በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በሙሉ ልብህ ጽድቅን ውደድ

በሙሉ ልብህ ጽድቅን ውደድ

በሙሉ ልብህ ጽድቅን ውደድ

“ጽድቅን ወደድህ።”—መዝ. 45:7

1. “በጽድቅ መንገድ” ለመጓዝ ምን ይረዳናል?

ይሖዋ በቃሉና በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ሕዝቡን “በጽድቅ መንገድ” እየመራቸው ነው። (መዝ. 23:3) ይሁንና ፍጹማን ባለመሆናችን ከዚህ መንገድ መውጣት ይቀናናል። ወደ ትክክለኛው ጎዳና ለመመለስ ብርቱ ጥረት ማድረግ ይጠይቃል። በዚህ ረገድ እንዲሳካልን ምን ሊረዳን ይችላል? እኛም እንደ ኢየሱስ ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግን ልንወድ ይገባል።—መዝሙር 45:7ን አንብብ።

2. ‘የጽድቅ መንገድ’ ምንድን ነው?

2 ‘የጽድቅ መንገድ’ ምንድን ነው? ይህ “መንገድ” በይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች ላይ የተመሠረተ ነው። በዕብራይስጥና በግሪክኛ “ጽድቅ” የሚለው ቃል “ቀና” የሆነውን ነገር የሚያመለክት ሲሆን ይህም የሥነ ምግባር መሥፈርቶችን በጥብቅ መከተልን ያመለክታል። ይሖዋ ‘የጽድቅ ማደሪያ’ ስለሆነ አምላኪዎቹ በሥነ ምግባር ረገድ ሊከተሉት የሚገባውን ቀና የሆነውን ጎዳና ለማወቅ ወደ እሱ ዘወር ማለት ይፈልጋሉ።—ኤር. 50:7 የ1954 ትርጉም

3. ስለ አምላክ ጽድቅ ይበልጥ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?

3 አምላክን ሙሉ በሙሉ ማስደሰት የምንችለው ከእሱ የጽድቅ መሥፈርቶች ጋር ተስማምተን ለመኖር በፍጹም ልባችን ጥረት የምናደርግ ከሆነ ብቻ ነው። (ዘዳ. 32:4) ይህን ለማድረግ በቅድሚያ ስለ ይሖዋ አምላክ ከቃሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የምንችለውን ያህል እውቀት መቅሰም ያስፈልገናል። ስለ ይሖዋ ይበልጥ ባወቅን መጠን በየዕለቱ ወደ እሱ እየቀረብን የምንሄድ ሲሆን ይህም ጽድቁን ይበልጥ እንድንወድ ይረዳናል። (ያዕ. 4:8) ከዚህም በተጨማሪ በሕይወታችን ውስጥ ከባድ ውሳኔዎችን በምናደርግበት ወቅት በመንፈስ መሪነት በተጻፈው የአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን መመሪያ መከተል ይኖርብናል።

የአምላክን ጽድቅ ፈልጉ

4. የአምላክን ጽድቅ መፈለግ ሲባል ምን ማድረግን ይጨምራል?

4 ማቴዎስ 6:33ን አንብብ። የአምላክን ጽድቅ መፈለግ፣ የመንግሥቱን ምሥራች ከመስበክ የበለጠ ነገርን ይጨምራል። የምናቀርበው ቅዱስ አገልግሎት በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ከአምላክ የላቁ መሥፈርቶች ጋር ተስማምተን መኖር አለብን። ታዲያ የይሖዋን ጽድቅ የሚፈልጉ ሁሉ ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል? “እንደ አምላክ ፈቃድ የተፈጠረውንና ከእውነተኛ ጽድቅና ታማኝነት ጋር የሚስማማውን አዲሱን ስብዕና መልበስ” ይገባቸዋል።—ኤፌ. 4:24

5. የተስፋ መቁረጥ ስሜትን ለመቋቋም ምን ሊረዳን ይችላል?

5 ከአምላክ የጽድቅ መሥፈርቶች ጋር ተስማምተን ለመኖር ስንጥር ባሉብን ድክመቶች የተነሳ አንዳንድ ጊዜ ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን። እንድንዝል የሚያደርግ የተስፋ መቁረጥ ስሜትን ለመቋቋም ብሎም ጽድቅን ለመውደድና ለመፈጸም ምን ሊረዳን ይችላል? (ምሳሌ 24:10) “ከእምነት በሚመነጭ ታላቅ የመተማመን መንፈስ በእውነተኛ ልብ” አዘውትረን በጸሎት ወደ ይሖዋ መቅረብ ይኖርብናል። (ዕብ. 10:19-22) ቅቡዓንም እንሁን በምድር ላይ የመኖር ተስፋ ያለን ክርስቲያኖች፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕትና ታላቅ ሊቀ ካህናችን ሆኖ በሚያከናውነው አገልግሎት ላይ እምነት አለን። (ሮም 5:8፤ ዕብ. 4:14-16) የዚህ መጽሔት የመጀመሪያ እትም፣ የፈሰሰው የኢየሱስ ደም ምን ያህል እንደሚጠቅመን የሚያብራራ ምሳሌ ይዞ ነበር። (1 ዮሐ. 1:6, 7) መጽሔቱ እንዲህ ይላል፦ “ደማቅ ቀይ የሆነ ወይም ደም የሚመስል ነገርን ብርሃን ላይ አድርገን ቀይ ቀለም ባለው መስታወት ብንመለከተው ነጭ መስሎ እንደሚታየን አሌ የማይባል ሐቅ ነው፤ በመሆኑም ኃጢአታችን እንደ ደማቅ ቀይ ወይም እንደ ደም ቢቀላም አምላክ በክርስቶስ ደም በኩል ሲመለከተው ነጭ ሆኖ ይታያል።” (ሐምሌ 1879 ገጽ 6) ይሖዋ በውድ ልጁ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ያደረገልን ዝግጅት እንዴት የሚያስደንቅ ነው!—ኢሳ. 1:18

መንፈሳዊ የጦር ትጥቃችሁን ፈትሹ

6. መንፈሳዊ የጦር ትጥቃችንን መፈተሻችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

6 በማንኛውም ጊዜ ቢሆን “የጽድቅን ጥሩር” መልበስ ያስፈልገናል፤ ምክንያቱም ይህ ጥሩር ከአምላክ የሚገኘው መንፈሳዊ የጦር ትጥቅ መሠረታዊ ክፍል ነው። (ኤፌ. 6:11, 14) ራሳችንን ለይሖዋ የወሰንነው በቅርቡ ሊሆን ይችላል፤ አሊያም ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ቅዱስ አገልግሎት ስናቀርብ ቆይተን ይሆናል፤ ያም ሆነ ይህ መንፈሳዊ የጦር ትጥቃችንን በየዕለቱ መፈተሻችን በጣም አስፈላጊ ነው። ለምን? ምክንያቱም ዲያብሎስና አጋንንቱ ወደ ምድር ተወርውረዋል። (ራእይ 12:7-12) ሰይጣን የቀረው ጊዜ አጭር እንደሆነ ስለሚያውቅ በጣም ተቆጥቷል። በመሆኑም በአምላክ ሕዝቦች ላይ የሚሰነዝረውን ጥቃት አፋፍሞታል። ታዲያ “የጽድቅን ጥሩር” መልበሳችን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ተገንዝበናል?

7. “የጽድቅን ጥሩር” መልበስ እንደሚያስፈልገን ከተገነዘብን ምን እናደርጋለን?

7 ጥሩር ልብን ከጥቃት ይከላከላል። ፍጽምና የጎደለን በመሆናችን ምሳሌያዊው ልባችን ተንኰለኛ ከመሆኑም ሌላ ምንም ነገር ከማድረግ አይመለስም። (ኤር. 17:9) ልባችን ስህተት የሆነውን ነገር እንድናደርግ የመገፋፋት አዝማሚያ ስላለው ልናሠለጥነውና ልንቆጣጠረው ይገባል። (ዘፍ. 8:21) “የጽድቅን ጥሩር” መልበስ ምን ያህል እንደሚያስፈልገን ከተገነዘብን አምላክ የሚጠላቸውን ነገሮች የሚያንጸባርቁ መዝናኛዎችን በመምረጥ ለአጭር ጊዜም ቢሆን ጥሩራችንን አናወልቅም፤ አሊያም መጥፎ ድርጊት ስለ መፈጸም በአእምሯችን አናውጠነጥንም። እንዲሁም ለረጅም ሰዓት ቴሌቪዥን በማየት ውድ የሆነውን ጊዜያችንን አናባክንም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋን የሚያስደስተውን ለማድረግ ምንጊዜም ከፍተኛ ጥረት እናደርጋለን። ከጽድቅ በራቀ ሥጋዊ አስተሳሰብ ለጊዜው ብንሸነፍም እንኳ በይሖዋ እርዳታ እንደገና እንነሳለን።—ምሳሌ 24:16ን አንብብ።

8. “ትልቅ የእምነት ጋሻ” የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

8 ከመንፈሳዊ የጦር ትጥቃችን መካከል “ትልቅ የእምነት ጋሻ” ይገኝበታል። ይህም “የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ማምከን” እንድንችል ይረዳናል። (ኤፌ. 6:16) እምነትና ለይሖዋ ከልብ የመነጨ ፍቅር ማዳበር ደግሞ ጽድቅን እንድናደርግ እንዲሁም ወደ ዘላለም ሕይወት ከሚመራው ጎዳና ሳንወጣ እንድንኖር ይረዳናል። ይሖዋን ይበልጥ እየወደድነው በሄድን መጠን ጽድቁን ከፍ አድርገን እንመለከታለን። ይሁንና ስለ ሕሊናችንስ ምን ማለት ይቻላል? ሕሊናችን፣ ለጽድቅ ፍቅር ለማዳበር በምናደርገው ጥረት የሚረዳን እንዴት ነው?

ጥሩ ሕሊና ይኑራችሁ

9. ምንጊዜም ጥሩ ሕሊና መያዛችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?

9 ስንጠመቅ ይሖዋ “ጥሩ ሕሊና” እንዲሰጠን ልመና አቅርበን ነበር። (1 ጴጥ. 3:21) በቤዛው ላይ እምነት ስላለን የኢየሱስ ደም ኃጢአታችንን ይሸፍንልናል፤ በዚህም የተነሳ በአምላክ ፊት ንጹሕ አቋም ይኖረናል። ይሁንና ይህን አቋማችንን ሳናበላሽ ለመቀጠል እንድንችል ምንጊዜም ጥሩ ሕሊና ሊኖረን ይገባል። አንዳንድ ጊዜ ሕሊናችን የሚወቅሰንና ማስጠንቀቂያ የሚሰጠን ከሆነ በሚገባ እየሠራ በመሆኑ አመስጋኞች ልንሆን ይገባል። ሕሊናችን በዚህ መንገድ ምልክት የሚሰጠን መሆኑ ከይሖዋ የጽድቅ መንገዶች ጋር በተያያዘ ንቁ ሕሊና እንዳለን ያሳያል። (1 ጢሞ. 4:2) ይሁንና ሕሊና፣ ለጽድቅ ፍቅር ማዳበር የሚፈልጉ ሰዎችን በሌላም መንገድ ሊጠቅማቸው ይችላል።

10, 11. (ሀ) በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነው ሕሊናችን የሚሰጠንን መመሪያ መስማት ያለብን ለምን እንደሆነ የሚያሳይ ተሞክሮ ተናገር። (ለ) ጽድቅን መውደድ ታላቅ ደስታ የሚያስገኘው ለምንድን ነው?

10 ስህተት የሆነ ነገር ስናደርግ ሕሊናችን ሊኮንነን ወይም ሊያሠቃየን ይችላል። ‘ከጽድቅ መንገድ’ ወጥቶ የነበረን አንድ ወጣት ሁኔታ እንመልከት። የብልግና ምስሎችንና ጽሑፎችን የማየትና የማንበብ ሱስ የተጠናወተው ከመሆኑም ሌላ ማሪዋና የተባለውን አደገኛ ዕፅ ማጨስ ጀመረ። ጉባኤ ሲሄድ የጥፋተኝነት ስሜት ስለሚያድርበትና በአገልግሎት ሲካፈል ግብዝ እንደሆነ ስለሚሰማው በእነዚህ ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች መካፈሉን አቆመ። ይሁንና “ሕሊናዬ ለምፈጽመው ድርጊት ተጠያቂ እንደሚያደርገኝ አልተገነዘብኩም ነበር” በማለት ተናግሯል። አክሎም “ለሁለት ዓመታት ያህል በዚህ የሞኝነት ጎዳና ስመላለስ ቆየሁ” ብሏል። ከዚያም ወደ እውነት ጎዳና ስለ መመለስ ማሰብ ጀመረ። ጸሎቱ እንደማይሰማለት ቢያስብም ወደ ይሖዋ በመጸለይ ይቅር እንዲለው ለመነው። ይህን ካደረገ አሥር ደቂቃ እንኳ ሳይሞላው እናቱ ልትጠይቀው የመጣች ሲሆን ወደ ስብሰባዎች መሄድ እንዲጀምር አበረታታችው። ይህ ወጣት ወደ መንግሥት አዳራሽ በመሄድ ወደ አንድ ሽማግሌ ቀርቦ እንዲያስጠናው ጠየቀ። ውሎ አድሮ ይህ ወጣት ራሱን ወስኖ ተጠመቀ፤ ይሖዋ ሕይወቱን ስላተረፈለት አመስጋኝ ነው።

11 ትክክል የሆነውን ማድረግ ታላቅ ደስታ እንደሚያስገኝ በራሳችን ሕይወት አልተመለከትንም? ጽድቅን እየወደድንና በሕይወታችን ውስጥ በተሟላ ሁኔታ እየፈጸምን ስንሄድ በሰማይ ያለውን አባታችንን የሚያስደስተውን ነገር በማድረጋችን ታላቅ እርካታ እናገኛለን። እስቲ አስበው፦ የሰው ልጆች በሙሉ ንጹሕ ሕሊና ስለሚኖራቸው ደስተኛ የሚሆኑበት ጊዜ ብዙም ሩቅ አይደለም፤ ሁሉም ሰው የአምላክን ባሕርያት በተሟላ ሁኔታ ያንጸባርቃል። እንግዲያው አሁኑኑ ለጽድቅ ከልብ የመነጨ ፍቅር በማዳበር ይሖዋን ለማስደሰት እንጣር።—ምሳሌ 23:15, 16

12, 13. ሕሊናችንን ለማሠልጠን ምን ማድረግ እንችላለን?

12 ሕሊናችንን ለማሠልጠን ምን ማድረግ እንችላለን? ቅዱሳን መጻሕፍትንና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎቻችንን ስናጠና “የጻድቅ ሰው ልብ የሚሰጠውን መልስ ያመዛዝናል” የሚለውን ጥቅስ ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው። (ምሳሌ 15:28) ይህን ማድረጋችን ከሥራ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች በሚያጋጥሙን ጊዜ እንዴት ሊጠቅመን እንደሚችል እስቲ እንመልከት። አንድ ሥራ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ከሚገኘው መመሪያ ጋር በቀጥታ የሚጋጭ ከሆነ አብዛኞቻችን ታማኝና ልባም ባሪያ የሚሰጠንን መመሪያ ምንም ሳናንገራግር በሥራ ላይ እናውላለን። ይሁንና ከሥራ ምርጫ ጋር በተያያዘ ለተነሳው ጥያቄ በግልጽ የተቀመጠ መልስ በማይኖርበት ጊዜ ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ከመረመርን በኋላ ጉዳዩን በጸሎት ልናስብበት ይገባል። * ይህም የሌሎችን ሕሊና የሚጎዳ ነገር ከማድረግ እንድንርቅ የሚያሳስቡትን መመሪያዎች ማጤንንም ይጨምራል። (1 ቆሮ. 10:31-33) በተለይም ከአምላክ ጋር ያለንን ግንኙነት የሚነኩ መመሪያዎችን በቁም ነገር ልንመለከታቸው ይገባል። ይሖዋ እውን ከሆነልን ‘ይህን ሥራ መሥራቴ ይሖዋ እንዲያዝንና እንዲቆጣ ያደርገዋል?’ ብለን ራሳችንን በቅድሚያ እንጠይቃለን።—መዝ. 78:40, 41

13 ለመጠበቂያ ግንብ ጥናት ወይም ለጉባኤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስንዘጋጅ በቀረበው ትምህርት ላይ ማሰላሰል አስፈላጊ መሆኑን ማስታወስ ይኖርብናል። በምንዘጋጅበት ጊዜ በሚጠናው ክፍል ላይ ለቀረቡት ጥያቄዎች መልስ የሚሆነውን ሐሳብ ቶሎ ቶሎ አስምረን ወደ ቀጣዩ አንቀጽ የማለፍ ልማድ አለን? እንዲህ ያለው የጥናት ፕሮግራም ለጽድቅ ያለንን ፍቅር ለማሳደግ ወይም ሕሊናችንን ለማሠልጠን እንደማይረዳን ምንም ጥያቄ የለውም። ለጽድቅ ፍቅር እንድናዳብር ትጋት የተሞላበት ጥናት ማድረግና ከአምላክ ቃል በምናነበው ነገር ላይ ማሰላሰል ያስፈልገናል። በሙሉ ልባችን ጽድቅን ለመውደድ የሚረዳ ሌላ አቋራጭ መንገድ የለም!

ጽድቅን መራብና መጠማት

14. ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ አገልግሎት ስናቀርብ ምን እንዲሰማን ይፈልጋሉ?

14 ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ አገልግሎት ስናቀርብ ደስተኞች እንድንሆን ይፈልጋሉ። ደስተኞች እንድንሆን ምን ሊረዳን ይችላል? ለጽድቅ ፍቅር ማዳበር ለደስታችን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ምንም ጥርጥር የለውም! ኢየሱስ በተራራው ስብከቱ ላይ “ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ደስተኞች ናቸው፤ ይጠግባሉና” ብሏል። (ማቴ. 5:6) ለጽድቅ ፍቅር ማዳበር ለሚፈልጉ ሰዎች እነዚህ ቃላት ምን ትርጉም አላቸው?

15, 16. በመንፈሳዊ የሚራቡና የሚጠሙ ሰዎች የሚረኩት እንዴት ነው?

15 የምንኖርበትን ዓለም የሚገዛው ክፉው ሰይጣን ነው። (1 ዮሐ. 5:19) በማንኛውም አገር የሚታተሙትን ጋዜጦች ብንቃኝ ከአሁን በፊት ታይቶ በማያውቅ መጠን የጭካኔና የዓመፅ ድርጊቶች እየተፈጸሙ እንዳሉ የሚገልጹ ዘገባዎችን እናነባለን። የሰው ልጆች አንዳቸው በሌላው ላይ የሚፈጽሙት የጭካኔ ድርጊት ጽድቅን ለሚወድ ሰው ለማሰብ እንኳ የሚዘገንን ነው። (መክ. 8:9) ይሖዋን የምንወድ ሰዎች፣ ጽድቅን ለመማር የሚፈልጉ ግለሰቦችን መንፈሳዊ ረሃብና ጥማት ማስታገስ የሚችለው አምላክ ብቻ እንደሆነ እናውቃለን። በቅርቡ ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎች ስለሚጠፉ ጽድቅን የሚወዱ ሁሉ ለሕግ በማይገዙ ሰዎችና እነሱ በሚፈጽሙት የክፋት ድርጊት እየተጨነቁ መኖራቸው ያበቃል። (2 ጴጥ. 2:7, 8) ይህ እንዴት ያለ እፎይታ ይሆናል!

16 የይሖዋ አገልጋዮችና የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች እንደመሆናችን መጠን ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ሁሉ ‘እንደሚጠግቡ’ እናውቃለን። አምላክ በሚያመጣው ‘ጽድቅ የሚሰፍንበት’ አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር ላይ የእነዚህ ሰዎች ፍላጎት ሙሉ በሙሉ ይረካል። (2 ጴጥ. 3:13) እንግዲያው ሰይጣን በሚገዛው በዚህ ዓለም ውስጥ ዓመፅና ጭቆና ከመብዛቱ የተነሳ ጽድቅ በመጥፋቱ ተስፋ መቁረጥ ወይም መደነቅ አይኖርብንም። (መክ. 5:8) ሉዓላዊ ጌታ የሆነው ይሖዋ ምን እየተፈጸመ እንዳለ የሚያውቅ ከመሆኑም ሌላ ጽድቅን የሚወዱ ሰዎችን ለማዳን በቅርቡ እርምጃ ይወስዳል።

ጽድቅን መውደድ የሚያስገኘው ጥቅም

17. ጽድቅን መውደድ ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

17 መዝሙር 146:8 በጽድቅ ጎዳና መመላለስ የሚያስገኘውን ትልቅ ጥቅም ያጎላል። መዝሙራዊው “እግዚአብሔር ጻድቃንን ይወዳል” በማለት ዘምሯል። እስቲ አስበው! ለጽድቅ ፍቅር በማዳበራችን የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዥ የሆነው አምላክ ይወደናል። በሕይወታችን ውስጥ መንግሥቱን ካስቀደምን ይሖዋ ስለሚወደን የሚያስፈልጉንን ነገሮች እንደሚሰጠን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (መዝሙር 37:25ን እና ምሳሌ 10:3ን አንብብ።) ጽድቅን የሚወዱ ሰዎች ውሎ አድሮ መላዋን ምድር ይወርሷታል። (ምሳሌ 13:22) አብዛኞቹ የአምላክ ሕዝቦች ጽድቅን በመፈጸማቸው ይህ ነው የማይባል ደስታ እንዲሁም ገነት በሆነችው ውብ ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ሽልማት ያገኛሉ። በአሁኑ ጊዜም እንኳ የአምላክን ጽድቅ የሚወዱ ሰዎች ውስጣዊ ሰላም የሚያገኙ ሲሆን ይህም በቤተሰባቸውም ሆነ በጉባኤያቸው ውስጥ ከሁሉ ጋር ተስማምተው እንዲኖሩ አስተዋጽኦ ያደርጋል።—ፊልጵ. 4:6, 7

18. የይሖዋን ቀን መምጣት ስንጠባበቅ ምን ማድረጋችንን መቀጠል ይኖርብናል?

18 ታላቁ የይሖዋ ቀን የሚመጣበትን ጊዜ ስንጠባበቅ ጽድቅን መፈለጋችንን መቀጠል አለብን። (ሶፎ. 2:2, 3) እንግዲያው ቀና ለሆኑት የይሖዋ አምላክ መንገዶች ከልብ የመነጨ ፍቅር እናዳብር። ይህም ምሳሌያዊ ልባችንን ከጥቃት ለመጠበቅ “የጽድቅን ጥሩር” ምንጊዜም መልበስን ይጨምራል። ከዚህም ሌላ እኛን የሚያስደስተን እንዲሁም የአምላክን ልብ ደስ የሚያሰኝ ጥሩ ሕሊና ይዘን ለመኖር ጥረት ማድረግ ይኖርብናል።—ምሳሌ 27:11

19. ቁርጥ ውሳኔያችን ምን መሆን አለበት? በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የትኛውን ነጥብ እንመለከታለን?

19 “በፍጹም ልባቸው የሚታመኑበትን ለማበርታት የእግዚአብሔር ዐይኖች በምድር ሁሉ ላይ ይመለከታሉ።” (2 ዜና 16:9) በመከራ በተሞላው በዚህ ዓለም ውስጥ አለመረጋጋት፣ ዓመፅና ክፋት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄድ ቢሆንም እኛ ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ ስንጥር ከላይ ያለው ጥቅስ ምንኛ የሚያጽናና ነው! እውነት ነው፣ የምንከተለው የጽድቅ ጎዳና ከአምላክ ለራቀው አብዛኛው የሰው ዘር ግራ የሚያጋባ ሊሆን ይችላል። ይሁንና የይሖዋን የጽድቅ ጎዳና መከተላችን ከፍተኛ ጥቅም ያስገኝልናል። (ኢሳ. 48:17፤ 1 ጴጥ. 4:4) እንግዲያው በሙሉ ልባችን ጽድቅን መውደዳችንንና ማድረጋችንን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ! ይህም ደስታ ያስገኝልናል። ይሁንና በሙሉ ልብ ይሖዋን ማገልገል ሲባል ዓመፅን መጥላትንም ይጨምራል። ዓመፅን መጥላት ሲባል ምን ማለት እንደሆነ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ይብራራል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.12 ከሥራ ጋር በተያያዘ ለሚነሱ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት የሚረዱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መመሪያዎችን ለማግኘት የሚያዝያ 15, 1999 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 28-30 ተመልከት።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ቤዛው ምን ያህል እንደሚጠቅመን መገንዘባችን ለጽድቅ ፍቅር ለማዳበር የሚረዳን እንዴት ነው?

• “የጽድቅን ጥሩር” መልበሳችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

• ሕሊናችንን ማሠልጠን የምንችለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሠለጠነ ሕሊና ከሥራ ጋር በተያያዘ ለሚነሱ ጥያቄዎች መፍትሔ ለማግኘት ይረዳናል