በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“የተለያዩ ሰዎችን ልብ ለመንካት አስችሎኛል”

“የተለያዩ ሰዎችን ልብ ለመንካት አስችሎኛል”

“የተለያዩ ሰዎችን ልብ ለመንካት አስችሎኛል”

በደቡብ ብራዚል የምትገኘው ፖርቶ አሌግሪ የተባለች ከተማ ከጥቂት ዓመታት በፊት በማኅበራዊ ሕይወት ዙሪያ የሚያጠነጥን አንድ ዓለም አቀፍ ስብሰባ አስተናግዳ ነበር። ከ135 አገሮች የመጡ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በዚህ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ነበር። በፖርቶ አሌግሪ በሚገኘው ጉባኤ ውስጥ ያሉ አንዳንድ አስፋፊዎች በእረፍት ሰዓት ወደ እነዚህ እንግዶች በመቅረብ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት አካፍለዋቸዋል። ታዲያ የእነዚህን ሰዎች ቋንቋ መናገር ሳይችሉ መልእክቱን ማካፈል የቻሉት እንዴት ነው?

ኤልሳቤት የተባለች አቅኚ እንደገለጸችው ለእነዚህ ሰዎች መልእክቱን ማካፈል የቻሉት “ለሰዎች ሁሉ የሚሆን ምሥራች የተባለውን ቡክሌት በመጠቀም ነው።” አክላም ኤልሳቤት እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “አብዛኞቹ እንግዶች ከዚህ በፊት የመንግሥቱን ምሥራች ሰምተው አያውቁም ነበር፤ ሆኖም ለመልእክቱ ጥሩ አመለካከት ነበራቸው። ከቦሊቪያ፣ ከቻይና፣ ከፈረንሳይ፣ ከሕንድ፣ ከእስራኤልና ከናይጄሪያ የመጡ ሰዎችን አነጋግረናል። በተለያየ ቋንቋ የተዘጋጁ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ይዘን ስለነበር ለአንዳንዶቹ በራሳቸው ቋንቋ የተዘጋጁ ጽሑፎችን ስንሰጣቸው በደስታ ተቀብለዋል።”

በሜክሲኮ የሚኖር ራውል የተባለ አንድ አቅኚም ይህን ቡክሌት ተጠቅሞ ጥሩ ውጤት አግኝቷል። ከጥቂት ዓመታት በፊት ባለቤታቸውን በሞት ያጡ የአረብ ዝርያ ያላቸው አንድ የ80 ዓመት አዛውንት አነጋግሮ ነበር። ሰውየው ከቡክሌቱ ላይ በአረብኛ ቋንቋ የተጻፈውን የመንግሥቱን መልእክት ካነበቡ በኋላ የደስታ እንባ አንብተዋል። ለምን? አምላክ ወደፊት ሞት እንደማይኖር በ⁠ራእይ 21:3, 4 ላይ የሰጠውን ተስፋ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ሲያነቡ ልባቸው በጣም ስለተነካ ነበር። በሌላ ወቅት ደግሞ ራውል መደበኛ ባልሆነ መንገድ ሲመሠክር የፖርቹጋል ቋንቋ ተናጋሪ የሆነ ሰው አገኘ። ይህም ሰው ቢሆን ልጁን በሞት አጥቶ ነበር። በዚህ ጊዜ ራውል ከዚህ ቡክሌት ላይ በፖርቹጋል ቋንቋ የተጻፈውን መልእክት አውጥቶ አስነበበው። ሰውየውም መልእክቱን ካነበበ በኋላ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የበለጠ ማወቅ እንደሚፈልግ የጠቆመ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠና የቀረበለትን ግብዣም ተቀብሏል።

ራውል አርመንኛ፣ ቻይንኛ፣ እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ጀርመንኛ እንዲሁም የሂንዲ፣ የኮሪያ፣ የሚክሲ፣ የፋርስ፣ የሩሲያና የዛፐቴክ ቋንቋ ለሚናገሩ ሰዎች ለመመሥከር ለሰዎች ሁሉ የሚሆን ምሥራች የተባለውን ቡክሌት ተጠቅሟል። ራውል እንዲህ ብሏል፦ “በአገልግሎት ላይ ይህን ቡክሌት መጠቀም ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ተመልክቻለሁ። ቋንቋቸውን መናገር ባልችልም እንኳ የተለያዩ ሰዎችን ልብ ለመንካት አስችሎኛል።”

ወደተለያዩ አገሮች የሚጓዙና ከአገራቸው ውጪ የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ ሌላ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎችን የማግኘት አጋጣሚያችንም የዚያኑ ያህል ይጨምራል። ለሰዎች ሁሉ የሚሆን ምሥራች የተባለውን ቡክሌት በመጠቀም ለእነዚህ ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት መስበክ እንችላለን። አንተስ ይህን ቡክሌት ሁልጊዜ ትይዛለህ?

[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ራውል የሰዎችን ልብ ለመንካት የሚያስችለውን ቡክሌት ይዞ