በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሐቀኝነት በጎደለው ዓለም ውስጥ ሐቀኛ ሆኖ መኖር

ሐቀኝነት በጎደለው ዓለም ውስጥ ሐቀኛ ሆኖ መኖር

ሐቀኝነት በጎደለው ዓለም ውስጥ ሐቀኛ ሆኖ መኖር

ሐቀኝነትን ማጉደል እንደምንተነፍሰው አየር በየትኛውም ቦታ ተስፋፍቶ ይገኛል። ሰዎች ይዋሻሉ፣ ይሰርቃሉ፣ ከዋጋ በላይ ያስከፍላሉ እንዲሁም ዕዳቸውን አይከፍሉም፤ ከዚህም ሌላ ከንግድ ጋር በተያያዘ የሚያምታቱ ሲሆን በዚህም ይኩራራሉ። የምንኖረው እንደዚህ ዓይነት መንፈስ በተስፋፋበት ዓለም ውስጥ በመሆኑ ሐቀኛ ለመሆን ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ የሚፈትኑ ሁኔታዎች ብዙ ጊዜ ያጋጥሙናል። ሐቀኝነት የጎደለው ተግባር እንድንፈጽም የሚገፋፋንን ዝንባሌ መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው? ይህን ለማድረግ የሚረዱንን ሦስት ቁልፍ ነጥቦች እስቲ እንመልከት። እነሱም ይሖዋን መፍራት፣ ንጹሕ ሕሊና እንዲሁም ባለን ነገር መርካት ናቸው።

ለይሖዋ ጤናማ ፍርሃት ማዳበር

ነቢዩ ኢሳይያስ “እግዚአብሔር ዳኛችን ነው፤ እግዚአብሔር ሕግ ሰጪያችን ነው፤ እግዚአብሔር ንጉሣችን ነው” በማለት ጽፏል። (ኢሳ. 33:22) የይሖዋን ሥልጣን መገንዘባችን አምላካዊ ፍርሃት እንድናዳብር የሚረዳን ሲሆን ይህ ደግሞ ሐቀኝነትን ከማጉደል ለመራቅ ቁርጥ ውሳኔ እንድናደርግ ያነሳሳናል። ምሳሌ 16:6 “እግዚአብሔርን በመፍራት ሰው ከክፋት ይርቃል” ይላል። እንዲህ ዓይነቱ ፍርሃት አምላክ ተበቃይ እንደሆነ በማሰብ መሸበርን ወይም መርበድበድን የሚያመለክት አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ስለ እኛ በጥልቅ የሚያስበውን በሰማይ የሚገኘውን አባታችንን ላለማሳዘን እንድንጠነቀቅ የሚያደርገን ጤናማ ፍርሃት ነው።—1 ጴጥ. 3:12

እንዲህ ያለ ጤናማ ፍርሃት የሚያሳድረውን በጎ ተጽዕኖ በምሳሌ ለማስረዳት አንድ ተሞክሮ እንመልከት። ሪካርዱና ባለቤቱ ፈርናንደ ከሰባት መቶ የአሜሪካ ዶላር ጋር የሚመጣጠን ገንዘብ ከባንክ ሒሳባቸው አወጡ። * ፈርናንደ ገንዘቡን እንደተቀበለች ሳትቆጥረው ቦርሳዋ ውስጥ ከተተችው። እነዚህ ባልና ሚስት አንዳንድ ወጪዎቻቸውን ከከፈሉ በኋላ ወደ ቤታቸው ሄዱ፤ ቤት ደርሰው የቀራቸውን ገንዘብ ሲመለከቱ ከባንኩ ያወጡትን የሚያህል ገንዘብ በፈርናንደ ቦርሳ ውስጥ አገኙ። “የባንክ ቤቷ ገንዘብ ተቀባይ ትርፍ ገንዘብ ሰጥታናለች ማለት ነው” ብለው አሰቡ። ያልተከፈሉ ሌሎች ብዙ ወጪዎች ስለነበሯቸው መጀመሪያ ላይ ገንዘቡን ለማስቀረት ተፈትነው ነበር። ሪካርዱ እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ ገንዘቡን ለመመለስ የሚያስችል ጥንካሬ እንዲሰጠን ጸለይን። አምላክ በ⁠ምሳሌ 27:11 ላይ ባቀረበው ልመና መሠረት እሱን ለማስደሰት ያለን ፍላጎት ገንዘቡን እንድንመልስ አደረገን።”

በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊና

ሕሊናችንን ለማሠልጠን መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና የምንማረውን በተግባር ለማዋል ጥረት ማድረግ ያስፈልገናል። እንዲህ ስናደርግ ‘ሕያውና ኃይለኛ የሆነው የአምላክ ቃል’ አእምሯችንን ብቻ ሳይሆን ልባችንንም በጥልቅ ይነካዋል። ይህ ደግሞ “በሁሉም ነገር በሐቀኝነት ለመኖር” ያነሳሳናል።—ዕብ. 4:12፤ 13:18

የዥዋውን ሁኔታ እንመልከት። አምስት ሺህ የአሜሪካ ዶላር የሚያህል ዕዳ ነበረበት። ዥዋው ዕዳውን ሳይከፍል ወደ ሌላ አገር ሄደ። ከስምንት ዓመት በኋላ ዥዋው እውነትን አወቀ፤ በዚህ ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊናው አበዳሪውን እንዲፈልግና ዕዳውን እንዲከፍል አነሳሳው። ዥዋው ሚስቱንና አራት ልጆቹን የሚያስተዳድረው በሚያገኛት አነስተኛ ገቢ ስለነበር በየወሩ የተወሰነ ገንዘብ በመክፈል ረዘም ባለ ጊዜ ውስጥ ዕዳውን ከፍሎ እንዲጨርስ አበዳሪው ፈቀደለት።

ባለን ነገር መርካት

ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ባለው ነገር ለሚረካ ሰው ለአምላክ ማደር ትልቅ ትርፍ ያስገኛል። . . . ምግብ እንዲሁም ልብስና መጠለያ ካለን በእነዚህ ነገሮች ረክተን መኖር ይገባናል።” (1 ጢሞ. 6:6-8) ይህን ጥበብ ያዘለ ምክር ልብ ማለታችን ስግብግብነት በሚንጸባረቅባቸውና አጠያያቂ በሆኑ ንግዶች ወይም በአጭር ጊዜ ለመክበር ያስችላሉ በሚባሉ ውጥኖች ውስጥ እጃችንን ከማስገባት ይጠብቀናል። (ምሳሌ 28:20) ከዚህም በተጨማሪ የጳውሎስን ምክር መከተላችን መሠረታዊ የሆነው ፍላጎታችን እንደሚሟላልን በመተማመን የአምላክን መንግሥት እንድናስቀድም ይረዳናል።—ማቴ. 6:25-34

ይሁን እንጂ ‘ሀብት የማታለል ኃይል’ ያለው በመሆኑ በስግብግብነትና በመጎምጀት ወጥመድ የመውደቅን አደጋ ፈጽሞ አቅልለን መመልከት አይኖርብንም። (ማቴ. 13:22) የአካንን ታሪክ እናስታውስ። አካን፣ እስራኤላውያን በተአምራዊ መንገድ የዮርዳኖስን ወንዝ ሲያቋርጡ ተመልክቷል። ያም ሆኖ በስግብግብነት ወጥመድ በመውደቁ ከኢያሪኮ ከተማ ከተማረከው ዕቃ መካከል ብርና ወርቅ እንዲሁም በጣም ውድ የሆነ ልብስ ወሰደ። እንዲህ ማድረጉ ሕይወቱን አሳጥቶታል። (ኢያሱ 7:1, 20-26) ከብዙ ዘመናት በኋላ ኢየሱስ “ተጠንቀቁ፤ ከመጎምጀትም ሁሉ ተጠበቁ” የሚል ማሳሰቢያ መስጠቱ ምንም አይገርምም።—ሉቃስ 12:15

በሥራ ቦታችሁ ሐቀኞች ሁኑ

በሁሉም ነገር ሐቀኞች ሆነን ለመኖር ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ሊፈትኑ የሚችሉ አንዳንድ ሁኔታዎችን እስቲ እንመልከት። በሥራ ቦታችን ሐቀኛ መሆን ‘አለመስረቅንም’ ይጨምራል፤ መስረቅ በሌሎች ዘንድ የተለመደ ቢሆንም እንኳ እኛ ከዚህ ድርጊት መራቅ ይኖርብናል። (ቲቶ 2:9, 10) በመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ የሚሠራው ጁራንዲር የጉዞ ወጪውን ሪፖርት የሚያደርገው በሐቀኝነት ነበር። አብረውት የሚሠሩት ሰዎች ግን ለጉዞ ካወጡት ገንዘብ በላይ ሪፖርት ያደርጉ ነበር። ይህን ማድረግ የቻሉት የዲፓርትመንቱ ኃላፊ ሐቀኛ ላልሆኑት ሠራተኞች ስለሚሸፍንላቸው ነው። እንዲያውም ይህ ኃላፊ ጁራንዲር ሐቀኛ በመሆኑ ተግሣጽ የሰጠው ከመሆኑም ባሻገር ለሥራ ወደ ሌላ ቦታ እንዳይወጣ አደረገው። ከጊዜ በኋላ ግን ድርጅቱ የሒሳብ ምርመራ የተደረገለት ሲሆን ጁራንዲርም ሐቀኛ በመሆኑ ተመሰገነ። ከዚህም በላይ የደረጃ እድገት አገኘ።

አንድሬ የተባለ የሽያጭ ሠራተኛ፣ ደንበኞቹን ላገኙት አገልግሎት እጥፍ እንዲያስከፍላቸው ከአሠሪው ትእዛዝ ተሰጠው። ወንድማችን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎችን መከተል እንዲችል ድፍረት እንዲሰጠው ወደ ይሖዋ ጸለየ። (መዝ. 145:18-20) በተጨማሪም የተሰጠውን መመሪያ መከተል የማይችለው ለምን እንደሆነ ለአሠሪው ለመግለጽ ሞከረ፤ ሆኖም አልተሳካለትም። በመሆኑም አንድሬ ጥሩ ደሞዝ የሚያስገኝለትን ይህን ሥራ ለማቆም ወሰነ። ይሁንና አንድ ዓመት ከሚጠጋ ጊዜ በኋላ የቀድሞው አሠሪው አንድሬን ወደ ሥራ ገበታው እንዲመለስ ጠየቀው፤ አሠሪው ደንበኞቹ ከተገቢው በላይ እንዲከፍሉ መደረጋቸው እንደቀረ ለወንድማችን ነገረው። አንድሬ እድገት ተሰጥቶት ሥራ አስኪያጅ ሆነ።

ዕዳችሁን ክፈሉ

ሐዋርያው ጳውሎስ “በማንም ላይ ምንም ዕዳ አይኑርባችሁ” በማለት ክርስቲያኖችን መክሯል። (ሮም 13:8) ያበደረን ግለሰብ ሀብታም ስለሆነ ገንዘቡ እንደማያስፈልገው በማሰብ ዕዳችንን ላለመክፈል ሰበብ እናቀርብ ይሆናል። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ “ኀጢአተኛ ይበደራል፤ መልሶም አይከፍልም” እንደሚል ማስታወስ ይኖርብናል።—መዝ. 37:21

ይሁን እንጂ ‘ባልተጠበቁ ክስተቶች’ ምክንያት የተበደርነውን ገንዘብ መክፈል ቢያቅተንስ? (መክ. 9:11 NW) ፍራንሲስኩ የቤቱን ዕዳ ለመክፈል ከሰባት ሺህ የአሜሪካ ዶላር ጋር የሚመጣጠን ገንዘብ ከአልፍሬዶ ይበደራል። ሆኖም ከንግዱ ጋር በተያያዘ አንዳንድ ችግሮች ስላጋጠሙት ዕዳውን በተባለው ቀን መክፈል አልቻለም። ፍራንሲስኩ ቅድሚያውን ወስዶ ወደ አልፍሬዶ በመሄድ ሁኔታውን ነገረው። አልፍሬዶም፣ ፍራንሲስኩ በየጊዜው የተወሰነ ገንዘብ በመክፈል ረዘም ባለ ጊዜ ውስጥ ዕዳውን ከፍሎ እንዲጨርስ ተስማማ።

የተሳሳተ መልእክት ከማስተላለፍ ተቆጠቡ

በአንደኛው መቶ ዘመን በነበረው የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ይገኙ የነበሩት ሐናንያና ሰጲራ የተባሉ ባልና ሚስት የተዉትን መጥፎ ምሳሌ አስታውስ። መሬት ከሸጡ በኋላ ከሽያጩ የተወሰነውን ገንዘብ ወደ ሐዋርያት በማምጣት ሙሉውን ገንዘብ እንደሰጡ ተናገሩ። እነዚህ ባልና ሚስት በሌሎች ዘንድ በጣም ለጋስ እንደሆኑ ተደርገው እንዲታዩ ፈልገው ነበር። ይሁንና ሐዋርያው ጴጥሮስ አታላይነታቸውን በአምላክ መንፈስ መሪነት ያጋለጠ ሲሆን እነዚህ ባልና ሚስትም ይሖዋ ስለቀሰፋቸው ሞቱ።—ሥራ 5:1-11

ሐቀኛ ካልነበሩት ከሐናንያና ከሰጲራ በተቃራኒ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ግልጽና ሐቀኞች ናቸው። ሙሴ፣ ቁጣውን ሳይቆጣጠር በመቅረቱ ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዳይገባ እንደተከለከለ በሐቀኝነት ዘግቧል። (ዘኍ. 20:7-13) በተመሳሳይም ዮናስ ወደ ነነዌ ከመሄዱ በፊትም ሆነ ለነነዌ ሰዎች ከሰበከ በኋላ ያሳየውን ድክመት ለመሸፋፈን አልሞከረም። ከዚህ ይልቅ ሁኔታውን በግልጽ ጽፎታል።—ዮናስ 1:1-3፤ 4:1-3

እውነቱን መናገር ደስ የማይል ውጤት ሊያስከትል ቢችልም እንኳ ይህን ማድረግ ድፍረት እንደሚጠይቅ እሙን ነው፤ የ14 ዓመት ወጣት የሆነችው ናታውየ በትምህርት ቤት ያጋጠማት ነገር ይህን ያሳያል። የፈተና ወረቀቷን ስትመለከት የጻፈችው መልስ የተሳሳተ ቢሆንም አስተማሪዋ ትክክል እንደሆነ አድርጎ እንዳረመላት አስተዋለች። ናታውየ ጉዳዩን ለአስተማሪዋ ብትናገር ያገኘችው ውጤት እንደሚቀንስባት ብታውቅም ይህን ከማድረግ ወደኋላ አላለችም። ናታውየ እንዲህ ብላለች፦ “ወላጆቼ ይሖዋን ለማስደሰት ሐቀኛ መሆን እንዳለብኝ ሁልጊዜ ያስተምሩኛል። ለአስተማሪዬ ባልናገር ኖሮ ሕሊናዬ እረፍት አይሰጠኝም ነበር።” አስተማሪዋም የናታውየን ሐቀኝነት አድንቋል።

ሐቀኝነት—ይሖዋን የሚያስከብር ባሕርይ

የ17 ዓመት ወጣት የሆነችው ጂዜል 35 የአሜሪካ ዶላር የሚያህል ገንዘብና ሰነዶችን የያዘ የገንዘብ ቦርሳ አገኘች። ጂዜል የትምህርት ቤቷ ኃላፊዎች ቦርሳውን ለባለቤቱ እንዲመልሱ አደረገች። ከአንድ ወር በኋላ የትምህርት ቤቱ ምክትል ርዕሰ መምህር፣ የጂዜልን ሐቀኝነት በማድነቅ የምስጋና ደብዳቤ በክፍሏ ተማሪዎች ፊት አነበበ፤ ከዚህም በላይ ቤተሰቧ ሃይማኖታዊ ሥልጠና በመስጠት ጥሩ አድርገው ስላሳደጓት አመሰገናቸው። የጂዜል “መልካም ሥራ” ለይሖዋ ክብር አምጥቷል።—ማቴ. 5:14-16

እርግጥ ነው፣ “ራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብ የሚወዱ፣ ጉረኞች፣ ትዕቢተኞች፣ . . . ታማኝ ያልሆኑ” ሰዎች በሞሉበት ዓለም ውስጥ ሐቀኛ መሆን ጥረት ይጠይቃል። (2 ጢሞ. 3:2) ያም ሆኖ ለይሖዋ ጤናማ ፍርሃት ካዳበርን፣ በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊና ካለንና ባለን ነገር የምንረካ ከሆነ ሐቀኝነት በጎደለው ዓለም ውስጥ ሐቀኞች ሆነን መኖር እንችላለን። በተጨማሪም ‘ጻድቅ ከሆነውና የጽድቅ ሥራ ከሚወደው’ ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ይኖረናል።—መዝ. 11:7

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.5 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ለይሖዋ ጤናማ ፍርሃት ማዳበራችን ሐቀኛ ለመሆን ያደረግነውን ውሳኔ ያጠነክርልናል

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሐቀኛ መሆናችን ይሖዋን ያስከብረዋል