በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ እንደሚመራን የሚያሳየውን ማስረጃ ታስተውላለህ?

አምላክ እንደሚመራን የሚያሳየውን ማስረጃ ታስተውላለህ?

አምላክ እንደሚመራን የሚያሳየውን ማስረጃ ታስተውላለህ?

እስራኤላውያንም ሆኑ ግብፃውያን እንዲህ ያለ ነገር ከዚህ ቀደም ጨርሶ አይተው አያውቁም። እስራኤላውያን ከግብፅ ወጥተው ሲጓዙ የደመና ዓምድ በፊታቸው ይሄድ ነበር፤ በሌሊት ደግሞ ብርሃን የሚሰጣቸው የእሳት ዓምድ ይታያቸው ነበር። ይህ ዓምድ በቀንም ሆነ በሌሊት ተለይቷቸው አያውቅም። ምንኛ የሚያስደንቅ ነገር ነው! ሆኖም ይህ ዓምድ የመጣው ከየት ነው? ዓላማውስ ምንድን ነው? ይህ ሁኔታ ከተፈጸመ ወደ 3,500 የሚጠጉ ዓመታት ቢያልፉም እስራኤላውያን ለዚህ ‘የእሳትና የደመና ዓምድ’ ከነበራቸው አመለካከት በዛሬው ጊዜ ምን ትምህርት እናገኛለን?—ዘፀ. 14:24

የአምላክ ቃል የዓምዱ ምንጭ ማን እንደሆነ እንዲሁም ምን ዓላማ እንደነበረው ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “በቀንም ሆነ በሌሊት መጓዝ ይችሉ ዘንድ፣ እግዚአብሔር በቀን በመንገዳቸው ሊመራቸው በደመና ዓምድ፣ በሌሊት ደግሞ ብርሃን ሊሰጣቸው በእሳት ዓምድ በፊታቸው ይሄድ ነበር።” (ዘፀ. 13:21, 22) ይሖዋ አምላክ ሕዝቡ ከግብፅ ወጥተው በምድረ በዳ ሲጓዙ በእሳትና በደመና ዓምድ ተጠቅሞ መርቷቸዋል። ሕዝቡ ይህን ዓምድ መከተል እንዲችሉ ለጉዞ ዝግጁ መሆን ነበረባቸው። ይከተሏቸው የነበሩት የግብፅ ወታደሮች በአምላክ ሕዝብ ላይ ጥቃት ሊሰነዝሩ ሲሉ ዓምዱ በግብፃውያንና በእስራኤላውያን መካከል በመቆም ለእስራኤላውያን ጥበቃ አድርጎላቸዋል። (ዘፀ. 14:19, 20) ዓምዱ የመራቸው በቀጥተኛው መንገድ ባይሆንም እንኳ እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት የሚያስችላቸው ብቸኛው አማራጭ የዓምዱን አመራር መከተል ነበር።

የአምላክ ሕዝብ ዓምዱን ሲያዩ ይሖዋ ከእነሱ ጋር እንዳለ እርግጠኞች ይሆኑ ነበር። ይህ ዓምድ ይሖዋን የሚወክል ሲሆን አንዳንድ ጊዜም ይሖዋ በደመና ዓምድ ሆኖ ሕዝቡን ያነጋግራቸው ነበር። (ዘኍ. 14:14፤ መዝ. 99:7) ከዚህም ባሻገር ብሔሩን ለመምራት ይሖዋ የሾመው ሙሴን መሆኑን ደመናው ይጠቁም ነበር። (ዘፀ. 33:9) በተመሳሳይም ኢያሱ የሙሴ ተተኪ እንዲሆን በይሖዋ መሾሙን ደመናው ለመጨረሻ ጊዜ በታየበት ወቅት አረጋግጧል። (ዘዳ. 31:14, 15) በእርግጥም እስራኤላውያን ከግብፅ ወጥተው ያደረጉት ጉዞ መሳካት የተመካው አምላክ እንደሚመራቸው የሚጠቁመውን ማስረጃ በማስተዋላቸውና አመራሩን በመከተላቸው ላይ ነበር።

ማስረጃውን አላስተዋሉትም

እስራኤላውያን ለመጀመሪያ ጊዜ ዓምዱን ሲመለከቱ በጣም ተደንቀው መሆን አለበት። የሚያሳዝነው ግን እስራኤላውያን በየዕለቱ ይህንን ተአምር መመልከታቸው አድናቆት እንዲያድርባቸውና ምንጊዜም በይሖዋ እንዲተማመኑ አላደረጋቸውም። በአምላክ አመራር ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው በተደጋጋሚ ጊዜያት አሳይተዋል። የግብፃውያን ሠራዊት ባሳደዳቸው ወቅት በይሖዋ የማዳን ኃይል አልታመኑም። ከዚህ ይልቅ የአምላክ አገልጋይ የነበረው ሙሴ ከሞት ጋር እንዲፋጠጡ የሚያደርግ ሁኔታ ውስጥ እንዳስገባቸው በመግለጽ ወቀሱት። (ዘፀ. 14:10-12) ቀይ ባሕርን ከተሻገሩ በኋላ ደግሞ ምግብና ውኃ አጣን ብለው በሙሴ፣ በአሮንና በይሖዋ ላይ አጉረመረሙ። (ዘፀ. 15:22-24፤ 16:1-3፤ 17:1-3, 7) ይህ ከሆነ ከጥቂት ሳምንታት በኋላም አሮን የወርቅ ጥጃ እንዲሠራላቸው ጫና አሳደሩበት። እስቲ አስበው! በእስራኤላውያን ሰፈር ውስጥ ሕዝቡን ከግብፅ ያወጣቸው አምላክ አብሯቸው መሆኑን የሚያሳየው አስደናቂ ማስረጃ ይኸውም የእሳቱና የደመናው ዓምድ ይታይ የነበረ ቢሆንም ከዚያ ብዙም ሳይርቅ እስራኤላውያን በድን የሆነ ጣዖት በመሥራት “እስራኤል ሆይ፤ ከግብፅ ያወጡህ አማልክት እነዚህ ናቸው” እያሉ ይህን ጣዖት ማምለክ ጀመሩ። ይህ እንዴት ያለ “አስጸያፊ የስድብ ቃል” ወይም የንቀት ተግባር ነው!—ዘፀ. 32:4፤ ነህ. 9:18

እስራኤላውያን በአምላክ ላይ በማመፅ የፈጸሙት ድርጊት ለይሖዋ አመራር ከፍተኛ ንቀት እንዳላቸው የሚያሳይ ነበር። ችግሩ የደመናውን ዓምድ ማየት አለመቻላቸው ሳይሆን ይሖዋ እንዴት እንደሚመራቸው አለማስተዋላቸውና አመራሩን አለመከተላቸው ነበር። ዓምዱን ቢመለከቱትም የይሖዋን አመራር እንደሚያመለክት ግን ዘነጉት። ድርጊታቸው ‘የእስራኤልን ቅዱስ አስቆጥቶታል’፤ ያም ሆኖ ይሖዋ ለእስራኤላውያን ምሕረት በማድረግ ወደ ተስፋይቱ ምድር እስኪገቡ ድረስ በዓምዱ አማካኝነት እነሱን መምራቱን ቀጥሎ ነበር።—መዝ. 78:40-42, 52-54፤ ነህ. 9:19

በዛሬው ጊዜ አምላክ እንደሚመራን የሚጠቁመውን ማስረጃ አስተውሉ

በዘመናችንም ይሖዋ ለሕዝቡ ግልጽ መመሪያዎች ያልሰጠበት ጊዜ የለም። እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር የሚጓዙበትን መንገድ ራሳቸው እንዲያገኙ እንዳልተዋቸው ሁሉ እኛም በዛሬው ጊዜ ወደ አዲሱ ዓለም የሚመራውን ጎዳና በራሳችን እንድንፈልግ አልተወንም። ኢየሱስ ክርስቶስ ጉባኤውን እንዲመራ ተሹሟል። (ማቴ. 23:10፤ ኤፌ. 5:23) እሱም በመንፈስ የተቀቡ ታማኝ ክርስቲያኖችን ላቀፈው ቡድን ይኸውም ለታማኙ ባሪያ የተወሰነ ኃላፊነት ሰጥቶታል። ይህ ታማኝ ባሪያ ደግሞ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የበላይ ተመልካቾችን ይሾማል።—ማቴ. 24:45-47፤ ቲቶ 1:5-9

ታማኙ ባሪያ ወይም መጋቢ ማን እንደሆነ በእርግጠኝነት ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ ስለዚህ ባሪያ ሲገልጽ ምን እንዳለ ልብ በል፦ “ጌታው የሚያስፈልጋቸውን በቂ ምግብ በተገቢው ጊዜ እንዲሰጣቸው በአገልጋዮቹ ላይ የሾመው ታማኝና ልባም መጋቢ በእርግጥ ማን ነው? ጌታው ተመልሶ በሚመጣበት ጊዜ እንዲህ ሲያደርግ ካገኘው ያ ባሪያ ደስተኛ ነው!”—ሉቃስ 12:42, 43

ከዚህ ማየት እንደምንችለው ይህ መጋቢ “ታማኝ” ነው፤ ይኸውም ይሖዋን፣ ኢየሱስን፣ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ወይም የአምላክን ሕዝቦች ፈጽሞ አይክድም ወይም አይተውም። በተጨማሪም መጋቢው “ልባም” ስለሆነ ከምንም በላይ አስፈላጊ የሆነውን ‘የመንግሥቱን ምሥራች’ የመስበኩንና “ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን . . . ደቀ መዛሙርት” የማድረጉን ሥራ ማስተዋል በሚንጸባረቅበት መንገድ ይመራዋል። (ማቴ. 24:14፤ 28:19, 20) መጋቢው ታዛዥ በመሆን ጠቃሚና ገንቢ የሆነ መንፈሳዊ ምግብ “በተገቢው ጊዜ” ያቀርባል። ይሖዋ ሕዝቦቹ በቁጥር እየጨመሩ እንዲሄዱ በማድረግ፣ አስፈላጊ የሆኑ ውሳኔዎች በሚያደርጉበት ጊዜ መመሪያ በመስጠት፣ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ይበልጥ መገንዘብ እንዲችሉ በመርዳት፣ ጠላቶቻቸው እንዳያጠፏቸው ጥበቃ በማድረግ እንዲሁም የአእምሮና የልብ ሰላም እንዲያገኙ በመርዳት ይህንን ባሪያ እንደሚደግፈው አሳይቷል።—ኢሳ. 54:17፤ ፊልጵ. 4:7

የአምላክን መመሪያ ተከተሉ

የአምላክን አመራር እንደምናደንቅ እንዴት ማሳየት እንችላለን? ሐዋርያው ጳውሎስ “በመካከላችሁ ግንባር ቀደም ሆነው አመራር ለሚሰጧችሁ ታዘዙ እንዲሁም ተገዙ” ብሏል። (ዕብ. 13:17) እንዲህ ማድረግ ሁልጊዜ ቀላል ላይሆን ይችላል። ነጥቡን በምሳሌ ለማስረዳት፣ ራስህን በሙሴ ዘመን በነበረ አንድ እስራኤላዊ ቦታ ለማስቀመጥ ሞክር። ለተወሰነ ጊዜ ስትጓዙ ከቆያችሁ በኋላ ዓምዱ ቆመ እንበል። ዓምዱ በዚህ ቦታ ላይ ምን ያህል ጊዜ ይቆይ ይሆን? ለአንድ ቀን? ለአንድ ሳምንት? ወይስ ለበርካታ ወራት? ‘ጓዜን በሙሉ መፍታት ይኖርብኝ ይሆን?’ ብለህ ታስብ ይሆናል። መጀመሪያ ላይ በጣም የሚያስፈልጉህን ነገሮች ብቻ ታወጣ ይሆናል። ከጥቂት ቀናት በኋላ ግን የምትፈልገውን ነገር ለማግኘት ስትል ተሸክፎ የተቀመጠውን ዕቃህን መበርበር ያታክትህና ዕቃህን በሙሉ ማውጣት ትጀምራለህ። ይሁንና ዕቃህን አወጣጥተህ ልትጨርስ ስትል ዓምዱ ሲንቀሳቀስ ትመለከታለህ፤ በመሆኑም ጓዝህን እንደገና መሸከፍ ይኖርብሃል! ይህን ማድረግ ቀላል እንደማይሆን የታወቀ ነው። እንደዚያም ሆኖ እስራኤላውያኑ “ወዲያውኑ ተነስተው [መጓዝ]” ነበረባቸው።—ዘኍ. 9:17-22

ታዲያ እኛስ መለኮታዊ መመሪያ ሲሰጠን ምላሻችን ምንድን ነው? መመሪያውን “ወዲያውኑ” ተግባራዊ ለማድረግ እንጥራለን? ወይስ ነገሮችን በለመድነው መንገድ መሥራታችንን እንቀጥላለን? የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ስለ ማስጠናት፣ የውጭ አገር ቋንቋ ለሚናገሩ ሰዎች ስለ መስበክ፣ አዘውትሮ የቤተሰብ አምልኮ ስለ ማድረግ፣ ከሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴዎች ጋር ስለ መተባበር እንዲሁም በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ተገቢ ምግባር ስለ ማሳየትና ስለመሳሰሉት ጉዳዮች በቅርብ የተሰጡንን መመሪያዎች በሚገባ ተረድተናቸዋል? የአምላክን መመሪያ እንደምናደንቅ ማሳየት የምንችልበት ሌላው መንገድ ደግሞ ምክር መቀበል ነው። ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ውሳኔዎች በምናደርግበት ጊዜ በራሳችን ጥበብ ከመታመን ይልቅ መመሪያ ለማግኘት ወደ ይሖዋና ወደ ድርጅቱ ዘወር እንላለን። አንድ ልጅ አውሎ ነፋስ የቀላቀለ ኃይለኛ ዝናብ በሚጥልበት ጊዜ ወደ ወላጆቹ እንደሚጠጋ ሁሉ እኛም በዚህ ዓለም ላይ ያሉት ችግሮች እንደ ኃይለኛ ወጀብ በሚዥጎደጎዱብን ጊዜ ጥበቃ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ድርጅት እንጠጋለን።

እርግጥ ነው፣ በአምላክ ድርጅት ምድራዊ ክፍል ውስጥ በኃላፊነት የሚሠሩት ሰዎች ፍጹማን አይደሉም፤ ሙሴም ቢሆን ፍጹም አልነበረም። እንደዚያም ሆኖ ሙሴ በአምላክ እንደተሾመና የአምላክ ድጋፍ እንዳልተለየው ዓምዱ ማስረጃ ነበር። በተጨማሪም ማንኛውም እስራኤላዊ ጉዞ የሚጀመረው መቼ እንደሆነ የመወሰን መብት እንዳልነበረው ልብ በል። ከዚህ ይልቅ ሕዝቡ “በሙሴ አማካይነት የተሰጠውን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ይጠብቁ ነበር።” (ዘኍ. 9:23) በመሆኑም አምላክ መመሪያ ለማስተላለፍ የሚጠቀምበት ሙሴ፣ ሕዝቡ ለጉዞ እንዲንቀሳቀስ ምልክት ሳይሰጥ አይቀርም።

በዛሬው ጊዜም የይሖዋ መጋቢ፣ አንድ እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ግልጽ ምልክት ይሰጣል። መጋቢው ይህን የሚያደርገው እንዴት ነው? በመጠበቂያ ግንብ እና በመንግሥት አገልግሎታችን ላይ በሚወጡት ትምህርቶች እንዲሁም በአዳዲስ ጽሑፎችና በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ በሚቀርቡት ንግግሮች አማካኝነት ነው። ከዚህም በተጨማሪ በተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ወይም በደብዳቤዎች አሊያም የጉባኤ ኃላፊነት ላላቸው ወንድሞች በሚሰጡ ሥልጠናዎች አማካኝነት ለጉባኤዎች መመሪያዎች ይተላለፋሉ።

አንተስ አምላክ እንደሚመራን የሚያሳየውን ማስረጃ በሚገባ ታስተውላለህ? ይሖዋ እንደ “ምድረ በዳ” በሆነው በዚህ ክፉ የሰይጣን ዓለም የመጨረሻ ቀኖች ውስጥ እኛን ለመምራት በድርጅቱ ይጠቀማል። ይህም አንድነትና ፍቅር እንዲሁም የደኅንነት ስሜት እንዲኖረን አስችሎናል።

እስራኤላውያን ተስፋይቱ ምድር ሲደርሱ ኢያሱ እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “አምላካችሁ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ መልካም ተስፋ ሁሉ አንዲቱን እንኳ እንዳላስቀረባችሁ፣ በፍጹም ልባችሁ በፍጹም ነፍሳችሁ ታውቃላችሁ፤ አንዱም ሳይቀር ሁሉም ተፈጽሞአል።” (ኢያሱ 23:14) በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ ያሉ የአምላክ ሕዝቦች ቃል ወደተገባላቸው አዲስ ዓለም እንደሚገቡ ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁንና እያንዳንዳችን ወደዚህ ዓለም መግባታችን በዋነኝነት የተመካው የአምላክን መመሪያዎች በትሕትና እና በፈቃደኝነት በመከተላችን ላይ ነው። እንግዲያው ሁላችንም ይሖዋ እንደሚመራን የሚያሳየውን ማስረጃ ምንጊዜም እናስተውል!

[በገጽ 5 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ድርጅት ይመራናል

በአውራጃ ስብሰባ ላይ በሚወጡ አዳዲስ ጽሑፎች

በቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶች

ለአገልግሎት በሚደረጉ ስብሰባዎች ላይ በምናገኘው ሥልጠና