በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቀለል ባለ እንግሊዝኛ የተዘጋጀ አዲስ የመጠበቂያ ግንብ እትም

ቀለል ባለ እንግሊዝኛ የተዘጋጀ አዲስ የመጠበቂያ ግንብ እትም

ቀለል ባለ እንግሊዝኛ የተዘጋጀ አዲስ የመጠበቂያ ግንብ እትም

ከዚህ የመጠበቂያ ግንብ የጥናት እትም ጀምሮ በየወሩ ከመደበኛው የጥናት እትም በተጨማሪ ቀለል ባለ እንግሊዝኛ የሚዘጋጅ እትም ለሙከራ ያህል ለአንድ ዓመት እንደሚታተም ስናሳውቃችሁ ደስ ይለናል! ይህ እትም የጥናት ርዕሶችንና ቦታ ካለ ደግሞ ሌሎች የተመረጡ ርዕሶችን ይዞ ይወጣል። ይህ ዝግጅት የብዙ የይሖዋ ምሥክሮችን መንፈሳዊ ፍላጎት እንደሚያሟላ ተስፋ እናደርጋለን። ይሁንና ይህን እትም ማዘጋጀት ያስፈለገው ለምንድን ነው?

እንደ ላይቤሪያ፣ ናይጄሪያ፣ ኬንያ፣ የሰለሞን ደሴቶች፣ ጋና፣ ፊጂና ፓፑዋ ኒው ጊኒ ባሉት አገሮች የሚኖሩ ወንድሞቻችን የዕለት ተዕለት መግባቢያ ቋንቋቸው እንግሊዝኛ ነው። በእነዚህ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ወንድሞች በአካባቢያቸው በሚነገሩ ሌሎች ቋንቋዎች ወይም በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የሚጠቀሙ ቢሆንም በጉባኤ ስብሰባዎችም ሆነ በመስክ አገልግሎት ላይ አዘውትረው የሚጠቀሙት እንግሊዝኛን ነው። ይሁንና እነዚህ ወንድሞች የሚናገሩት እንግሊዝኛ በጽሑፎቻችን ላይ ከምንጠቀምበት ይበልጥ ቀለል ያለ ነው። ሌሎች የይሖዋ ሕዝቦች ደግሞ እንግሊዝኛን በደንብ መረዳት ባይችሉም ወደ ሌላ አገር በመዛወራቸው ምክንያት እንግሊዝኛን እንደ መግባቢያ ቋንቋ ለመጠቀም ይገደዳሉ። ከዚህም በተጨማሪ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በሚመሩ የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት አይችሉም።

በየሳምንቱ በመጠበቂያ ግንብ ጥናት ወቅት የምናጠናቸው ርዕሶች ወቅታዊ የሆነ መንፈሳዊ ምግብ የምናገኝባቸው ዋነኛ መንገዶች ናቸው። በስብሰባው ላይ የሚገኙ ሁሉ ከሚጠናው ጽሑፍ የተሟላ ጥቅም ማግኘት እንዲችሉ ቀለል ባለ እንግሊዝኛ የተዘጋጀው እትም ከባድ ያልሆነ ሰዋስውና ያልተወሳሰበ የዓረፍተ ነገር አወቃቀር የሚጠቀም ከመሆኑም ሌላ ቃላት አያበዛም። ይህ አዲስ እትም ለየት ያለ ሽፋን ይኖረዋል። በጥናት ርዕሶቹ ውስጥ ያሉት ንዑስ ርዕሶች፣ አንቀጾች፣ የክለሳ ጥያቄዎችና ሥዕሎች ከመደበኛው እትም እምብዛም አይለዩም። በመሆኑም በመጠበቂያ ግንብ ጥናት ወቅት መደበኛውንም ሆነ ቀለል ያለውን እትም የያዙ ሰዎች አንድ ላይ መከታተልና ተሳትፎ ማድረግ ይችላሉ። በሁለቱ እትሞች መካከል ያለውን ልዩነት ለመመልከት እንዲቻል ከዚህ መጠበቂያ ግንብ የመጀመሪያ የጥናት ርዕስ አንቀጽ 2 ላይ የተወሰደ ሐሳብ ከታች እንደ ምሳሌ ቀርቧል።

ይህ አዲስ ዝግጅት፣ ይሖዋን “ትእዛዛትህን እንድማር ማስተዋልን ስጠኝ” ብለው ለለመኑ በርካታ ሰዎች የጸሎታቸው መልስ እንደሚሆን እንተማመናለን። (መዝ. 119:73) እንግሊዝኛ ተናጋሪ የሆኑ አንዳንድ ልጆችን ጨምሮ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታቸው ውስን የሆኑ ሰዎች በየሳምንቱ ለሚደረገው የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ዝግጅት ሲያደርጉ ይህ እትም እንደሚረዳቸው ተስፋ እናደርጋለን። ይሖዋ ‘ለመላው የወንድማማች ማኅበር ባለው ፍቅር’ ተነሳስቶ ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ በመጠቀም የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ እያቀረበልን በመሆኑ እናመሰግነዋለን።​—1 ጴጥ. 2:17፤ ማቴ. 24:45

የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል