በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መንፈስ ቅዱስ ፈተናዎችን ለመወጣትና የተስፋ መቁረጥ ስሜትን ለማሸነፍ ኃይል ይሰጠናል

መንፈስ ቅዱስ ፈተናዎችን ለመወጣትና የተስፋ መቁረጥ ስሜትን ለማሸነፍ ኃይል ይሰጠናል

መንፈስ ቅዱስ ፈተናዎችን ለመወጣትና የተስፋ መቁረጥ ስሜትን ለማሸነፍ ኃይል ይሰጠናል

“መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በሚወርድበት ጊዜ ኃይል ትቀበላላችሁ።”—ሥራ 1:8

1, 2. ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ምን እርዳታ እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቶላቸው ነበር? እንዲህ ዓይነት እርዳታ ያስፈለጋቸውስ ለምን ነበር?

ኢየሱስ፣ ለደቀ መዛሙርቱ የሰጣቸውን ተልእኮ በሙሉ በራሳቸው ኃይል መወጣት እንደማይችሉ ያውቅ ነበር። የስብከቱ ሥራ ሰፊ ከመሆኑ እንዲሁም ተቃዋሚዎቻቸው ኃያል ከመሆናቸውና ደቀ መዛሙርቱ ካለባቸው ሰብዓዊ ድክመት አንጻር ተልእኳቸውን ለመወጣት ከሰው በላይ የሆነ ኃይል እንደሚያስፈልጋቸው ግልጽ ነበር። በመሆኑም ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ ጥቂት ቀደም ብሎ ለደቀ መዛሙርቱ የሚከተለውን ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል፦ “መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በሚወርድበት ጊዜ ኃይል ትቀበላላችሁ፤ በኢየሩሳሌምም ሆነ በመላው ይሁዳ፣ በሰማርያ እንዲሁም እስከ ምድር ዳር ድረስ ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ።”—ሥራ 1:8

2 ኢየሱስ የገባላቸው ቃል መፈጸም የጀመረው በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት ነበር፤ በዚህ ዕለት የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች ኢየሩሳሌምን በስብከታቸው ለመሙላት የሚያስችል ኃይል በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ተቀበሉ። የስብከቱን ሥራ ምንም ዓይነት ተቃውሞ ሊገታው አልቻለም። (ሥራ 4:20) እኛን ጨምሮ “እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ ድረስ” የሚኖሩት ታማኝ የኢየሱስ ተከታዮች አምላክ የሚሰጠውን ይህን ኃይል ማግኘታቸው አንገብጋቢ ጉዳይ ነው።—ማቴ. 28:20

3. (ሀ) በመንፈስ ቅዱስና በኃይል መካከል ያለውን ልዩነት አስረዳ። (ለ) ከይሖዋ የምናገኘው ኃይል ምን እንድናደርግ ሊረዳን ይችላል?

3 ኢየሱስ፣ ‘መንፈስ ቅዱስ በእነሱ ላይ በሚወርድበት ጊዜ ኃይል እንደሚቀበሉ’ ለደቀ መዛሙርቱ ቃል ገብቶላቸዋል። “ኃይል” የሚለው ቃል እዚህ ጥቅስ ላይ በገባበት መንገድ የሚሰጠው ትርጉም “መንፈስ” የሚለው ቃል ካለው ትርጉም የተለየ ነው። የአምላክ መንፈስ ወይም በሥራ ላይ ያለው የአምላክ ኃይል የሚያመለክተው የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም ሲባል በሰዎች ወይም በነገሮች ላይ የሚያድረውን ጉልበት ነው። “ኃይል” የሚለው ቃል በራሱ ግን “አንድን ሥራ ለማከናወን ወይም ውጤት ለማስገኘት የሚያስችል አቅም” የሚል ፍቺ አለው። ይህ “ኃይል” አንድን ነገር ለማከናወን ወይም ውጤት ለማስገኘት እስኪያስፈልግ ድረስ በአንድ ሰው ወይም ነገር ውስጥ ታምቆ ሊቀመጥ ይችላል። በመሆኑም “መንፈስ ቅዱስ” አንድን ባትሪ ድንጋይ ለመሙላት ከሚያገለግል የኤሌክትሪክ ጅረት ጋር ሊመሳሰል ይችላል፤ በሌላ በኩል ግን “ኃይል” በኤሌክትሪክ ጅረት በተሞላው ባትሪ ድንጋይ ውስጥ እንደተጠራቀመው እምቅ ጉልበት ነው። ይሖዋ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ለአገልጋዮቹ የሚሰጣቸው ኃይል እያንዳንዳችን ራሳችንን ስንወስን የገባነውን ቃል ለመፈጸም የሚያስችል አቅም እንዲኖረን ያደርገናል፤ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ደግሞ ይህ ኃይል፣ መጥፎ ነገር እንድንፈጽም የሚደርስብንን ተጽዕኖ ለመቋቋም ያስችለናል።—ሚክያስ 3:8ን እና ቆላስይስ 1:29ን አንብብ።

4. በዚህ የጥናት ርዕስ ላይ የትኞቹን ነጥቦች እንመለከታለን? እነዚህን ነጥቦች መመርመራችን ምን ጥቅም አለው?

4 አምላክ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት የሚሰጠን ኃይል የሚገለጠው በምን መንገድ ነው? መንፈስ ቅዱስ ምን ዓይነት ተግባሮችን እንድንፈጽም ያነሳሳናል? እንዲሁም የተለያዩ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ምን ዓይነት ምላሽ እንድንሰጥ ይገፋፋናል? አምላክን በታማኝነት ለማገልገል በምንጥርበት ጊዜ ሰይጣን፣ የእሱ ሥርዓትና ፍጹም ያልሆነው ሥጋችን በርካታ እንቅፋቶች እንዲጋረጡብን ያደርጋሉ። በክርስትና ጎዳና መመላለሳችንን ለመቀጠል፣ አዘውትረን በአገልግሎት ለመካፈልና ከይሖዋ ጋር ያለንን ጥሩ ወዳጅነት ላለማጣት ከፈለግን እንዲህ ያሉትን እንቅፋቶች መቋቋማችን በጣም አስፈላጊ ነው። መንፈስ ቅዱስ፣ ፈተናዎችን ለመወጣት እንዲሁም የመዛልና የተስፋ መቁረጥ ስሜትን ለመቋቋም እንዴት እንደሚረዳን እስቲ እንመልከት።

ፈተናን ለመወጣት የሚያስችል ኃይል

5. ጸሎት ኃይል እንድናገኝ ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?

5 ኢየሱስ ተከታዮቹን “ከክፉው አድነን እንጂ ወደ ፈተና አታግባን” ብለው እንዲጸልዩ አስተምሯቸዋል። (ማቴ. 6:13) ይሖዋ እንዲህ ብለው የሚለምኑትን ታማኝ አገልጋዮቹን ችላ አይላቸውም። በሌላ ወቅት ደግሞ ኢየሱስ “በሰማይ ያለው አባት ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን እንዴት አብልጦ አይሰጣቸውም” ብሎ ነበር። (ሉቃስ 11:13) ይሖዋ ትክክለኛውን ነገር ማድረግ እንድንችል የሚረዳንን ኃይል እንደሚሰጠን ቃል መግባቱ ምንኛ የሚያበረታታ ነው! እንዲህ ሲባል ግን ይሖዋ ምንም ዓይነት ፈተና እንዳይደርስብን ይከላከልልናል ማለት አይደለም። (1 ቆሮ. 10:13) ሆኖም ፈተና ሲያጋጥመን ከወትሮው በበለጠ አጥብቀን ወደ ይሖዋ መጸለይ አለብን።—ማቴ. 26:42

6. ኢየሱስ ሰይጣን ላቀረበለት ፈተና መልስ የሰጠው ከየት ነው?

6 ኢየሱስ፣ ዲያብሎስ ላቀረበለት ፈተና መልስ የሰጠው ከቅዱሳን መጻሕፍት ነው። ኢየሱስ በተደጋጋሚ ጊዜ “ተብሎ ተጽፏል” ማለቱ እንዲሁም “አንተ ሰይጣን፣ ከፊቴ ራቅ! ‘ይሖዋ አምላክህን ብቻ አምልክ፤ ለእሱም ብቻ ቅዱስ አገልግሎት አቅርብ’ ተብሎ ተጽፏልና” ብሎ መመለሱ የአምላክን ቃል ጠንቅቆ ያውቅ እንደነበር ያሳያል። ኢየሱስ ለይሖዋና ለቃሉ ያለው ፍቅር ፈታኙ ባቀረበለት ማባበያዎች እንዳይሸነፍ ረድቶታል። (ማቴ. 4:1-10) ኢየሱስ በተደጋጋሚ የቀረበለትን ፈተና ከተቋቋመ በኋላ ሰይጣን ትቶት ሄደ።

7. መጽሐፍ ቅዱስ ፈተናዎችን ለመቋቋም የሚረዳን እንዴት ነው?

7 ኢየሱስ፣ ዲያብሎስ ያቀረበለትን ፈተና ለመቋቋም በቅዱሳን መጻሕፍት ከተጠቀመ እኛማ እንዲህ ማድረጋችን ምንኛ አስፈላጊ ነው! ዲያብሎስንና ወኪሎቹን መቃወም እንድንችል መጀመሪያ የአምላክን መሥፈርቶች ለማወቅና ከእነዚህ መሥፈርቶች ጋር ሙሉ በሙሉ ተስማምተን ለመኖር ቁርጥ አቋም ሊኖረን ይገባል። ብዙ ሰዎች ቅዱሳን መጻሕፍትን ማጥናታቸው እንዲሁም የአምላክን ጥበብና የጽድቅ መሥፈርቶች መረዳታቸው ብሎም ከፍ አድርገው መመልከታቸው በመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች ለመመራት አነሳስቷቸዋል። በእርግጥም “የአምላክ ቃል” ኃይለኛ ነው፤ “የልብንም ሐሳብና ዓላማ መረዳት ይችላል።” (ዕብ. 4:12) አንድ ሰው ቅዱሳን መጻሕፍትን ባነበበና በዚያ ላይ ባሰላሰለ መጠን የይሖዋን “እውነት” ይበልጥ መረዳት ይችላል። (ዳን. 9:13) በመሆኑም ያሉብንን ድክመቶች ለማሸነፍ በሚረዱን ጥቅሶች ላይ ማሰላሰል አለብን።

8. መንፈስ ቅዱስን ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

8 ኢየሱስ ፈተናዎችን ለመቋቋም የቻለው ቅዱሳን መጻሕፍትን ከማወቁም በተጨማሪ “በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ” ስለነበር ነው። (ሉቃስ 4:1) እኛም እንደ ኢየሱስ ዓይነት ጥንካሬና ችሎታ እንዲኖረን ይሖዋ ለእኛ መንፈስ ቅዱስን ለመስጠት ባደረጋቸው ዝግጅቶች ሙሉ በሙሉ በመጠቀም ወደ እሱ ይበልጥ መቅረብ ያስፈልገናል። (ያዕ. 4:7, 8) ከእነዚህም መካከል መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት፣ መጸለይና ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር መሰብሰብ ይገኙበታል። ከዚህም በተጨማሪ ብዙዎች በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች መጠመዳቸው አእምሯቸው በሚያንጹ መንፈሳዊ ሐሳቦች ላይ እንዲያተኩር ለማድረግ አስችሏቸዋል።

9, 10. (ሀ) በአካባቢህ የተለመዱት ፈተናዎች የትኞቹ ናቸው? (ለ) ማሰላሰልና ጸሎት፣ በምትዝልበት ጊዜም እንኳ ፈተናዎችን ለመቋቋም የሚያስችል ኃይል እንድታገኝ የሚረዱህ እንዴት ነው?

9 ምን ዓይነት ፈተናዎች ያጋጥሙሃል? የትዳር ጓደኛህ ያልሆነን ግለሰብ ለማሽኮርመም ተፈትነህ ታውቃለህ? ያላገባህ ከሆንክ ደግሞ ከማያምን ሰው ጋር የፍቅር ግንኙነት ለመጀመር ቃጥቶህ ያውቃል? ክርስቲያኖች ቴሌቪዥን ሲመለከቱ ወይም ኢንተርኔት ሲጠቀሙ ርኩስ የሆነ ነገር ድንገት ብቅ ሊልባቸው ይችላል። እንዲህ ያለ ነገር አጋጥሞህ ያውቃል? ከሆነ ምን እርምጃ ወሰድህ? አንድ ስህተት መሥራት ወደ ሌላ ስህተት እንደሚመራና ይህም ውሎ አድሮ ለከባድ ኃጢአት እንደሚዳርግ ማስታወሱ ጠቃሚ ነው። (ያዕ. 1:14, 15) ኃጢአት ብትሠራ ይሖዋ፣ ጉባኤውና ቤተሰቦችህ ምን ያህል እንደሚጎዱ አስብ። በሌላ በኩል ግን የአምላክን መመሪያዎች በታማኝነት ስንጠብቅ ንጹሕ ሕሊና ይኖረናል። (መዝሙር 119:37ን እና ምሳሌ 22:3ን አንብብ።) እንዲህ ያሉ ፈተናዎች ሲያጋጥሙህ እነሱን ለመቋቋም የሚያስችል ጥንካሬ እንዲሰጥህ ወደ ይሖዋ ለመጸለይ ቁርጥ ውሳኔ አድርግ።

10 ኢየሱስ ካጋጠመው ፈተና ጋር በተያያዘ ልናስታውሰው የሚገባ ሌላም ነገር አለ። ሰይጣን ኢየሱስን የፈተነው ኢየሱስ በምድረ በዳ ለ40 ቀናት ከጾመ በኋላ ነበር። ዲያብሎስ የኢየሱስን ታማኝነት ለመፈተን ይህ በጣም “አመቺ ጊዜ” እንደሆነ ሳይሰማው አልቀረም። (ሉቃስ 4:13) ሰይጣን የእኛንም ታማኝነት ለመፈተን አመቺ ጊዜ ይፈልጋል። በመሆኑም ሁልጊዜ በመንፈሳዊ ጠንካራ መሆናችን አስፈላጊ ነው። ሰይጣን አብዛኛውን ጊዜ ጥቃት የሚሰነዝረው ዒላማ ያደረገው ሰው በጣም በሚደክምበት ወቅት ነው። እንግዲያው በምንዝልበት ወይም ተስፋ በምንቆርጥበት ጊዜ ይሖዋ ጥበቃ እንዲያደርግልንና መንፈስ ቅዱሱን እንዲሰጠን ከምንጊዜውም የበለጠ አጥብቀን ለመለመን ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ አለብን።—2 ቆሮ. 12:8-10

የመዛልና የተስፋ መቁረጥ ስሜትን ለመቋቋም የሚያስችል ኃይል

11, 12. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ብዙዎች ተስፋ የሚቆርጡት ለምንድን ነው? (ለ) የተስፋ መቁረጥ ስሜትን ለመቋቋም የሚረዳን ኃይል ማግኘት የምንችለው ከየት ነው?

11 ፍጹማን ባለመሆናችን አልፎ አልፎ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ያጋጥመናል። በተለይ አሁን ያለንበት ጊዜ በውጥረት የተሞላ በመሆኑ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ማጋጠሙ የተለመደ ነው። የምንኖርበት ጊዜ በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ከነበሩት ሁሉ ይበልጥ እጅግ አስቸጋሪው ሳይሆን አይቀርም። (2 ጢሞ. 3:1-5) አርማጌዶን እየቀረበ ሲሄድ የኢኮኖሚው ሁኔታ ወይም ሌሎች ነገሮች በስሜታችን ላይ የሚፈጥሩት ጫና ይጨምራል። በመሆኑም አንዳንዶች ቤተሰባቸውን የመንከባከብና የሚያስፈልጋቸውን የማቅረብ ኃላፊነታቸውን መወጣት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከበዳቸው መምጣቱ ሊያስገርመን አይገባም። እነዚህ ሰዎች እንደደከሙ፣ እንደዛሉ፣ ጫና እንደበዛባቸው፣ አቅም እንዳጡና ኃይላቸው እንደተሟጠጠ ይሰማቸዋል። አንተም እንደዚህ የሚሰማህ ከሆነ የሚደርስብህን ጫና መቋቋም የምትችለው እንዴት ነው?

12 ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ረዳት ይኸውም የአምላክን ቅዱስ መንፈስ እንደሚሰጣቸው የገባውን ቃል አስታውስ። (ዮሐንስ 14:16, 17ን አንብብ።) ይህ መንፈስ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ካለ ከየትኛውም ኃይል ይበልጣል። በዚህ መንፈስ አማካኝነት ይሖዋ ማንኛውንም ፈተና በጽናት ለመቋቋም የሚያስችለንን ጥንካሬ “እጅግ አብልጦ” ሊሰጠን ይችላል። (ኤፌ. 3:20) ሐዋርያው ጳውሎስ “በየአቅጣጫው ብንደቆስም” በዚህ መንፈስ የምንታመን ከሆነ “ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነው ኃይል” እንደሚሰጠን ተናግሯል። (2 ቆሮ. 4:7, 8) ይሖዋ ጭንቀትን እንደሚያስወግድልን ቃል አልገባም፤ ሆኖም የሚያጋጥመንን ውጥረት ለመወጣት የሚያስችለንን ብርታት በመንፈሱ አማካኝነት እንደሚሰጠን አረጋግጦልናል።—ፊልጵ. 4:13

13. (ሀ) አንዲት ወጣት በጣም አስቸጋሪ የሆነን ሁኔታ ለመቋቋም የሚያስችል ኃይል ያገኘችው እንዴት ነው? (ለ) አንተስ ከዚህ ጋር የሚመሳሰል የምታውቀው ተሞክሮ አለ?

13 በዘወትር አቅኚነት የምታገለግለውን የ19 ዓመቷን ስቴፋኒን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። በ12 ዓመቷ በጭንቅላቷ ውስጥ የደም መርጋት ችግር ያጋጠማት ከመሆኑም ሌላ የአንጎል ዕጢ እንዳለባት ታወቀ። ከዚያን ጊዜ ወዲህ ሁለት ጊዜ ቀዶ ሕክምና ያደረገች ሲሆን የጨረር ሕክምናም ተደርጎላታል፤ እንዲሁም ሁለት ጊዜ በጭንቅላቷ ውስጥ የደም መርጋት ችግር ስላጋጠማት በስተግራ በኩል ያለውን የሰውነቷን ክፍል እንደ ልብ ማንቀሳቀስ የማትችል ከመሆኑም ሌላ በደንብ ለማየት ትቸገራለች። ስቴፋኒ ያላትን ኃይል ይበልጥ አስፈላጊ እንደሆኑ አድርጋ ለምታስባቸው ነገሮች ይኸውም ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች፣ ለመስክ አገልግሎትና ለመሳሰሉት ነገሮች ብቻ ማዋል አስፈልጓት ነበር። ያም ሆኖ የይሖዋ መንፈስ መጽናት እንድትችል በብዙ መንገዶች እንደረዳት ይሰማታል። የተስፋ መቁረጥ ስሜት በሚሰማት ጊዜ የሌሎች ክርስቲያኖችን ተሞክሮ የያዙ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ማንበቧ አበረታቷታል። ወንድሞችና እህቶች ደብዳቤ በመጻፍ አሊያም ከስብሰባዎች በፊትና በኋላ የሚያንጹ ሐሳቦችን በማካፈል ያበረታቷታል። ፍላጎት ያላቸው ሰዎችም ቤቷ ሄደው መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ስቴፋኒ ለምታስተምራቸው ነገሮች አመስጋኝ መሆናቸውን ያሳያሉ። ስቴፋኒ ለዚህ ሁሉ ነገር ይሖዋን በጣም ታመሰግነዋለች። በጣም የምትወደው ጥቅስ መዝሙር 41:3 ሲሆን ይህ ጥቅስ በእሷ ላይ እንደተፈጸመ ይሰማታል።

14. ተስፋ በምንቆርጥበት ጊዜ የትኛውን አመለካከት ማስወገድ ይኖርብናል? ለምንስ?

14 ስንዝል ወይም ጫና ሲበዛብን ውጥረቱ ቀለል እንዲልልን ለማድረግ መፍትሔው መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎቻችንን መቀነስ እንደሆነ ፈጽሞ ሊሰማን አይገባም። እንዲህ ማድረግ ከሁሉ የከፋ እርምጃ ነው። ይህን የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ኃይላችንን ለማደስ የሚያስችለንን መንፈስ ቅዱስ የምናገኘው የግልና የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስናደርግ፣ በመስክ አገልግሎት ስንካፈል እንዲሁም በስብሰባ ላይ ስንገኝና እነዚህን የመሳሰሉትን ነገሮች ስናከናውን ነው። ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች ምንጊዜም ቢሆን እረፍት ይሰጡናል። (ማቴዎስ 11:28, 29ን አንብብ።) ወንድሞችና እህቶች ብዙውን ጊዜ ወደ ስብሰባ ሲመጡ በጣም ዝለው የነበረ ቢሆንም ወደ ቤታቸው ሲሄዱ ግን መንፈሳዊ ባትሪያቸው የተሞላ ያህል ኃይላቸው እንደታደሰ ይሰማቸዋል፤ አንተስ ይህ እውነት መሆኑን አትመሠክርም?

15. (ሀ) ይሖዋ፣ የክርስቲያኖችን ሕይወት አልጋ በአልጋ እንደሚያደርግላቸው ቃል ገብቷል? በጥቅሶች ተጠቅመህ አብራራ። (ለ) አምላክ ምን ቃል ገብቶልናል? ይህስ ምን ብለን እንድንጠይቅ ሊያነሳሳን ይገባል?

15 ይህ ሲባል ግን ክርስቲያን ደቀ መዝሙር መሆን የሚያስከትለው ኃላፊነት ቀላል ነው ማለት አይደለም። ታማኝ ክርስቲያን መሆን ጥረት ይጠይቃል። (ማቴ. 16:24-26፤ ሉቃስ 13:24) ያም ሆኖ ይሖዋ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ለደከሙት ብርታት ይሰጣቸዋል። ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን፣ ኀይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፤ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ፤ አይደክሙም።” (ኢሳ. 40:29-31) እንግዲያው መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ሸክም እንደሆኑ እንዲሰማን ያደረገው ምን እንደሆነ ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል።

16. እንድንዝል ወይም ተስፋ እንድንቆርጥ ሊያደርጉን የሚችሉ ነገሮችን ለማስወገድ ምን ማድረግ እንችላለን?

16 የይሖዋ ቃል “ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ [እወቁ]” በማለት ያሳስበናል። (ፊልጵ. 1:10) ሐዋርያው ጳውሎስ የክርስትናን ሕይወት ከረጅም ርቀት የሩጫ ውድድር ጋር በማመሳሰል በመንፈስ መሪነት እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ማንኛውንም ሸክም . . . ከላያችን ጥለን ከፊታችን የሚጠብቀንን ሩጫ በጽናት እንሩጥ።” (ዕብ. 12:1) ጳውሎስ እዚህ ላይ ሊያጎላው የፈለገው ነጥብ እንድንዝል ሊያደርጉን የሚችሉ አላስፈላጊ ግቦችንና ሸክሞችን ማስወገድ እንዳለብን ነው። አንዳንዶቻችን ከአቅማችን በላይ ብዙ ነገሮችን ለማከናወን እየጣርን ይሆናል። እንግዲያው ብዙውን ጊዜ እንደዛልክ ወይም ጫና እንደበዛብህ የሚሰማህ ከሆነ እንደሚከተለው ብለህ ራስህን መጠየቅህ ጠቃሚ ነው፦ ሰብዓዊ ሥራዬ ምን ያህል ኃይሌን እያሟጠጠብኝ ነው? ለመዝናናት ብዬ ምን ያህል እጓዛለሁ? እንዲሁም በስፖርት ወይም በሌሎች የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያዎች ምን ያህል ጊዜ አጠፋለሁ? ምክንያታዊነትና ልክን የማወቅ ባሕርይ ሁላችንም አቅማችንን ከግምት በማስገባት አላስፈላጊ እንቅስቃሴዎችን እንድንቀንስ ሊያነሳሱን ይገባል።

17. አንዳንዶች የተስፋ መቁረጥ ስሜት እንዲያድርባቸው የሚያደርገው ምን ሊሆን ይችላል? በዚህ ረገድ ይሖዋ ምን ማረጋገጫ ሰጥቶናል?

17 አንዳንዶቻችን በተወሰነ መጠን የተስፋ መቁረጥ ስሜት እንዲያድርብን የሚያደርገው ሌላው ነገር የዚህ ሥርዓት መጨረሻ እንደጠበቅነው ቶሎ አለመምጣቱ ሊሆን ይችላል። (ምሳሌ 13:12) እንዲህ የሚሰማው ማንኛውም ግለሰብ በ⁠ዕንባቆም 2:3 ላይ ከሚገኘው ከሚከተለው ሐሳብ ማበረታቻ ማግኘት ይችላል፦ “ራእዩ የተወሰነለትን ጊዜ ይጠብቃልና፤ ስለ መጨረሻውም ይናገራል፤ እርሱም አይዋሽም፤ የሚዘገይ ቢመስልም ጠብቀው፤ በእርግጥ ይመጣል፤ ከቶም አይዘገይም።” ይሖዋ የዚህ ሥርዓት መጨረሻ እሱ በወሰነለት ጊዜ እንደሚመጣ ማረጋገጫ ሰጥቶናል!

18. (ሀ) የትኞቹ ተስፋዎች ብርታት እንድታገኝ ይረዱሃል? (ለ) ቀጣዩ የጥናት ርዕስ የሚጠቅመን እንዴት ነው?

18 የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች በሙሉ የመዛልም ሆነ የተስፋ መቁረጥ ስሜት የሚወገዱበትንና ሁሉም ሰው “ወደ ወጣትነቱ” ዘመን የሚመለስበትን ጊዜ ለማየት እንደሚናፍቁ ጥርጥር የለውም። (ኢዮብ 33:25) ብርታት በሚሰጡ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች የምንካፈል ከሆነ በአሁኑ ጊዜም እንኳ መንፈስ ቅዱስ ውስጣዊ ሰውነታችንን ያጠነክረዋል። (2 ቆሮ. 4:16፤ ኤፌ. 3:16) የመዛል ስሜት ዘላለማዊ በረከቶችን እንዲያሳጣህ አትፍቀድ! ማንኛውም መከራ፣ መንስኤው ፈተናም ይሁን የመዛል ወይም የተስፋ መቁረጥ ስሜት በአሁኑ ጊዜ ባይሆንም እንኳ በአምላክ አዲስ ዓለም መወገዱ አይቀርም። በቀጣዩ የጥናት ርዕስ ላይ ክርስቲያኖች ስደትን፣ እኩዮች የሚያሳድሩትን ጎጂ ተጽዕኖና የተለያዩ ሌሎች መከራዎችን እንዲቋቋሙ መንፈስ ቅዱስ ኃይል የሚሰጣቸው እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ኃይል የሚሰጠን እንዴት ነው?

• ጸሎትና ማሰላሰል ኃይል የሚሰጡን እንዴት ነው?

• ለተስፋ መቁረጥ መንስኤ ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮችን ማስወገድ የምትችለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች መንፈሳዊ ኃይላችንን ያድሱልናል