ጋብቻን ከአምላክ እንደተገኘ ስጦታ በመቁጠር አክብሩት
ጋብቻን ከአምላክ እንደተገኘ ስጦታ በመቁጠር አክብሩት
“ስለዚህ ሰው ከአባቱና ከእናቱ ተለይቶ ከሚስቱ ጋር ይጣመራል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።”—ዘፍ. 2:24
1. ይሖዋን ልናከብረው ይገባል የምንለው ለምንድን ነው?
የጋብቻ መሥራች ለሆነው ለይሖዋ አምላክ አክብሮት ማሳየት እንደሚኖርብን ምንም ጥያቄ የለውም። ይሖዋ ፈጣሪያችን፣ ሉዓላዊ ገዥያችንና ሰማያዊ አባታችን እንደመሆኑ መጠን “መልካም ስጦታ ሁሉና ፍጹም ገጸ በረከት ሁሉ” የሚገኘው ከእሱ እንደሆነ ተደርጎ መገለጹ ተገቢ ነው። (ያዕ. 1:17፤ ራእይ 4:11) ይሖዋ እንዲህ ማድረጉ ለእኛ ታላቅ ፍቅር እንዳለው ያሳያል። (1 ዮሐ. 4:8) ይሖዋ የሚያስተምረን፣ የሚያዝዘን እንዲሁም የሚሰጠን ነገር በሙሉ ለራሳችን ደኅንነትና ጥቅም ነው።—ኢሳ. 48:17
2. ይሖዋ ለመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ምን መመሪያዎች ሰጥቷቸው ነበር?
2 መጽሐፍ ቅዱስ፣ ጋብቻ ከአምላክ ካገኘናቸው ከእነዚህ “መልካም” ስጦታዎች አንዱ እንደሆነ ይገልጻል። (ሩት 1:9፤ 2:12) ይሖዋ የመጀመሪያውን የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ባስፈጸመ ጊዜ ለአዳምና ለሔዋን ትዳራቸው የተሳካ እንዲሆን የሚረዷቸውን ግልጽ መመሪያዎች ሰጥቷቸዋል። (ማቴዎስ 19:4-6ን አንብብ።) እነዚህ ባልና ሚስት የአምላክን መመሪያዎች ተከትለው ቢሆን ኖሮ ዘላቂ የሆነ ደስታ ማግኘት በቻሉ ነበር። ይሁንና የአምላክን መመሪያዎች ችላ በማለት የሞኝነት አካሄድ መከተላቸው ከባድ መዘዝ አስከተለባቸው።—ዘፍ. 3:6-13, 16-19, 23
3, 4. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ብዙዎች ይሖዋ አምላክንም ሆነ ጋብቻን እያቃለሉ ያሉት እንዴት ነው? (ለ) በዚህ የጥናት ርዕስ ላይ የትኞቹን ምሳሌዎች እንመለከታለን?
3 ልክ እንደ መጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ሁሉ በዛሬው ጊዜም ብዙ ሰዎች ከጋብቻ ጋር የተያያዙ ውሳኔዎችን ሲያደርጉ ለይሖዋ መመሪያዎች ያን ያህል ቦታ አይሰጡም፤ አሊያም ምንም ዓይነት አክብሮት የላቸውም። አንዳንዶች ሳይጋቡ አብረው በመኖር ወይም ከበርካታ ሰዎች ጋር የፍቅር ጓደኝነት በመመሥረት የጋብቻን ዝግጅት ያቃልላሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ተመሳሳይ ፆታ ያላቸው ሰዎች ትዳር በመመሥረት ወይም ትዳርን ሲያሻቸው አውልቀው እንደሚጥሉት ልብስ በማንኛውም ጊዜ በማፍረስ ጋብቻ ትርጉሙን እንዲያጣ የሚያደርጉ ሰዎችም አሉ። (ሮም 1:24-32፤ 2 ጢሞ. 3:1-5) እነዚህ ሰዎች፣ ጋብቻ ከአምላክ የተገኘ ስጦታ መሆኑን ለመቀበል ፈቃደኞች አይደሉም፤ ይህን ስጦታ ማቃለላቸው ደግሞ የስጦታው ምንጭ ለሆነው ለይሖዋ አምላክ አክብሮት እንደሌላቸው የሚያሳይ ነው።
4 አንዳንድ የአምላክ ሕዝቦችም እንኳ ይሖዋ ለጋብቻ ያለውን አመለካከት በተመለከተ ነገር ዓለሙ ጠፍቶባቸዋል ማለት ይቻላል። አንዳንድ ክርስቲያን ባለትዳሮች ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት ሳይኖራቸው ለመለያየት ወይም ለመፋታት ይወስናሉ። እንዲህ ዓይነት ነገር እንዳይፈጠር ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? በዘፍጥረት 2:24 ላይ ያለው የአምላክ መመሪያ ክርስቲያን ባሎችና ሚስቶች ትዳራቸውን እንዲያጠናክሩ ሊረዳቸው የሚችለው እንዴት ነው? ትዳር ለመመሥረት የሚያስቡ ሰዎችስ ራሳቸውን ለጋብቻ ማዘጋጀት የሚችሉት እንዴት ነው? ዘላቂ ለሆነ ጋብቻ ቁልፉ ይሖዋን ማክበር መሆኑን የሚያሳዩ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ስኬታማ ትዳር የነበራቸው ሦስት ባለትዳሮችን ምሳሌ እንመልከት።
ምንጊዜም ታማኞች ሁኑ
5, 6. ዘካርያስና ኤልሳቤጥ ምን ፈታኝ ሁኔታ አጋጥሟቸው ነበር? ታማኝ በመሆናቸው የተባረኩትስ እንዴት ነው?
5 ዘካርያስና ኤልሳቤጥ ትዳራቸውን ስኬታማ ለማድረግ የተቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል። ሁለቱም ለትዳር የመረጡት መንፈሳዊ የሆነ ሰው ነበር። ዘካርያስ የክህነት አገልግሎቱን በታማኝነት ያከናውን የነበረ ሲሆን ሁለቱም በተቻላቸው መጠን የአምላክን ሕግ ለመጠበቅ ይጥሩ ነበር። አመስጋኞች እንዲሆኑ የሚያደርጓቸው ብዙ ምክንያቶች እንደነበሯቸው ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁንና በይሁዳ የሚገኘውን ቤታቸው የማየት አጋጣሚ ብታገኙ ኖሮ አንድ ነገር ሉቃስ 1:5-7
እንደጎደለ መገንዘባችሁ አይቀርም። እነዚህ ባልና ሚስት ልጆች አልነበሯቸውም። ኤልሳቤጥ መሃን ስትሆን ሁለቱም ዕድሜያቸው ገፍቶ ነበር።—6 በጥንቷ እስራኤል ልጅ መውለድ ትልቅ ቦታ ይሰጠው የነበረ ሲሆን በእስራኤላውያን ዘንድ ብዙ ልጆች መውለድ የተለመደ ነበር። (1 ሳሙ. 1:2, 6, 10፤ መዝ. 128:3, 4) በዚያ ዘመን የሚኖር አንድ እስራኤላዊ፣ ሚስቱ ልጅ ካልወለደችለት ይህን ሰበብ አድርጎ ሊፈታት ይችል ነበር። ዘካርያስ ግን ለትዳሩ ታማኝ ስለነበር እንዲህ አላደረገም። ትዳራቸውን ለማፍረስ ምክንያት አልፈላለገም፤ ኤልሳቤጥም ብትሆን እንዲህ አላደረገችም። ልጆች መውለድ አለመቻላቸው ቢያሳዝናቸውም ለትዳራቸውና ለይሖዋ ታማኝ በመሆን በአንድነት አምላክን ማገልገላቸውን ቀጥለዋል። ከጊዜ በኋላ ይሖዋ በተአምራዊ መንገድ በስተርጅናቸው ወንድ ልጅ እንዲወልዱ በማድረግ በእጅጉ ባርኳቸዋል።—ሉቃስ 1:8-14
7. ኤልሳቤጥ ለባሏ ያላትን ታማኝነት ያሳየችበት ሌላው መንገድ ምንድን ነው?
7 ኤልሳቤጥ ታማኝነቷን ያሳየችበት ሌላም መንገድ ነበር። ዘካርያስ የአምላክን መልአክ በመጠራጠሩ ምክንያት ልጃቸው ዮሐንስ በተወለደበት ጊዜ የመናገር ችሎታውን እንዲያጣ ተደርጎ ነበር። ያም ሆኖ ልጃቸው “ዮሐንስ” ተብሎ መጠራት እንዳለበት የይሖዋ መልአክ መግለጹን ዘካርያስ ለሚስቱ በሆነ መንገድ ሳያሳውቃት አልቀረም። ጎረቤቶቿና ዘመዶቿ ልጁን በአባቱ ስም ሊጠሩት ፈልገው ነበር። ኤልሳቤጥ ግን ለባሏ ታማኝ በመሆን የእሱን ሐሳብ ደግፋለች። “አይሆንም! ዮሐንስ መባል አለበት” በማለት ተናግራለች።—ሉቃስ 1:59-63
8, 9. (ሀ) ታማኝነት ትዳርን የሚያጠናክረው እንዴት ነው? (ለ) ባልና ሚስት አንዳቸው ለሌላው ታማኝ መሆናቸውን የሚያሳዩባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?
8 እንደ ዘካርያስና ኤልሳቤጥ ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ ባለትዳሮችም የሚያሳዝኗቸው ሁኔታዎች እንዲሁም ሌሎች ፈተናዎች ሊያጋጥሟቸው ይችላሉ። ታማኝነት የጎደለው ትዳር ስኬታማ ሊሆን አይችልም። የትዳር ጓደኛ ያልሆነን ሰው ማሽኮርመም፣ የብልግና ምስሎችንና ጽሑፎችን መመልከት፣ ምንዝር መፈጸም እንዲሁም ሌሎች ለትዳር ጠንቅ የሆኑ ነገሮች በትዳር ጓደኛሞች መካከል ያለው የመተማመን ስሜት እንዲጠፋ ሊያደርጉ ይችላሉ። በትዳር ውስጥ መተማመን እየጠፋ ከሄደ ደግሞ በመካከላቸው ያለው ፍቅር መቀዝቀዝ ይጀምራል። ታማኝነት በቤት ዙሪያ ከሚደረግ አጥር ጋር ሊመሳሰል ይችላል፤ ይህ አጥር ማንም ሰው ዘው ብሎ እንዳይገባ የሚከላከል ከመሆኑም ሌላ ቤተሰቡን ከአደገኛ ሁኔታዎች ስለሚጠብቃቸው የደኅንነት ስሜት እንዲሰማቸው ያደርጋል። በመሆኑም ባልና ሚስት አንዳቸው ለሌላው ታማኝ ከሆኑ ያለ ስጋት አብረው የሚኖሩ ሲሆን የልባቸውንም አውጥተው ይነጋገራሉ፤ ይህ ደግሞ ፍቅራቸው እያደገ እንዲሄድ አስተዋጽኦ ያደርጋል። በእርግጥም ታማኝነት በጣም አስፈላጊ ነው።
9 ይሖዋ ለአዳም “ሰው ከአባቱና ከእናቱ ተለይቶ ከሚስቱ ጋር ይጣመራል” ብሎት ነበር። (ዘፍ. 2:24) ይህ ምን ማለት ነው? ትዳር ከተመሠረተ በኋላ ባልና ሚስት ቤተሰቦቻቸውን ጨምሮ ከዘመዶቻቸውና ከጓደኞቻቸው ጋር ባላቸው ግንኙነት ረገድ ማስተካከያ ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። ሁለቱም ጊዜያቸውንና ትኩረታቸውን በዋነኝነት መስጠት ያለባቸው ለትዳር ጓደኛቸው ነው። ትዳር ከመሠረቱበት ጊዜ አንስቶ ለጓደኞቻቸው ወይም ለዘመዶቻቸው ቅድሚያ መስጠታቸውን ማቆም ይኖርባቸዋል። የትዳር ጓደኛሞች ውሳኔዎች በሚያደርጉበት ወይም በመካከላቸው አለመግባባት በሚፈጠርበት ጊዜ ወላጆቻቸው ጣልቃ እንዲገቡ መፍቀድ አይኖርባቸውም። ትዳር ከመሠረቱ በኋላ ባልና ሚስት አንዳቸው ከሌላው ጋር መጣመር ወይም መጣበቅ አለባቸው። ይህ የአምላክ መመሪያ ነው።
10. የትዳር ጓደኛሞች ምንጊዜም ታማኞች እንዲሆኑ ምን ይረዳቸዋል?
10 በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥም እንኳ ታማኝነት በረከት ያስገኛል። የማያምን ባል ያላቸው አንዲት እህት እንዲህ ብለዋል፦ “ለባለቤቴ መገዛትና ጥልቅ አክብሮት ማሳየት የምችለው እንዴት እንደሆነ ስላስተማረኝ ይሖዋን በጣም አመሰግነዋለሁ። ታማኝ መሆኔ በመካከላችን ያለው ፍቅርና አክብሮት ሳይቀንስ 47 ዓመታት በትዳር ለማሳለፍ አስችሎናል።” (1 ቆሮ. 7:10, 11፤ 1 ጴጥ. 3:1, 2) እንግዲያው የትዳር ጓደኛችሁ እንዲተማመንባችሁ ለማድረግ ጥረት አድርጉ። ለትዳር ጓደኛችሁ በምድር ላይ ከእሱ ወይም ከእሷ የሚበልጥባችሁ ማንም ሰው እንደሌለ ባገኛችሁት አጋጣሚ ሁሉ በንግግራችሁም ሆነ በድርጊታችሁ ግለጹ። በተቻላችሁ መጠን በእናንተና በትዳር ጓደኛችሁ መሃል ማንም ወይም ምንም ነገር እንዳይገባ ለማድረግ ጥረት አድርጉ። (ምሳሌ 5:15-20ን አንብብ።) በትዳር ዓለም ከ35 ዓመት በላይ በደስታ የኖሩት ሮን እና ጃኔት የተባሉ ባልና ሚስት “አምላክ ከእኛ የሚፈልግብንን በታማኝነት ስለምናደርግ ደስተኛና ስኬታማ ትዳር ሊኖረን ችሏል” በማለት ተናግረዋል።
አንድነት ትዳርን ያጠናክራል
11, 12. አቂላና ጵርስቅላ (ሀ) በቤታቸው ውስጥ፣ (ለ) ሰብዓዊ ሥራቸውን ሲያከናውኑ እንዲሁም (ሐ) በክርስቲያናዊ አገልግሎታቸው ተባብረው ይሠሩ የነበረው እንዴት ነው?
11 ሐዋርያው ጳውሎስ የቅርብ ወዳጆቹ የሆኑትን አቂላንና ጵርስቅላን ሁልጊዜም የሚጠቅሳቸው አንድ ላይ ነው። አንድነት ያላቸው እነዚህ ባለትዳሮች፣ ባልና ሚስት “አንድ ሥጋ” መሆን እንዳለባቸው የሚገልጸውን የአምላክን መመሪያ በመከተል ረገድ ግሩም ምሳሌ ናቸው። (ዘፍ. 2:24) የቤት ውስጥ ሥራዎችንም ሆነ ሰብዓዊ ሥራቸውንና ክርስቲያናዊ አገልግሎታቸውን በሚያከናውኑበት ጊዜ አይነጣጠሉም ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ጳውሎስ ለመጀመሪያ ጊዜ ቆሮንቶስ ሲሄድ አቂላና ጵርስቅላ ቤታቸው እንዲያርፍ በደግነት ጋብዘውታል፤ ከዚያ በኋላ ለተወሰነ ጊዜ ያህል ጳውሎስ የተለያዩ ሥራዎችን የሚያከናውነው በዚያ ተቀምጦ ሳይሆን አይቀርም። ቆየት ብሎ በኤፌሶን፣ እነዚህ ባልና ሚስት የጉባኤ ስብሰባዎች በቤታቸው እንዲደረጉ የፈቀዱ ከመሆኑም በላይ እንደ አጵሎስ ያሉ አዲሶችን በመንፈሳዊ እንዲያድጉ ለመርዳት አንድ ላይ ሆነው ሠርተዋል። (ሥራ 18:2, 18-26) ከጊዜ በኋላ እነዚህ ቀናተኛ ባልና ሚስት ወደ ሮም ሄዱ፤ እዚያም ቤታቸውን ለጉባኤ ስብሰባዎች ሰጥተው ነበር። በኋላም ወደ ኤፌሶን ተመልሰው ወንድሞችን አበረታተዋል።—ሮም 16:3-5
12 አቂላና ጵርስቅላ ለተወሰነ ጊዜ ከጳውሎስ ጋር ሆነው ድንኳን የሰፉበት ጊዜም ነበር። በዚህ ወቅትም ቢሆን እነዚህ ባልና ሚስት በመካከላቸው ፉክክር ወይም ግጭት ሳይኖር ተባብረው ይሠሩ ነበር። (ሥራ 18:3) ትዳራቸው ጠንካራና ደስታ የሰፈነበት እንዲሆን ይበልጥ አስተዋጽኦ ያደረገው ግን በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች አብረው መካፈላቸው እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። በቆሮንቶስም ሆነ በኤፌሶን አሊያም በሮም በነበሩበት ጊዜ ‘በክርስቶስ ኢየሱስ አብረው የሚሠሩ’ በመሆናቸው ይታወቁ ነበር። (ሮም 16:3) በሄዱበት ቦታ ሁሉ የመንግሥቱን ስብከት ሥራ ለማስፋፋት አብረው ይሠሩ ነበር።
13, 14. (ሀ) በትዳር ውስጥ አንድነት እንዳይኖር እንቅፋት የሚፈጥሩት የትኞቹ ሁኔታዎች ናቸው? (ለ) ባልና ሚስት “አንድ ሥጋ” የሆኑ ያህል ጠንካራ ጥምረት እንዲኖራቸው ሊረዷቸው የሚችሉ አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?
13 በእርግጥም ባልና ሚስት ግብ በሚያወጡበትና በአንዳንድ እንቅስቃሴዎች በሚካፈሉበት ጊዜ በመካከላቸው አንድነት መኖሩ ትዳራቸውን ያጠናክረዋል። (መክ. 4:9, 10) የሚያሳዝነው ግን በዛሬው ጊዜ ያሉ በርካታ ባልና ሚስቶች አብረው የሚያሳልፉት ጊዜ ጥቂት ነው። ሁለቱም በየፊናቸው ረጅም ሰዓት ይሠራሉ። ሌሎች ደግሞ በሥራቸው ምክንያት በተደጋጋሚ ጊዜ ይጓዛሉ፤ አሊያም ደግሞ ከቤተሰባቸው ተነጥለው ወደ ሌላ አገር በመሄድ እየሠሩ ገንዘብ ይልካሉ። አንዳንድ ባለትዳሮች በቴሌቪዥን፣ በትርፍ ጊዜ ማሳለፊያዎች፣ በስፖርት፣ በቪዲዮ ጨዋታዎች ወይም በኢንተርኔት ስለሚጠመዱ አብረው ቤት እያሉም እንኳ የብቸኝነት ሕይወት ይመራሉ። የእናንተስ ትዳር እንዲህ ይሆን? ከሆነ አብራችሁ የምታሳልፉት የበለጠ ጊዜ እንዲኖራችሁ ሁኔታችሁን ማስተካከል ትችሉ ይሆን? ምግብ እንደ ማዘጋጀት፣ ዕቃ እንደ ማጠብ ወይም አትክልት እንደ መንከባከብ ባሉት የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ለምን አብራችሁ አትካፈሉም? ልጆቻችሁን ወይም በዕድሜ የገፉ ወላጆቻችሁን ስትንከባከቡ አብራችሁ መሆን ትችላላችሁ?
14 ከሁሉ በላይ ደግሞ ከይሖዋ አምልኮ ጋር በተያያዙ እንቅስቃሴዎች ዘወትር አብራችሁ ጊዜ አሳልፉ። በዕለቱ ጥቅስ ላይ አብራችሁ መወያየታችሁና የቤተሰብ አምልኮ ማድረጋችሁ ቤተሰባችሁ አንድ ዓይነት አስተሳሰብና ግብ እንዲኖረው ለማድረግ ግሩም አጋጣሚ ይፈጥራል። ከዚህም በተጨማሪ አብራችሁ አገልግሎት ውጡ። የምትችሉ ከሆነ አብራችሁ በአቅኚነት ለማገልገል ሞክሩ፤ ሁኔታችሁ የሚፈቅድላችሁ ለአንድ ወርም ይሁን ለአንድ ዓመት እንዲህ ማድረጋችሁ ጠቃሚ ነው። (1 ቆሮንቶስ 15:58ን አንብብ።) በአንድ ወቅት ከባለቤቷ ጋር አቅኚ ሆና ያገለገለች አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “አብረን ጊዜ ለማሳለፍም ሆነ የልባችንን አውጥተን ለማውራት ከሚያስችሉን አጋጣሚዎች አንዱ አገልግሎት ነበር። ሁለታችንም ሌሎችን በመንፈሳዊ የመርዳት ግብ ስላለን ተባብረን እንሠራ ነበር። በጣም ከመቀራረባችን የተነሳ ባሌ ብቻ ሳይሆን ጓደኛዬም እንደሆነ ጭምር ይሰማኝ ነበር።” ትርጉም ባላቸው እንቅስቃሴዎች አብራችሁ በተካፈላችሁ መጠን ፍላጎታችሁ፣ ቅድሚያ የምትሰጧቸው ነገሮችና ልማዶቻችሁ ተመሳሳይ እየሆኑ ስለሚሄዱ ልክ እንደ አቂላና ጵርስቅላ እናንተም “አንድ ሥጋ” የሆናችሁ ያህል አስተሳሰባችሁ፣ ስሜታችሁና ድርጊታችሁ እያደር አንድ እየሆነ ይመጣል።
በትዳራችሁ ውስጥ አምላክን አስቀድሙ
15. ጋብቻ ስኬታማ እንዲሆን ቁልፉ ምንድን ነው? አብራራ።
15 ኢየሱስ በጋብቻ ውስጥ አምላክን ማስቀደም ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያውቅ ነበር። ይሖዋ የመጀመሪያዎቹን ሰዎች ሲያጋባ አይቷል። አዳምና ሔዋን የአምላክን መመሪያ በተከተሉበት ጊዜ ምን ያህል ተደስተው ይኖሩ እንደነበርና የአምላክን መመሪያ ችላ ማለታቸው ያስከተለባቸውን ጣጣ ተመልክቷል። በመሆኑም ኢየሱስ ሌሎችን ሲያስተምር በዘፍጥረት 2:24 ላይ የሚገኘውን የአባቱን መመሪያ በድጋሚ ተናግሯል። እንዲሁም “አምላክ ያጣመረውን ማንም ሰው አይለያየው” የሚለውን ሐሳብ አክሎ ተናግሯል። (ማቴ. 19:6) ከዚህ ለማየት እንደሚቻለው ዛሬም ቢሆን ጋብቻ ደስታ የሰፈነበትና ስኬታማ እንዲሆን ቁልፉ ለይሖዋ ጥልቅ አክብሮት ማሳየት ነው። በዚህ ረገድ የኢየሱስ ወላጆች የነበሩት ዮሴፍና ማርያም ግሩም ምሳሌ ይሆኑናል።
16. ዮሴፍና ማርያም በቤተሰባቸው ውስጥ አምላክን ያስቀድሙ እንደነበር ያሳዩት እንዴት ነው?
16 ዮሴፍ፣ ለማርያም ደግ ከመሆኑም ሌላ ያከብራት ነበር። ነፍሰ ጡር መሆኗን ባወቀበት ጊዜ ሁኔታውን የያዘው ምሕረት በሚንጸባረቅበት መንገድ ሲሆን ይህንንም ያደረገው ማርያም ያረገዘችው እንዴት እንደሆነ የአምላክ መልአክ ሳይነግረው በፊት ነበር። (ማቴ. 1:18-20) ከተጋቡ በኋላም ቄሳር ያወጣውን አዋጅ የታዘዙ ከመሆኑም በላይ የሙሴን ሕግ በጥብቅ ይከተሉ ነበር። (ሉቃስ 2:1-5, 21, 22) በኢየሩሳሌም በሚከበሩት ትላልቅ ሃይማኖታዊ በዓላት ላይ እንዲገኙ የሚጠበቅባቸው ወንዶች ብቻ ቢሆኑም ዮሴፍና ማርያም ከሌሎች የቤተሰባቸው አባላት ጋር በመሆን በየዓመቱ በእነዚህ በዓላት ላይ ይገኙ ነበር። (ዘዳ. 16:16፤ ሉቃስ 2:41) ፈሪሃ አምላክ የነበራቸው ዮሴፍና ማርያም በእነዚህና በሌሎች መንገዶች ይሖዋን ለማስደሰት ይጥሩ እንዲሁም ለመንፈሳዊ ነገሮች ጥልቅ አክብሮት ያሳዩ ነበር። በእርግጥም፣ ይሖዋ ልጁን ኢየሱስን እንዲያሳድጉ እነዚህን ባልና ሚስት መምረጡ ምንም አያስደንቅም።
17, 18. (ሀ) ባለትዳሮች በቤተሰባቸው ውስጥ አምላክን ማስቀደም የሚችሉባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው? (ለ) እንዲህ ማድረጋቸውስ ምን ጥቅም ያስገኝላቸዋል?
17 እናንተም በተመሳሳይ በትዳራችሁ ውስጥ አምላክን ታስቀድማላችሁ? ለምሳሌ ያህል፣ አስፈላጊ የሆኑ ውሳኔዎችን ከማድረጋችሁ በፊት መጀመሪያ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን መመሪያ ለማወቅ ምርምር ታደርጋላችሁ? እንዲሁም ስለ ጉዳዩ ትጸልያላችሁ? ከዚያም የጎለመሱ ክርስቲያኖችን ምክር ትጠይቃላችሁ? ወይስ ችግሮችን የምትፈቱት የራሳችሁን መንገድ አሊያም ቤተሰባችሁና ጓደኞቻችሁ የሚሰጧችሁን ምክር በመከተል ነው? ታማኙ ባሪያ ጋብቻንና የቤተሰብ ሕይወትን አስመልክቶ ያወጣቸውን በርካታ ጠቃሚ ሐሳቦች ተግባራዊ ለማድረግ ትጥራላችሁ? ወይስ የአካባቢያችሁን ባሕል ወይም ዘመን አመጣሹን ሰብዓዊ ጥበብ መከተል ይቀናችኋል? አንድ ላይ የመጸለይና የማጥናት ልማድ አላችሁ? መንፈሳዊ ግቦችንስ ታወጣላችሁ? ቤተሰባችሁ ቅድሚያ ሊሰጣቸው ስለሚገቡ ነገሮች አንስታችሁ ታወራላችሁ?
18 ወንድም ሬ በትዳር ዓለም ያሳለፏቸውን 50 አስደሳች ዓመታት አስመልክተው እንዲህ ብለዋል፦ “በትዳራችን ውስጥ ልንወጣው የማንችለው ችግር አጋጥሞን አያውቅም፤ ምክንያቱም ‘በሦስት እንደተገመደ ገመድ’ ይሖዋ ምንጊዜም በትዳራችን ውስጥ እንዲኖር እናደርጋለን።” (መክብብ 4:12ን አንብብ።) ዳኒ እና ትሪናም በዚህ ይስማማሉ። “አንድ ላይ ሆነን አምላክን ስለምናገለግል ትዳራችን ጠንካራ ሆኖልናል” ብለዋል። እነዚህ ባልና ሚስት ከ34 ለሚበልጡ ዓመታት አስደሳች የትዳር ሕይወት አሳልፈዋል። በትዳራችሁ ውስጥ ምንጊዜም ይሖዋን የምታስቀድሙ ከሆነ ጋብቻችሁ ስኬታማ እንዲሆን የሚረዳችሁ ከመሆኑም ሌላ አብዝቶ ይባርካችኋል።—መዝ. 127:1
ለአምላክ ስጦታ አክብሮት ማሳየታችሁን ቀጥሉ
19. አምላክ ጋብቻን ለሰው ልጆች ስጦታ አድርጎ የሰጣቸው ለምንድን ነው?
19 በዛሬው ጊዜ ብዙዎች የሚያሳስባቸው ነገር የራሳቸው ደስታ ብቻ ነው። አንድ የይሖዋ አገልጋይ ግን ነገሮችን የሚያየው ከዚህ በተለየ መንገድ ነው። አምላክ፣ ለሰው ልጆች ጋብቻን ስጦታ አድርጎ የሰጠው ዓላማውን ዳር ለማድረስ እንደሆነ ያውቃል። (ዘፍ. 1:26-28) አዳምና ሔዋን የተሰጣቸውን ስጦታ አክብረው ቢመለከቱት ኖሮ መላዋ ምድር ገነት ሆና ደስተኛና ጻድቅ በሆኑ የአምላክ አገልጋዮች ትሞላ ነበር።
20, 21. (ሀ) ጋብቻን እንደ ቅዱስ አድርገን መመልከት ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) በሚቀጥለው ሳምንት ስለ የትኛው ስጦታ እናጠናለን?
20 ከዚህም በላይ የአምላክ አገልጋዮች ጋብቻን የሚመለከቱት ለይሖዋ ክብር ለማምጣት እንደሚያስችላቸው አጋጣሚ አድርገው ነው። (1 ቆሮንቶስ 10:31ን አንብብ።) እስከ አሁን እንደተመለከትነው ታማኝነት፣ አንድነትና በትዳር ውስጥ አምላክን ማስቀደም ጋብቻን ለማጠናከር የሚረዱ አምላካዊ ባሕርያት ናቸው። እንግዲያው ለማግባት እየተዘጋጀንም እንሁን ጋብቻችንን ለማጠናከር ወይም ከመፍረስ ለመታደግ እየሞከርን፣ በቅድሚያ ጋብቻን መለኮታዊና ቅዱስ ዝግጅት እንደሆነ አድርገን መመልከት አለብን። ይህን ሐቅ በአእምሯችን መያዛችን ከጋብቻ ጋር የተያያዙ ውሳኔዎችን ምንጊዜም በአምላክ ቃል ላይ ተመሥርተን ለማድረግ እንድንጥር ያነሳሳናል። እንዲህ ስናደርግ ስጦታ ለሆነው የጋብቻ ዝግጅት ብቻ ሳይሆን ስጦታውን ለሰጠን ለይሖዋ አምላክም ጭምር አክብሮት እንዳለን እናሳያለን።
21 እርግጥ ነው፣ ከይሖዋ ያገኘነው ስጦታ ጋብቻ ብቻ አይደለም። እንዲሁም ጋብቻ በሕይወት ውስጥ ደስተኛ ለመሆን የሚያስችለው ብቸኛው መንገድ አይደለም። በሚቀጥለው የጥናት ርዕስ ላይ ከአምላክ ያገኘነውን ሌላ ውድ ስጦታ ይኸውም የነጠላነትን ስጦታ እንመለከታለን።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• ታማኝነት በክርስቲያኖች ትዳር ውስጥ ምን ሚና ይጫወታል?
• ባለትዳሮች በአንድነት አብረው መሥራታቸው ትዳራቸውን ያጠናክራል የምንለው ለምንድን ነው?
• ባልና ሚስቶች በትዳራቸው ውስጥ ለአምላክ ቅድሚያ የሚሰጡባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?
• የጋብቻ መሥራች ለሆነው ለይሖዋ አክብሮት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 15 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ባልና ሚስት አብረው መሥራታቸው አንድነታቸውን ለማጠናከር ይረዳቸዋል