በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“የመጽሐፍ ጥቅልሎቹን በተለይም ብራናዎቹን አምጣልኝ”

“የመጽሐፍ ጥቅልሎቹን በተለይም ብራናዎቹን አምጣልኝ”

“የመጽሐፍ ጥቅልሎቹን በተለይም ብራናዎቹን አምጣልኝ”

ሐዋርያው ጳውሎስ፣ እንደ እሱ ሚስዮናዊ የሆነው ጢሞቴዎስ አንዳንድ ጽሑፎችን እንዲያመጣለት ስለፈለገ ከላይ ያለውን መልእክት ልኮለት ነበር። ጳውሎስ የጠቀሰው ስለ ምን ዓይነት ጥቅልሎችና ብራናዎች ነበር? እንዲህ ዓይነት መልእክት የላከው ለምን ነበር? ይህንን ጥያቄ ማቅረቡስ ምን ያስተምረናል?

ጳውሎስ ከላይ ያለውን ሐሳብ በጻፈበት ወቅት ይኸውም በመጀመሪያው መቶ ዘመን አጋማሽ አካባቢ፣ አይሁዳውያን በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ከሚገኙት 39 መጻሕፍት መካከል የተወሰኑትን አንድ ላይ በማጣመር እንደ 22 ወይም 24 መጻሕፍት አድርገው ይመለከቷቸው ነበር፤ ከእነዚህ መጻሕፍት አብዛኞቹ የሚገኙት በተለያዩ ጥቅልሎች ነበር። ፕሮፌሰር አለን ሚለርድ እንደተናገሩት እነዚህ ጥቅልሎች ውድ የነበሩ ቢሆንም “ሀብታም የሆኑ ሰዎች ሊያገኟቸው” ይችሉ ነበር። አንዳንድ ሰዎች፣ ከእነዚህ ጥቅልሎች መካከል ቢያንስ አንድ ይኖራቸው ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ በሠረገላው ውስጥ የመጽሐፍ ጥቅልል የነበረው ሲሆን “የነቢዩ ኢሳይያስን መጽሐፍ ድምፁን ከፍ አድርጎ እያነበበ ነበር።” ይህ ሰው “የኢትዮጵያ ንግሥት የህንደኬ ባለሥልጣንና የገንዘቧ ሁሉ ኃላፊ” ነበር። ጃንደረባው የተወሰኑ የቅዱሳን መጻሕፍት ክፍሎችን ለመግዛት የሚያስችል ሀብት ነበረው ማለት ነው።—ሥራ 8:27, 28

ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በጻፈው መልእክት ላይ “ስትመጣ በጥሮአስ፣ ካርጶስ ጋር የተውኩትን ካባ እንዲሁም የመጽሐፍ ጥቅልሎቹን በተለይም ብራናዎቹን አምጣልኝ” የሚል ሐሳብ አስፍሮ ነበር። (2 ጢሞ. 4:13) ይህም ጳውሎስ በርካታ መጻሕፍት እንደነበሩት ይጠቁማል። ሐዋርያው ካሉት መጻሕፍት ሁሉ የበለጠ ከፍ አድርጎ የሚመለከተው የአምላክን ቃል ነበር። አርኪባልድ ቶማስ ሮበርትሰን የተባሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር፣ በዚህ ጥቅስ ላይ ‘ብራናዎች’ የተባሉት “ከፓፒረስ የበለጠ ውድ በሆነው [እና ሳይበላሽ ረጅም ጊዜ በሚቆየው] በብራና ላይ የተጻፉ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ቅጂዎች ሳይሆኑ አይቀሩም” ብለዋል። ጳውሎስ ከልጅነቱ ጀምሮ ‘የተማረው’ በሕዝቡ ሁሉ ዘንድ የተከበረ የሙሴ ሕግ አስተማሪ በሆነው “በገማልያል እግር ሥር” ነበር። ይህም ሐዋርያው በጥቅልል መልክ የተዘጋጀው የአምላክ ቃል የግሉ ቅጂ ሊኖረው የቻለው ለምን እንደሆነ ለመረዳት ያስችለናል።—ሥራ 5:34፤ 22:3

ክርስቲያኖች በጥቅልሎች የሚጠቀሙት እንዴት ነበር?

አብዛኞቹ ሰዎች በጥቅልል መልክ የተዘጋጁት የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች አልነበሯቸውም። ታዲያ በዚያን ጊዜ የነበሩት አብዛኞቹ ክርስቲያኖች የአምላክን ቃል መስማትና ማንበብ የሚችሉት እንዴት ነበር? ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የጻፈለት የመጀመሪያው ደብዳቤ ፍንጭ ይሰጠናል። “እኔ እስክመጣ ድረስ በሕዝብ ፊት ለማንበብ . . . የተቻለህን ሁሉ ጥረት ማድረግህን ቀጥል” ብሎት ነበር። (1 ጢሞ. 4:13) በክርስቲያን ጉባኤዎች ውስጥ በሚደረጉት ስብሰባዎች ላይ ከሚኖሩት ፕሮግራሞች አንዱ በሕዝብ ፊት ማንበብ ሲሆን ይህም ከሙሴ ዘመን ጀምሮ በአምላክ ሕዝቦች መካከል ሲሠራበት የኖረ ልማድ ነበር።—ሥራ 13:15፤ 15:21፤ 2 ቆሮ. 3:15

ጢሞቴዎስ ሽማግሌ እንደመሆኑ መጠን ድምፁን ከፍ አድርጎ ለማንበብ “[የተቻለውን] ሁሉ ጥረት ማድረግ” ነበረበት፤ እንዲህ ማድረጉ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂ የሌላቸውን ሰዎች ለመርዳት ያስችላል። የአምላክ ቃል በሕዝብ ፊት በሚነበብበት ወቅት ሁሉም አንድም ቃል እንዳያመልጣቸው በጥሞና ያዳምጡ እንደነበር ጥርጥር የለውም፤ በተጨማሪም ወላጆችና ልጆች ወደ ቤት ከተመለሱ በኋላ በስብሰባዎች ላይ በተነበበው ሐሳብ ላይ ይወያዩ ነበር።

በብዙዎች ዘንድ የሚታወቀው በሙት ባሕር የተገኘው የኢሳይያስ ጥቅልል ርዝመቱ 7.3 ሜትር ገደማ ነው። ጥቅልሎች ጫፍና ጫፋቸው ላይ ዘንግ ስለሚኖራቸውና እንዳይበላሹ መሸፈኛ ስለሚደረግላቸው ክብደት ይኖራቸዋል። ምናልባትም አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ለስብከት ሲወጡ ብዙ ጥቅልሎችን ይዘው መሄድ ሊከብዳቸው ይችላል። ጳውሎስ በጥቅልል መልክ የተዘጋጁ አንዳንድ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች የነበሩት ቢሆንም ከቦታ ወደ ቦታ ሲጓዝ ያሉትን ጥቅልሎች ሁሉ ይዞ መሄድ አይችልም ነበር። አንዳንዶቹን ጥቅልሎች በጥሮአስ በሚኖረው ካርጶስ የተባለ ወዳጁ ዘንድ ሳይተዋቸው አልቀረም።

ጳውሎስ ከተወው ምሳሌ ምን እንማራለን?

በሮም ለሁለተኛ ጊዜ ታስሮ የነበረው ጳውሎስ፣ ጢሞቴዎስ ጥቅልሎቹን እንዲያመጣለት ከመጠየቁ በፊት እንዲህ በማለት ጽፎ ነበር፦ “መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፤ ሩጫውን እስከ መጨረሻ ሮጫለሁ፤ . . . ከዚህ በኋላ የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶ ይጠብቀኛል።” (2 ጢሞ. 4:7, 8) ጳውሎስ ይህን ሐሳብ የጻፈው ኔሮ ስደት ባስነሳበት ወቅት ይኸውም በ65 ዓ.ም. አካባቢ ሳይሆን አይቀርም። በዚህ ወቅት ሲታሰር የነበረው ሁኔታ መጥፎ ነበር። እንዲያውም የሚገደልበት ጊዜ እንደቀረበ ተሰምቶት ነበር። (2 ጢሞ. 1:16፤ 4:6) በመሆኑም ጳውሎስ ጥቅልሎቹን ለማግኘት አጥብቆ እንደሚፈልግ መግለጹ አያስገርምም። መልካሙን ገድል እስከ መጨረሻው እንደተጋደለ እርግጠኛ ቢሆንም እንደ ወትሮው ሁሉ የአምላክን ቃል በማንበብ ጥንካሬ ለማግኘት ከፍተኛ ፍላጎት ነበረው።

ጢሞቴዎስ የጳውሎስ ደብዳቤ ሲደርሰው በኤፌሶን የነበረ ይመስላል። (1 ጢሞ. 1:3) በጥሮአስ በኩል አቋርጦ ከኤፌሶን ወደ ሮም ለመሄድ 1,600 ኪሎ ሜትር ገደማ መጓዝ ይጠይቃል። ጳውሎስ በዚሁ ደብዳቤ ላይ ጢሞቴዎስን “ክረምቱ ከመግባቱ በፊት ለመምጣት የተቻለህን ሁሉ አድርግ” በማለት አሳስቦታል። (2 ጢሞ. 4:21) ጢሞቴዎስ ወደ ሮም የሚወስድ መርከብ አግኝቶ ጳውሎስ በፈለገው ጊዜ ሮም ደርሶ ይሁን አይሁን መጽሐፍ ቅዱስ የሚገልጸው ነገር የለም።

ጳውሎስ “የመጽሐፍ ጥቅልሎቹን በተለይም ብራናዎቹን አምጣልኝ” ብሎ መጠየቁ ምን ያስተምረናል? በሕይወቱ ውስጥ በጣም አስጨናቂ በሆነው በዚህ ወቅትም እንኳ ለአምላክ ቃል የነበረው ጉጉት እንደ ቀድሞው ነበር። ጳውሎስ ምንጊዜም ጥሩ መንፈሳዊ አቋም እንዲኖረው፣ በመንፈሳዊ ንቁ እንዲሆንና ለብዙዎች የብርታት ምንጭ እንዲሆን የረዳው ቁልፍ ለአምላክ ቃል የነበረው ጉጉት አይመስልህም?

በዛሬው ጊዜ የራሳችን የሆነ ሙሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ ካለን ይህ ትልቅ በረከት ነው! እንዲያውም አንዳንዶቻችን የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ እትሞችና ከአንድ በላይ መጽሐፍ ቅዱሶች አሉን። እኛም እንደ ጳውሎስ ቅዱሳን መጻሕፍትን በጥልቀት የመረዳት ጉጉት እንዲኖረን ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት ከጻፋቸው 14 ደብዳቤዎች መካከል የመጨረሻው፣ ለጢሞቴዎስ የጻፈው ሁለተኛ ደብዳቤ ነው። ሐዋርያው ከላይ ያለውን ጥያቄ ያቀረበው በደብዳቤው መደምደሚያ አካባቢ ነው። እንዲያውም ጳውሎስ “የመጽሐፍ ጥቅልሎቹን በተለይም ብራናዎቹን አምጣልኝ” በማለት ለጢሞቴዎስ የላከው መልእክት በጽሑፍ ሰፍረው ከምናገኛቸው የመጨረሻ ጥያቄዎቹ አንዱ ነው።

አንተስ ጳውሎስ እንዳደረገው መልካሙን የእምነት ገድል እስከ መጨረሻው የመጋደል ጠንካራ ፍላጎት አለህ? ጌታ እስከሚፈልገው ጊዜ ድረስ ዘወትር በይሖዋ አገልግሎት በንቃት ለመካፈልና በስብከቱ ሥራ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆን ትፈልጋለህ? ከሆነ ጳውሎስ ለክርስቲያኖች የሰጠውን ማበረታቻ ለምን ተግባራዊ አታደርግም? ከጥቅልል ይልቅ አመቺ በሆነ መልኩ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በብዙዎች እጅ የሚገኘውን መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረህ በጉጉት በማጥናት “ለራስህና ለምታስተምረው ትምህርት ምንጊዜም ትኩረት ስጥ።”—1 ጢሞ. 4:16

[በገጽ 18 እና 19 ላይ የሚገኝ ካርታ/​ሥዕል]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ኤፌሶን

ጥሮአስ

ሮም