በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሰበብ ማቅረብ—ይሖዋ እንዴት ይመለከተዋል?

ሰበብ ማቅረብ—ይሖዋ እንዴት ይመለከተዋል?

ሰበብ ማቅረብ​—ይሖዋ እንዴት ይመለከተዋል?

ሰውየው “ከእኔ ጋር እንድትኖር የሰጠኸኝ ሴት፣ እርሷ ከዛፉ ፍሬ ሰጠችኝና በላሁ” ሲል ሴቲቱ ደግሞ “እባብ አሳሳተኝና በላሁ” በማለት መለሰች። በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ረጅም ዘመን ያስቆጠረው ሰበብ የማቅረብ ዝንባሌ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን የሆኑት አዳምና ሔዋን ለአምላክ ይህን መልስ በሰጡበት ጊዜ ነበር።—ዘፍ. 3:12, 13

ይሖዋ በአዳምና በሔዋን ላይ ያስተላለፈው ፍርድ እነዚህ ባልና ሚስት ሆን ብለው ላደረጉት ነገር ያቀረቡትን ሰበብ እንዳልተቀበለ በግልጽ ያሳያል። (ዘፍ. 3:16-19) ታዲያ ከዚህ በመነሳት ይሖዋ ሰዎች የሚያቀርቡትን ምክንያት በሙሉ አይቀበልም ብለን መደምደም ይኖርብናል? ወይስ ደግሞ በእሱ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ምክንያቶች አሉ? ይህ ከሆነ ታዲያ ተቀባይነት ያለውን ምክንያትና ተቀባይነት የሌለውን ሰበብ ለይተን ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት በመጀመሪያ ሰበብ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ እንመልከት።

ሰበብ አንድ ነገር የተደረገው፣ ያልተደረገው ወይም የማይደረገው ለምን እንደሆነ ለመግለጽ የሚቀርብ ምክንያት ነው። ሰበብ አንድ ሰው ለፈጸመው ስህተት የሚቀርብ ተቀባይነት ያለው ምክንያት ሊሆን ይችላል፤ ይህ ደግሞ ግለሰቡ ቅጣት እንዲቀልለት ወይም ምሕረት እንዲያገኝ መሠረት የሚሆነውን እውነተኛ ይቅርታ ያስገኝለታል። ይሁን እንጂ አዳምና ሔዋን የሰጡት መልስ እንደሚያሳየው ሰበብ እውነተኛውን ምክንያት ለመደበቅ የሚቀርብ ማስተባበያ ወይም የውሸት ምክንያት ሊሆን ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ ሰበብ እንዲህ ዓይነት አሉታዊ ገጽታ ስላለው ሰዎች የሚቀርብላቸውን ሰበብ መጠራጠራቸው የተለመደ ነገር ነው።

በተለይ ደግሞ ለአምላክ ከምናቀርበው አገልግሎት ጋር በተያያዘ ሰበብ ስናቀርብ ‘የውሸት ምክንያት እያቀረብን ራሳችንን የምናታልል’ እንዳንሆን መጠንቀቅ አለብን። (ያዕ. 1:22) እንግዲያው ‘በጌታ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ነገር ምን እንደሆነ ምንጊዜም መርምረን እንድናረጋግጥ’ የሚረዱንን አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች እንመርምር።—ኤፌ. 5:10

አምላክ ምን እንድናደርግ ይጠብቅብናል?

የይሖዋ ሕዝቦች እንደመሆናችን መጠን በአምላክ ቃል ውስጥ በግልጽ የተቀመጡትን ትእዛዞች መፈጸም ይኖርብናል። ለምሳሌ ያህል፣ ክርስቶስ “ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” በማለት የሰጠውን ተልእኮ በዛሬው ጊዜ የሚገኙ እውነተኛ የክርስቶስ ተከታዮች ሁሉ ሊፈጽሙት ይገባል። (ማቴ. 28:19, 20) እንዲያውም ይህን ትእዛዝ መፈጸም በጣም አስፈላጊ ከመሆኑ የተነሳ ሐዋርያው ጳውሎስ “ምሥራቹን ባልሰብክ ግን ወዮልኝ” በማለት ተናግሯል።—1 ቆሮ. 9:16

ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን ለረጅም ጊዜ ከእኛ ጋር ሲያጠኑ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች የአምላክን መንግሥት ምሥራች እስካሁን መስበክ አልጀመሩም። (ማቴ. 24:14) ከዚህ ቀደም በስብከቱ ሥራ ይካፈሉ የነበሩ ሌሎች ደግሞ መስበካቸውን አቁመዋል። በስብከቱ ሥራ የማይካፈሉ ሰዎች አንዳንድ ጊዜ የሚያቀርቧቸው ሰበቦች ምንድን ናቸው? ይሖዋ፣ በጥንት ዘመን እሱ የሰጠውን ግልጽ ትእዛዝ ሰዎች ሳይታዘዙ ሲቀሩ ምን አድርጎ ነበር?

በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት የሌላቸው ሰበቦች

“በጣም ከባድ ነው።” በተለይ በተፈጥሯቸው ዓይናፋር የሆኑ ሰዎች በስብከቱ ሥራ መካፈል በጣም ከባድ እንደሆነ ሊሰማቸው ይችላል። ይሁንና ከዮናስ ታሪክ ምን መማር እንደሚቻል እንመልከት። ይሖዋ ለዮናስ ነነዌ በቅርብ የምትጠፋ መሆኑን እንዲያውጅ ተልእኮ ሰጥቶት የነበረ ሲሆን ዮናስ እንዲህ ያለውን መልእክት መናገር በጣም ከብዶት ነበር። ዮናስ የተሰጠውን ሥራ መፈጸም የከበደው ለምን እንደሆነ መረዳት አዳጋች አይደለም። ነነዌ የአሦር ዋና ከተማ የነበረች ሲሆን አሦራውያን ደግሞ በሚፈጽሙት ከፍተኛ የጭካኔ ድርጊት ይታወቁ ነበር። ዮናስ ‘በእነዚህ ሰዎች ፊት ቀርቤ መናገር የምችለው እንዴት ነው? ሰዎቹ ምን ያደርጉኝ ይሆን?’ የሚለው ጉዳይ አሳስቦት ሊሆን ይችላል። ብዙም ሳይቆይ ዮናስ ተልእኮውን ላለመፈጸም ወደ ሌላ አካባቢ ሸሽቶ ሄደ። ሆኖም ይሖዋ ዮናስ ያቀረበውን ሰበብ አልተቀበለም። ከዚህ ይልቅ ለነነዌ ሰዎች እንዲሰብክ በድጋሚ አዘዘው። በዚህ ጊዜ ዮናስ የተሰጠውን ሥራ በድፍረት የፈጸመ ሲሆን ይሖዋም ጥረቱን ባርኮለታል።—ዮናስ 1:1-3፤ 3:3, 4, 10

ምሥራቹን የመስበኩ ሥራ በጣም ከባድ እንደሆነ የሚሰማህ ከሆነ ‘በአምላክ ዘንድ ሁሉ ነገር እንደሚቻል’ አስታውስ። (ማር. 10:27) ይሖዋ አገልግሎትህን መፈጸም እንድትችል እንዲረዳህ ዘወትር ከጠየቅከው ብርታት እንደሚሰጥህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ፤ ከዚህም በላይ እንደምንም ብለህ ለመስበክ ጥረት የምታደርግ ከሆነ ይባርክሃል።—ሉቃስ 11:9-13

“የመስበክ ፍላጎት የለኝም።” ክርስቲያናዊ አገልግሎትህን የመፈጸም ልባዊ ፍላጎት ከሌለህ ምን ማድረግ ትችላለህ? ይሖዋ በውስጥህ በመሥራት ፍላጎት እንዲያድርብህ ማድረግ እንደሚችል አስታውስ። ጳውሎስ “እሱ ደስ ለሚሰኝበት ነገር ሲል ፍላጎት እንዲያድርባችሁም ሆነ ለተግባር እንድትነሳሱ በውስጣችሁ የሚሠራው አምላክ ነው” በማለት ተናግሯል። (ፊልጵ. 2:13) በመሆኑም ፈቃዱን የመፈጸም ፍላጎት እንዲያሳድርብህ ይሖዋን ልትለምነው ትችላለህ። ንጉሥ ዳዊትም ያደረገው ይህንኑ ነበር። ይሖዋን “በእውነትህ እንድመላለስ አድርገኝ” በማለት ተማጽኖታል። (መዝ. 25:4, 5 NW) አንተም እንደ ዳዊት ይሖዋ እሱን የሚያስደስተውን የማድረግ ፍላጎት እንዲያሳድርብህ በጸሎት አጥብቀህ ልትለምነው ትችላለህ።

አንዳንድ ጊዜ ሲደክመን ወይም ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር ሲያጋጥመን በመንግሥት አዳራሹ በሚደረገው ስብሰባ ላይ ለመገኘት ወይም በአገልግሎት ለመካፈል ራሳችንን ማስገደድ እንደሚኖርብን አይካድም። እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥመን ለይሖዋ እውነተኛ ፍቅር የለንም ብለን መደምደም ይኖርብናል? በፍጹም። በጥንት ዘመን የኖሩ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮችም ፈቃዱን ለመፈጸም ከፍተኛ ጥረት ማድረግ አስፈልጓቸው ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ጳውሎስ የአምላክን ትእዛዝ ለመፈጸም በምሳሌያዊ ሁኔታ ‘ሰውነቱን ይጎስም’ እንደነበር ተናግሯል። (1 ቆሮ. 9:26, 27) ስለዚህ እኛም የተሰጠንን አገልግሎት ለመፈጸም ራሳችንን ማስገደድ ቢኖርብንም እንኳ ይሖዋ እንደሚባርከን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ራሳችንን የምናስገድደው ትክክለኛ ምክንያት ስላለን ማለትም ይሖዋን ስለምንወድ ነው። እንዲህ በማድረግ ሰይጣን የአምላክ አገልጋዮች ፈተና ቢደርስባቸው እንደሚክዱት የሰነዘረው ክስ ሐሰት መሆኑ እናረጋግጣለን።—ኢዮብ 2:4

“በጣም ሥራ ይበዛብኛል።” በአገልግሎት የማትካፈለው በጣም ሥራ እንደሚበዛብህ ተሰምቶህ ከሆነ ቅድሚያ የምትሰጠው ለምን ነገር እንደሆነ ቆም ብለህ ማሰብህ በጣም አስፈላጊ ነው። ኢየሱስ “ከሁሉ አስቀድማችሁ የአምላክን መንግሥት . . . መፈለጋችሁን ቀጥሉ” በማለት ተናግሯል። (ማቴ. 6:33) አንተም ይህን መሠረታዊ ሥርዓት ለመከተል አኗኗርህን ቀላል ማድረግ አሊያም ለመዝናኛ የምታውለውን ጊዜ ቀንሰህ ለአገልግሎት ማዋል ያስፈልግህ ይሆናል። እርግጥ ነው፣ መዝናኛና ሌሎች የግል ጉዳዮቻችን አስፈላጊ እንደሆኑ አይካድም፤ ሆኖም አገልግሎታችንን ችላ እንድንል ሰበብ ሊሆኑ አይገባም። አንድ የአምላክ አገልጋይ በሕይወቱ ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጠው ከአምላክ መንግሥት ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች ነው።

“ጥሩ ችሎታ የለኝም።” የምሥራቹ አገልጋይ ለመሆን ብቃት እንደሌለህ ይሰማህ ይሆናል። በጥንት ጊዜ የኖሩ አንዳንድ የአምላክ ታማኝ አገልጋዮችም ይሖዋ የሰጣቸውን ሥራ ለመፈጸም ችሎታ እንደሌላቸው ተሰምቷቸው ነበር። ሙሴን እንደ ምሳሌ እንመልከት። ሙሴ ይሖዋ ግልጽ የሆነ ተልእኮ በሰጠው ጊዜ “ጌታ ሆይ፣ ቀድሞም ሆነ፣ አንተ ከባሪያህ ጋር ከተነጋገርህ ወዲህ፣ ከቶ አንደበተ ርቱዕ ሰው አይደለሁም። እኔ ኮልታፋና ንግግር የማልችል ሰው ነኝ” ብሎ ነበር። ይሖዋ ቢያበረታታውም እንኳ ሙሴ “ጌታ ሆይ ፤ እባክህ ሌላ ሰው ላክ” በማለት ተናግሯል። (ዘፀ. 4:10-13) በዚህ ጊዜ ይሖዋ ምን አደረገ?

ይሖዋ፣ ሙሴን የተሰጠውን ተልእኮ ከመፈጸም ነጻ እንዲሆን አላደረገውም። ከዚህ ይልቅ ሥራውን ማከናወን እንዲችል አሮንን መደበለት። (ዘፀ. 4:14-17) ከዚህም በላይ በቀጣዮቹ ዓመታት ይሖዋ ከሙሴ ጎን በመቆም የሰጠውን ማንኛውንም ሥራ በተሳካ ሁኔታ እንዲፈጽም የሚያስፈልገውን ድጋፍ ሁሉ አድርጎለታል። በዛሬው ጊዜም ይሖዋ ተሞክሮ ያላቸውን የእምነት አጋሮችህን በማነሳሳት አገልግሎትህን እንድትፈጽም እንዲረዱህ ሊያደርግ እንደሚችል እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። ከሁሉ በላይ ይሖዋ እንድንፈጽመው ለሰጠን ሥራ ብቁ እንደሚያደርገን የአምላክ ቃል ያረጋግጥልናል።—2 ቆሮ. 3:5 “በሕይወቴ በጣም የተደሰትኩባቸው ዓመታት” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

“አንድ ሰው ጎድቶኛል።” አንዳንዶች በሌሎች በመጎዳታቸው ምክንያት በአገልግሎት መካፈል ወይም በስብሰባዎች ላይ መገኘት ያቆሙ ሲሆን ይሖዋ በመንፈሳዊ ለመቀዝቀዛቸው የሚያቀርቡትን ይህን ሰበብ እንደሚቀበል ይሰማቸዋል። አንድ ሰው ሲጎዳን መበሳጨታችን ያለ ነገር ነው፤ ይሁንና ይህ ሁኔታ በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች ላይ መካፈላችንን ለማቆም አጥጋቢ ምክንያት ይሆናል? ጳውሎስና የእምነት አጋሩ የነበረው በርናባስ በመካከላቸው አለመግባባት ተነስቶ ‘ኃይለኛ ጭቅጭቅ በተፈጠረበት’ ወቅት ስሜታቸው ተጎድቶ ሊሆን ይችላል። (ሥራ 15:39) ይሁን እንጂ በዚህ የተነሳ በአገልግሎት መካፈላቸውን አቁመው ነበር? በፍጹም!

በተመሳሳይ አንተም በአንድ የእምነት አጋርህ ምክንያት ስሜትህ ሲጎዳ፣ ጠላትህ ፍጹም ያልሆነው ክርስቲያን ወንድምህ ሳይሆን ሊውጥህ የሚፈልገው ሰይጣን መሆኑን አስታውስ። ይሁንና ዲያብሎስን ‘በእምነት ጸንተህ በመቆም ብትቃወመው’ አንተን ለመዋጥ የሚያደርገው ጥረት አይሳካለትም። (1 ጴጥ. 5:8, 9፤ ገላ. 5:15) እንዲህ ዓይነት እምነት ካለህ በምንም ዓይነት ‘ለኀፍረት አትዳረግም።’—ሮም 9:33

ማድረግ የምንችለው ነገር ውስን ሲሆን

ከላይ ከቀረቡት ምሳሌዎች በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ምሥራቹን መስበክን ጨምሮ ይሖዋ የሰጠንን ግልጽ ትእዛዝ ላለመፈጸም ልናቀርበው የምንችለው አጥጋቢ የሆነ ቅዱስ ጽሑፋዊ ሰበብ የለም። ይሁን እንጂ አገልግሎታችንን በምንፈልገው መጠን እንዳንፈጽም አቅማችንን ሊገድቡብን የሚችሉ አጥጋቢ ምክንያቶች ይኖሩ ይሆናል። ሌሎች ቅዱስ ጽሑፋዊ ኃላፊነቶቻችን ለስብከቱ ሥራ ልናውለው የምንችለውን የጊዜ መጠን ሊቀንሱብን ይችላሉ። በተጨማሪም አልፎ አልፎ በጣም ሲደክመን ወይም በጣም ስንታመም በይሖዋ አገልግሎት የምንፈልገውን ያህል መካፈል አንችል ይሆናል። ይሁን እንጂ ይሖዋ የልባችንን ፍላጎት እንደሚያውቅ እንዲሁም ያለብንን የአቅም ገደብ ከግምት እንደሚያስገባ የአምላክ ቃል ያረጋግጥልናል።—መዝ. 103:14፤ 2 ቆሮ. 8:12

በመሆኑም ይህን ጉዳይ በተመለከተ በራሳችንም ሆነ በሌሎች ላይ ምክንያታዊ ያልሆነ ፍርድ እንዳንሰጥ መጠንቀቅ ያስፈልገናል። ሐዋርያው ጳውሎስ “በሌላው ሰው የቤት አገልጋይ ላይ የምትፈርድ አንተ ማን ነህ? እሱ ቢቆምም ሆነ ቢወድቅ ለጌታው ነው” በማለት ጽፏል። (ሮም 14:4) የራሳችንን ሁኔታ ከሌሎች ጋር ከማወዳደር ይልቅ ‘እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለአምላክ መልስ እንደምንሰጥ’ ማስታወስ ይኖርብናል። (ሮም 14:12፤ ገላ. 6:4, 5) ወደ ይሖዋ በጸሎት ቀርበን ምክንያታችንን ስንናገር እያንዳንዳችን “ሐቀኛ ሕሊና” ይዘን ይህን ማድረግ ይኖርብናል።—ዕብ. 13:18

ይሖዋን ማገልገል ደስታ ይሰጣል የምንለው ለምንድን ነው?

ያለንበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን፣ ይሖዋ የሚያወጣቸው መሥፈርቶች ምንጊዜም ምክንያታዊና ልንፈጽማቸው የምንችላቸው በመሆናቸው ሁላችንም በደስታ ልናገለግለው እንችላለን። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?

የአምላክ ቃል “ማድረግ እየቻልህ ለሚገባቸው መልካም ነገር ከማድረግ አትቈጠብ” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 3:27) ይህ ምሳሌ የአምላክን መሥፈርቶች በተመለከተ ምን እንድታስተውል አድርጎሃል? ይሖዋ የሚያዝህ ወንድምህ ማድረግ የሚችለውን ያህል እንድታደርግ ሳይሆን አንተ ‘ማድረግ የምትችለውን’ ያህል በማድረግ እንድታገለግለው ነው። አዎን፣ ማድረግ የምንችለው ነገር በጣም አነስተኛም ይሁን ብዙ እያንዳንዳችን ይሖዋን በሙሉ ልብ ማገልገል እንችላለን።—ሉቃስ 10:27፤ ቆላ. 3:23

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

 “በሕይወቴ በጣም የተደሰትኩባቸው ዓመታት”

በአካላችንም ሆነ በስሜታችን ላይ በደረሰው ነገር የተነሳ ከባድ የአቅም ገደብ ቢኖርብንም ይህ ሁኔታ በአገልግሎት ላይ የተሟላ ተሳትፎ እንዳናደርግ ያግደናል ብለን ለመደምደም መቸኮል አይኖርብንም። ይህን በምሳሌ ለማስረዳት፣ በካናዳ ይኖር የነበረው ኧርነስት የሚባል ወንድም ያደረገውን እንመልከት።

ኧርነስት የመናገር ችግር የነበረበት ከመሆኑም በላይ በጣም ዓይናፋር ነበር። ከባድ አደጋ ከደረሰበት በኋላ የተሰማራበትን የግንባታ ሥራ ለመተው ተገደደ። ምንም እንኳ የአካል ጉዳተኛ ቢሆንም ይህ ሁኔታ በአገልግሎት ላይ ሰፋ ያለ ጊዜ እንዳያሳልፍ አላገደውም ነበር። አስፋፊዎች ረዳት አቅኚ እንዲሆኑ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ የቀረበው ማበረታቻ ረዳት አቅኚ የመሆን ፍላጎት አሳደረበት። ይሁን እንጂ ረዳት አቅኚ ሆኖ ለማገልገል ብቁ እንዳልሆነ ተሰማው።

ረዳት አቅኚ መሆን ከእሱ አቅም በላይ እንደሆነ ራሱን ለማሳመን ስለፈለገ ለአንድ ወር ረዳት አቅኚ ሆኖ ለማገልገል ማመልከቻ አቀረበ። ይሁንና ከረዳት አቅኚዎች የሚጠበቀውን የሰዓት ግብ በተሳካ ሁኔታ እንዳሟላ ሲገነዘብ በጣም ገረመው። ሆኖም ‘እንደገና ብሞክር አይሳካልኝም’ ብሎ አሰበ። ስለዚህ ያሰበው ነገር ትክክል መሆኑን ለማረጋገጥ ለሁለተኛ ጊዜ አመለከተ፤ ይሁንና በዚህ ጊዜም ተሳካለት።

ኧርነስት ለአንድ ዓመት ያህል በረዳት አቅኚነት ቢያገለግልም “የዘወትር አቅኚ መሆን ግን ፈጽሞ አልችልም” የሚል አመለካከት ነበረው። አሁንም ይህ አመለካከቱ ትክክል መሆኑን ለማረጋገጥ ሲል የዘወትር አቅኚ ሆኖ ለማገልገል ማመልከቻ አቀረበ። ዘወትር አቅኚ ሆኖ ያገለገለበትን የመጀመሪያውን ዓመት በተሳካ ሁኔታ እንዳጠናቀቀ ሲገነዘብ በጣም ተደነቀ። ከዚያም በአቅኚነቱ ለመቀጠል የወሰነ ሲሆን የደረሰበት አደጋ ባስከተለው መዘዝ የተነሳ ሕይወቱ እስካለፈበት ጊዜ ድረስ ለሁለት ዓመት የዘወትር አቅኚ ሆኖ አገልግሏል፤ ይህም አቅኚነት የሚያስገኘውን ደስታ እንዲያጣጥም አድርጎታል። ይሁን እንጂ ከመሞቱ በፊት ሊጠይቁት ለሚመጡት ሰዎች ዓይኖቹ እንባ እያቀረሩ “አቅኚ ሆኜ ይሖዋን ያገለገልኩባቸው እነዚያ ዓመታት በሕይወቴ በጣም የተደሰትኩባቸው ዓመታት ነበሩ” በማለት ብዙ ጊዜ ይናገር ነበር።

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አገልግሎታችንን እንዳናከናውን መሰናክል ሊሆኑብን የሚችሉ ነገሮችን መወጣት እንችላለን

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ ሁኔታችን የሚፈቅደውን ሁሉ በማድረግ እሱን በሙሉ ነፍስ ስናገለግለው ይደሰታል