በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በሕይወትህ ውስጥ ከሁሉ የላቀውን ቦታ የምትሰጠው ለማን ነው?

በሕይወትህ ውስጥ ከሁሉ የላቀውን ቦታ የምትሰጠው ለማን ነው?

በሕይወትህ ውስጥ ከሁሉ የላቀውን ቦታ የምትሰጠው ለማን ነው?

“አንተ ብቻ፣ በምድር ሁሉ ላይ ልዑል እንደ ሆንህ ይወቁ።”​—መዝ. 83:18

1, 2. ከመዳናችን ጋር በተያያዘ የይሖዋን ስም ማወቃችን ብቻ በቂ አይደለም የምንለው ለምንድን ነው?

የይሖዋን ስም⁠ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመለከትኸው የት ነው? ምናልባትም በ⁠ዘፀአት 6:3 ላይ ሊሆን ይችላል። ጥቅሱ በ1879 ትርጉም እንዲህ ይላል፦ “ሁሉን እንደሚችል አምላክ ተገለጥሁ በስሜም እግዚእ ይሖዋ አልታወቅሁላቸውም።” ከዚያ ጊዜ ወዲህ አንተም ሰዎች አፍቃሪ ስለሆነው አምላካችን ስለ ይሖዋ እንዲያውቁ ለመርዳት በዚህ ጥቅስ ተጠቅመህ ሊሆን እንደሚችል ጥርጥር የለውም።​—ሮም 10:12, 13

2 ሰዎች የይሖዋን ስም ማወቃቸው አስፈላጊ ቢሆንም ይህ ብቻ ግን በቂ አይደለም። መዝሙራዊው፣ ይሖዋ “በምድር ሁሉ ላይ ልዑል” ወይም ከሁሉ በላይ እንደሆነ በመግለጽ ለመዳን ወሳኝ ስለሆነ አንድ እውነታ ጎላ አድርጎ ገልጿል። (መዝ. 83:18) አዎን፣ በጽንፈ ዓለም ውስጥ ከሁሉ የላቀውን ቦታ የሚይዘው ይሖዋ ነው። ይሖዋ የሁሉ ነገር ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን ሁሉም ፍጡሮቹ ለእሱ ሙሉ በሙሉ እንዲገዙለት የመጠበቅ መብት አለው። (ራእይ 4:11) እንግዲያው ‘በሕይወቴ ውስጥ ከሁሉ የላቀውን ቦታ የምሰጠው ለማን ነው?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን የተገባ ነው። እያንዳንዳችን ለዚህ ጥያቄ የምንሰጠውን መልስ በጥንቃቄ መመርመራችን በጣም አስፈላጊ ነው።

በኤደን ገነት የተነሳው ጉዳይ

3, 4. ሰይጣን ሔዋንን ሊያታልላት የቻለው እንዴት ነው? ውጤቱስ ምን ሆነ?

3 ከላይ ያለው ጥያቄ ምን ያህል በቁም ነገር ሊታይ የሚገባው እንደሆነ በኤደን ገነት የተከናወነው ሁኔታ በግልጽ ያሳየናል። ከጊዜ በኋላ ሰይጣን ዲያብሎስ ተብሎ የተጠራው ዓመፀኛ መልአክ የመጀመሪያዋን ሴት ሔዋንን፣ ከዛፉ ፍሬ እንዳይበሉ ይሖዋ የሰጣቸውን ትእዛዝ ከማክበር ይልቅ የራሷን ፍላጎት እንድታስቀድም አግባባት። (ዘፍ. 2:17፤ 2 ቆሮ. 11:3) ሔዋን በዚህ ማታለያ የወደቀች ሲሆን ይህም ለይሖዋ ሉዓላዊነት አክብሮት እንደሌላት የሚያመለክት ነበር። ሔዋን በሕይወቷ ውስጥ ከሁሉ የላቀውን ቦታ የምትሰጠው ለይሖዋ መሆኑን አላሳየችም። ይሁንና ሰይጣን ሔዋንን ሊያታልላት የቻለው እንዴት ነው?

4 ሰይጣን ሔዋንን ካናገረበት መንገድ መመልከት እንደሚቻለው እሷን ለማታለል ተንኮል ያዘሉ የተለያዩ ዘዴዎችን ተጠቅሟል። (ዘፍጥረት 3:1-5ን አንብብ።) በመጀመሪያ ደረጃ፣ ሰይጣን ስለ ፈጣሪ ሲናገር ይሖዋ በሚለው የግል ስሙ ከመጥራት ይልቅ አምላክ (ኤሎሂም) በሚለው መጠሪያ ተጠቅሟል። ከዚህ በተቃራኒ የዘፍጥረት መጽሐፍ ጸሐፊ በዚህ ምዕራፍ የመጀመሪያ ቁጥር ላይ የይሖዋን የግል ስም ተጠቅሟል። * በሁለተኛ ደረጃ፣ ሰይጣን ሔዋንን ስለተከለከለው ዛፍ ሲጠይቃት አምላክ ‘አዟልን?’ በማለት ፋንታ ‘ብሏልን?’ የሚል አባባል ተጠቅሟል። (ዘፍ. 2:16) ሰይጣን እንዲህ ያለ የተንኮል አነጋገር የተጠቀመው ሔዋን የአምላክን ትእዛዝ አቅልላ እንድትመለከት ለማድረግ ሊሆን ይችላል። በሦስተኛ ደረጃ፣ የሚያነጋግረው ሔዋንን ብቻ ሆኖ ሳለ ‘እንዳትበሉ ብሏልን?’ ብሎ በመጠየቅ በብዙ ቁጥር ተጠቅሟል። ይህን ሲል ስለ ራሷም ሆነ ስለ ባሏ መልስ መስጠት እንደምትችልና ትልቅ ቦታ የሚሰጣት እንደሆነች እንዲሰማት በማድረግ ራሷን ከፍ አድርጋ እንድትመለከት ለማነሳሳት መሞከሩ ሊሆን ይችላል። ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? ሔዋን ራሷንም ሆነ ባሏን ወክላ መናገር እንደምትችል ስለተሰማት ሳይሆን አይቀርም፣ ያለ ቦታዋ በመግባት ለእባቡ “በአትክልቱ ስፍራ ካሉት ዛፎች ፍሬ መብላት እንችላለን” በማለት መልስ ሰጠች።

5. (ሀ) ሰይጣን፣ ሔዋን ትኩረቷ በምን ላይ እንዲያርፍ አደረገ? (ለ) ሔዋን ከተከለከለው ፍሬ መብላቷ ምን ያሳያል?

5 በተጨማሪም ሰይጣን እውነታውን ያቀረበው በተዛባ መንገድ ነበር። “እግዚአብሔር፣ ‘በአትክልቱ ስፍራ ካሉ ዛፎች ከማናቸውም እንዳትበሉ’ ብሎአልን?” በማለት አምላክ ለአዳምና ለሔዋን ምክንያታዊ ያልሆነ ትእዛዝ እንደሰጣቸው የሚያስመስል ጥያቄ አቅርቧል። ቀጥሎም ሰይጣን፣ ሔዋን ስላለችበት ሁኔታና “እንደ እግዚአብሔር” በመሆን ያለችበትን ሁኔታ ማሻሻል ስለምትችልበት መንገድ እንድታስብ አደረጋት። ያሰበውም አልቀረ ሔዋን ሁሉን ነገር ከሰጣት አምላክ ጋር ስላላት ግንኙነት ከማሰብ ይልቅ ትኩረቷን በዛፉና በፍሬው ላይ አደረገች። (ዘፍጥረት 3:6ን አንብብ።) የሚያሳዝነው ሔዋን ፍሬውን የበላች ሲሆን ይህን በማድረጓም በሕይወቷ ውስጥ ከሁሉ የላቀውን ቦታ የምትሰጠው ለይሖዋ እንዳልሆነ አሳይታለች።

በኢዮብ ዘመን የተነሳው ጉዳይ

6. ሰይጣን በኢዮብ ንጹሕ አቋም ጠባቂነት ላይ ጥያቄ ያስነሳው እንዴት ነው? ኢዮብ ምን ለማድረግ የሚያስችል አጋጣሚ ተሰጠው?

6 ከላይ የተጠቀሰው ሁኔታ ከተከናወነ ከበርካታ ዘመናት በኋላ ኢዮብ የተባለው ታማኝ ሰው በሕይወቱ ውስጥ ከሁሉ የላቀውን ቦታ የሚሰጠው ለማን እንደሆነ ለማሳየት የሚያስችል አጋጣሚ አግኝቶ ነበር። ኢዮብ ንጹሕ አቋሙን በመጠበቅ ረገድ በዘመኑ ከነበሩት ሰዎች ሁሉ የላቀ መሆኑን ይሖዋ በተናገረበት ወቅት ሰይጣን “ኢዮብ እግዚአብሔርን የሚፈራው እንዲሁ ነውን?” በማለት በሐሳቡ አለመስማማቱን ገልጿል። (ኢዮብ 1:7-10ን አንብብ።) ሰይጣን፣ ኢዮብ ለአምላክ ታዛዥ መሆኑን አልካደም፤ ከዚህ ይልቅ ጥያቄ ያስነሳው ለአምላክ ለመታዘዝ በተነሳሳበት ዓላማ ላይ ነበር። ኢዮብ ይሖዋን የሚያገለግለው በፍቅር ተነሳስቶ ሳይሆን የራሱን ጥቅም ፍለጋ እንደሆነ በመግለጽ የሐሰት ክስ ሰነዘረበት። ለዚህ ክስ መልስ መስጠት የሚችለው ኢዮብ ብቻ በመሆኑ ይህን ለማድረግ የሚያስችል አጋጣሚ ተሰጠው።

7, 8. ኢዮብ ምን ዓይነት መከራዎች አጋጥመውታል? በታማኝነት በመጽናቱ ምን አሳይቷል?

7 ሰይጣን በኢዮብ ላይ ተደራራቢ መከራዎችን እንዲያመጣበት ይሖዋ ፈቀደ። (ኢዮብ 1:12-19) ኢዮብ ሰይጣን ባመጣበት መከራ የተነሳ ሰማይ ምድሩ ሲገለባበጥበት ምን አደረገ? መጽሐፍ ቅዱስ “ኢዮብ አልበደለም፤ በእግዚአብሔርም ላይ ክፉ አልተናገረም” በማለት መልሱን ይሰጠናል። (ኢዮብ 1:22) ሰይጣን ግን መሸነፉን አምኖ አልተቀበለም። “‘ቍርበት ስለ ቍርበት ነው’ እንዲሉ ሰው ለሕይወቱ ሲል ያለውን ሁሉ ይሰጣል” * የሚል ሌላ ተቃውሞ አሰማ። (ኢዮብ 2:4) ኢዮብ በአካሉ ላይ መከራ ቢደርስበት በሕይወቱ ውስጥ ከሁሉ የላቀውን ቦታ ለይሖዋ መስጠቱን እንደሚተው ሰይጣን ተናገረ።

8 ኢዮብ በአሰቃቂ ቁስል ሰውነቱ መበላሸቱ ሳያንስ ሚስቱ አምላክን ሰድቦ እንዲሞት ጫና ታደርግበት ነበር። ቆየት ብሎም ሦስት የሐሰት አጽናኞች የፈጸመው መጥፎ ነገር እንዳለ በመግለጽ ወነጀሉት። (ኢዮብ 2:11-13፤ 8:2-6፤ 22:2, 3) ይሁንና ኢዮብ ይህ ሁሉ መከራ ቢደርስበትም ንጹሕ አቋሙን አላጎደፈም። (ኢዮብ 2:9, 10ን አንብብ።) ኢዮብ በታማኝነት በመጽናት በሕይወቱ ውስጥ ከሁሉ የላቀውን ቦታ የሚይዘው ይሖዋ እንደሆነ አሳይቷል። ከዚህም በተጨማሪ ኢዮብ፣ ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች ለዲያብሎስ የሐሰት ክሶች በተወሰነ መጠንም እንኳ ቢሆን መልስ መስጠት እንደሚችሉ አሳይቷል።​—ከ⁠ምሳሌ 27:11 ጋር አወዳድር።

ኢየሱስ የሰጠው የማያዳግም መልስ

9. (ሀ) ሰይጣን ኢየሱስን በሥጋዊ ፍላጎቱ ተጠቅሞ ሊፈትነው የሞከረው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ ምን አደረገ?

9 ኢየሱስ ከተጠመቀ ብዙም ሳይቆይ ሰይጣን ፈተና ያቀረበለት ሲሆን በሕይወቱ ውስጥ ከሁሉ የላቀውን ቦታ ለይሖዋ ከመስጠት ይልቅ የራሱን ፍላጎት እንዲያስቀድም ሊያግባባው ሞክሮ ነበር። ዲያብሎስ ለኢየሱስ ሦስት ፈተናዎችን አቀረበለት። መጀመሪያ ላይ ድንጋዩን ወደ ዳቦ እንዲቀይር በመጠየቅ በሥጋዊ ፍላጎቱ ተጠቅሞ ሊፈትነው ሞከረ። (ማቴ. 4:2, 3) ኢየሱስ ለ40 ቀናት ጾሞ ስለነበር በጣም ተርቦ ሊሆን እንደሚችል ግልጽ ነው። በመሆኑም ዲያብሎስ ረሃቡን ለማስታገስ ተአምር የመፈጸም ኃይሉን አግባብ ባልሆነ መንገድ እንዲጠቀምበት ገፋፋው። ታዲያ ኢየሱስ ምን አደረገ? ከሔዋን በተለየ መንገድ ኢየሱስ ትኩረት ያደረገው በይሖዋ ቃል ላይ ከመሆኑም ሌላ ጥያቄውን ያለምንም ማቅማማት ውድቅ አድርጎታል።​—ማቴዎስ 4:4ን አንብብ።

10. ኢየሱስ ከቤተ መቅደሱ ግንብ አናት ላይ ራሱን እንዲወረውር ሰይጣን የተፈታተነው ለምንድን ነው?

10 ሰይጣን ኢየሱስን እልህ ውስጥ ለማስገባትና ራስ ወዳድነት የሚንጸባረቅበት እርምጃ እንዲወስድ ለማነሳሳትም ሞክሯል። ከቤተ መቅደሱ ግንብ አናት ላይ ራሱን እንዲወረውር ኢየሱስን ተፈታተነው። (ማቴ. 4:5, 6) ሰይጣን ዓላማው ምን ነበር? ኢየሱስ ራሱን ሲወረውር ምንም ጉዳት ካልደረሰበት “የአምላክ ልጅ” መሆኑ እንደሚረጋገጥ ሰይጣን ገለጸ። የዲያብሎስ ዓላማ ኢየሱስ ስለ ስሙ ከሚገባው በላይ እንዲጨነቅና ማንነቱን ለማሳየት እንዲነሳሳ ማድረግ እንደሆነ ግልጽ ነው። ኩራትና በሌሎች ፊት ላለመዋረድ መፈለግ አንድ ሰው አደገኛ ነገር እንዲፈጽም የሚቀርብለትን ፈተና እንኳ ለመቀበል እንዲነሳሳ ሊያደርጉት እንደሚችሉ ሰይጣን ያውቃል። ሰይጣን ጥቅሱን አለቦታው ቢጠቅሰውም ኢየሱስ የይሖዋን ቃል ሙሉ በሙሉ እንደሚረዳ አሳይቷል። (ማቴዎስ 4:7ን አንብብ።) ኢየሱስ ሰይጣን ባቀረበለት ፈተና ባለመሸነፍ በሕይወቱ ውስጥ ከሁሉ የላቀውን ቦታ የሚሰጠው ለይሖዋ መሆኑን በድጋሚ አሳይቷል።

11. ዲያብሎስ የዓለምን መንግሥታት በሙሉ እንደሚሰጠው ያቀረበለትን ግብዣ ኢየሱስ ያልተቀበለው ለምንድን ነው?

11 ሰይጣን ፈተናውን እያከበደ በመምጣት ኢየሱስን ለሦስተኛ ጊዜ ሲፈትነው የዓለምን መንግሥታት በሙሉ እንደሚሰጠው ቃል ገባለት። (ማቴ. 4:8, 9) ኢየሱስ የቀረበለትን ግብዣ እንደማይቀበል ወዲያውኑ ገለጸ። ኢየሱስ የሰይጣንን ግብዣ መቀበል የይሖዋን ሉዓላዊነት ይኸውም ከሁሉ በላይ የመሆን መብቱን ለመቀበል አሻፈረኝ ከማለት ተለይቶ እንደማይታይ ተገንዝቦ ነበር። (ማቴዎስ 4:10ን አንብብ።) ሰይጣን ላቀረበው ለእያንዳንዱ ፈተና ኢየሱስ መልስ የሰጠው የይሖዋን የግል ስም የያዘ ጥቅስ በመጥቀስ ነበር።

12. ኢየሱስ ምድራዊ ሕይወቱን ሊያገባድድ በተቃረበበት ወቅት ምን ከባድ ውሳኔ ተደቅኖበት ነበር? ይህን አስጨናቂ ሁኔታ ከተወጣበት መንገድ ምን ትምህርት እናገኛለን?

12 ኢየሱስ ምድራዊ ሕይወቱን ሊያገባድድ በተቃረበበት ወቅት በጣም ከባድ ውሳኔ ከፊቱ ተደቅኖበት ነበር። እርግጥ ነው፣ አገልግሎቱን ባከናወነባቸው ጊዜያት ሁሉ ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ ለማቅረብ ፈቃደኛ መሆኑን ገልጾ ነበር። (ማቴ. 20:17-19, 28፤ ሉቃስ 12:50፤ ዮሐ. 16:28) ያም ሆኖ ኢየሱስ በሐሰት እንደሚወነጀልና በአይሁድ የፍርድ ሥርዓት መሠረት እንደሚፈረድበት ከዚያም አምላክን እንደተሳደበ ተቆጥሮ እንደሚገደልም ተገንዝቦ ነበር። በዚህ መንገድ የሚገደል መሆኑ በጣም አስጨንቆታል። “አባቴ ሆይ፣ የሚቻል ከሆነ ይህ ጽዋ ከእኔ ይለፍ” ብሎ ጸለየ። ይሁንና አክሎ “እንደ እኔ ፈቃድ ሳይሆን እንደ አንተ ፈቃድ ይሁን” አለ። (ማቴ. 26:39) አዎን፣ ኢየሱስ እስከ ሞት ድረስ ታማኝነቱን መጠበቁ በሕይወቱ ውስጥ ከሁሉ የላቀውን ቦታ የሚሰጠው ለይሖዋ መሆኑን በማያሻማ መልኩ ያረጋግጣል።

ለጥያቄው የምንሰጠው መልስ

13. ከሔዋን፣ ከኢዮብና ከኢየሱስ ክርስቶስ ምን ትምህርት አግኝተናል?

13 እስከ አሁን ከተወያየንባቸው ነጥቦች ምን ትምህርት አግኝተናል? ከሔዋን ሁኔታ እንደተመለከትነው የራሳቸውን ፍላጎት የሚያስቀድሙ ወይም ራሳቸውን ከፍ አድርገው የሚመለከቱ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ ከሁሉ የላቀውን ቦታ ለይሖዋ እንደማይሰጡ ያሳያሉ። ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ ኢዮብ ንጹሕ አቋሙን በመጠበቅ የተከተለው ጎዳና፣ ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎችም ሳይቀሩ መከራዎች በሚደርሱባቸው ጊዜ መንስኤውን ሙሉ በሙሉ ባይረዱትም እንኳ በታማኝነት በመጽናት በሕይወታቸው ውስጥ አንደኛ ቦታ የሚሰጡት ለይሖዋ መሆኑን ማሳየት እንደሚችሉ ያስተምረናል። (ያዕ. 5:11) በመጨረሻም ኢየሱስ ከተወው ምሳሌ ውርደትን ለመቀበል ፈቃደኛ መሆን እንዳለብንና ለስማችን ከልክ በላይ መጨነቅ እንደሌለብን ተምረናል። (ዕብ. 12:2) ይሁንና እነዚህን ትምህርቶች ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

14, 15. ኢየሱስ ፈተና ሲቀርብለት የወሰደው እርምጃ ከሔዋን የሚለየው እንዴት ነው? እኛስ ኢየሱስን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው? (በገጽ 18 ላይ በሚገኘው ሥዕል ላይ ሐሳብ ስጥ።)

14 ፈተናዎች ይሖዋን እንድትረሳ እንዲያደርጉህ ፈጽሞ አትፍቀድ። ሔዋን ትኩረት ያደረገችው በቀረበላት ፈተና ላይ ብቻ ነበር። “የዛፉ ፍሬ ለመብል መልካም፣ ለዐይን የሚያስደስትና ጥበብንም ለማግኘት የሚያጓጓ እንደ ሆነ” አየች። (ዘፍ. 3:6) ሔዋን ያደረገችው ነገር ኢየሱስ ለቀረቡለት ሦስት ፈተናዎች ከሰጠው ምላሽ ምንኛ የተለየ ነው! ኢየሱስ በሦስቱም ጊዜያት ከፈተናው ባሻገር ያለውን ነገር የተመለከተ ከመሆኑም ሌላ እርምጃው ምን ውጤት እንደሚያስከትል ያጤን ነበር። በአምላክ ቃል ላይ ይታመን የነበረ ሲሆን የይሖዋን ስምም ተጠቅሟል።

15 ይሖዋን የሚያሳዝኑ ነገሮችን እንድንፈጽም ፈተና ሲቀርብልን ትኩረታችን የሚያርፈው በምን ላይ ነው? ፈተና በሆነብን ነገር ላይ ባተኮርን መጠን ድርጊቱን ለመፈጸም የሚገፋፋን መጥፎ ምኞት ይበልጥ እያየለ ይሄዳል። (ያዕ. 1:14, 15) ይህን ምኞት ከሥሩ ነቅለን ለማስወገድ ፈጣን እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል፤ ይህ የሰውነታችንን ክፍል ቆርጦ የመጣል ያህል ከባድ ሆኖ ቢታየንም እንዲህ ማድረጋችን ወሳኝ ነው። (ማቴ. 5:29, 30) ኢየሱስ እንዳደረገው እኛም እርምጃችን በሚያስከትለው ውጤት ላይ ማተኮር ይኸውም ከይሖዋ ጋር ያለንን ግንኙነት እንዴት እንደሚነካው ማሰብ ይኖርብናል። ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ማስታወስ አለብን። በሕይወታችን ውስጥ ከሁሉ የላቀውን ቦታ የምንሰጠው ለይሖዋ መሆኑን ማሳየት የምንችለው በዚህ መንገድ ብቻ ነው።

16-18. (ሀ) ተስፋ እንድንቆርጥ የሚያደርጉን ምን ሁኔታዎች ሊያጋጥሙን ይችላሉ? (ለ) የሚያስጨንቁ ሁኔታዎችን ለመቋቋም ምን ሊረዳን ይችላል?

16 በሕይወትህ ውስጥ የሚያጋጥሙህ መከራዎች በይሖዋ ላይ እንድትመረር እንዲያደርጉህ ፈጽሞ አትፍቀድ። (ምሳሌ 19:3) የዚህ ክፉ ዓለም መጨረሻ እየቀረበ በመጣ መጠን አደጋዎችና መከራዎች የሚያጋጥሟቸው የይሖዋ ሕዝቦች ቁጥር እየጨመረ ነው። በዚህ ጊዜ ተአምራዊ ጥበቃ እናገኛለን ብለን አናስብም። ያም ሆኖ ልክ እንደ ኢዮብ እኛም የምንወዳቸውን ሰዎች በሞት ስናጣ ወይም በሕይወታችን ውስጥ ችግር ሲያጋጥመን ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን።

17 ኢዮብ አንዳንድ ነገሮች እንዲደርሱበት ይሖዋ ለምን እንደፈቀደ አላወቀም ነበር፤ እኛም አንዳንድ ጊዜ መጥፎ ነገሮች የሚፈጸሙት ለምን እንደሆነ ላይገባን ይችላል። ምናልባት በሄይቲ እንዳሉት ወንድሞች በምድር መናወጥ ወይም በሌላ የተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ሕይወታቸውን ስላጡ አንዳንድ ታማኝ ወንድሞች ሰምተን ይሆናል። አሊያም ደግሞ የዓመፅ ድርጊት የተፈጸመበት ወይም አሰቃቂ በሆነ አደጋ የሞተ አንድ ታማኝ የይሖዋ አገልጋይ እናውቅ ይሆናል። ሌላው ቀርቶ እኛ ራሳችን የሚያስጨንቁ ሁኔታዎች ሊያጋጥሙን አሊያም የፍትሕ መጓደል እንደተፈጸመብን ሆኖ ሊሰማን ይችላል። ከጭንቀታችን ብዛት የተነሳ ‘ምነው ይሖዋ፣ ምን በደልኩ? ይህ ሁሉ የሚደርስብኝ ለምንድን ነው?’ እንል ይሆናል። (ዕን. 1:2, 3) እንዲህ በሚሰማን ጊዜ ሁኔታውን ለመቋቋም ምን ሊረዳን ይችላል?

18 እንዲህ ያሉ ነገሮች የደረሱብን የይሖዋን ሞገስ ስላጣን ነው የሚል አመለካከት እንዳንይዝ መጠንቀቅ ይኖርብናል። ኢየሱስ በዘመኑ ስለተፈጸሙ ሁለት አሳዛኝ ክስተቶች በመጥቀስ ይህን ሐቅ ጎላ አድርጎ ገልጾታል። (ሉቃስ 13:1-5ን አንብብ።) ለብዙዎቹ መከራዎች መንስኤ የሚሆኑት “ጊዜና ያልተጠበቁ ክስተቶች” ናቸው። (መክ. 9:11 NW) ይሁንና የመከራችን መንስኤ ምንም ይሁን ምን “የመጽናናት ሁሉ አምላክ” ወደሆነው ወደ ይሖዋ ዘወር ካልን የደረሰብንን ሁኔታ መቋቋም እንችላለን። ይሖዋ በታማኝነት ለመጽናት የሚያስችለንን ጥንካሬ ይሰጠናል።​—2 ቆሮ. 1:3-6

19, 20. ኢየሱስ ውርደት የሚያስከትሉ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙት ለመጽናት የረዳው ምንድን ነው? እኛስ እንዲህ ለማድረግ ምን ሊረዳን ይችላል?

19 ለስምህ መጨነቅ ወይም ውርደትን መፍራት ሕይወትህን እንዲቆጣጠረው ፈጽሞ አትፍቀድ። ኢየሱስ ትሑት በመሆኑ ‘ራሱን ባዶ በማድረግ እንደ ባሪያ ሆኖ በሰው አምሳል’ መጥቷል። (ፊልጵ. 2:5-8) በይሖዋ መታመኑ ውርደት የሚያስከትሉ በርካታ ሁኔታዎችን በጽናት ለመቋቋም አስችሎታል። (1 ጴጥ. 2:23, 24) ኢየሱስ እንዲህ በማድረግ የይሖዋን ፈቃድ ያስቀደመ ሲሆን በዚህም ምክንያት ይሖዋ የላቀ ቦታ በመስጠት ከፍ ከፍ አድርጎታል። (ፊልጵ. 2:9) ኢየሱስ የእሱ ዓይነት የሕይወት ጎዳና እንዲከተሉ ደቀ መዛሙርቱን አበረታቷቸዋል።​—ማቴ. 23:11, 12፤ ሉቃስ 9:26

20 አንዳንድ ጊዜ በእምነታችን ምክንያት የሚያጋጥሙን ፈተናዎች ውርደት የሚያስከትሉ ሊሆኑ ይችላሉ። ያም ቢሆን እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ዓይነት የመተማመን ስሜት ሊኖረን ይገባል። ሐዋርያው እንዲህ ብሏል፦ “ይህን መከራ እየተቀበልኩ ያለሁትም ለዚሁ ነው፤ ሆኖም አላፍርበትም። ምክንያቱም ያመንኩበትን እሱን አውቀዋለሁ፤ በአደራ የሰጠሁትንም እስከዚያ ቀን ድረስ ጠብቆ ማቆየት እንደሚችል እተማመናለሁ።”​—2 ጢሞ. 1:12

21. ዓለም ራስ ወዳድነት የሚንጸባረቅበት አመለካከት ቢኖረውም ምን ቁርጥ ውሳኔ ልታደርግ ይገባል?

21 መጽሐፍ ቅዱስ በዘመናችን “ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ” እንደሚሆኑ አስቀድሞ ተናግሯል። (2 ጢሞ. 3:2) “ከራስ በላይ ነፋስ” የሚል አመለካከት ያላቸው ሰዎች መብዛታቸው ምንም አያስገርምም። እንዲህ ያለ ራስ ወዳድነት የሚንጸባረቅበት አመለካከት እንዳይጋባብን እንጠንቀቅ! ፈተናዎች ቢያጋጥሙን፣ መከራዎች ቢደርሱብን አሊያም ውርደት የሚያስከትሉ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙን ሁላችንም በሕይወታችን ውስጥ ከሁሉ የላቀውን ቦታ የምንሰጠው ለይሖዋ መሆኑን ለማረጋገጥ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ!

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.4 በአዲሱ መደበኛ ትርጉም መቅድም ላይ ገጽ 6 ላይ “መለኮታዊው ስም” በሚለው ንዑስ ርዕስ ሥር የሚገኘውን ማብራሪያ ተመልከት።

^ አን.7 አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራን “ቍርበት ስለ ቍርበት ነው” የሚለው አገላለጽ ኢዮብ የራሱ ቍርበት ወይም ሕይወት እስካልተነካ ድረስ የልጆቹና የእንስሶቹ ቁርበት ወይም ሕይወት ቢያልፍ ምንም እንደማይመስለው የሚያመለክት ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ። ሌሎች ደግሞ ይህ አነጋገር፣ አንድ ሰው ሕይወቱን ለማዳን ሲል ከቍርበቱ የተወሰነውን ለማጣት ፈቃደኛ ሊሆን እንደሚችል የሚያጎላ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሰው ጭንቅላቱ እንዳይመታ በእጁ ሊመክት በሌላ አባባል ቍርበቱን ወይም ሕይወቱን ለማትረፍ ሲል ከቍርበቱ የተወሰነውን ለማጣት ፈቃደኛ ሊሆን ይችላል። ይህ ምሳሌያዊ አነጋገር ትርጉሙ ምንም ይሁን ምን፣ ኢዮብ ሕይወቱን ለማትረፍ ሲል ማንኛውንም ነገር መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኛ እንደሚሆን የሚጠቁም መሆኑ ግልጽ ነው።

ከሚከተሉት ነገሮች ምን ትምህርት እናገኛለን?

• ሰይጣን ሔዋንን ካታለለበት መንገድ፣

• ኢዮብ በሕይወቱ ውስጥ መከራ ሲያጋጥመው ከሰጠው ምላሽ፣

• ኢየሱስ በዋነኝነት ትኩረት ካደረገበት ነገር።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሔዋን ከይሖዋ ጋር ባላት ግንኙነት ላይ ትኩረት አላደረገችም

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ሰይጣን ባቀረበለት ፈተና አልተሸነፈም፤ ትኩረቱ ያረፈው የይሖዋን ፈቃድ በማድረግ ላይ ነበር

[በገጽ 20 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በሄይቲ ከደረሰው የመሬት መናወጥ በኋላ ወንድሞች በየድንኳኑ እየዞሩ ሲሰብኩ

በጭንቀታችን ወቅት ትኩረታችንን “የመጽናናት ሁሉ አምላክ” በሆነው በይሖዋ ላይ ማድረግ እንችላለን