በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በይሖዋ ሙሉ በሙሉ መታመን የደኅንነት ስሜት እንዲያድርብን ያደርጋል

በይሖዋ ሙሉ በሙሉ መታመን የደኅንነት ስሜት እንዲያድርብን ያደርጋል

በይሖዋ ሙሉ በሙሉ መታመን የደኅንነት ስሜት እንዲያድርብን ያደርጋል

“እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ወደ እርሱ በተጣራሁ ጊዜ ይሰማኛል።”​—መዝ. 4:3

1, 2. (ሀ) ዳዊት ምን አደገኛ ሁኔታ አጋጥሞት ነበር? (ለ) የትኞቹን መዝሙሮች እንመረምራለን?

ንጉሥ ዳዊት⁠ ለተወሰኑ ዓመታት እስራኤልን ሲያስተዳድር ቆይቷል፤ ይሁንና ይህ ንጉሥ አንድ አደገኛ ሁኔታ ተጋርጦበታል። ልጁ አቤሴሎም አባቱን ለመገልበጥ እያሴረ ሲሆን ራሱን ንጉሥ አድርጎ ሾሟል፤ በዚህም የተነሳ ዳዊት ኢየሩሳሌምን ጥሎ ለመሸሽ ተገደደ። ከዚህም በላይ ንጉሡ የሚያምነው አማካሪው እንደ ከዳው ሰማ። በመሆኑም ከጥቂት ታማኝ አገልጋዮቹ ጋር በመሆን እያለቀሰ ባዶ እግሩን የደብረ ዘይትን ተራራ ሽቅብ መውጣት ጀመረ። ዳዊት ያጋጠመው መከራ በዚህ እንዳያበቃ ደግሞ ከሳኦል ቤተሰብ የሆነው ሳሚ፣ ንጉሡን ይረግመው እንዲሁም በእሱ ላይ ድንጋይ ይወረውርበትና ዐፈር ይበትንበት ነበር።​—2 ሳሙ. 15:30, 31፤ 16:5-14

2 ዳዊት ባጋጠመው መከራ እንዳዘነና እንደተዋረደ ወደ መቃብሩ ይወርድ ይሆን? በፍጹም፤ ምክንያቱም ዳዊት በይሖዋ ይታመናል። ንጉሡ ከልጁ ከአቤሴሎም በሸሸ ጊዜ ባቀናበረው በ3ኛው መዝሙር ላይ ይህን በግልጽ መመልከት ይቻላል። መዝሙር 4⁠ንም የጻፈው ዳዊት ነው። ዳዊት በሁለቱም መዝሙሮች ላይ አምላክ ጸሎትን እንደሚሰማና ምላሽ እንደሚሰጥ ያለውን እምነት ገልጿል። (መዝ. 3:4፤ 4:3) እነዚህ መዝሙሮች፣ ይሖዋ ቀንና ሌት ከታማኝ አገልጋዮቹ ጋር እንደሚሆንና እንደሚደግፋቸው እንዲሁም ሰላምና የደኅንነት ስሜት እንዲኖራቸው እንደሚያደርግ ያረጋግጡልናል። (መዝ. 3:5፤ 4:8) እንግዲያው እነዚህ መዝሙሮች የደኅንነት ስሜት እንዲያድርብንና በአምላክ እንድንታመን የሚረዱን እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

ብዙዎች ‘በእኛ ላይ ሲነሱ’

3. በ⁠መዝሙር 3:1, 2 ላይ እንደተገለጸው ዳዊት ምን ዓይነት ሁኔታ አጋጥሞት ነበር?

3 አንድ መልእክተኛ “የእስራኤል ሰዎች ልብ ከአቤሴሎም ጋር ሆኖአል” ብሎ ለዳዊት ነገረው። (2 ሳሙ. 15:13) አቤሴሎም ይህን ያህል ድጋፍ ማግኘት መቻሉ ግራ ያጋባው ዳዊት እንዲህ አለ፦ “እግዚአብሔር ሆይ፤ ጠላቶቼ ምንኛ በዙ! ስንቱስ በእኔ ላይ ተነሣ! ብዙዎች ነፍሴን፣ ‘እግዚአብሔር አይታደግሽም’ አሏት።” (መዝ. 3:1, 2) በርካታ እስራኤላውያን፣ ይሖዋ ከአቤሴሎምና ከደጋፊዎቹ እጅ ዳዊትን እንደማይታደገው ተሰምቷቸው ነበር።

4, 5. (ሀ) ዳዊት ስለ ምን ነገር እርግጠኛ ነበር? (ለ) “ራሴንም ቀና ቀና የምታደርግ” የሚለው አገላለጽ ምን ትርጉም አለው?

4 ይሁንና ዳዊት በአምላክ ላይ ሙሉ በሙሉ መተማመኑ የደኅንነት ስሜት እንዲያድርበት አድርጎት ነበር። “እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ግን ዙሪያዬን የምትከልል ጋሻ ነህ፤ ክብሬና፣ ራሴንም ቀና ቀና የምታደርግ አንተ ነህ” በማለት ዘምሯል። (መዝ. 3:3) ጋሻ አንድ ወታደር የሚሰነዘርበትን ጥቃት እንደሚመክትለት ሁሉ ይሖዋም ለዳዊት እንደ ጋሻ እንደሚሆንለት ንጉሡ ይተማመን ነበር። በእርግጥ በዕድሜ የገፋው ይህ ንጉሥ በሽሽት ላይ ነው፤ የደረሰበት ሁኔታ ራሱን እንዲከናነብና አንገቱን እንዲደፋ አድርጎታል። ይሁንና ልዑሉ አምላክ የዳዊትን ሁኔታ በመለወጥ እንዲከበር ያደርገዋል። በልበ ሙሉነት እንደገና ራሱን ቀና አድርጎና ቀጥ ብሎ እንዲሄድ ያስችለዋል። ዳዊት አምላክ መልስ እንደሚሰጠው በመተማመን ወደ እሱ ጸልዮአል። አንተስ እንደ ዳዊት በይሖዋ ላይ ትተማመናለህ?

5 ዳዊት “ራሴንም ቀና ቀና የምታደርግ” ብሎ ሲናገር ይሖዋ እንደሚረዳው ያለውን እምነት መግለጹ ነው። ቱዴይስ ኢንግሊሽ ቨርሽን ይህን ጥቅስ እንደሚከተለው በማለት አስቀምጦታል፦ “ጌታ ሆይ፣ አንተ ግን ምንጊዜም ከአደጋ የምትከልለኝ ጋሻዬ ነህ፤ ድል ታጎናጽፈኛለህ እንዲሁም ድፍረቴን ትመልስልኛለህ።” አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ “ራሴንም ቀና ቀና የምታደርግ” የሚለውን አገላለጽ በተመለከተ እንዲህ ይላል፦ “አምላክ የአንድን ሰው ‘ራስ’ ቀና ሲያደርግ . . . ያንን ሰው ተስፋ እንዲኖረውና የመተማመን ስሜት እንዲያድርበት ያደርገዋል።” ዳዊት ዙፋኑን እንዲለቅቅ በመገደዱ ቢያዝን አይፈረድበትም። ይሁን እንጂ አምላክ ‘ራሱን ቀና ስላደረገለት’ እንደገና ድፍረት የሚያገኝ ከመሆኑም ሌላ የደኅንነት ስሜቱና በአምላክ ላይ ያለው መተማመን ይጨምራል።

ይሖዋ ‘ይመልሳል’

6. ዳዊት ጸሎቱ ምላሽ የሚያገኘው ከተቀደሰው የይሖዋ ተራራ እንደሆነ የገለጸው ለምንድን ነው?

6 ዳዊት በይሖዋ ስለሚታመንና ለጸሎቱ ምላሽ እንደሚሰጠው ስለሚያውቅ ቀጥሎ እንዲህ ብሏል፦ “ወደ እግዚአብሔር ድምፄን ከፍ አድርጌ እጮሃለሁ፤ እርሱም ከተቀደሰ ተራራው ይመልስልኛል።” (መዝ. 3:4) ዳዊት ባዘዘው መሠረት የአምላክን መገኘት የሚያመለክተው የኪዳኑ ታቦት ወደ ጽዮን ተራራ ተወስዶ ነበር። (2 ሳሙኤል 15:23-25ን አንብብ።) ከዚህ አንጻር ዳዊት ጸሎቱ ምላሽ የሚያገኘው ከተቀደሰው የይሖዋ ተራራ እንደሆነ መግለጹ የተገባ ነው።

7. ዳዊት ያለ ስጋት እንዲቀመጥ ያደረገው ምን ነበር?

7 ዳዊት ለአምላክ ያቀረበው ጸሎት ምላሽ ሳያገኝ በከንቱ እንደማይቀር እርግጠኛ ስለነበር ምንም ስጋት አላደረበትም። ከዚህ ይልቅ “እተኛለሁ፤ አንቀላፋለሁ፤ እግዚአብሔር ደግፎ ይዞኛልና እነቃለሁ” በማለት ዘምሯል። (መዝ. 3:5) ሌሊት ላይ ጠላት ድንገተኛ ጥቃት የመሰንዘሩ አጋጣሚ ሰፊ ሊሆን ቢችልም ዳዊት ያለ ስጋት ይተኛ ነበር። ከእንቅልፉ እንደሚነቃ እርግጠኛ ነበር፤ ምክንያቱም ከዚህ ቀደም ያጋጠሙት ሁኔታዎች አምላክ ምንጊዜም እንደሚደግፈው ሙሉ በሙሉ እንዲተማመን አድርገውታል። እኛም “የእግዚአብሔርን መንገድ” የምንጠብቅና ከዚያ ፈቀቅ የማንል ከሆነ በእሱ ላይ ሙሉ በሙሉ ልንታመን እንችላለን።​—2 ሳሙኤል 22:21, 22ን አንብብ።

8. መዝሙር 27:1-4 ዳዊት በአምላክ ላይ እንደሚተማመን የሚያሳየው እንዴት ነው?

8 ዳዊት በአምላክ ላይ ሙሉ በሙሉ እንደሚተማመንና የደኅንነት ስሜት እንደነበረው በመንፈስ መሪነት በጻፈው ሌላ መዝሙር ላይም መመልከት ይቻላል። ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “እግዚአብሔር ብርሃኔና መድኅኔ ነው፤ የሚያስፈራኝ ማን ነው? እግዚአብሔር ለሕይወቴ ዐምባዋ ነው፤ ማንን እፈራለሁ? . . . ሰራዊት ቢከበኝ እንኳ፣ ልቤ አይፈራም፤ . . . እግዚአብሔርን አንዲት ነገር እለምነዋለሁ፤ እርሷንም እሻለሁ፤ ይኸውም በሕይወቴ ዘመን ሁሉ፣ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ፣ የእግዚአብሔርን ክብር ውበት አይ ዘንድ፣ በመቅደሱም ሆኜ አሰላስል ዘንድ ነው።” (መዝ. 27:1-4) አንተም እንደ ዳዊት የሚሰማህና ሁኔታህ የሚፈቅድልህ ከሆነ ይሖዋን ከሚያመልኩ የእምነት አጋሮችህ ጋር ዘወትር ትሰበሰባለህ።​—ዕብ. 10:23-25

9, 10. ዳዊት በ⁠መዝሙር 3:6, 7 ላይ ያለውን ሐሳብ ቢናገርም የበቀል መንፈስ እንዳልነበረው እንዴት እናውቃለን?

9 ዳዊት አቤሴሎም የከዳው ከመሆኑም በላይ ሌሎች በርካታ ሰዎች ለእሱ ታማኝ ሳይሆኑ ቢቀሩም እንዲህ ሲል ዘምሯል፦ “በየአቅጣጫው የከበበኝን፣ አእላፍ ሕዝብ አልፈራም። እግዚአብሔር ሆይ ተነሥ! አምላኬ ሆይ፤ ታደገኝ፤ የጠላቶቼን ሁሉ መንጋጋ ትመታለህ፤ የክፉዎችንም ጥርስ ትሰባብራለህ።”​መዝ. 3:6, 7

10 ዳዊት የበቀል መንፈስ አልነበረውም። የጠላቶቹ ‘መንጋጋ ቢመታም’ ይህን የሚያደርገው አምላክ ነው። ንጉሥ ዳዊት ሕጉን በመገልበጥ የራሱን ቅጂ ስላዘጋጀ በዚህ ሕግ ላይ ይሖዋ “በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ” ብሎ እንደተናገረ ያውቅ ነበር። (ዘዳ. 17:14, 15, 18፤ 32:35) ‘የክፉዎችን ጥርስ መስበርም’ የአምላክ ድርሻ ነው። ጥርሳቸውን መስበር የሚለው አገላለጽ ጉዳት እንዳያደርሱ ማሽመድመድን ያመለክታል። ይሖዋ ‘ልብን ስለሚያይ’ እነማን ክፉዎች እንደሆኑ ያውቃል። (1 ሳሙ. 16:7) የክፋት ጠንሳሽ የሆነውን ሰይጣንን በጽናት መቃወም እንድንችል አምላክ እምነትና ጥንካሬ ስለሚሰጠን ምንኛ አመስጋኞች ነን! ሰይጣን በቅርቡ ወደ ጥልቁ ይጣላል፤ እንደሚያገሳ አንበሳ ቢሆንም ጥርስ ስለሌለው ዕጣ ፈንታው ጥፋት ብቻ ይሆናል።​—1 ጴጥ. 5:8, 9፤ ራእይ 20:1, 2, 7-10

‘ማዳን የይሖዋ ነው’

11. ለእምነት ባልንጀሮቻችን መጸለይ ያለብን ለምንድን ነው?

11 ዳዊት በወቅቱ ካጋጠመው ከባድ ችግር ሊገላግለው የሚችለው ይሖዋ ብቻ መሆኑን ተገንዝቦ ነበር። ይሁንና መዝሙራዊው ያሳሰበው የራሱ ጉዳይ ብቻ አልነበረም። የይሖዋን ሞገስ ያገኙት ሕዝቦች ሁኔታም አሳስቦት ነበር። ዳዊት በመንፈስ መሪነት ያቀናበረውን ይህን መዝሙር “ማዳን የእግዚአብሔር ነው፤ በረከትህ በሕዝብህ ላይ ይሁን” ብሎ መደምደሙ ምንኛ የተገባ ነው! (መዝ. 3:8) እውነት ነው፣ ዳዊት እንደ ተራራ የሆኑ ችግሮች ተጋርጠውበታል፤ ያም ቢሆን ስለ ሁሉም የይሖዋ ሕዝቦች የሚያስብ ከመሆኑም ሌላ አምላክ እንደሚባርካቸው እርግጠኛ ነበር። እኛስ ለእምነት ባልንጀሮቻችን ልናስብ አይገባንም? ምሥራቹን በድፍረትና በልበ ሙሉነት ማወጅ እንዲችሉ ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጣቸው በመለመን በጸሎታችን እናስባቸው።​—ኤፌ. 6:17-20

12, 13. አቤሴሎም ምን ደረሰበት? ዳዊትስ ምን ተሰማው?

12 አቤሴሎም አሳፋሪ በሆነ መንገድ ሕይወቱን አጣ፤ ይህ ሌሎችን በተለይ እንደ ዳዊት ያሉ በአምላክ የተቀቡ ሰዎችን ለሚያዋርዱ ሁሉ ማስጠንቀቂያ ይሆናል። (ምሳሌ 3:31-35ን አንብብ።) የዳዊት ሠራዊት ከአቤሴሎም ጋር የተዋጋ ሲሆን የአቤሴሎም ሠራዊት ተሸነፈ። አቤሴሎም በበቅሎ ተቀምጦ ሲሄድ በቅሎዋ በአንድ ትልቅ ዛፍ ሥር በምታልፍበት ጊዜ ጥቅጥቅ ያለው ፀጉሩ በዛፉ ቅርንጫፍ ተያዘ። በዛፉ ላይ ተንጠልጥሎ ራሱን መከላከል በማይችልበት ሁኔታ ላይ እያለ ኢዮአብ ሦስት ጦሮች ይዞ በመሄድ በአቤሴሎም ልብ ላይ ተከላቸው።​—2 ሳሙ. 18:6-17

13 ዳዊት ልጁ ምን እንደደረሰበት ሲያውቅ ተደስቶ ይሆን? በፍጹም። ከዚህ ይልቅ በሐዘን ተውጦ ወዲያ ወዲህ እየተንጎራደደ እንዲህ በማለት አለቀሰ፦ “ልጄ አቤሴሎም ሆይ! ልጄ አቤሴሎም! በአንተ ፈንታ ምነው እኔ በሞትሁ ኖሮ! አቤሴሎም ሆይ፣ ልጄን፣ ወየው ልጄን!” (2 ሳሙ. 18:24-33) ዳዊትን ከደረሰበት ጥልቅ ሐዘን ሊያጽናናው የቻለው ኢዮአብ ብቻ ነበር። የሥልጣን ጥማት የተጠናወተው የአቤሴሎም መጨረሻ እንዴት የሚያሳዝን ነው፤ ይሖዋ የቀባውን የገዛ አባቱን ለመገልበጥ መነሳቱ ታላቅ ውድቀት አስከትሎበታል!​—2 ሳሙ. 19:1-8፤ ምሳሌ 12:21፤ 24:21, 22

ዳዊት በአምላክ ላይ ያለውን እምነት በድጋሚ ገለጸ

14. መዝሙር 4 የተቀናበረው ለምን ሊሆን ይችላል?

14 እንደ 3ኛው መዝሙር ሁሉ በ4ኛውም መዝሙር ላይ ዳዊት በይሖዋ ሙሉ በሙሉ እንደሚተማመን የሚያሳይ ከልብ የመነጨ ጸሎት አቅርቧል። (መዝ. 3:4፤ 4:3) ዳዊት ይህን መዝሙር ያቀናበረው አቤሴሎም መንግሥት ለመገልበጥ የጠነሰሰው ሴራ በመክሸፉ የተሰማውን እፎይታ ለመግለጽ እንዲሁም አምላክን ለማመስገን ሳይሆን አይቀርም። አሊያም ደግሞ ይህን መዝሙር የጻፈው ሌዋውያን ዘማሪዎችን በአእምሮው ይዞ ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ በዚህ መዝሙር ላይ ማሰላሰላችን በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት ያጠናክርልናል።

15. በልጁ በኩል ወደ ይሖዋ በሙሉ ልብ መጸለይ የምንችለው ለምንድን ነው?

15 አሁንም በድጋሚ ዳዊት በአምላክ ላይ ሙሉ በሙሉ እንደሚተማመን እንዲሁም ጸሎቱ እንደሚሰማለትና ምላሽ እንደሚያገኝ እርግጠኛ መሆኑን ገልጿል። እንዲህ በማለት ዘምሯል፦ “የጽድቄ አምላክ ሆይ፤ በጠራሁህ ጊዜ መልስልኝ፤ ከጭንቀቴ አሳርፈኝ፤ ማረኝ፤ ጸሎቴንም ስማ።” (መዝ. 4:1) እኛም ጽድቅን የምናደርግ ከሆነ እንዲህ ዓይነት ስሜት ሊኖረን ይችላል። ‘የጽድቅ አምላክ’ የሆነው ይሖዋ ቅን የሆኑትን ሕዝቦቹን እንደሚባርክ ስለምናውቅ በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት በማመን በልጁ አማካኝነት ወደ እሱ በሙሉ ልብ መጸለይ እንችላለን። (ዮሐ. 3:16, 36) ይህ እንዴት ያለ እፎይታ ያስገኝልናል!

16. ዳዊት ተስፋ የቆረጠው ለምን ሊሆን ይችላል?

16 አንዳንድ ጊዜ ሰላም የሚነሳን ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ያጋጥመን ይሆናል። ዳዊት እንዲህ የተሰማው ጊዜ የነበረ ይመስላል፤ ምክንያቱም “ሰዎች ሆይ፤ እስከ መቼ ድረስ ክብሬን ዝቅ ታደርጋላችሁ? እስከ መቼስ ድረስ ከንቱ ነገርን ትወዳላችሁ? ሐሰትንስ ትሻላችሁ?” በማለት ዘምሯል። (መዝ. 4:2) “ሰዎች ሆይ” የሚለው አባባል የሰው ልጆችን አሉታዊ በሆነ መንገድ የሚገልጽ ሳይሆን አይቀርም። የዳዊት ጠላቶች “ከንቱ ነገርን [የሚወዱ]” ነበሩ። ኒው ኢንተርናሽናል ቨርሽን ይህን ጥቅስ “እስከ መቼ ድረስ ቅዠትን ትወዳላችሁ? እስከ መቼስ የሐሰት አማልክትን ትሻላችሁ?” በማለት ተርጉሞታል። ሌሎች የሚያደርጉት ነገር ተስፋ ቢያስቆርጠንም ከልባችን መጸለያችንን እና ብቻውን እውነተኛ አምላክ በሆነው በይሖዋ ሙሉ በሙሉ እንደምንታመን ማሳየታችንን እንቀጥል።

17. ከ⁠መዝሙር 4:3 ጋር በሚስማማ መልኩ መመላለስ የምንችለው እንዴት ነው?

17 ዳዊት እንደሚከተለው ብሎ ሲናገር በአምላክ እንደሚተማመን አሳይቷል፦ “እግዚአብሔር ጻድቁን ለራሱ እንደ ለየ ዕወቁ፤ እግዚአብሔር ወደ እርሱ በተጣራሁ ጊዜ ይሰማኛል።” (መዝ. 4:3) ጻድቅ ወይም ለይሖዋ ታማኝ ሆኖ ለመኖር ድፍረትና በእሱ ላይ ሙሉ በሙሉ መታመን ያስፈልጋል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ክርስቲያን ቤተሰብ ንስሐ የማይገባ ዘመዳቸው በሚወገድበት ጊዜ እነዚህን ባሕርያት ማሳየት ያስፈልጋቸዋል። አምላክ ለእሱና ለመንገዶቹ ታማኝ የሆኑትን ይባርካል። በሌላ በኩል ደግሞ ታማኝነትና በይሖዋ ሙሉ በሙሉ መታመን በአምላክ ሕዝቦች መካከል ደስታ እንዲኖር ያደርጋል።​—መዝ. 84:11, 12

18. ሰዎች ደግነት የጎደለው ነገር ቢናገሩን ወይም ቢያደርጉብን ከ⁠መዝሙር 4:4 ጋር በሚስማማ መልኩ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

18 አንድ ሰው የሚያስቆጣን ነገር ቢናገረን ወይም ቢያደርግብንስ? ዳዊት የሰጠውን የሚከተለውን ምክር ተግባራዊ ካደረግን ደስታችንን ጠብቀን መመላለስ እንችላለን፦ “ስትቈጡ ኀጢአት አትሥሩ፤ በዐልጋችሁም ላይ ሳላችሁ፣ ልባችሁን መርምሩ፤ ጸጥም በሉ።” (መዝ. 4:4) ሰዎች ደግነት የጎደለው ነገር ቢናገሩን ወይም ቢያደርጉብን አጸፋውን በመመለስ ኃጢአት አንሥራ። (ሮም 12:17-19) በአልጋችን ላይ ሳለን ወደ ይሖዋ በመጸለይ ስሜታችንን ልንገልጽለት እንችላለን። ስለ ጉዳዩ አንስተን መጸለያችን አመለካከታችን እንዲለወጥና በፍቅር ተነሳስተን ይቅር እንድንል ሊያደርገን ይችላል። (1 ጴጥ. 4:8) በዚህ ረገድ ሐዋርያው ጳውሎስ የሰጠው ምክር ትኩረት የሚስብ ነው፤ ጳውሎስ የሚከተለውን ሐሳብ የጻፈው በመዝሙር 4:4 ላይ ተመሥርቶ ሳይሆን አይቀርም፦ “ተቆጡ፤ ነገር ግን ኃጢአት አትሥሩ፤ ተቆጥታችሁ እያለ ፀሐይ አይጥለቅባችሁ፤ ዲያብሎስም ስፍራ እንዲያገኝ አትፍቀዱለት።”​—ኤፌ. 4:26, 27

19. ከምናቀርባቸው መንፈሳዊ መሥዋዕቶች ጋር በተያያዘ መዝሙር 4:5 ምን ትምህርት ይሰጠናል?

19 ዳዊት በአምላክ ላይ የመታመንን አስፈላጊነት ሲያጎላ “የጽድቅን መሥዋዕት አቅርቡ፤ በእግዚአብሔርም ታመኑ” በማለት ዘምሯል። (መዝ. 4:5) እስራኤላውያን የሚያቀርቧቸው መሥዋዕቶች ዋጋ የሚኖራቸው ሕዝቡ ጥሩ የልብ ዝንባሌ ካላቸው ብቻ ነበር። (ኢሳ. 1:11-17) እኛም ለአምላክ የምናቀርባቸው መንፈሳዊ መሥዋዕቶች ተቀባይነት እንዲኖራቸው ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ሊኖረንና በእሱ ላይ ሙሉ በሙሉ ልንታመን ይገባል።​—ምሳሌ 3:5, 6ን እና ዕብራውያን 13:15, 16ን አንብብ።

20. “የፊትህ ብርሃን” የሚለው አገላለጽ ምን ያመለክታል?

20 ዳዊት በመቀጠል “ብዙዎች፣ ‘አንዳች በጎ ነገር ማን [ያሳየናል?’] ይላሉ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ የፊትህ ብርሃን በላያችን ይብራ” ብሏል። (መዝ. 4:6) የይሖዋ ‘ፊት ብርሃን’ የሚለው አገላለጽ መለኮታዊ ሞገስን ያመለክታል። (መዝ. 89:15) እንግዲያው ዳዊት “የፊትህ ብርሃን በላያችን ይብራ” ብሎ ሲጸልይ ‘ሞገስን አሳየን’ ማለቱ ነበር። በይሖዋ ስለምንታመንና የእሱን ፈቃድ ስለምንፈጽም ሞገሱን ያሳየናል እንዲሁም ከፍተኛ ደስታ እናገኛለን።

21. በዛሬ ጊዜ በሚከናወነው መንፈሳዊ የመከር ሥራ ሙሉ በሙሉ ከተካፈልን ምን እንደምናገኝ ማረጋገጫ ተሰጥቶናል?

21 ዳዊት በመከር ወቅት ከሚኖረው ደስታ የሚበልጠውን ከአምላክ የሚገኘውን ደስታ በተመለከተ ለይሖዋ እንዲህ ሲል ዘምሯል፦ “ስንዴና አዲስ የወይን ጠጅ በብዛት ባመረቱ ጊዜ ከሚያገኙት ደስታ ይልቅ፣ አንተ ልቤን በታላቅ ሐሤት ሞልተኸዋል።” (መዝ. 4:7) በዛሬ ጊዜ በሚከናወነው መንፈሳዊ የመከር ሥራ የተሟላ ተሳትፎ የምናደርግ ከሆነ እውነተኛ ደስታ እንደምናገኝ እርግጠኛ መሆን እንችላለን። (ሉቃስ 10:2) ኢሳይያስ “ሕዝብን አበዛህ” በማለት የተናገረላቸው ቅቡዓን ይህን ሥራ ቅድሚያውን ወስደው የሚሠሩ ሲሆን እኛም ‘የመከሩ ሠራተኞች’ ቁጥር እያደገ መሄዱን ስንመለከት እንደሰታለን። (ኢሳ. 9:3) አንተስ በዚህ አስደሳች የመከር ሥራ የተሟላ ተሳትፎ በማድረግ እውነተኛ እርካታ እያገኘህ ነው?

በአምላክ ሙሉ በሙሉ ታምናችሁ ወደፊት ግፉ

22. ከ⁠መዝሙር 4:8 ጋር በሚስማማ መልኩ እስራኤላውያን የአምላክን ሕግ ይጠብቁ በነበረ ጊዜ ምን ያገኙ ነበር?

22 ዳዊት ይህን መዝሙር የሚደመድመው እንዲህ በማለት ነው፦ “በሰላም እተኛለሁ፤ አንቀላፋለሁም፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ ያለ ሥጋት የምታሳድረኝ አንተ ብቻ ነህና።” (መዝ. 4:8) እስራኤላውያን የይሖዋን ሕግ ይጠብቁ በነበረ ጊዜ ከእሱ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት የነበራቸው ከመሆኑም ሌላ ያለ ሥጋት ይኖሩ ነበር። ለምሳሌ በሰለሞን የግዛት ዘመን “ይሁዳና እስራኤል . . . በሰላም” ወይም ያለ ሥጋት ይኖር ነበር። (1 ነገ. 4:25) በአካባቢያቸው የነበሩት ብሔራት ቢጠሏቸውም እንኳ በአምላክ የሚታመኑ ሁሉ በሰላም ይኖሩ ነበር። እኛም እንደ ዳዊት አምላክ የደኅንነት ስሜት እንዲያድርብን ስለሚያደርግ በሰላም እንተኛለን።

23. በአምላክ ሙሉ በሙሉ ከታመንን ምን እናገኛለን?

23 እንግዲያው በአምላክ ሙሉ በሙሉ ታምነን ወደፊት እንግፋ! እንዲሁም በእምነት ወደ ይሖዋ በመጸለይ “ከማሰብ ችሎታ ሁሉ በላይ [የሆነውን] የአምላክ ሰላም” እናግኝ። (ፊልጵ. 4:6, 7) ይህ እንዴት ያለ ደስታ ያስገኝልናል! በይሖዋ ሙሉ በሙሉ ከታመንን የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት መጠባበቅ እንችላለን።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ዳዊት በአቤሴሎም ምክንያት ምን ችግሮች አጋጥመውት ነበር?

መዝሙር 3 የደኅንነት ስሜት እንዲያድርብን የሚያደርገው እንዴት ነው?

መዝሙር 4 በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት ሊያጠናክርልን የሚችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

• በአምላክ ሙሉ በሙሉ መታመናችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዳዊት ከአቤሴሎም ቢሸሽም በይሖዋ ሙሉ በሙሉ ይታመን ነበር

[በገጽ 32 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በይሖዋ ሙሉ በሙሉ ትታመናለህ?