በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች የሚያንጹ እንዲሆኑ አስተዋጽኦ ታደርጋላችሁ?

ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች የሚያንጹ እንዲሆኑ አስተዋጽኦ ታደርጋላችሁ?

ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች የሚያንጹ እንዲሆኑ አስተዋጽኦ ታደርጋላችሁ?

“አንድ ላይ በምትሰበሰቡበት ጊዜ . . . ሁሉም ነገር ለማነጽ ይሁን።”—1 ቆሮ. 14:26

1. በ1 ቆሮንቶስ ምዕራፍ 14 መሠረት ከክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ዋነኛ ዓላማዎች አንዱ ምንድን ነው?

‘በጣም የሚያንጽ ስብሰባ ነበር!’ በመንግሥት አዳራሽ በሚደረገው ስብሰባ ላይ ከተገኘህ በኋላ እንዲህ ብለህ ታውቃለህ? ምንም ጥርጥር የለውም! በእርግጥም የጉባኤ ስብሰባዎች የብርታት ምንጭ ናቸው፤ ለነገሩ ይህ ምንም አያስገርምም። በጥንቶቹ ክርስቲያኖች ዘመን እንደነበረው ሁሉ በዛሬው ጊዜም ከስብሰባዎቻችን ዋነኛ ዓላማዎች አንዱ ተሰብሳቢዎቹ በሙሉ በመንፈሳዊ እንዲጠናከሩ መርዳት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው የመጀመሪያ ደብዳቤ ላይ ይህን ዓላማ እንዴት እንዳጎላው እንመልከት። ጳውሎስ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ የሚቀርበው እያንዳንዱ ክፍል ተመሳሳይ ዓላማ ሊኖረው እንደሚገባ ይኸውም “ጉባኤው እንዲታነጽ” ማድረግ እንደሚኖርበት በምዕራፍ 14 ላይ በተደጋጋሚ ጊዜ ገልጿል።—1 ቆሮንቶስ 14:3, 12, 26ን አንብብ። *

2. (ሀ) ስብሰባዎቻችን የሚያንጹ እንዲሆኑ የሚያደርጋቸው ምንድን ነው? (ለ) የትኛውን ጥያቄ እንመረምራለን?

2 ስብሰባዎቻችን የሚያንጹና ትምህርት ሰጪ እንዲሆኑ በዋነኝነት አስተዋጽኦ የሚያደርገው የአምላክ መንፈስ መሆኑን እንገነዘባለን። በመሆኑም እያንዳንዱን ስብሰባ ከመጀመራችን በፊት የሰማዩ አባታችን ይሖዋ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ስብሰባችንን እንዲባርክልን ከልብ የመነጨ ጸሎት እናቀርባለን። ያም ቢሆን ሁሉም የጉባኤው አባላት የስብሰባው ፕሮግራም የሚያንጽ እንዲሆን የተቻላቸውን ያህል አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚችሉ እናውቃለን። ታዲያ በየሳምንቱ በመንግሥት አዳራሾቻችን የሚደረጉት ስብሰባዎች ምንጊዜም በመንፈሳዊ የሚያድሱና የሚያበረታቱ እንዲሆኑ እያንዳንዳችን ምን ማድረግ እንችላለን?

3. ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ምን ያህል አስፈላጊ ናቸው?

3 የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት ስብሰባዎቻችንን የሚመሩት ወንድሞች በአእምሯቸው ሊይዟቸው የሚገቡ አንዳንድ ነጥቦችን እንመረምራለን። በተጨማሪም መላው ጉባኤ፣ ስብሰባዎቻችን ሁሉንም የሚያንጹ እንዲሆኑ ለማድረግ ምን ድርሻ ማበርከት እንደሚችል እንመለከታለን። ስብሰባዎቻችን ቅዱስ በመሆናቸው ለዚህ ጉዳይ ትልቅ ቦታ እንሰጠዋለን። በእርግጥም በስብሰባዎች ላይ መገኘትና ተሳትፎ ማድረግ ለይሖዋ የምናቀርበው አምልኮ ወሳኝ ገጽታዎች ናቸው።—መዝ. 26:12፤ 111:1፤ ኢሳ. 66:22, 23

መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የተዘጋጀ ስብሰባ

4, 5. የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ዓላማ ምንድን ነው?

4 ሁላችንም ብንሆን ከሳምንታዊው የመጠበቂያ ግንብ ጥናት የተሟላ ጥቅም ማግኘት እንፈልጋለን። እንግዲያው የዚህን ስብሰባ ዋነኛ ዓላማ በግልጽ ለመረዳት እንድንችል በመጠበቂያ ግንብ መጽሔትና በጥናት ርዕሶቹ ላይ የተደረጉትን አንዳንድ ለውጦች እስቲ መለስ ብለን እንመልከት።

5 ጥር 15, 2008 ከወጣው የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት የመጀመሪያው የጥናት እትም አንስቶ በሽፋን ገጹ ላይ ጉልህ ለውጥ ተደርጓል። ይህን ለውጥ ልብ ብለኸዋል? የያዝከውን መጽሔት ሽፋን እስቲ በደንብ ተመልከተው። በመጠበቂያ ማማው ግርጌ ተገልጦ የተቀመጠ መጽሐፍ ቅዱስ ይታያል። ይህ አዲስ ገጽታ የመጠበቂያ ግንብ ጥናት የምናደርግበትን ምክንያት ያጎላል። የጥናቱ ዓላማ በዚህ መጽሔት አማካኝነት መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ነው። በእርግጥም በሳምንታዊው የመጠበቂያ ግንብ ጥናታችን ላይ ጥንት በነህምያ ዘመን ይደረግ እንደነበረው የአምላክ ቃል ‘ይተነተናል’ እንዲሁም ‘ትርጉሙ’ ምን እንደሆነ ይብራራል።—ነህ. 8:8፤ ኢሳ. 54:13

6. (ሀ) በመጠበቂያ ግንብ ጥናት ረገድ ምን ማስተካከያዎች ተደርገዋል? (ለ) “አንብብ” ከሚሉት ጥቅሶች ጋር በተያያዘ ምን ማስታወስ ይኖርብናል?

6 ዋነኛው መማሪያ መጽሐፋችን መጽሐፍ ቅዱስ በመሆኑ በመጠበቂያ ግንብ ጥናት ረገድ አንዳንድ ማስተካከያዎች ተደርገዋል። በጥናት ርዕሶቹ ውስጥ ከተወሰኑ ጥቅሶች አጠገብ “አንብብ” የሚል መመሪያ ተጨምሯል። በስብሰባው ወቅት እነዚህ ጥቅሶች ሲነበቡ ሁላችንም በራሳችን መጽሐፍ ቅዱስ እንድንከታተል ማበረታቻ ተሰጥቶናል። (ሥራ 17:11) ይህ ምን ጥቅም አለው? የአምላክን ምክር በራሳችን መጽሐፍ ቅዱስ ላይ መመልከታችን ልባችን በጥልቅ እንዲነካ ያደርጋል። (ዕብ. 4:12) ስብሰባውን የሚመራው ወንድም እንደነዚህ ያሉት ጥቅሶች ከመነበባቸው በፊት ሁሉም ተሰብሳቢዎች ጥቅሶቹን አውጥተው መከታተል እንዲችሉ በቂ ጊዜ መስጠት ይኖርበታል።

እምነታችንን ለመግለጽ የሚያስችለን ተጨማሪ ጊዜ

7. በመጠበቂያ ግንብ ጥናት ወቅት ምን አጋጣሚዎች አሉን?

7 ከመጠበቂያ ግንብ የጥናት ርዕሶች ጋር በተያያዘ የተደረገው ሌላ ማስተካከያ ርዝመታቸው ነው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አጠር እንዲሉ ተደርጓል። በመሆኑም በመጠበቂያ ግንብ ጥናት ወቅት አንቀጾቹን ለማንበብ የሚውለው ጊዜ መቀነሱ ተሰብሳቢዎች ሐሳብ ለመስጠት ተጨማሪ ጊዜ እንዲያገኙ አድርጓል። ይህ መሆኑ ብዙ የጉባኤው አባላት በመጽሔቱ ላይ ለሚገኘው ጥያቄ መልስ በመስጠት፣ ጥቅሶቹን ከነጥቡ ጋር በማዛመድ፣ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች መከተል የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች የሚያሳይ ተሞክሮ በመናገር ወይም በሌሎች መንገዶች እምነታቸውን መግለጽ እንዲችሉ አጋጣሚ ሰጥቷቸዋል። በሥዕላዊ መግለጫዎቹ ላይ ለመወያየት የተወሰነ ጊዜ መመደብም አስፈላጊ ነው።—መዝሙር 22:22⁠ን፤ 35:18⁠ን እና 40:9ን አንብብ።

8, 9. የመጠበቂያ ግንብ ጥናት የሚመራው ወንድም ድርሻ ምንድን ነው?

8 ይሁንና የተለያዩ ሐሳቦችን ለመስጠት አጋጣሚ የሚከፍተውን ይህን ተጨማሪ ጊዜ ማግኘት የሚቻለው በመጠበቂያ ግንብ ጥናት ወቅት ተሰብሳቢዎች አጠር ያለ ሐሳብ የሚሰጡ ከሆነና የሚመራው ወንድምም ብዙ ሐሳብ ከመስጠት የሚቆጠብ ከሆነ ነው። ታዲያ ስብሰባው ለሁሉም የሚያንጽ እንዲሆን ጥናቱን የሚመራው ወንድም እሱም ሆነ የጉባኤው አባላት የሚሰጡት ሐሳብ ርዝመት ሚዛኑን እንዲጠብቅ ለማድረግ ምን ሊረዳው ይችላል?

9 ይህን ጥያቄ ለመመለስ አንድ ምሳሌ እንመልከት። በጥሩ ሁኔታ የሚመራ የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ለዓይን እንደሚማርክ እቅፍ አበባ ነው። በአንድ ትልቅ እቅፍ አበባ ውስጥ የተለያዩ አበቦች እንደሚገኙ ሁሉ የመጠበቂያ ግንብ ጥናትም ተሰብሳቢዎች የሚሰጡትን የተለያየ ሐሳብ ያካተተ ነው። በእቅፍ አበባው ውስጥ ያሉት አበቦች መጠንና ቀለም የተለያየ እንደሆነ ሁሉ በስብሰባ ወቅት ተሰብሳቢዎች የሚሰጧቸው ሐሳቦች ርዝመትም ሆነ የሚቀርቡበት መንገድ የተለያየ ነው። ታዲያ የሚመራው ወንድም ድርሻ ምንድን ነው? የሚመራው ወንድም አልፎ አልፎ የሚሰጠው ሐሳብ እቅፍ አበባው ላይ ጣል ጣል እንደሚደረጉት ማሳመሪያዎች ነው። እነዚህ ማሳመሪያዎች በጣም እንዲበዙ አይደረግም፤ ከዚህ ይልቅ አበቦቹ አንድ ላይ ሲታዩ ውበት እንዲኖራቸው በሚያደርግ መንገድ አለፍ አለፍ ተደርገው ይሰካሉ። በተመሳሳይም ጥናቱን የሚመራው ወንድም እሱ ብቻ ተናጋሪ መሆን እንደሌለበት ይልቁንም የእሱ ሚና ጉባኤው በሚያቀርበው ሐሳብ ላይ ማሟያ የሚሆኑ ነጥቦችን መጨመር እንደሆነ ማስታወስ ይኖርበታል። በእርግጥም ተሰብሳቢዎቹ የሚሰጧቸው ልዩ ልዩ ሐሳቦችና የሚመራው ወንድም አስፈላጊ በሆኑ ቦታዎች ላይ የሚጨምራቸው ጥቂት ነጥቦች አንድ ላይ ሲቀናጁ ውብ እንደሆነ እቅፍ አበባ መላውን ጉባኤ የሚያስደስቱ ይሆናሉ።

“የምስጋና መሥዋዕት ዘወትር ለአምላክ እናቅርብ”

10. የጥንቶቹ ክርስቲያኖች የጉባኤ ስብሰባዎችን እንዴት አድርገው ይመለከቷቸው ነበር?

10 ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ 14:26-33 ላይ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችን በተመለከተ የሰጠው መግለጫ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እነዚህ ስብሰባዎች እንዴት ይመሩ እንደነበር የተወሰነ ግንዛቤ ይሰጠናል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር ስለዚህ ጥቅስ ሐሳብ ሲሰጡ እንዲህ ብለዋል፦ “የጥንቶቹን የቤተ ክርስቲያን ሥርዓቶች በተመለከተ ትኩረታችንን የሚስበው ነገር፣ በስብሰባው ላይ የሚገኝ እያንዳንዱ ግለሰብ ማለት ይቻላል የተወሰነ አስተዋጽኦ የማበርከት መብትም ሆነ ግዴታ እንዳለው ይሰማው የነበረ መሆኑ ነው። አንድ ሰው በስብሰባ ላይ የሚገኘው አዳማጭ ብቻ ለመሆን ብሎ አይደለም፤ የሚመጣው ለመቀበል ብቻ ሳይሆን ለመስጠትም ጭምር ነበር።” በእርግጥም የጥንቶቹ ክርስቲያኖች የጉባኤ ስብሰባዎችን እምነታቸውን ለመግለጽ እንደሚያስችሉ አጋጣሚዎች አድርገው ይመለከቷቸው ነበር።—ሮም 10:10

11. (ሀ) ስብሰባዎች የሚያንጹ እንዲሆኑ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክተው ምንድን ነው? እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) የትኞቹን ነጥቦች ተግባራዊ ማድረጋችን በስብሰባዎች ላይ የምንሰጠውን ሐሳብ ለማሻሻል ይረዳናል? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)

11 በስብሰባዎች ላይ እምነታችንን መግለጻችን “ጉባኤው እንዲታነጽ” ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል። በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ለረጅም ዓመታት የተገኘን ቢሆንም እንኳ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የሚሰጧቸውን ሐሳቦች ማዳመጥ ከፍተኛ ደስታ እንደሚያስገኝ ሳትስማማ አትቀርም። በዕድሜ የገፉ አንድ ታማኝ ወንድም የሚሰጡትን ከልብ የመነጨ ሐሳብ መስማት ልዩ ስሜት ይፈጥርብናል፤ አንድ አሳቢ የጉባኤ ሽማግሌ ማስተዋል የታከለበት መልስ ሲሰጥ መንፈሳችን ይታደሳል፤ አንድ ትንሽ ልጅ ይሖዋን ከልቡ እንደሚወደው የሚያሳይ ሐሳብ በልጅ አንደበቱ ሲሰጥ በጣም ደስ ይለናል። ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው በጉባኤ ላይ ሐሳብ በመስጠት ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች የሚያንጹ እንዲሆኑ ሁላችንም የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናደርጋለን። *

12. (ሀ) ከሙሴና ከኤርምያስ ሁኔታ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን? (ለ) ሐሳብ ከመስጠት ጋር በተያያዘ ጸሎት ምን ሚና ይጫወታል?

12 ይሁንና ዓይናፋር የሆኑ ሰዎች በጉባኤ ሐሳብ መስጠት ተራራ ሊሆንባቸው ይችላል። አንተም እንደዚህ የሚሰማህ ከሆነ ስሜትህን የሚጋሩ ብዙ ሰዎች እንዳሉ ማስታወስህ ጠቃሚ ነው። እንደ ሙሴና ኤርምያስ ያሉ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች እንኳ በሕዝብ ፊት መናገር እንደሚያስፈራቸው ገልጸዋል። (ዘፀ. 4:10፤ ኤር. 1:6) ሆኖም ይሖዋ ለእነዚህ የጥንት አገልጋዮቹ በሕዝብ ፊት እሱን ለማወደስ የሚያስችላቸውን ድፍረት እንደሰጣቸው ሁሉ አንተም የምስጋና መሥዋዕት ማቅረብ እንድትችል ይረዳሃል። (ዕብራውያን 13:15ን አንብብ።) በጉባኤ ውስጥ ሐሳብ ለመስጠት የሚሰማህን ፍርሃት ለማሸነፍ የይሖዋን እርዳታ ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ለስብሰባ በሚገባ ተዘጋጅ። ከዚያም ወደ መንግሥት አዳራሽ ከመሄድህ በፊት ወደ ይሖዋ ጸልይ፤ በተለይ ደግሞ ሐሳብ ለመስጠት የሚያስችልህን ድፍረት እንዲሰጥህ ለምነው። (ፊልጵ. 4:6) የምትጠይቀው ነገር ‘ከፈቃዱ ጋር የሚስማማ’ በመሆኑ ይሖዋ ጸሎትህን እንደሚመልስልህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ።—1 ዮሐ. 5:14፤ ምሳሌ 15:29

‘ለማነጽ፣ ለማበረታታትና ለማጽናናት’ የተዘጋጁ ስብስባዎች

13. (ሀ) ስብሰባዎቻችን በተሰብሳቢዎቹ ላይ ምን በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይገባል? (ለ) ሽማግሌዎች በተለይ የትኛውን ጥያቄ ትኩረት ሊሰጡት ይገባል?

13 ጳውሎስ የጉባኤ ስብሰባዎች ዋነኛ ዓላማ ተሰብሳቢዎቹን ‘ማነጽ፣ ማበረታታትና ማጽናናት’ እንደሆነ ገልጿል። * (1 ቆሮ. 14:3) በዛሬው ጊዜ ያሉ የጉባኤ ሽማግሌዎች በስብሰባዎች ላይ የሚያቀርቧቸው ክፍሎች ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን የሚያንጹና የሚያጽናኑ እንዲሆኑ ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው? ይህን ለመመለስ ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ ብዙም ሳይቆይ ከተከታዮቹ ጋር ያደረገውን ስብሰባ እንመልከት።

14. (ሀ) ኢየሱስ ከተከታዮቹ ጋር ስብሰባ ከማድረጉ በፊት ምን ተከስቶ ነበር? (ለ) ሐዋርያቱ ‘ኢየሱስ ቀርቦ’ ሲያነጋግራቸው እፎይታ የተሰማቸው ለምን ሊሆን ይችላል?

14 በመጀመሪያ ከዚህ ስብሰባ በፊት የነበሩትን ሁኔታዎች እንመልከት። ኢየሱስ ከመገደሉ ጥቂት ቀደም ብሎ ሐዋርያቱ ‘ጥለውት የሸሹ’ ሲሆን አስቀድሞ እንደተነገረው ‘ሁሉም ወደየቤታቸው ተበታተኑ።’ (ማር. 14:50፤ ዮሐ. 16:32) ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ግን በሐዘን የተዋጡትን ሐዋርያቱን በአንድ ለየት ያለ ስብሰባ ላይ እንዲገኙ ጋበዛቸው። * ከዚያም “አሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርት በገሊላ ወደሚገኘው፣ ኢየሱስ ወዳመለከታቸው ተራራ ሄዱ።” እዚያ ሲደርሱም ‘ኢየሱስ ቀርቦ’ አነጋገራቸው። (ማቴ. 28:10, 16, 18) ሐዋርያቱ ኢየሱስ ቅድሚያውን ወስዶ ስላነጋገራቸው ትልቅ እፎይታ ተሰምቷቸው እንደሚሆን መገመት ትችላለህ! ኢየሱስ በስብሰባው ላይ ምን ነጥቦችን አንስቶ ይሆን?

15. (ሀ) ኢየሱስ በስብሰባው ወቅት ምን ነጥቦችን አነሳ? ምንስ አላደረገም? (ለ) ስብሰባው በሐዋርያቱ ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድሯል?

15 ኢየሱስ ንግግሩን የጀመረው “ሥልጣን ሁሉ . . . ተሰጥቶኛል” በማለት ነበር። ከዚያም ለተከታዮቹ “ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” በማለት ተልዕኮ ሰጣቸው። በመጨረሻም “እኔ እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” በማለት ፍቅር የሚንጸባረቅበት ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል። (ማቴ. 28:18-20) ሆኖም ኢየሱስ በዚህ ወቅት ምን እንዳላደረገ አስተዋልክ? በዚህ ስብሰባ ላይ ለሐዋርያቱ እርማት አልሰጣቸውም፤ አሊያም ደግሞ ውስጣዊ ዝንባሌያቸውን እንደሚጠራጠር የሚያሳይ ወይም እምነታቸው ደክሞ የነበረበትን ወቅት በማስታወስ ይበልጥ በጥፋተኝነት ስሜት እንዲዋጡ የሚያደርግ ነገር አልተናገረም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ ለተከታዮቹ ከባድ ኃላፊነት በመስጠት እሱም ሆነ አባቱ እንደሚወዷቸው በድጋሚ አረጋግጦላቸዋል። ኢየሱስ ያደረገው ነገር በሐዋርያቱ ላይ ምን ተጽዕኖ አሳደረባቸው? በእጅጉ በመታነጻቸው፣ በመበረታታታቸውና በመጽናናታቸው ይህ ስብሰባ ከተካሄደ ብዙም ሳይቆይ ‘ምሥራቹን ማስተማራቸውንና ማወጃቸውን መቀጠል’ ችለዋል።—ሥራ 5:42

16. በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያን ሽማግሌዎች፣ ስብሰባዎች መንፈስን የሚያድሱ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ የሚከተሉት እንዴት ነው?

16 እንደ ኢየሱስ ሁሉ በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ሽማግሌዎችም ስብሰባዎችን የሚመለከቷቸው ይሖዋ ለሕዝቡ የማይነጥፍ ፍቅር እንዳለው ለእምነት ባልንጀሮቻቸው ለማረጋገጥ እንደሚያስችሏቸው አጋጣሚዎች አድርገው ነው። (ሮም 8:38, 39) በመሆኑም ሽማግሌዎች በስብሰባዎች ላይ ክፍል ሲያቀርቡ ትኩረት የሚያደርጉት በወንድሞቻቸው ጠንካራ ጎኖች እንጂ በድክመቶቻቸው ላይ አይደለም። የወንድሞቻቸውን ውስጣዊ ዝንባሌ አይጠራጠሩም። ከዚህ ይልቅ ሽማግሌዎች፣ የእምነት ባልንጀሮቻቸው ይሖዋን እንደሚወዱና ትክክለኛውን ነገር ለማድረግ እንደሚጥሩ ያላቸውን እምነት የሚያሳይ ነገር ይናገራሉ። (1 ተሰ. 4:1, 9-12) እርግጥ ነው፣ ሽማግሌዎች ለጉባኤው በአጠቃላይ እርማት መስጠት የሚያስፈልጋቸው ጊዜ ሊኖር ይችላል፤ መስተካከል የሚያስፈልጋቸው ጥቂት ግለሰቦች ብቻ ከሆኑ ግን ብዙውን ጊዜ እንዲህ ያለው ምክር ለሚመለከታቸው ሰዎች በግለሰብ ደረጃ ቢሰጥ የተሻለ ነው። (ገላ. 6:1፤ 2 ጢሞ. 2:24-26) ሽማግሌዎች ለጉባኤው በአጠቃላይ ንግግር ሲያቀርቡ ተገቢ በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ ምስጋናቸውን ለመግለጽ ይጥራሉ። (ኢሳ. 32:2) ስብሰባው ሲያበቃ ሁሉም ተሰብሳቢዎች መንፈሳቸው እንደታደሰና እንደተነቃቁ እንዲሰማቸው በሚያደርግ መንገድ ለመናገር ጥረት ያደርጋሉ።—ማቴ. 11:28፤ ሥራ 15:32

የእረፍት ቦታ

17. (ሀ) ከምንጊዜውም በላይ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን የእረፍት ቦታ መሆናቸው አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ስብሰባዎች የሚያንጹ እንዲሆኑ አንተ በግለሰብ ደረጃ ምን ማድረግ ትችላለህ? (“ስብሰባዎቻችን አንተንም ሆነ ሌሎችን የሚያንጹ እንዲሆኑ ማድረግ የምትችልባቸው አሥር መንገዶች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

17 የሰይጣን ዓለም ከምንጊዜውም በላይ አስጨናቂ እየሆነ ሲሄድ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ሁላችንም መጽናኛ የምናገኝበት የእረፍት ቦታ ይሆኑልናል። (1 ተሰ. 5:11) ከተወሰኑ ዓመታት በፊት አንዲት እህትና ባለቤቷ ከባድ መከራ አጋጥሟቸው ነበር፤ እህት እንዲህ ብላለች፦ “መንግሥት አዳራሽ ስንሆን በይሖዋ እቅፍ ውስጥ እንዳለን ሆኖ ይሰማን ነበር። በዚያ በምንሆንበት ጊዜ ክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በዙሪያችን ስለሚሆኑ ሸክማችንን በይሖዋ ላይ እንደጣልን ይሰማን ነበር፤ ይህ ደግሞ በተወሰነ መጠን ውስጣችን እንዲረጋጋ አድርጎናል።” (መዝ. 55:22) በስብሰባዎቻችን ላይ የሚገኙ ሁሉ ልክ እንደዚህች እህት ማበረታቻና ማጽናኛ እንዳገኙ እንዲሰማቸው ምኞታችን ነው! ይህ እንዲሆን ክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችንን የሚያንጹ ለማድረግ ምንጊዜም የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናበርክት።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.1 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይደረጉ በነበሩት ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ከሚካሄዱት ነገሮች አንዳንዶቹ የሚቀሩበት ጊዜ እንደሚመጣ ትንቢት ተነግሮ ነበር። ለምሳሌ፣ “በልሳን” መናገር ወይም “ትንቢት” መናገር ቀርቷል። (1 ቆሮ. 13:8፤ 14:5) ያም ሆኖ ጳውሎስ የሰጠው መመሪያ በዛሬው ጊዜ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች እንዴት መካሄድ እንዳለባቸው ይበልጥ ለመረዳት ያስችለናል።

^ አን.11 በስብሰባዎች ላይ የምንሰጠውን ሐሳብ ለማሻሻል የሚረዱ ነጥቦች ለማግኘት የመስከረም 1, 2003 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 19-22 ተመልከት።

^ አን.13 በቫይን የተዘጋጀው ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ኦልድ ኤንድ ኒው ቴስታመንት ዎርድስ “ማበረታታት” እና “ማጽናናት” በሚሉት ቃላት መካከል ስላለው ልዩነት ሲያብራራ “ማጽናናት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “[ከማበረታታት] ይበልጥ ልባዊ አሳቢነት” እንደሚንጸባረቅበት ገልጿል።—ከዮሐንስ 11:19 ጋር አወዳድር።

^ አን.14 ከጊዜ በኋላ ጳውሎስ፣ ኢየሱስ “ከአምስት መቶ ለሚበልጡ ወንድሞች [እንደታየ]” የተናገረው ይህን ስብሰባ በማስመልከት ሊሆን ይችላል።—1 ቆሮ. 15:6

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ምን ያህል አስፈላጊ ናቸው?

• በስብሰባዎች ላይ የሚሰጡት ሐሳቦች “ጉባኤው እንዲታነጽ” አስተዋጽኦ ያደርጋሉ የምንለው ለምንድን ነው?

• ኢየሱስ ከተከታዮቹ ጋር ካደረገው ስብሰባ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 22 እና 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

ስብሰባዎቻችን አንተንም ሆነ ሌሎችን የሚያንጹ እንዲሆኑ ማድረግ የምትችልባቸው አሥር መንገዶች

አስቀድመህ ተዘጋጅ። በመንግሥት አዳራሽ የሚወሰደውን ክፍል አስቀድመህ ከተዘጋጀህ ትኩረትህ ሳይከፋፈል ማዳመጥ የምትችል ከመሆኑም ሌላ ስብሰባው በጥልቅ ይነካሃል።

አዘውትረህ በስብሰባዎች ላይ ተገኝ። በርከት ያሉ ተሰብሳቢዎች ስናይ ሁላችንም እንበረታታለን፤ በመሆኑም የአንተ መኖር ለውጥ ያመጣል።

በጊዜ ድረስ። ስብሰባው ከመጀመሩ በፊት ቦታህን ከያዝክ ለይሖዋ የምናቀርበው አምልኮ ክፍል በሆኑት በመክፈቻው መዝሙርና በጸሎቱ መካፈል ትችላለህ።

የሚያስፈልጉህን ጽሑፎች ይዘህ ሂድ። በስብሰባው ወቅት መከታተልና ትምህርቱን ይበልጥ መረዳት እንድትችል መጽሐፍ ቅዱስህንና የሚያስፈልጉህን ጽሑፎች ይዘህ ሂድ።

ትኩረት የሚሰርቁ ነገሮችን አስወግድ። ለምሳሌ ያህል፣ በሞባይል የሚደርሱህን መልእክቶች በስብሰባ ወቅት ከማንበብ ይልቅ ስብሰባው እስኪያልቅ ማቆየት ትችላለህ። በዚህ መንገድ የግል ጉዳዮችህ ለመንፈሳዊ ጉዳዮች የምትሰጠውን ጊዜ እንዳይሻሙብህ ታደርጋለህ።

ተሳትፎ አድርግ። ብዙዎች ተሳትፎ በማድረግ እምነታቸውን ሲገልጹ በርካታ አድማጮች ይበረታታሉ እንዲሁም ይታነጻሉ።

አጠር ያለ መልስ ስጥ። እንዲህ ማድረግህ በተቻለ መጠን ብዙዎች ሐሳብ እንዲሰጡ አጋጣሚ ይከፍታል።

የተሰጠህን ክፍል በሚገባ አቅርብ። በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ወይም በአገልግሎት ስብሰባ ላይ ክፍል ሲሰጥህ በሚገባ ተዘጋጅ፣ አስቀድመህ ተለማመድ እንዲሁም ክፍልህን ሳታቀርብ ላለመቅረት የምትችለውን ሁሉ አድርግ።

አመስግን። በስብሰባው ላይ ክፍል የነበራቸውን ወይም ሐሳብ የሰጡትን ላደረጉት ጥረት አመስግናቸው።

ከወንድሞች ጋር ጊዜ አሳልፍ። ስብሰባው ከመጀመሩ በፊት ወይም ካበቃ በኋላ ደግነት በሚንጸባረቅበት መንገድ ለወንድሞች ሰላምታ መስጠትና ከእነሱ ጋር የሚያንጽ ጭውውት ማድረግ በስብሰባ ላይ መገኘት ይበልጥ አስደሳችና ጠቃሚ እንዲሆን ያደርጋል።