በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዓመፅን ትጠላለህ?

ዓመፅን ትጠላለህ?

ዓመፅን ትጠላለህ?

“ዓመፅን ጠላህ።”—ዕብ. 1:9

1. ኢየሱስ ስለ ፍቅር ምን አስተምሯል?

ኢየሱስ ክርስቶስ የፍቅርን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ሲገልጽ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ አዲስ ትእዛዝ እየሰጠኋችሁ ነው፤ ልክ እኔ እንደ ወደድኳችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ። በመካከላችሁ ፍቅር ካለ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ።” (ዮሐ. 13:34, 35) ኢየሱስ ተከታዮቹን አንዳቸው ለሌላው ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር እንዲያሳዩ አዟቸዋል። ይህ ፍቅር የክርስቲያኖች መለያ ምልክት ነው። ኢየሱስ “ለጠላቶቻችሁ ፍቅር ማሳየታችሁን እንዲሁም ስደት ለሚያደርሱባችሁ መጸለያችሁን ቀጥሉ” የሚል ምክርም ሰጥቷቸዋል።—ማቴ. 5:44

2. የክርስቶስ ተከታዮች ለምን ነገር ጥላቻ ሊያዳብሩ ይገባል?

2 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ስለ ፍቅር ከማስተማሩም ባሻገር ሊጠሉት የሚገባውንም ነገር አስተምሯቸዋል። ኢየሱስን በተመለከተ “ጽድቅን ወደድክ፣ ዓመፅን ጠላህ” ተብሏል። (ዕብ. 1:9፤ መዝ. 45:7) ይህ ደግሞ ለጽድቅ ፍቅር ከማዳበር በተጨማሪ ኃጢአትን ወይም ዓመፅን መጥላትም እንዳለብን ያሳያል። ሐዋርያው ዮሐንስ እንደሚከተለው ብሎ መጻፉ ትኩረት የሚስብ ነው፦ “ኀጢአት የሚያደርግ ሁሉ ዐመፅን ያደርጋል፤ ኀጢአትም ዐመፅ ነው።”—1 ዮሐ. 3:4 አ.መ.ት

3. በዚህ የጥናት ርዕስ ላይ ዓመፅን ከመጥላት ጋር በተያያዘ ስለ የትኞቹ ነገሮች እንመለከታለን?

3 እንግዲያው ክርስቲያኖች የሆንን ሁሉ ‘ዓመፅን እጠላለሁ?’ ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል። ቀጥሎ ከቀረቡት አራት አቅጣጫዎች አንጻር መጥፎ የሆነውን ነገር እንደምንጠላ ማሳየት የምንችለው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት፦ (1) አልኮልን ከመጠን በላይ ስለ መጠጣት ያለን አመለካከት፣ (2) መናፍስታዊ ስለሆኑ ድርጊቶች ያለን አመለካከት፣ (3) ስለ ሥነ ምግባር ብልግና ያለን አመለካከት እንዲሁም (4) ዓመፅን ስለሚወዱ ሰዎች ያለን አመለካከት።

የአልኮል ባሪያ አትሁን

4. ኢየሱስ ከመጠን በላይ መጠጣትን አስመልክቶ ማስጠንቀቂያ ለመስጠት የመናገር ነፃነት ሊኖረው የቻለው ለምንድን ነው?

4 ኢየሱስ ወይን ከአምላክ የተገኘ ስጦታ እንደሆነ በመገንዘብ አልፎ አልፎ ወይን ይጠጣ ነበር። (መዝ. 104:14, 15) ይሁንና ከመጠን በላይ በመጠጣት ይህን ስጦታ ፈጽሞ አላግባብ አልተጠቀመበትም። (ምሳሌ 23:29-33) በመሆኑም ኢየሱስ ተከታዮቹ እንዲህ ካለው ልማድ እንዲርቁ ለመምከር የመናገር ነፃነት ነበረው። (ሉቃስ 21:34ን አንብብ።) ከመጠን በላይ አልኮል መጠጣት ሌሎች ከባድ ኃጢአቶችን ወደ መፈጸም ይመራል። ስለሆነም ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “መረን ለለቀቀ ሕይወት ስለሚዳርጋችሁ በወይን ጠጅ አትስከሩ፤ ከዚህ ይልቅ በመንፈስ መሞላታችሁን ቀጥሉ።” (ኤፌ. 5:18) በተጨማሪም ጳውሎስ በጉባኤ ውስጥ ያሉ አረጋውያን ሴቶች “ለብዙ ወይን ጠጅ የማይገዙ” እንዲሆኑ መክሯል።—ቲቶ 2:3

5. የአልኮል መጠጥ ለመጠጣት የሚወስኑ ሰዎች የትኞቹን ጥያቄዎች ራሳቸውን መጠየቅ አለባቸው?

5 የአልኮል መጠጦችን ለመጠጣት ከወሰንክ ራስህን እንዲህ እያልክ መጠየቅ ይኖርብሃል፦ ‘ከመጠን በላይ መጠጣትን በተመለከተ የኢየሱስ ዓይነት አመለካከት አለኝ? በዚህ ረገድ ለሌሎች ሰዎች ምክር መስጠት ቢኖርብኝ የመናገር ነፃነት ይኖረኛል? ከውጥረት ለመገላገል ወይም ጭንቀቴ ቀለል እንዲልልኝ ለማድረግ ስል እጠጣለሁ? በየሳምንቱ ምን ያህል እጠጣለሁ? አንድ ሰው ብዙ እንደምጠጣ ቢጠቁመኝ ምን ዓይነት ምላሽ እሰጣለሁ? ድርጊቴን ማስተባበል ይቀናኛል? ይባስ ብሎም እቆጣለሁ?’ ለብዙ የወይን ጠጅ የምንገዛ ከሆነ ነገሮችን በትክክል አመዛዝነን ጥበብ የተንጸባረቀበት ውሳኔ የማድረግ ችሎታችን ሊዛባ ይችላል። የክርስቶስ ተከታዮች የማመዛዘን ችሎታቸውን ለመጠበቅ ጥረት ያደርጋሉ።—ምሳሌ 3:21, 22

ከመናፍስታዊ ድርጊቶች ራቅ

6, 7. (ሀ) ኢየሱስ ሰይጣንንና አጋንንቱን ምን አድርጓቸዋል? (ለ) በዛሬው ጊዜ ከመናፍስታዊ ድርጊቶች ጋር የተያያዙ ነገሮች የተስፋፉት ለምንድን ነው?

6 ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ሰይጣንንና አጋንንቱን በጥብቅ ተቃውሟቸዋል። ሰይጣን፣ ኢየሱስ ታማኝነቱን እንዲያጎድፍ ለማድረግ ሲል ያቀረበውን ቀጥተኛ ፈተና ኢየሱስ ተቃውሟል። (ሉቃስ 4:1-13) ከዚህም በላይ በአስተሳሰቡና በድርጊቱ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ ስውር ፈተናዎችን የተገነዘበ ከመሆኑም ሌላ በተሳካ ሁኔታ ተቋቁሟቸዋል። (ማቴ. 16:21-23) በተጨማሪም ኢየሱስ ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች ጨካኝ ከሆኑት አጋንንት ተጽዕኖ አላቋቸዋል።—ማር. 5:2, 8, 12-15፤ 9:20, 25-27

7 ኢየሱስ በ1914 ንጉሥ ሆኖ ከተሾመ በኋላ ሰይጣንንና አጋንንቱን ወደ ምድር በመወርወር ሰማይ እነሱ ከሚያሳድሩት በካይ ተጽዕኖ የጸዳ እንዲሆን አድርጓል። በዚህም ምክንያት ሰይጣን ከምንጊዜውም በበለጠ ዛሬ “መላውን ዓለም [ለማሳሳት]” ቆርጦ ተነስቷል። (ራእይ 12:9, 10) በመሆኑም ከመናፍስታዊ ድርጊቶች ጋር ንክኪ ያላቸው ነገሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ የብዙዎችን ትኩረት እየሳቡ መሆናቸው ሊያስገርመን አይገባም። ታዲያ ራሳችንን ከመናፍስታዊ ድርጊቶች ለመጠበቅ ምን እርምጃዎች መውሰድ አለብን?

8. በመዝናኛ ምርጫችን ረገድ ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ ይኖርብናል?

8 መጽሐፍ ቅዱስ በመናፍስታዊ ድርጊቶች መካፈል አደገኛ መሆኑን በግልጽ ያስጠነቅቃል። (ዘዳግም 18:10-12ን አንብብ።) በዛሬው ጊዜ ሰይጣንና አጋንንቱ መናፍስታዊ ድርጊቶችን በሚያስፋፉ ፊልሞች፣ መጻሕፍትና ኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎች አማካኝነት የሰዎችን አስተሳሰብ እየበከሉ ናቸው። እንግዲያው እያንዳንዳችን መዝናኛዎችን ስንመርጥ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል፦ ‘ባለፉት ወራት ውስጥ የመረጥኳቸው መዝናኛዎች ምን ይመስላሉ? የመረጥኳቸው ፊልሞች፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች፣ የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎች፣ መጻሕፍት ወይም የቀልድ ጽሑፎች የአስማት ድርጊቶች የሚንጸባረቁባቸው ነበሩ? ከመናፍስታዊ ድርጊቶች መራቅ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ተገንዝቤያለሁ ወይስ አደጋዎቹን አቅልዬ እመለከታለሁ? በመዝናኛ ምርጫዬ ረገድ ይሖዋ ምን ሊሰማው እንደሚችል ግምት ውስጥ አስገባለሁ? እንዲህ ላሉ ሰይጣናዊ ተጽዕኖዎች ራሴን አጋልጬ ከሆነ ለይሖዋና ለጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶቹ ያለኝ ፍቅር ከመናፍስታዊ ድርጊቶች ለመራቅ ቆራጥ እርምጃ እንድወስድ ይገፋፋኛል?’—ሥራ 19:19, 20

ኢየሱስ ስለ ሥነ ምግባር ብልግና የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ልብ በል

9. አንድ ሰው ለዓመፅ ፍቅር ሊያዳብር የሚችለው እንዴት ነው?

9 ኢየሱስ፣ ይሖዋ ስለ ፆታ ሥነ ምግባር ያለውን አመለካከት ደግፏል። እንዲህ ብሏል፦ “ፈጣሪ ከመጀመሪያውም ወንድና ሴት አድርጎ እንደፈጠራቸው አላነበባችሁም? ‘በዚህ ምክንያት ሰው ከአባትና ከእናቱ ይለያል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ’ ብሎ እንደተናገረስ አላነበባችሁም? በመሆኑም ከዚህ በኋላ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም። ስለዚህ አምላክ ያጣመረውን ማንም ሰው አይለያየው።” (ማቴ. 19:4-6) ኢየሱስ የምናየው ነገር በልባችን ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ያውቅ ነበር። በመሆኑም በተራራው ስብከቱ ላይ እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “‘አታመንዝር’ እንደተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፣ የፆታ ስሜቱ እስኪቀሰቀስ ድረስ አንዲትን ሴት በምኞት የሚመለከት ሁሉ በዚያን ጊዜ በልቡ ከእሷ ጋር አመንዝሯል።” (ማቴ. 5:27, 28) ኢየሱስ የሰጠውን ይህን ማስጠንቀቂያ ችላ የሚሉ ሰዎች ለዓመፅ ፍቅር እያዳበሩ ናቸው።

10. የብልግና ምስሎችንና ጽሑፎችን የመመልከትና የማንበብ ልማድን ማሸነፍ እንደሚቻል የሚያሳይ ተሞክሮ ተናገር።

10 ሰይጣን የብልግና ምስሎችንና ጽሑፎችን በመጠቀም የፆታ ብልግናን ያስፋፋል። የምንኖርበት ዓለም በዚህ የተሞላ ነው። የብልግና ምስሎችን የሚመለከቱ ሰዎች እነዚህን ምስሎች ከአእምሯቸው ለማውጣት በጣም ይቸገራሉ። አልፎ ተርፎም እንደነዚህ ዓይነት ምስሎችን የማየት ሱስ ሊጠናወታቸው ይችላል። በዚህ ረገድ አንድ ክርስቲያን ምን እንዳጋጠመው እንመልከት። እንዲህ ብሏል፦ “በድብቅ የብልግና ምስሎችን መመልከት ጀመርኩ። ከማየው ነገር ጋር በተያያዘ በፈጠርኩት የቅዠት ዓለም ውስጥ የገባሁ ሲሆን የምፈጽመው ድርጊት ለይሖዋ የማቀርበውን አምልኮ እንደማይነካብኝ አስብ ነበር። ይህ ድርጊት ትክክል እንዳልሆነ ባውቅም ለአምላክ የማቀርበው አገልግሎት አሁንም ቢሆን ተቀባይነት እንዳለው ራሴን ለማሳመን እሞክር ነበር።” ይህ ወንድም አመለካከቱን እንዲለውጥ የረዳው ምንድን ነው? እንዲህ ይላል፦ “ያለብኝን ችግር ለሽማግሌዎች ለመንገር ወሰንኩ፤ በእርግጥ ይህን ማድረግ በሕይወቴ ውስጥ ካከናወንኳቸው ነገሮች ሁሉ በጣም ከብዶኝ ነበር።” ውሎ አድሮ ይህ ወንድም ከዚህ ወራዳ ልማድ ተላቀቀ። “ከዚህ የኃጢአት ድርጊት ሙሉ በሙሉ ከተላቀቅኩ በኋላ ሕሊናዬ ንጹሕ እንደሆነ ተሰማኝ።” በእርግጥም ዓመፅን የሚጠሉ ሰዎች የብልግና ምስሎችንና ጽሑፎችን መጥላት አለባቸው።

11, 12. በሙዚቃ ምርጫችን ረገድ ዓመፅን እንደምንጠላ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

11 ሙዚቃም ሆነ የሙዚቃው ግጥሞች ስሜታችንን በጥልቅ ሊነኩት ስለሚችሉ በምሳሌያዊ ልባችን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። ሙዚቃ የአምላክ ስጦታ ሲሆን ከጥንት ጊዜ ጀምሮ በእውነተኛው አምልኮ ውስጥ ትልቅ ቦታ ነበረው። (ዘፀ. 15:20, 21፤ ኤፌ. 5:19) ይሁንና ክፉ የሆነው የሰይጣን ዓለም የሥነ ምግባር ብልግናን የሚያወድስ ሙዚቃን ያስፋፋል። (1 ዮሐ. 5:19) የምታዳምጠው ሙዚቃ የሚያረክስ እንደሆነና እንዳልሆነ ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው?

12 ራስህን እንዲህ እያልክ መጠየቅ ትችላለህ፦ ‘የማዳምጣቸው ዘፈኖች ግድያን፣ ምንዝርንና ዝሙትን ያበረታታሉ? አምላክን ወይም ቅዱስ ነገሮችን ያቃልላሉ? የማዳምጣቸውን ዘፈኖች ግጥም ለአንድ ሰው ባነብለት ግለሰቡ ግጥሞቹን ሲሰማ ለዓመፅ ጥላቻ እንዳለኝ ያስባል? ወይስ ግጥሞቹ ልብን የሚያረክሱ እንደሆኑ ይሰማዋል?’ ዓመፅን የሚያበረታታ ዘፈን እያዳመጥን ዓመፅን እጠላለሁ ማለት አንችልም። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “ከአፍ የሚወጣ ሁሉ ከልብ ይወጣል፤ ሰውንም የሚያረክሰው ይህ ነው። ለምሳሌ ያህል ከልብ ክፉ ሐሳብ፣ ግድያ፣ ምንዝር፣ ዝሙት፣ ሌብነት፣ በሐሰት መመስከርና ስድብ ይወጣሉ።”—ማቴ. 15:18, 19፤ ከያዕቆብ 3:10, 11 ጋር አወዳድር።

ዓመፅን ስለሚወዱ ሰዎች የኢየሱስ ዓይነት አመለካከት አዳብር

13. በኃጢአት ጎዳና በመመላለስ ልባቸው የደነደነ ሰዎችን በተመለከተ ኢየሱስ ምን አመለካከት ነበረው?

13 ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው ኃጢአተኞች ወይም ዓመፀኞች ንስሐ እንዲገቡ ለመጥራት መሆኑን ተናግሯል። (ሉቃስ 5:30-32) ይሁንና በኃጢአት ጎዳና በመመላለስ ልባቸው የደነደነ ሰዎችን በተመለከተ ምን አመለካከት ነበረው? ኢየሱስ እንዲህ ያሉ ሰዎች ተጽዕኖ እንዳያሳድሩብን መጠንቀቅ እንዳለብን ጠንካራ ማሳሰቢያ ሰጥቷል። (ማቴ. 23:15, 23-26) በተጨማሪም እንዲህ በማለት በግልጽ ተናግሯል፦ “‘ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ’ የሚለኝ ሁሉ ወደ መንግሥተ ሰማያት አይገባም፤ ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚገባው በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ነው። በዚያ ቀን [አምላክ የፍርድ እርምጃ ሲወስድ] ብዙዎች ‘ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣ በስምህ ትንቢት አልተናገርንም? በስምህ አጋንንትን አላወጣንም? በስምህስ ብዙ ተአምራት አላደረግንም?’ ይሉኛል።” ይሁንና ኢየሱስ፣ ኃጢአትን ልማድ ያደረጉና ንስሐ የማይገቡ ሰዎችን “ከእኔ ራቁ” ይላቸዋል። (ማቴ. 7:21-23) እነዚህ ግለሰቦች እንዲህ ያለ ፍርድ የተበየነባቸው ለምንድን ነው? ምክንያቱም እንዲህ ያሉ ሰዎች አምላክን የሚያዋርዱ ከመሆናቸውም በላይ በዓመፅ ድርጊታቸው ሌሎችን ይጎዳሉ።

14. ንስሐ የማይገቡ ኃጢአተኞች ከጉባኤ የሚወገዱት ለምንድን ነው?

14 የአምላክ ቃል፣ ንስሐ የማይገቡ ኃጢአተኞች ከጉባኤ መወገድ እንዳለባቸው መመሪያ ይሰጣል። (1 ቆሮንቶስ 5:9-13ን አንብብ።) ይህ እርምጃ ቢያንስ በሦስት ምክንያቶች የተነሳ አስፈላጊ ነው፦ (1) የይሖዋ ስም ከነቀፋ የጸዳ እንዲሆን፣ (2) ጉባኤው እንዳይበከል እንዲሁም (3) ከተቻለ ኃጢአተኛው ንስሐ እንዲገባ ለመርዳት።

15. ለይሖዋ ያለንን ታማኝነት ጠብቀን መኖር ከፈለግን የትኞቹን ጥያቄዎች በቁም ነገር ልናስብባቸው ይገባል?

15 ከዓመፅ ጎዳናቸው ለመመለስ የማይፈልጉ ሰዎችን በተመለከተ የኢየሱስ ዓይነት አመለካከት አለን? የሚከተሉትን ጥያቄዎች ልናስብባቸው ይገባል፦ ‘ከክርስቲያን ጉባኤ ከተወገደ ወይም ራሱን ካገለለ ግለሰብ ጋር አዘውትሬ ጊዜ አሳልፋለሁ? ግለሰቡ አብሮኝ የማይኖር የቅርብ ዘመዴ ቢሆንስ ምን አደርጋለሁ?’ እንዲህ ያለው ሁኔታ ለጽድቅ ያለንን ፍቅርና ለአምላክ ያለንን ታማኝነት በእጅጉ የሚፈትን ነው። *

16, 17. አንዲት ክርስቲያን እናት ምን ዓይነት ከባድ ሁኔታ አጋጠማት? ንስሐ የማይገቡ ኃጢአተኞች ከጉባኤ እንዲወገዱ የሚያዘውን መመሪያ እንድትደግፍ የረዳት ምንድን ነው?

16 የአንዲትን እህት ምሳሌ እንመልከት፤ ለአቅመ አዳም የደረሰው ልጇ በአንድ ወቅት ይሖዋን ይወድ ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን የዓመፅን ጎዳና የተከተለ ሲሆን ንስሐ ለመግባትም ፈቃደኛ አልነበረም። ስለሆነም ከክርስቲያን ጉባኤ ተወገደ። እህታችን ይሖዋን ትወዳለች፤ ይሁንና ልጇንም ስለምትወደው ከእሱ ጋር ያላትን ግንኙነት እንድታቆም የሚያዘውን ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያ መከተል እጅግ ከብዷት ነበር።

17 አንተ ለዚህች እህት ምን ምክር ትሰጣት ነበር? አንድ ሽማግሌ፣ ይህች እህት የሚሰማትን ሥቃይ ይሖዋ እንደሚረዳላት እንድትገነዘብ ረዳት። ይሖዋ፣ መላእክት ከሆኑት ልጆቹ መካከል አንዳንዶቹ የዓመፅን ጎዳና ሲከተሉ ምን ያህል ተጎድቶ ሊሆን እንደሚችል ይህች እህት እንድታስብ ሽማግሌው አበረታታት። ይሖዋ እንዲህ ያለው ሁኔታ ምን ያህል ስሜትን እንደሚጎዳ ቢያውቅም ንስሐ የማይገቡ ኃጢአተኞች ከጉባኤ እንዲወገዱ እንደሚፈልግ ሽማግሌው ለእህት አስረዳት። እህትም ሽማግሌው የሰጣትን ማሳሰቢያዎች የተቀበለች ሲሆን የውገዳውን ዝግጅት በታማኝነት መደገፏን ቀጠለች። * እንዲህ ያለው ታማኝነት የይሖዋን ልብ ያስደስታል።—ምሳሌ 27:11

18, 19. (ሀ) ዓመፅ የመፈጸም ልማድ ካለው ግለሰብ ጋር ያለንን ግንኙነት ማቋረጣችን ምንን እንደምንጠላ ያሳያል? (ለ) ለአምላክና ለዝግጅቱ ታማኞች መሆናችን ምን ውጤት ሊያስገኝ ይችላል?

18 አንተም ተመሳሳይ ነገር አጋጥሞህ ከሆነ ይሖዋ ስሜትህን እንደሚረዳልህ እንድታስታውስ እናበረታታሃለን። ከተወገደው ወይም ራሱን ካገለለው ግለሰብ ጋር ያለህን ግንኙነት በማቋረጥ ግለሰቡ እንዲህ ያለ እርምጃ እንዲወሰድበት ምክንያት የሆነውን አመለካከት ወይም ድርጊት እንደምትጠላ ታሳያለህ። በተጨማሪም የተሳሳተውን ሰው ስለምትወደው ለእሱ የሚጠቅመውን ለማድረግ እንደምትፈልግ ታሳያለህ። ምናልባትም በታማኝነት ከይሖዋ ጋር መቆምህ የተወገደው ሰው ንስሐ ገብቶ ወደ ይሖዋ የመመለስ አጋጣሚው ሰፊ እንዲሆንለት ሊያደርግ ይችላል።

19 ተወግዳ የነበረችና ከጊዜ በኋላ የተመለሰች አንዲት ሴት እንዲህ በማለት ጽፋለች፦ “ይሖዋ ለሕዝቡ ያለው ፍቅር፣ ድርጅቱ ንጽሕናውን ጠብቆ እንዲቀጥል ለማድረግ የሚያነሳሳው መሆኑ ያስደስተኛል። ውገዳ ከጉባኤው ውጭ ላሉ ሰዎች የጭካኔ ድርጊት ቢመስልም አስፈላጊና እውነተኛ ፍቅር የሚንጸባረቅበት ዝግጅት ነው።” ይህች ሴት ተወግዳ በነበረችበት ጊዜ ቤተሰቧን ጨምሮ የጉባኤው አባላት ከእሷ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት እንደ ወትሮው ቀጥለው ቢሆን ኖሮ ከላይ ያለው መደምደሚያ ላይ መድረስ የምትችል ይመስልሃል? በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተውን የውገዳ ዝግጅት መደገፋችን ጽድቅን እንደምንወድና ይሖዋ የሥነ ምግባር መሥፈርቶችን የማውጣት መብት እንዳለው አምነን እንደምንቀበል ያሳያል።

“ክፋትን ጥሉ”

20, 21. ለዓመፅ ጥላቻ ማዳበር አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

20 ሐዋርያው ጴጥሮስ “የማስተዋል ስሜቶቻችሁን ጠብቁ፤ ንቁዎች ሆናችሁ ኑሩ” በማለት አስጠንቅቋል። እንዲህ ያለው ለምን ነበር? “ጠላታችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን በመፈለግ እንደሚያገሳ አንበሳ ይንጎራደዳል” በማለት ምክንያቱን ነግሮናል። (1 ጴጥ. 5:8) ሰይጣን የሚውጠው ግለሰብ አንተ ትሆን? ይህ በአብዛኛው የተመካው ለዓመፅ ባለህ ጥላቻ ላይ ነው።

21 ለክፋት ጥላቻ ማዳበር ቀላል ነገር አይደለም። ስንወለድ ጀምሮ ኃጢአተኞች ከመሆናችንም ባሻገር የምንኖረው ሥጋዊ ፍላጎቶቻችንን እንድናረካ በሚያበረታታ ዓለም ውስጥ ነው። (1 ዮሐ. 2:15-17) ይሁንና ኢየሱስ ክርስቶስ የተወውን ምሳሌ ከተከተልንና ለይሖዋ አምላክ ጥልቅ ፍቅር ካዳበርን ዓመፅን በመጥላት ረገድ ሊሳካልን ይችላል። እንግዲያው ይሖዋ ‘ታማኞቹን እንደሚጠብቅና ከዐመፀኞች እጅ እንደሚታደጋቸው’ ሙሉ በሙሉ በመተማመን ‘ክፋትን ለመጥላት’ የቆረጥን መሆናችንን እናሳይ!—መዝ. 97:10

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.15 በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ለማግኘት የመስከረም 15, 1981 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ከገጽ 26-31 [መግ 9-102 ከገጽ 14-16] ተመልከት።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ከአልኮል መጠጥ ጋር በተያያዘ አመለካከታችንን ለመመርመር ምን ሊረዳን ይችላል?

• ለመናፍስታዊ ነገሮች እንዳንጋለጥ ምን እርምጃዎች መውሰድ እንችላለን?

• የብልግና ምስሎችንና ጽሑፎችን መመልከትና ማንበብ አደገኛ የሆነው ለምንድን ነው?

• የምንወደው ሰው በሚወገድበት ጊዜ ለዓመፅ ጥላቻ እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአልኮል መጠጥ ለመጠጣት ከወሰንክ የትኞቹን ነጥቦች ልታስብባቸው ይገባል?

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የምትመርጠው መዝናኛ ለመናፍስታዊ ነገሮች እንዳያጋልጥህ ተጠንቀቅ

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የብልግና ምስሎችን የሚመለከት ሰው ለምን ነገር ፍቅር እያዳበረ ነው?