በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋን ፍቅራዊ አመራር ትከተላለህ?

የይሖዋን ፍቅራዊ አመራር ትከተላለህ?

የይሖዋን ፍቅራዊ አመራር ትከተላለህ?

“የሐሰትን መንገድ ሁሉ ጠላሁ።”​—መዝ. 119:128

1, 2. (ሀ) ያሰብከው ቦታ ለመድረስ አቅጣጫ በምትጠይቅበት ወቅት ምን ዓይነት ማስጠንቀቂያ ቢሰጥህ ደስ ይልሃል? ለምንስ? (ለ) ይሖዋ፣ ለአገልጋዮቹ ምን ዓይነት ማስጠንቀቂያዎችን ይሰጣል? ለምንስ?

አንድ ቦታ ለመሄድ አስበሃል እንበል። መንገዱን የሚያውቅና የምትተማመንበት አንድ ጓደኛህ አቅጣጫ እንዲጠቁምህ ጠየቅኸው። ጓደኛህ የምትሄድበትን አቅጣጫ ጥሩ አድርጎ ከጠቆመህ በኋላ “እዚያ ጋ ያለው ምልክት ስለሚያሳስት ተጠንቀቅ፤ ብዙ ሰዎች ያንን ምልክት ተከትለው ሲሄዱ መንገዳቸውን ስተው ጠፍተዋል” ይልህ ይሆናል። ጓደኛህ ያሳየህን አሳቢነት አታደንቅም? ማስጠንቀቂያውንስ ሰምተህ ተግባራዊ አታደርግም? በአንዳንድ መንገዶች ይሖዋ ከዚህ ወዳጅህ ጋር ይመሳሰላል። ይሖዋ፣ ሁላችንም ያሰብንበት ቦታ ላይ መድረስ ይኸውም የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንዴት እንደምንችል የሚጠቁሙ ጥሩ ምልክቶችን ይሰጠናል። ከዚህም በላይ የተሳሳተ ጎዳና እንድንከተል ሊያደርጉን ስለሚችሉ መጥፎ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ነገሮች ያስጠነቅቀናል።​—ዘዳ. 5:32፤ ኢሳ. 30:21

2 ወዳጃችን የሆነው ይሖዋ አምላክ፣ ተጽዕኖ ሊያሳድሩብን የሚችሉ አንዳንድ ነገሮችን በተመለከተ የሰጠንን ማስጠንቀቂያዎች በዚህና በሚቀጥለው የጥናት ርዕስ ላይ እንመረምራለን። ይሖዋ እንዲህ ዓይነት ማስጠንቀቂያ የሚሰጠን ለእኛ ባለው አሳቢነትና ፍቅር ተገፋፍቶ እንደሆነ እናስታውስ። ያሰብንበት ቦታ እንድንደርስ ይፈልጋል። ሰዎች በመጥፎ ተጽዕኖ ተሸንፈው አቅጣጫቸውን ሲስቱ ማየት በጣም ያሳዝነዋል። (ሕዝ. 33:11) በዚህ የጥናት ርዕስ ላይ መጥፎ ተጽዕኖ ከሚያሳድሩብን ነገሮች መካከል ሦስቱን እንመለከታለን። አንደኛው ተጽዕኖ የሚመጣው ከሌሎች ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከራሳችን የሚመጣ ነው። ሦስተኛው እውን ያልሆኑ ነገሮች የሚያሳድሩብን ተጽዕኖ ነው፤ ይህ ተጽዕኖ እውን ባይሆንም በጣም አደገኛ ነው። እነዚህ ተጽዕኖዎች ምን እንደሆኑና በሰማይ ያለው አባታችን ይህን ተጽዕኖ ለመቋቋም እንድንችል የሚያሠለጥነን እንዴት እንደሆነ ማወቅ ያስፈልገናል። አንድ መዝሙራዊ “የሐሰትን መንገድ ሁሉ ጠላሁ” በማለት በአምላክ መንፈስ መሪነት ጽፏል። (መዝ. 119:128) አንተስ እንዲህ ይሰማሃል? ‘ከሐሰት መንገድ ሁሉ’ ለመራቅ ቁርጥ ያለ አቋም መውሰድ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

“ብዙዎችን አትከተል”

3. (ሀ) በየትኛው አቅጣጫ መሄድ እንዳለብን እርግጠኛ በማንሆንበት ጊዜ ሌሎች ተጓዦችን መከተል አደገኛ ሊሆን የሚችለው ለምንድን ነው? (ለ) በ⁠ዘፀአት 23:2 ላይ ምን ጠቃሚ መሠረታዊ ሥርዓት እናገኛለን?

3 ወደ ሩቅ ቦታ ለመጓዝ ስትነሳ በየትኛው አቅጣጫ መሄድ እንዳለብህ እርግጠኛ ባትሆን ምን ታደርጋለህ? ምናልባት ሌሎች ተጓዦችን ለመከተል ትፈተን ይሆናል፤ በተለይ ደግሞ ብዙዎች በአንድ አቅጣጫ እንደሚጓዙ ስታይ ይህን ለማድረግ ይቃጣህ ይሆናል። ይሁንና ይህ ዓይነቱ አካሄድ አደገኛ ነው። እነዚህ ሰዎች የሚሄዱት አንተ ወዳሰብከው ቦታ ላይሆን ይችላል፤ አሊያም እነሱ ራሳቸው መንገዱን አያውቁት ይሆናል። ከዚህ ጋር በተያያዘ፣ ለጥንቶቹ እስራኤላውያን ከተሰጣቸው አንድ ሕግ በስተጀርባ ያለውን መሠረታዊ ሥርዓት እንመልከት። ዳኞች ወይም የፍርድ ጉዳዮችን በሚመለከቱ ነገሮች ላይ የምሥክርነት ቃል የሚሰጡ ሰዎች ‘ብዙዎችን መከተል’ ያለውን አደጋ የሚገልጽ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ነበር። (ዘፀአት 23:2ን አንብብ።) ፍጹም ያልሆኑት የሰው ልጆች፣ በእኩዮች ተጽዕኖ በቀላሉ ተሸንፈው ፍትሕን ሊያዛቡ እንደሚችሉ ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁንና “ብዙዎችን አትከተል” የሚለው መሠረታዊ ሥርዓት ተግባራዊ የሚሆነው ፍርድ ነክ ከሆኑ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ብቻ ነው? በፍጹም።

4, 5. ኢያሱና ካሌብ ብዙዎችን ለመከተል ተጽዕኖ የተደረገባቸው እንዴት ነበር? ተጽዕኖውን ለመቋቋም የረዳቸው ምንድን ነው?

4 እንደ እውነቱ ከሆነ ‘ብዙዎችን እንድንከተል’ የሚደረግብን ተጽዕኖ በማንኛውም ጊዜ ሊያጋጥመን የሚችል ነገር ነው። እንዲህ ያለው ጫና የሚደረግብን ባላሰብነው ሁኔታ ውስጥ ሊሆን ይችላል፤ ጫናውን መቋቋም ደግሞ በጣም ይከብደን ይሆናል። ኢያሱና ካሌብ በአንድ ወቅት ያጋጠማቸውን ተጽዕኖ እንደ ምሳሌ እንመልከት። ተስፋይቱን ምድር ለመሰለል ከተላኩት 12 ሰዎች መካከል ኢያሱና ካሌብ ይገኙበት ነበር። ከሰላዮቹ መካከል አሥሩ በጣም መጥፎና ተስፋ አስቆራጭ የሆነ ዜና ይዘው ተመለሱ። ይባስ ብለው ደግሞ ከምድሪቱ ነዋሪዎች መካከል አንዳንዶቹ፣ ከዓመፀኞቹ መላእክትና ከሰው ሴት ልጆች የተወለዱት የኔፊሊሞች ዝርያ የሆኑ ግዙፍ ሰዎች መሆናቸውን ተናገሩ። (ዘፍ. 6:4) ይህ ፈጽሞ ከእውነት የራቀ ነበር። ከበርካታ መቶ ዓመታት በፊት የተከሰተው የጥፋት ውኃ እነዚህን ክፉ ዲቃላዎች አንድም ሳያስቀር ጠራርጎ አጥፍቷቸዋል። ይሁን እንጂ ጨርሶ መሠረት የሌለው ሐሳብ እንኳ ጠንካራ እምነት በሌላቸው ሰዎች ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። አሥሩ ሰላዮች ያሰራጩት መጥፎ ወሬ ሕዝቡ በፍርሃት እንዲርድና እንዲሸበር አደረገ። ብዙም ሳይቆይ አብዛኞቹ ሰዎች ይሖዋ እንዳዘዛቸው ወደ ተስፋይቱ ምድር መግባት የተሳሳተ እርምጃ እንደሆነ ተሰማቸው። በዚህ ያልተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ ኢያሱና ካሌብ ምን ያደርጉ ይሆን?​—ዘኍ. 13:25-33

5 ብዙዎችን አልተከተሉም። ኢያሱና ካሌብ የሚናገሩትን ነገር ሕዝቡ መስማት ባይፈልግም እነዚህ ሁለት ሰዎች እውነቱን ተናግረዋል፤ ከዚህም ሌላ ሕዝቡ በድንጋይ እንደሚወግራቸው ቢዝትባቸውም እንኳ ከእውነት ጎን ጸንተው ቆመዋል! እንዲህ ያለ ድፍረት ያገኙት ከየት ነው? እምነታቸው ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳደረገ ጥርጥር የለውም። እምነት ያላቸው ሰዎች፣ መሠረተ ቢስ በሆኑ ሰብዓዊ አመለካከቶችና ይሖዋ አምላክ በሚሰጣቸው ተስፋዎች መካከል ያለውን ልዩነት በግልጽ መመልከት አያዳግታቸውም። ከጊዜ በኋላ ኢያሱና ካሌብ፣ ይሖዋ ቃል የገባውን እያንዳንዱን ነገር የሚፈጽም መሆኑ ያሳደረባቸውን ስሜት ገልጸዋል። (ኢያሱ 14:6, 8፤ 23:2, 14ን አንብብ።) ኢያሱና ካሌብ ታማኝ የሆነውን አምላካቸውን ይወዱ እንዲሁም በእሱ ይታመኑ ስለነበር እምነት የለሽ የሆነውን ሕዝብ ለመከተል ሲሉ አምላካቸውን ማሳዘን ጨርሶ የማያስቡት ነገር ነበር። በመሆኑም በአቋማቸው በመጽናት በዛሬው ጊዜ ለምንገኘው ግሩም ምሳሌ ትተውልናል።​—ዘኍ. 14:1-10

6. ብዙዎችን እንድንከተል ጫና የሚደረግብን በየትኞቹ መንገዶች ሊሆን ይችላል?

6 ብዙዎችን ለመከተል ጫና እንደተደረገብህ የሚሰማህ ጊዜ አለ? በዛሬው ጊዜ ከይሖዋ የራቁና የሥነ ምግባር መሥፈርቶቹን የሚያቃልሉ ሰዎች በርካታ እንደሆኑ አይካድም። እነዚህ ሰዎች ከመዝናኛ ጋር በተያያዘ ትክክል ያልሆኑ ሐሳቦችን ያሰራጫሉ። በቴሌቪዥን ፕሮግራሞች፣ በፊልሞችና በቪዲዮ ጨዋታዎች አማካኝነት የሚስፋፋው የሥነ ምግባር ብልግና፣ ዓመፅና መናፍስታዊ ድርጊት ምንም ጉዳት እንደሌለው አድርገው ለማቅረብ ይሞክሩ ይሆናል። (2 ጢሞ. 3:1-5) ለራስህም ሆነ ለቤተሰብህ መዝናኛ ስትመርጥ ትክክል ወይም ስህተት የሆነውን ነገር የምትወስነው በሌሎች ሰዎች በመመራት ነው? እንዲህ ማድረግ ብዙዎችን ከመከተል በምን ይለያል?

7, 8. (ሀ) ‘የማስተዋል ችሎታችንን’ ማሠልጠን የምንችለው እንዴት ነው? እንዲህ ያለው ሥልጠና በዝርዝር የሰፈሩ ሕጎችን ከመከተል ይልቅ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) በርካታ ክርስቲያን ወጣቶች ግሩም ምሳሌ እንደተዉ የሚሰማህ ለምንድን ነው?

7 ይሖዋ ውሳኔ በማድረግ ረገድ የሚረዳን ውድ ስጦታ ይኸውም “የማስተዋል ችሎታ” ሰጥቶናል። ይሁንና ይህን ችሎታችንን “በማሠራት” ማሠልጠን ይኖርብናል። (ዕብ. 5:14) ብዙዎችን መከተል የማስተዋል ችሎታችንን ለማሠልጠን አይረዳንም፤ በሕሊናችን ተመርተን ልንወስን የሚገባንን ነገሮች በተመለከተ ዝርዝር ሕጎች መኖራቸውም ቢሆን የማስተዋል ችሎታችንን ለማሠልጠን አይረዳንም። የይሖዋ ሕዝቦች ሊያዩአቸው የማይገቡ ፊልሞችና የኢንተርኔት ድረ ገጾች እንዲሁም ሊያነቧቸው የማይገቡ መጻሕፍት በዝርዝር የማይነገሯቸው ለዚህ ነው። ዓለም በጣም ስለሚለዋወጥ ይህ ዓይነቱ ዝርዝር ቢዘጋጅ እንኳ ብዙም ሳይቆይ ማስተካከያ ያስፈልገዋል። (1 ቆሮ. 7:31) ከዚህ የከፋው ደግሞ እንዲህ ዓይነት ዝርዝር መዘጋጀቱ፣ አንድን ጉዳይ በተመለከተ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በጥንቃቄ ከመረመርንና ጉዳዩን በጸሎት ካሰብንበት በኋላ ውሳኔ እንዳናደርግ እንቅፋት መሆኑ ነው።​—ኤፌ. 5:10

8 እርግጥ ነው፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ውሳኔዎችን ማድረጋችን አንዳንድ ጊዜ በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት እንድናጣ ሊያደርገን ይችል ይሆናል። ተማሪ የሆኑ ክርስቲያን ወጣቶች፣ ብዙዎች የሚያዩትን ነገር እንዲያዩና የሚያደርጉትን እንዲያደርጉ ከፍተኛ ተጽዕኖ ይደርስባቸው ይሆናል። (1 ጴጥ. 4:4) ከዚህ አንጻር ወጣትም ሆኑ አዋቂ የሆኑ ክርስቲያኖች ብዙዎችን ከመከተል በመራቅ ኢያሱና ካሌብ የተዉትን ምሳሌ እንደሚኮርጁ መመልከት እንዴት ያስደስታል!

‘ልብህ የተመኘውንና ዓይንህ ያየውን’ አትከተል

9. (ሀ) በጉዞ ላይ ሳለን ደስ ያለንን መንገድ መከተል አደገኛ ሊሆን የሚችለው ለምንድን ነው? (ለ) በ⁠ዘኍልቍ 15:37-39 ላይ የሚገኘው ሕግ በጥንት ጊዜ ለነበሩት የአምላክ ሕዝቦች አስፈላጊ የነበረው ለምንድን ነው?

9 ሁለተኛው አደገኛ ተጽዕኖ ደግሞ ከራሳችን የሚመጣ ነው። ሁኔታውን ለማስረዳት የሚከተለውን ምሳሌ እንመልከት፦ ወደ አንድ ቦታ እየተጓዝክ ነው እንበል፤ አቅጣጫ የሚጠቁምህን ካርታ ጥለህ ደስ ባለህ መንገድ ለመሄድ ምናልባትም የሚያምር እይታ ያለውን ማንኛውንም መንገድ ለመከተል ትወስናለህ? ምንም ሳታመዛዝን እንዲያው ደስ ያለህን ነገር ማድረግ ግብህ ላይ ለመድረስ እንደማያስችልህ ግልጽ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ ይሖዋ ለጥንቶቹ እስራኤላውያን የሰጣቸውን ሌላ ሕግ እንመልከት። በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ሰዎች፣ እስራኤላውያን በልብሳቸው ላይ ዘርፍ እንዲያደርጉና ዘርፉ ሰማያዊ ጥለት እንዲኖረው የሚያዝዝ ሕግ የተሰጣቸው ለምን እንደሆነ ላይገባቸው ይችላል። (ዘኍልቍ 15:37-39ን አንብብ።) አንተስ ይህ ሕግ አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት ገብቶሃል? የአምላክ ሕዝቦች እንዲህ ያለውን ሕግ መታዘዛቸው በዙሪያቸው ከነበሩት አረማዊ ብሔራት የተለዩ ሆነው እንዲኖሩ ይረዳቸው ነበር። የይሖዋን ሞገስ ለማግኘትና ላለማጣት ከፈለጉ ይህን ማድረጋቸው በጣም አስፈላጊ ነበር። (ዘሌ. 18:24, 25) በተጨማሪም ይህ ሕግ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን ጎዳና ስተን በተሳሳተ አቅጣጫ እንድንሄድ ሊያደርገን የሚችለውን ከራሳችን የሚመጣ አደገኛ ተጽዕኖ ይጠቁመናል። እንዴት?

10. ይሖዋ የሰውን አፈጣጠር በሚገባ እንደሚያውቅ ያሳየው እንዴት ነው?

10 ይሖዋ ለሕዝቦቹ ይህን ሕግ የሰጠበትን ምክንያት ሲገልጽ “ልባችሁ የተመኘውን፣ ዐይናችሁ ያየውን ሁሉ ተከትላችሁ እንዳታመነዝሩ . . . ማስታወሻ ይሆኑአችኋል” ብሏቸው ነበር። ይሖዋ የሰውን አፈጣጠር በሚገባ ያውቃል። የምናየው ነገር ልባችንን በቀላሉ ሊያማልለው እንደሚችል ይገነዘባል። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ “የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ ነው፤ ፈውስም የለውም፤ ማንስ ሊረዳው ይችላል?” የሚል ማሳሰቢያ ይሰጠናል። (ኤር. 17:9) ታዲያ ይሖዋ ለእስራኤላውያን የሰጠው ማሳሰቢያ ምን ያህል አስፈላጊ እንደነበረ ተገነዘብህ? እስራኤላውያን በዙሪያቸው የነበሩትን አረማዊ ብሔራት በማየት ሊታለሉ እንደሚችሉ ይሖዋ ያውቅ ነበር። እነዚያን አረማዊ ሰዎች ለመምሰል፣ እንደነሱ ለማሰብና የሚያደርጉትን ለማድረግ ሊፈተኑ ይችሉ ነበር።​—ምሳሌ 13:20

11. ልባችን በምናየው ነገር ተማርኮ ሊታለል የሚችለው እንዴት ነው?

11 በዛሬው ጊዜም ተንኰለኛው ልባችን በምናየው ነገር በቀላሉ ሊታለል ይችላል። የምንኖርበት ዓለም ሥጋዊ ፍላጎቶቻችንን እንድናረካ ይገፋፋናል። ታዲያ በ⁠ዘኍልቍ 15:39 ላይ የሚገኘውን መሠረታዊ ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ በትምህርት ቤትህ፣ በሥራ ቦታህ ወይም በአካባቢህ ያሉ ሰዎች አለባበሳቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ የፆታ ስሜትን የሚቀሰቅስ እየሆነ ከሄደ ይህ በአንተ ላይ ተጽዕኖ ያሳድር ይሆን? ‘ልብህ የተመኘውንና ዓይንህ ያየውን ለመከተል’ ትፈተን እንዲሁም ባየኸው ነገር ትማረክ ይሆን? እንደ እነሱ በመልበስ አቋምህን ለማላላት ትፈተን ይሆን?​—ሮም 12:1, 2

12, 13. (ሀ) ዓይናችን ተገቢ ያልሆነ ነገር ለማየት የሚፈተን ከሆነ ምን ማድረግ ይኖርብናል? (ለ) ለሌሎች ፈተና ላለመሆን እንድንጠነቀቅ የሚያነሳሳን ምንድን ነው?

12 ራስን የመግዛት ባሕርይ ማዳበራችን በጣም አስፈላጊ ነው። ዓይናችን ተገቢ ያልሆነ ነገር ለማየት የሚፈተን ከሆነ ታማኙ ኢዮብ ከዓይኑ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን እናስታውስ፤ ኢዮብ ሚስቱ ያልሆነችን ሴት በፍቅር ስሜት ላለመመልከት ቁርጥ ውሳኔ አድርጎ ነበር። (ኢዮብ 31:1) በተመሳሳይም ንጉሥ ዳዊት “በዐይኔ ፊት፣ ክፉ ነገር አላኖርም” በማለት ተናግሯል። (መዝ. 101:3) ንጹሕ ሕሊናችንን የሚያቆሽሽ እንዲሁም ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና የሚያበላሽ ማንኛውም ነገር “ክፉ” ወይም የማይረባ ነገር ነው። ይህም ዓይናችንን የሚማርክና ልባችን መጥፎ ነገር ወደ መፈጸም እንዲያዘነብል የሚያነሳሳ ማንኛውንም ፈተና ይጨምራል።

13 በሌላ በኩል ደግሞ ሌሎች መጥፎ ድርጊት ለመፈጸም እንዲፈተኑ በማድረግ እኛ ራሳችን “ክፉ” ወይም የማይረባ ነገር መሆን እንደማንፈልግ ጥርጥር የለውም። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓታማና ልከኛ የሆነ ልብስ እንድንለብስ የሚሰጠንን ምክር በቁም ነገር መመልከት ይኖርብናል። (1 ጢሞ. 2:9) ልከኝነት በራሳችን መሥፈርት ብቻ የምንወስነው ነገር አይደለም። የሌሎችን ሕሊና ላለመጉዳት በመጠንቀቅና ስሜታቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት ከራሳችን ምርጫ ይልቅ የእነሱን የአእምሮ ሰላምና ደስታ ማስቀደም ይኖርብናል። (ሮም 15:1, 2) በዚህ ረገድ ግሩም ምሳሌ የሚሆኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ መሆኑ ትልቅ በረከት ነው። እነዚህ ወጣቶች ‘ልባቸው የተመኘውንና ዓይናቸው ያየውን ከመከተል’ ይልቅ አለባበሳቸውን ጨምሮ በማንኛውም እንቅስቃሴያቸው ይሖዋን ለማስደሰት በመምረጣቸው በጣም እንኮራባቸዋለን!

“ከንቱ” ነገሮችን አትከተል

14. ሳሙኤል “ከንቱ” ነገሮችን ስለመከተል ምን ማሳሰቢያ ሰጥቷል?

14 በጉዞህ ላይ አንድ ሰፊ በረሃ እያቋረጥህ እያለ ከሩቅ ውኃ ያየህ መሰለህ፤ ውኃ እንደሆነ ያሰብከውን ነገር ለማግኘት ከመንገድህ ወጥተህ ወደዚያ ብታመራ ምን ሊያጋጥምህ ይችላል? ይህን እውን ያልሆነ ነገር ለማግኘት የምታደርገው ጥረት ሕይወትህን ሊያሳጣህ ይችላል! ይሖዋ እንዲህ ዓይነት አደገኛ ሁኔታ ሊያጋጥመን እንደሚችል በሚገባ ያውቃል። አንድ ምሳሌ እንመልከት። እስራኤላውያን፣ በሰብዓዊ ነገሥታት እንደሚመሩት በዙሪያቸው እንዳሉት ሕዝቦች መሆን ፈልገው ነበር። እንደ እውነቱ ከሆነ እንዲህ ዓይነት ፍላጎት እንዳላቸው መግለጻቸው ይሖዋ ንጉሣቸው እንዲሆን እንደማይፈልጉ ከመግለጽ የማይተናነስ በመሆኑ ከባድ ኃጢአት የፈጸሙ ያህል ነበር። ይሖዋ ሰብዓዊ ንጉሥ እንዲኖራቸው የፈቀደላቸው ቢሆንም “ከንቱ” ነገሮችን መከተል ተገቢ አለመሆኑን በነቢዩ ሳሙኤል አማካኝነት አሳስቧቸው ነበር።​—1 ሳሙኤል 12:21ን አንብብ።

15. እስራኤላውያን ከንቱ ነገሮችን የተከተሉት በየትኞቹ መንገዶች ነው?

15 ሕዝቡ፣ የሚሾምላቸው ሰብዓዊ ንጉሥ ከይሖዋ ይልቅ እውንና አስተማማኝ እንደሚሆንላቸው አስበው ይሆን? እንደዚያ አስበው ከሆነ በእርግጥም ከንቱ ነገሮችን እየተከተሉ ነበር! ይህም ሰይጣን የሚያስፋፋቸውን ሌሎች በርካታ ከንቱ ነገሮች ወደ መከተል እንዲያዘነብሉ ያደርጋቸዋል። ሰብዓዊ ነገሥታት ሕዝቡን በቀላሉ ወደ ጣዖት አምልኮ ሊመሯቸው ይችላሉ። ጣዖት አምላኪዎች፣ ከእንጨት ወይም ከድንጋይ የተሠሩ የሚታዩ አማልክት ሁሉን ነገር ከፈጠረው ሆኖም በዓይን ከማይታየው ከይሖዋ አምላክ ይልቅ እውንና አስተማማኝ እንደሆኑ በማሰብ ይሳሳታሉ። ይሁንና ሐዋርያው ጳውሎስ እንደገለጸው ጣዖታት “ከንቱ” ናቸው። (1 ቆሮ. 8:4) ማየት፣ መስማት፣ መናገር ወይም ምንም ነገር ማድረግ አይችሉም። ጣዖታትን ማየትና መንካት ይቻል ይሆናል፤ እነሱን ማምለክ ግን ከንቱ የሆነና ወደ ጥፋት የሚመራ እውን ያልሆነ ነገርን እንደ መከተል ይሆንብሃል።​—መዝ. 115:4-8

16. (ሀ) ሰይጣን በአሁኑ ጊዜ ብዙዎችን በማታለል ከንቱ ነገሮችን እንዲከተሉ የሚያደርገው እንዴት ነው? (ለ) ቁሳዊ ነገሮች በተለይ ከይሖዋ አምላክ ጋር ሲወዳደሩ ከንቱ ናቸው የምንለው ለምንድን ነው?

16 ዛሬም ቢሆን ሰይጣን፣ ሰዎች ከንቱ ነገሮችን እንዲከተሉ በማሳመን ረገድ የተካነ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ አስተማማኝ ሕይወት ለማግኘት ቁሳዊ ነገሮችን ወደ ማሳደድ ዘወር እንዲሉ በማድረግ ያታለላቸው ሰዎች በርካታ ናቸው። ገንዘብና ንብረት መሰብሰብ እንዲሁም ዳጎስ ያለ ደሞዝ የሚያስገኝ ሥራ መያዝ የሚጠቅም ሊመስል ይችላል። ይሁንና ጤንነት ሲጓደል፣ ኢኮኖሚው ሲንኮታኮት ወይም የተፈጥሮ አደጋ ሲከሰት ቁሳዊ ነገሮች ምን የሚፈይዱት ነገር ይኖራል? ሰዎች የሕይወትን ዓላማ መረዳትና መመሪያ ማግኘት ባለመቻላቸው እንዲሁም በሕይወት ውስጥ ለሚነሱት ከባድ ጥያቄዎች መልስ በማጣታቸው የባዶነት ስሜት ሲያድርባቸው ቁሳዊ ነገሮች ምን ሊጠቅሟቸው ይችላሉ? ከሞት ጋር ሲፋጠጡስ ቁሳዊ ነገሮች ምን ይበጇቸዋል? መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ለማሟላት ወደ ቁሳዊ ነገሮች ዘወር የምንል ከሆነ ለሐዘን እንዳረጋለን። ቁሳዊ ነገሮች ከንቱ ስለሆኑ ሊያድኑን አይችሉም። እነዚህ ነገሮች ደስተኛ ሊያደርጉንም ሆነ ከበሽታና ከሞት ሊታደጉን አይችሉም። (ምሳሌ 23:4, 5) ከንቱ ከሆኑት ከእነዚህ ነገሮች በተቃራኒ አምላካችን ይሖዋ እውን ነው! አስተማማኝ ሕይወት ማግኘት የምንችለው ከእሱ ጋር ጠንካራ ዝምድና ሲኖረን ብቻ ነው። ይህ እንዴት ያለ ታላቅ በረከት ነው! እንግዲያው ከንቱ ነገሮችን ለማሳደድ ስንል ፈጽሞ ይሖዋን አንተው።

17. ከላይ የተመለከትናቸውን መጥፎ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ነገሮች በተመለከተ ምን ቁርጥ ውሳኔ አድርገሃል?

17 ወደ ዘላለም ሕይወት በምናደርገው ጉዞ ላይ ይሖዋ እንደ ወዳጅ በመሆን መመሪያ የሚሰጠን መሆኑ ታላቅ በረከት አይደለም? መጥፎ ተጽዕኖ የሚያሳድሩብንን ሦስት ነገሮች ማለትም ብዙሃኑን፣ ልባችንንና ከንቱ ነገሮችን ከመከተል እንድንርቅ ይሖዋ የሚሰጠንን ፍቅራዊ አመራር ምንጊዜም ተግባራዊ የምናደርግ ከሆነ ወዳሰብንበት ቦታ የመድረስ ይኸውም የዘላለም ሕይወት የማግኘት አጋጣሚያችን ሰፊ ይሆናል። ብዙዎችን ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ የመራቸውን የሐሰት መንገድ እንድንጠላና ይህን መንገድ ከመከተል እንድንርቅ ለመርዳት ይሖዋ የሚሰጠንን ሦስት ተጨማሪ ማስጠንቀቂያዎች በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንመለከታለን።​—መዝ. 119:128

ምን ይመስልሃል?

ከዚህ በታች ባሉት ጥቅሶች ላይ የሚገኙትን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሕይወትህ ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

ዘፀአት 23:2

ዘኍልቍ 15:37-39

1 ሳሙኤል 12:21

መዝሙር 119:128

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ብዙዎችን ለመከተል ተፈትነህ ታውቃለህ?

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቆም ብለን ሳናስብ አንድን ነገር ደስ ስላለን ብቻ ማድረግ አደገኛ የሆነው ለምንድን ነው?

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከንቱ ነገሮችን እየተከተልክ ነው?