በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በሰላም ለመኖር ጥረት አድርጉ

በሰላም ለመኖር ጥረት አድርጉ

በሰላም ለመኖር ጥረት አድርጉ

“ሰላም የሚገኝበትን . . . ነገር ለማድረግ የተቻለንን ሁሉ ጥረት እናድርግ።”​—ሮም 14:19

1, 2. በይሖዋ ምሥክሮች መካከል ሰላም እንዲኖር አስተዋጽኦ ያደረገው ምንድን ነው?

በአሁኑ ጊዜ እውነተኛ ሰላም ማግኘት አስቸጋሪ ነው። አንድ ዓይነት ብሔር ያላቸውና አንድ ዓይነት ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎችም እንኳ ብዙውን ጊዜ በማኅበራዊ ሁኔታ፣ በሃይማኖትና በፖለቲካ የተከፋፈሉ ናቸው። ከዚህ በተቃራኒ የይሖዋ ሕዝቦች “ከሁሉም ብሔራት፣ ነገዶች፣ ሕዝቦችና ቋንቋዎች የተውጣጡ” ቢሆኑም አንድነት አላቸው።​—ራእይ 7:9

2 በመካከላችን የሚታየው ሰላማዊ ሁኔታ እንዲያው በአጋጣሚ የተገኘ አይደለም። ለዚህ ሰላም በዋነኝነት አስተዋጽኦ ያደረገው በደሙ አማካኝነት ኃጢአታችንን በሸፈነልን በአምላክ ልጅ ላይ ባለን እምነት ምክንያት ‘ከአምላክ ጋር ሰላም ያለን’ መሆኑ ነው። (ሮም 5:1፤ ኤፌ. 1:7) በተጨማሪም እውነተኛው አምላክ ለታማኝ አገልጋዮቹ መንፈስ ቅዱስን የሚሰጣቸው ሲሆን ከመንፈስ ፍሬ ገጽታዎች አንዱ ደግሞ ሰላም ነው። (ገላ. 5:22) ሰላምና አንድነት እንዲኖረን አስተዋጽኦ ያደረገው ሌላው ነገር ‘የዓለም ክፍል አለመሆናችን’ ነው። (ዮሐ. 15:19) በፖለቲካዊ ጉዳዮች ረገድ ከአንድ ጎራ ጋር ከመወገን ይልቅ የገለልተኝነት አቋም እንይዛለን። ‘ሰይፋችንን ቀጥቅጠን ማረሻ ስላደረግን’ በእርስ በርስ ግጭቶችም ሆነ በአገራት መካከል በሚደረጉ ጦርነቶች አንካፈልም።​—ኢሳ. 2:4

3. በመካከላችን ያለው ሰላም ምን ዓይነት ሁኔታ እንዲኖር አስችሏል? በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

3 በመካከላችን ያለው ሰላም እንዳይደፈርስ ወንድሞቻችንን የሚጎዳ ነገር ላለመፈጸም ከመጠንቀቅ የበለጠ ነገር ማድረግ ይኖርብናል። ጉባኤያችን የተለያየ ዘርና ባሕል ባላቸው ክርስቲያኖች የተዋቀረ ቢሆንም ሁላችንም ‘እርስ በርሳችን እንዋደዳለን።’ (ዮሐ. 15:17) በመካከላችን ያለው ሰላም “ለሁሉም፣ በተለይ ደግሞ በእምነት ለሚዛመዱን ሰዎች መልካም ነገር” እንድናደርግ ያነሳሳናል። (ገላ. 6:10) በይሖዋ ሕዝቦች መካከል ያለውን ሰላም የሰፈነበት መንፈሳዊ ገነት ከፍ አድርገን ልንመለከተውና ልንንከባከበው ይገባል። በጉባኤ ውስጥ በሰላም መኖር የምንችለው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

በምንሰናከልበት ጊዜ

4. አንድ ሰው ቅር እንደተሰኘብን ከተሰማን ሰላም ለመፍጠር ምን ማድረግ እንችላለን?

4 ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ሁላችንም ብዙ ጊዜ እንሰናከላለን። በቃል የማይሰናከል ማንም ቢኖር ይህ . . . ፍጹም ሰው ነው” በማለት ጽፏል። (ያዕ. 3:2) በመሆኑም በወንድሞች መካከል የሐሳብ ልዩነቶችና አለመግባባቶች መፈጠራቸው አይቀርም። (ፊልጵ. 4:2, 3) ያም ሆኖ በግለሰቦች መካከል የሚነሳው አለመግባባት የጉባኤውን ሰላም ሳያደፈርስ ሊፈታ ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሰው ቅር እንደተሰኘብን ከተሰማን ተግባራዊ ልናደርገው የሚገባንን ምክር ልብ በል።​—ማቴዎስ 5:23, 24ን አንብብ።

5. በደል ቢፈጸምብን ሰላም ለመፍጠር ምን ማድረግ እንችላለን?

5 አንድ ሰው ቀላል የሆነ በደል ቢፈጽምብንስ? ያስቀየመን ሰው መጥቶ ይቅርታ እንዲጠይቀን መጠበቅ ይኖርብናል? አንደኛ ቆሮንቶስ 13:5 “ፍቅር የበደል መዝገብ የለውም” ይላል። ቅር የሚያሰኝ ነገር ሲያጋጥመን የበደለንን ሰው ይቅር በማለትና ጉዳዩን በመርሳት በሌላ አባባል “የበደል መዝገብ” ባለመያዝ ሰላም ለመፍጠር እንጥራለን። (ቆላስይስ 3:13ን አንብብ።) በዕለት ተዕለት ሕይወታችን የሚያጋጥሙንን ያን ያህል ከባድ ያልሆኑ ቅር የሚያሰኙ ነገሮች በዚህ መንገድ ማለፋችን የተሻለ ነው፤ እንዲህ ማድረጋችን ከእምነት ባልንጀራችን ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረን የሚረዳን ከመሆኑም ሌላ የአእምሮ ሰላም ይሰጠናል። አንድ ጥበብ ያዘለ ምሳሌ “በደልን ንቆ መተውም መከበሪያው ነው” ይላል።​—ምሳሌ 19:11

6. ቅር የተሰኘንበትን ነገር ማለፍ ቢከብደን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

6 ቅር የተሰኘንበትን ነገር ማለፍ ቢከብደንስ? ጆሯቸውን ሰጥተው ለሚያዳምጡን ሁሉ ጉዳዩን ማውራት የጥበብ አካሄድ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። እንዲህ ያለው ሐሜት የጉባኤውን ሰላም ከማደፍረስ ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም። ጉዳዩን በሰላም ለመፍታት ምን ማድረግ ይኖርብናል? ማቴዎስ 18:15 እንዲህ ይላል፦ “ወንድምህ አንድ በደል ቢፈጽም አንተና እሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ጥፋቱን በግልጽ ንገረው። ከሰማህ ወንድምህን መልሰህ የራስህ ታደርገዋለህ።” በ⁠ማቴዎስ 18:15-17 ላይ ያለው ሐሳብ የሚሠራው ከባድ ከሆነ ኃጢአት ጋር በተያያዘ ቢሆንም በቁጥር 15 ላይ የሚገኘው መሠረታዊ ሥርዓት ያስቀየመንን ሰው ደግነት በተንጸባረቀበት መንገድ በግል ማነጋገርና ከእሱ ጋር ያለንን ሰላማዊ ግንኙነት ለማደስ መጣር እንደሚኖርብን ይጠቁማል። *

7. አለመግባባቶች ቶሎ እልባት እንዲያገኙ ማድረግ የሚኖርብን ለምንድን ነው?

7 ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ተቆጡ፤ ነገር ግን ኃጢአት አትሥሩ፤ ተቆጥታችሁ እያለ ፀሐይ አይጥለቅባችሁ፤ ዲያብሎስም ስፍራ እንዲያገኝ አትፍቀዱለት።” (ኤፌ. 4:26, 27) ኢየሱስ “ክስ ከመሠረተብህ ሰው ጋር ወደ ፍርድ ቤት እየሄዳችሁ ሳለ ወዲያው እርቅ ለመፍጠር ጥረት አድርግ” ብሏል። (ማቴ. 5:25) ሰላም ለመፍጠር አለመግባባቶች ቶሎ እልባት እንዲያገኙ ማድረግ ይኖርብናል። ለምን? ቁስል ቶሎ ካልታከመ እንደሚያመረቅዝ ሁሉ የተፈጠረውም አለመግባባት ወዲያው መፍትሔ ካልተሰጠው ይበልጥ ሥር እየሰደደ ይሄዳል። እንግዲያው ኩራት፣ ቅናት ወይም ለቁሳዊ ነገሮች ትልቅ ቦታ መስጠት አለመግባባቶችን ቶሎ ከመፍታት እንዲያግደን አንፍቀድ።​—ያዕ. 4:1-6

ብዙ ሰዎችን የሚያነካካ አለመግባባት

8, 9. (ሀ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን በሮም ጉባኤ ውስጥ ምን ዓይነት የአመለካከት ልዩነት ተፈጥሮ ነበር? (ለ) ጳውሎስ በሮም በነበሩት ክርስቲያኖች መካከል የተነሳውን አለመግባባት በተመለከተ ምን ምክር ሰጥቷል?

8 አንዳንድ ጊዜ በጉባኤ ውስጥ የሚፈጠሩት አለመግባባቶች ሁለት ሰዎችን ብቻ ሳይሆን ብዙዎችን የሚያነካኩ ሊሆኑ ይችላሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት ደብዳቤ በጻፈላቸው በሮም በነበሩት ክርስቲያኖች መካከል እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። አይሁድና አሕዛብ በሆኑ ክርስቲያኖች መካከል አለመግባባት ተነስቶ ነበር። አንዳንድ የጉባኤው አባላት ደካማ ወይም የማያፈናፍን ሕሊና ያላቸውን ሰዎች በንቀት መመልከት ጀምረው ነበር። እነዚህ ግለሰቦች፣ ለእያንዳንዱ ሰው ሕሊና በተተዉ ጉዳዮች ረገድ በሌሎች ላይ አላግባብ ይፈርዱ ነበር። ታዲያ ጳውሎስ ለጉባኤው ምን ምክር ሰጠ?​—ሮም 14:1-6

9 ጳውሎስ በሁለቱም ወገን ለነበሩት ሰዎች ምክር ሰጥቷል። በሙሴ ሕግ ሥር እንዳልሆኑ የተገነዘቡት ክርስቲያኖች የእምነት ባልንጀሮቻቸውን እንዳይንቁ መክሯል። (ሮም 14:2, 10) የእነዚህ ክርስቲያኖች አመለካከት፣ በሕጉ ሥር ያልተፈቀዱትን ነገሮች መብላት የሚከብዳቸውን የእምነት አጋሮቻቸውን ሊያደናቅፋቸው ይችላል። ጳውሎስ “ለምግብ ብለህ የአምላክን ሥራ ማፍረስ ተው” በማለት መክሯቸዋል። አክሎም “ወንድምህ የሚሰናከልበት ከሆነ ሥጋ አለመብላት ወይም የወይን ጠጅ አለመጠጣት ወይም ማንኛውንም የሚያሰናክል ነገር አለማድረግ መልካም ነው” ብሏል። (ሮም 14:14, 15, 20, 21) በሌላ በኩል ጳውሎስ የማያፈናፍን ሕሊና ያላቸው ክርስቲያኖች፣ ሰፋ ያለ አመለካከት ያላቸውን ወንድሞች ታማኝ እንዳልሆኑ አድርገው ሊመለከቷቸው እንደማይገባ ተናግሯል። (ሮም 14:13) “እያንዳንዱ ሰው ከሚገባው በላይ ስለ ራሱ በማሰብ ራሱን ከፍ አድርጎ አይመልከት” ብሏቸዋል። (ሮም 12:3) ሐዋርያው ለሁለቱም ወገኖች ምክር ከሰጠ በኋላ “ስለዚህ ሰላም የሚገኝበትንና እርስ በርሳችን የምንተናነጽበትን ነገር ለማድረግ የተቻለንን ሁሉ ጥረት እናድርግ” በማለት ጽፏል።​—ሮም 14:19

10. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት የሮም ክርስቲያኖች እንዳደረጉት ሁሉ በዛሬው ጊዜም አለመግባባቶችን ለመፍታት ምን ማድረግ ያስፈልጋል?

10 በሮም የነበረው ጉባኤ አባላት የጳውሎስን ምክር ሰምተው አስፈላጊውን ማስተካከያ እንዳደረጉ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። በዛሬው ጊዜም በክርስቲያኖች መካከል አለመግባባት ሲነሳ ቅዱሳን መጻሕፍት ምን እንደሚሉ ለማወቅና ይህን በተግባር ለማዋል በትሕትና ጥረት ማድረግ እንዲሁም ችግሩን በፍቅር ለመፍታት መሞከር አይኖርብንም? በሮም የነበሩት ክርስቲያኖች እንዳደረጉት ሁሉ በዛሬው ጊዜም አለመግባባት ሲፈጠር በሁለቱም ወገን ያሉት ሰዎች ‘እርስ በርስ ሰላም እንዲኖር’ አስፈላጊውን ማስተካከያ ማድረግ ያስፈልጋቸዋል።​—ማር. 9:50

ሽማግሌዎች እርዳታ እንዲሰጡ ሲጠየቁ

11. አንድ ክርስቲያን ከእምነት ባልንጀራው ጋር ስለተፈጠረው ችግር ለአንድ ሽማግሌ ቢነግረው ሽማግሌው ምን ከማድረግ መቆጠብ ይኖርበታል?

11 አንድ ክርስቲያን፣ ከቤተሰቡ አባላት ወይም ከእምነት ባልንጀራው ጋር የተፈጠረውን ችግር አስመልክቶ አንድን ሽማግሌ ለማነጋገር ቢፈልግስ? ምሳሌ 21:13 “ሰው የድኾችን ጩኸት ላለመስማት ጆሮውን ቢዘጋ፣ እርሱም ይጮሃል፤ መልስም አያገኝም” ይላል። አንድ ሽማግሌ የሌሎችን ችግር ላለመስማት ‘ጆሮውን እንደማይዘጋ’ ምንም ጥርጥር የለውም። አንድ ምሳሌ ደግሞ እንዲህ ይላል፦ “አስቀድሞ ጕዳዩን የሚያሰማ ትክክለኛ ይመስላል፤ ይኸውም ባላንጣው መጥቶ እስከሚመረመር ድረስ ነው።” (ምሳሌ 18:17) አንድ ሽማግሌ፣ ወንድሞች ሲያናግሩት በደግነት ማዳመጥ ይኖርበታል፤ ሆኖም ቀድሞ ቅሬታውን ላሰማው ሰው እንዳያደላ መጠንቀቅ አለበት። ይልቁንም ጉዳዩን ካዳመጠ በኋላ ተበዳዩ፣ ቅር ያሰኘውን ሰው አነጋግሮት እንደሆነ ይጠይቀዋል። በተጨማሪም ሽማግሌው፣ ቅር ለተሰኘው ሰው ሰላም ለመፍጠር መውሰድ የሚገባውን ቅዱስ ጽሑፋዊ እርምጃዎች ይገልጽለታል።

12. አንድ ሰው ያቀረበውን ቅሬታ ብቻ ሰምቶ በችኮላ እርምጃ መውሰድ የሚያስከትለውን ችግር የሚያሳዩ ምሳሌዎችን ጥቀስ።

12 አለመግባባት በሚፈጠርበት ጊዜ አንደኛው ወገን የተናገረውን ብቻ ሰምቶ እርምጃ መውሰድ የሚያስከትለውን ችግር የሚያሳዩ ሦስት የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎችን እንመልከት። የጲጥፋራ ሚስት፣ ዮሴፍ ሊደፍራት እንደሞከረ ለባሏ በነገረችው ጊዜ ጲጥፋራ ወሬውን ስላመነ በነገሩ ተቆጥቶ ዮሴፍን እስር ቤት በማስገባት ተገቢ ያልሆነ እርምጃ ወሰደ። (ዘፍ. 39:19, 20) ሲባ፣ ጌታው ሜምፊቦስቴ ከዳዊት ጠላቶች ጋር እንዳበረ ለንጉሥ ዳዊት ሲነግረው ንጉሡ አመነው። ስለሆነም ዳዊት ስለ ጉዳዩ ቆም ብሎ ሳያስብ ሲባን “የሜምፊቦስቴ የነበረው ሁሉ ከእንግዲህ ያንተ ነው” አለው። (2 ሳሙ. 16:4፤ 19:25-27) ንጉሥ አርጤክስስ አይሁዳውያን የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች እንደገና እየሠሩ እንዳሉና በፋርስ ግዛት ላይ ሊያምፁ እንደሆነ የሚገልጽ ወሬ ደረሰው። ንጉሡም ይህን የሐሰት ወሬ ስላመነ በኢየሩሳሌም የሚካሄደው የግንባታ ሥራ ሁሉ እንዲቆም አዘዘ። በዚህም የተነሳ አይሁዳውያኑ የአምላክን ቤተ መቅደስ ማደሳቸውን አቆሙ። (ዕዝራ 4:11-13, 23, 24) በእርግጥም ጳውሎስ፣ አንድን ጉዳይ በደንብ ሳያጤን ቸኩሎ ውሳኔ እንዳያደርግ ለጢሞቴዎስ የሰጠውን ምክር ክርስቲያን ሽማግሌዎች መከተላቸው ጥበብ ነው።​—1 ጢሞቴዎስ 5:21ን አንብብ።

13, 14. (ሀ) በሰዎች መካከል የተፈጠረ አለመግባባትን በምንሰማበት ጊዜ ሁላችንም ልናስታውሰው የሚገባው ነገር ምንድን ነው? (ለ) ሽማግሌዎች ከእምነት ባልንጀሮቻቸው ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ተገቢውን ውሳኔ ለማስተላለፍ ምን ሊረዳቸው ይችላል?

13 ከተፈጠረው አለመግባባት ጋር በተያያዘ የሁለቱንም ወገኖች ሐሳብ ብንሰማም እንኳ “አንድ ሰው ስለ አንድ ነገር እውቀት አለኝ ብሎ የሚያስብ ከሆነ ስለዚያ ነገር ማወቅ የሚገባውን ያህል ገና አላወቀም” የሚለውን ምክር መከተላችን አስፈላጊ ነው። (1 ቆሮ. 8:2) አለመግባባቱ እንዲፈጠር ምክንያት የሆኑትን ዝርዝር ጉዳዮች በሙሉ እናውቃለን? ስለ ግለሰቦቹ ሁሉንም ነገር እናውቃለን? ሽማግሌዎች የፍርድ ጉዳዮችን በሚመለከቱበት ጊዜ በውሸት ወሬ፣ በአሉባልታ ወይም ብልጠት በተሞላበት አነጋገር እንዳይታለሉ መጠንቀቃቸው ምንኛ አስፈላጊ ነው! አምላክ የሾመው ዳኛ ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስ የሚፈርደው በጽድቅ ነው። “ዐይኑ እንዳየ አይፈርድም፤ ጆሮውም እንደ ሰማ አይበይንም።” (ኢሳ. 11:3, 4) ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ የሚመራው በይሖዋ መንፈስ ነው። ክርስቲያን ሽማግሌዎችም በአምላክ ቅዱስ መንፈስ መመራታቸው ጠቃሚ ነው።

14 ሽማግሌዎች ከእምነት ባልንጀሮቻቸው ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ከማስተላለፋቸው በፊት የይሖዋን መንፈስ እርዳታ ለማግኘት መጸለይ እንዲሁም የአምላክን ቃል ብሎም ታማኝና ልባም ባሪያ ያዘጋጃቸውን ጽሑፎች በመመርመር የመንፈስ ቅዱስን አመራር ለማግኘት መጣር ይኖርባቸዋል።​—ማቴ. 24:45

ለሰላም ሲባል ማንኛውንም መሥዋዕትነት መክፈል ይኖርብናል?

15. አንድ ክርስቲያን ከባድ ኃጢአት እንደፈጸመ ብናውቅ ጉዳዩን ለሽማግሌዎች መናገር ያለብን መቼ ነው?

15 ክርስቲያኖች በሰላም ለመኖር ጥረት እንድናደርግ ተመክረናል። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ “ከላይ የሆነው ጥበብ . . . በመጀመሪያ ንጹሕ . . . ከዚያም ሰላማዊ” እንደሆነ ይናገራል። (ያዕ. 3:17) ሰላማዊ መሆን ንጹሕ ከመሆን ይኸውም ንጹሕ የሆኑትን የአምላክ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ከመጠበቅና የጽድቅ መሥፈርቶቹን ከማክበር ቀጥሎ የሚመጣ ነገር ነው። አንድ ክርስቲያን፣ የእምነት ባልንጀራው ከባድ ኃጢአት እንደፈጸመ ቢያውቅ ግለሰቡ ኃጢአቱን ለሽማግሌዎች እንዲናገር ሊያበረታታው ይገባል። (1 ቆሮ. 6:9, 10፤ ያዕ. 5:14-16) ኃጢአት የሠራው ግለሰብ እንዲህ ካላደረገ ስለ ጉዳዩ ያወቀው ክርስቲያን ሁኔታውን ለሽማግሌዎች መናገር አለበት። ይህ ክርስቲያን፣ ኃጢአት ከሠራው ሰው ጋር ያለውን ሰላም ለመጠበቅ በሚል ጉዳዩን ሳይናገር ቢቀር በኃጢአቱ ተባባሪ ይሆናል።​—ዘሌ. 5:1፤ ምሳሌ 29:24ን አንብብ።

16. ኢዩ ከንጉሥ ኢዮራም ጋር በተገናኘበት ጊዜ ካደረገው ነገር ምን እንማራለን?

16 ስለ ኢዩ የሚገልጽ አንድ ዘገባ፣ ሰላም ፈጣሪ ከመሆን የበለጠ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው የአምላክን የጽድቅ መሥፈርቶች ማክበር እንደሆነ ያሳያል። አምላክ በንጉሥ አክዓብ ቤት ላይ የፍርድ እርምጃ እንዲወስድ ኢዩን ልኮት ነበር። የአክዓብና የኤልዛቤል ልጅ የነበረው ክፉው ንጉሥ ኢዮራም፣ ኢዩን ለመገናኘት በሠረገላው ሄደ፤ ሲገናኙም “ኢዩ፣ የመጣኸው በሰላም ነውን?” ሲል ጠየቀው። ኢዩ ምን ምላሽ ሰጠ? “የእናትህ የኤልዛቤል የጣዖት አምልኮና መተት እንዲህ በዝቶ እያለ ምን ሰላም አለ!” ሲል መለሰለት። (2 ነገ. 9:22) ከዚያም ኢዩ ቀስቱን በማስፈንጠር ኢዮራምን ልቡ ላይ ወጋው። ኢዩ እንዳደረገው ሁሉ ሽማግሌዎችም ሰላምን ለማስፈን ሲሉ፣ ሆን ብለው ኃጢአት በሚሠሩና ንስሐ ለመግባት ፈቃደኛ በማይሆኑ ሰዎች ላይ እርምጃ ይወስዳሉ። ሽማግሌዎች፣ ጉባኤው ከአምላክ ጋር ያለውን ሰላም ጠብቆ እንዲኖር ለማድረግ ሲሉ ንስሐ የማይገቡ ኃጢአተኞችን ያስወግዷቸዋል።​—1 ቆሮ. 5:1, 2, 11-13

17. ሁሉም ክርስቲያኖች ሰላም ፈጣሪ በመሆን ረገድ ምን አስተዋጽኦ ያደርጋሉ?

17 በወንድሞች መካከል የሚነሱት አብዛኞቹ አለመግባባቶች የፍርድ እርምጃ መውሰድ የሚጠይቁ ከባድ ኃጢአቶች አይደሉም። በመሆኑም የሌሎችን ስህተት በፍቅር ማለፉ ምንኛ የተሻለ ነው! የአምላክ ቃል “በደልን የሚሸፍን ፍቅርን ያዳብራል፤ ነገርን የሚደጋግም ግን የልብ ወዳጆችን ይለያያል” ይላል። (ምሳሌ 17:9) ሁላችንም ይህን ምክር መታዘዛችን የጉባኤውን ሰላም ለመጠበቅና ከይሖዋ ጋር ያለንን ጥሩ ወዳጅነት ጠብቀን ለመኖር ያስችለናል።​—ማቴ. 6:14, 15

በሰላም ለመኖር ጥረት ማድረግ በረከት ያስገኛል

18, 19. ሰላም ፈጣሪዎች ለመሆን ጥረት ማድረጋችን ምን ጥቅሞች ያስገኝልናል?

18 “ሰላም የሚገኝበትን” ነገር ለማድረግ የተቻለንን ሁሉ ጥረት ማድረጋችን የተትረፈረፈ በረከት ያስገኝልናል። የይሖዋን ምሳሌ ስንከተል ከእሱ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ይኖረናል፤ እንዲሁም በይሖዋ ሕዝቦች መካከል ያለው መንፈሳዊ ገነት ሰላምና አንድነት የሰፈነበት እንዲሆን አስተዋጽኦ እናደርጋለን። በጉባኤ ውስጥ ሰላም ለመፍጠር ጥረት ማድረጋችን “የሰላምን ምሥራች” ከምንሰብክላቸው ሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ሰላም ፈጣሪ መሆን የምንችልባቸውን መንገዶች እንድናስተውልም ይረዳናል። (ኤፌ. 6:15) እንዲሁም ‘ለሰው ሁሉ ገርና ክፉ ነገር ሲደርስብን በትዕግሥት የምናሳልፍ’ እንድንሆን ያስችለናል።​—2 ጢሞ. 2:24

19 ከዚህም በተጨማሪ “ጻድቃንም ሆኑ ዓመፀኞች ከሞት እንደሚነሱ” እናስታውስ። (ሥራ 24:15) ይህ ተስፋ ፍጻሜውን ሲያገኝ የተለያየ አስተዳደግ፣ ባሕርይና ስብዕና ያላቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከሞት ይነሳሉ፤ ይህም ሲባል “ዓለም ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ” በሞት ያንቀላፉ ሰዎች በሙሉ ትንሣኤ ያገኛሉ ማለት ነው። (ሉቃስ 11:50, 51) ከሞት የተነሡትን ሰዎች ሰላም ወዳድ እንዲሆኑ ማስተማር እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! ሰላም ፈጣሪዎች እንድንሆን በአሁኑ ጊዜ የምናገኘው ሥልጠና በዚያ ወቅት በጣም እንደሚጠቅመን ምንም ጥርጥር የለውም።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.6 እንደ ስም ማጥፋትና ማጭበርበር ያሉትን ከባድ ኃጢአቶች በተመለከተ ምን መደረግ እንዳለበት ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያ ለማግኘት የጥቅምት 15, 1999 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 17-22 ተመልከት።

ምን ትምህርት አግኝተሃል?

• አንድ ሰው ቅር እንደተሰኘብን ከተሰማን ሰላም ለመፍጠር ምን ማድረግ እንችላለን?

• በደል ቢፈጸምብን ሰላም ለመፍጠር ምን ማድረግ እንችላለን?

• በሰዎች መካከል ስለተፈጠረ አለመግባባት በምንሰማበት ጊዜ ከአንደኛው ወገን ጎን መቆማችን ጥበብ ያልሆነው ለምንድን ነው?

• ለሰላም ሲባል ማንኛውንም መሥዋዕትነት መክፈል ተገቢ ያልሆነው ለምን እንደሆነ አብራራ።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 29 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ይሖዋ በነፃ ይቅር የሚሉ ሰዎችን ይወዳል