በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የእምነት ባልንጀሮቻችሁን ለማክበር ቀዳሚ ናችሁ?

የእምነት ባልንጀሮቻችሁን ለማክበር ቀዳሚ ናችሁ?

የእምነት ባልንጀሮቻችሁን ለማክበር ቀዳሚ ናችሁ?

“በወንድማማች ፍቅር እርስ በርሳችሁ ከልብ ተዋደዱ። አንዳችሁ ሌላውን ለማክበር ቀዳሚ ሁኑ።”—ሮም 12:10

1, 2. (ሀ) ጳውሎስ ለሮም ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ምን ምክር ሰጥቷል? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

ሐዋርያው ጳውሎስ ለሮም ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን በጉባኤ ውስጥ ፍቅር ማሳየታችን አስፈላጊ መሆኑን አጉልቷል። ፍቅራችን “ግብዝነት የሌለበት” ሊሆን እንደሚገባ አሳስቦናል። ከዚህም በተጨማሪ “በወንድማማች ፍቅር እርስ በርሳችሁ ከልብ ተዋደዱ” ብሏል።—ሮም 12:9, 10ሀ

2 የወንድማማች ፍቅር ማሳየት ሲባል ለሌሎች ሞቅ ያለ ወዳጃዊ ስሜት ከማሳየት ያለፈ ነገርን እንደሚጨምር ጥርጥር የለውም። እንዲህ ያለው ፍቅር በተግባር መታየት ይኖርበታል። ደግሞስ ፍቅራችንን በተግባር ካላሳየን ወንድሞቻችንን እንደምንወዳቸው እንዴት ይታወቃል? ጳውሎስ አክሎ “አንዳችሁ ሌላውን ለማክበር ቀዳሚ ሁኑ” የሚል ምክር የሰጠው በዚህ ምክንያት ነው። (ሮም 12:10ለ) ታዲያ ሌሎችን ማክበር ምን ይጨምራል? የእምነት ባልንጀሮቻችንን በማክበር ረገድ ቀዳሚ መሆናችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ይህንን ማድረግ የምንችለውስ እንዴት ነው?

ሌሎችን ማክበር ምን ይጨምራል?

3. “ክብር” የሚለው ቃል መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈባቸው ቋንቋዎች ምን ትርጉም ያስተላልፋል?

3 “ክብር” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል፣ ቀጥተኛ ትርጉሙ “ክብደት” ማለት ነው። ክብር የሚሰጠው ሰው ከባድ እንደሆነ ወይም ትልቅ ቦታ እንዳለው ተደርጎ ይታያል። ቃሉ፣ የሚከበረው ሰው ከፍተኛ ቦታ እንደሚሰጠው ያመለክታል። (ዘፍ. 45:13) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ክብር” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው፣ ዋጋ ያለው፣ ውድ የሚል ሐሳብ ያስተላልፋል። (ሉቃስ 14:10) በእርግጥም የምናከብራቸው ሰዎች ለእኛ ውድ ከመሆናቸውም ሌላ ከፍተኛ ግምት እንሰጣቸዋለን።

4, 5. ሌሎችን በአክብሮት በመመልከትና በአክብሮት በመያዝ መካከል ያለው ተዛምዶ ምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ።

4 ሌሎችን ማክበር ምን ይጨምራል? ሌሎችን ማክበር ለእነሱ ካለን አመለካከት ይጀምራል። አመለካከታችን ሰዎችን በምንይዝበት መንገድ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። በሌላ አባባል በመጀመሪያ ወንድማችንን በአክብሮት ልንመለከተው ይገባል ማለት ነው፤ ይህ ደግሞ በአክብሮት እንድንይዘው ያነሳሳናል።

5 አንድ ክርስቲያን የእምነት ባልንጀሮቹን የሚያከብረው ከልቡ ካልሆነ እውነተኛ አክብሮት አሳይቷል ሊባል ይችላል? (3 ዮሐ. 9, 10) አንድ ተክል ሥር ሊሰድና ሊያብብ የሚችለው በጥሩ አፈር ላይ ከተተከለ ብቻ እንደሆነ ሁሉ ለሌሎች የምናሳየው አክብሮት እውነተኛና ቀጣይ የሚሆነውም ከልብ ከመነጨ ብቻ ነው። ጥሩ አፈር ያላገኘ ተክል እንደሚጠወልግ ሁሉ ከልብ ያልሆነ አክብሮትም ይዋል ይደር እንጂ እየቀነሰ መሄዱ አይቀርም። በመሆኑም ጳውሎስ፣ ወንድሞቻችንን እንድናከብር ምክር ከመስጠቱ በፊት “ፍቅራችሁ ግብዝነት የሌለበት ይሁን” የሚል ግልጽ መመሪያ መስጠቱ አያስገርምም።—ሮም 12:9፤ 1 ጴጥሮስ 1:22ን አንብብ።

“በአምላክ አምሳል” የተፈጠሩትን አክብሩ

6, 7. ሌሎችን ማክበር ያለብን ለምንድን ነው?

6 የእምነት ባልንጀሮቻችንን በአክብሮት ለመያዝ የሚረዳን ቁልፍ ነገር ለእነሱ ልባዊ አክብሮት ማዳበር ነው፤ ስለሆነም ሁሉንም ወንድሞቻችንን እንድናከብር የሚያነሳሱንን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያቶች ፈጽሞ ልንዘነጋቸው አይገባም። እስቲ ሁለቱን ምክንያቶች እንመልከት።

7 በምድር ላይ ካሉት ሌሎች ፍጥረታት በተለየ የሰው ልጆች የተፈጠርነው “በአምላክ አምሳል” ነው። (ያዕ. 3:9) በመሆኑም እንደ ፍቅር፣ ጥበብና ፍትሕ ያሉትን አምላካዊ ባሕርያት እናንጸባርቃለን። ከፈጣሪያችን የተቀበልናቸውን ሌሎች ነገሮችም እንመልከት። መዝሙራዊው እንዲህ ብሏል፦ “እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ፤  . . . ክብርህ ከሰማያት በላይ፣ ከፍ ከፍ ብሎአል። . . . [ሰውን] ከመላእክት በጥቂት አሳነስኸው፤ የክብርንና የሞገስን ዘውድ አቀዳጀኸው።” (መዝ. 8:1, 4, 5፤ 104:1) * አምላክ ለሰው ልጆች በአጠቃላይ በተወሰነ መጠን የክብር ዘውድ አጎናጽፏቸዋል። በመሆኑም አንድን ሰው ስናከብረው ለሰው ልጆች ሁሉ በተወሰነ መጠን ክብር የሰጠውን ይሖዋን እያከበርን ነው ማለት ይቻላል። ታዲያ ለሁሉም ሰው ክብር እንድናሳይ የሚያነሳሱን በቂ ምክንያቶች ካሉን የእምነት ባልንጀሮቻችንንማ ይበልጥ ልናከብራቸው አይገባም?—ዮሐ. 3:16፤ ገላ. 6:10

የአንድ ቤተሰብ አባላት

8, 9. ጳውሎስ የእምነት ባልንጀሮቻችንን ለማክበር የሚያነሳሳንን የትኛውን ምክንያት ገልጿል?

8 እርስ በርስ ለመከባበር የሚያነሳሳንን ሌላውን ምክንያት ጳውሎስ ጠቅሶታል። ሌሎችን እንድናከብር ምክር ከመስጠቱ በፊት “በወንድማማች ፍቅር እርስ በርሳችሁ ከልብ ተዋደዱ” ብሏል። “ከልብ ተዋደዱ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ አገላለጽ የሚዋደዱና እርስ በርስ የሚደጋገፉ የቤተሰብ አባላት አንድነት እንዲኖራቸው የሚያደርገውን ጠንካራ ትስስር ያመለክታል። በመሆኑም ጳውሎስ ይህን አገላለጽ ሲጠቀም በጉባኤ ውስጥ የሚኖረን ግንኙነት አንድነት ባለው ቤተሰብ ውስጥ የሚታየውን ያህል ጠንካራና ፍቅር የሚንጸባረቅበት ሊሆን እንደሚገባ ማጉላቱ ነበር። (ሮም 12:5) ከዚህም በተጨማሪ ጳውሎስ እነዚህን ቃላት የጻፈው ይሖዋ እንደ ልጅ አድርጎ ለቆጠራቸው በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች መሆኑን ማስታወስ የተገባ ነው። እነዚህ ክርስቲያኖች የአንድ አባት ልጆች ተደርገው ስለተቆጠሩ የአንድ ቤተሰብ አባላት ናቸው ማለት ይቻላል። ከዚህ አንጻር በጳውሎስ ዘመን የነበሩት በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች እርስ በርስ እንዲከባበሩ የሚያነሳሳቸው አጥጋቢ ምክንያት ነበራቸው። ይህ በዛሬው ጊዜ ለሚገኙ ቅቡዓን ክርስቲያኖችም ይሠራል።

9 ‘ሌሎች በጎችን’ በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? (ዮሐ. 10:16) ሌሎች በጎች እንደ አምላክ ልጆች የመቆጠር መብት ባያገኙም አንድነት ያለው ዓለም አቀፋዊ የክርስቲያን ቤተሰብ አባላት ስለሆኑ እርስ በርሳቸው ወንድም እና እህት እየተባባሉ መጠራራታቸው ተገቢ ነው። (1 ጴጥ. 2:17፤ 5:9) ሌሎች በጎች፣ እርስ በርስ “ወንድም” ወይም “እህት” እየተባባሉ የሚጠራሩት ለምን እንደሆነ በሚገባ ከተረዱ እነሱም ቢሆኑ የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ከልብ እንዲያከብሩ የሚያነሳሳ አጥጋቢ ምክንያት ይኖራቸዋል።1 ጴጥሮስ 3:8ን አንብብ።

አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

10, 11. ከልብ የመነጨ አክብሮት ማሳየት ይህን ያህል አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

10 ከልብ የመነጨ አክብሮት ማሳየት ይህን ያህል አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን አክብሮት ማሳየታችን ለመላው ጉባኤ ደኅንነትና አንድነት ትልቅ አስተዋጽኦ ስለሚያበረክት ነው።

11 እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ከሁሉ የላቀ ብርታት የሚሰጠን ከይሖዋ ጋር ያለን የጠበቀ ዝምድና እንዲሁም ከመንፈሱ የምናገኘው ድጋፍ መሆኑን እንገነዘባለን። (መዝ. 36:7፤ ዮሐ. 14:26) ከዚህም በተጨማሪ የእምነት ባልንጀሮቻችን ከፍ አድርገው እንደሚመለከቱን ሲያሳዩን እንበረታታለን። (ምሳሌ 25:11) ከልብ የመነጨ አድናቆትና አክብሮት ሲቸረን መንፈሳችን ይታደሳል። ይህም ደስተኛና ቆራጥ ሆነን በሕይወት ጎዳና ላይ መመላለሳችንን እንድንቀጥል ብርታት ይጨምርልናል። አንተ ራስህ እንዲህ ተሰምቶህ ሊያውቅ ይችላል።

12. በጉባኤ ውስጥ ሞቅ ያለ መንፈስና ፍቅር እንዲኖር እያንዳንዳችን አስተዋጽኦ ማበርከት የምንችለው እንዴት ነው?

12 ይሖዋ የመከበር ተፈጥሯዊ ፍላጎት እንዳለን ስለሚያውቅ “እርስ በርሳችሁ ለመከባበርም ተሽቀዳደሙ” በማለት በቃሉ በኩል ማሳሰቢያ ሰጥቷል። (ሮም 12:10 የ1980 ትርጉም፤ ማቴዎስ 7:12ን አንብብ።) ጊዜ የማይሽረውን ይህን ምክር ተግባራዊ የሚያደርጉ ክርስቲያኖች በሙሉ በክርስቲያናዊው የወንድማማች ማኅበር ውስጥ ሞቅ ያለ መንፈስና ፍቅር እንዲኖር አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። እንግዲያው ‘በጉባኤ ውስጥ አንድን ወንድም ወይም አንዲትን እህት ከልቤ እንደማከብራቸው በንግግሬ ወይም በድርጊቴ ከገለጽኩ ምን ያህል ጊዜ ሆኖኛል?’ በማለት ቆም ብለን ማሰባችን ጠቃሚ ነው።—ሮም 13:8

ለእያንዳንዳችን የተሰጠ ኃላፊነት

13. (ሀ) ሌሎችን በማክበር ረገድ ቀዳሚ መሆን ያለበት ማን ነው? (ለ) በ⁠ሮም 1:7 ላይ የሚገኘው የጳውሎስ ሐሳብ ምን ይጠቁማል?

13 ሌላውን ለማክበር ቀዳሚ መሆን ያለበት ማን ነው? ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ሽማግሌዎች በጉባኤ ውስጥ “ግንባር ቀደም” እንደሆኑ ገልጿል። (ዕብ. 13:17) በእርግጥም ሽማግሌዎች በተለያዩ እንቅስቃሴዎች ግንባር ቀደም ሆነው ይሠራሉ። የመንጋው እረኞች እንደመሆናቸው መጠን ሌሎች ሽማግሌዎችን ጨምሮ የእምነት ባልንጀሮቻቸውን በማክበር ረገድም ግንባር ቀደም መሆን እንዳለባቸው ምንም ጥርጥር የለውም። ለምሳሌ ሽማግሌዎች የጉባኤውን መንፈሳዊ ሁኔታ አስመልክተው ስብሰባ ሲያደርጉ እገሌ ከገሌ ሳይሉ ሁሉም ሽማግሌዎች የሚሰጡትን ሐሳብ በጥሞና በማዳመጥ እንደሚከባበሩ ያሳያሉ። ከዚህም ባሻገር ውሳኔ በሚያደርጉበት ወቅት የሁሉንም ሽማግሌዎች አመለካከትና የሰጡትን አስተያየት ከግምት በማስገባት አንዳቸው ሌላውን ያከብራሉ። (ሥራ 15:6-15) ይሁንና ጳውሎስ ለሮም ክርስቲያኖች የጻፈው ደብዳቤ ለሽማግሌዎች ብቻ ሳይሆን ለመላው ጉባኤ የተጻፈ መሆኑን ማስታወስ ይኖርብናል። (ሮም 1:7) በመሆኑም ክርስቲያኖች አክብሮት በማሳየት ረገድ ቀዳሚ እንዲሆኑ የተሰጠው ምክር በዛሬው ጊዜ ለምንኖረው ክርስቲያኖች በሙሉ ይሠራል።

14. (ሀ) ሌሎችን በማክበርና በዚህ ረገድ ቀዳሚ በመሆን መካከል ያለውን ልዩነት በምሳሌ አስረዳ። (ለ) ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ እንችላለን?

14 የጳውሎስን ምክር ከሌላ አቅጣጫም እንመልከተው። በሮም የሚገኙትን የእምነት ባልንጀሮቹን ያሳሰባቸው ሌሎችን እንዲያከብሩ ብቻ ሳይሆን በዚህ ረገድ ቀዳሚ እንዲሆኑም ጭምር ነው። በሁለቱ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? እስቲ የሚከተለውን ምሳሌ እንመልከት። አንድ መምህር ማንበብና መጻፍ የሚችሉ ተማሪዎችን ማንበብ እንዲማሩ ይነግራቸዋል? በፍጹም። እነዚህ ተማሪዎች ቀድሞውንም ቢሆን ማንበብ ይችላሉ። ሆኖም መምህሩ የማንበብ ችሎታቸውን እንዲያሻሽሉ ሊረዳቸው ይፈልግ ይሆናል። በተመሳሳይም ሌሎችን እንድናከብር የሚያነሳሳን አንዳችን ለሌላው ያለን ፍቅር ሲሆን ይህ ደግሞ የእውነተኛ ክርስቲያኖች መለያ ምልክት ነው። (ዮሐ. 13:35) ይሁንና ማንበብና መጻፍ የሚችሉ ተማሪዎች የንባብ ችሎታቸውን በማሻሻል ተጨማሪ እድገት ማድረግ እንደሚችሉ ሁሉ እኛም አክብሮት በማሳየት ረገድ ቀዳሚ በመሆን እድገት ማድረግ እንችላለን። (1 ተሰ. 4:9, 10) ይህ ለእያንዳንዳችን የተሰጠ ኃላፊነት ነው። ‘ቅድሚያውን በመውሰድ በጉባኤ ውስጥ የሚገኙትን ክርስቲያኖች አከብራለሁ?’ በማለት ራሳችንን ልንጠይቅ እንችላለን።

‘ድኾችን’ አክብሩ

15, 16. (ሀ) አክብሮት ስናሳይ እነማንን ችላ ማለት አይኖርብንም? ለምንስ? (ለ) ለሁሉም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ከልብ የመነጨ አክብሮት እንዳለን የሚጠቁመው ምን ሊሆን ይችላል?

15 አክብሮት በማሳየት ረገድ በጉባኤ ውስጥ እነማንን ችላ ማለት አይገባንም? የአምላክ ቃል “ለድኻ የሚራራ ለእግዚአብሔር ያበድራል፤ ስላደረገውም ተግባር ዋጋ ይከፍለዋል” ይላል። (ምሳሌ 19:17) ሌሎችን በማክበር ረገድ ቀዳሚ ለመሆን ጥረት ስናደርግ ይህን መሠረታዊ ሥርዓት በተግባር ማዋል የምንችለው እንዴት ነው?

16 ብዙዎች በሥልጣን ለሚበልጧቸው ሰዎች አክብሮት ማሳየት እንደማይከብዳቸው ሆኖም ከእነሱ እንደሚያንሱ አድርገው የሚቆጥሯቸውን ያን ያህል ወይም እስከነጭራሹ እንደማያከብሯቸው አስተውለህ ይሆናል። ይሖዋ ግን እንደዚህ አያደርግም፤ “የሚያከብሩኝን አከብራለሁ” ብሏል። (1 ሳሙ. 2:30፤ መዝ. 113:5-7) ይሖዋ እሱን ለሚያገለግሉና ለሚያከብሩት ሁሉ አክብሮት ያሳያል። “ድኻውን” አይንቅም። (1 ሳሙኤል 2:8ን አንብብ፤ 2 ዜና 16:9) እኛም ይሖዋን መምሰል እንደምንፈልግ ምንም ጥርጥር የለውም። ለሌሎች የምናሳየው አክብሮት ምን ያህል ከልብ የመነጨ መሆኑን መገምገም ከፈለግን ‘በጉባኤ ውስጥ ትልቅ ቦታ ወይም ኃላፊነት የሌላቸውን ወንድሞች የምይዛቸው እንዴት ነው?’ በማለት ራሳችንን መጠየቃችን የተገባ ነው። (ዮሐ. 13:14, 15) ለዚህ ጥያቄ የምንሰጠው ምላሽ ለሌሎች የምናሳየው አክብሮት ምን ያህል ከልብ የመነጨ መሆኑን ይጠቁማል።ፊልጵስዩስ 2:3, 4ን አንብብ።

ጊዜያችንን በመስጠት አክብሮት ማሳየት

17. አክብሮት በማሳየት ረገድ ቀዳሚ መሆን የምንችልበት ዋነኛው መንገድ ምንድን ነው? ለምንስ?

17 በጉባኤ ውስጥ ላሉት ሁሉ አክብሮት በማሳየት ረገድ ቀዳሚ መሆን የምንችልበት ዋነኛው መንገድ ምንድን ነው? ለሌሎች ጊዜያችንን በመስጠት ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ሕይወታችን በሥራ የተወጠረ ነው፤ ያሉብንን በርካታ አስፈላጊ የጉባኤ እንቅስቃሴዎች ማከናወን ብዙ ጊዜ ይወስድብናል። በመሆኑም ጊዜን ውድ እንደሆነ አድርገን መመልከታችን አያስገርምም። በተጨማሪም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ከሚገባው በላይ ጊዜ እንዲሰጡን መጠበቅ እንደሌለብን እንገነዘባለን። ሌሎች የጉባኤው አባላትም ብዙ ጊዜ እንድንሰጣቸው ሊጠብቁብን እንደማይገባ የሚገነዘቡ መሆናቸው ያስደስተናል።

18. በገጽ 18 ላይ ካለው ፎቶግራፍ መመልከት እንደሚቻለው ለእምነት ባልንጀሮቻችን የተወሰነ ጊዜ ለመስጠት ፈቃደኞች እንደሆንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

18 ያም ሆኖ ግን በተለይ በጉባኤ ውስጥ እረኞች ሆነን የምናገለግል ወንዶች፣ ለእምነት ባልንጀሮቻችን የተወሰነ ጊዜ ለመስጠት ስንል የምንሠራውን ለማቋረጥ ፈቃደኞች መሆናችን እነሱን እንደምናከብራቸው የሚያሳይ መሆኑንም እንገነዘባለን። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ለአንድ ወንድማችን የተወሰነ ጊዜ ለመስጠት ስንል አንዳንድ ሥራዎችን ማቋረጣችን ‘በጣም ከፍ አድርጌ ስለምመለከትህ የምሠራውን ነገር ከመቀጠል ይልቅ ከአንተ ጋር የተወሰነ ጊዜ ማሳለፍ ይበልጥብኛል’ የማለት ያህል ነው። (ማር. 6:30-34) በሌላ በኩል ደግሞ ለወንድማችን የተወሰነ ጊዜ ለመስጠት ስንል የምንሠራውን ለማቋረጥ የምናቅማማ ከሆነ ወንድማችን ብዙም ቦታ እንደማንሰጠው ሊሰማው ይችላል። እርግጥ ነው፣ ልናቋርጠው የማንችል አጣዳፊ ጉዳይ ሊኖረን እንደሚችል እሙን ነው። ያም ሆኖ ለሌሎች የተወሰነ ጊዜ ለመስጠት ፈቃደኞች መሆናችን አሊያም ማቅማማታችን ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ምን ያህል ከልባችን እንደምናከብራቸው ያሳያል።—1 ቆሮ. 10:24

ቀዳሚ ለመሆን ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ

19. ጊዜያችንን ከመስጠት በተጨማሪ በምን መንገድ ለእምነት ባልንጀሮቻችን አክብሮት ማሳየት እንችላለን?

19 ለእምነት ባልንጀሮቻችን አክብሮት ማሳየት የምንችልባቸው ሌሎች መንገዶችም አሉ። ለምሳሌ ጊዜያችንን ስንሰጣቸው ትኩረታችንንም ልንሰጣቸው ይገባል። በዚህ ረገድም ቢሆን ይሖዋ ምሳሌ ትቶልናል። መዝሙራዊው ዳዊት “የእግዚአብሔር ዐይኖች ወደ ጻድቃን ናቸው፤ ጆሮዎቹም ለጩኸታቸው ክፍት ናቸው” ብሏል። (መዝ. 34:15) ለወንድሞቻችን በተለይም እርዳታ ፈልገው ለሚቀርቡን ዓይናችንንና ጆሯችንን በሌላ አባባል ሙሉ ትኩረታችንን በመስጠት ይሖዋን ለመምሰል ጥረት እናደርጋለን። እንዲህ በማድረግ አክብሮት እናሳያቸዋለን።

20. አክብሮት በማሳየት ረገድ የትኞቹን ማሳሰቢያዎች ፈጽሞ ልንዘነጋቸው አይገባም?

20 ከላይ እንደተመለከትነው ለእምነት ባልንጀሮቻችን ከልብ የመነጨ አክብሮት እንድናሳይ የሚገፋፉንን ምክንያቶች ፈጽሞ ልንዘነጋቸው አይገባም። ከዚህም ሌላ ድኾችን ጨምሮ ለሁሉም ሰው አክብሮት በማሳየት ረገድ ቀዳሚ መሆን የምንችልባቸውን አጋጣሚዎች መፈለግ ይኖርብናል። እነዚህን እርምጃዎች በመውሰድ በጉባኤ ውስጥ ያለው የወንድማማች ፍቅርና አንድነት እንዲጠናከር እናደርጋለን። እንግዲያው አንዳችን ለሌላው አክብሮት ለማሳየት ብቻ ሳይሆን በዚህ ረገድ ቀዳሚ ለመሆን ሁላችንም ጥረት ማድረጋችንን እንቀጥል። አንተስ እንዲህ ለማድረግ ቆርጠሃል?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.7 ዳዊት በ8ኛው መዝሙር ላይ የተናገራቸው ቃላት ትንቢታዊ ትርጉምም ያላቸው ሲሆን ፍጹም ሰው የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ያመለክታሉ።—ዕብ. 2:6-9

ታስታውሳለህ?

• ሌሎችን በአክብሮት በመመልከትና በአክብሮት በመያዝ መካከል ያለው ተዛምዶ ምንድን ነው?

• የእምነት ባልንጀሮቻችንን እንድናከብር የሚያነሳሱን ምን ምክንያቶች አሉን?

• አንዳችን ለሌላው አክብሮት ማሳየታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

• ለእምነት ባልንጀሮቻችን አክብሮት ማሳየት የምንችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለእምነት ባልንጀሮቻችን አክብሮት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?