በመከራ ውስጥ እያለሁም ይሖዋን የማገልገል መብት በማግኘቴ አመስጋኝ ነኝ
በመከራ ውስጥ እያለሁም ይሖዋን የማገልገል መብት በማግኘቴ አመስጋኝ ነኝ
ማርቼ ደ ዮንግ ቫን ደን ሆቨል እንደተናገሩት
ዘጠና ስምንት ዓመቴ ነው። ላለፉት 70 ዓመታት ይሖዋን የማገልገል መብት አግኝቻለሁ፤ እርግጥ ነው፣ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ እምነቴ ፈተና አልገጠመውም ማለት አይደለም። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ማጎሪያ ካምፕ ገብቼ ነበር፤ እዚያ እያለሁ በአንድ ወቅት በጣም ተስፋ ከመቁረጤ የተነሳ በኋላ ላይ የተጸጸትኩበትን አንድ ነገር አደረግኩ። ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ደግሞ ሌላ ከባድ ፈተና አጋጠመኝ። እንደዚያም ሆኖ በመከራ ውስጥ እያለሁ ይሖዋን የማገልገል መብት በማግኘቴ አመስጋኝ ነኝ።
ጥቅምት 1940 ሕይወቴን የሚለውጥ ነገር አጋጠመኝ። የምኖረው ከአምስተርዳም፣ ኔዘርላንድ በስተደቡብ ምሥራቅ 24 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ በምትገኘው በሂልቨርሰም ከተማ ነበር። በወቅቱ አገሪቱ በናዚ አገዛዝ ሥር ነበረች። ከያፕ ደ ዮንግ ጋር ከተጋባን አምስት ዓመታችን ነበር፤ ባለቤቴ አሳቢ ሰው ሲሆን ቪሊ የምትባል በጣም የምንወዳት የሦስት ዓመት ልጅ ነበረችን። ጎረቤታችን ደግሞ ስምንት ልጆቻቸውን ለማሳደግ ደፋ ቀና የሚሉ አንድ ድሃ ባልና ሚስት ነበሩ። እነዚህ ሰዎች ይህን ሁሉ ቤተሰብ ማስተዳደር ሳያንሳቸው በቋሚነት በቤታቸው የሚያኖሩት አንድ ወጣት ነበር። ‘በራሳቸው ላይ ተጨማሪ ሸክም የሚጭኑት ለምንድን ነው?’ ብዬ አስብ ነበር። አንድ ቀን ምግብ ልወስድላቸው ስሄድ ወጣቱ ልጅ አቅኚ መሆኑን ተረዳሁ። ይህ ወጣት ስለ አምላክ መንግሥትና ይህ መንግሥት ስለሚያመጣው በረከት ነገረኝ። የነገረኝ ነገር ልቤን ስለነካው እውነትን ለመቀበል ጊዜ አልወሰደብኝም። በመሆኑም በዚያው ዓመት ራሴን ለይሖዋ በመወሰን ተጠመቅኩ። ከአንድ ዓመት በኋላ ባለቤቴም ተጠመቀ።
ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያለኝ እውቀት አነስተኛ ቢሆንም የይሖዋ ምሥክር ስሆን በመንግሥት የታገደ ድርጅት አባል እንደምሆን በሚገባ ተገንዝቤ ነበር። በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥቱን መልእክት በመስበካቸው ምክንያት እንደታሰሩም አውቃለሁ። እንደዚያም ሆኖ ወዲያውኑ ከቤት ወደ ቤት መስበክ የጀመርኩ ሲሆን እኔና ባለቤቴም አቅኚዎችንና ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችን በእንግድነት ለመቀበል ቤታችንን ክፍት አደረግን። ከዚህም በተጨማሪ አምስተርዳም የሚኖሩ ወንድሞችና እህቶች የሚያመጡልን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ቤታችን ይቀመጡ ነበር። እነዚህ ወንድሞች መጻሕፍቱን በሚያመጡበት ጊዜ ጠንካራ በሆኑት ብስክሌቶቻቸው ላይ ከጫኑ በኋላ በሸራ ይሸፍኗቸዋል። ወንድሞች ያሳዩት ፍቅርና ድፍረት በጣም አስገራሚ ነው! ለወንድሞቻቸው ሲሉ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ነበር።—1 ዮሐ. 3:16
“ቶሎ ትመለሻለሽ እማዬ?”
ከተጠመቅሁ ከስድስት ወር ገደማ በኋላ ሦስት ፖሊሶች ቤታችን መጡ። ፖሊሶቹ ወደ ቤት ገብተው መፈተሽ ጀመሩ። በጽሑፎች የተሞላውን ቁም ሣጥን ባያገኙትም አልጋችን ሥር የደበቅናቸውን አንዳንድ መጻሕፍት አገኙ። ወዲያውኑ በሂልቨርሰም ወደሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ ይዘውኝ ሄዱ። ከመሄዴ በፊት ልጄን ቪሊን ለመሰናበት ሳቅፋት “ቶሎ ትመለሻለሽ እማዬ?” ብላ
ጠየቀችኝ። እኔም “አዎን የኔ ቆንጆ፣ አሁን እመለሳለሁ” አልኳት። ይሁንና ቪሊን እንደገና ያገኘኋት በመከራ የተሞሉ 18 ወራት ካለፉ በኋላ ነበር።አንድ ፖሊስ ለምርመራ በባቡር ወደ አምስተርዳም ወሰደኝ። መርማሪዎቹ በሂልቨርሰም የሚገኙ ሦስት ወንድሞችን በመጥቀስ የይሖዋ ምሥክሮች መሆናቸውን እንዳረጋግጥላቸው ለማድረግ ሞከሩ። እኔም “ከአንዱ በቀር ሌሎቹን አላውቃቸውም። ይኼኛው ወተት የሚያመጣልን ሰው ነው” ብዬ መለስኩላቸው። ደግሞም እውነቴን ነበር፤ ያ ወንድም ሥራው ወተት ማድረስ ነበር። አክዬም “የይሖዋ ምሥክር መሆን አለመሆኑን ግን እኔን ሳይሆን እሱን ጠይቁት” አልኳቸው። ከዚህ ውጭ ምንም ለመናገር ፈቃደኛ አለመሆኔን ሲመለከቱ ፊቴ ላይ ከመቱኝ በኋላ በአንድ ክፍል ውስጥ ለሁለት ወር ዘጉብኝ። ባለቤቴ የት እንዳለሁ ሲያውቅ ልብስና ምግብ አመጣልኝ። ከዚያም ነሐሴ 1941 ከበርሊን፣ ጀርመን በስተሰሜን 80 ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ ወደሚገኘውና በአስከፊነቱ ወደሚታወቀው የራቨንስብሩክ የሴቶች ማጎሪያ ካምፕ ተወሰድኩ።
“አይዞሽ፣ በርቺ!”
እዚያም እምነታችንን እንደካድን በሚገልጽ ሰነድ ላይ ከፈረምን ልንለቀቅ እንደምንችል ተነገረን። እኔ ግን አልፈረምኩም። ያለኝን ነገር በሙሉ ካስረከብኩ በኋላ ልብሴን ለማወላለቅ ወደ መታጠቢያ ክፍል ገባሁ፤ እዚያም ከኔዘርላንድ ከመጡ አንዳንድ እህቶች ጋር ተገናኘሁ። ሦስት ማዕዘን ቅርጽ ያለው ወይን ጠጅ ጨርቅ የተሰፋበት የእስረኛ ልብስ እንዲሁም ሳህን፣ ኩባያና ማንኪያ ተሰጠን። የመጀመሪያውን ሌሊት በጊዜያዊ ማቆያ ክፍል ውስጥ አደርን። ከታሰርኩ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ያለቀስሁት በዚህ ጊዜ ነበር። “ከዚህ በኋላ ምንድን ነው የምሆነው? እዚህ የምቆየው ለስንት ጊዜ ነው?” እያልኩ ማልቀሴን ቀጠልኩ። እውነቱን ለመናገር በወቅቱ ከይሖዋ ጋር የነበረኝ ዝምድና ያን ያህል ጠንካራ አልነበረም፤ ምክንያቱም እውነትን ካወቅሁ ገና ጥቂት ወራት ነበር። ብዙ ማወቅ ያለብኝ ነገር እንዳለ ይሰማኝ ነበር። በማግሥቱ ስማችን እየተጠራ ሳለ ከኔዘርላንድ የመጣች አንዲት እህት በጣም እንደተጨነቅሁ አስተውላ መሆን አለበት “አይዞሽ፣ በርቺ! ምንም አንሆንም” አለችኝ።
ስማችን ከተጠራ በኋላ ወደ ሌላ ክፍል ተዛወርን፤ በዚያም ከጀርመንና ከኔዘርላንድ ከመጡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ክርስቲያን እህቶች ጋር ተገናኘን። አንዳንድ የጀርመን እህቶች በዚህ ክፍል ውስጥ ከአንድ ዓመት ለሚበልጥ ጊዜ ቆይተዋል። እውነትም ከእነሱ ጋር መሆኔ አጠናክሮኛል እንዲሁም ብርታት ጨምሮልኛል። በተጨማሪም እህቶቻችን ያሉበት ክፍል በካምፑ ውስጥ ካሉት ሌሎች ክፍሎች በጣም ንጹሕ መሆኑ አስገረመኝ። ያለንበት ክፍል ንጹሕ ከመሆኑ ባሻገር ሌብነት፣ ስድብ ወይም ድብድብ የሌለበት በመሆኑ ይታወቃል። በካምፑ ውስጥ ከሚታየው ዘግናኝ ሁኔታ አንጻር የእኛ ክፍል ቆሻሻ በሆነ ባሕር መሃል እንደሚገኝ ንጹሕ ደሴት ነበር።
ሕይወት በካምፕ ውስጥ
በካምፕ ውስጥ ስንኖር ብዙ መሥራት የሚጠበቅብን ሲሆን የምንበላው ግን ላመል ያህል ነበር። ከጠዋቱ 11:00 ሰዓት ከእንቅልፋችን ከተነሳን በኋላ ብዙም ሳይቆይ ስም መጠራት ይጀምራል። ጠባቂዎቹ ፀሐይ ዝናብ ሳይሉ ለአንድ ሰዓት ያህል ውጭ እንድንቆም ያደርጉን ነበር። ቀኑን ሙሉ በሥራ ስንደክም ከዋልን በኋላ 11:00 ሰዓት ላይ ድጋሚ የስም ጥሪ ይደረግ ነበር። ከዚያም ጥቂት ሾርባና ዳቦ ከበላን በኋላ ሰውነታችን ውልቅልቅ እንዳለ ወደ መኝታችን እንሄዳለን።
ከእሁድ በስተቀር እያንዳንዱን ቀን ከግብርና ጋር የተያያዙ ሥራዎችን በመሥራት ይኸውም ስንዴ በማጨድ፣ ለመስኖ የሚያገለግለውን ቦይ በመጥረግና የአሳማ ቤቶችን
በማጽዳት አሳልፍ ነበር። ሥራው እጅግ አድካሚና የሚያቆሽሽ ቢሆንም ገና ወጣትና ጠንካራ ስለነበርሁ አልከበደኝም። በተጨማሪም በምሠራበት ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ያላቸውን መዝሙሮች መዘመሬ ብርታት ይሰጠኝ ነበር። ያም ሆኖ ባለቤቴንና ልጄን ሳልናፍቅ የምውልበት ቀን አልነበረም።የሚሰጠን ምግብ በጣም አነስተኛ ቢሆንም እሁድ እሁድ ተሰባስበን በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ርዕሶች ላይ ለመወያየት አጋጣሚ በምናገኝበት ጊዜ የምንበላው ነገር እንዲኖረን ሁላችንም በየዕለቱ ከሚሰጠን ዳቦ የተወሰነ እናስቀምጥ ነበር። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ባይኖሩንም በዕድሜ ከእኔ ከፍ ያሉ ታማኝ የጀርመን እህቶች መንፈሳዊ ነገሮችን አንስተው ሲወያዩ በጉጉት አዳምጥ ነበር። በዚያ ሳለን የክርስቶስን ሞት መታሰቢያ ጭምር ማክበር ችለን ነበር።
ጭንቀት፣ ጸጸትና ማበረታቻ
ናዚዎች ለሚያደርጉት ጦርነት በቀጥታ ድጋፍ የሚሰጥ ሥራ እንድንሠራ የምንታዘዝበት ጊዜ ነበር። ከፖለቲካ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ባለን የገለልተኝነት አቋም የተነሳ ሁሉም እህቶች ይህን ሥራ ለመሥራት ፈቃደኞች አልነበሩም፤ እኔም የእነዚህን ደፋር እህቶች ምሳሌ ተከተልኩ። በዚህም የተነሳ ለበርካታ ቀናት ምግብ የተከለከልን ሲሆን ስም በሚጠራበት ቦታም ለሰዓታት እንድንቆም ተደረግን። እንዲያውም ኃይለኛ ቅዝቃዜ በነበረበት አንድ ወቅት ምንም ዓይነት ማሞቂያ በሌለው ክፍል ውስጥ ለ40 ቀናት ዘጉብን።
እምነታችንን እንደካድን በሚገልጸው ሰነድ ላይ የምንፈርም ከሆነ እንደምንለቀቅ በተደጋጋሚ ይነገረን ነበር። በራቨንስብሩክ ከአንድ ዓመት በላይ ከቆየሁ በኋላ በጣም ተስፋ ቆረጥኩ። ባለቤቴንና ልጄን ለማግኘት ካለኝ ጉጉት የተነሳ ወደ ጠባቂዎቹ በመሄድ ሰነዱን እንዲሰጡኝ ጠየቅኳቸው፤ ከዚያም ከእንግዲህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ እንደማልሆን በሚገልጸው ሰነድ ላይ ፈረምኩ።
አንዳንድ እህቶች ያደረግሁትን ነገር ሲሰሙ አገለሉኝ። ይሁን እንጂ ሄትቪክ እና ጌርትሩት የተባሉ አረጋዊ የሆኑ ሁለት የጀርመን እህቶች ፈልገው ካገኙኝ በኋላ እንደሚወዱኝ ነገሩኝ። የአሳማ ቤቶችን አብረን እያጸዳን ሳለ ለይሖዋ ምንጊዜም ታማኝ የመሆንን አስፈላጊነትና አቋማችንን ባለማላላት ለእሱ ያለንን ፍቅር የምንገልጸው እንዴት እንደሆነ እነዚህ እህቶች በደግነት አስረዱኝ። እንደ እናት በመሆን ያሳዩኝ አሳቢነትና ፍቅር ልቤን በጥልቅ ነካው። * ያደረግሁት ነገር ትክክል እንዳልሆነ አውቅ ነበር፤ በመሆኑም ሰነዱ እንዲሰረዝልኝ ፈለግሁ። አንድ ምሽት፣ የፈረምኩበት ሰነድ እንዲሰረዝልኝ ለመጠየቅ መወሰኔን ለአንዲት እህት ነገርኳት። አንድ የካምፕ ኃላፊ ሰምቶን መሆን አለበት የዚያኑ ዕለት ምሽት ወዲያውኑ ከእስር እንድፈታና በባቡር ተሳፍሬ ወደ ኔዘርላንድ እንድመለስ ተደረግኩ። ከተቆጣጣሪዎቹ መካከል አንዷ “አሁንም ቢሆን ቢቤልፎርሸር (የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ) ነሽ፤ ወደፊትም በዚሁ ትቀጥያለሽ” አለችኝ፤ የዚህች ሴት ፊት አሁንም ድረስ ዓይኔ ላይ አለ። እኔም “አዎን፣ የይሖዋ ፈቃድ ከሆነ እቀጥልበታለሁ” በማለት መለስኩላት። እንደዚያም ሆኖ ‘ሰነዱን መሰረዝ የምችለው እንዴት ነው?’ የሚለው ነገር ሁልጊዜ ያሳስበኝ ነበር።
በሰነዱ ላይ ከሰፈሩት ነጥቦች አንዱ “ከእንግዲህ ከዓለም አቀፉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ማኅበር ጋር እንደማልተባበር በፊርማዬ አረጋግጣለሁ” የሚል ነበር። አሁን ምን ማድረግ እንዳለብኝ ገባኝ! ጥር 1943 ወደ ቤት ከተመለስኩ ብዙም ሳይቆይ በስብከቱ ሥራ መካፈል ጀመርኩ። እርግጥ ነው፣ የናዚ ባለሥልጣናት ስለ አምላክ መንግሥት ስሰብክ በድጋሚ ቢይዙኝ የሚደርስብኝ ቅጣት ከፍተኛ እንደሚሆን አውቃለሁ።
በተጨማሪም ታማኝ አገልጋይ የመሆን ልባዊ ፍላጎት እንዳለኝ ለይሖዋ ለማሳየት እኔና ባለቤቴ፣ ጽሑፍ የሚያመጡልንን ወንድሞችና ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችን እንደገና በቤታችን ተቀብለን ማስተናገድ ጀመርን። ለይሖዋና ለሕዝቡ ያለኝን ፍቅር ለማሳየት የሚያስችል አጋጣሚ በድጋሚ በማግኘቴ በጣም አመስጋኝ ነኝ!
ከባድ መከራ
ጦርነቱ ከማብቃቱ ከተወሰኑ ወራት በፊት እኔና ባለቤቴ ከባድ መከራ አጋጠመን። ጥቅምት 1944 ልጃችን በድንገት ታመመች። ቪሊ፣ ዘጊ አናዳ የሚባል በሽታ ያዛት። በሽታው በፍጥነት ስለተባባሰባት ከሦስት ቀን
በኋላ ሞተች። በዚህ ጊዜ ገና የስምንት ዓመት ልጅ ነበረች።አንዷን ልጃችንን በማጣታችን በጣም ተጎዳን። በራቨንስብሩክ ያሳለፍኩት መከራ ልጄን በማጣቴ ከደረሰብኝ ሐዘን ጋር ሲወዳደር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ጥልቅ ሐዘን በሚሰማን ጊዜ ሁሉ በመዝሙር 16:8 ላይ የሚገኘውን “እግዚአብሔርን ሁልጊዜ በፊቴ አድርጌአለሁ፤ እርሱ በቀኜ ስላለ አልናወጥም” የሚለውን ጥቅስ በማንበብ ማጽናኛ ለማግኘት እንሞክራለን። እኔና ባለቤቴ ይሖዋ በሰጠው የትንሣኤ ተስፋ ላይ ጠንካራ እምነት አለን። በእውነት ውስጥ ጸንተን የኖርን ከመሆኑም ሌላ ምንጊዜም ምሥራቹን በቅንዓት እንሰብክ ነበር። ባለቤቴ፣ በ1969 እስከሞተበት ጊዜ ድረስ ይሖዋን በአመስጋኝነት ስሜት እንዳገለግለው ረድቶኛል።
አስደሳች ነገሮችና በረከት
ላለፉት አሥርተ ዓመታት ለደስታዬ ዋነኛ ምክንያት ከሆኑት ነገሮች አንዱ ከሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ጋር የተቀራረበ ወዳጅነት መመሥረቴ ነው። በጦርነቱ ጊዜ እናደርገው እንደነበረ ሁሉ ምንጊዜም ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችና ሚስቶቻቸው ጉባኤያችንን ለመጎብኘት ሲመጡ ቤታችን ያርፉ ነበር። እንዲያውም ተጓዥ የበላይ ተመልካች የሆነው ማርተን እና ባለቤቱ ኔል ካፕታይን ለ13 ዓመታት እኛ ቤት ኖረዋል! ኔል በጠና በታመመችበት ጊዜ እስከ ዕለተ ሞቷ ድረስ ለሦስት ወራት እሷን የመንከባከብ መብት አግኝቻለሁ። ከእነዚህ ባልና ሚስትም ሆነ በአካባቢው ካሉ ሌሎች ውድ ወንድሞችና እህቶች ጋር መቀራረቤ አሁን ባለንበት መንፈሳዊ ገነት ውስጥ በደስታ መኖር እንድችል ረድቶኛል።
በ1995 በራቨንስብሩክ የነበረውን ሁኔታ ለማስታወስ በተደረገ አንድ ዝግጅት ላይ እንድገኝ ግብዣ ቀረበልኝ፤ ይህ ዕለት በሕይወቴ ውስጥ ትልቅ ስፍራ ከሚይዙት ጊዜያት አንዱ ነው። በዚያም በካምፕ አብሬያቸው ከታሰርኩት እህቶች ጋር ተገናኘሁ! ከእነዚህ እህቶች ጋር ከ50 ለሚበልጡ ዓመታት አልተያየንም። ከእነሱ ጋር ያሳለፍኩት ጊዜ የማይረሳና አስደሳች ነበር፤ እንዲሁም እርስ በርስ ለመበረታታት የሚያስችል ጥሩ አጋጣሚ በማግኘታችን በሞት ያጣናቸውን የምንወዳቸውን ሰዎች በድጋሚ የምናገኝበትን ጊዜ በጉጉት እንድንጠብቅ አድርጎናል።
ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም 15:4 ላይ “በምናሳየው ጽናትና ከቅዱሳን መጻሕፍት በምናገኘው መጽናኛ ተስፋ [ይኖረናል]” በማለት ጽፏል። ይሖዋ ይህን ተስፋ ስለሰጠኝ አመሰግነዋለሁ፤ ተስፋው በመከራ ውስጥ እያለሁም እሱን እንዳገለግለው አስችሎኛል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.19 በዚያን ወቅት ወንድሞች ከዋናው መሥሪያ ቤት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ስላልነበራቸው ከገለልተኝነት አቋም ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የሚፈቱት በጊዜው የነበራቸውን ግንዛቤ መሠረት በማድረግ ነበር። በመሆኑም ከዚህ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በሚያጋጥሙበት ጊዜ ክርስቲያኖች በግለሰብ ደረጃ የሚወስዱት እርምጃ መጠነኛ ልዩነት ነበረው።
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከያፕ ጋር፣ በ1930
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ልጃችን ቪሊ በስምንት ዓመቷ
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አብረውኝ ከታሰሩት ጋር በ1995 በድጋሚ የመገናኘት አስደሳች አጋጣሚ አገኘሁ። ፊት ለፊት ካሉት በስተግራ ሁለተኛዋ ነኝ