በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ብዙ ጥሩ ነገሮችን አግኝቻለሁ

ብዙ ጥሩ ነገሮችን አግኝቻለሁ

ብዙ ጥሩ ነገሮችን አግኝቻለሁ

አርተር ቦኖ እንደተናገሩት

ጊዜው 1951 ነበር። እኔና ባለቤቴ ኢደት በአንድ የአውራጃ ስብሰባ ላይ እያለን በሚስዮናዊነት አገልግሎት መካፈል ለሚፈልጉ ስለተዘጋጀው ስብሰባ የሚገልጽ ማስታወቂያ ሲነገር ሰማን።

በዚህ ጊዜ ባለቤቴን “እስቲ እንሂድና ንግግሩን እንስማ!” አልኳት።

ኢደትም “አርት፣ ይህ ለእኛ የሚሆን አይደለም!” አለችኝ።

“ምናለበት ኢዲ፣ ማዳመጥ ብቻ እኮ ነው።”

ስብሰባው ካለቀ በኋላ የጊልያድ ትምህርት ቤት ማመልከቻ ቅጽ ተሰጠን።

ኢደትን “ቅጾቹን እንሙላቸው!” አልኳት።

እሷም “እንዴ አርት፣ ቤተሰቦቻችንስ?” በማለት ጠየቀችኝ።

ይህ የአውራጃ ስብሰባ ከተካሄደ ከአንድ ዓመት ከመንፈቅ በኋላ በጊልያድ ትምህርት ቤት ሠልጥነን በኢኳዶር፣ ደቡብ አሜሪካ እንድናገለግል ተመደብን።

እኔና ባለቤቴ በአውራጃ ስብሰባ ላይ ካደረግነው ውይይት መገንዘብ እንደምትችሉት ማንኛውም ነገር ይቻላል የሚል አመለካከት ያለኝና ያሰብኩትን ከማድረግ ወደኋላ የማልል ቆራጥ ሰው ነኝ። ኢደት ደግሞ ገራምና ጭምት ሰው ናት። ያደገችው በፔንሲልቬንያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በምትገኝ ኤልዛቤት የምትባል አነስተኛ ከተማ ሲሆን ከአካባቢዋ ራቅ ወደሚል ቦታ ተጉዛም ሆነ የሌላ አገር ሰው አግኝታ አታውቅም። ለኢደት ከቤተሰቧ መለየት ከባድ ነበር። ያም ሆኖ ወደ ሌላ አገር ሄደን እንድናገለግል የተሰጠንን ተልእኮ ለመቀበል ሙሉ በሙሉ ፈቃደኛ ነበረች። በ1954 ኢኳዶር የደረስን ሲሆን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በዚህች አገር በሚስዮናዊነት እያገለገልን ነው። ባሳለፍናቸው ዓመታት ውስጥ ብዙ ጥሩ ነገሮችን አግኝተናል። አንዳንዶቹን መስማት ትፈልጋላችሁ?

አስደሳች ትዝታዎች

የመጀመሪያው ምድባችን 2,850 ሜትር ያህል ከፍታ ባላትና በአንዲስ ተራሮች ላይ በምትገኘው በዋና ከተማዋ በኪቶ ነበር። በባሕር ዳርቻ ላይ ከምትገኘው ከጉዋያኪል ተነስተን ኪቶ ለመድረስ በባቡርና በጭነት መኪና ለሁለት ቀናት መጓዝ ነበረብን፤ በአሁኑ ጊዜ በአውሮፕላን እንዲህ ያለውን ጉዞ ለማድረግ 30 ደቂቃ ብቻ በቂ ነው! በኪቶ አራት የማይረሱ ዓመታትን አሳልፈናል። ከዚያም በ1958 ሌላ ጥሩ ነገር አገኘን፤ በወረዳ ሥራ እንድናገለግል ተጋበዝን።

በወቅቱ በመላ አገሪቱ የነበሩት ሁለት ትናንሽ ወረዳዎች ብቻ ነበሩ። ስለሆነም ጉባኤዎችን ከመጎብኘት በተጨማሪ በዓመት ውስጥ ለበርካታ ሳምንታት፣ የአሜሪካ ሕንዶች በሚኖሩባቸውና አንድም የይሖዋ ምሥክር በሌለባቸው አነስተኛ መንደሮች ውስጥ እንሰብክ ነበር። በእነዚህ መንደሮች ውስጥ በአብዛኛው የምናገኘው ማረፊያ መስኮት የሌለው ጠባብ ክፍል ሲሆን ከአልጋ በስተቀር ሌላ ምንም ነገር አልነበረውም። በአንድ የእንጨት ሣጥን ውስጥ የጋዝ ምድጃ፣ ድስት፣ ሳህኖች፣ ለማጠቢያ የሚሆን ጎድጓዳ ሳህን፣ አንሶላዎች፣ የወባ መከላከያ አጎበር፣ ልብሶች፣ የጋዜጣ ወረቀቶችና ሌሎች ነገሮች እንይዝ ነበር። አይጦች ወደ ክፍላችን በቀላሉ እንዳይገቡ ለመከላከል ስንል በጋዜጣ ወረቀት ተጠቅመን ግድግዳው ላይ ያሉትን ቀዳዳዎች እንደፍናቸው ነበር።

የምናርፍበት ክፍል ጭልምልም ያለ ቢሆንም ምሽት ላይ በጋዝ ምድጃችን ያበሰልነውን ቀለል ያለ ምግብ አልጋችን ላይ ቁጭ ብለን እየበላን አስደሳች ጭውውት እናደርግ የነበረበት ጊዜ ዛሬም ድረስ ወለል ብሎ ይታየናል። እኔ ችኩል በመሆኔ ብዙውን ጊዜ ሳላስብ እናገራለሁ፤ አንዳንድ ጊዜ ባለቤቴ በጉብኝቱ ወቅት ለማገኛቸው ወንድሞች ሐሳቤን በተሻለ መንገድ መግለጽ የምችልባቸውን ዘዴዎች ረጋ ብለን በምንጨዋወትባቸው በእነዚያ ምሽቶች ትጠቁመኛለች። የሰጠችኝን ሐሳቦች በተግባር ሳውል የማደርጋቸው ጉብኝቶች ወንድሞችን ይበልጥ የሚያበረታቱ እየሆኑ መጡ። በሌላ በኩል ደግሞ ስለ ሌሎች ደግነት የጎደለው ነገር ስናገር ባለቤቴ ዝም በማለት በተናገርኩት ነገር እንዳልተደሰተች ትጠቁመኛለች። በዚህም የተነሳ ለወንድሞቼ አዎንታዊ አመለካከት መያዝን ተምሬያለሁ። አብዛኛውን ጊዜ ግን ምሽት ላይ የምናደርገው ጭውውት ከመጠበቂያ ግንብ ባገኘናቸው ትምህርቶች ወይም በዕለቱ በአገልግሎት ባጋጠሙን ነገሮች ላይ ያተኮረ ነበር። ደግሞም በጣም የሚያስደስቱ ተሞክሮዎች ነበሩን!

ካርሎስን ያገኘንበት መንገድ

በምዕራብ ኢኳዶር በምትገኘው ሂፒሃፓ በምትባል ከተማ የሚኖር ካርሎስ ሜሂያ የተባለ ፍላጎት ያለው ሰው እንድናገኝ ተነገረን፤ ከስሙ በስተቀር የዚህ ሰው አድራሻ አልተሰጠንም። ጠዋት ላይ ከተከራየነው ቤት ወጥተን ሰውየውን ፍለጋ ስንጀምር ወዴት እንደምንሄድ አናውቅም ነበር፤ በመሆኑም ዝም ብለን በአንድ አቅጣጫ መጓዝ ጀመርን። ማታ ኃይለኛ ዝናብ በመጣሉ መንገዱ ጭቃ በጭቃ ሆኖ ስለነበር ጉድጓድ ውስጥ ላለመግባት እየተጠነቀቅን እንጓዝ ነበር። ከባለቤቴ ፊት ፊት እየሄድኩ ሳለ በድንገት ከኋላዬ “አርት!” የሚል የድረሱልኝ ጥሪ ሰማሁ። ዞር ስል ኢዲ እስከ ጉልበቷ ድረስ ጭቃ ውስጥ ገብታለች። ፊቷ ላይ የሚነበበውን ጭንቀት ባላይ ኖሮ ሁኔታው በሳቅ ፍርስ የሚያደርግ ነበር።

ኢዲን ከጭቃው ውስጥ ጎትቼ ባወጣትም ጫማዋ ተቀርቅሮ ቀረ። ሁለት ትንንሽ ልጆች ይመለከቱን ስለነበር “ጫማውን ከጭቃው ውስጥ ካወጣችሁ ገንዘብ እሰጣችኋለሁ” አልኳቸው። ልጆቹ በብርሃን ፍጥነት ጫማውን አወጡት፤ ሆኖም ኢዲ መታጠብ ነበረባት። የልጆቹ እናት ሁኔታውን ትከታተል ስለነበር ወደ ቤቷ እንድንገባ ጋበዘችን፤ ከዚያም ልጆቹ ጫማውን ሲያጸዱ እናታቸው ደግሞ ባለቤቴ እግሯን እንድትታጠብ አደረገች። ከዚያ ቤት ተሰናብተን ከመሄዳችን በፊት አንድ ጥሩ ነገር አጋጠመን። ሴትየዋን ካርሎስ ሜሂያ የሚባል ሰው ታውቅ እንደሆነ ጠየቅኋት። በመገረም ስሜት “ባለቤቴ ነው” አለችን። ከጊዜ በኋላ እነዚህ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የተጀመረላቸው ሲሆን ሁሉም የቤተሰቡ አባላት ተጠመቁ። ከዓመታት በኋላ ካርሎስ፣ ሚስቱ እንዲሁም አንድ ወንድና አንዲት ሴት ልጃቸው ልዩ አቅኚዎች ሆኑ።

አስቸጋሪ ጉዞ ሆኖም ሞቅ ያለ አቀባበል

በወረዳ ሥራ የምናደርገው ጉዞ አስቸጋሪ ነበር። በአውቶቡሶች፣ በባቡሮች፣ በጭነት መኪኖች፣ ከግንድ በተፈለፈሉ ታንኳዎችና በትናንሽ አውሮፕላኖች እንጠቀም ነበር። በአንድ ወቅት በኮሎምቢያ ድንበር አቅራቢያ ባሉ ዓሣ በማስገር የሚተዳደሩ ሰዎች በሚገኙባቸው መንደሮች ውስጥ ስንሰብክ የአውራጃ የበላይ ተመልካች የሆነው ጆን መክሌነከን እና ባለቤቱ ዶረቲ ከእኛ ጋር ሄዱ። የተጓዝነው ከግንድ ተፈልፍሎ በተሠራና ሞተር በተገጠመለት ታንኳ ነበር። ግዝፈታቸው ታንኳውን የሚያህል ሻርኮች በአጠገባችን ይዋኙ ጀመር! ልምድ ያለው የታንኳው ነጂ እንኳ የሻርኮቹ ትልቅነት በጣም ስላስደነገጠው በፍጥነት ወደ ባሕሩ ዳርቻ ወሰደን።

በወረዳ ሥራ ላይ ያጋጠሙን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ካገኘነው በረከት ጋር ሲወዳደሩ እዚህ ግቡ የሚባሉ አይደሉም። እንግዳ ተቀባይ ከሆኑ ግሩም ወንድሞች ጋር መተዋወቅ ችለናል። ብዙውን ጊዜ በእንግድነት የተቀበሉን ቤተሰቦች እነሱ በቀን ውስጥ አንድ ጊዜ ብቻ እየተመገቡ እኛ ሦስት ጊዜ እንድንበላ ግድ ይሉን ነበር። አሊያም ደግሞ ያላቸውን አንድ አልጋ ለእኛ ለቀው እነሱ መሬት ላይ ይተኙ ነበር። ባለቤቴ “እነዚህ ውድ ወንድሞችና እህቶች፣ ለመኖር የሚያስፈልጉን ነገሮች በጣም ጥቂት እንደሆኑ እንድገነዘብ ያደርጉኛል” በማለት ሁልጊዜ ትናገራለች።

“ወደኋላ ማለት አንፈልግም”

በ1960 ሌላ ጥሩ ነገር አገኘን፤ በጉዋያኪል ቅርንጫፍ ቢሮ እንድናገለግል ተጋበዝን። እኔ በቢሮ ውስጥ ስሠራ ኢደት ደግሞ በቅርንጫፍ ቢሮው አቅራቢያ በሚገኝ ጉባኤ ውስጥ በስብከቱ ሥራ ትካፈል ነበር። የቢሮ ሰው እሆናለሁ ብዬ ፈጽሞ አስቤ ስለማላውቅ ለሥራው ብቁ እንዳልሆንኩ ተሰምቶኝ ነበር፤ ሆኖም በዕብራውያን 13:21 ላይ እንደተገለጸው አምላክ ‘ፈቃዱን እንድናደርግ በመልካም ነገር ሁሉ ያስታጥቀናል።’ ከሁለት ዓመት በኋላ በብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው ቤቴል ውስጥ በሚሰጥ የአሥር ወር የጊልያድ ሥልጠና ላይ እንድገኝ ተጋበዝኩ። በዚያን ጊዜ ሚስቶች፣ በተመደቡበት ቦታ እንዲቆዩ ይጠበቅባቸው ነበር። ከብሩክሊን ለባለቤቴ ደብዳቤ ተላከላት። ደብዳቤው ከባለቤቷ ተለይታ ለአሥር ወራት ለመቆየት ፈቃደኛ መሆን አለመሆኗን በደንብ አስባበት እንድትገልጽ የሚጠይቅ ነበር።

ኢደትም በምላሹ እንዲህ ስትል ጻፈች፦ “ይህ ለእኔ ቀላል እንደማይሆንልኝ ምንም ጥያቄ የለውም፤ ይሁንና ምንም ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ቢያጋጥመን ይሖዋ ያለምንም ጥርጥር እንደሚረዳን እናውቃለን። . . . ከፊታችን የሚዘረጋልንን ማንኛውንም መብት ከመቀበል ወይም ኃላፊነታችንን በተሻለ ሁኔታ ለመወጣት የሚያስታጥቀንን ማንኛውንም አጋጣሚ ከመጠቀም ወደኋላ ማለት አንፈልግም።” ብሩክሊን በነበርኩባቸው ጊዜያት ሁሉ ባለቤቴ በየሳምንቱ ደብዳቤ ትጽፍልኝ ነበር።

ታማኝ ከሆኑ የእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ማገልገል

በ1966 እኔና ኢደት በሕመም ምክንያት እንደገና ወደ ሚስዮናዊነት አገልግሎት በመመለስ ኪቶ ከሚገኙ ወንድሞችና እህቶች ጋር ማገልገል ጀመርን። እነዚህ ወንድሞች በታማኝነት ረገድ እንዴት ያሉ ግሩም ምሳሌዎች ናቸው!

አንዲት ታማኝ እህት የማያምን ባል ያላት ሲሆን ብዙ ጊዜ ይደበድባት ነበር። አንድ ቀን ከንጋቱ አሥራ ሁለት ሰዓት ላይ አንድ ሰው ስልክ ደውሎ የዚህች እህት ባል እንደደበደባት ነገረን። በፍጥነት ወደ እህት ቤት ሄድኩ። እህትን ሳያት ዓይኔን ማመን አቃተኝ። አልጋ ላይ ተኝታ የነበረ ሲሆን ሰውነቷ አባብጦና በልዞ ነበር። ባለቤቷ የመጥረጊያው እንጨት ለሁለት እስኪሰበር ድረስ ደብድቧት ነበር። የዚያኑ ዕለት ወደ በኋላ ላይ ባለቤቷን ቤት ሳገኘው ያደረገው ነገር የፈሪ ሥራ እንደሆነ ነገርኩት። ሰውየው ደጋግሞ ይቅርታ ጠየቀ።

በ1970ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ጤንነቴ ስለተሻሻለ እንደገና በወረዳ ሥራ መካፈል ጀመርን። ኢባራ የተባለችው ከተማ በእኛ ወረዳ ሥር ነበረች። በ1950ዎቹ መገባደጃ ላይ ይህችን ከተማ ስንጎበኝ በዚያ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች አንድ ሚስዮናዊና አንድ የአካባቢው ወንድም ብቻ ነበሩ። በመሆኑም ከዚያ ወዲህ ወደ ጉባኤው የመጡትን በርካታ አዳዲስ ሰዎች ለመተዋወቅ ጓጉተን ነበር።

በዚያ ጉባኤ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በተገኘንበት ስብሰባ ላይ ወንድም ሮድሪጎ ቫካ ከመድረክ ሆኖ አድማጮችን የሚያሳትፍ ክፍል ያቀርብ ነበር። ወንድም ቫካ ጥያቄ ሲጠይቅ አድማጮቹ እጃቸውን በማውጣት ፋንታ “ዮ፣ ዮ!” (“እኔ፣ እኔ!”) ይላሉ። እኔና ኢደት በመገረም ተያየን። ‘እንዴ፣ ምን እያደረጉ ነው?’ ብዬ አሰብኩ። በኋላ ላይ ግን ወንድም ቫካ ማየት የተሳነው እንደሆነና የጉባኤውን አባላት የሚለያቸው በድምፃቸው መሆኑን አወቅን። በእውነትም በጎቹን በደንብ የሚያውቅ እረኛ ነው! ይህ ሁኔታ ኢየሱስ፣ እርስ በርሳቸው በደንብ ስለሚተዋወቁት ስለ ጥሩው እረኛና ስለ በጎቹ የተናገረውን በ⁠ዮሐንስ 10:3, 4, 14 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ እንዳስታውስ አደረገኝ። በአሁኑ ጊዜ በኢባራ ስድስት የስፓንኛ ጉባኤዎች፣ አንድ በኬችዋ ቋንቋ የሚመራ ጉባኤና አንድ የምልክት ቋንቋ ጉባኤ ይገኛሉ። ወንድም ቫካ አሁንም ሽማግሌና ልዩ አቅኚ ሆኖ በታማኝነት እያገለገለ ነው። *

ይሖዋ ላሳየን ጥሩነት አመስጋኝ ነን

በ1974 የይሖዋ ጥሩነት መግለጫ የሆነ ሌላ ግብዣ ቀረበልን፤ በቤቴል እንድናገለግል የተጋበዝን ሲሆን በዚህ ጊዜም የቢሮ ሥራ እንድሠራ ተመደብኩ። ከጊዜ በኋላ ደግሞ የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል እንድሆን ተሾምኩ። ኢደት መጀመሪያ ላይ የተመደበችው ኩሽና ሲሆን በኋላ ላይ ቢሮ ውስጥ መሥራት ጀመረች፤ አሁንም ድረስ በዚህ ቦታ ደብዳቤዎችን በመቀበልና በመላክ ታገለግላለች።

ባለፉት ዓመታት በጊልያድ የሠለጠኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሚስዮናውያን እኛ ወዳለንበት አገር ተመድበው በመምጣታቸው ተደስተናል፤ እነዚህ ሚስዮናውያን በሚያገለግሉባቸው ጉባኤዎች ውስጥ ወንድሞች ወደ መንፈሳዊ ጉልምስና እንዲደርሱና ቅንዓት እንዲኖራቸው ረድተዋል። ከዚህም በላይ ከ30 ከሚበልጡ አገሮች የተውጣጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ወንድሞችና እህቶች በዚህች አገር ለማገልገል መምጣታቸው አበረታትቶናል። የሚያሳዩት የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ ምንኛ የሚያስደንቅ ነው! አንዳንዶች የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት አካባቢ ለማገልገል ሲሉ ቤታቸውንና ንግዳቸውን ሸጠው ወደዚህ መጥተዋል። ራቅ ባሉ አካባቢዎች ለመስበክ መኪና ገዝተዋል፣ አዳዲስ ጉባኤዎችን አቋቁመዋል እንዲሁም የመንግሥት አዳራሾችን በመገንባቱ ሥራ እገዛ አበርክተዋል። በርካታ ነጠላ እህቶች በኢኳዶር በአቅኚነት ለማገልገል ሲሉ ከሌላ አገር መጥተዋል፤ እነዚህ እህቶች እንዴት ያሉ ቀናተኛና ታታሪ ሠራተኞች ናቸው!

በእርግጥም አምላክን ባገለገልኩባቸው ዓመታት ውስጥ ብዙ ጥሩ ነገሮችን አግኝቻለሁ። ከእነዚህ መካከል ትልቁን ቦታ የሚይዘው ከይሖዋ ጋር የመሠረትኩት ዝምድና ነው። በተጨማሪም ይሖዋ “ረዳት” ስለሰጠኝ አመስጋኝ ነኝ። (ዘፍ. 2:18) በትዳር ያሳለፍናቸውን 69 ዓመታት መለስ ብዬ ሳስብ በ⁠ምሳሌ 18:22 ላይ ያለውን “ሚስት የሚያገኝ መልካም ነገርን ያገኛል” የሚለውን ጥቅስ አስታውሳለሁ። ኢደትን የመሰለ አጋር በማግኘቴ ደስተኛ ነኝ። በብዙ መንገዶች ረድታኛለች። ከዚህም ሌላ እናቷን የምትወድ ልጅ መሆኗን አሳይታለች። ባለቤቴ ኢኳዶር ከደረስንበት ጊዜ አንስቶ እናቷ በ1990 በ97 ዓመታቸው እስከሞቱበት ጊዜ ድረስ በየሳምንቱ ደብዳቤ ትጽፍላቸው ነበር።

በአሁኑ ጊዜ እኔ 90 ዓመቴ ሲሆን ኢደት ደግሞ 89 ዓመቷ ነው። ወደ 70 የሚሆኑ ሰዎች ይሖዋን እንዲያውቁ በመርዳታችን ከፍተኛ ደስታ ይሰማናል። ከ60 ዓመት በፊት የጊልያድ ትምህርት ቤት ማመልከቻ ቅጽ በመሙላታችን በጣም ደስተኞች ነን። በዚያን ወቅት ያደረግነው ውሳኔ በሕይወታችን ውስጥ ብዙ ጥሩ ነገሮች ለማግኘት አስችሎናል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.29 የወንድም ቫካ የሕይወት ታሪክ በመስከረም 8, 1985 ንቁ! (እንግሊዝኛ) መጽሔት ላይ ይገኛል።

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጊልያድ ትምህርት ቤት አንድ ክፍል ውስጥ ከነበርን ሚስዮናውያን ጋር በኒው ዮርክ ያንኪ ስታዲየም፣ በ1958

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በወረዳ ሥራ ላይ እያለን የይሖዋ ምሥክር የሆነን አንድ ቤተሰብ ስንጎበኝ፣ በ1959

[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በኢኳዶር ቅርንጫፍ ቢሮ፣ በ2002