በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መሲሑን አገኙት!

መሲሑን አገኙት!

መሲሑን አገኙት!

“መሲሑን . . . አገኘነው።”​—ዮሐ. 1:41

1. እንድርያስ “መሲሑን . . . አገኘነው” ብሎ የተናገረው ለምንድን ነው?

አጥማቂው ዮሐንስ ከሁለት ደቀ መዛሙርቱ ጋር ቆሞ ነበር። ዮሐንስ፣ ኢየሱስ ሲመጣ ሲያይ “የአምላክ በግ ይኸውላችሁ!” አለ። እንድርያስና አብሮት የነበረው ደቀ መዝሙር ይህን ሲሰሙ ወዲያውኑ ኢየሱስን ተከተሉት፤ በዚያም ዕለት አብረውት ዋሉ። ቆየት ብሎም እንድርያስ፣ ስምዖን ጴጥሮስ የተባለውን ወንድሙን ሲያገኘው “መሲሑን . . . አገኘነው” ብሎ ከነገረው በኋላ ወደ ኢየሱስ ወሰደው።​—ዮሐ. 1:35-41

2. ስለ መሲሑ የሚናገሩ ተጨማሪ ትንቢቶችን መመርመራችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?

2 ጊዜ እያለፈ ሲሄድ እንድርያስ፣ ጴጥሮስና ሌሎች ደቀ መዛሙርት ቅዱሳን መጻሕፍትን በጥልቀት የመመርመር ሰፊ አጋጣሚ የሚያገኙ ሲሆን የናዝሬቱ ኢየሱስ ተስፋ የተደረገው መሲሕ መሆኑን በእርግጠኝነት ማወጃቸው አይቀርም። እኛም ስለ መሲሑ የሚናገሩትን ትንቢቶች መመርመራችንን ስንቀጥል በአምላክ ቃልና በመሲሑ ላይ ያለን እምነት ይጠናከራል።

‘እነሆ ንጉሥሽ ይመጣል’

3. ኢየሱስ እንደ ንጉሥ ሆኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ የትኞቹ ትንቢቶች ተፈጽመዋል?

3 መሲሑ እንደ ድል አድራጊ ንጉሥ ሆኖ ወደ ኢየሩሳሌም ይገባል። ዘካርያስ እንዲህ የሚል ትንቢት ተናግሮ ነበር፦ “አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ፤ እጅግ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፤ እልል በዪ፤ እነሆ፤ ጻ[ድ]ቁና አዳኙ ንጉሥሽ፣ ትሑት ሆኖ፣ በአህያ ላይ ተቀምጦ፣ በአህያ ግልገል፣ በውርንጫዪቱ ላይ ሆኖ ወደ አንቺ ይመጣል።” (ዘካ. 9:9) መዝሙራዊው “በእግዚአብሔር [“በይሖዋ፣” NW] ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው” በማለት ጽፏል። (መዝ. 118:26) ኢየሱስ ሕዝቡ በዚያ ዓይነት ሁኔታ እንዲቀበሉት ለማድረግ ነገሮችን አላቀነባበረም። ይሁንና ሕዝቡ ልክ በትንቢቱ ላይ እንደተነገረው በራሳቸው ተነሳስተው በደስታ እየጮኹ ተቀብለውታል። ዘገባውን በምታነብበት ጊዜ ሁኔታውን በዓይነ ሕሊናህ ለመሳልና የሕዝቡን የደስታ ጩኸት ለመስማት ሞክር።​—ማቴዎስ 21:4-9ን አንብብ።

4. በ⁠መዝሙር 118:22, 23 ላይ ያለው ትንቢት የተፈጸመው እንዴት እንደሆነ አብራራ።

4 ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን የሚያረጋግጡ በርካታ ማስረጃዎች ቢኖሩም ብዙዎች ሊቀበሉት ፈቃደኞች አይሆኑም፤ ያም ሆኖ በአምላክ ፊት ክቡር ነው። አስቀድሞ እንደተነገረው ማስረጃዎቹን ለማመን አሻፈረኝ ባሉ ሰዎች ዘንድ ኢየሱስ ‘የተናቀና ክብር የማይሰጠው’ ሰው ነበር። (ኢሳ. 53:3፤ ማር. 9:12) ሆኖም መዝሙራዊው በአምላክ መንፈስ መሪነት እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣ እርሱ የማእዘን ራስ ሆነ። እግዚአብሔር ይህን አደረገ።” (መዝ. 118:22, 23) ኢየሱስ ይህን ጥቅስ ተቃዋሚዎቹ ለሆኑት ሃይማኖታዊ መሪዎች የጠቀሰላቸው ሲሆን ጴጥሮስም ጥቅሱ በክርስቶስ ላይ እንደተፈጸመ ተናግሯል። (ማር. 12:10, 11፤ ሥራ 4:8-11) በእርግጥም ኢየሱስ የክርስቲያን ጉባኤ “የማዕዘን የመሠረት ድንጋይ” ሆኗል። ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎች ባይቀበሉትም ‘በአምላክ ፊት ግን የተመረጠና ክቡር’ ነው።​—1 ጴጥ. 2:4-6

መሲሑን ወዳጁ ይከዳዋል፤ ደቀ መዛሙርቱም ትተውት ይሸሻሉ!

5, 6. በመሲሑ ላይ ከተፈጸመው ክህደት ጋር በተያያዘ ምን ትንቢት ተነግሮ ነበር? ትንቢቱ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?

5 መሲሑን አታላይ የሆነ ወዳጁ እንደሚከዳው አስቀድሞ ተነግሯል። ዳዊት “እንጀራዬን ተካፍሎኝ የበላ፣ የምተማመንበትም የቅርብ ወዳጄ፣ በእኔ ላይ ተረከዙን አነሣ” የሚል ትንቢት ተናግሯል። (መዝ. 41:9) አብረው ማዕድ የሚቋደሱ ሰዎች ወዳጆች ተደርገው ይቆጠሩ ነበር። (ዘፍ. 31:54) ስለሆነም አስቆሮቱ ይሁዳ በኢየሱስ ላይ የፈጸመው ተግባር ከሁሉ የከፋ ክህደት ነው። ኢየሱስ የሚከዳውን ሰው አስመልክቶ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ብሏል፦ “ይህን ስል ስለ ሁላችሁም መናገሬ አይደለም፤ የመረጥኳቸውን አውቃለሁ። ይሁንና ‘ከማዕዴ ይበላ የነበረ ተረከዙን በእኔ ላይ አነሳ’ የሚለው የቅዱሳን መጻሕፍት ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው”፤ ኢየሱስ ይህን ያለው ዳዊት የተናገረው ትንቢት ፍጻሜውን እንዳገኘ ለመጠቆም ነበር።​—ዮሐ. 13:18

6 መሲሑን አሳልፎ የሚሰጠው ግለሰብ 30 የብር ሳንቲሞችን ይኸውም የአንድ ባሪያ ዋጋ ይቀበላል። ማቴዎስ፣ ዘካርያስ 11:12, 13⁠ን በመጥቀስ ኢየሱስ እዚህ ግባ በማይባል ዋጋ አልፎ እንደተሰጠ ገልጿል። ይሁን እንጂ ማቴዎስ ይህ ትንቢት “በነቢዩ ኤርምያስ” እንደተነገረ አድርጎ የጻፈው ለምንድን ነው? ማቴዎስ በኖረበት ዘመን፣ የኤርምያስ መጽሐፍ በመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ስብስብ ላይ መጀመሪያ ይደረግ የነበረ ይመስላል፤ በዚህ ስብስብ ውስጥ የዘካርያስ መጽሐፍም ይገኝበታል። (ከሉቃስ 24:44 ጋር አወዳድር።) ይሁዳ፣ የብር ሳንቲሞቹን ቤተ መቅደሱ ውስጥ ከበተነ በኋላ ራሱን ስለገደለ በሸፍጥ ያገኘውን ገንዘብ አልተጠቀመበትም።​—ማቴ. 26:14-16፤ 27:3-10

7. ዘካርያስ 13:7 ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?

7 የመሲሑ ደቀ መዛሙርት እንኳ ሳይቀሩ ትተውት ይበተናሉ። ዘካርያስ “እረኛውን ምታ፤ በጎቹ ይበተናሉ” ሲል ጽፎ ነበር። (ዘካ. 13:7) ኒሳን 14, 33 ዓ.ም. ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፦ “‘እረኛውን እመታለሁ፤ የመንጋውም በጎች ይበተናሉ’ ተብሎ ስለተጻፈ በዚህች ሌሊት ሁላችሁም በእኔ ምክንያት ትሰናከላላችሁ።” የተፈጸመውም ይኸውም ነበር፤ ማቴዎስ “ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ [ኢየሱስን] ጥለውት ሸሹ” በማለት ዘግቧል።​—ማቴ. 26:31, 56

ይወነጀላል እንዲሁም ይመታል

8. ኢሳይያስ 53:8 የተፈጸመው እንዴት ነው?

8 መሲሑ ችሎት ፊት ይቀርባል እንዲሁም ይፈረድበታል። (ኢሳይያስ 53:8ን አንብብ።) ኒሳን 14 ንጋት አካባቢ የሳንሄድሪን ሸንጎ አባላት በሙሉ ተሰብስበው ከተማከሩ በኋላ ኢየሱስን አስረው በመውሰድ ለሮማዊው አገረ ገዥ ለጳንጥዮስ ጲላጦስ አስረከቡት። ጲላጦስ ኢየሱስን ሲመረምረው ምንም ጥፋት ስላላገኘበት ሊፈታው እንደሆነ ገለጸ፤ ሕዝቡ ግን “ስቀለው!” ብለው ጮኹ። ከእሱ ይልቅ በርባን የተባለው ወንጀለኛ እንዲፈታላቸው ጠየቁ። በዚህ ጊዜ ጲላጦስ ሕዝቡን ለማስደሰት ስለፈለገ በርባንን ፈታላቸው፤ ኢየሱስንም ካስገረፈው በኋላ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠው።​—ማር. 15:1-15

9. በ⁠መዝሙር 35:11 ላይ በተነገረው ትንቢት መሠረት በኢየሱስ ላይ ምን ተፈጸመ?

9 የሐሰት ምሥክሮች በመሲሑ ላይ ይመሠክራሉ። መዝሙራዊው ዳዊት “ጨካኝ ምስክሮች ተነሡ፤ ስለማላውቀውም ነገር ጠየቁኝ” ብሎ ነበር። (መዝ. 35:11) ልክ በትንቢት እንደተነገረው “የካህናት አለቆችና የሳንሄድሪን ሸንጎ በሙሉ ኢየሱስን ለመግደል በእሱ ላይ የሐሰት የምሥክርነት ቃል እየፈለጉ ነበር።” (ማቴ. 26:59) እንዲያውም “ብዙዎች በእሱ ላይ የሐሰት ምሥክርነት ይሰጡ ነበር፤ ሆኖም ቃላቸው ሊስማማ አልቻለም።” (ማር. 14:56) ኢየሱስን ለማስገደል ቆርጠው የተነሱት ጠላቶቹ ግን የቀረበው ምሥክርነት ሐሰት ቢሆንም ግድ አልነበራቸውም።

10. ኢሳይያስ 53:7 እንዴት ፍጻሜውን እንዳገኘ ግለጽ።

10 መሲሑ ለሚከሱት ሰዎች መልስ አይሰጥም። ኢሳይያስ እንዲህ የሚል ትንቢት ተናግሯል፦ “ተጨነቀ፤ ተሠቃየም፤ ነገር ግን አፉን አልከፈተም፤ እንደ ጠቦትም ለዕርድ ተነዳ፤ በሸላቾች ፊት ዝም እንደሚል በግ፣ አፉን አልከፈተም።” (ኢሳ. 53:7) ኢየሱስ “የካህናት አለቆቹና ሽማግሌዎቹ ሲከሱት . . . ምንም መልስ አልሰጠም።” በዚህ ጊዜ ጲላጦስ “በስንት ነገር እየመሠከሩብህ እንዳሉ አትሰማም?” አለው። ኢየሱስ ግን “አገረ ገዥው እጅግ እስኪደነቅ ድረስ አንዲት ቃል እንኳ አልመለሰለትም።” (ማቴ. 27:12-14) በእርግጥም ኢየሱስ የከሰሱትን ሰዎች አልተሳደበም።​—ሮም 12:17-21፤ 1 ጴጥ. 2:23

11. ኢሳይያስ 50:6 እና ሚክያስ 5:1 ፍጻሜያቸውን ያገኙት እንዴት ነው?

11 ኢሳይያስ፣ መሲሑ እንደሚመታ ትንቢት ተናግሯል። ነቢዩ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ለሚገርፉኝ ጀርባዬን፣ ጢሜን ለሚነጩ ጕንጬን ሰጠሁ፤ ፊቴን ከውርደት፣ ከጥፋትም [“ከትፋት፣” የ1954 ትርጉም] አልሰወርሁም።” (ኢሳ. 50:6) ሚክያስ “የእስራኤልን ገዥ፣ ጕንጩን በበትር ይመቱታል” በማለት አስቀድሞ ተናግሯል። (ሚክ. 5:1) የወንጌል ጸሐፊው ማርቆስ እነዚህ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ማግኘታቸውን ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “አንዳንዶች [በኢየሱስ ላይ] ይተፉበት ጀመር፤ ፊቱንም ሸፍነው በቡጢ እየመቱት ‘ነቢይ ከሆንክ እስቲ ማን እንደመታህ ንገረን!’ ይሉት ነበር። የሸንጎው አገልጋዮችም ፊቱን በጥፊ እየመቱ ወሰዱት።” ማርቆስ፣ ወታደሮቹ “ራሱን በመቃ ይመቱት፣ ይተፉበት” እንዲሁም ‘ተንበርክከው በመስገድ’ ይቀልዱበት እንደነበር ጽፏል። (ማር. 14:65፤ 15:19) እርግጥ ነው፣ ኢየሱስ እንዲህ ያለ በደል እንዲፈጸምበት ምክንያት የሚሆን አንዳች ጥፋት አልሠራም።

እስከ ሞት ድረስ ታማኝ ይሆናል

12. መዝሙር 22:16 እና ኢሳይያስ 53:12 በኢየሱስ ላይ የተፈጸሙት እንዴት ነው?

12 ከመሲሑ መሰቀል ጋር የተያያዙ ትንቢቶች ተነግረው ነበር። መዝሙራዊው ዳዊት “የክፉዎች ሸንጎ በዙሪያዬ ተሰልፎአል፤ እጆቼንና እግሮቼንም ቸነከሩኝ” ብሏል። (መዝ. 22:16) መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነቡ ብዙዎች እንደሚያውቁት ይህ ትንቢት በትክክል ተፈጽሟል፤ የወንጌል ጸሐፊው ማርቆስ “ሲሰቅሉትም ጊዜው ሦስት ሰዓት ነበር” ብሏል። (ማር. 15:25) መሲሑ ከኃጢአተኞች ጋር እንደሚቆጠርም ትንቢት ተነግሮ ነበር። ኢሳይያስ “እስከ ሞት ድረስ ሕይወቱን አሳልፎ [ሰጠ]፣ ከክፉ አድራጊዎችም ጋር [ተቆጠረ]” ሲል ጽፏል። (ኢሳ. 53:12) በዚህ ትንቢት መሠረት ከኢየሱስ ጋር “ሁለት ወንበዴዎች፣ አንዱ በቀኙ አንዱ በግራው ተሰቅለው ነበር።”​—ማቴ. 27:38

13. መዝሙር 22:7, 8 በኢየሱስ ላይ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?

13 ዳዊት፣ መሲሑ እንደሚሰደብ ትንቢት ተናግሯል። (መዝሙር 22:7, 8ን አንብብ።) ኢየሱስ በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ በሚሠቃይበት ወቅት ሰዎች ይሰድቡትና ያፌዙበት እንደነበር ማቴዎስ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “በመንገድ የሚያልፉም ይሰድቡት ጀመር፤ ራሳቸውን እየነቀነቁም ‘አይ አንተ፣ ቤተ መቅደሱን አፍርሼ በሦስት ቀን መልሼ እሠራለሁ ባይ፣ እስቲ ራስህን አድን! የአምላክ ልጅ ከሆንክ እስቲ ከተሰቀልክበት እንጨት ላይ ውረድ!’ ይሉት ነበር።” በተጨማሪም የካህናት አለቆች፣ ጸሐፍትና ሽማግሌዎች እንዲህ እያሉ ያፌዙበት ነበር፦ “ሌሎችን አዳነ፤ ራሱን ግን ማዳን አልቻለም! የእስራኤል ንጉሥ እኮ ነው፤ እስቲ አሁን ከተሰቀለበት እንጨት ይውረድና እኛም እንመንበት። በአምላክ ታምኗል፤ ‘የአምላክ ልጅ ነኝ’ ስላለ ከወደደው እስቲ አሁን ያድነው።” (ማቴ. 27:39-43) ይህ ሁሉ ቢደርስበትም ኢየሱስ ፍጹም እርጋታ ይነበብበት ነበር። ኢየሱስ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል!

14, 15. ከመሲሑ ልብስ እንዲሁም እንዲጠጣ ከተሰጠው ሆምጣጤ ጋር በተያያዘ በዝርዝር የተነገሩት ትንቢቶች የተፈጸሙት እንዴት እንደሆነ አብራራ።

14 በመሲሑ ልብሶች ላይ ዕጣ ይጣጣላሉ። መዝሙራዊው “ልብሶቼን ተከፋፈሉ፤ በእጀ ጠባቤም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ” በማለት ጽፏል። (መዝ. 22:18) የተፈጸመውም ይኸው ነበር፤ ኢየሱስን “ከሰቀሉት በኋላ” የሮም ወታደሮች “ዕጣ ተጣጥለው መደረቢያዎቹን ተከፋፈሉ።”​—ማቴ. 27:35፤ ዮሐንስ 19:23, 24ን አንብብ።

15 ለመሲሑ ሆምጣጤና ሐሞት ይሰጡታል። መዝሙራዊው “ምግቤን ከሐሞት ቀላቀሉ፤ ለጥማቴም ሆምጣጤ ሰጡኝ” ብሏል። (መዝ. 69:21) ማቴዎስ እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “ሐሞት የተቀላቀለበት ወይን ጠጅ እንዲጠጣ [ለኢየሱስ] ሰጡት፤ እሱ ግን ከቀመሰው በኋላ ሊጠጣው አልፈለገም።” በኋላም “ከመካከላቸው አንዱ ሮጦ በመሄድ ሰፍነግ ወስዶ የኮመጠጠ ወይን ጠጅ ውስጥ ከነከረ በኋላ በመቃ ላይ አድርጎ እንዲጠጣ ሰጠው።”​—ማቴ. 27:34, 48

16. በ⁠መዝሙር 22:1 ላይ የተነገረው ትንቢት የተፈጸመው እንዴት እንደሆነ አብራራ።

16 መሲሑን አምላክ የተወው ይመስላል። (መዝሙር 22:1ን አንብብ።) ልክ በትንቢት እንደተነገረው “[በዘጠነኛው] ሰዓት ኢየሱስ በታላቅ ድምፅ ‘ኤሊ፣ ኤሊ፣ ላማ ሳባቅታኒ?’ ብሎ ጮኸ፤ ትርጉሙም ‘አምላኬ፣ አምላኬ ለምን ተውከኝ?’ ማለት ነው።” (ማር. 15:34) ኢየሱስ ይህን ማለቱ በሰማይ በሚገኘው አባቱ ላይ ያለው እምነት እንደጠፋ የሚያሳይ አይደለም። አምላክ፣ የክርስቶስ ታማኝነት ሙሉ በሙሉ እንዲፈተን ሲል ለእሱ ጥበቃ ማድረጉን በማቆሙ ኢየሱስን በጠላቶቹ እጅ ትቶታል ማለት ይችላል። ኢየሱስ ከላይ እንደተገለጸው ብሎ መጮኹ መዝሙር 22:1 እንዲፈጸም አድርጓል።

17. ዘካርያስ 12:10 እና መዝሙር 34:20 የተፈጸሙት እንዴት ነው?

17 መሲሑ ይወጋል፤ ሆኖም ከአጥንቶቹ መካከል አንዱም አይሰበርም። የኢየሩሳሌምን ነዋሪዎች በተመለከተ “ወደ ወጉኝ ወደ እኔም ይመለከታሉ” የሚል ትንቢት ተነግሮ ነበር። (ዘካ. 12:10) በተጨማሪም መዝሙር 34:20 አምላክ “ዐጥንቶቹን ሁሉ ይጠብቃል፤ ከእነርሱም አንድ አይሰበርም” ይላል። ሐዋርያው ዮሐንስ እነዚህ ትንቢቶች መፈጸማቸውን ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ከወታደሮቹ አንዱ [ኢየሱስን] ጎኑን በጦር ወጋው፤ ወዲያውም ደምና ውኃ ፈሰሰ። ይህን ያየው ሰውም [ይኸውም ዮሐንስ] ምሥክርነት ሰጥቷል፤ ምሥክርነቱም እውነት ነው፤ . . . ይህም የሆነው ‘ከእሱ አንድ አጥንት እንኳ አይሰበርም’ የሚለው የቅዱስ መጽሐፉ ቃል እንዲፈጸም ነው። ደግሞም ሌላ የቅዱስ መጽሐፉ ቃል ‘የወጉትን ያዩታል’ ይላል።”​—ዮሐ. 19:33-37

18. ኢየሱስ ከባለጠጎች ጋር ሊቀበር የቻለው እንዴት ነው?

18 መሲሑ ከባለጠጎች ጋር ይቀበራል። (ኢሳይያስ 53:5, 8, 9ን አንብብ።) ኒሳን 14 ምሽት ላይ “የአርማትያስ ሰው የሆነ ዮሴፍ የሚባል አንድ ሀብታም” ሰው ወደ ጲላጦስ ሄዶ የኢየሱስ አስከሬን እንዲሰጠው ጠየቀ፤ ጲላጦስም እንዲሰጠው አዘዘ። ማቴዎስ አክሎም በዘገባው ላይ እንዲህ ብሏል፦ “ዮሴፍም አስከሬኑን ወስዶ በንጹሕ በፍታ ገነዘው፤ ከዐለት ፈልፍሎ በሠራው በራሱ አዲስ የመታሰቢያ መቃብር ውስጥም አኖረው። ከዚያም አንድ ትልቅ ድንጋይ አንከባሎ የመታሰቢያ መቃብሩን ደጃፍ ዘጋውና ሄደ።”​—ማቴ. 27:57-60

መሲሐዊውን ንጉሥ አወድሱት!

19. በ⁠መዝሙር 16:10 ላይ ከሚገኘው ትንቢት ጋር በሚስማማ መልኩ ምን ተፈጽሟል?

19 መሲሑ ከሞት ይነሳል። ዳዊት “በሲኦል ውስጥ አትተወኝምና” በማለት ጽፏል። (መዝ. 16:10) የኢየሱስ አስከሬን ወደተቀመጠበት መቃብር የመጡት ሴቶች በተመለከቱት ነገር ምን ያህል ተገርመው ሊሆን እንደሚችል አስበው! በዚያ ያገኙት ሥጋ የለበሰ መልአክ እንዲህ አላቸው፦ “አትደንግጡ። የምትፈልጉት ተሰቅሎ የነበረውን የናዝሬቱን ኢየሱስን ነው። እሱ ተነስቷል፤ እዚህ የለም። ተመልከቱ! እሱን ያኖሩበት ስፍራ ይኸውና።” (ማር. 16:6) በ33 ዓ.ም. በጴንጤቆስጤ በዓል ዕለት በኢየሩሳሌም ተሰብስበው ለነበሩት ሰዎች ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “አምላክ ክርስቶስን በሔዲስ እንደማይተወውና ሥጋውም እንደማይበሰብስ [ዳዊት] አስቀድሞ ተረድቶ ስለ ትንሣኤው ተናገረ።” (ሥራ 2:29-31) አምላክ የሚወደው ልጁ ሥጋ እንዲበሰብስ አልፈቀደም። ከዚህም በላይ ኢየሱስ በተአምራዊ ሁኔታ መንፈስ ሆኖ ከሞት ተነስቷል።​—1 ጴጥ. 3:18

20. ስለ መሲሑ አገዛዝ ምን ትንቢቶች ተነግረዋል?

20 አስቀድሞ እንደተነገረው አምላክ፣ ኢየሱስ ልጁ እንደሆነ ተናግሯል። (መዝሙር 2:7ን እና ማቴዎስ 3:17ን አንብብ።) ብዙ ሕዝብም ኢየሱስንና የሚመጣውን መንግሥት አወድሰዋል፤ እኛም ስለ ኢየሱስና ስለ መንግሥቱ በደስታ እንናገራለን። (ማር. 11:7-10) ክርስቶስ በቅርቡ “ስለ እውነት፣ ስለ ትሕትና ስለ ጽድቅ . . . በድል አድራጊነት [በመገሥገሥ]” ጠላቶቹን ያጠፋል። (መዝ. 2:8, 9፤ 45:1-6) ከዚያም በእሱ አገዛዝ ሥር በመላው ምድር ላይ ሰላምና ብልጽግና ይሰፍናል። (መዝ. 72:1, 3, 12, 16፤ ኢሳ. 9:6, 7) ውድ የሆነው የይሖዋ ልጅ በአሁኑ ጊዜ በሰማይ መሲሐዊ ንጉሥ ሆኖ እየገዛ ነው፤ እኛም የይሖዋ ምሥክሮች በመሆን እነዚህን እውነቶች ማወጃችን እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው!

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ኢየሱስን ወዳጁ የከዳውና ደቀ መዛሙርቱ ትተውት የሸሹት እንዴት ነው?

• ከኢየሱስ ክርስቶስ መሰቀል ጋር በተያያዘ ከተነገሩት ትንቢቶች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

• ኢየሱስ ተስፋ የተደረገበት መሲሕ መሆኑን እንድታምን ያደረገህ ምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ እንደ ድል አድራጊ ንጉሥ ሆኖ ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱ የየትኛው ትንቢት ፍጻሜ ነው?

[በገጽ 15 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ኢየሱስ ስለ ኃጢአታችን ሞቷል፤ አሁን ግን መሲሐዊ ንጉሥ ሆኖ እየገዛ ነው