በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ፍጹም መሪያችን የሆነውን ክርስቶስን መከተል

ፍጹም መሪያችን የሆነውን ክርስቶስን መከተል

ፍጹም መሪያችን የሆነውን ክርስቶስን መከተል

ሰብዓዊ መሪዎችን የሚከተሉ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ያሰቡት ሳይሳካ ሲቀር ለሐዘን ይዳረጋሉ። ለክርስቶስ አመራር የሚገዙ ግን ሁኔታቸው ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነው። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “እናንተ የደከማችሁና ሸክም የከበዳችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም እረፍት እሰጣችኋለሁ። ቀንበሬን ተሸከሙ፣ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ ገርና በልቤ ትሑት ነኝ፤ ለነፍሳችሁም እረፍት ታገኛላችሁ።” (ማቴ. 11:28, 29) ኢየሱስ የሚሰጠው አመራር እረፍት የሚሰጥና መንፈስን የሚያድስ ነው። ዝቅ ተደርገው ለሚታዩና ለተጨቆኑ ሰዎች በጥልቅ የሚያስብ ሲሆን ልዝብ የሆነውን ቀንበሩን እንዲሸከሙ ጋብዟቸዋል። ይሁንና የኢየሱስን አመራር መከተል ምን ነገሮችን ያካትታል?

ሐዋርያው ጴጥሮስ “ክርስቶስም . . . የእሱን ፈለግ በጥብቅ እንድትከተሉ አርዓያ ትቶላችሁ ለእናንተ መከራ ተቀብሏል” በማለት ጽፏል። (1 ጴጥ. 2:21) የኢየሱስን ፈለግ መከተላችን ምን ያህል አስፈላጊ ነው? ፈንጂ የተቀበረበትን አካባቢ አቋርጠህ ማለፍ ቢኖርብህና አብረውህ ካሉት ሰዎች መካከል ጉዳት ሳይደርስባችሁ ማለፍ የምትችሉበትን መንገድ ሊመራችሁ የሚችለው አንድ ሰው ብቻ ቢሆን ምን እንደምታደርግ አስብ። የእሱን ፈለግ በጥብቅ የምትከተል ምናልባትም እሱ የረገጠበት ቦታ ላይ እየረገጥክ የምትሄድ አይመስልህም? በተመሳሳይም የወደፊቱ ደኅንነታችን የተመካው በሕይወታችን ውስጥ የኢየሱስን ምሳሌ በመከተላችን ላይ ነው። እንዲህ ማድረግ እሱን መስማትና መታዘዝን እንዲሁም የእሱ ወኪሎች ከሆኑ ሰዎች ጋር መተባበርን ያካትታል።

መስማትና መታዘዝ

ኢየሱስ በተራራው ስብከቱ መጨረሻ ላይ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ይህን ቃሌን ሰምቶ በተግባር የሚያውል ሁሉ ቤቱን በዐለት ላይ የሠራን አስተዋይ ሰው ይመስላል። ዶፍ ወረደ፣ ጎርፍ ጎረፈ፣ ነፋስም ነፈሰ፤ ያንንም ቤት በኃይል መታው፤ ሆኖም ቤቱ በዐለት ላይ ስለተመሠረተ አልተደረመሰም።”​—ማቴ. 7:24, 25

እዚህ ላይ ኢየሱስ የእሱን ቃል ሰምቶ የሚታዘዝን ሰው “አስተዋይ” በማለት ገልጾታል። እኛስ ከልብ በመታዘዝ ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ እንደምናከብርና እንደምናደንቅ እናሳያለን? ወይስ ከኢየሱስ ትእዛዛት መካከል ቀላል የሆኑትን ወይም የሚመቹንን ብቻ እየመረጥን መታዘዝ ይቀናናል? ኢየሱስ “ሁልጊዜ [አምላክን] ደስ የሚያሰኘውን [አደርጋለሁ]” ብሏል። (ዮሐ. 8:29) እኛም የኢየሱስን ምሳሌ ለመከተል እንጣር።

በመጀመሪያው መቶ ዘመን፣ ሐዋርያት ለክርስቶስ አመራር በመገዛት ረገድ ጥሩ ምሳሌ ትተዋል። በአንድ ወቅት ጴጥሮስ ለኢየሱስ “እነሆ፣ እኛ ሁሉን ትተን እየተከተልንህ ነው” ብሎት ነበር። (ማር. 10:28) በእርግጥም ሐዋርያት ለኢየሱስ አመራር ከፍተኛ ግምት ይሰጡ ስለነበር እሱን ለመከተል ሲሉ ሌሎች ነገሮችን ሁሉ በፈቃደኝነት ትተዋል።​—ማቴ. 4:18-22

ከክርስቶስ ወኪሎች ጋር ተባበሩ

ኢየሱስ ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ የእሱን አመራር መከተል የምንችልበትን ሌላውን መንገድ ጠቅሷል። “እኔ የምልከውን ሁሉ የሚቀበል እኔንም ይቀበላል” ብሏል። (ዮሐ. 13:20) እንዲያውም ኢየሱስ የተቀቡ ወኪሎቹን “ወንድሞቼ” በማለት ጠርቷቸዋል። (ማቴ. 25:40) ኢየሱስ ከሙታን ተነስቶ ወደ ሰማይ ከሄደ በኋላ ‘ወንድሞቹ’ በእሱ ቦታ ሆነው እንዲሠሩ ተሹመው ነበር፤ እነዚህ ቅቡዓን እንደ አምባሳደር በመሆን ‘ክርስቶስን ተክተው’ ሰዎች ከይሖዋ አምላክ ጋር እንዲታረቁ ጥሪ ያቀርባሉ። (2 ቆሮ. 5:18-20) የክርስቶስን አመራር መቀበላችን ‘ለወንድሞቹ’ መገዛትን ይጨምራል።

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመሠረቱ ጽሑፎቻችን ላይ ለሚቀርቡት ወቅታዊ የሆኑ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክሮች ምን ምላሽ እንደምንሰጥ ቆም ብለን ብናስብ እንጠቀማለን። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት የክርስቶስን ቃል እንድናስታውስ ይረዳናል። (2 ጴጥ. 3:1, 2) በዚህ መንገድ የሚቀርበውን መንፈሳዊ ምግብ አዘውትረን በመመገብ ከልብ የመነጨ አድናቆታችንን እናሳያለን። ይሁንና በአንድ ጉዳይ ላይ ተደጋጋሚ ምክር እንደተሰጠ ብናስተውል ምላሻችን ምን መሆን ይኖርበታል? ለምሳሌ ያህል፣ የአምላክ ቃል ክርስቲያኖችን “በጌታ ብቻ” እንዲያገቡ ይመክራል። (1 ቆሮ. 7:39) ስለዚህ ጉዳይ የሚያወሳ ትምህርት በመጠበቂያ ግንብ ላይ ከመቶ ለሚበልጡ ዓመታት በየተወሰነ ጊዜ ሲወጣ ቆይቷል። የክርስቶስ ወንድሞች በዚህ ጉዳይና በመንፈስ መሪነት በተሰጡ ሌሎች ምክሮች ዙሪያ ትምህርቶችን የሚያወጡት በፍቅር ተነሳስተውና ለመንፈሳዊ ደኅንነታችን በማሰብ እንደሆነ ጥርጥር የለውም። ለእነዚህ ማሳሰቢያዎች ትኩረት መስጠታችን ፍጹም መሪያችን የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን እየተከተልን እንደሆነ የምናሳይበት አንዱ መንገድ ነው።

ምሳሌ 4:18 “የጻድቃን መንገድ ሙሉ ቀን እስኪሆን ድረስ፣ ብርሃኑ እየጐላ እንደሚሄድ የማለዳ ውጋጋን ነው” በማለት ይናገራል። አዎን፣ የክርስቲያን ጉባኤ መሪ የሆነው ኢየሱስ ተከታዮቹ ሁልጊዜ አንድ ቦታ ላይ እንዲቆሙ ከማድረግ ይልቅ ማሻሻያ፣ ለውጥና ማስተካከያ እንዲኖር ያደርጋል። ከክርስቶስ ‘ወንድሞች’ ጋር የምንተባበርበት ሌላው መንገድ “ታማኝና ልባም ባሪያ” መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነቶችን በምንረዳበት መንገድ ረገድ ማስተካከያ ሲያደርግ ለመቀበል ፈቃደኛ መሆን ነው።​—ማቴ. 24:45

በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ከተሾሙት የበላይ ተመልካቾች ጋር በመተባበርም ለክርስቶስ ‘ወንድሞች’ እንደምንገዛ እናሳያለን። ሐዋርያው ጳውሎስ “ነፍሳችሁን ተግተው ስለሚጠብቁ . . . በመካከላችሁ ግንባር ቀደም ሆነው አመራር ለሚሰጧችሁ ታዘዙ እንዲሁም ተገዙ” በማለት ተናግሯል። (ዕብ. 13:17) ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሽማግሌ ቋሚ የቤተሰብ አምልኮ የምናደርግበት ምሽት መመደብ አስፈላጊ መሆኑን በተመለከተ ማበረታቻ ሊሰጠን ወይም ከአንዳንድ የመስክ አገልግሎታችን ዘርፎች ጋር በተያያዘ ምክር ሊለግሰን ይችላል። አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ደግሞ ከክርስቲያናዊ ሕይወታችን ጋር በተያያዘ በአንድ ጉዳይ ላይ ጠቃሚ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ይለግሰን ይሆናል። እንዲህ ዓይነቱን ምክር በደስታ ተቀብለን ተግባራዊ ማድረጋችን ኢየሱስን እንደ መሪያችን አድርገን እንደምንከተለው ያሳያል።

ዓለም ውጤታማ አመራር የሌለው መሆኑ ያሳዝናል። የክርስቶስን ፍቅራዊ አመራር መከተል ግን ምንኛ መንፈስን የሚያድስ ነው! እንግዲያው መሪያችንን መታዘዛችንንና እሱ በዛሬው ጊዜ እየተጠቀመባቸው ካሉት ወኪሎቹ ጋር መተባበራችንን እንቀጥል።

[በገጽ 27 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ከማያምኑ ጋር በጋብቻ እንዳንጣመር የተሰጠንን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ትቀበላለህ?