ይሖዋ ልባቸው የተሰበረ ሰዎች የሚያሰሙትን ጩኸት ይሰማል
ይሖዋ ልባቸው የተሰበረ ሰዎች የሚያሰሙትን ጩኸት ይሰማል
የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ጠቢቡ ሰለሞን እንደተናገረው ሁላችንም “መጥፎ ጊዜና ያልተጠበቁ ክስተቶች” ያጋጥሙናል። (መክ. 9:11 NW) አንድ አሳዛኝ ሁኔታ ወይም መከራ ሕይወታችንን ሊያመሰቃቅለው ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሰው የቤተሰቡ አባል በድንገት ሲሞት ስሜቱ ክፉኛ ሊጎዳ ይችላል። ከዚያ በኋላ ባሉት ሳምንታትና ወራት የሚሰማው ሐዘንና የተስፋ መቁረጥ ስሜት ከአቅሙ በላይ ሊሆንበት ይችላል። እንዲሁም ግለሰቡ በጣም ግራ ከመጋባቱ የተነሳ በጸሎት ወደ ይሖዋ ለመቅረብ ብቃቱ እንደሌለው ይሰማው ይሆናል።
እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ የሚገኝ ሰው ማበረታቻና ፍቅር እንዲሁም የሌሎች አሳቢነት ያስፈልገዋል። መዝሙራዊው ዳዊት “[ይሖዋ] የሚንገዳገዱትን ሁሉ ይደግፋል፤ የወደቁትንም ሁሉ ያነሣል” በማለት የተናገረው ሐሳብ የሚያጽናና ነው። (መዝ. 145:14) መጽሐፍ ቅዱስ “በፍጹም ልባቸው የሚታመኑበትን ለማበርታት የእግዚአብሔር [“የይሖዋ፣” NW] ዐይኖች በምድር ሁሉ ላይ ይመለከታሉ” በማለት ይናገራል። (2 ዜና 16:9) በተጨማሪም ይሖዋ እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “የተዋረዱትን መንፈሳቸውን ለማነሣሣት፣ የተሰበረ ልብ ያላቸውን ለማነቃቃት . . . የተሰበረ ልብ ካለውና በመንፈሱ ከተዋረደው ጋር እሆናለሁ።” (ኢሳ. 57:15) ታዲያ ይሖዋ የተዋረደ መንፈስ ያላቸውንና ልባቸው የተሰበረ ሰዎችን የሚደግፈው እንዲሁም የሚያጽናናው እንዴት ነው?
‘በወቅቱ የተሰጠ ቃል’
ይሖዋ እንዲህ ላሉ ሰዎች በወቅቱ ወይም በትክክለኛው ጊዜ እርዳታ ለመስጠት በክርስቲያን ወንድሞቻችን ይጠቀማል። ክርስቲያኖች “የተጨነቁትን ነፍሳት አጽናኗቸው” የሚል ምክር ተሰጥቷቸዋል። (1 ተሰ. 5:14) አንድ ሰው አስጨናቂና አሳዛኝ ሁኔታ ሲያጋጥመው ሩኅሩኅ የሆኑ የእምነት አጋሮቹ በአሳቢነትና በፍቅር ተነሳስተው የሚናገሩት ሐሳብ ሊያረጋጋው ይችላል። በሐዘን ለተደቆሰ ሰው ጥቂት የሚያጽናኑ ቃላት መናገር ብቻ እንኳ የተሰበረ መንፈሱ እንዲያንሰራራ ሊረዳው ይችላል። ግለሰቡ እንዲህ ያለውን አሳቢነት የሚንጸባረቅበት ማበረታቻ ያገኘው ተመሳሳይ የአእምሮና የስሜት ሥቃይ ደርሶበት በጽናት ከተቋቋመ ሰው ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ እንዲህ ስላሉ ሁኔታዎች ብዙ ተሞክሮ ካካበተ ወዳጁ ሊሆን ይችላል። ይሖዋ እንዲህ ባሉ መንገዶች ተጠቅሞ የተሰበረ ልብ ያላቸውን ሰዎች ያነቃቃል።
ትዳር ከያዘ ከጥቂት ጊዜ በኋላ በማይድን በሽታ ምክንያት ባለቤቱን በድንገት የተነጠቀውን አሌክስ የሚባል የጉባኤ ሽማግሌ ሁኔታ እንመልከት። ሩኅሩኅ የሆነ አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ለአሌክስ የሚያጽናና ሐሳብ ለማካፈል በቁም ነገር አሰበበት። እሱም ባለቤቱን በሞት ያጣ ሲሆን በኋላ ላይ ግን እንደገና አግብቷል። ይህ ወንድም ሐዘኑ ከአቅም በላይ ሆኖበት እንደነበር ለአሌክስ ገለጸለት። በአገልግሎትና በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ከሌሎች ጋር በሚሆንበት ጊዜ ሐዘኑን ይረሳ እንደነበር ምሳሌ 15:23
ነገረው። ሆኖም ልክ ቤቱ ገብቶ በሩን ሲዘጋ የብቸኝነቱ ስሜት ይጀምረው ነበር። አሌክስ “እኔ የሚሰማኝ ስሜት የተለመደና ሌሎችም የሚያጋጥማቸው መሆኑን ማወቄ በጣም አጽናንቶኛል” በማለት ተናግሯል። በእርግጥም ‘በወቅቱ የተሰጠ ቃል’ በሐዘን የተደቆሰን ሰው በእጅጉ ሊያጽናና ይችላል።—የትዳር ጓደኞቻቸውን በሞት የተነጠቁ በርካታ ግለሰቦችን የሚያውቅ አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ ደግሞ ለአሌክስ ጥቂት የሚያጽናኑ ቃላትን ማካፈል እንዳለበት ተሰማው። ይሖዋ ስሜታችንን እንደሚረዳልንና ምን እንደሚያስፈልገን እንደሚያውቅ ሐዘኔታና ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ ገለጸለት። ይህ ወንድም “በመጪዎቹ ወራት ወይም ዓመታት ጓደኛ እንደሚያስፈልግህ ከተሰማህ ይሖዋ ለአንተ ያለው ፍቅራዊ ዝግጅት እንደገና ማግባት ነው” በማለት መከረው። እርግጥ ነው፣ የትዳር ጓደኛቸውን በሞት የተነጠቁና እንደገና ማግባት የሚፈልጉ ሁሉ ሁኔታቸው እንደዚያ ለማድረግ ይፈቅድላቸዋል ማለት አይደለም። አሌክስ ይህ ወንድም በተናገረው ሐሳብ ላይ አሰላስሎ እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “እንደገና ማግባት የይሖዋ ዝግጅት መሆኑን መስማታችሁ ‘እንደገና ባገባ ለትዳር ጓደኛዬም ሆነ ይሖዋ ላቋቋመው የጋብቻ ዝግጅት ታማኝ ሳልሆን እቀራለሁ’ ከሚለው አፍራሽ ስሜት እንድትገላገሉ ያደርጋችኋል።”—1 ቆሮ. 7:8, 9, 39
ብዙ ችግርና መከራ ደርሶበት የነበረው መዝሙራዊው ዳዊት “[የይሖዋ] ዐይኖች ወደ ጻድቃን ናቸው፤ ጆሮዎቹም ለጩኸታቸው ክፍት ናቸው” በማለት ተናግሯል። (መዝ. 34:15) ይሖዋ ሩኅሩኅና ጎልማሳ ክርስቲያኖች በሚሰነዝሩት ማስተዋል የታከለበት ሐሳብ አማካኝነት ልባቸው የተሰበረ ሰዎች ለሚያሰሙት ጩኸት በትክክለኛው ጊዜ መልስ እንደሚሰጥ እርግጠኛ ሁን። በእርግጥም ይህ ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጠው ጠቃሚ ዝግጅት ነው።
በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች አማካኝነት የሚገኝ እርዳታ
በሐዘን የተደቆሰ ሰው ራሱን እንዲያገል ለሚያደርጉት አሉታዊ አስተሳሰቦች የተጋለጠ ነው። ይሁን እንጂ ምሳሌ 18:1 (NW) “ራሱን የሚያገል ሰው የራስ ወዳድነት ምኞቱን ለማሟላት ይሻል፤ ጥበብንም ሁሉ ይቃወማል” በማለት ያስጠነቅቃል። አሌክስ “የትዳር ጓደኛችሁን በሞት ስታጡ አእምሯችሁ በአፍራሽ አስተሳሰቦች ይሞላል” በማለት ሐቁን ተናግሯል። “ማድረግ የምችለው ሌላ ነገር ነበር? ይበልጥ አሳቢና የሰው ስሜት የሚገባኝ መሆን እችል ነበር?” ብሎ ራሱን ይጠይቅ እንደነበር ትዝ ይለዋል። “ብቸኛ ሆኜ መኖር አልፈልግም ነበር፤ ነጠላ መሆን አልፈልግም ነበር። እያንዳንዱ ቀን ብቸኛ መሆናችሁን ስለሚያስታውሳችሁ እንዲህ ዓይነቱን አስተሳሰብ ማስወገድ በጣም ከባድ ይሆንባችኋል።”
መንፈሱ የተሰበረ ሰው ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ከሌሎች ጋር መቀራረብ ያስፈልገዋል። የጉባኤ ስብሰባዎች ደግሞ ከሌሎች ጋር ለመቀራረብ ሰፊ አጋጣሚ ይከፍቱልናል። በስብሰባ ላይ ስንሆን አእምሯችን አዎንታዊና ገንቢ በሆነ አምላካዊ አስተሳሰብ ይሞላል።
ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላለንበት ሁኔታ ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖረን ይረዱናል። መጽሐፍ ቅዱስ ሲነበብ ስናዳምጥ ብሎም በሰማነው ነገር ላይ ስናሰላስል አእምሯችን በደረሰብን መከራ ላይ ብቻ ሳይሆን በእርግጥ አስፈላጊ በሆኑት ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩር እናደርጋለን፤ በሌላ አባባል ይበልጥ ትኩረት የምናደርገው በይሖዋ ሉዓላዊነት መረጋገጥና በስሙ መቀደስ ላይ ይሆናል። ከዚህም በላይ ሰዎች የደረሰብንን ጭንቀት ባያውቁም ወይም ባይረዱልንም እንኳ እንደነዚህ ባሉት ቦታዎች የምናገኘው መንፈሳዊ ትምህርት ይሖዋ ሁኔታችንን በእርግጥ እንደሚረዳልን እንድንገነዘብ ስለሚያደርገን መንፈሳችን ይጠናከራል። ይሖዋ ‘የልብ ሐዘን መንፈስን እንደሚሰብር’ ያውቃል። (ምሳሌ 15:13) እውነተኛው አምላክ ሊረዳን እንደሚፈልግ ማወቃችን፣ ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ ወደፊት እንድንገፋ የሚስችለንን ብርታት ይሰጠናል።—መዝ. 27:14
ንጉሥ ዳዊት ከጠላቶቹ ከባድ ጫና ይደርስበት በነበረ ጊዜ “መንፈሴ በውስጤ ዝላለች፤ ልቤም በውስጤ ደንግጦአል” በማለት ወደ አምላክ ጮዃል። (መዝ. 143:4) የመከራዎች መደራረብ ብዙውን ጊዜ አካላዊም ሆነ ስሜታዊ ጥንካሬን ሊያሟጥጥ አልፎ ተርፎም ልብን ሊያዝል ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ሕመም አሊያም የአካል ጉዳት መከራ ሊሆንብን ይችላል። ይሁን እንጂ ይሖዋ እንድንጸና እንደሚረዳን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (መዝ. 41:1-3) አምላክ በዛሬው ጊዜ ማንንም ሰው ተአምራዊ በሆነ መንገድ ባይፈውስም የታመመው ግለሰብ ችግሩን እንዲቋቋም ጥበብና የመንፈስ ጥንካሬ ይሰጠዋል። ዳዊት መከራዎች ሲደራረቡበት እርዳታ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ዞር እንዳለ አትዘንጋ። ዳዊት “የቀድሞውን ዘመን አስታወስሁ፤ ሥራህንም ሁሉ አሰላሰልሁ፤ የእጅህንም ሥራ አውጠነጠንሁ” በማለት ዘምሯል።—መዝ. 143:5
በአምላክ ቃል ውስጥ የተመዘገቡ እንደነዚህ ያሉ በመንፈስ መሪነት የተነገሩ ሐሳቦች ይሖዋ ስሜታችንን እንደሚረዳልን ያመለክታሉ። እንደነዚህ ያሉ ጥቅሶች ይሖዋ ልመናችንን እንደሚሰማ ዋስትና ይሰጣሉ። የይሖዋን እርዳታ የምንቀበል ከሆነ እሱ ራሱ ‘ደግፎ ይይዘናል።’—መዝ. 55:22
“ያለማቋረጥ ጸልዩ”
ያዕቆብ 4:8 “ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል” ይላል። ወደ አምላክ መቅረብ የሚቻልበት አንዱ መንገድ ጸሎት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “ያለማቋረጥ ጸልዩ” በማለት ምክር ሰጥቶናል። (1 ተሰ. 5:17) ስሜታችንን በቃላት መግለጽ ቢያቅተን እንኳ “መንፈስ ራሱ ስለ እኛ ይማልዳል።” (ሮም 8:26, 27) ይሖዋ ስሜታችንን እንደሚረዳልን ምንም ጥርጥር የለውም።
ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት የመሠረተች ሞኒካ የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “ጸሎት፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብና የግል ጥናት ይሖዋ የቅርብ ወዳጄ እንደሆነ እንዲሰማኝ አድርጎኛል። ይሖዋ በጣም እውን ስለሆነልኝ በሕይወቴ ውስጥ ብዙ ጊዜ እጁን ማየት ችያለሁ። እኔ ራሴ የሚሰማኝን ነገር መግለጽ በማልችልበት ጊዜም እንኳ እሱ እንደሚረዳኝ ማወቄ ያጽናናኛል። የይሖዋ ደግነትና በረከት መቼም እንደማይነጥፍ አውቃለሁ።”
እንግዲያው የእምነት ባልንጀሮቻችን የሚሰነዝሯቸውን አጽናኝ የሆኑ ሐሳቦች እንቀበል፤ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የሰማናቸውን በደግነት የተሰጡ ምክሮችና እምነት የሚያጠነክሩ ማሳሰቢያዎች ተግባራዊ እናድርግ እንዲሁም በጸሎት ወደ ይሖዋ በመቅረብ የልባችንን አውጥተን እንንገረው። ይሖዋ እነዚህን ወቅታዊ ዝግጅቶች ማድረጉ እንደሚያስብልን ያሳያል። አሌክስ ከራሱ ተሞክሮ በመነሳት እንደተናገረው “ይሖዋ እኛን በመንፈሳዊ ለማጠንከር ባደረገልን ዝግጅቶች በሚገባ ለመጠቀም የበኩላችንን ጥረት የምናደርግ ከሆነ የሚደርስብንን መከራ ሁሉ ለመቋቋም የሚያስችል ‘ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነ ኃይል’ እናገኛለን።”—2 ቆሮ. 4:7
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ልባቸው ለተሰበረ ሰዎች የሚሆን መጽናኛ
የመዝሙር መጽሐፍ፣ የሰዎችን ስሜት የሚገልጹ በርካታ አገላለጾችን የያዘ ከመሆኑም በላይ ይሖዋ ስሜታቸው ከመጎዳቱ የተነሳ ልባቸው የተሰበረ ሰዎች የሚያሰሙትን ጩኸት እንደሚሰማ ዋስትና የሚሰጡ በርካታ ሐሳቦችን ይዟል። የሚከተሉትን ስንኞች እንመልከት፦
“በተጨነቅሁ ጊዜ እግዚአብሔርን [“ይሖዋን፣” NW] ጠራሁት፤ እንዲረዳኝም ወደ አምላኬ ጮኽሁ፤ እርሱም ከመቅደሱ ድምፄን ሰማ፤ ጩኸቴም ከፊቱ ደረሰ፤ ወደ ጆሮውም ገባ።”—መዝ. 18:6
“እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፤ መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል።”—መዝ. 34:18
“[ይሖዋ] ልባቸው የተሰበረውን ይፈውሳል፤ ቍስላቸውንም ይጠግናል።”—መዝ. 147:3
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መከራ ሲደርስብን ‘በወቅቱ የሚሰጠን ቃል’ እንዴት የሚያጽናና ነው!