በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ያሉህን በረከቶች ከልብህ ታደንቃለህ?

ያሉህን በረከቶች ከልብህ ታደንቃለህ?

ያሉህን በረከቶች ከልብህ ታደንቃለህ?

እስራኤላውያን ከግብፅ ባርነት በተአምራዊ ሁኔታ ነፃ ከወጡ በኋላ ይሖዋን በነፃነት ለማምለክ በመቻላቸው መጀመሪያ ላይ በጣም ተደስተው ነበር። (ዘፀ. 14:29 እስከ 15:1, 20, 21) ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ግን አመለካከታቸው ተለወጠ። ያሉበትን ሁኔታ በተመለከተ ማማረር ጀመሩ። ለምን? ይሖዋ ያደረገላቸውን ነገሮች ከማሰብ ይልቅ በምድረ በዳ መኖራቸው ባስከተለባቸው አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ስላተኮሩ ነው። ለሙሴ እንዲህ አሉት፦ “በምድረ በዳ እንድንሞት ከግብፅ ያወጣችሁን ለምንድነው? ምግብ የለም ውሃ የለም ይህን የማይረባ ምግብ [መና] ሰውነታችን ተጸይፎታል።”—ዘኍ. 21:5

ይህ ከሆነ ከበርካታ ዘመናት በኋላ የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊት እንዲህ በማለት ዘምሮ ነበር፦ “እኔ ግን በጸናች ፍቅርህ እታመናለሁ፤ ልቤም በማዳንህ ደስ ይለዋል። ቸርነቱ በዝቶልኛልና፣ ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ።” (መዝ. 13:5, 6) ዳዊት፣ ይሖዋ ያሳየውን ፍቅራዊ ደግነት አልረሳም። እንዲያውም ይሖዋ ባደረገለት ነገሮች ላይ አዘውትሮ ያሰላስል ነበር። (መዝ. 103:2) ይሖዋ ለእኛም ብዙ መልካም ነገሮች አድርጎልናል፤ በመሆኑም ያደረገልንን ነገሮች አቅልለን እንዳንመለከት መጠንቀቃችን ጥበብ ነው። እስቲ በዛሬው ጊዜ አምላክ ከሰጠን በረከቶች መካከል አንዳንዶቹን እንመልከት።

ከይሖዋ ጋር ያለን ‘ወዳጅነት’

መዝሙራዊው “እግዚአብሔር ምስጢሩን ከሚፈሩት ወዳጆቹ አይሰውርም” በማለት ዘምሯል። (መዝ. 25:14) ፍጹም ያልሆኑ የሰው ልጆች በግለሰብ ደረጃ ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት መቻላቸው እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! ይሁንና በዕለት ተዕለት ጉዳዮቻችን በጣም ከመጠመዳችን የተነሳ ለጸሎት ሰፋ ያለ ጊዜ መመደብ ቢያቅተንስ? ይህ ከይሖዋ ጋር በመሠረትነው ጥሩ ወዳጅነት ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ አስብ። ይሖዋ፣ ወዳጆቹ እንደመሆናችን መጠን በእሱ እንድንታመንና በጸሎት አማካኝነት የልባችንን አውጥተን እንድንነግረው ይኸውም ስጋታችንን፣ ፍላጎታችንና ጭንቀታችንን እንድንገልጽለት ይፈልጋል። (ምሳሌ 3:5, 6፤ ፊልጵ. 4:6, 7) ታዲያ የጸሎታችንን ይዘት በተመለከተ በቁም ነገር ልናስብበት አይገባም?

ፖል የተባለ አንድ ወጣት የይሖዋ ምሥክር ለይሖዋ ስለሚያቀርበው ጸሎት ቆም ብሎ ሲያስብ አንዳንድ ማሻሻያዎችን ማድረግ እንደሚያስፈልገው ተገነዘበ። * “ወደ ይሖዋ ስጸልይ ሁልጊዜ ተመሳሳይ አባባሎችን የመጠቀም ልማድ ነበረኝ” በማለት ተናግሯል። ፖል በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ማውጫ (እንግሊዝኛ) በመጠቀም ጸሎትን በተመለከተ ምርምር ያደረገ ሲሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ 180 የሚያህሉ ጸሎቶች እንዳሉ ተረዳ። በእነዚህ ጸሎቶች አማካኝነት በጥንት ጊዜ የነበሩት የይሖዋ አገልጋዮች ውስጣዊ ስሜታቸውን ገልጸዋል። ፖል እንዲህ ብሏል፦ “እንዲህ ባሉት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ምሳሌዎች ላይ በማሰላሰሌ ጸሎት ሳቀርብ ለይሖዋ መናገር የምፈልጋቸውን ነገሮች በዝርዝር መጥቀስ እንደምችል ተምሬያለሁ። ይህ ደግሞ ለይሖዋ የልቤን ግልጽልጽ አድርጌ እንድነግረው ረድቶኛል። አሁን ወደ ይሖዋ መጸለይ በጣም የሚያስደስተኝ ሲሆን ይህም ከእሱ ጋር ለመቀራረብ አስችሎኛል።”

“በተገቢው ጊዜ” የቀረበ ‘ምግብ’

ይሖዋ ከሰጠን በረከቶች መካከል ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማርናቸው በርካታ እውነቶችም ይገኙበታል። ይሖዋ ካዘጋጀልን የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ድግስ መቋደሳችን “ከልብ በመነጨ ደስታ [እንድንዘምር]” ያነሳሳናል። (ኢሳ. 65:13, 14) ይሁን እንጂ መጥፎ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ነገሮች ለእውነት ያለንን ቅንዓት እንዳያቀዘቅዙብን መጠንቀቅ አለብን። ለምሳሌ ያህል፣ ከሃዲዎች ለሚነዙት ፕሮፖጋንዳ ጆሯችንን የምንሰጥ ከሆነ በአስተሳሰባችን ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድርብንና ይሖዋ ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ አማካኝነት “በተገቢው ጊዜ” ለሚያቀርበው መንፈሳዊ ‘ምግብ’ አድናቆት እንድናጣ ሊያደርገን ይችላል።—ማቴ. 24:45-47

ይሖዋን ለዓመታት ያገለገለው አንድሬ የከሃዲዎችን ፕሮፖጋንዳ በማንበቡ ከእውነት ጎዳና የመውጣት አደጋ አጋጥሞት ነበር። ከሃዲዎች ያዘጋጁትን ድረ ገጽ ለአፍታ ያህል ቢመለከት ምንም ችግር እንደማያጋጥመው ተሰምቶት ነበር። እንዲህ ይላል፦ “ከሃዲዎች እውነት እንደሆኑ አድርገው የሚያቀርቧቸው ትምህርቶች መጀመሪያ ላይ ትኩረቴን ስበውት ነበር። ያቀረቧቸውን ሐሳቦች ይበልጥ ባነበብኩ ቁጥር የይሖዋን ድርጅት እንድተው የሚያደርግ በቂ ምክንያት እንዳለኝ ተሰማኝ። ውሎ አድሮ ግን ከሃዲዎች የይሖዋ ምሥክሮችን በመቃወም በሚያነሷቸው ነጥቦች ላይ ምርምር ሳደርግ እነዚህ ሐሰተኛ አስተማሪዎች ምን ያህል መሠሪ እንደሆኑ ተገነዘብሁ። የይሖዋ ምሥክሮች እንደተሳሳቱ ለማረጋገጥ የሚጠቅሱት ‘ጠንካራ ማስረጃ’ ያለ ቦታው የገባ ቁንጽል ሐሳብ መሆኑን ተረዳሁ። በመሆኑም እንደገና ጽሑፎቻችንን ለማንበብ እንዲሁም በስብሰባዎቻችን ላይ ለመገኘት ወሰንኩ። እነዚህን ነገሮች በማቆሜ ብዙ ነገር እንዳመለጠኝ ለመገንዘብ ጊዜ አልወሰደብኝም።” ደስ የሚለው ነገር አንድሬ ወደ ጉባኤ ተመለሰ።

“መላው የወንድማማች ማኅበር”

አፍቃሪ በሆኑ ወንድሞች የተሞላውና አንድነት ያለው የወንድማማች ማኅበር ከይሖዋ ያገኘነው በረከት ነው። (መዝ. 133:1) ሐዋርያው ጴጥሮስ “ለመላው የወንድማማች ማኅበር ፍቅር ይኑራችሁ” በማለት መጻፉ በእርግጥም የተገባ ነው። (1 ጴጥ. 2:17) የክርስቲያናዊው የወንድማማች ማኅበር አባላት በመሆናችን የእምነት አጋሮቻችን የሆኑ መንፈሳዊ አባቶችን፣ እናቶችን ወንድሞችንና እህቶችን ፍቅራዊ ድጋፍ እናገኛለን።—ማር. 10:29, 30

ያም ሆኖ አንዳንድ ጊዜ ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር ያለን ግንኙነት እንዲሻክር የሚያደርጉ የተለያዩ ሁኔታዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ወንድማችን ፍጹም ባለመሆኑ ምክንያት ባሉት ድክመቶች በቀላሉ ልንበሳጭና ግለሰቡ በሚፈጽማቸው ስህተቶች ላይ ብቻ ልናተኩር እንችላለን። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ካጋጠመን ይሖዋ አገልጋዮቹ ፍጹማን ባይሆኑም እንኳ እንደሚወዳቸው ማስታወሱ ጠቃሚ አይሆንም? በተጨማሪም “‘ኃጢአት የለብንም’ ብለን የምንናገር ከሆነ ራሳችንን እያሳሳትን ነው፤ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም።” (1 ዮሐ. 1:8) እንግዲያው “እርስ በርስ መቻቻላችሁንና እርስ በርስ በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ” የሚለውን ጥቅስ ተግባራዊ ለማድረግ ልንጥር አይገባንም?—ቆላ. 3:13

አን የተባለች አንዲት ወጣት፣ ከክርስቲያን ወንድሞቻችን ጋር ያላትን ወዳጅነት ከፍ አድርጋ የመመልከትን አስፈላጊነት የተማረችው ከመከራ ነው። በኢየሱስ ምሳሌ ላይ እንደተጠቀሰው አባካኝ ልጅ ይህች እህትም ከክርስቲያን ጉባኤ እየራቀች ሄደች። ከጊዜ በኋላ ግን ወደ ልቧ የተመለሰች ሲሆን በእውነት ጎዳና መመላለሷን ቀጠለች። (ሉቃስ 15:11-24) አን ካጋጠማት ሁኔታ ምን ትምህርት አገኘች? እንዲህ ብላለች፦ “ወደ ይሖዋ ድርጅት ከተመለስኩ በኋላ፣ ወንድሞችና እህቶች ድክመቶች ቢኖሩባቸውም ሁሉንም ውድ እንደሆኑ አድርጌ መመልከት ጀመርኩ። ከዚህ ቀደም ስህተት መለቃቀም ይቀናኝ ነበር። አሁን ግን በእምነት ባልንጀሮቼ መካከል መሆኔ የሚያስገኝልኝን በረከት በምንም ምክንያት ላለማጣት ቆርጫለሁ። ዓለም፣ ያለንበትን መንፈሳዊ ገነት መሥዋዕት ልናደርግለት የሚገባ ምንም ነገር ሊያቀርብልን አይችልም።”

ላሉህ በረከቶች ምንጊዜም አድናቆት ይኑርህ

የሰው ልጆች ለሚደርሱባቸው ችግሮች ሁሉ መፍትሔው የአምላክ መንግሥት እንደሆነ ያለን ተስፋ በዋጋ የማይተመን ውድ ሀብት ነው። ይህን ተስፋ መጀመሪያ ባወቅንበት ጊዜ ልባችን በደስታ ፈንድቆ ነበር! ኢየሱስ በምሳሌው ላይ እንደገለጸው ነጋዴ ተሰምቶን ነበር፤ ይህ ነጋዴ “ከፍተኛ ዋጋ ያለው አንድ ዕንቁ” ባገኘ ጊዜ “ያለውን ሁሉ ወዲያውኑ በመሸጥ ዕንቁውን ገዛው።” (ማቴ. 13:45, 46) ኢየሱስ፣ ነጋዴው ለዕንቁው ያለው አድናቆት እየቀነሰ እንደሄደ አልተናገረም። በተመሳሳይ እኛም ግሩም ለሆነው ተስፋችን ያለንን አድናቆት በፍጹም ላለማጣት እንጠንቀቅ።—1 ተሰ. 5:8፤ ዕብ. 6:19

ይሖዋን ከ60 ዓመታት በላይ ያገለገሉትን ጂን የተባሉ እህት እንደ ምሳሌ እንውሰድ። እንዲህ ብለዋል፦ “የአምላክ መንግሥት ምንጊዜም እውን ሆኖ እንዲታየኝ የረዳኝ ስለዚህ መንግሥት ለሰዎች መናገሬ ነው። ሰዎች ስለዚህ መንግሥት ምንነት ሲያውቁ በፊታቸው ላይ የሚነበበውን የደስታ ስሜት መመልከቴ በእኔ ላይ በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል። የመንግሥቱ እውነት መጽሐፍ ቅዱስን በማስጠናቸው ሰዎች ሕይወት ላይ የሚያመጣውን ለውጥ ስመለከት ‘ለሰዎች ላካፍለው የምችለው እንዴት ያለ አስደናቂ እውነት አለኝ!’ ብዬ አስባለሁ።”

ላሉን በርካታ መንፈሳዊ በረከቶች አመስጋኝ እንድንሆን የሚያነሳሳን በቂ ምክንያት አለን። ስደት፣ ሕመም፣ እርጅና፣ የመንፈስ ጭንቀት፣ ሐዘን፣ የኢኮኖሚ ችግርና እነዚህን የመሳሰሉ መከራዎች ቢደርሱብንም እነዚህ ሁሉ ነገሮች ጊዜያዊ እንደሆኑ እናውቃለን። በአምላክ መንግሥት ሥር ከመንፈሳዊ በረከቶች በተጨማሪ ሌሎች በረከቶችም እናገኛለን። በአሁኑ ጊዜ በጽናት እየተቋቋምን ያለነው ማንኛውም መከራ በአዲሱ ሥርዓት እንደሚወገድ እናውቃለን።—ራእይ 21:4

እስከዚያው ድረስ ግን ያሉንን መንፈሳዊ በረከቶች እናድንቅ፤ እንዲሁም እንደሚከተለው በማለት እንደዘመረው መዝሙራዊ ዓይነት የአድናቆት ስሜት እናሳይ፦ “እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ አንተ ያደረግኸው ድንቅ ነገር ብዙ ነው፤ ለእኛ ያቀድኸውን፣ ሊዘረዝርልህ የሚችል ማንም የለም፤ ላውራው ልናገረው ብል፣ ስፍር ቍጥር አይኖረውም።”—መዝ. 40:5

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.6 ስሞቹ ተቀይረዋል።

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በመከራችን ጊዜ የምናገኘው መንፈሳዊ ድጋፍ ካሉን በረከቶች አንዱ ነው