በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለቤተሰብ አምልኮና ለግል ጥናት የሚሆኑ ጠቃሚ ሐሳቦች

ለቤተሰብ አምልኮና ለግል ጥናት የሚሆኑ ጠቃሚ ሐሳቦች

ለቤተሰብ አምልኮና ለግል ጥናት የሚሆኑ ጠቃሚ ሐሳቦች

በ2009 መጀመሪያ ላይ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች፣ ስብሰባ በሚያደርጉበት ፕሮግራም ላይ ማስተካከያ አድርገዋል። በሳምንቱ መሃል የምናደርጋቸው ሁለት ስብሰባዎች በአንድ ቀን እንዲከናወኑ የተደረገ ሲሆን ሁላችንም ቀድሞ ለጉባኤ ስብሰባ እናውለው የነበረውን ምሽት ለቤተሰብ አምልኮ ወይም ለግል ጥናት እንድንጠቀምበት ተበረታትተናል። በዚህ አዲስ ዝግጅት ሙሉ በሙሉ እየተጠቀማችሁ ነው?

አንዳንዶች በቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማቸው ወቅት ምን ቢያጠኑ እንደሚሻል ጥያቄ አንስተዋል። የበላይ አካሉ፣ ሁሉም ቤተሰቦች የሚያጠኑትን ነገር መወሰን አይፈልግም። የእያንዳንዱ ቤተሰብ ሁኔታ የተለያየ በመሆኑ የቤተሰብ ራሶች ወይም ግለሰቦች ይህን ሳምንታዊ ፕሮግራም ከሁሉ በተሻለ መንገድ ሊጠቀሙበት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ማሰብ ይኖርባቸዋል።

በቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማቸው ወቅት ለጉባኤ ስብሰባዎች የሚዘጋጁ ቤተሰቦች አሉ፤ ይሁንና በዚህ ምሽት ላይ ሌሎች ነገሮችንም ማድረግ ይቻላል። መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነቡ፣ ባነበቡት ላይ የሚወያዩ አልፎ ተርፎም በድራማ መልክ የሚሠሩት ቤተሰቦችም አሉ፤ ይህን ማድረጋቸው በተለይ ለትንንሽ ልጆች ጠቃሚ ነው። በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ እንደሚደረገው ሁሉ በቤተሰብ አምልኮ ላይም ውይይቱን ሁልጊዜ በጥያቄና መልስ መልክ ማድረግ ላያስፈልግ ወይም ተመራጭ ላይሆን ይችላል። ብዙውን ጊዜ በቤተሰብ አምልኮ ወቅት ዘና ያለ መንፈስ መኖሩ አስደሳች ውይይት ለማድረግ ይበልጥ ያመቻል። እንዲህ ያለ ሁኔታ መኖሩ ቤተሰቦች የሚወያዩበትን ነገር በዓይነ ሕሊናቸው ለመሳል እንዲችሉ መንገድ የሚከፍትላቸው ሲሆን ይህ ደግሞ ጥናቱ ለሁሉም የቤተሰቡ አባላት የማይረሳና አስደሳች እንዲሆንላቸው ያደርጋል።

የሦስት ልጆች አባት የሆነ አንድ ወንድም እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “በአብዛኛው በቤተሰብ አምልኳችን ወቅት የምናደርገው ውይይት ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ጋር የተያያዘ ነው። እያንዳንዳችን ምዕራፎቹን አስቀድመን እናነባለን፤ ከዚያም ልጆቹ ምርምር ሊያደርጉበት የፈለጉትን አንድ ነጥብ ከመረጡ በኋላ ያገኙትን ሐሳብ በጥናቱ ወቅት ያቀርባሉ። ማይክል [ሰባት ዓመቱ ነው] ብዙውን ጊዜ ሥዕል ይስላል ወይም ያነበበውን ነገር በራሱ አባባል ይጽፋል። ዴቪድ [13 ዓመቱ ነው] እና ኬትሊን [15 ዓመቷ ነው] ስለ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ እንደ ተመልካች ሆነው ይጽፋሉ። ለምሳሌ ዮሴፍ ለፈርዖን መጠጥ አሳላፊና የእንጀራ ቤቱ አዛዥ ሕልማቸውን እንደተረጎመላቸው የሚገልጸውን ዘገባ ስናነብ ኬትሊን ይህን ክንውን በቦታው ሆኖ እንደተመለከተ እስረኛ ሆና ሥነ ጽሑፍ አዘጋጀች።”​—ዘፍ. ምዕ. 40

የእያንዳንዱ ቤተሰብ ሁኔታ የተለያየ እንደሆነ ግልጽ ነው። ለአንድ ግለሰብ ወይም ቤተሰብ የሚሆነው ሐሳብ ለሌላው ላይሆነው ይችላል። በሚቀጥለው ገጽ ላይ ባለው ሣጥን ውስጥ የቤተሰብ አምልኮ ወይም የግል ጥናት በምታደርጉበት ጊዜ ልትጠቀሙባቸው የምትችሉ የተወሰኑ ሐሳቦች ቀርበዋል። እናንተም ሌሎች ሐሳቦች ይኖሯችሁ ይሆናል።

[በገጽ 6 እና 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ልጆች ላሏቸው ቤተሰቦች፦

ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች የሚለውን መጽሐፍ እያነበባችሁ መወያየት።

• “በዚያን ጊዜ ብትኖር ኖሮ . . . ?” እንደሚሉት ያሉ ጥያቄዎችን እያነሳችሁ ከልጆቻችሁ ጋር መወያየት። (የግንቦት 15, 1996 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 14 አንቀጽ 17, 18⁠ን ተመልከቱ።)

• ስለ ረጅምና የአጭር ጊዜ ግቦቻችሁ መነጋገር።

• አልፎ አልፎ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ቪዲዮዎችን እየተመለከታችሁ መወያየት።

• “ለታዳጊ ወጣቶች” የሚለውን የመጠበቂያ ግንብ ዓምድ ማጥናት።

ልጅ ለሌላቸው ባለትዳሮች፦

ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው? በተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 1, 3, 11-16 ላይ መወያየት።

• በመጽሐፍ ቅዱስ ንባባችሁ ወቅት ምርምር ስታደርጉ ባገኛችኋቸው ሐሳቦች ላይ መነጋገር።

• ለጉባኤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ወይም ለመጠበቂያ ግንብ ጥናት መዘጋጀት።

• አገልግሎታችሁን ማስፋት የምትችሉባቸውን መንገዶች መወያየት።

ነጠላ ለሆኑ ወንድሞችና እህቶች ወይም በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ ለሚኖሩ፦

• በአውራጃ ስብሰባ ላይ የወጡ አዳዲስ ጽሑፎችን ማጥናት።

• የዘንድሮውንና ያለፉትን የዓመት መጻሕፍት ማንበብ።

• በክልላችሁ ውስጥ በሚያጋጥሙ የተለመዱ ጥያቄዎች ላይ ምርምር ማድረግ።

• ለአገልግሎት የሚሆን የመግቢያ ሐሳብ መዘጋጀት።

ትንንሽ ልጆች ላሏቸው ቤተሰቦች፦

• የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን በድራማ መልክ መሥራት።

በንቁ! መጽሔት ገጽ 30 እና 31 ላይ እንደሚወጡት ያሉ የማስታወስ ችሎታን የሚፈትኑ ጨዋታዎችን መጫወት።

• አልፎ አልፎ ደግሞ ለየት ያለ ነገር ማድረግ። (“ምንም ያህል ጥረት ቢደረግለት አያስቆጭም!” የሚለውን በየካቲት 15, 2011 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 11 ላይ የወጣውን ርዕስ ተመልከቱ።)

• “ልጆቻችሁን አስተምሩ” የሚለውን በመጠበቂያ ግንብ ላይ የሚወጣውን ዓምድ ማጥናት።