በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ረጅም ጊዜ የፈጀው የፍርድ ቤት ክርክር በድል ተቋጨ!

ረጅም ጊዜ የፈጀው የፍርድ ቤት ክርክር በድል ተቋጨ!

ረጅም ጊዜ የፈጀው የፍርድ ቤት ክርክር በድል ተቋጨ!

ጉዳዩ የጀመረው በ1995 ሲሆን 15 ዓመታት ፈጅቷል። በእነዚህ ሁሉ ዓመታት በሩሲያ የሚኖሩ እውነተኛ ክርስቲያኖች የሃይማኖት ነፃነት ተቃዋሚ በሆኑ ግለሰቦች ጥቃት ይደርስባቸው ነበር። እነዚህ ተቃዋሚዎች የይሖዋ ምሥክሮች በሞስኮ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ቦታዎችም እንዲታገዱ ለማድረግ ቆርጠው ተነስተው ነበር። ያም ሆኖ ይሖዋ፣ በሩሲያ የሚኖሩ ውድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በፍርድ ቤት ድል እንዲያገኙ በማድረግ ለታማኝነታቸው ወሮታቸውን ከፍሏቸዋል። ይሁንና የክርክሩ መንስኤ ምን ነበር?

በመጨረሻ ነፃነት ተገኘ!

በ1990ዎቹ አጋማሽ ላይ በሩሲያ የሚኖሩ ወንድሞቻችን በ1917 ያጡትን ሃይማኖታዊ ነፃነት መልሰው አገኙ። የይሖዋ ምሥክሮች በ1991 በሶቪየት ኅብረት መንግሥት ሕጋዊ እውቅና ያለው ሃይማኖት ሆነው ተመዘገቡ። ከሶቪየት ኅብረት መፈረካከስ በኋላ ደግሞ በሩሲያ ፌዴራላዊ መንግሥት እውቅና ተሰጣቸው። ከዚህም በተጨማሪ ከበርካታ አሥርተ ዓመታት በፊት ሃይማኖታዊ ስደት የደረሰባቸው የይሖዋ ምሥክሮች የፖለቲካ ጭቆና ሰለባዎች እንደነበሩ መንግሥት አምኖ ተቀበለ። በ1993 የሞስኮ የፍትሕ ቢሮ፣ በሞስኮ ለሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ማኅበረሰብ (በዚያ አገር የምንታወቅበት ሕጋዊ መጠሪያ ነው) እውቅና ሰጠ። በዚያው ዓመት የሃይማኖት ነፃነትን የሚፈቅደው አዲሱ የሩሲያ ሕገ መንግሥትም በሥራ ላይ ዋለ። አንድ ወንድም “እንኳንስ በእውናችን በሕልማችንም እንዲህ ዓይነት ነፃነት እናገኛለን ብለን አስበን አናውቅም” ብሎ መናገሩ ምንም አያስገርምም። አክሎም “ይህ ለ50 ዓመታት ስንመኘው የነበረ ነገር ነው” በማለት ተናግሯል።

በሩሲያ የሚገኙ ወንድሞችና እህቶች የስብከቱን ሥራቸውን በማጧጧፍ ይህን ‘አመቺ የሆነ ወቅት’ በሚገባ ተጠቀሙበት፤ በርካታ ሰዎችም ምሥራቹን ተቀበሉ። (2 ጢሞ. 4:2) አንዲት ሴት “ሰዎች ስለ ሃይማኖት ለማወቅ በጣም ይፈልጉ ነበር” በማለት ተናግረዋል። ብዙም ሳይቆይ የአስፋፊዎች፣ የአቅኚዎችና የጉባኤዎች ቁጥር ከፍተኛ ጭማሪ አሳየ። እንዲያውም በ1990 ሦስት መቶ ገደማ የነበሩት በሞስኮ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች በ1995 ከ5,000 በላይ ሆኑ! በሞስኮ ያሉት የይሖዋ አገልጋዮች ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ የሃይማኖት ነፃነትን የሚቃወሙ ሰዎች ስጋት አደረባቸው። በ1990ዎቹ አጋማሽ ላይ እነዚህ ተቃዋሚዎች በፍርድ ቤቶች ክስ በመመሥረት የይሖዋ ምሥክሮችን ማጥቃት ጀመሩ። ይህ ክርክር እልባት ከማግኘቱ በፊት ለረጅም ጊዜ የተጓተቱ አራት ምዕራፎችን አልፏል።

የወንጀል ምርመራው ባልታሰበ መንገድ ተጠናቀቀ

የክርክሩ የመጀመሪያ ምዕራፍ የጀመረው ሰኔ 1995 ነበር። ከሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋር በግልጽ የሚታይ ኅብረት ያለው በሞስኮ የሚገኝ አንድ ቡድን፣ ወንድሞቻችን በወንጀል እንቅስቃሴዎች እንደሚካፈሉ የሚገልጽ ክስ መሠረተ። ቡድኑ፣ የትዳር ጓደኞቻቸው ወይም ልጆቻቸው የይሖዋ ምሥክሮች በመሆናቸው ቅሬታ ያደረባቸውን ሰዎች ወክሎ እንደሚንቀሳቀስ ገልጾ ነበር። ሰኔ 1996 የይሖዋ ምሥክሮች ጥፋተኞች እንደሆኑ የሚያረጋግጥ ማስረጃ ለማግኘት ምርመራ የተጀመረ ቢሆንም አንድም ማስረጃ ማግኘት አልተቻለም። ያም ሆኖ ይኸው ቡድን፣ ወንድሞች በወንጀል ድርጊት እንደሚሳተፉ በመግለጽ በድጋሚ ሌላ ክስ አቀረበ። መርማሪዎቹ ሌላ ምርመራ ቢያደርጉም የተሰነዘሩት ክሶች በሙሉ መሠረተ ቢስ መሆናቸው ተረጋገጠ። የሚያስገርመው ተቃዋሚዎቹ ለሦስተኛ ጊዜ ይህንኑ ክስ አቀረቡ። በዚህ ጊዜም በሞስኮ በሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ላይ ምርመራ ተካሄደ፤ ሆኖም አቃቤ ሕጓ እንደ ቀድሞው ሁሉ አሁንም የወንጀል ክስ ለመመሥረት የሚያበቃ ማስረጃ እንደሌለ ገለጸች። ተቃዋሚዎቹ ግን በዚህ ሳይበገሩ ለአራተኛ ጊዜ ያንኑ ክስ አቀረቡ፤ አሁንም አቃቤ ሕጓ ምንም ማስረጃ አላገኘችም። የሚያስደንቀው ይኸው ቡድን ሌላ ምርመራ እንዲካሄድ ጠየቀ። በመጨረሻም ሚያዝያ 13, 1998 አዲሷ መርማሪ መዝገቡ እንዲዘጋ አደረገች።

ሆኖም በጉዳዩ ውስጥ የነበሩ አንድ ጠበቃ እንደገለጹት “ግራ የሚያጋባ ነገር ተፈጸመ።” አምስተኛውን ምርመራ ያደረገችው የአቃቤ ሕጉ ቢሮ ተወካይ፣ የይሖዋ ምሥክሮች ወንጀል መፈጸማቸውን የሚያረጋግጥ ምንም ማስረጃ እንደሌለ ብትገልጽም በወንድሞቻችን ላይ የፍትሐ ብሔር ክስ እንዲመሠረት ሐሳብ አቀረበች። የአቃቤ ሕግ ቢሮ ተወካይዋ በሞስኮ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ማኅበረሰብ የአገሪቱንም ሆነ ዓለም አቀፍ ሕጎችን እንደጣሰ ተናገረች። የሰሜን ሞስኮ አስተዳደር አቃቤ ሕግ በዚህ ሐሳብ በመስማማት ክስ መሠረተ። * መስከረም 29, 1998 በሞስኮ የገለቪንስኪ አውራጃ ፍርድ ቤት ክሱን አዳመጠ። ሁለተኛው ምዕራፍ የጀመረው በዚህ ጊዜ ነበር።

መጽሐፍ ቅዱስ በችሎት ፊት

በሰሜናዊ ሞስኮ በሚገኝ ጠባብ ፍርድ ቤት ውስጥ በተካሄደው ችሎት ላይ ታትያነ ኮንድራትዬቨ የተባለች አቃቤ ሕግ፣ በ1997 የጸደቀውን ፌዴራላዊ ሕግ መሠረት በማድረግ ክስ መሠረተች፤ ይህ ሕግ ከጥንት ጀምሮ ሲወርዱ ሲዋረዱ የመጡት ሃይማኖቶች ኦርቶዶክስ፣ እስልምና፣ የአይሁድ እምነትና ቡዲዝም እንደሆኑ ይገልጻል። * ይህ ሕግ ሥራ ላይ መዋሉ ሌሎች ሃይማኖቶች ሕጋዊ እውቅና ማግኘት አስቸጋሪ እንዲሆንባቸው አድርጓል። በተጨማሪም ሕጉ፣ ጥላቻ የሚያስፋፉ ሃይማኖቶችን የማገድ መብት ለፍርድ ቤቶች ሰጥቷቸዋል። አቃቤ ሕጓ፣ የይሖዋ ምሥክሮች ጥላቻን እንደሚያስፋፉና ቤተሰብን እንደሚያናጉ የሚገልጽ የሐሰት ክስ የሰነዘረች ሲሆን ከላይ በተጠቀሰው ሕግ መሠረት መታገድ እንዳለባቸው ገለጸች።

ለወንድሞቻችን የምትከራከር አንዲት ጠበቃ፦ “ከሞስኮ ጉባኤ አባላት መካከል ሕጉን የጣሱት ግለሰቦች እነማን ናቸው?” በማለት ጠየቀች። አቃቤ ሕጓ የአንድ ሰው ስም እንኳ መጥቀስ አልቻለችም። ያም ሆኖ የይሖዋ ምሥክሮች ጽሑፎች ሃይማኖታዊ ጥላቻ እንደሚያነሳሱ ተናገረች። ለዚህ ማስረጃ እንዲሆናት ከመጠበቂያ ግንብ እና ከንቁ! መጽሔቶች እንዲሁም ከሌሎች ጽሑፎች (ከላይ ያለውን ተመልከት) ላይ አንዳንድ ሐሳቦችን አነበበች። እነዚህ ጽሑፎች ጥላቻን የሚቀሰቅሱት እንዴት እንደሆነ ስትጠየቅ “የይሖዋ ምሥክሮች እውነተኛ ሃይማኖት ያላቸው እነሱ እንደሆኑ ያስተምራሉ” በማለት መለሰች።

ጠበቃ የሆነ አንድ ወንድም ለዳኛዋና ለአቃቤ ሕጓ መጽሐፍ ቅዱስ ከሰጣቸው በኋላ “አንድ ጌታ፣ አንድ እምነት፣ አንድ ጥምቀት አለ” የሚለውን በ⁠ኤፌሶን 4:5 ላይ የሚገኘውን ጥቅስ አነበበ። ብዙም ሳይቆይ ዳኛዋ፣ አቃቤ ሕጓና ጠበቃው መጽሐፍ ቅዱስ ይዘው እንደ ዮሐንስ 17:18 እና ያዕቆብ 1:27 ባሉት ጥቅሶች ላይ መወያየት ጀመሩ። ፍርድ ቤቱ “እነዚህ ጥቅሶች ሃይማኖታዊ ጥላቻ ይቀሰቅሳሉ?” የሚል ጥያቄ አነሳ። አቃቤ ሕጓ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሐሳብ ለመስጠት ብቃት እንደሌላት ገለጸች። ጠበቃው፣ የይሖዋ ምሥክሮችን አጥብቀው የሚያወግዙ በሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የተዘጋጁ ጽሑፎችን ካሳየ በኋላ “እነዚህ ሐሳቦች ሕጉን ይተላለፋሉ?” ሲል ጠየቀ። አቃቤ ሕጓ “በሃይማኖታዊ ጉዳዮች ረገድ ሊቅ አይደለሁም” በማለት መለሰች።

አቃቤ ሕጓ መልስ አጣች

አቃቤ ሕጓ፣ የይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰብን እንደሚያናጉ ለሰነዘረችው ክስ እንደ ማስረጃ አድርጋ ያቀረበችው ገናን የመሳሰሉ በዓላትን የማያከብሩ መሆኑን ነው። ይሁንና በሩሲያ ሕግ መሠረት ገናን ማክበር ግዴታ እንዳልሆነ በኋላ ላይ አመነች። በሩሲያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮችን ጨምሮ ማንኛውም ሩሲያዊ የፈለገውን ነገር የመምረጥ ነፃነት አለው። በተጨማሪም አቃቤ ሕጓ ድርጅታችን ‘ልጆች ተገቢውን እረፍት እንዳያገኙና አስደሳች ጊዜ እንዳያሳልፉ እንደሚያደርግ’ ገልጻ ነበር። ይሁን እንጂ የይሖዋ ምሥክር ወላጆች ያሏቸውን ወጣቶች አነጋግራ ታውቅ እንደሆነ ስትጠየቅ ማንንም እንዳላነጋገረች ገለጸች። ለወንድሞቻችን የቆመችው ጠበቃ፣ አቃቤ ሕጓን በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ ተገኝታ ታውቅ እንደሆነ ስትጠይቃት “መሄድ አላስፈለገኝም” የሚል መልስ ሰጠች።

ቀጥሎም አቃቤ ሕጓ፣ አንድን የሥነ አእምሮ ፕሮፌሰር እንደ ምሥክር አድርጋ አቀረበች። ፕሮፌሰሩ ጽሑፎቻችንን ማንበብ የአእምሮ መቃወስ እንደሚያስከትል ተናገሩ። የተከሳሽ ጠበቃዋ፣ ፕሮፌሰሩ ለፍርድ ቤቱ በጽሑፍ ያቀረቡት ሐሳብ የሞስኮ የፓትሪያርክ ጽሕፈት ቤት ካቀረበው ጽሑፍ ጋር አንድ ዓይነት መሆኑን ስትገልጽ ፕሮፌሰሩ አንዳንዶቹ ሐሳቦች ጽሕፈት ቤቱ ካዘጋጀው ጽሑፍ ላይ ቃል በቃል የተገለበጡ መሆናቸውን አመኑ። ፕሮፌሰሩ ተጨማሪ ጥያቄዎች ሲቀርቡላቸው፣ የይሖዋ ምሥክር የሆነ አንድም ታካሚ ኖሯቸው እንደማያውቅ ግልጽ ሆነ። ከዚህ በተቃራኒ በሞስኮ በሚገኙ ከ100 በላይ የይሖዋ ምሥክሮች ላይ ጥናት ያካሄዱ ሌላ የሥነ አእምሮ ፕሮፌሰር ለፍርድ ቤቱ የምሥክርነት ቃላቸውን ሰጥተው ነበር። እኚህ ፕሮፌሰር፣ ጥናት ያካሄዱባቸው ሰዎች በጥሩ አእምሯዊ ጤንነት ላይ እንደሚገኙና የይሖዋ ምሥክሮች ከሆኑ በኋላ ከሌሎች ሃይማኖቶች ጋር ይበልጥ ተቻችለው መኖር እንደጀመሩ ተናግረዋል።

ድል ቢገኝም ክርክሩ ግን አላበቃም

መጋቢት 12, 1999 ዳኛዋ የይሖዋ ምሥክሮችን ጽሑፎች እንዲመረምሩ አምስት ምሑራንን ከሾሙ በኋላ የፍርድ ሂደቱ ለጊዜው እንዲቆም አደረጉ። ይህ ከመሆኑ በፊት የሩሲያ ፌዴራላዊ መንግሥት የፍትሕ ሚኒስቴር፣ የተወሰኑ ምሑራንን ያቀፈ አንድ ቡድን ጽሑፎቻችንን እንዲመረምር አዝዞ ነበር። በፍትሕ ሚኒስቴሩ የተሾመው ይህ ቡድን በጽሑፎቻችን ላይ አንድም ጎጂ ነገር እንዳላገኘ ሚያዝያ 15, 1999 ሪፖርት አደረገ። በመሆኑም የፍትሕ ሚኒስቴሩ፣ የይሖዋ ምሥክሮች በሩሲያ ውስጥ ሕጋዊ እውቅና ያለው ሃይማኖት እንዲሆኑ የተሰጣቸውን ፈቃድ ሚያዝያ 29, 1999 አደሰላቸው። ያም ሆኖ የሞስኮው ፍርድ ቤት፣ የመረጣቸው ምሑራን ጽሑፎቻችንን መመርመራቸውን እንዲቀጥሉ ትእዛዝ ሰጠ። ይህም ግራ የሚያጋባ ሁኔታ ፈጠረ፤ የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖት ሕግ አክባሪና በመንግሥት የታወቀ እንደሆነ ተደርጎ በአገር አቀፍ ደረጃ በሩሲያ የፍትሕ ሚኒስቴር ተቀባይነት ቢያገኝም የሞስኮ የፍትሕ ቢሮ የይሖዋ ምሥክሮች ሕግ ተላልፈዋል በሚል ምርመራ እያካሄደባቸው ነበር።

ችሎቱ እንደገና የታየው ከሁለት ዓመት ገደማ በኋላ ሲሆን የካቲት 23, 2001 የሌና ፕሮሆሪቼቨ የተባሉት ዳኛ ብይን ሰጡ። ዳኛዋ የሾሟቸው ምሑራን ያቀረቡትን ሪፖርት ከመረመሩ በኋላ የሚከተለውን ፍርድ አስተላለፉ፦ “በሞስኮ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ማኅበረሰብ እንዲፈርስ ወይም እንቅስቃሴው እንዲታገድ የሚያደርግ ምንም ምክንያት የለም።” በመጨረሻም ወንድሞቻችን ከተከመረባቸው ክስ በሙሉ ነፃ መሆናቸው በፍርድ ቤት ተረጋገጠ! ይሁንና አቃቤ ሕጓ ብይኑን ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆኗ ለሞስኮ ከተማ ፍርድ ቤት ይግባኝ አለች። ከሦስት ወራት በኋላ ማለትም ግንቦት 30, 2001 የሞስኮ ከተማ ፍርድ ቤት የዳኛ ፕሮሆሪቼቨን ውሳኔ ሻረው። ይህ ፍርድ ቤት ጉዳዩ በሌላ ዳኛ በድጋሚ እንዲታይ ትእዛዝ አስተላለፈ፤ ይሁንና አቃቤ ሕጓ አልተለወጠችም። አሁን ጉዳዩ ወደ ሦስተኛው ምዕራፍ ተሸጋገረ።

በክርክሩ ብንረታም ጉዳዩ አላበቃም

ጥቅምት 30, 2001 ቬረ ዱቢንስካየ የተባሉ ዳኛ ጉዳዩን በድጋሚ መመልከት ጀመሩ። * አቃቤ ሕግ ኮንድራትዬቨ፣ የይሖዋ ምሥክሮች ጥላቻ ያስፋፋሉ የሚለውን ክስ እንደገና አነሳች፤ አክላም የይሖዋ ምሥክሮች ሕጋዊ ማኅበረሰብ መታገዱ በሞስኮ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችን መብት ለማስጠበቅ እንደሚረዳ ገለጸች። ወዲያውኑ በሞስኮ የሚገኙት 10,000 የይሖዋ ምሥክሮች በሙሉ አቃቤ ሕጓ የይሖዋ ምሥክሮችን “መብት ለማስጠበቅ” በሚል ያቀረበችውን ከእውነት የራቀ ሐሳብ ፍርድ ቤቱ እንዳይቀበለው በመጠየቅ ፊርማቸውን ያሰፈሩበትን ሰነድ አቀረቡ።

አቃቤ ሕጓ፣ የይሖዋ ምሥክሮች ሕግ እንደተላለፉ የሚያረጋግጥ ማስረጃ ማቅረብ እንደማያስፈልጋት ተናገረች። ክሱ የተነሳው የይሖዋ ምሥክሮችን እንቅስቃሴ በሚመለከት ሳይሆን ከጽሑፎቻቸውና ከሚያምኑባቸው ነገሮች ጋር በተያያዘ እንደሆነ ገለጸች። ከዚያም የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቃል አቀባይ የሆነውን ግለሰብ እንደ ምሥክር አድርጋ እንደምታቀርብ ተናገረች። ይህን ማለቷ ቀሳውስቱ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ እገዳ እንዲጣል በሚደረገው ጥረት ውስጥ እጃቸው እንዳለበት የሚያረጋግጥ ነው። ዳኛዋ የተወሰኑ ምሑራንን ያቀፈ አንድ ቡድን የይሖዋ ምሥክሮችን ጽሑፎች አሁንም በድጋሚ እንዲመረምር ግንቦት 22, 2003 ትእዛዝ ሰጡ።

የካቲት 17, 2004 የምሑራኑ ቡድን ያቀረበውን ሪፖርት ለማየት ችሎቱ እንደገና ተሰየመ። ጽሑፎቻችን፣ ሰዎች “የቤተሰብ ሕይወታቸውን አስደሳች ለማድረግና የጋብቻ ትስስራቸውን ለማጠናከር” እንዲጥሩ እንደሚያበረታቱ ምሑራኑ ተናገሩ፤ አክለውም ጽሑፎቻችን ጥላቻን ያስፋፋሉ የሚለው ክስ “መሠረተ ቢስ እንደሆነ” ገለጹ። ሌሎች ምሑራንም በዚህ ሐሳብ ተስማምተዋል። አንድ የሃይማኖት ታሪክ ፕሮፌሰር “የይሖዋ ምሥክሮች የሚሰብኩት ለምንድን ነው?” የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር። ፕሮፌሰሩ ለፍርድ ቤቱ እንዲህ የሚል መልስ ሰጥተዋል፦ “ለአንድ ክርስቲያን መስበክ ግዴታው ነው። ወንጌሎች የሚናገሩት ይህንን ነው፤ ክርስቶስም ለደቀ መዛሙርቱ ‘ሂዱና በምድር ዙሪያ ስበኩ’ የሚል ተልእኮ ሰጥቷቸዋል።” ያም ሆኖ መጋቢት 26, 2004 ዳኛዋ በሞስኮ የሚገኙትን የይሖዋ ምሥክሮች እንቅስቃሴ አገዱ። ሰኔ 16, 2004 ደግሞ የሞስኮ ከተማ ፍርድ ቤት ይህን ውሳኔ ደገፈው። * አንድ የቆዩ የይሖዋ ምሥክር ውሳኔውን አስመልክተው እንዲህ ብለዋል፦ “በሶቪየት ኅብረት አገዛዝ ወቅት ሩሲያውያን አምላክ የለሽ መሆን ነበረባቸው። ዛሬ ደግሞ ሩሲያውያን ኦርቶዶክስ መሆን ይጠበቅባቸዋል።”

ታዲያ ወንድሞች ይህ እገዳ ሲጣልባቸው ምን አደረጉ? በጥንት ዘመን የነበረውን የነህምያን ምሳሌ ተከትለዋል። በዚያን ጊዜ የአምላክ ሕዝብ ጠላቶች፣ ነህምያ የኢየሩሳሌምን ቅጥር በድጋሚ ለመገንባት የሚያደርገውን ጥረት ተቃውመው ነበር፤ ያም ቢሆን ነህምያም ሆነ ሕዝቡ ያጋጠማቸው ማንኛውም ዓይነት ተቃውሞ ሥራቸውን እንዲያስተጓጉልባቸው አልፈቀዱም። ከዚህ ይልቅ ‘ቅጥሩን መገንባታቸውን’ እና ‘ሥራውን ከልባቸው መሥራታቸውን ቀጠሉ።’ (ነህ. 4:1-6) በተመሳሳይም በሞስኮ የሚገኙት ወንድሞቻችን ተቃዋሚዎች የሰነዘሩት ጥቃት በዛሬው ጊዜ መከናወን ያለበትን ሥራ ይኸውም ምሥራቹን የመስበክ ሥራቸውን እንዲያስተጓጉልባቸው አልፈቀዱም። (1 ጴጥ. 4:12, 16) ይሖዋ እንደሚደግፋቸው እርግጠኞች ነበሩ፤ እንዲሁም ረጅም ጊዜ የፈጀውን የዚህን ክርክር አራተኛ ምዕራፍ ለመጀመር ተዘጋጅተው ነበር።

ጥቃቱ ጨመረ

ነሐሴ 25, 2004 ወንድሞቻችን በወቅቱ የሩሲያ ፕሬዚዳንት ለነበሩት ቭለዲሚር ፑቲን አቤቱታ አቀረቡ። በ76 ጥራዞች የተካተቱ 315,000 ፊርማዎችን የያዘው ይህ አቤቱታ ወንድሞች እገዳው በጥልቅ እንዳሳሰባቸው የሚገልጽ ነበር። በዚህ መሃል የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቀሳውስት እውነተኛ ማንነት በግልጽ ታየ። የሞስኮ ፓትሪያርክ ጽሕፈት ቤት ቃል አቀባይ “የይሖዋ ምሥክሮችን እንቅስቃሴ በጥብቅ እንቃወማለን” ብሎ ነበር። አንድ የእስልምና ሃይማኖት መሪ ደግሞ እገዳው “ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው ጥሩ እርምጃ” እንደሆነ ተናግረዋል።

የተወሰደው እርምጃ ትክክል እንደሆነ የተሰማቸው አንዳንድ ሩሲያውያን፣ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ጥቃት ለመሰንዘር የልብ ልብ ተሰማቸው። በሞስኮ የሚገኙ አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች በስብከቱ ሥራ ላይ እያሉ ተቃዋሚዎች ደበደቧቸው። በቁጣ የተሞላ አንድ ሰው አንዲትን እህት ከሕንፃ ውስጥ አባርሮ ጀርባዋን በእርግጫ ሲመታት ወደቀች፤ በዚህ ጊዜ ጭንቅላቷ ላይ ጉዳት ስለደረሰባት የሕክምና እርዳታ ማግኘት አስፈልጓት ነበር። ይሁንና ፖሊሶች ጥቃቱን በሰነዘረው ግለሰብ ላይ ምንም እርምጃ አልወሰዱም። ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ደግሞ በፖሊሶች ተይዘው የጣት አሻራቸው ከተወሰደና ፎቶግራፍ ከተነሱ በኋላ ማረፊያ ቤት እንዲያድሩ ተደርገዋል። በሞስኮ የሚገኙ የመሰብሰቢያ አዳራሾች ኃላፊ የሆኑ ሰዎች ለይሖዋ ምሥክሮች አዳራሾቻቸውን ማከራየታቸውን ከቀጠሉ ከሥራ እንደሚባረሩ ዛቻ ተሰንዝሮባቸው ነበር። ብዙም ሳይቆይ በርካታ ጉባኤዎች በኪራይ ያገኙትን የመሰብሰቢያ ቦታ አጡ። አራት አዳራሾች ባሉት አንድ የመንግሥት አዳራሽ ውስጥ 40 ጉባኤዎች ለመሰብሰብ ተገድደው ነበር። በዚህ ሕንፃ ውስጥ ካሉት አዳራሾች በአንዱ ውስጥ የሚሰበሰብ አንድ ጉባኤ ሕዝባዊ ስብሰባውን ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ተኩል ላይ መጀመር ነበረበት። “አስፋፊዎቹ በስብሰባው ላይ ለመገኘት ከማለዳው አሥራ አንድ ሰዓት ከእንቅልፋቸው መነሳት ነበረባቸው፤ ሆኖም ከአንድ ዓመት ለሚበልጥ ጊዜ ይህን በፈቃደኝነት ሲያደርጉ ቆይተዋል” በማለት አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ተናግሯል።

“ምሥክር ይሆናል”

ጠበቆቻችን፣ በሞስኮ የተጣለው እገዳ ተገቢ አለመሆኑን ለማሳየት ሲሉ ታኅሣሥ 2004 ጉዳዩን ለአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት አቀረቡት። (“በሩሲያ የተላለፈው ፍርድ ፈረንሳይ ውስጥ የታየው ለምንድን ነው?” የሚለውን በገጽ 6 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።) ከስድስት ዓመታት በኋላ ይኸውም ሰኔ 10, 2010 የአውሮፓው ፍርድ ቤት፣ የይሖዋ ምሥክሮች ከተሰነዘረባቸው ክስ ሙሉ በሙሉ ነፃ መሆናቸውን በሙሉ ድምፅ ወሰነ! * ፍርድ ቤቱ በእኛ ላይ የቀረቡትን ክሶች በሙሉ ከመረመረ በኋላ ጨርሶ መሠረተ ቢስ ሆነው አግኝቷቸዋል። በተጨማሪም ሩሲያ፣ በአገሪቱ የሚፈጸመውን የሕግ ጥሰት የማስቆምና በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የደረሰውን ችግር ለማስተካከል ማንኛውንም እርምጃ የመውሰድ ሕጋዊ ግዴታ እንዳለባት ችሎቱ ገልጿል።​—“የፍርድ ቤቱ ብይን” የሚለውን በገጽ 8 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።

የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ ለይሖዋ ምሥክሮች የሚሰጣቸውን ከለላ በተመለከተ ፍርድ ቤቱ ያስተላለፈው ግልጽ ውሳኔ ተፈጻሚነት የሚኖረው በሩሲያ ብቻ ሳይሆን የአውሮፓ ምክር ቤት አባላት በሆኑት 46 ሌሎች አገሮች ውስጥ ጭምር ነው። ከዚህም በላይ ክሱ የተመሠረተው ከተለያዩ ጉዳዮች አንጻር በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ያስተላለፈው ውሳኔ ሕጉ በእነዚህ ጉዳዮች ረገድ ምን እንደሚል በስፋትና በጥልቀት የሚዳስስ ነው፤ በመሆኑም ይህ ውሳኔ የሕግ ምሑራንን፣ የዳኞችን፣ የሕግ አርቃቂዎችንና በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎችን ትኩረት ይስባል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ፍርድ ቤቱ እዚህ ውሳኔ ላይ ሲደርስ ከዚህ ቀደም ይኸው ችሎት ለይሖዋ ምሥክሮች የፈረደላቸውን ስምንት ውሳኔዎች ብቻ ሳይሆን የይሖዋ ምሥክሮች በሩሲያ፣ በስፔን፣ በአርጀንቲና፣ በካናዳ፣ በዩናይትድ ስቴትስ፣ በዩናይትድ ኪንግደም፣ በደቡብ አፍሪካና በጃፓን ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ያገኟቸውን ዘጠኝ ድሎችም እንደ ምሳሌ ጠቅሷል። እነዚህ ጉዳዮች መጠቀሳቸው እንዲሁም የአውሮፓው ፍርድ ቤት፣ የሞስኮ አቃቤ ሕግ ያቀረበቻቸውን ክሶች ሙሉ በሙሉ ውድቅ ማድረጉ በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ስለ እምነታቸውና እንቅስቃሴዎቻቸው መከላከያ ለማቅረብ የሚያስችል ጠንካራ ድጋፍ ሰጥቷቸዋል።

ኢየሱስ ተከታዮቹን “በእኔ ምክንያት በገዥዎችና በነገሥታት ፊት ያቀርቧችኋል፤ ይህም ለእነሱም ሆነ ለአሕዛብ ምሥክር ይሆናል” ብሏቸዋል። (ማቴ. 10:18) ላለፉት 15 ዓመታት የተካሄደው የፍርድ ቤት ክርክር ወንድሞቻችን በሞስኮና በሌሎች ቦታዎች የይሖዋን ስም ከመቼውም ጊዜ የበለጠ እንዲያሳውቁ አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል። በይሖዋ ምሥክሮች ላይ በተካሄደው ምርመራ፣ በፍርድ ቤቱ ሂደት እንዲሁም በተለያዩ አገሮች ላይ ሥልጣን ያለው ፍርድ ቤት ባስተላለፈው ብይን የተነሳ ለወንድሞቻችን የተሰጠው ትኩረት “ምሥክር” ከመሆኑም ሌላ “ምሥራቹ . . . ይበልጥ እንዲስፋፋ” አስተዋጽኦ አድርጓል። (ፊልጵ. 1:12) በሞስኮ የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች በአሁኑ ጊዜ በስብከቱ ሥራ ሲካፈሉ ብዙዎች “እናንተ ሰዎች ግን አልታገዳችሁም እንዴ?” ይሏቸዋል። ብዙውን ጊዜ ይህ ጥያቄ መነሳቱ ወንድሞቻችን ስለ እምነታችን ለሰዎች ሰፋ ያለ ማብራሪያ እንዲሰጡ አጋጣሚ ይከፍትላቸዋል። ከዚህ በግልጽ መመልከት እንደሚቻለው ማንኛውም ኃይል የስብከቱን ሥራችንን እንዳናከናውን ሊያግደን አይችልም። ይሖዋ፣ ደፋር የሆኑትን ውድ የሩሲያ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን መባረኩንና ማጠንከሩን እንዲቀጥል እንጸልያለን።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.8 ክሱ የተመሠረተው ሚያዝያ 20, 1998 ነበር። ከሁለት ሳምንት በኋላ ማለትም ግንቦት 5 ሩሲያ የአውሮፓን የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ ተቀበለች።

^ አን.10 “ይህ ሕግ እንዲረቅቅ የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ ጫና አሳድራለች፤ ቤተ ክርስቲያኗ በሩሲያ ያላትን ቦታ ለማስጠበቅ የምትጥር ከመሆኑም ሌላ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ እገዳ እንዲጣል ከፍተኛ ፍላጎት አላት።”​—አሶሺዬትድ ፕሬስ፣ ሰኔ 25, 1999

^ አን.20 በጣም የሚያስገርመው ይህ ዕለት የይሖዋ ምሥክሮች በሶቪየት አገዛዝ ሥር የሃይማኖታዊ ጭቆና ሰለባዎች እንደነበሩ የሩሲያ መንግሥት አምኖ የተቀበለበት አሥረኛ ዓመት ነበር።

^ አን.22 ይህ እገዳ በሞስኮ ያሉትን ጉባኤዎች የሚወክለው ሕጋዊ ድርጅት እንዲፈርስ ያደርጋል። ተቃዋሚዎቹ እገዳው ወንድሞቻችን አገልግሎታቸውን እንዳያከናውኑ እንቅፋት እንደሚፈጥርባቸው ተስፋ አድርገው ነበር።

^ አን.28 ሩሲያ ከአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት በላይ ያለው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጉዳዩን በድጋሚ እንዲያየው ጠየቀች። ይሁንና ኅዳር 22, 2010 ከዚህ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተውጣጡ አምስት ዳኞች ጉዳዩ በድጋሚ እንደማይታይ ውሳኔ አስተላለፉ። ፍርድ ቤቱ ይህን ሲል ሰኔ 10, 2010 የተላለፈው ውሳኔ የመጨረሻ እንደሆነና ተግባራዊ መሆን እንዳለበት መግለጹ ነበር።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

በሩሲያ የተላለፈው ፍርድ ፈረንሳይ ውስጥ የታየው ለምንድን ነው?

የካቲት 28, 1996 ሩሲያ የአውሮፓን የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ ፈረመች። (ግንቦት 5, 1998 ሩሲያ ድንጋጌውን መቀበሏን ገለጸች።) የሩሲያ መንግሥት ይህን ሰነድ ሲፈርም ዜጎቹ የሚከተሉት መብቶች እንዳሏቸው መግለጹ ነበር፦

‘የሃይማኖት ነፃነት፣ ሃይማኖታቸውን በቤታቸው ወይም በይፋ የማራመድ እንዲሁም ከፈለጉ ሃይማኖታቸውን የመለወጥ መብት።’​—አንቀጽ 9

‘ተጠያቂነት እንዳለባቸው መገንዘባቸውን በሚያሳይ መልኩ ሐሳባቸውን የመናገር ወይም የመጻፍ እንዲሁም ለሌሎች መረጃ የመስጠት መብት።’​—አንቀጽ 10

‘ሰላማዊ በሆኑ ስብሰባዎች ላይ የመገኘት መብት።’​—አንቀጽ 11

እነዚህ መብቶች ያልተከበሩላቸው ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች በአገራቸው ውስጥ ያሉት የፍትሕ አካላት በሙሉ መፍትሔ ሊያስገኙላቸው ካልቻሉ በስትራዝቡር፣ ፈረንሳይ ለሚገኘው የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ጉዳያቸውን ማቅረብ ይችላሉ። (ከላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት) ይህ ፍርድ ቤት፣ የአውሮፓን የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ በፈረሙት አገሮች ቁጥር መሠረት 47 ዳኞችን ያቀፈ ነው። ፍርድ ቤቱ የሚያደርጋቸው ወሳኔዎች የጸኑ ይሆናሉ። ስምምነቱን የፈረሙት አገሮች ውሳኔዎቹን በሥራ ላይ የማዋል ግዴታ አለባቸው።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የፍርድ ቤቱ ብይን

ፍርድ ቤቱ ካስተላለፋቸው ውሳኔዎች መካከል ሦስቱ ከዚህ በታች በአጭሩ ቀርበዋል፦

አንደኛው ክስ የይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰብን እንደሚያፈራርሱ የሚገልጽ ነበር። ፍርድ ቤቱ ይህ እውነት እንዳልሆነ በመግለጽ የሚከተለውን ውሳኔ አስተላለፈ፦

“የግጭቱ መንስኤ፣ ሃይማኖተኛ ያልሆኑት የቤተሰብ አባላት ዘመዳቸው ሃይማኖቱን የመግለጽና የመተግበር መብት እንዳለው ለመቀበልና ይህን መብቱን ለማክበር ፈቃደኛ አለመሆናቸው ነው።”​—አን. 111

ፍርድ ቤቱ የይሖዋ ምሥክሮች፣ ሰዎች በራሳቸው ምርጫ እንዳይመሩ ያደርጋሉ የሚለውን ክስ የሚደግፍ ምንም ማስረጃ እንዳላገኘ የገለጸ ሲሆን እንዲህ ብሏል፦

“[የሩሲያ] ፍርድ ቤቶች በዚህ መንገድ የሕሊና ነፃነቱ የተጣሰበት የአንድም ሰው ስም አለመጥቀሳቸው [የአውሮፓውን] ፍርድ ቤት አስገርሞታል።”​—አን. 129

ሌላው ክስ ደግሞ የይሖዋ ምሥክሮች ደም ስለማይወስዱ የእምነቱ ተከታዮች ጤንነት አደጋ ላይ እንዲወድቅ ያደርጋሉ የሚል ነው። ፍርድ ቤቱ ይህን ክስ ውድቅ በማድረግ እንዲህ የሚል ውሳኔ አስተላልፏል፦

“አንድን ዓይነት ሕክምና የመቀበል ወይም ያለመቀበል እንዲሁም አማራጭ የሕክምና ዘዴዎችን ለመጠቀም የመወሰን ነፃነት፣ የራስን ውሳኔ ወይም ምርጫ ከማድረግ መብት ጋር የተያያዘ ነው። በጥሩ የአእምሮ ጤንነት ላይ የሚገኝ አዋቂ ሰው የራሱ ምርጫ የማድረግ ነፃነት አለው፤ ለምሳሌ ቀዶ ሕክምና ለማድረግ ወይም አንድን ዓይነት ሕክምና ለመቀበል ሊስማማ ወይም ላይስማማ እንደሚችል ሁሉ ደም ለመውሰድ ወይም ላለመውሰድም ሊወስን ይችላል።”​—አን. 136