በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአሮን ልጆች ናዳብና አብዩድ ከሞቱ በኋላ ሙሴ የእነሱ ወንድሞች በሆኑት በአልዓዛርና በኢታምር ላይ የተቆጣው ለምን ነበር? ቁጣው እንዲበርድ ያደረገውስ ምንድን ነው?—ዘሌ. 10:16-20

በመገናኛ ድንኳኑ ለሚከናወነው አገልግሎት የክህነት ሥርዓቱ ከተቋቋመ ብዙም ሳይቆይ የአሮን ልጆች ናዳብና አብዩድ ያልተፈቀደ እሳት በማቅረባቸው ምክንያት ይሖዋ በሞት ቀጣቸው። (ዘሌ. 10:1, 2) ሙሴ በሕይወት የተረፉትን የአሮን ልጆች ለሞቱት ወንድሞቻቸው እንዳያለቅሱ አዝዟቸው ነበር። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ፣ አልዓዛርና ኢታምር ለኃጢአት መሥዋዕት የቀረበውን የፍየል ሥጋ ስላልበሉ ሙሴ ተቆጣቸው። (ዘሌ. 9:3) ሙሴ የተቆጣው ለምን ነበር?

ይሖዋ ለሙሴ በሰጠው ሕግ መሠረት የኃጢአት መሥዋዕቱን ያቀረበው ካህን ከፊሉን በመገናኛው ድንኳን ግቢ ውስጥ በአደባባዩ ላይ መብላት ነበረበት። ካህኑ እንዲህ ማድረጉ መሥዋዕቱን ያቀረቡት ሰዎች የሠሩትን ኃጢአት በማስወገድ ስርየት እንደሚያስገኝላቸው ተደርጎ ይቆጠር ነበር። ከመሥዋዕቱ ላይ ጥቂት ደም ተወስዶ የመገናኛው ድንኳን የመጀመሪያ ክፍል በሆነው በቅድስቱ ከቀረበ ግን መሥዋዕቱ መበላት አይገባውም ነበር። ከዚህ ይልቅ ሙሉ በሙሉ መቃጠል ነበረበት።—ዘሌ. 6:24-26, 30

የአሮን ሁለት ልጆች ከሞቱ በኋላ ሙሴ የይሖዋን ትእዛዝ ሙሉ በሙሉ መከተል ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ የተገነዘበ ይመስላል። ለኃጢአት መሥዋዕት የሚቀርበው ፍየል ደም፣ በይሖዋ ፊት በቅድስቱ ያልቀረበ ቢሆንም አልዓዛርና ኢታምር የመሥዋዕቱን ሥጋ ከመብላት ይልቅ እንዳቃጠሉት ሙሴ ሲያውቅ እንደታዘዙት ያላደረጉት ለምን እንደሆነ በቁጣ ጠየቃቸው።—ዘሌ. 10:17, 18

ሙሴ ላቀረበው ጥያቄ መልስ የሰጠው አሮን ነበር፤ ምክንያቱም በሕይወት የተረፉት ካህናት እንዲህ ያለ እርምጃ ሲወስዱ አባታቸውም ተስማምቶ መሆን አለበት። አሮን ሁለቱ ልጆቹ በሞት ከመቀጣታቸው አንጻር ካህናቱ በዚያ ዕለት የቀረበውን የኃጢአት መሥዋዕት ሕሊናቸው ሳይወቅሳቸው መብላት የመቻላቸው ጉዳይ አጠራጥሮት ሊሆን ይችላል። ናዳብና አብዩድ ለፈጸሙት ስህተት በሕይወት ያሉት ካህናት በቀጥታ ተጠያቂ ባይሆኑም ከመሥዋዕቱ መብላታቸው ይሖዋን እንደማያስደስተው አሮን ተሰምቶት ይሆናል።—ዘሌ. 10:19

አሮን፣ የቤተሰቡ አባላት የክህነት ተግባራቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ ባከናወኑበት ዕለት አምላክን ለማስደሰት በጥቃቅን ጉዳዮች ረገድም እንኳ ሳይቀር ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደነበረባቸው አስቦ ይሆናል። ይሁን እንጂ ናዳብና አብዩድ የይሖዋን ስም አቃልለዋል፤ በመሆኑም የአምላክ ቁጣ በእነሱ ላይ ነድዷል። ስለዚህ አሮን፣ እንዲህ ዓይነት በደል የተገኘበት የካህናት ቤተሰብ አባላት ቅዱስ ከሆነው መሥዋዕት መካፈል እንደሌለባቸው ተሰምቶት ይሆናል።

ዘገባው “ሙሴም ይህን በሰማ ጊዜ መልሱ አረካው” ስለሚል ሙሴ ወንድሙ የሰጠውን መልስ አጥጋቢ ሆኖ ያገኘው ይመስላል። (ዘሌ. 10:20) ይሖዋም ቢሆን አሮን በሰጠው መልስ እንደረካ ከሁኔታዎቹ መረዳት ይቻላል።