ወይም መሲሕ ሆነ። (ማቴ. 3:13-17፤ ዮሐ. 1:29-34፤ ገላ. 4:4) ኢየሱስ መሲሕ መሆኑ ተወዳዳሪ የማይገኝለት መሪ እንዲሆን ያደርገዋል።

5. ክርስቶስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት የመሪነት ሚና የተጫወተው እንዴት ነው?

5 ኢየሱስ በምድር ላይ አገልግሎቱን ማከናወን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ “መሪው መሲሕ” መሆኑን አስመሥክሯል። አገልግሎቱን ከጀመረ ከጥቂት ቀናት በኋላ ደቀ መዛሙርቱን መሰብሰብ የጀመረ ከመሆኑም በላይ የመጀመሪያውን ተአምር አከናውኗል። (ዮሐ. 1:35 እስከ 2:11) ኢየሱስ ስለ አምላክ መንግሥት ለመስበክ በፓለስቲና ምድር በተዘዋወረባቸው ጊዜያት ሁሉ ደቀ መዛሙርቱ አብረውት ይጓዙ ነበር። (ሉቃስ 8:1) የስብከቱን ሥራ እንዴት እንደሚያከናውኑ ያሠለጠናቸው ሲሆን በመስበኩና በማስተማሩ ሥራ ግንባር ቀደም በመሆን ግሩም ምሳሌ ትቶላቸዋል። (ሉቃስ 9:1-6) በአሁኑ ጊዜ ያሉ ክርስቲያን ሽማግሌዎችም በዚህ ረገድ ኢየሱስን መምሰል ይኖርባቸዋል።

6. ክርስቶስ እረኛና መሪ መሆኑን ያስመሠከረው በምን መንገድ ነው?

6 ኢየሱስ ራሱን ከአንድ አፍቃሪ እረኛ ጋር በማመሳሰል መሪ ሆኖ የሚያከናውነውን ሌላውን ተግባር ጠቁሟል። በምሥራቁ ዓለም የሚኖሩ እረኞች መንጎቻቸውን የሚመሩት ከፊት ከፊት በመሄድ ነው። በዊልያም ቶምሰን የተዘጋጀው ዘ ላንድ ኤንድ ዘ ቡክ የተሰኘው መጽሐፍ “እረኛው ከፊት ከፊት የሚሄደው መንገዱን ለማሳየት ብቻ ሳይሆን መንገዱ አመቺና በጎቹን ለአደጋ የማያጋልጥ መሆኑን ለማየት ጭምር ነው። . . . በትሩን ተጠቅሞ በጎቹን ወደ ለመለመ መስክ ይመራቸዋል እንዲሁም ከጠላት ይጠብቃቸዋል።” ኢየሱስ እውነተኛ እረኛና መሪ መሆኑን ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “እኔ ጥሩ እረኛ ነኝ፤ ጥሩ እረኛ ነፍሱን ለበጎቹ ሲል አሳልፎ ይሰጣል። በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ፤ እኔም አውቃቸዋለሁ፤ እነሱም ይከተሉኛል።” (ዮሐ. 10:11, 27) ኢየሱስ ልክ እንደተናገረው ለበጎቹ ሲል ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ ሰጥቷል፤ ይሖዋ ግን ከሞት በማስነሳት “መሪና አዳኝ” አድርጎታል።—ሥራ 5:31 የ1980 ትርጉም፤ ዕብ. 13:20

የክርስቲያን ጉባኤ የበላይ ተመልካች

7. ኢየሱስ የክርስቲያን ጉባኤን የሚመራው በምን አማካኝነት ነው?

7 ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ ከጥቂት ጊዜ በፊት ለደቀ መዛሙርቱ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል” ብሏቸው ነበር። (ማቴ. 28:18) ይሖዋ፣ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ክርስቲያናዊውን እውነት አጥብቀው እንዲይዙ ለመርዳት በኢየሱስ በኩል መንፈስ ቅዱስን ሰጥቷቸዋል። (ዮሐ. 15:26) ኢየሱስ ለጥንቶቹ ክርስቲያኖች ይህን መንፈስ የሰጠው በ33 ዓ.ም. በተከበረው የጴንጤቆስጤ ዕለት ነበር። (ሥራ 2:33) መንፈስ ቅዱስ በደቀ መዛሙርቱ ላይ መውረዱ የክርስቲያን ጉባኤ መቋቋሙን የሚያበስር ነበር። ይሖዋ በመላው ምድር የሚገኘውን ጉባኤ ከሰማይ ሆኖ እንዲመራ ለልጁ ሥልጣን ሰጥቶታል። (ኤፌሶን 1:22ን እና ቆላስይስ 1:13, 18ን አንብብ።) ኢየሱስ ‘እንዲገዙለት በተደረጉት’ መላእክት እየታገዘ በይሖዋ ቅዱስ መንፈስ አማካኝነት የክርስቲያን ጉባኤን ይመራል።—1 ጴጥ. 3:22

8. በመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ለመምራት እንደ መሣሪያ አድርጎ የተጠቀመው ማንን ነበር? በዛሬው ጊዜስ የሚጠቀመው ማንን ነው?

8 በተጨማሪም ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ለጉባኤው ‘ወንዶችን እንደ ስጦታ አድርጎ’ የሰጠ ሲሆን አንዳንዶቹ “እረኞችና አስተማሪዎች” ሆነው አገልግለው ነበር። (ኤፌ. 4:8, 11) ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾችን እንዲህ በማለት አሳስቧቸዋል፦ “ለራሳችሁም ሆነ . . . ጉባኤውን እንድትጠብቁ መንፈስ ቅዱስ የበላይ ተመልካቾች አድርጎ በላዩ ለሾማችሁ መንጋ ሁሉ ተጠንቀቁ።” (ሥራ 20:28) የክርስቲያን ጉባኤ በተቋቋመበት ወቅት ሁሉም የበላይ ተመልካቾች በመንፈስ የተቀቡ ነበሩ። ሐዋርያትና በኢየሩሳሌም የሚገኘው ጉባኤ ሽማግሌዎች የበላይ አካል ሆነው ያገለግሉ ነበር። ክርስቶስ የበላይ አካሉን በምድር ዙሪያ የሚገኘውን መላውን የቅቡዓን “ወንድሞች” ቡድን ለመምራት እንደ መሣሪያ አድርጎ ተጠቅሞበታል። (ዕብ. 2:11፤ ሥራ 16:4, 5) በዚህ የመጨረሻ ዘመን ክርስቶስ ‘ታማኝና ልባም ባሪያን’ እንዲሁም ይህን ባሪያ ወክሎ የሚሠራውንና ቅቡዕ ወንድሞችን ያቀፈውን የበላይ አካል “በንብረቱ ሁሉ ላይ” ይኸውም በምድር ላይ በሚገኙ ከመንግሥቱ ጋር በተያያዙ ነገሮች ሁሉ ላይ ሾሞታል። (ማቴ. 24:45-47) ቅቡዓን ክርስቲያኖችና አጋሮቻቸው የሆኑት ሌሎች በጎች በዘመናችን የሚገኘውን የበላይ አካል መመሪያ መከተል መሪያቸው የሆነውን የክርስቶስን መመሪያ እንደ መከተል አድርገው ይቆጥሩታል።

ክርስቶስ የስብከቱን ሥራ ጀመረ

9, 10. ክርስቶስ የመንግሥቱን ምሥራች በማሰራጨት ረገድ አመራር የሰጠው እንዴት ነበር?

9 ኢየሱስ ገና ከጅምሩ አንስቶ ዓለም አቀፉን የስብከትና የማስተማር ሥራ በቀጥታ መርቷል። የመንግሥቱ ምሥራች በምድር ላይ ለሚኖሩ ሰዎች ደረጃ በደረጃ እንዴት መዳረስ እንዳለበት መመሪያ ሰጥቷል። አገልግሎቱን ባከናወነባቸው ወቅቶች ለሐዋርያቱ የሚከተለውን መመሪያ ሰጥቷቸው ነበር፦ “ወደ አሕዛብ በሚወስደው መንገድ አትሂዱ፤ ወደ ሳምራውያን ከተማም አትግቡ፤ ከዚህ ይልቅ ከእስራኤል ቤት ወደጠፉት በጎች ብቻ ሂዱ። ሄዳችሁም ‘መንግሥተ ሰማያት ቀርቧል’ ብላችሁ ስበኩ።” (ማቴ. 10:5-7) ሐዋርያቱ ይህን መመሪያ በመከተል በተለይ በ33 ዓ.ም. ከተከበረው የጴንጤቆስጤ ዕለት ጀምሮ ለአይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት ለተቀየሩ ሰዎች በቅንዓት ሰብከዋል።—ሥራ 2:4, 5, 10, 11፤ 5:42፤ 6:7

10 ከጊዜ በኋላ ደግሞ ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት የመንግሥቱ የስብከት ሥራ ወደ ሳምራውያን ከዚያም አይሁድ ወዳልሆኑ ሌሎች ሰዎች እንዲስፋፋ አድርጓል። (ሥራ 8:5, 6, 14-17፤ 10:19-22, 44, 45) ኢየሱስ፣ ምሥራቹ ለአሕዛብ እንዲዳረስ ለማድረግ ሲል የጠርሴሱ ሳኦል ክርስቲያን እንዲሆን በቀጥታ አነጋግሮታል። ኢየሱስ ለደቀ መዝሙሩ ለአናንያ እንዲህ የሚል መመሪያ ሰጥቶት ነበር፦ “ተነስተህ ‘ቀጥተኛ’ ወደተባለው መንገድ ሂድ፤ በይሁዳም ቤት ሳኦል የሚባለውን የጠርሴስ ሰው ፈልግ። . . . ይህ ሰው በአሕዛብ እንዲሁም በነገሥታትና በእስራኤል ልጆች ፊት ስሜን እንዲሸከም ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ስለሆነ ወደ እሱ ሂድ።” (ሥራ 9:3-6, 10, 11, 15) “ይህ ሰው” ሐዋርያው ጳውሎስ ሆነ።—1 ጢሞ. 2:7

11. ክርስቶስ የስብከቱን ሥራ ለማስፋፋት በመንፈስ ቅዱስ የተጠቀመው እንዴት ነበር?

11 የመንግሥቱን ስብከት ሥራ አይሁድ ወዳልሆኑት አሕዛብ የሚዳረስበት ጊዜ ሲመጣ ጳውሎስ በትንሿ እስያና በአውሮፓ የሚስዮናዊ ጉዞ እንዲያደርግ መንፈስ ቅዱስ መመሪያ ሰጥቶታል። በሐዋርያት ሥራ ላይ የሚገኘው የሉቃስ ዘገባ እንዲህ ይላል፦ “እነዚህ [በሶርያ የምትገኘው የአንጾኪያ ጉባኤ ክርስቲያን ነቢያትና አስተማሪዎች] ይሖዋን እያገለገሉና እየጾሙ ሳሉ መንፈስ ቅዱስ ‘ከመካከላችሁ በርናባስንና ሳኦልን እኔ ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ’ አለ። እነሱም ጾመውና ጸልየው እጃቸውን ከጫኑባቸው በኋላ አሰናበቷቸው።” (ሥራ 13:2, 3) ኢየሱስ የጠርሴሱ ሳኦል በአሕዛብ ፊት የእሱን ስም እንዲሸከም በማሰብ የእሱ ‘የተመረጠ ዕቃ’ አድርጎ በቀጥታ መርጦታል፤ በመሆኑም የስብከቱ ሥራ በግለት እንዲካሄድ የሚረዳውን ይህን ምርጫ ያከናወነው የጉባኤው መሪ የሆነው ክርስቶስ ነው። ኢየሱስ የስብከቱን ሥራ ለመምራት መንፈስ ቅዱስን እንደሚጠቀም ጳውሎስ ሁለተኛ ሚስዮናዊ ጉዞውን ባደረገበት ወቅት በግልጽ ታይቷል። “የኢየሱስ መንፈስ” በሌላ አባባል ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ በኩል ለጳውሎስና አብረውት ለሚጓዙት ባልደረቦቹ መቼና የት መሄድ እንዳለባቸው አመራር እንደሰጣቸው ከዚያም በራእይ ተመርተው ወደ አውሮፓ እንደተጓዙ ዘገባው ይናገራል።—የሐዋርያት ሥራ 16:6-10ን አንብብ።

ኢየሱስ ለጉባኤው የሚሰጠው አመራር

12, 13. ክርስቶስ በእያንዳንዱ ጉባኤ ውስጥ የሚከናወነውን ነገር በቅርብ እንደሚከታተል የራእይ መጽሐፍ የሚያሳየው እንዴት ነው?

12 ኢየሱስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ቅቡዓን ተከታዮቹ በተሰባሰቡባቸው ጉባኤዎች ውስጥ የሚከናወነውን ነገር በቅርበት ይከታተል ነበር። እያንዳንዱ ጉባኤ የነበረበትን መንፈሳዊ ሁኔታ በደንብ ያውቅ ነበር። ራእይ ምዕራፍ 2⁠ን እና 3⁠ን በማንበብ ይህን ሁኔታ መረዳት እንችላለን። በትንሿ እስያ የሚገኙትን ሰባቱንም ጉባኤዎች በስማቸው ጠርቷቸዋል። (ራእይ 1:11) ኢየሱስ በወቅቱ በምድር ላይ የሚገኙት ሌሎች ጉባኤዎች የነበሩበትን መንፈሳዊ ሁኔታም ጠንቅቆ ያውቅ ነበር ብለን እንድናምን የሚያደርገን በቂ ምክንያት አለን።—ራእይ 2:23ን አንብብ።

13 ኢየሱስ ከሰባቱ ጉባኤዎች ውስጥ አንዳንዶቹን ስለ ጽናታቸው፣ በመከራ ወቅት ስላሳዩት ታማኝነት፣ ቃሉን በታማኝነት ስለጠበቁ እንዲሁም ከሃዲዎችን በተመለከተ ስለወሰዱት አቋም አመስግኗቸዋል። (ራእይ 2:2, 9, 13, 19፤ 3:8) በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ ጉባኤዎች ለእሱ የነበራቸው ፍቅር እንዲቀዘቅዝ በመፍቀዳቸው እንዲሁም ጣዖት አምልኮና ዝሙት የሚፈጽሙትን ብሎም በጉባኤ ውስጥ ክፍፍል የሚፈጥሩትን ሰዎች ችላ በማለታቸው ጠንከር ያለ ምክር ሰጥቷቸዋል። (ራእይ 2:4, 14, 15, 20፤ 3:15, 16) ኢየሱስ አፍቃሪ የሆነ መንፈሳዊ መሪ እንደመሆኑ መጠን ጠንካራ ምክር ለሰጣቸው ተከታዮቹ እንኳ እንዲህ ብሏቸዋል፦ “እኔ የምወዳቸውን ሁሉ እገሥጻለሁ እንዲሁም እቀጣለሁ። ስለዚህ ቀናተኛ ሁን፣ ንስሐም ግባ።” (ራእይ 3:19) ኢየሱስ በሰማይ የሚኖር ቢሆንም ደቀ መዛሙርቱ የተሰባሰቡባቸውን በምድር ላይ የሚገኙ ጉባኤዎች በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ይመራቸው ነበር። ኢየሱስ ለእነዚህ ጉባኤዎች በላከው በእያንዳንዱ መልእክት መደምደሚያ ላይ “መንፈስ ለጉባኤዎቹ የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ” ብሏል።—ራእይ 3:22

14-16. (ሀ) ኢየሱስ በምድር ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ሕዝቦች ደፋር መሪ መሆኑን ያስመሠከረው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ “እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ ድረስ ሁልጊዜ” ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ‘መሆኑ’ ምን ውጤት አስገኝቷል? (ሐ) በሚቀጥለው ርዕስ ስለ ምን ጉዳይ እንመረምራለን?

14 ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ብርቱ መልአክ የነበረው ሚካኤል (ኢየሱስ) እስራኤላውያንን ይመራ ነበር። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ኢየሱስ ለጥንቶቹ ደቀ መዛሙርት ደፋር መሪና አፍቃሪ እረኛ ሆኖ ነበር። ምድራዊ አገልግሎቱን ባከናወነበት ጊዜ የስብከቱን ሥራ ግንባር ቀደም ሆኖ ያከናውን ነበር። ከሞት ከተነሳ በኋላም የመንግሥቱን ምሥራች የማስፋፋቱን ሥራ በቅርብ እንደሚከታተል አሳይቷል።

15 ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት የስብከቱ ሥራ ደረጃ በደረጃ እስከ ምድር ዳር ድረስ እንዲስፋፋ የማድረግ ዓላማ ነበረው። ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በሚወርድበት ጊዜ ኃይል ትቀበላላችሁ፤ በኢየሩሳሌምም ሆነ በመላው ይሁዳ፣ በሰማርያ እንዲሁም እስከ ምድር ዳር ድረስ ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ።” (ሥራ 1:8፤ 1 ጴጥሮስ 1:12ን አንብብ።) በመጀመሪያው መቶ ዘመን በክርስቶስ አመራር አማካኝነት መጠነ ሰፊ ምሥክርነት መስጠት ተችሎ ነበር።—ቆላ. 1:23

16 ሆኖም ኢየሱስ የስብከቱ ሥራ እስከ ፍጻሜው ዘመን ድረስ እንደሚቀጥል ጠቁሟል። ኢየሱስ እንዲሰብኩና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ ለተከታዮቹ ተልእኮ ከሰጣቸው በኋላ “እኔ እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” በማለት ቃል ገብቶላቸዋል። (ማቴ. 28:19, 20) ክርስቶስ ከ1914 ጀምሮ ንጉሣዊ ሥልጣን ስለተሰጠው ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በአሁኑ ወቅት ከደቀ መዛሙርቱ “ጋር” ነው፤ እንዲሁም ገዢ ሆኖ እየመራቸው ነው። ከ1914 አንስቶ ያከናወነው ከፍተኛ እንቅስቃሴ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ይብራራል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.4 ይህን ትንቢት በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የዳንኤልን ትንቢት በትኩረት ተከታተል! የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 11 ተመልከት።

ለክለሳ ያህል

• የአምላክ ልጅ የእስራኤላውያን መሪ እንደነበር ያስመሠከረው እንዴት ነው?

• ክርስቶስ በምድር ያለውን ጉባኤውን ለመምራት በምን ይጠቀማል?

• ክርስቶስ ምሥራቹን ለማስፋፋት መመሪያ ይሰጥ የነበረው እንዴት ነው?

• ክርስቶስ የእያንዳንዱን ጉባኤ መንፈሳዊ ሁኔታ በቅርብ እንደሚከታተል የሚያሳየው ምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“መልአክ በፊትህ ልኬልሃለሁ”

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እንደ ቀድሞው ዘመን ሁሉ በዛሬው ጊዜም ክርስቶስ መንጋውን ለመጠበቅ ‘እንደ ስጦታ አድርጎ በሰጣቸው ወንዶች’ ይጠቀማል