በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ያከናወነው ሥራ ወዲያው ተከትሎታል’

‘ያከናወነው ሥራ ወዲያው ተከትሎታል’

‘ያከናወነው ሥራ ወዲያው ተከትሎታል’

የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ቴዎዶር ጃራዝ ረቡዕ ሰኔ 9, 2010 ጠዋት ላይ በ84 ዓመቱ ምድራዊ ሕይወቱን አጠናቋል። ወንድም ጃራዝ ከባለቤቱ ከእህት ሜሊታ ጋር በትዳር ዓለም 53 ዓመት አሳልፏል። ታላቅ እህቱ በሕይወት የምትገኝ ሲሆን አንድ ወንድና ሁለት ሴት ልጆች አሏት።

ወንድም ጃራዝ የተወለደው መስከረም 28, 1925 በፓይክ ግዛት ኬንታኪ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ሲሆን ነሐሴ 10, 1941 በ15 ዓመቱ ራሱን ለይሖዋ ወስኖ ተጠመቀ። ከሁለት ዓመት በኋላ ማለትም በ17 ዓመቱ የዘወትር አቅኚ ሆነ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ወደ 67 ለሚጠጉ ዓመታት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ተካፍሏል።

ወንድም ጃራዝ በ1946 በ20 ዓመቱ በጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ሰባተኛው ክፍል ላይ እንዲካፈል ተጋበዘ። ከተመረቀ በኋላም ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በክሌቭላንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኖ እንዲያገለግል ተመደበ። ከዚያም በ1951 በአውስትራሊያ ቅርንጫፍ ቢሮ የሚከናወነውን ሥራ በበላይነት እንዲከታተል ወደ አውስትራሊያ ተላከ። የ1983 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ ሪፖርት እንዳደረገው ወንድም ጃራዝ “ቲኦክራሲያዊውን ሥርዓት በጥብቅ መከተሉ እንዲሁም በመስክ አገልግሎት ግሩም ምሳሌ መሆኑ በመላው አገሪቱ የሚገኙ ወንድሞችን በእጅጉ አበረታቷል።”

ወንድም ጃራዝ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ከተመለሰ በኋላ ታኅሣሥ 10, 1956 ከእህት ሜሊታ ላስኮ ጋር ትዳር መሠረተ። የትዳር ሕይወታቸውን ሀ ብለው የጀመሩት በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ሥራ ሲሆን የዩናይትድ ስቴትስን ሰፊ ክፍል በሚይዙ ወረዳዎችና አውራጃዎች ላይ በትጋት አገልግለዋል። በ1974 መገባደጃ አካባቢ ወንድም ጃራዝ የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባል እንዲሆን ግብዣ ቀረበለት።

ወንድም ጃራዝ ሙሉ ትኩረቱን በቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ያደረገ ቀናተኛና ታማኝ የይሖዋ አገልጋይ የነበረ በመሆኑ ምንጊዜም ይታወሳል። ለባለቤቱ አፍቃሪና ተንከባካቢ ባል የነበረ ሲሆን ከራሱ ይልቅ የሌሎችን ፍላጎት የሚያስቀድም መንፈሳዊ ሰው ነበር። (1 ቆሮ. 13:4, 5) የሌሎችን ፍላጎት የሚያስቀድም ሰው መሆኑ ሁሉንም ሰው በተገቢው መንገድና በርኅራኄ ለመያዝ ያደርግ በነበረው ጥረት ታይቷል። በተጨማሪም ለሰዎች የነበረው የማይለወጥ ፍቅርና አሳቢነቱ ለመስክ አገልግሎት በነበረው ቅንዓት ተንጸባርቋል።

የዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበርና የቤቴል ቤተሰብ አባል የነበረውን ይህን ተወዳጅና ትጉህ ወንድም በማጣታችን ብናዝንም ለብዙ አሥርተ ዓመታት ይሖዋን በታማኝነት በማገልገሉ ደስተኞች ነን። ወንድም ጃራዝ ‘እስከ ሞት ድረስም እንኳ ታማኝነቱን እንዳስመሠከረና የሕይወትን አክሊል እንደተቀበለ’ እንተማመናለን። (ራእይ 2:10) ‘ያከናወነው ሥራም ወዲያው እንደተከተለው’ እርግጠኞች ነን።—ራእይ 14:13