ክርስቲያን ቤተሰቦች ‘ነቅታችሁ ኑሩ’
ክርስቲያን ቤተሰቦች ‘ነቅታችሁ ኑሩ’
“ነቅተን እንኑር እንዲሁም የማመዛዘን ችሎታችንን እንጠብቅ።”—1 ተሰ. 5:6
1, 2. አንድ ቤተሰብ እስከ መጨረሻው በመንፈሳዊ ንቁ ሆኖ እንዲኖር ምን ማድረግ ያስፈልጋል?
ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ “ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን” በተሰሎንቄ ለሚገኙት ክርስቲያኖች ሲጽፍ እንዲህ ብሏል፦ “ወንድሞች፣ በጨለማ ውስጥ ስላልሆናችሁ ሌሊቱ ድንገት እንደሚነጋበት ሌባ ያ ቀን ድንገት አይደርስባችሁም፤ ምክንያቱም እናንተ ሁላችሁ የብርሃን ልጆችና የቀን ልጆች ናችሁ። እኛ የሌሊት ወይም የጨለማ ሰዎች አይደለንም።” አክሎም “ስለዚህ ነቅተን እንኑር እንዲሁም የማመዛዘን ችሎታችንን እንጠብቅ እንጂ እንደ ሌሎቹ አናንቀላፋ” ብሏል።—ኢዩ. 2:31፤ 1 ተሰ. 5:4-6
2 ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ክርስቲያኖች የሰጠው ምክር በተለይ ‘በፍጻሜው ዘመን’ ለሚኖሩ የአምላክ አገልጋዮች ወቅታዊ ነው። (ዳን. 12:4) የዚህ ክፉ ሥርዓት ፍጻሜ እየተቃረበ ሲመጣ ሰይጣን በተቻለው መጠን በርካታ እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች ይሖዋን ከማምለክ ዘወር እንዲሉ ለማድረግ የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም። በመሆኑም ጳውሎስ ምንጊዜም በመንፈሳዊ ንቁ እንድንሆን የሰጠንን ምክር ልብ ማለታችን የጥበብ አካሄድ ነው። አንድ የክርስቲያን ቤተሰብ እስከ መጨረሻው ንቁ ሆኖ እንዲኖር እያንዳንዱ የቤተሰቡ አባል ቅዱስ ጽሑፋዊ ኃላፊነቱን መሸከም ይኖርበታል። ታዲያ ባሎች፣ ሚስቶችና ልጆች ቤተሰባቸው ‘ነቅቶ እንዲኖር’ ለማድረግ ምን ሚና ይጫወታሉ?
ባሎች—‘ጥሩውን እረኛ’ ምሰሉ
3. በ1 ጢሞቴዎስ 5:8 መሠረት አንድ ወንድ የቤተሰብ ራስ ሲሆን የሚኖረው ኃላፊነት ምን ነገሮችን ይጨምራል?
3 መጽሐፍ ቅዱስ ‘የሴት ራስ ወንድ’ እንደሆነ ይናገራል። (1 ቆሮ. 11:3) አንድ ወንድ፣ የቤተሰብ ራስ እንዲሆን የተሰጠው ኃላፊነት ምን ነገሮችን ይጨምራል? የአምላክ ቃል የራስነት ሥልጣን ከሚያስከትላቸው ኃላፊነቶች አንዱን ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦ “አንድ ሰው የራሱ ለሆኑት በተለይ ደግሞ ለቤተሰቡ አባላት የሚያስፈልጋቸውን ነገር የማያቀርብ ከሆነ እምነትን የካደ ከመሆኑም በላይ እምነት የለሽ ከሆነ ሰው የከፋ ነው።” (1 ጢሞ. 5:8) እውነት ነው፣ አንድ ሰው የቤተሰቡን ቁሳዊ ፍላጎት ማሟላት አለበት። ይሁንና ቤተሰቡ በመንፈሳዊ ንቁ ሆኖ እንዲኖር ለመርዳት ከፈለገ ከዚህ የበለጠ ነገር ማድረግ ይኖርበታል። ሁሉም የቤተሰቡ አባላት ከአምላክ ጋር ያላቸውን ወዳጅነት እንዲያጠናክሩ በመርዳት ቤተሰቡን በመንፈሳዊ መገንባት ይገባዋል። (ምሳሌ 24:3, 4) እንዲህ ማድረግ የሚችለው እንዴት ነው?
4. አንድ አባት ቤተሰቡን በመንፈሳዊ በመገንባት ረገድ ስኬታማ ለመሆን የሚረዳው ቁልፍ ምንድን ነው?
4 “ክርስቶስ . . . [ለጉባኤው] ራስ እንደሆነ ሁሉ ባልም የሚስቱ ራስ” በመሆኑ አንድ ያገባ ወንድ ኢየሱስ በጉባኤው ላይ ያለውን የራስነት ሥልጣን የተጠቀመበትን መንገድ መመርመርና የእሱን ምሳሌ መከተል ይኖርበታል። (ኤፌ. 5:23) ኢየሱስ ከተከታዮቹ ጋር የነበረውን ግንኙነት የገለጸበትን መንገድ ልብ በል። (ዮሐንስ 10:14, 15ን አንብብ።) ቤተሰቡን በመንፈሳዊ ለመገንባት የሚፈልግ አባት በዚህ ረገድ ስኬታማ ለመሆን የሚረዳው ቁልፍ ምንድን ነው? ቁልፉ፦ “በጣም ጥሩ እረኛ” የሆነው ኢየሱስ የተናገራቸውንና ያደረጋቸውን ነገሮች ማጥናት እንዲሁም “የእሱን ፈለግ በጥብቅ [መከተል]” ነው።—1 ጴጥ. 2:21
5. ጥሩው እረኛ ስለ ጉባኤው ምን ያህል ያውቃል?
5 በእረኛና በበጎች መካከል ያለው ግንኙነት በእውቀትና በመተማመን ላይ የተመሠረተ ነው። እረኛው በጎቹን በደንብ ያውቃቸዋል፤ በጎቹም እረኛቸውን የሚያውቁት ከመሆኑም ሌላ ይተማመኑበታል። ድምፁን ለይተው ያውቁታል፤ እንዲሁም ይታዘዙታል። ኢየሱስ “በጎቼን አውቃቸዋለሁ፤ በጎቼም ያውቁኛል” ብሏል። ጉባኤውን የሚያውቀው እንዲሁ ላይ ላዩን ብቻ አይደለም። እዚህ ላይ ‘ማወቅ’ ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ
ቃል “በግለሰብ ደረጃ ጠንቅቆ ማወቅን” ያመለክታል። አዎን፣ ጥሩው እረኛ እያንዳንዱን በግ ያውቀዋል። በጎቹ በግለሰብ ደረጃ የሚያስፈልጋቸውን ነገር እንዲሁም ድክመታቸውንና ጥንካሬያቸውን ያውቃል። አርዓያችን የሆነው ኢየሱስ ስለ በጎቹ የማያውቀው ነገር የለም። በጎቹም ቢሆኑ እረኛቸውን በሚገባ የሚያውቁት ሲሆን በሚሰጣቸው አመራር ይተማመናሉ።6. ባሎች ጥሩውን እረኛ መምሰል የሚችሉት እንዴት ነው?
6 አንድ ባል የራስነት ሥልጣኑን ክርስቶስ በተጠቀመበት መንገድ መጠቀም ከፈለገ ራሱን እንደ እረኛ፣ በእሱ ኃላፊነት ሥር ያሉትን ደግሞ እንደ በጎች አድርጎ መመልከትን መማር ይኖርበታል። ስለ ቤተሰቡ ጠንቅቆ ለማወቅ መጣር አለበት። አንድ ባል እንዲህ ያለ እውቀት ሊኖረው ይችላል? አዎን፣ ከሁሉም የቤተሰቡ አባላት ጋር ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ የሚያደርግ፣ የሚያሳስባቸውን ነገሮች ጆሮ ሰጥቶ የሚያዳምጥ፣ ቤተሰቡ አንድ ላይ ሆኖ በሚያከናውናቸው ነገሮች ረገድ ጥሩ ምሳሌ የሚሆን እንዲሁም እንደ ቤተሰብ አምልኮ፣ ስብሰባ፣ አገልግሎት፣ ሽርሽርና መዝናኛ የመሳሰሉ ነገሮችን በተመለከተ ለቤተሰቡ የሚጠቅም ውሳኔ በማድረግ ረገድ ኃላፊነቱን በሚገባ የሚወጣ ከሆነ ቤተሰቡን ጠንቅቆ ማወቅ ይችላል። አንድ ክርስቲያን ባል የአምላክን ቃል ብቻ ሳይሆን የቤተሰቡንም አባላት በሚገባ በማወቅ ረገድ አርዓያ የሚሆንና ጥበብ የተንጸባረቀባቸውን ውሳኔዎች የሚያደርግ ከሆነ የቤተሰቡ አባላት በራስነት ሥልጣኑ ይተማመናሉ፤ እሱም ቢሆን ቤተሰቡ በእውነተኛው አምልኮ አንድነቱን ጠብቆ ሲመላለስ በማየት ይደሰታል።
7, 8. አንድ ባል በእሱ ኃላፊነት ሥር ላሉት ፍቅር በማሳየት ረገድ የጥሩውን እረኛ ምሳሌ መከተል የሚችለው እንዴት ነው?
7 በተጨማሪም ጥሩ እረኛ በጎቹን ይወዳቸዋል። ስለ ኢየሱስ ሕይወትና አገልግሎት የሚያወሱትን የወንጌል ዘገባዎች ስናጠና ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ምን ያህል ፍቅር እንደነበረው እንረዳለን፤ ይህም ልባችን በአድናቆት እንዲሞላ ያደርጋል። ኢየሱስ ‘ነፍሱን ለበጎቹ ሲል አሳልፎ’ እስከ መስጠት ድረስ ለእነሱ ፍቅር ነበረው። ባሎችም በእነሱ ኃላፊነት ሥር ላሉት ፍቅር በማሳየት ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል አለባቸው። በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት የሚፈልግ ባል ሚስቱን ከመጨቆን ይልቅ “ክርስቶስ ጉባኤውን እንደወደደ” ሁሉ ምንጊዜም ሚስቱን ይወዳታል። (ኤፌ. 5:25) ሚስቱ ክብር የሚገባት በመሆኑ አነጋገሩ ደግነትና አሳቢነት የሚንጸባረቅበት መሆን አለበት።—1 ጴጥ. 3:7
8 የቤተሰቡ ራስ ልጆቹን በሚያሠለጥንበት ጊዜ አምላካዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በጥብቅ መከተል ይኖርበታል። በሌላ በኩል ግን ለልጆቹ ፍቅር የማያሳይ ሰው እንዳይሆን መጠንቀቅ ይገባዋል። ተግሣጽ መስጠት አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ይህን በፍቅር ማድረግ አለበት። አንዳንድ ልጆች ከእነሱ የሚጠበቀውን ነገር ለመረዳት ከሌሎቹ የበለጠ ጊዜ ሊወስድባቸው ይችላል። አንድ አባት ለእንደነዚህ ዓይነት ልጆች ይበልጥ ታጋሽ መሆን ይኖርበታል። ባሎች ምንጊዜም የኢየሱስን ምሳሌ የሚከተሉ ከሆነ ቤተሰባቸው ተማምኖና ተረጋግቶ እንዲኖር ያደርጋሉ። ቤተሰባቸው ልክ መዝሙራዊው እንደጠቀሰው በመንፈሳዊ ሁኔታ ተረጋግቶ መኖር ይችላል።—መዝሙር 23:1-6ን አንብብ።
9. እንደ ኖኅ ሁሉ ክርስቲያን ባሎችም ምን ኃላፊነት አለባቸው? ይህን ኃላፊነታቸውን ለመወጣትስ ምን ሊረዳቸው ይችላል?
9 የቤተሰብ ራስ የሆነው ኖኅ የኖረው በዘመኑ የነበረው ዓለም ሊጠፋ በተቃረበበት ጊዜ ላይ ነበር። ይሁንና ይሖዋ “ፈሪሃ አምላክ ባልነበራቸው ሰዎች በተሞላው ዓለም ላይ የጥፋት ውኃ ባመጣ ጊዜ” ኖኅን “ከሌሎች ሰባት ሰዎች ጋር [አድኖታል]።” (2 ጴጥ. 2:5) ኖኅ ቤተሰቡ ከጥፋት ውኃው እንዲተርፉ የመርዳት ኃላፊነት ነበረበት። በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች ውስጥ የሚኖሩ ክርስቲያን የቤተሰብ ራሶችም ተመሳሳይ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል። (ማቴ. 24:37) የቤተሰብ ራሶች ‘የጥሩውን እረኛ’ ምሳሌ ማጥናታቸውና እሱን ለመምሰል ጥረት ማድረጋቸው ምንኛ አስፈላጊ ነው!
ሚስቶች—‘ቤታችሁን የምትሠሩ’ ሁኑ
10. አንዲት ሚስት ለባሏ ትገዛለች ሲባል ምን ማለት ነው?
10 ሐዋርያው ጳውሎስ “ሚስቶች ለጌታ እንደሚገዙ ሁሉ ለባሎቻቸው ይገዙ” በማለት ጽፏል። (ኤፌ. 5:22) ይህ ጥቅስ ሚስቶች ዝቅ ያለ ቦታ እንዳላቸው የሚጠቁም አይደለም። እውነተኛው አምላክ፣ የመጀመሪያዋ ሴት የሆነችውን ሔዋንን ከመፍጠሩ በፊት “ሰው ብቻውን መሆኑ መልካም አይደለምና የሚስማማውን ረዳት አበጅለታለሁ” በማለት ተናግሮ ነበር። (ዘፍ. 2:18) አንዲት ሚስት “ረዳት” እና ማሟያ ሆና የምትጫወተው ሚና ይኸውም ባሏ የቤተሰብ ኃላፊነቱን በሚወጣበት ጊዜ እሱን መደገፏ በእርግጥም የተከበረ ድርሻ ነው።
11. ምሳሌ የምትሆን ሚስት ‘ቤቷን የምትሠራው’ እንዴት ነው?
11 ምሳሌ የምትሆን ሚስት ቤተሰቧን የሚጠቅም ነገር ለማድረግ ትጥራለች። (ምሳሌ 14:1ን አንብብ።) ለራስነት ዝግጅት አክብሮት ከሌላት ተላላ ወይም ሞኝ ሴት በተቃራኒ ጠቢብ ሴት ለዚህ ሥርዓት ጥልቅ አክብሮት እንዳላት ታሳያለች። እንዲህ ዓይነቷ ሴት በዓለም ላይ የሚታየውን የዓመፀኝነትና በራስ የመመራት መንፈስ ከማንጸባረቅ ይልቅ ለትዳር ጓደኛዋ ትገዛለች። (ኤፌ. 2:2) ሞኝ ሴት ስለ ባሏ አሉታዊ ነገር ከመናገር ወደኋላ አትልም፤ በሌላ በኩል ግን ጠቢብ ሴት ልጆቿም ሆኑ ሌሎች ሰዎች ባሏን ይበልጥ እንዲያከብሩት ጥረት ታደርጋለች። እንዲህ ያለች ሴት ባሏን በመነዝነዝ ወይም ከእሱ ጋር በመጨቃጨቅ የራስነት ሥልጣኑን አታቃልልም። ሌላው ሊነሳ የሚገባው ጉዳይ ደግሞ ቆጣቢነት ነው። ሞኝ ሴት በብዙ ልፋት የተገኘውን የቤተሰቡን ገንዘብና ንብረት ታባክናለች። ባሏን የምትደግፍ ሚስት ግን እንዲህ አታደርግም። በገንዘብ ነክ ጉዳዮች ረገድ ከባሏ ጋር ትተባበራለች። ነገሮችን የምታከናውንበት መንገድም አስተዋይና ቆጣቢ መሆኗን ያሳያል። እንዲሁም ባለቤቷ ተጨማሪ ሰዓት እንዲሠራ ጫና አታሳድርበትም።
12. አንዲት ሚስት፣ ቤተሰቧ ‘ነቅቶ እንዲኖር’ ለመርዳት ምን ማድረግ ትችላለች?
12 ምሳሌ የምትሆን ሚስት ለልጆቻቸው መንፈሳዊ ትምህርት በመስጠት ረገድ ባሏን በመደገፍ ቤተሰቡ ‘ነቅቶ እንዲኖር’ አስተዋጽኦ ታደርጋለች። (ምሳሌ 1:8) የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማቸው እንዲሳካ ከፍተኛ እገዛ ታበረክታለች። ከዚህም በላይ ባለቤቷ ለልጆቻቸው ምክርና ተግሣጽ ሲሰጥ ትደግፈዋለች። እንዲህ ዓይነቷ ሚስት ከባሏ ጋር ለመተባበር ፈቃደኛ ካልሆነች ሴት ምንኛ የተለየች ናት! በሌላ በኩል ግን ተባባሪ ያልሆነች ሚስት፣ ልጆቿ በአካላዊም ሆነ በመንፈሳዊ ሁኔታ መጎዳታቸው አይቀርም።
13. አንዲት ሚስት ባለቤቷ በተለያዩ ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች በሚካፈልበት ጊዜ እሱን መደገፏ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
13 ባሏን የምትደግፍ ሚስት ባለቤቷ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የተለያዩ ኃላፊነቶችን ተቀብሎ ሲሠራ ምን ይሰማታል? በጣም እንደምትደሰት ምንም ጥርጥር የለውም! ባለቤቷ የጉባኤ አገልጋይም ሆነ ሽማግሌ አሊያም በሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴ፣ በሕሙማን ጠያቂ ቡድን ወይም በስብሰባ አዳራሽ ኮሚቴና በሌሎች ኮሚቴዎች ውስጥ የሚያገለግል ከሆነ ባገኘው መብት ደስተኛ ናት። በንግግሯም ሆነ በድርጊቷ ባለቤቷን መደገፍ መሥዋዕትነት መክፈል እንደሚጠይቅባት ጥርጥር የለውም። ያም ሆኖ ባለቤቷ በቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች መካፈሉ መላው ቤተሰብ በመንፈሳዊ ንቁ ሆኖ እንዲኖር አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ትገነዘባለች።
14. (ሀ) ባሏን የምትደግፍ ሚስት የትኛው ሁኔታ ፈታኝ ሊሆንባት ይችላል? ይህንንስ እንዴት ልትወጣው ትችላለች? (ለ) አንዲት ሚስት መላው ቤተሰብ ደስተኛ እንዲሆን አስተዋጽኦ የምታበረክተው እንዴት ነው?
14 አንዲት ሚስት ባሏ እሷ የማትስማማበትን ውሳኔ በሚያደርግበት ጊዜ እሱን መደገፍ አስቸጋሪ ሊሆንባት ይችላል። በዚህ ጊዜም ቢሆን “ጭምትና ገር መንፈስ” የምታሳይ ከመሆኗም በላይ ውሳኔው እንዲሳካ ለማድረግ ከእሱ ጋር ትተባበራለች። (1 ጴጥ. 3:4) በተጨማሪም አንዲት ጥሩ ሚስት እንደ ሣራ፣ ሩት፣ አቢግያና የኢየሱስ እናት እንደሆነችው ማርያም ያሉት በጥንት ዘመን የኖሩ አምላክን የሚፈሩ ሴቶች የተዉትን ግሩም ምሳሌ ለመከተል ትጥራለች። (1 ጴጥ. 3:5, 6) ከዚህም በላይ “ለቅዱሳን ሰዎች የሚገባ ባሕርይ” ያላቸውን በዘመናችን ያሉ በዕድሜ የገፉ ሴቶች ምሳሌ ትከተላለች። (ቲቶ 2:3, 4) አርዓያ የምትሆን ሚስት ለባሏ ፍቅርና አክብሮት በማሳየት ትዳራቸው እንዲሳካና መላው ቤተሰብ ደስተኛ እንዲሆን አስተዋጽኦ ታደርጋለች። ቤታቸው እፎይታ የሚገኝበት ከመሆኑም ሌላ የቤተሰቡ አባላት የደኅንነት ስሜት ይኖራቸዋል። መንፈሳዊ የሆነ ባል፣ ሚስቱ ድጋፍ የምትሰጠው ከሆነ እንደ ውድ ዕንቁ አድርጎ ይመለከታታል።—ምሳሌ 18:22
ወጣቶች—‘ዓይናችሁ በማይታዩት ነገሮች ላይ እንዲያተኩር አድርጉ’
15. ወጣቶች፣ ቤተሰባቸው ‘ነቅቶ እንዲኖር’ ከወላጆቻቸው ጋር ተባብረው መሥራት የሚችሉት እንዴት ነው?
15 እናንት ወጣቶች፣ ቤተሰባችሁ በመንፈሳዊ ‘ነቅቶ እንዲኖር’ ከወላጆቻችሁ ጋር ተባብራችሁ መሥራት የምትችሉት እንዴት ነው? ይሖዋ በፊታችሁ ያስቀመጠላችሁን ሽልማት አስቡ። ምናልባት ወላጆቻችሁ በገነት ውስጥ የሚኖረውን ሕይወት የሚያሳዩ ሥዕሎችን ከልጅነታችሁ ጀምረው አሳይተዋችሁ ይሆናል። እያደጋችሁ ስትሄዱ ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስና በክርስቲያናዊ ጽሑፎች በመጠቀም በአዲሱ ዓለም ውስጥ የሚኖረው የዘላለም ሕይወት ምን እንደሚመስል በዓይነ ሕሊናችሁ እንድትስሉ ረድተዋችሁ ይሆናል። ዓይናችሁ ምንጊዜም በይሖዋ አገልግሎት ላይ እንዲያተኩር ማድረጋችሁና በሕይወታችሁ ውስጥ እቅድ ስታወጡ ይህን ግምት ውስጥ ማስገባታችሁ ‘ነቅታችሁ እንድትኖሩ’ ይረዳችኋል።
16, 17. ወጣቶች ለሕይወት የሚደረገውን ሩጫ በተሳካ ሁኔታ ለመሮጥ ምን ማድረግ ይችላሉ?
16 ሐዋርያው ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ 9:24 ላይ የሰጠውን ምክር ልብ በሉ። (ጥቅሱን አንብብ።) ለሕይወት የሚደረገውን ሩጫ የማሸነፍ ግብ በመያዝ ሩጡ። የዘላለም ሕይወት ሽልማት የሚያስገኝላችሁን ጎዳና ምረጡ። ብዙዎች ቁሳዊ ነገሮችን ማሳደዳቸው ዓይናቸው ሽልማቱ ላይ እንዳያተኩር እንቅፋት ሆኖባቸዋል። ይህ እንዴት ያለ ሞኝነት ነው! ሀብት በማካበት ላይ ያተኮረ ሕይወት መምራት እውነተኛ ደስታ አያስገኝም። ገንዘብ ሊገዛቸው የሚችሉ ነገሮች ዘላቂ አይደሉም። እናንተ ግን ዓይናችሁ “በማይታዩት ነገሮች” ላይ እንዲያተኩር አድርጉ። ለምን? ምክንያቱም “የማይታዩት ነገሮች . . . ዘላለማዊ ናቸው።”—2 ቆሮ. 4:18
17 “የማይታዩት ነገሮች” ከተባሉት መካከል መንግሥቱ የሚያመጣቸው በረከቶች ይገኙበታል። በሕይወታችሁ ውስጥ የምታወጧቸው እቅዶች እነዚህን በረከቶች ለማግኘት የሚያስችሏችሁ እንዲሆኑ አድርጉ። እውነተኛ ደስታ የምታገኙት ሕይወታችሁን በይሖዋ አገልግሎት ስትጠቀሙበት ነው። እውነተኛውን አምላክ ማገልገል የአጭርና የረጅም ጊዜ ግቦች ላይ ለመድረስ አጋጣሚ ይሰጣችኋል። * ልትደርሱባቸው የምትችሏቸውን መንፈሳዊ ግቦች ማውጣታችሁ የዘላለም ሕይወት ሽልማት ለማግኘት በማሰብ ምንጊዜም አምላክን በማገልገል ላይ ትኩረት እንድታደርጉ ይረዳችኋል።—1 ዮሐ. 2:17
18, 19. አንድ ወጣት እውነትን የራሱ ማድረግ አለማድረጉን ማወቅ የሚችለው እንዴት ነው?
18 ወጣቶች በሕይወት ጎዳና ላይ ለመጓዝ የምትወስዱት የመጀመሪያው እርምጃ እውነትን የራሳችሁ ማድረግ ነው። አንተ ይህን እርምጃ ወስደሃል? እስቲ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘መንፈሳዊ ሰው ነኝ ወይስ በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች የምካፈለው ወላጆቼ ስለሚሉኝ ብቻ ነው? አምላክ የሚደሰትብኝ ዓይነት ሰው ለመሆን የሚያስችሉኝን ባሕርያት ለማዳበር እጥራለሁ? ከእውነተኛው አምልኮ ጋር በተያያዙ እንደ ጸሎት፣ ጥናት፣ በስብሰባዎች ላይ መገኘትና የመስክ አገልግሎት ያሉ እንቅስቃሴዎች አዘውትሬ ለመካፈል ጥረት አደርጋለሁ? ከአምላክ ጋር የመሠረትሁትን የግል ዝምድና በማጠናከር ወደ እሱ ይበልጥ ለመቅረብ እሞክራለሁ?’—ያዕ. 4:8
19 ሙሴ በተወው ምሳሌ ላይ አሰላስል። ሙሴ በባዕድ ዕብራውያን 11:24-27ን አንብብ።) ክርስቲያን ወጣቶች፣ እናንተም ይሖዋን በታማኝነት ለማገልገል ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ያስፈልጋችኋል። እንዲህ የምታደርጉ ከሆነ በአሁኑ ጊዜ እውነተኛ ደስታና ከሁሉ የተሻለ ሕይወት የምታገኙ ሲሆን “እውነተኛ የሆነውን ሕይወት” የማግኘት ተስፋም ይኖራችኋል።—1 ጢሞ. 6:19
አገር ቢያድግም የፈርዖን ሴት ልጅ፣ ልጅ ተብሎ ከመጠራት ይልቅ የይሖዋ አምላኪ ሆኖ መታወቅን መርጧል። (20. ለሕይወት በሚደረገው ሩጫ ሽልማቱን የሚያገኘው ማን ነው?
20 በጥንት ዘመን በሚደረጉ የሩጫ ውድድሮች ላይ የሚያሸንፈው አንድ ሰው ብቻ ነበር። ለሕይወት የሚደረገው ሩጫ ግን እንዲህ አይደለም። የአምላክ ፈቃድ “ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲድኑ እንዲሁም የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ ነው።” (1 ጢሞ. 2:3, 4) ከእናንተ በፊት የነበሩ ብዙዎች ይህን ሩጫ በተሳካ ሁኔታ ሮጠዋል፤ አሁንም ብዙዎች አብረዋችሁ እየሮጡ ነው። (ዕብ. 12:1, 2) ሽልማቱን የሚያገኙት ተስፋ ሳይቆርጡ እስከ መጨረሻው የሚጸኑ ናቸው። እንግዲያው ይህን ሩጫ ለማሸነፍ ቆርጣችሁ ተነሱ!
21. በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?
21 “ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን” መምጣቱ አይቀሬ ነው። (ሚል. 4:5) ክርስቲያን ቤተሰቦች ይህ ቀን በድንገት ሊመጣባቸው አይገባም። እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ቅዱስ ጽሑፋዊ ኃላፊነቱን መወጣቱ አስፈላጊ ነው። በመንፈሳዊ ንቁ ለመሆንና ከአምላክ ጋር ያላችሁን ወዳጅነት ለማጠናከር ሌላስ ምን ማድረግ ይኖርባችኋል? በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ለመላው ቤተሰብ መንፈሳዊ ደኅንነት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ሦስት ነጥቦችን እንመለከታለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
ምን ትምህርት አግኝተሃል?
• ክርስቲያን ቤተሰቦች ‘ነቅተው መኖራቸው’ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
• አንድ ባል ጥሩውን እረኛ መምሰል የሚችለው እንዴት ነው?
• ምሳሌ የምትሆን ሚስት ባሏን ለመደገፍ ምን ማድረግ ትችላለች?
• ልጆች ቤተሰባቸው በመንፈሳዊ ነቅቶ እንዲኖር አስተዋጽኦ የሚያደርጉት እንዴት ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንዲት ሚስት ለባሏ ድጋፍ የምትሰጠው ከሆነ ባሏ እንደ ውድ ዕንቁ አድርጎ ይመለከታታል