በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ነጠላነታችሁን በጥበብ ተጠቀሙበት

ነጠላነታችሁን በጥበብ ተጠቀሙበት

ነጠላነታችሁን በጥበብ ተጠቀሙበት

“ይህን ሊቀበለው የሚችል ይቀበለው።”—ማቴ. 19:12

1, 2. (ሀ) ኢየሱስ፣ ጳውሎስና ሌሎች ለነጠላነት ምን ዓይነት አመለካከት ነበራቸው? (ለ) አንዳንዶች ነጠላነትን እንደ ስጦታ አድርገው የማያስቡት ለምን ሊሆን ይችላል?

አምላክ ለሰው ዘር ከሰጠው ውድ ስጦታዎች መካከል አንዱ ጋብቻ መሆኑ ምንም ጥያቄ የለውም። (ምሳሌ 19:14) በሌላ በኩል ደግሞ ነጠላ የሆኑ በርካታ ክርስቲያኖች አስደሳችና አርኪ ሕይወት ይመራሉ። የ95 ዓመት አረጋዊ የሆኑትና ዕድሜ ልካቸውን ሳያገቡ የኖሩት ወንድም ሃሮልድ እንዲህ ብለዋል፦ “ምንም እንኳ ከሌሎች ጋር ጊዜ ማሳለፍና ሰዎችን በእንግድነት መቀበል ቢያስደስተኝም አጠገቤ ሰው በማይኖርበት ጊዜ በፍጹም ብቸኝነት አይሰማኝም። ነጠላነትን እንደ ስጦታ አድርጌ ተቀብዬዋለሁ ማለት እችላለሁ።”

2 ኢየሱስ ክርስቶስም ሆነ ሐዋርያው ጳውሎስ ነጠላነትን ልክ እንደ ጋብቻ ከአምላክ የሚገኝ ስጦታ እንደሆነ አድርገው ገልጸውታል። (ማቴዎስ 19:11, 12ን እና 1 ቆሮንቶስ 7:7ን አንብብ።) እውነቱን ለመናገር ግን ያላገባ ሁሉ ነጠላ የሆነው በምርጫው አይደለም። በአንዳንድ ሁኔታዎች የተነሳ ተስማሚ የትዳር ጓደኛ ማግኘት አስቸጋሪ የሚሆንበት ጊዜ አለ። በተጨማሪም በትዳር ለተወሰኑ ዓመታት የቆዩ አንዳንድ ሰዎች በፍቺ ወይም የትዳር ጓደኛቸውን በሞት በማጣታቸው ምክንያት የነጠላነትን ሕይወት ለመምራት ተገድደዋል። ታዲያ ነጠላነት ስጦታ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? ነጠላ የሆኑ ክርስቲያኖች ይህን ስጦታ በአግባቡ ሊጠቀሙበት የሚችሉትስ እንዴት ነው?

ልዩ ስጦታ

3. ነጠላ የሆኑ ክርስቲያኖች በአብዛኛው ምን አጋጣሚ አላቸው?

3 ነጠላ የሆነ አንድ ግለሰብ በአብዛኛው ካገባ ሰው ይልቅ የበለጠ ጊዜና የተሻለ ነፃነት አለው። (1 ቆሮ. 7:32-35) ይህ ደግሞ አገልግሎቱን ለማስፋት፣ ለሌሎች ፍቅር በማሳየት ረገድ ልቡን ወለል አድርጎ ለመክፈትና ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብ ልዩ አጋጣሚ ይፈጥርለታል። በመሆኑም በርካታ ክርስቲያኖች የነጠላነትን ጥቅም እየተገነዘቡ ከመሆኑም ሌላ ለጊዜውም ቢሆን ይህን ስጦታ ‘ለመቀበል’ ወስነዋል። ሌሎች ደግሞ ነጠላ ለመሆን አቅደው አልተነሱ ይሆናል፤ ሆኖም ያሉበት ሁኔታ ሲለወጥ በጉዳዩ ላይ በጸሎት ካሰቡበት በኋላ በይሖዋ እርዳታ የነጠላነትን ሕይወት ሊቀበሉት እንደሚችሉ ተሰምቷቸዋል። በመሆኑም ከአዲሱ ሁኔታቸው ጋር ተስማምተው በመኖር የነጠላነትን ሕይወት ለመቀበል መርጠዋል።—1 ቆሮ. 7:37, 38

4. ነጠላ የሆኑ ክርስቲያኖች በአምላክ አገልግሎት ትልቅ ቦታ እንዳላቸው ሊሰማቸው የሚገባው ለምንድን ነው?

4 ነጠላ የሆኑ ክርስቲያኖች በይሖዋም ሆነ በድርጅቱ ዘንድ ውድ ተደርገው ለመታየት የግድ ማግባት እንደሌለባቸው ያውቃሉ። አምላክ እያንዳንዳችንን በግለሰብ ደረጃ ይወደናል። (ማቴ. 10:29-31) ማንም ወይም ምንም ነገር ከአምላክ ፍቅር ሊለየን አይችልም። (ሮም 8:38, 39) ያገባንም እንሁን ያላገባን በአምላክ አገልግሎት ትልቅ ቦታ እንዳለን ሊሰማን ይገባል።

5. የነጠላነትን ሕይወት በጥበብ ለመጠቀም ምን ይጠይቃል?

5 እንደ ሙዚቃ ወይም አትሌቲክስ ያሉ ተሰጥኦዎችን ለማዳበር ትጋት እንደሚጠይቅ ሁሉ የነጠላነትን ስጦታ በጥበብ ለመጠቀምም ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። ታዲያ በዛሬው ጊዜ ያሉ ነጠላ ክርስቲያኖች (ወንድሞችም ሆኑ እህቶች፣ ወጣቶችም ሆኑ ጎልማሶች እንዲሁም ነጠላ የሆኑት በምርጫቸውም ይሁን በሁኔታዎች አስገዳጅነት) ይህን ስጦታቸውን በአግባቡ ሊጠቀሙበት የሚችሉት እንዴት ነው? እስቲ ከጥንቱ የክርስቲያን ጉባኤ አንዳንድ አበረታች ምሳሌዎችን እንመርምር፤ እንዲሁም ከእነዚህ ምሳሌዎች ምን ትምህርት እንደምናገኝ እንመልከት።

ነጠላነት—በወጣትነት ዘመን

6, 7. (ሀ) ደናግል የሆኑት የፊልጶስ ሴቶች ልጆች በአምላክ አገልግሎት ምን መብት አግኝተው ነበር? (ለ) ጢሞቴዎስ የነጠላነት ሕይወቱን በአግባቡ የተጠቀመበት በምን መንገድ ነው? በወጣትነት ዕድሜው ራሱን ለአገልግሎት ማቅረቡ ምን በረከት አስገኝቶለታል?

6 ወንጌላዊው ፊልጶስ፣ ልክ እንደ እሱ ቀናተኛ ወንጌላውያን የሆኑ አራት ደናግል ሴቶች ልጆች ነበሩት። (ሥራ 21:8, 9) ከመንፈስ ቅዱስ ተአምራዊ ስጦታዎች አንዱ ትንቢት መናገር ሲሆን እነዚህ ወጣት ሴቶች ይህን ስጦታቸውን በመጠቀም ኢዩኤል 2:28, 29 ላይ የሚገኘውን ትንቢት ፈጽመዋል።

7 የነጠላነት ሕይወቱን በአግባቡ የተጠቀመበት ሌላው ወጣት ደግሞ ጢሞቴዎስ ነው። እናቱ ኤውንቄ እና አያቱ ሎይድ ጢሞቴዎስን ከጨቅላነቱ ጀምሮ ‘ቅዱሳን መጻሕፍትን’ አስተምረውታል። (2 ጢሞ. 1:5፤ 3:14, 15) ክርስትናን የተቀበሉት ጳውሎስ ለመጀመሪያ ጊዜ ልስጥራን በጎበኘበት ወቅት ማለትም በ47 ዓ.ም. ገደማ ሳይሆን አይቀርም። ከሁለት ዓመት በኋላ ጳውሎስ ልስጥራን ለሁለተኛ ጊዜ ሲጎበኝ ጢሞቴዎስ ምናልባት በአሥራዎቹ ዕድሜ መገባደጃ ወይም በ20ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ ይገኝ ነበር። በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ በዕድሜ ገና ወጣት ከመሆኑም በላይ እውነትን ከተቀበለ ብዙም አልቆየም፤ ያም ሆኖ በልስጥራና በኢቆንዮን በሚገኙ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ዘንድ “በመልካም ምግባሩ የተመሠከረለት ነበር።” (ሥራ 16:1, 2) በመሆኑም ጳውሎስ የጉዞ ጓደኛው እንዲሆን ጢሞቴዎስን ጋበዘው። (1 ጢሞ. 1:18፤ 4:14) ጢሞቴዎስ ጨርሶ አላገባም ብለን በእርግጠኝነት መናገር አንችልም። ሆኖም በወጣትነት ዕድሜው የጳውሎስን ግብዣ እንደተቀበለና ከዚያ በኋላ ባሉት በርካታ ዓመታት ነጠላ በመሆን በሚስዮናዊነትና በበላይ ተመልካችነት እንዳገለገለ እናውቃለን።—ፊልጵ. 2:20-22

8. ዮሐንስ ማርቆስ መንፈሳዊ ግቦችን እንዲከታተል የረዳው ምንድን ነው? እንዲህ በማድረጉስ ምን በረከት አግኝቷል?

8 ዮሐንስ ማርቆስም ወጣት በነበረበት ጊዜ ነጠላነቱን በአግባቡ ተጠቅሞበታል። እሱና እናቱ ማርያም እንዲሁም የአክስቱ ልጅ በርናባስ ከመጀመሪያዎቹ የኢየሩሳሌም ጉባኤ አባላት መካከል ነበሩ። በተጨማሪም የማርቆስ ቤተሰብ በከተማው ውስጥ የራሳቸው ቤትና አገልጋይ ስለነበራቸው የተደላደለ ሕይወት ይመሩ እንደነበር መገመት ይቻላል። (ሥራ 12:12, 13) ማርቆስ የራሱን ፍላጎት ለማሳደድ የተመቻቸ አጋጣሚ ቢኖረውም በወጣትነት ጊዜውም እንኳ እንዲህ ያለውን የራስ ወዳድነት ጎዳና አልተከተለም። አሊያም ጎጆ በመቀለስ የተደላደለ ኑሮ መምራት አልፈለገም። በልጅነቱ ከሐዋርያት ጋር መቀራረቡ በሚስዮናዊነት የማገልገል ፍላጎት በውስጡ እንዲተከል ሳያደርገው አልቀረም። በመሆኑም ጳውሎስና በርናባስ የመጀመሪያውን ሚስዮናዊ ጉዞ ባደረጉበት ወቅት አብሯቸው በመሄድ እንደ አገልጋይ ሆኖ በደስታ ይረዳቸው ነበር። (ሥራ 13:5) ከጊዜ በኋላም ከበርናባስ ጋር አብሮ የተጓዘ ሲሆን ቆየት ብሎ ደግሞ ከጴጥሮስ ጋር በባቢሎን አገልግሏል። (ሥራ 15:39፤ 1 ጴጥ. 5:13) ማርቆስ በነጠላነት የቆየው ለምን ያህል ጊዜ እንደሆነ የምናውቀው ነገር የለም። ይሁንና ሌሎችን ለማገልገልና በአምላክ አገልግሎት የበለጠ ለመሥራት ፈቃደኛ በመሆኑ ጥሩ ስም አትርፎ ነበር።

9, 10. በዛሬው ጊዜ ያሉ ያላገቡ ወጣት ክርስቲያኖች አገልግሎታቸውን ማስፋት የሚችሉባቸው ምን አጋጣሚዎች አሏቸው? ምሳሌ ስጥ።

9 በዛሬው ጊዜ በጉባኤ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ወጣቶችም በነጠላነት የሚያሳልፉትን ጊዜ በአምላክ አገልግሎት ያላቸውን ተሳትፎ ከፍ ለማድረግ ተጠቅመውበታል። ልክ እንደ ማርቆስና ጢሞቴዎስ፣ ነጠላነት ‘ልባቸው ሳይከፋፈል ዘወትር ጌታን ለማገልገል’ እንደሚያስችላቸው ይገነዘባሉ። (1 ቆሮ. 7:35) ነጠላ የሆኑ ወጣቶች ልባቸው ሳይከፋፈል ማገልገላቸው ብዙ ጥቅም አለው። በዚህ መልክ ይሖዋን ማገልገል የሚችሉባቸው በርካታ መንገዶች ያሉ ሲሆን ከእነዚህም መካከል አቅኚነት፣ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ማገልገል፣ ሌላ ቋንቋ መማር፣ በመንግሥት አዳራሽ ወይም በቅርንጫፍ ቢሮ ግንባታ መካፈል፣ በአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት መካፈልና በቤቴል ማገልገል ይገኙበታል። ያላገባህና በዕድሜ ገና ወጣት ከሆንክ ነጠላነትህን በአግባቡ እየተጠቀምክበት ነው?

10 ማርክ የተባለ አንድ ወንድም አቅኚነትን የጀመረው ገና 20 ዓመት ሳይሞላው ነበር፤ በኋላም በአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት የተካፈለ ሲሆን ወደተለያዩ አገሮች በመሄድ አገልግሏል። በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ያሳለፋቸውን 25 ዓመታት ወደኋላ መለስ ብሎ ሲያስበው እንዲህ ብሏል፦ “ከጉባኤው አባላት ጋር አብሬ በማገልገል፣ እረኝነት በማድረግ፣ ወደ ቤቴ መጥተው ምግብ እንዲበሉ በመጋበዝ ሌላው ቀርቶ መንፈሳዊ ነገሮችን መጫወት የምንችልባቸውን ዝግጅቶች በማድረግ ወንድሞችንና እህቶችን ለማበረታታት ሞክሬያለሁ። እንዲህ ማድረጌ ከፍተኛ ደስታ አምጥቶልኛል።” ማርክ ከሰጠው ሐሳብ በግልጽ መመልከት እንደሚቻለው በሕይወታችን ውስጥ ከሁሉ የላቀ ደስታ ማግኘት የምንችለው በመስጠት ነው፤ ሙሉ ጊዜያችንን በቅዱስ አገልግሎት የምናሳልፍ ከሆነ ደግሞ ለሌሎች መስጠት የምንችልባቸው በርካታ አጋጣሚዎች እናገኛለን። (ሥራ 20:35) በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ወጣቶች ፍላጎታቸው፣ ተሰጥኦዎቻቸው ወይም የሕይወት ተሞክሯቸው ምንም ይሁን ምን የጌታ ሥራ የበዛላቸው ሊሆኑ ይችላሉ።—1 ቆሮ. 15:58

11. ትዳር ለመመሥረት አለመጣደፍ ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች አንዳንዶቹ የትኞቹ ናቸው?

11 አብዛኞቹ ወጣቶች ከጊዜ በኋላ የማግባት ፍላጎት ቢኖራቸውም ትዳር ለመመሥረት መጣደፍ የለባቸውም የምንልበት በቂ ምክንያት አለን። ጳውሎስ ወጣቶችን ቢያንስ የፆታ ፍላጎታቸው የሚያይልበት “አፍላ የጉርምስና ዕድሜ” እስኪያልፍ ድረስ እንዲታገሡ አበረታቷቸዋል። (1 ቆሮ. 7:36) ትክክለኛ ፍላጎትህን ለማወቅና ተስማሚ የትዳር ጓደኛ ለመምረጥ የሚያስችል የሕይወት ተሞክሮ ለማካበት ጊዜ ይጠይቃል። ጋብቻ እስከ ሕይወት ፍጻሜ ድረስ መዝለቅ ያለበት በመሆኑ እንዲህ ያለ ቃል ኪዳን ውስጥ መግባት ከባድ ውሳኔ ነው።—መክ. 5:2-5

ነጠላነት—በጉልምስና ዕድሜ

12. (ሀ) መበለቲቷ ሐና ባለቤቷን በሞት ማጣቷ ያስከተለውን ለውጥ የተቋቋመችው እንዴት ነው? (ለ) ምን መብት አግኝታለች?

12 በሉቃስ ዘገባ ውስጥ የተጠቀሰችው ሐና በትዳር ሕይወት ሰባት ዓመት ብቻ ካሳለፈች በኋላ ባለቤቷን ባልታሰበ ሁኔታ በሞት ስታጣ ጥልቅ ሐዘን ተሰምቷት ሊሆን እንደሚችል ጥርጥር የለውም። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሐና ልጆች ወልዳ እንደነበር ወይም እንደገና ለማግባት አስባ ታውቅ እንደሆነ የሚገልጸው ነገር የለም። ይሁንና ሐና በ84 ዓመቷም መበለት እንደነበረች የአምላክ ቃል ይነግረናል። ከመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ በመነሳት ሐና፣ ያለችበት ሁኔታ መለወጡ የፈጠረውን አጋጣሚ ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብ ተጠቅማበታለች ብለን መደምደም እንችላለን። ሐና “ሌትና ቀንም በጾምና በምልጃ ቅዱስ አገልግሎት እያቀረበች ከቤተ መቅደስ ፈጽሞ አትጠፋም ነበር።” (ሉቃስ 2:36, 37) በመሆኑም በሕይወቷ ውስጥ ትልቁን ቦታ የምትሰጠው ለመንፈሳዊ ነገሮች ነበር። እንዲህ ማድረግ ከፍተኛ ጥረትና ጽናት ቢጠይቅባትም በእጅጉ ተባርካለች። ሕፃኑን ኢየሱስን የማየት መብት ያገኘች ሲሆን ወደፊት መሲሕ በሚሆነው በዚህ ልጅ የሚገኘውን ነፃነት ለሌሎች መሥክራለች።—ሉቃስ 2:38

13. (ሀ) ዶርቃ በጉባኤ ውስጥ ብዙ እርዳታ ታበረክት እንደነበር የሚጠቁመው ምንድን ነው? (ለ) ዶርቃ ያሳየችው ጥሩነትና ደግነት ምን ውጤት አስገኝቷል?

13 ዶርቃ ወይም ጣቢታ የምትባል አንዲት ሴት ከኢየሩሳሌም በስተሰሜን ምዕራብ በምትገኘውና ጥንታዊት የወደብ ከተማ በሆነችው በኢዮጴ ትኖር ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ዶርቃ ባል እንደነበራት የሚጠቅሰው ነገር ስለሌለ በወቅቱ ትዳር አልመሠረተችም ብለን መደምደም እንችላለን። ዶርቃ “መልካም በማድረግና ምጽዋት በመስጠት የምትታወቅ ነበረች።” ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው ችግረኛ ለሆኑ መበለቶችና ሌሎች ሰዎች በርካታ ልብሶችን ትሠራላቸው ነበር፤ በዚህም በጣም ይወዷት ነበር። ዶርቃ ድንገት ታማ በሞተች ጊዜ የጉባኤው አባላት በሙሉ ይህችን ውድ እህታቸውን እንዲያስነሳላቸው ለጴጥሮስ መልእክት ላኩ። ዶርቃ ከሞት የመነሳቷ ዜና በመላው ኢዮጴ የተሰራጨ ሲሆን ብዙዎችም አማኞች ሆኑ። (ሥራ 9:36-42) ዶርቃ በፈጸመችው የደግነት ተግባር አማካኝነት ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ እውነትን እንዲሰሙ አስተዋጽኦ ሳታደርግ አትቀርም።

14. ነጠላ የሆኑ ክርስቲያኖች ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንዲቀርቡ የረዳቸው ነገር ምንድን ነው?

14 በዛሬው ጊዜም ልክ እንደ ሐና እና ዶርቃ በጉልምስና ዕድሜ ላይ ያሉ ነጠላ የሆኑ በርካታ ወንድሞችና እህቶች በጉባኤዎች ውስጥ ይገኛሉ። አንዳንዶች ተስማሚ የትዳር ጓደኛ አላገኙ ይሆናል። ሌሎች ደግሞ በፍቺ ወይም የትዳር ጓደኛቸውን በሞት በማጣታቸው የተነሳ ነጠላ ሆነዋል። ነጠላ የሆኑ ክርስቲያኖች የሚያማክሩት የትዳር ጓደኛ ስለሌላቸው ትምክህታቸውን ይበልጥ በይሖዋ ላይ ማድረግ እንዳለባቸው ተገንዝበዋል። (ምሳሌ 16:3) ከ38 ለሚበልጡ ዓመታት በቤቴል ያገለገለችው ሲልቪያ የተባለች ነጠላ እህት ይህን ሁኔታ እንደ በረከት ትቆጥረዋለች። እንዲህ ብላለች፦ “ሁልጊዜ እኔ ብቻ ሌሎችን ማበረታታት የሚታክተኝ ጊዜ አለ። ‘እኔንስ የሚያበረታታኝ ማን ነው?’ የሚለው ነገር ያሳስበኛል።” ሆኖም እንዲህ ስትል አክላ ተናግራለች፦ “ይሖዋ ምን እንደሚያስፈልገኝ ከእኔ በተሻለ የሚያውቅ መሆኑን እምነት ማሳደሬ ይበልጥ ወደ እሱ እንድቀርብ አድርጎኛል። ማበረታቻ ሳላገኝ የቀረሁበት ጊዜ የለም፤ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ማበረታቻ የማገኘው ካልጠበቅኩት አቅጣጫ ነው።” ወደ ይሖዋ ይበልጥ እየቀረብን በሄድን መጠን ፍቅርና አሳቢነት በሚንጸባረቅበት መንገድ ምንጊዜም የሚያስፈልገንን ነገር ያሟላልናል።

15. ያላገቡ ክርስቲያኖች ፍቅር በማሳየት ረገድ ‘ልባቸውን ወለል አድርገው መክፈት’ የሚችሉት እንዴት ነው?

15 ነጠላነት፣ ፍቅር በማሳየት ረገድ ‘ልብን ወለል አድርጎ ለመክፈት’ ግሩም አጋጣሚ ይሰጣል። (2 ቆሮንቶስ 6:11-13ን አንብብ።) ላለፉት 34 ዓመታት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ያሳለፈችው ጆሊን የተባለች ነጠላ እህት እንዲህ ብላለች፦ “ከእኩዮቼ ጋር ብቻ ሳይሆን ከሁሉም ዓይነት ሰዎች ጋር የተቀራረበ ወዳጅነት ለመመሥረት ከፍተኛ ጥረት አድርጌያለሁ። ይሖዋን፣ ቤተሰቦቼን እንዲሁም ወንድሞቼንና እህቶቼን ብሎም ሌሎች ሰዎችን ለማገልገል ነጠላነት ጥሩ አጋጣሚ ከፍቶልኛል። ዕድሜዬ እየጨመረ በሄደ ቁጥር የነጠላነት ሕይወቴን ይበልጥ እየወደድሁት መጥቻለሁ።” አረጋውያን፣ አቅመ ደካሞች፣ ነጠላ ወላጆች፣ ወጣቶችና ሌሎች የጉባኤ አባላት ነጠላ የሆኑ ክርስቲያኖች ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንፈስ የሚያደርጉላቸውን ድጋፍ ከፍ አድርገው እንደሚመለከቱት ምንም ጥርጥር የለውም። በእርግጥም ለሌሎች ፍቅር ስናሳይ ለራሳችን ጥሩ ግምት ይኖረናል። እናንተስ ለሌሎች ፍቅር በማሳየት ረገድ “ልባችሁን ወለል አድርጋችሁ [መክፈት]” ትችላላችሁ?

በሕይወት ዘመን ሙሉ ነጠላ ሆኖ መኖር

16. (ሀ) ኢየሱስ ሕይወቱን ሙሉ ሳያገባ የኖረው ለምንድን ነው? (ለ) ጳውሎስ ነጠላነቱን በጥበብ የተጠቀመበት እንዴት ነው?

16 ኢየሱስ አላገባም ነበር፤ ለተሰጠው አገልግሎት ራሱን ማዘጋጀትና ተልእኮውን ዳር ማድረስ ነበረበት። ኢየሱስ በርካታ ኪሎ ሜትሮችን የተጓዘ ከመሆኑም ሌላ ከማለዳ አንስቶ እስከ ምሽት ይሠራ ነበር፤ ከጊዜ በኋላም ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ ሰጥቷል። ኢየሱስ ነጠላ መሆኑ የተሰጠውን ተልእኮ ለመወጣት አስችሎታል። ሐዋርያው ጳውሎስም በሺህ የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን የተጓዘ ሲሆን አገልግሎቱን በሚያከናውንበት ጊዜ ከባድ መከራዎች ደርሰውበታል። (2 ቆሮ. 11:23-27) ጳውሎስ ቀደም ባለው ሕይወቱ ባለትዳር የነበረ ሊሆን ቢችልም ሐዋርያ የመሆን ተልእኮ ከተቀበለ በኋላ ነጠላ ሆኖ ለመኖር መርጧል። (1 ቆሮ. 7:7፤ 9:5) ኢየሱስና ጳውሎስ ሌሎችም የሚችሉ ከሆነ ለአገልግሎቱ ሲሉ የእነሱን ምሳሌ እንዲከተሉ አበረታተዋል። ሆኖም ሁለቱም አለማግባትን ለአገልጋይነት እንደ ብቃት አድርገው አልገለጹም።—1 ጢሞ. 4:1-3

17. በዛሬው ጊዜ አንዳንዶች የኢየሱስንና የጳውሎስን አርዓያ የተከተሉት እንዴት ነው? ይሖዋ እንዲህ ያሉ መሥዋዕቶችን የሚከፍሉ ክርስቲያኖችን ከፍ አድርጎ ይመለከታቸዋል ብለን በእርግጠኝነት መናገር የምንችለው ለምንድን ነው?

17 በዛሬው ጊዜ ያሉ አንዳንዶችም አገልግሎታቸውን በተሻለ መንገድ ለማከናወን ሲሉ ሕይወታቸውን ሙሉ ነጠላ ሆነው ለመኖር መርጠዋል። ቀደም ሲል የተጠቀሱት ወንድም ሃሮልድ በቤቴል አገልግሎት ከ56 ዓመታት በላይ ያሳለፉ ሲሆን እንዲህ ብለዋል፦ “በቤቴል ባሳለፍኩት የመጀመሪያ አሥር ዓመት ጊዜ ውስጥ በርካታ ባለትዳሮች በሕመም ምክንያት አሊያም በዕድሜ የገፉ ወላጆቻቸውን ለመርዳት ሲሉ ከቤቴል ሲወጡ ተመልክቻለሁ። የእኔ ወላጆች ግን በሕይወት አልነበሩም። ቤቴልን በጣም ስለምወደው ትዳር በመመሥረት ይህን መብቴን አደጋ ላይ መጣል አልፈለግኩም።” ለረጅም ጊዜ በአቅኚነት ያገለገለችው ማርግሬትም በተመሳሳይ ከዓመታት በፊት የነበረውን ሁኔታ አስታውሳ ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “በሕይወቴ ውስጥ የማግባት አጋጣሚ ነበረኝ፤ ሆኖም ለትዳር ያን ያህል ትኩረት አልሰጠሁትም። ነጠላነቴ ያስገኘልኝን ተጨማሪ ነፃነት በመጠቀም ራሴን በአገልግሎት ማስጠመድ ችዬ ነበር፤ ይህ ደግሞ ከፍተኛ ደስታ አምጥቶልኛል።” በእርግጥም ይሖዋ ለእውነተኛው አምልኮ ብለው እንዲህ ያለ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ መሥዋዕት የሚከፍሉ ክርስቲያኖችን ፈጽሞ አይረሳም።—ኢሳይያስ 56:4, 5ን አንብብ።

ነጠላነታችሁን በጥበብ ተጠቀሙበት

18. የጉባኤ አባላት ነጠላ የሆኑ ክርስቲያኖችን ማበረታታትና መደገፍ የሚችሉት እንዴት ነው?

18 ይሖዋን ለማገልገል ከልባቸው የሚጥሩ ያላገቡ ክርስቲያኖችን ልናበረታታቸው ብሎም አድናቆታችንን ልንገልጽላቸው ይገባል። በማንነታቸው እንወዳቸዋለን እንዲሁም በጉባኤ ውስጥ ለሚያከናውኗቸው እንቅስቃሴዎች አመስጋኞች ነን። በእውነትም መንፈሳዊ ‘ወንድም፣ እህት፣ እናትና ልጆች’ ከሆንንላቸው ፈጽሞ ብቸኝነት አይሰማቸውም።—ማርቆስ 10:28-30ን አንብብ።

19. የነጠላነት ሕይወትህን በአግባቡ ለመጠቀም ምን ማድረግ ትችላለህ?

19 ነጠላ የሆንከው በምርጫህም ይሁን በሁኔታዎች አስገዳጅነት ከላይ የተጠቀሱት ቅዱስ ጽሑፋዊና ዘመናዊ ምሳሌዎች ደስተኛና ትርጉም ያለው ሕይወት መምራት እንደምትችል ማረጋገጫ ይሆኑሃል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። አንዳንድ ስጦታዎች በጉጉት የሚጠበቁ ሲሆኑ ሌሎች ግን ጨርሶ ያላሰብናቸው ሊሆኑ ይችላሉ። አንዳንድ ስጦታዎችን ገና እንደተቀበልናቸው ማድነቅ ስንጀምር ሌሎቹ ግን ያላቸውን ጠቀሜታ የምንረዳው በጊዜ ሂደት ነው። በመሆኑም ለስጦታው የምንሰጠው ግምት በአብዛኛው የተመካው በአመለካከታችን ላይ ነው። ታዲያ የነጠላነት ሕይወትህን በአግባቡ ለመጠቀም ምን ማድረግ ትችላለህ? ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብ፣ በአምላክ አገልግሎት ሥራ የበዛልህ ለመሆን እንዲሁም ለሌሎች ፍቅር በማሳየት ረገድ ልብህን ወለል አድርገህ ለመክፈት ተጠቀምበት። እንደ ጋብቻ ሁሉ ለነጠላነትም የይሖዋ ዓይነት አመለካከት የምናዳብርና ይህን ስጦታ በጥበብ የምንጠቀምበት ከሆነ በረከት ይሆንልናል።

ታስታውሳለህ?

• ነጠላነት ስጦታ ሊሆን የሚችለው በምን መንገድ ነው?

• ነጠላነት በወጣትነት ዘመን በረከት ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?

• ነጠላ የሆኑ ክርስቲያኖች ይበልጥ ወደ ይሖዋ ለመቅረብና ለሌሎች ፍቅር በማሳየት ረገድ ልባቸውን ወለል አድርገው ለመክፈት የሚያስችል ምን አጋጣሚ አላቸው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 18 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ያለህን አጋጣሚ ለአምላክ አገልግሎት በማዋል በጥበብ እየተጠቀምክበት ነው?