በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘የይሖዋን ስም መጠጊያችሁ አድርጉት’

‘የይሖዋን ስም መጠጊያችሁ አድርጉት’

‘የይሖዋን ስም መጠጊያችሁ አድርጉት’

“ትሑት የሆነና ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ሕዝብ . . . እንዲቀር አደርጋለሁ፤ እነሱም የይሖዋን ስም መጠጊያቸው ያደርጉታል።”—ሶፎ. 3:12 NW

1, 2. የሰው ልጆች በቅርቡ እንደ አውሎ ነፋስ ያለ ምን ዓይነት ክስተት ያጋጥማቸዋል?

ነፋስ የቀላቀለ ኃይለኛ ዝናብ ወይም የበረዶ ውሽንፍር አጋጥሞህ በረንዳ ሥር ተጠልለህ ታውቃለህ? ዝናቡና አውሎ ነፋሱ በጣም ከበረታ ግን በረንዳው በቂ መጠለያ ስለማይሆንህ ቤት ውስጥ መግባት አስፈልጎህ ይሆናል።

2 የሰው ዘር እስከ ዛሬ ካጋጠሙት ሁሉ ለየት ያለ አውሎ ነፋስ ከፊት ለፊቱ የሚጠብቀው ሲሆን ይህ አውሎ ነፋስ የሰው ልጆችን ሕልውና አደጋ ላይ የሚጥል ጥፋት ነው። ይህ “የጥፋት ቀን” በምሳሌያዊ ሁኔታ ‘የአውሎ ነፋስ ቀን’ (NW) ተብሎ ተጠርቷል። ‘ታላቁ የይሖዋ ቀን’ የተባለው ይህ የጥፋት ቀን ሁሉንም የሰው ልጆች የሚነካ ይሆናል። ይሁንና በዚያ ቀን የሚያስፈልገንን መጠጊያ ማግኘት እንችላለን። (ሶፎንያስ 1:14-18ን አንብብ።) ታዲያ በቅርቡ በሚመጣው ‘የይሖዋ የቍጣ ቀን’ መጠጊያ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

በጥንት ዘመን የተከሰቱት ‘የአውሎ ነፋስ ቀኖች’

3. አሥሩን ነገድ ያቀፈው የእስራኤል መንግሥት ምን ዓይነት ኃይለኛ “ወጀብ” አጋጥሞት ነበር?

3 የይሖዋ ቀን የሚጀምረው በምድር ላይ ያሉትን የሐሰት ሃይማኖቶች በሙሉ በማጥፋት ነው። በዚያ ወቅት መጠጊያ ማግኘት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ለማወቅ የጥንቶቹን የአምላክ ሕዝቦች ታሪክ መመልከት እንችላለን። በስምንተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. የኖረው ኢሳይያስ፣ ይሖዋ ከሃዲ በሆነው አሥሩን ነገድ ባቀፈው የእስራኤል መንግሥት ላይ ያመጣውን ፍርድ ማንም ሰው ሊያስቆመው ከማይችል ኃይለኛ “ወጀብ” ጋር አመሳስሎታል። (ኢሳይያስ 28:1, 2ን አንብብ።) ይህ ትንቢት በ740 ዓ.ዓ. አሦር የእስራኤልን ምድር በወረረችበት ወቅት ፍጻሜውን አግኝቷል።

4. በ607 ዓ.ዓ. ‘ታላቁ የይሖዋ ቀን’ በኢየሩሳሌም ላይ የመጣው እንዴት ነው?

4 ይሖዋ፣ ታማኝ ባልሆነው የእስራኤል መንግሥት ላይ የወሰደውን የፍርድ እርምጃ ተከትሎ በ607 ዓ.ዓ. በኢየሩሳሌምና በይሁዳ መንግሥት ላይ ‘ታላቁ የይሖዋ ቀን’ መጣ። ይህ የሆነው የይሁዳ ሕዝብም ከሃዲ በመሆናቸው ነበር። በንጉሥ ናቡከደነፆር የሚመሩት ባቢሎናውያን ይሁዳንና ዋና ከተማዋን ኢየሩሳሌምን ለማጥፋት ተነስተው ነበር። የይሁዳ ሕዝብ እርዳታ ለማግኘት የሞከሩት ‘የውሸት መጠጊያ’ ከሆነው ከግብፅ ነበር፤ ይህንንም ያደረጉት ከግብፅ ጋር ስምምነት ስለነበራቸው ነው። ይሁንና ባቢሎናውያን ልክ እንደ በረዶ ውሽንፍር ይህን የውሸት “መጠጊያ” ጠራርገው አጠፉት።—ኢሳ. 28:14, 17

5. የሐሰት ሃይማኖቶች በሙሉ በሚጠፉበት ጊዜ የአምላክ ሕዝቦች በቡድን ደረጃ ምን ይሆናሉ?

5 በኢየሩሳሌም ላይ የመጣው ታላቁ የይሖዋ ቀን በዘመናችን በከሃዲዋ ሕዝበ ክርስትና ላይ ምን ዓይነት ፍርድ እንደሚመጣ የሚጠቁም ነው። የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት የሆነችው ‘የታላቂቱ ባቢሎን’ ቀሪው ክፍልም ከዚህ ጥፋት አያመልጥም። ከዚያም የቀረው የሰይጣን ክፉ ሥርዓት ድምጥማጡ ይጠፋል። ይሁንና የአምላክ ሕዝቦች ይሖዋን መጠጊያቸው ስላደረጉት በቡድን ደረጃ ከዚህ ጥፋት ይተርፋሉ።—ራእይ 7:14፤ 18:2, 8፤ 19:19-21

በመንፈሳዊም ሆነ በአካላዊ ሁኔታ መጠጊያ ማግኘት

6. የይሖዋ ሕዝቦች መጠጊያ ማግኘት የሚችሉት እንዴት ነው?

6 በዚህ የመጨረሻ ዘመን የሚኖሩት የአምላክ ሕዝቦች በዛሬው ጊዜም እንኳ መጠጊያ ማግኘት የሚችሉት እንዴት ነው? ‘የአምላክን ስም በማክበር’ እንዲሁም እሱን በቅንዓት በማገልገል በመንፈሳዊ ሁኔታ መጠጊያ እናገኛለን። (ሚልክያስ 3:16-18ን አንብብ።) ይሁንና የአምላክን ስም ከማክበር የበለጠ ነገር ማድረግ እንደሚጠበቅብን እንገነዘባለን። መጽሐፍ ቅዱስ “የይሖዋን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል” ይላል። (ሮም 10:13) የይሖዋን ስም መጥራትና መዳን ማግኘት የተቆራኙ ነገሮች ናቸው። በርካታ ልበ ቅን ሰዎች፣ የአምላክን ‘ስም በሚያከብሩ’ እንዲሁም ስለ እሱ በሚመሠክሩ እውነተኛ ክርስቲያኖችና እሱን በማያገለግለው የሰው ዘር መካከል ያለውን ልዩነት መመልከት ይችላሉ።

7, 8. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች በአካላዊ ሁኔታ ከጥፋት የተረፉት እንዴት ነው? በዛሬው ጊዜስ ምን ተመሳሳይ ሁኔታ ይፈጸማል?

7 መዳን እንድናገኝ የተደረገው ዝግጅት መንፈሳዊ መጠጊያ በማግኘት ብቻ የተወሰነ አይደለም። የአምላክ ሕዝቦች በአካላዊ ሁኔታ መጠጊያ እንደሚያገኙ ቃል ተገብቶላቸዋል። በሴስቲየስ ጋለስ የሚመራው የሮም ሠራዊት በ66 ዓ.ም. በኢየሩሳሌም ላይ ጥቃት ከሰነዘረ በኋላ የተፈጸመው ነገር የአምላክ ሕዝቦች በአካላዊ ሁኔታ መጠጊያ እንደሚያገኙ ይጠቁማል። ኢየሱስ ይህ የመከራ ቀን ‘እንደሚያጥር’ አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። (ማቴ. 24:15, 16, 21, 22) ይህ የሆነው ኢየሩሳሌምን ከብቦ የነበረው የሮም ሠራዊት ሳይታሰብ ከተማዋን ትቶ በሄደበት ጊዜ ነበር፤ በዚህ ወቅት “ሥጋ” ማለትም እውነተኛ ክርስቲያኖች ‘መዳን’ የሚያገኙበት አጋጣሚ ተከፈተላቸው። እነዚህ ክርስቲያኖች ከከተማዋና ከአካባቢዋ ሸሹ። አንዳንዶች መጠጊያ ለማግኘት ዮርዳኖስን አቋርጠው ከዚህ ወንዝ በስተምሥራቅ ወደሚገኙት ተራሮች ሄዱ።

8 እነዚያን ክርስቲያኖችና በዛሬው ጊዜ ያሉ የአምላክ አገልጋዮችን የሚያመሳስላቸው ነገር አለ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት የጥንት ክርስቲያኖች መጠጊያ ለማግኘት ጥረት አድርገዋል፤ በዛሬው ጊዜ ያሉ የአምላክ አገልጋዮችም እንዲሁ ያደርጋሉ። ይሁንና በዛሬው ጊዜ እውነተኛ ክርስቲያኖች የሚገኙት በመላው ዓለም በመሆኑ ቃል በቃል ወደ አንድ ቦታ አይሸሹም። ያም ሆኖ ‘የተመረጡት’ እና ታማኝ አጋሮቻቸው ከሃዲዋ ሕዝበ ክርስትና ስትጠፋ ይሖዋንና በተራራ የተመሰለውን ድርጅቱን መጠጊያ በማድረግ በቡድን ደረጃ በአካላዊ ሁኔታ ከጥፋቱ ይተርፋሉ።

9. የይሖዋ ስም እንዳይታወቅ ጥረት የሚያደርጉት እነማን ናቸው? ምሳሌ ስጥ።

9 በሌላ በኩል ደግሞ ሕዝበ ክርስትና ምዕመኖቿን ለመንፈሳዊ ድንቁርና በመዳረጓ እንዲሁም በአምላክ ስም ለመጠቀም ጨርሶ ፈቃደኛ ባለመሆኗ መጥፋት ይገባታል። በመካከለኛው ክፍለ ዘመን የአምላክ ስም በአውሮፓ በስፋት ይታወቅ ነበር። ቴትራግራማተን ተብለው በሚጠሩት አራት የዕብራይስጥ ፊደላት የሚጻፈውንና ብዙውን ጊዜ የሐወሐ በሚሉት ፊደላት የሚወከለውን የአምላክን ስም በሳንቲሞችና በቤቶች ውጨኛ ግድግዳ ላይ እንዲሁም በበርካታ መጻሕፍትና መጽሐፍ ቅዱሶች ሌላው ቀርቶ በአንዳንድ የካቶሊክና የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ እንኳ የመጻፍ ልማድ ነበር። ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአምላክን ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች የማውጣት እንዲሁም በሌሎች መንገዶች ጥቅም ላይ እንዳይውል የማድረግ አዝማሚያ እየታየ ነው። ይህን የሚጠቁመው አንዱ ማስረጃ አምልኮንና የሃይማኖት ሥነ ሥርዓቶችን በተመለከተ መመሪያ የሚያወጣው ጉባኤ ሰኔ 29, 2008 ‘የአምላክን ስም’ በተመለከተ ለጳጳሳት የላከው ደብዳቤ ነው። በዚህ ደብዳቤ ላይ የሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መለኮታዊውን ስም የሚወክሉት የዕብራይስጥ ፊደላት “ጌታ” በሚለው ቃል እንዲተኩ መመሪያ አስተላልፋለች። ቫቲካን፣ የካቶሊክ የሃይማኖት ሥነ ሥርዓቶች በሚካሄዱበት ጊዜ በመዝሙሮችም ሆነ በጸሎቶች ላይ የአምላክ ስም ሊጠራም ሆነ ሊሠራበት እንደማይገባ ገልጻለች። በሕዝበ ክርስትና ውስጥም ሆነ ከዚያ ውጭ የሚገኙ የሌሎች ሃይማኖቶች መሪዎችም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የእውነተኛውን አምላክ ማንነት እንዳያውቁ አድርገዋል።

የአምላክን ስም የሚቀድሱ የሚያገኙት ጥበቃ

10. በዛሬው ጊዜ የአምላክ ስም ከፍ ከፍ እየተደረገ ያለው እንዴት ነው?

10 ከሌሎች ሃይማኖቶች ፍጹም ተቃራኒ በሆነ መንገድ የይሖዋ ምሥክሮች መለኮታዊውን ስም ያከብሩታል፤ እንዲሁም ከፍ ከፍ ያደርጉታል። የአምላክን ስም አክብሮት በተሞላበት መንገድ በመጠቀም ስሙን ይቀድሳሉ። ይሖዋ በሚተማመኑበት ሰዎች ይደሰታል፤ እንዲሁም ሕዝቡን ለመባረክና ለመጠበቅ የሚያስፈልገውን ሁሉ ይሆናል። “እሱን መጠጊያ ማድረግ የሚፈልጉትንም ያውቃል።”—ናሆም 1:7 NW፤ ሥራ 15:14

11, 12. በጥንቷ ይሁዳ ለይሖዋ ታማኝ የነበሩት እነማን ናቸው? በዘመናችንስ?

11 በጥንቷ ይሁዳ አብዛኞቹ ሰዎች ከሃዲዎች ቢሆኑም “የይሖዋን ስም መጠጊያቸው” ያደረጉ አንዳንድ ሰዎች ነበሩ። (ሶፎንያስ 3:12, 13ን አንብብ።) አምላክ፣ ከሃዲዋን ይሁዳን በባቢሎናውያን እንድትወረርና ሕዝቧ እንዲማረክ በማድረግ በቀጣት ጊዜ እንደ ኤርምያስ፣ ባሮክና አቤሜሌክ ላሉ አንዳንዶች ጥበቃ አድርጎላቸዋል። እነዚህ ሰዎች በከሃዲው ሕዝብ ‘መካከል’ እየኖሩም ታማኝ ነበሩ። ሌሎች ደግሞ በምርኮ ቢወሰዱም በታማኝነት ጸንተዋል። በ539 ዓ.ዓ. በቂሮስ የሚመራው የሜዶንና የፋርስ ሠራዊት ባቢሎንን ድል አደረገ። ብዙም ሳይቆይ ቂሮስ አይሁዳውያን ቀሪዎች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ አዋጅ አወጣ።

12 እውነተኛው አምልኮ እንደገና ሲቋቋም የማየት አጋጣሚ የነበራቸውን እስራኤላውያን በተመለከተ ሶፎንያስ፣ ይሖዋ እንደሚያድናቸውና በእነሱ እጅግ እንደሚደሰት አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። (ሶፎንያስ 3:14-17ን አንብብ።) እንዲህ ያለ ሁኔታ በዘመናችንም ተፈጽሟል። የአምላክ መንግሥት በሰማይ ከተቋቋመ በኋላ ይሖዋ፣ ታማኞቹን ቅቡዓን ቀሪዎች በመንፈሳዊ ሁኔታ ከታላቂቱ ባቢሎን ምርኮ ነፃ አውጥቷቸዋል። በእነዚህ ክርስቲያኖችም እስከ ዛሬ ድረስ መደሰቱን ቀጥሏል።

13. ከብሔራት ሁሉ የተውጣጡ ሰዎች ምን ዓይነት ነፃነት እያገኙ ነው?

13 በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖችም ከታላቂቱ ባቢሎን በመውጣታቸው ከሐሰት ሃይማኖታዊ ትምህርቶች ነፃ ወጥተዋል። (ራእይ 18:4) በመሆኑም “እናንት የምድር ትሑታን ሁሉ፣ . . . እግዚአብሔርን [“ይሖዋን፣” NW] እሹ” የሚለው በ⁠ሶፎንያስ 2:3 ላይ የሚገኘው ጥቅስ ዋነኛ ፍጻሜውን ያገኘው በዘመናችን ነው። ከብሔራት ሁሉ የተውጣጡ ትሑት ሰዎች ተስፋቸው ወደ ሰማይ መሄድም ሆነ በምድር ላይ መኖር የይሖዋን ስም መጠጊያ እያደረጉት ነው።

የአምላክ ስም ምትሃታዊ ኃይል የለውም

14, 15. (ሀ) አንዳንዶች የትኞቹ ነገሮች ምትሃታዊ ኃይል እንዳላቸው ያስቡ ነበር? (ለ) ምን ማድረግ ልዩ ጥበቃ እንደሚያስገኝ ሊሰማን አይገባም?

14 አንዳንድ እስራኤላውያን፣ ቤተ መቅደሱ እነሱን ከጠላቶቻቸው ለመጠበቅ የሚያስችል ምትሃታዊ ኃይል እንዳለው ይሰማቸው ነበር። (ኤር. 7:1-4) ከዚያ ቀደም ብሎም ታቦቱ በጦርነት ወቅት ጥበቃ እንደሚያደርግላቸው ያስቡ ነበር። (1 ሳሙ. 4:3, 10, 11) ታላቁ ቆስጠንጢኖስ በግሪክኛ “ክርስቶስ” የሚለው ስም የሚጻፍባቸውን ካይ እና የተባሉትን የመጀመሪያ ሁለት ፊደላት በወታደሮቹ ጋሻ ላይ ጽፎ ነበር፤ ይህን ያደረገው ይህ ምልክት በውጊያ ላይ ለወታደሮቹ ጥበቃ እንደሚያደርግላቸው በማሰብ ነበር። በተመሳሳይም የሠላሳ ዓመቱን ጦርነት ያካሄደው የስዊድኑ ንጉሥ ዳግማዊ ጉስታቭ አዶልፍ፣ በገጽ 7 ላይ የሚታየውን የብረት ጥሩር ይለብስ እንደነበር ይታመናል። በዚህ ጥሩር ላይ “ዬሆቫ” የሚለው ስም ጎላ ተደርጎ እንደተጻፈ ልብ በል።

15 አጋንንት ጥቃት ያደረሱባቸው አንዳንድ የአምላክ አገልጋዮች የይሖዋን ስም ጮክ ብለው በመጥራታቸው ይሖዋ መጠጊያ ሆኖላቸዋል። ያም ቢሆን የአምላክ ስም የተጻፈበት ነገር ልዩ ጥበቃ የሚያስገኝ ምትሃታዊ ኃይል ያለው ይመስል በዕለት ተዕለት ሕይወታችን እንደ ክታብ ልንጠቀምበት አይገባም። የይሖዋን ስም መጠጊያ ማድረግ የምንችለው በዚህ መንገድ አይደለም።

በዛሬው ጊዜ መጠጊያ ማግኘት

16. በዛሬው ጊዜ በመንፈሳዊ ሁኔታ መጠጊያ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

16 በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ለሕዝቡ ጥበቃ የሚያደርግበት አንዱ መንገድ በመንፈሳዊ ሁኔታ መጠጊያ እንዲያገኙ ማድረግ ነው። (መዝ. 91:1) መንፈሳዊ ደኅንነታችንን አደጋ ላይ ሊጥሉ ከሚችሉ በዓለም ላይ ከሚታዩ አዝማሚያዎች እንድንርቅ ይሖዋ ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ እንዲሁም በጉባኤ ሽማግሌዎች አማካኝነት ማሳሰቢያ ይሰጠናል። (ማቴ. 24:45-47፤ ኢሳ. 32:1, 2) ፍቅረ ንዋይን በተመለከተ ምን ያህል ጊዜ ማሳሰቢያ እንደተሰጠንና እንደነዚህ ያሉት ማሳሰቢያዎች ከመንፈሳዊ አደጋ እንዴት እንደጠበቁን እስቲ አስበው። በይሖዋ አገልግሎት ያለንን ተሳትፎ ሊያቀዘቅዝ የሚችል የቸልተኝነት ዝንባሌ ማዳበር የሚያስከትለውን አደጋ በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? የአምላክ ቃል “ተላሎችንም ቸልተኝነታቸው ያጠፋቸዋል፤ የሚያዳምጠኝ ሁሉ ግን በሰላም ይኖራል፤ ክፉን ሳይፈራ ያለ ሥጋት ይቀመጣል” ይላል። (ምሳሌ 1:32, 33) በተጨማሪም በሥነ ምግባር ንጹሕ ሆነን ለመኖር ጥረት ማድረጋችን መንፈሳዊ ደኅንነታችን እንደተጠበቀ እንዲቀጥል ይረዳናል።

17, 18. በዛሬው ጊዜ ያሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የይሖዋን ስም መጠጊያቸው እንዲያደርጉት የረዳቸው ምንድን ነው?

17 ኢየሱስ በመላው ምድር የመንግሥቱን ምሥራች እንድንሰብክ የሰጠንን ትእዛዝ እንድንፈጽም ከታማኙ ባሪያ የምናገኘውን ማበረታቻም አስብ። (ማቴ. 24:14፤ 28:19, 20) ሶፎንያስ፣ ሰዎች የአምላክን ስም መጠጊያቸው እንዲያደርጉት የሚረዳ ለውጥ እንደሚከናወን ሲናገር እንዲህ ብሎ ነበር፦ “በዚያን ጊዜ ሰዎች ሁሉ የይሖዋን ስም እንዲጠሩና ትከሻ ለትከሻ ተደጋግፈው እንዲያገለግሉት ቋንቋቸውን ለውጬ ንጹሕ ቋንቋ እሰጣቸዋለሁ።”—ሶፎ. 3:9 NW

18 ይህ ንጹሕ ቋንቋ ምንድን ነው? ንጹሑ ቋንቋ ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ዓላማዎቹ የሚገልጸው በመንፈስ መሪነት በተጻፈው ቃሉ ውስጥ የሚገኘው እውነት ነው። ስለ አምላክ መንግሥት እውነቱን ለሰዎች ስትናገርና ይህ መንግሥት የአምላክን ስም እንዴት እንደሚቀድሰው ስትገልጽ፣ ስለ አምላክ ሉዓላዊነት መረጋገጥ ጎላ አድርገህ ስትናገር እንዲሁም ታማኝ የሆኑ የሰው ልጆች ስለሚያገኟቸው ዘላለማዊ በረከቶች ከልብ በመነጨ ስሜት ስታወራ በዚህ ቋንቋ እየተጠቀምክ ነው ማለት ይቻላል። ብዙዎች በዚህ ምሳሌያዊ ቋንቋ በመጠቀማቸው የተነሳ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ሰዎች “የይሖዋን ስም [እየጠሩ]” እንዲሁም “ትከሻ ለትከሻ ተደጋግፈው” እያገለገሉት ነው። አዎን፣ በዓለም ዙሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይሖዋን መጠጊያቸው እያደረጉት ነው።—መዝ. 1:1, 3

19, 20. በጥንት ጊዜ ‘በውሸት መጠጊያ’ መታመን ዋጋ እንደሌለው የታየው እንዴት ነው?

19 በዓለም ላይ ያሉ ሰዎች የማይገፉ የሚመስሉ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል። ለችግሮቻቸው ከየት መፍትሔ እንደሚያገኙ ግራ የተጋቡ ብዙዎች ፍጽምና የጎደላቸውን ሰዎች እርዳታ ይሻሉ። አሊያም ደግሞ አንዳንድ ጊዜ ከጎረቤት አገሮች ጋር ስምምነት በመፍጠር የእነሱን እርዳታ ለማግኘት ትጥር እንደነበረችው እንደ ጥንቷ እስራኤል ሁሉ በዛሬው ጊዜም አንዳንዶች ከፖለቲካዊ ተቋማት መፍትሔ ለማግኘት ይሞክራሉ። ያም ሆኖ እስራኤላውያን ከጎረቤት አገሮች እርዳታ መሻታቸው እንዳልጠቀማቸው እናውቃለን። ዛሬም ቢሆን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ሆነ የትኛውም አገር፣ የሰው ልጆችን ችግሮች ሙሉ በሙሉ ሊያስወግድ አይችልም። ታዲያ ከፖለቲካ ተቋማትም ሆነ ከሌሎች መንግሥታት ጋር ስምምነት በመፍጠር መጠጊያ ለማግኘት መሞከር ምን ትርጉም ይኖረዋል? መጽሐፍ ቅዱስ እንደነዚህ ያሉትን ነገሮች ‘የውሸት መጠጊያ’ በማለት ይጠራቸዋል። እንዲህ ተብለው መጠራታቸው በእርግጥም ተገቢ ነው፤ ምክንያቱም በእነዚህ ነገሮች ተስፋ የሚያደርጉ ሁሉ ያሰቡት ሳይፈጸም ቀርቶ ለከፍተኛ ሐዘን መዳረጋቸው አይቀርም።—ኢሳይያስ 28:15, 17ን አንብብ።

20 የይሖዋን ቀን የሚያመለክተው የበረዶ ውሽንፍር በቅርቡ ምድርን ይመታታል። ከኑክሌር ጥቃት ለመዳን ተብለው የተዘጋጁ መሸሸጊያዎችም ሆኑ ሀብት አሊያም የሰው ልጆች መፍትሔ ብለው የሚያቀርቧቸው ነገሮች ጥበቃ ማስገኘት አይችሉም። ኢሳይያስ 28:17 “ውሸት መጠጊያችሁን የበረዶ ዝናብ ይጠራርገዋል መደበቂያችሁንም ውሃ ያጥለቀልቀዋል” ይላል።

21. የ2011ን የዓመት ጥቅስ ተግባራዊ ማድረጋችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?

21 በአሁኑ ጊዜም ሆነ የይሖዋ ቀን ሲመጣ ለአምላክ ሕዝቦች፣ አምላካቸው ይሖዋ እውነተኛ መጠጊያና መሸሸጊያ ይሆንላቸዋል። “ይሖዋ ሸሸገ” የሚል ትርጉም ያለው የሶፎንያስ ስም እውነተኛ መሸሸጊያ የሚገኘው ከይሖዋ እንደሆነ ይጠቁማል። የ2011 የዓመት ጥቅስ ‘የይሖዋን ስም መጠጊያችሁ አድርጉት’ የሚል ጥበብ የተንጸባረቀበት ምክር የያዘ መሆኑ ተገቢ ነው። (ሶፎ. 3:12) በዛሬው ጊዜም ቢሆን በይሖዋ ሙሉ በሙሉ በመታመን ስሙን መጠጊያችን ማድረግ እንችላለን፤ ይህንንም ማድረግ ይኖርብናል። (መዝ. 9:10) እንግዲያው “የእግዚአብሔር [“የይሖዋ፣” NW] ስም ጽኑ ግንብ ነው፤ ጻድቅ ወደ እርሱ በመሮጥ ተገን ያገኝበታል” የሚለውን በመንፈስ መሪነት የተጻፈ ማረጋገጫ በየዕለቱ እናስታውስ።—ምሳሌ 18:10

ታስታውሳለህ?

• በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ስም መጠጊያ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

• ‘በውሸት መጠጊያ’ መታመን የሌለብን ለምንድን ነው?

• ለወደፊቱ ጊዜ ምን ዓይነት መጠጊያ እንደምናገኝ ማረጋገጫ ተሰጥቶናል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የ2011 የዓመት ጥቅስ ‘የይሖዋን ስም መጠጊያችሁ አድርጉት’ የሚል ነው።—ሶፎንያስ 3:12 NW

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል ምንጭ]

Thüringer Landesmuseum Heidecksburg Rudolstadt, Waffensammlung “Schwarzburger Zeughaus”