በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ያለውን ኃይል ተመልክቻለሁ

የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ያለውን ኃይል ተመልክቻለሁ

የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ያለውን ኃይል ተመልክቻለሁ

ቪቶ ፍራኤዜ እንደተናገረው

ትሬንቲናራ ስለምትባለው ከተማ ሰምታችሁ አታውቁ ይሆናል። ትሬንቲናራ የምትገኘው ከኔፕልስ፣ ጣሊያን በስተ ደቡብ ሲሆን ወላጆቼና ታላቅ ወንድሜ አንጀሎ የተወለዱት በዚህች ከተማ ነው። አንጀሎ ከተወለደ በኋላ ወላጆቼ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ በመዛወር ሯችስተር፣ ኒው ዮርክ ውስጥ መኖር ጀመሩ፤ እኔም በ1926 በዚህ አካባቢ ተወለድኩ። አባቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ከመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች (በወቅቱ የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠሩበት ስም ነው) ጋር የተገናኘው በ1922 ነበር። ብዙም ሳይቆይ አባቴና እናቴ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ሆኑ።

አባቴ ለሌሎች የሚጨነቅ ረጋ ያለ ሰው ቢሆንም የፍትሕ መጓደል በጣም ያስቆጣው ነበር። የሃይማኖት መሪዎቹ ሕዝቡን ለድንቁርና መዳረጋቸው ያንገበግበው ስለነበር የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሰዎች ለማካፈል ያገኘውን አጋጣሚ ሁሉ ይጠቀም ነበር። አባቴ ጡረታ ሲወጣ ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት የገባ ሲሆን በጤና ማጣትና በክረምቱ ቅዝቃዜ የተነሳ ለማቆም እስከተገደደበት እስከ 74 ዓመቱ ድረስ በዚህ አገልግሎት ጸንቷል። የሚገርመው የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ካቆመበት ጊዜ ጀምሮ ዕድሜው በ90ዎቹ ዓመታት ውስጥ ሆኖም እንኳ በወር ከ40 እስከ 60 ሰዓት በስብከቱ ሥራ ያሳልፍ ነበር። የአባቴ ምሳሌነት በእኔ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ አሳድሯል። ተጫዋች ቢሆንም ቁምነገረኛ ነበር። ብዙ ጊዜ አባቴ “እውነትን በቁም ነገር መያዝ ይገባል” ይል ነበር።

አባቴና እናቴ ለአምስቱም ልጆቻቸው የአምላክን ቃል ለማስተማር ጥረት አድርገዋል። እኔም ነሐሴ 23, 1943 የተጠመቅኩ ሲሆን ሰኔ 1944 አቅኚ ሆንኩ። እህቴ ካርሜላ ፍልቅልቅ ከሆነችው ፈርን የተባለች የአገልግሎት ጓደኛዋ ጋር በጄኔቫ፣ ኒው ዮርክ በአቅኚነት ታገለግል ነበር። ቀሪ ሕይወቴን ማሳለፍ የምፈልገው ከዚህች ወጣት ጋር እንደሆነ ለመገንዘብ ጊዜ አልፈጀብኝም። በመሆኑም ነሐሴ 1946 ከፈርን ጋር ተጋባን።

የሚስዮናዊነት አገልግሎት

ከፈርን ጋር ከተጋባን በኋላ ጄኔቫ እና ኖርዊች በተባሉ የኒው ዮርክ ከተሞች ልዩ አቅኚ ሆነን እንድናገለግል ተመደብን። ነሐሴ 1948 በጊልያድ ትምህርት ቤት 12ኛው ክፍል ውስጥ ገብተን የመሠልጠን መብት አገኘን። ከዚያም ካርልና ጆአን ከሚባሉ ባልና ሚስት ሚስዮናውያን ጋር በኔፕልስ፣ ጣሊያን እንድናገለግል ተመደብን። ኔፕልስ በወቅቱ ጦርነቱ ካስከተለባት ጉዳት ለማገገም እየታገለች ነበር። መኖሪያ ቤት ማግኘት አስቸጋሪ ነበር፤ በመሆኑም ሁለት ትንንሽ ክፍሎች ባለው አንድ አፓርታማ ውስጥ ለጥቂት ወራት ኖርን።

ወላጆቼ የኔፕልስን ቀበልኛ ሲናገሩ እሰማ ስለነበር ጣሊያንኛዬ ወደ አሜሪካዎቹ ወሰድ ቢያደርገውም ለመግባባት ያህል በቂ ነበር። ፈርን ቋንቋውን መልመድ አስቸግሯት ነበር። ብዙም ሳይቆይ ግን ከእኔ እኩል መናገር ቻለች፤ እንዲያውም በኋላ ላይ ከእኔ የተሻለች ሆናለች።

መጀመሪያ ላይ በኔፕልስ ውስጥ ለእውነት ፍላጎት ያሳየው አራት አባላት ያሉት አንድ ቤተሰብ ብቻ ነበር። ይህ ቤተሰብ ሲጋራ በኮንትሮባንድ ይሸጥ ነበር። ቴሬዛ የምትባለው የቤተሰቡ አባል በእያንዳንዱ የሥራ ቀን አስገራሚ ለውጥ ይታይባት ነበር። ጠዋት ላይ በልብሷ ኪሶች ውስጥ ሲጋራ አጭቃ ስለምትወጣ ወፍራም ትመስላለች። ማታ ላይ ግን ስንጥር ታክላለች። እውነት ይህን ቤተሰብ ሙሉ በሙሉ ቀይሮታል። ከጊዜ በኋላ 16 የሚሆኑ የዚህ ቤተሰብ አባላት የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል። በአሁኑ ጊዜ በኔፕልስ ከተማ 3,700 የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ይገኛሉ።

ሥራችን ተቃውሞ ገጠመው

በኔፕልስ ዘጠኝ ወር ብቻ ከኖርን በኋላ ባለሥልጣናቱ አራታችንም ከተማዋን ለቀን እንድንወጣ አስገደዱን። ለአንድ ወር ገደማ ስዊዘርላንድ ከቆየን በኋላ የቱሪስት ቪዛ በማስመታት ወደ ጣሊያን ተመለስን። ከዚያም እኔና ፈርን ቱሪን ተመደብን። እዚያ እንደደረስን አንድ ክፍል ቤት የተከራየን ሲሆን ካከራየችን ሴት ጋር ባኞ ቤቱንና ወጥ ቤቱን በጋራ እንጠቀም ነበር። ካርልና ጆአን ወደ ቱሪን ሲመጡ ግን አብረን አንድ አፓርታማ ተከራየን። ከጊዜ በኋላ ባልና ሚስት የሆኑ አሥር ሚስዮናውያን ሚስዮናውያን በዚህ ቤት ውስጥ ኖረዋል።

በ1955 ባለሥልጣናቱ ቱሪንን ለቀን እንድንወጣ እስካስገደዱን ጊዜ ድረስ አራት አዳዲስ ጉባኤዎች መቋቋም ችለው ነበር። ከመውጣታችን በፊት ጥሩ መሠረት ስለተጣለ የአካባቢው ወንድሞች ጉባኤዎቹን መምራት ይችሉ ነበር። ባለሥልጣናቱ “እናንተ አሜሪካውያን ከከተማችን ውጡ እንጂ የገነባችሁት ሁሉ እንዳልነበር እንደሚሆን እርግጠኞች ነን” ብለውን ነበር። ይሁንና ከዚያ በኋላ የተገኘው ጭማሪ እንደሚያሳየው የሥራው ስኬታማነት የተመካው በአምላክ ነው። ዛሬ በቱሪን ከ4,600 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮችና 56 ጉባኤዎች ይገኛሉ።

ፍሎረንስ —ውብ የሆነች ከተማ

ቀጣዩ የአገልግሎት ምድባችን ፍሎረንስ ነበር። እህቴ ካርሜላና ባለቤቷ መርለን ሃርትስለር በፍሎረንስ ሚስዮናዊ ሆነው ያገለግሉ ስለነበር ስለ ከተማዋ ብዙ ሰምተናል። በዚያ መኖር ደግሞ ምን ያህል አስደሳች ሊሆን እንደሚችል መገመት ትችላላችሁ። እንደ ፒያሳ ዴላ ሲኞሪያ፣ ፖንቴ ቬኪዮ፣ ፒያሳሌ ሚኬላንጀሎ እና ፓላትሶ ፒቲ ያሉ ቦታዎች ከተማዋን ውበት እንድትላበስ አድርገዋታል። በፍሎረንስ የሚኖሩ አንዳንድ ሰዎች ለምሥራቹ ጥሩ ምላሽ ሲሰጡ መመልከት እንዴት የሚያስደስት ነበር!

በዚያ አንድ ቤተሰብ ያስጠናን ሲሆን አባትየውና እናትየው ተጠመቁ። ይሁንና አባትየው የማጨስ ልማድ ነበረው። በ1973 የወጣው መጠበቂያ ግንብ ማጨስ የሚያረክስ ልማድ እንደሆነና የሚያጨሱ ሰዎች ይህን ልማዳቸውን እንዲያቆሙ የሚያስጠነቅቅ ሐሳብ ይዞ ወጣ። በዚህ ጊዜ ትልልቆቹ ልጆች አባታቸው ማጨሱን እንዲያቆም ለመኑት። አባትየው ላለማጨስ ቃል ቢገባም ሊያቆም አልቻለም። አንድ ቀን ምሽት ባለቤቱ ዘጠኝ ዓመት ዕድሜ ያላቸውን መንታ ልጆቻቸውን ወደ መኝታቸው እንዲሄዱ ነገረቻቸው፤ ከመተኛታቸው በፊት ከልጆቹ ጋር የመጸለይ ልማድ ቢኖራትም በዚህ ጊዜ ግን እንዲህ አላደረገችም። በኋላ ላይ ያደረገችው ነገር ትክክል እንዳልሆነ ተሰምቷት ወደ ክፍላቸው ስትሄድ እሷ ከመምጣቷ በፊት እንደጸለዩ ነገሯት። “ምን ብላችሁ ጸለያችሁ?” በማለት ጠየቀቻቸው። “እባክህ ይሖዋ፣ አባባ ማጨስ እንዲያቆም እርዳው” በማለት እንደጸለዩ ነገሯት። እሷም ባለቤቷን “ና፣ ልጆችህ ምን ብለው እንደጸለዩ ስማ” አለችው። እሱም ልጆቹ የጸለዩትን ሲሰማ ማልቀስ ጀመረ፤ ከዚያም “ከእንግዲህ ወዲህ አላጨስም!” አለ። አባትየው ቃሉን የጠበቀ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ከ15 በላይ የሚሆኑ የዚህ ቤተሰብ አባላት የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል።

በአፍሪካ ያከናወንነው አገልግሎት

በ1959 ከአርቱሮ ሌቨረስና ከወንድሜ ከአንጀሎ ጋር ሆነን በሚስዮናዊነት እንድናገለግል ሞቃዲሾ፣ ሶማሊያ ተመደብን። እዚያ በደረስንበት ወቅት የፖለቲካው ሁኔታ ውጥረት የነገሠበት ነበር። የጣሊያን መንግሥት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሰጠው ሥልጣን መሠረት ሶማሊያ ነፃ አገር እንድትሆን የመርዳት ኃላፊነት ነበረበት፤ ሆኖም ሁኔታው ተስፋ አስቆራጭ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ እናስጠናቸው የነበሩ አንዳንድ ጣሊያናውያን አገሪቷን ለቀው ስለወጡ በሶማሊያ ጉባኤ ማቋቋም አልተቻለም።

በዚያን ጊዜ የዞን የበላይ ተመልካቹ የእሱ ረዳት ሆኜ እንዳገለግል ሐሳብ አቀረበ። በመሆኑም አብረን በአካባቢው ያሉ አገሮችን መጎብኘት ጀመርን። እናስጠናቸው ከነበሩት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ እድገት ያደረጉ ቢሆንም በስደት ምክንያት አገራቸውን ለቀው ለመሄድ ተገደዋል። ሌሎቹ ግን ከፍተኛ ስደት ቢኖርም በዚያው ለመቆየት መርጠዋል። * ለይሖዋ ያላቸውን ፍቅር እንዲሁም ታማኝነታቸውን ለመጠበቅ ሲሉ የተቋቋሙትን መከራ ስናስብ ዓይናችን በእንባ ይሞላል።

በሶማሊያና በኤርትራ የሙቀቱ መጠን በአብዛኛው ከፍተኛ የነበረ ከመሆኑም በላይ አየሩ በጣም ይወብቅ ነበር። በዚያ ላይ የተወሰኑት የባሕል ምግቦቻቸው የሚያቃጥሉ ስለሆኑ ይበልጥ ሙቀት እንዲሰማን ያደርጉን ነበር። እንዲህ ያሉ ምግቦችን ለመጀመሪያ ጊዜ የበላነው መጽሐፍ ቅዱስ በምናስጠናት አንዲት ሴት ቤት ውስጥ ነበር፤ በዚያን ጊዜ ባለቤቴ ጆሮዋ እንደ ቀይ የትራፊክ መብራት እንዳበራ በቀልድ መልክ ተናግራለች።

አንጀሎና አርቱሮ ሌላ ቦታ ሲመደቡ ብቻችንን ቀረን። አይዟችሁ የሚለን ሰው ከጎናችን አለመኖሩ ከብዶን ነበር። ያም ሆኖ ሁኔታው የበለጠ ወደ ይሖዋ እንድንቀርብና ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በእሱ ሙሉ በሙሉ እንድንታመን አድርጎናል። የስብከቱ ሥራ በታገደባቸው አገሮች እናደርገው የነበረው ጉብኝት የብርታት ምንጭ ሆኖልናል።

በሶማሊያ የተለያዩ ችግሮች አጋጥመውናል። ማቀዝቀዣ ስላልነበረን ማንኛውንም ምግብ ለምሳሌ የሻርክ ሥጋም ይሁን በአካባቢው የሚበቅሉትን እንደ ማንጎ፣ ፓፓያ፣ ግሬፕ፣ ኮከናትና ሙዝ ያሉ ፍራፍሬዎችን የምንገዛው ለዕለቱ የሚበቃንን ያህል ብቻ ነበር። የተለያዩ በራሪ ነፍሳትም መከራችንን ያሳዩን ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ስናስጠና አንዳንድ ጊዜ ነፍሳቱ አንገታችን ላይ እያረፉ ያስቸግሩን ነበር። ትንሽዬ ሞተር ብስክሌት ስለነበረችን ቢያንስ ቢያንስ በሚለበልበው ፀሐይ ለሰዓታት በእግራችን መጓዝ አያስፈልገንም ነበር።

ወደ ጣሊያን ተመለስን

ለጋስ ለሆኑት ወዳጆቻችን ምስጋና ይግባውና ሙዝ በጫነ ጀልባ ላይ ተሳፍረን ወደ ጣሊያን በመሄድ በ1961 በቱሪም ተካሂዶ በነበረው ብሔራት አቀፍ የአውራጃ ስብሰባ ላይ መካፈል ቻልን። እዚያ ከደረስን በኋላ ወደ ሌላ ቦታ እንደተመደብን አወቅን። መስከረም 1962 ወደ ጣሊያን ከተመለስን በኋላ በወረዳ ሥራ ማገልገል ጀመርን። በዚያን ወቅት አነስ ያለች መኪና የገዛን ሲሆን ለአምስት ዓመት ያህል በሁለት ወረዳዎች ውስጥ ሥራችንን ለማከናወን ጠቅማናለች።

ሞቃታማ ከሆነችው አፍሪካ ወጥተን አሁን ደግሞ በጣም ቀዝቃዛ የሆነውን አየር መቋቋም ነበረብን። የወረዳ ሥራችንን ከጀመርን በኋላ በመጀመሪያው ክረምት ከአልፕ ተራሮች ግርጌ የሚገኝ አንድ ጉባኤ በጎበኘንበት ወቅት ያደርነው የሣር ድርቆሽ ከሚከመርበት ክፍል በላይ በሚገኝ ምንም ማሞቂያ በሌለው ክፍል ውስጥ ነበር። በጣም ስለሚበርድ የተኛነው የለበስነውን ልብስ ሳናወልቅ ነበር። በዚያን ምሽት ከቅዝቃዜው የተነሳ አራት ዶሮዎችና ሁለት ውሾች በአቅራቢያችን ሞተው ተገኙ!

ከጊዜ በኋላ የአውራጃ የበላይ ተመልካች በመሆንም አገልግያለሁ። በእነዚህ ዓመታት መላውን ጣሊያን አዳርሰናል። እንደ ካላብሪያና ሲሲሊ ያሉ ቦታዎችን በተደጋጋሚ ጊዜ ጎብኝተናል። ወጣቶችን በመንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ እንዲሁም የጉባኤ የበላይ ተመልካቾች፣ ተጓዥ አገልጋዮች እና ቤቴላውያን ለመሆን እንዲጣጣሩ አበረታትተናቸዋል።

ይሖዋን በሙሉ ልባቸው ከሚያገለግሉ ታማኝ ወዳጆቻችን ብዙ ተምረናል። ለይሖዋ ያላቸውን ፍጹም ታማኝነት፣ ለጋስነታቸውን፣ ለወንድሞች ያላቸውን ፍቅር፣ ከሁኔታዎች ጋር ተስማምቶ ለመኖር የሚያደርጉትን ጥረትና ያላቸውን የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ በጣም እናደንቅላቸዋለን። በመንግሥት አዳራሽ በተደረጉ የሠርግ ሥነ ሥርዓቶች ላይ ተገኝተናል። ሃይማኖታዊ አገልጋዮች እንደሆኑ ተደርገው በሕግ እውቅና ያገኙ የይሖዋ ምሥክሮች እነዚህን የሠርግ ሥነ ሥርዓቶች ያስፈጽማሉ፤ ከዓመታት በፊት ግን በአገሪቱ በዚህ መንገድ ጋብቻ መፈጸም የማይታሰብ ነበር። በቱሪን ያሉ ጉባኤዎች፣ ቀድሞ ያደርጉት እንደነበረው በወንድሞች ወጥ ቤት ውስጥ ሆነው ወይም አግዳሚ ወንበር ላይ ቁጭ ብለው ስብሰባ ማድረጋቸው ቀርቷል። ከዚህ ይልቅ አብዛኞቹ ጉባኤዎች ለይሖዋ ክብር የሚያመጡ ማራኪ የመንግሥት አዳራሾች አሏቸው። ትላልቅ ስብሰባዎቻችንን ጠባብ በሆኑ የትያትር ቤቶች ውስጥ ማድረጋችን ቀርቶ ሰፋፊ በሆኑ የስብሰባ አዳራሾች ውስጥ እንሰበሰባለን። ለመጀመሪያ ጊዜ ጣሊያን ስንሄድ የአስፋፊዎች ቁጥር 490 ብቻ ነበር። አሁን ግን ከ243,000 በላይ አስፋፊዎች እንዳሉ መመልከት በጣም የሚያስደስት ነው።

ጥሩ ውሳኔ አድርገናል

አንዳንድ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን አሳልፈናል፤ ለምሳሌ የሚናፍቁን ነገሮች የነበሩ ከመሆኑም በላይ ከሕመም ጋር መታገል ነበረብን። ፈርን ባሕር ባየች ቁጥር ያደገችበት ቦታ ይናፍቃት ነበር። በተጨማሪም ሦስት ጊዜ ከባድ ቀዶ ሕክምና ተደርጎላታል። በአንድ ወቅት ጥናት ለማስጠናት እየሄደች ሳለ አንድ ተቃዋሚ በመንሽ መታት። በዚህ ጊዜም ቢሆን ጉዳት ስለደረሰባት ሆስፒታል መሄድ አስፈልጓት ነበር።

አንዳንድ ጊዜ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ቢሰማንም በሰቆቃወ ኤርምያስ 3:24 ላይ እንደተገለጸው ይሖዋን ‘ተስፋ እናደርጋለን።’ ይሖዋ የመጽናናት አምላክ ነው። ተስፋ በቆረጥንበት በአንድ ወቅት ፈርን ከወንድም ናታን ኖር ደስ የሚል ደብዳቤ ደረሳት። ፈርን አቅኚነት በጀመረችበት በቤተልሔም፣ ፔንሲልቬንያ የተወለደው ወንድም ኖር እንደ እሷ ያሉ የፔንሲልቬንያ ደች ሴቶች ጠንካራና ቆራጥ መሆናቸውን እንደሚያውቅ በደብዳቤው ላይ ገልጿል። የተናገረው እውነት ነበር። ባለፉት ዓመታት ከተለያየ አቅጣጫ ማበረታቻ አግኝተናል።

የተለያዩ ችግሮች ቢኖሩብንም ለአገልግሎቱ ያለን ቅንዓት እንዳይቀዘቅዝ ጥረት እናደርግ ነበር። ፈርን የቅንዓት መንፈስን ላምብሮስኮ ከሚባለው ጋዝ ያለው ጣፋጭ የጣሊያን ወይን ጋር በማመሳሰል “የመንፈሳችን ጋዝ ወጥቶ እንዲያልቅ ማድረግ የለብንም” በማለት በቀልድ መልክ ተናግራለች። በወረዳና በአውራጃ ሥራ ከ40 ለሚበልጡ ዓመታት ካገለገልን በኋላ ከጣሊያንኛ ውጪ ባሉ ቋንቋዎች የሚመሩ ቡድኖችንና ጉባኤዎችን የመጎብኘትና የማደራጀት መብት አገኘን። እነዚህ ቡድኖች ከሕንድ፣ ከስሪላንካ፣ ከቻይና፣ ከናይጄሪያ፣ ከኢትዮጵያ፣ ከኤርትራ፣ ከጋና፣ ከፊሊፒንስና ከሌሎች አገሮች ለመጡ ሰዎች ምሥራቹን ይሰብካሉ። የአምላክ ቃል ያለው ኃይል በሰዎች ሕይወት ውስጥ አስገራሚ ለውጥ ሲያመጣ ተመልክተናል፤ እነዚህ ሰዎች የአምላክን ምሕረት የቀመሱት እንዴት እንደሆነ እንዘርዝር ብንል መጽሐፍ አይበቃንም።—ሚክ. 7:18, 19

ይሖዋ አገልግሎታችንን እንድንፈጽም የሚረዳንን ስሜታዊም ሆነ አካላዊ ጥንካሬ ዘወትር እንዲሰጠን በየቀኑ እንጸልያለን። ጌታ የሚሰጠው ደስታ ብርታታችን ነው። ዓይናችንን የሚያበራ ከመሆኑም በላይ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለማሰራጨት ያደረግነው ውሳኔ ትክክለኛ እንደሆነ እንዲሰማን ያደርገናል።—ኤፌ. 3:7፤ ቆላ. 1:29

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.18 የ1992 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ ከገጽ 95-184 ተመልከት።

[በገጽ 27-29 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ/ሥዕሎች]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ወላጆቼ በሯችስተር፣ ኒው ዮርክ

1948

በሳውዝ ላንሲንግ የ12ኛው ክፍል የጊልያድ ትምህርት ቤት

1949

ወደ ጣሊያን ከመሄዳችን በፊት ከፈርን ጋር

ካፕሪ፣ ጣሊያን

1952

ከሌሎች ሚስዮናውያን ጋር፣ በቱሪንና በኔፕልስ

1963

ፈርን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቿ ጋር

“የመንፈሳችን ጋዝ ወጥቶ እንዲያልቅ ማድረግ የለብንም”