የአምላክ ስም በሸለቆ ውስጥ
የአምላክ ስም በሸለቆ ውስጥ
ሴንት ሞሪትዝ። ይህን ስም ሰምተኸው ታውቃለህ? በስዊዘርላንድ በሚገኘው በኤንገዲን ሸለቆ ያለ ታዋቂ የሆነ የመዝናኛ ስፍራ ነው። በጣሊያን ድንበር አቅራቢያ በስዊዘርላንድ ደቡባዊ ምሥራቅ ክልል በበረዶ በተሸፈኑት የአልፕስ ተራሮች መካከል ወደሚገኘው ወደዚህ ውብ የሆነ ሸለቆ ጎብኚዎች የሚጎርፉት ሴንት ሞሪትዝን ለማየት ብቻ አይደለም። የስዊዝ ብሔራዊ ፓርክ የሚገኘውም በዚህ ቦታ ሲሆን የፓርኩ ተፈጥሯዊ ውበት እንዲሁም የተለያዩ የእንስሳትና የዕፅዋት ዝርያዎች ታላቁን ፈጣሪያችንን ይሖዋን ያወድሳሉ። (መዝ. 148:7-10) በ17ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ በዚህ አካባቢ የነበረ አንድ ልማድም እንዲሁ ለይሖዋ ውዳሴ ያመጣል።
በዚህ ሸለቆ ውስጥ በሚገኙት በርካታ ቤቶች ላይ የሚታይ አንድ ያልተለመደ ነገር ትኩረትህን ይስበው ይሆናል። የአምላክን ስም በቤቶቹ ውጨኛ ግድግዳ ላይ ለምሳሌ በዋናው በር አናት ላይ ተቀርጾ ማየት የተለመደ ነው። ቀደም ባሉት ዘመናት የቤቶቹን ውጨኛ ግድግዳ በጽሑፍ የማስጌጥ ልማድ ነበረ፤ ይህም የሚደረገው
ግድግዳው ላይ በቀለም በመጻፍ ወይም ግድግዳውን በመቅረጽ አሊያም በድንጋይ ላይ የተቀረጸ ጽሑፍ በመጠቀም ነበር። ከታች ባለው ሥዕል ላይ በቤቨር መንደር የሚገኝ አንድ ቤት ይታያል። በግድግዳው ላይ የተቀረጸው ጽሑፍ እንዲህ የሚል ትርጉም አለው፦ “በ1715 ተሠራ። መጀመሪያው ይሖዋ ነው፤ መጨረሻውም ይሖዋ ነው። ሁሉ ነገር የሚሆነው በአምላክ ነው፤ ያለ እሱ የሚሆን ምንም ነገር የለም።” በዚህ ጥንታዊ ምልክት ላይ የአምላክ የግል ስም ሁለት ጊዜ መጠቀሱ ትኩረት የሚስብ ነው።በማዱላይን መንደር ደግሞ ከዚህም ይበልጥ ጥንታዊ የሆነ በግድግዳ ላይ የተቀረጸ ጽሑፍ ማየት ትችላለህ። ምልክቱ እንዲህ ይላል፦ “መዝሙር 127። ይሖዋ ቤትን ካልሠራ፣ ሠራተኞቹ የሚደክሙት በከንቱ ይሆናል። ሉክየስ ሩሜድየስ። በ1654 ተሠራ።”
በዚህ ሸለቆ ውስጥ በሚገኙት በእነዚህ ቤቶች ላይ መለኮታዊው ስም እንዲህ ባሉ በግልጽ በሚታዩ ቦታዎች የተጻፈው ለምንድን ነው? በተሃድሶው ዘመን መጽሐፍ ቅዱስ በሮማንሽ (በኤንገዲን የሚነገር ከላቲን የመጣ ቋንቋ ነው) ታትሞ ነበር። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ቋንቋ መጀመሪያ የተተረጎመው መጽሐፍ ነው። በርካታ የአካባቢው ሰዎች በአምላክ ቃል ውስጥ ያነበቡት ነገር ልባቸውን ስለነካው በቤታቸው ውጨኛ ግድግዳ ላይ የራሳቸውን ስም ብቻ ሳይሆን የአምላክን የግል ስም የያዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችንም ጽፈዋል።
በእርግጥም እነዚህ ጽሑፎች በቤቶቹ ላይ ከተጻፉ በርካታ ዘመናት ያለፉ ቢሆንም ዛሬም ቢሆን የይሖዋን ስም እያስታወቁና እያወደሱት ነው። በሸለቆ ውስጥ የሚገኘውን ይህን አካባቢ የሚጎበኙ ሰዎችም ሆኑ ነዋሪዎቹ፣ ይህ ስም ወደተጻፈበት ሌላ ሕንፃ ይኸውም በቤቨር ወደሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ በመሄድ ይሖዋ ስለተባለው አስደናቂ አምላክ ይበልጥ መማር ይችላሉ።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል ምንጭ]
© Stähli Rolf A/age fotostock