በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ስለ መሲሑ የሚናገሩት ትንቢቶች ምን ያህል እንደሆኑ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል?
የአንባቢያን ጥያቄዎች
በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ስለ መሲሑ የሚናገሩት ትንቢቶች ምን ያህል እንደሆኑ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል?
የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን በጥልቀት ስንመረምር በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የተፈጸሙ በርካታ ትንቢቶችን ማግኘት እንችላለን። እነዚህ ትንቢቶች ስለ መሲሑ ታሪክ፣ ስለሚገለጥበት ጊዜ፣ ስለሚያከናውናቸው ተግባሮች፣ ስለሚደርሱበት ነገሮች እንዲሁም በይሖዋ አምላክ ዝግጅት ውስጥ ስለሚኖረው ድርሻ በዝርዝር ይናገራሉ። እነዚህ ሁሉ ትንቢቶች አንድ ላይ ሲጣመሩ ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ለማወቅ ያስችሉናል። ይሁን እንጂ በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙት ስለ መሲሑ የሚናገሩት ትንቢቶች ትክክለኛ ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ የምንሞክር ከሆነ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል።
ስለ መሲሑ የሚናገሩት ትንቢቶች የትኞቹ ናቸው? በሚለው ጉዳይ ላይ ያለው አመለካከት የተለያየ ነው። አልፍሬድ ኢደርሻይም ዘ ላይፍ ኤንድ ታይምስ ኦቭ ጂሰስ ዘ መሳያ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንደገለጹት የጥንቱ የረቢዎች ጽሑፍ፣ ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ 456 ጥቅሶችን ስለ መሲሑ የሚናገሩ ትንቢቶች እንደሆኑ አድርጎ ይቆጥራቸዋል፤ እርግጥ ነው፣ ከእነዚህ መካከል ብዙዎቹ መሲሑን በቀጥታ አይጠቅሱም። እነዚህን 456 ጥቅሶች በጥልቀት ስንመረምራቸው አንዳንዶቹ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚናገሩ ትንቢቶች መሆናቸው ጥያቄ ያስነሳል። ለምሳሌ ያህል፣ ኢደርሻይም እንደተናገሩት አይሁዶች በዘፍጥረት 8:11 ላይ ያለውን ሐሳብ ስለ መሲሑ የሚናገር ትንቢት እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል። አይሁዳውያን “ርግቧ ያመጣችው የወይራ ቅጠል ከመሲሑ ተራራ የተወሰደ” እንደሆነ ይናገራሉ። ኢደርሻይም ዘፀአት 12:42ንም ጠቅሰዋል። አይሁዳውያን ይህን ጥቅስ “ሙሴ ከበረሃው እንደወጣ ሁሉ መሲሑም ከሮም ይወጣል” ብለው በተሳሳተ መንገድ እንደተረዱት ጽፈዋል። በርካታ ምሑራንና ሌሎች ብዙ ሰዎች እነዚህን ሁለት ጥቅሶች ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ከተሰጡት የተሳሳቱ ማብራሪያዎች ጋር ማዛመድ ይከብዳቸዋል።
በትክክል በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ፍጻሜያቸውን ያገኙ ትንቢቶችን ብቻ እንኳ ብንወስድ ቁጥራቸው ምን ያህል ነው? በሚለው ነጥብ ላይ ሁሉም ሰው ላይስማማ ይችላል። ኢሳይያስ ምዕራፍ 53ን እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ በዚህ ምዕራፍ ላይ ስለ መሲሑ የሚገልጹ በርካታ ሐሳቦች አሉ። በኢሳይያስ 53:2-7 ላይ እንዲህ የሚል ትንቢት እናገኛለን፦ “የሚስብ ውበት ወይም ግርማ የለውም፤ . . . በሰዎች የተናቀና የተጠላ [ነበር]። . . . እርሱ ደዌያችንን ወሰደ፤ . . . እርሱ ስለ መተላለፋችን ተወጋ፤ . . . እንደ ጠቦትም ለዕርድ ተነዳ።” በኢሳይያስ ምዕራፍ 53 ላይ የሚገኘው ይህ ጥቅስ በአጠቃላይ፣ ስለ መሲሑ እንደሚናገር አንድ ትንቢት ተደርጎ ሊቆጠር ይገባል? ወይስ ስለ መሲሑ የተነገሩት ነገሮች እያንዳንዳቸው ራሳቸውን የቻሉ ትንቢቶች ናቸው?
በኢሳይያስ 11:1 ላይ የሚገኘውን “ከእሴይ ግንድ ቍጥቋጥ ይወጣል፤ ከሥሮቹም አንዱ ቅርንጫፍ ፍሬ ያፈራል” የሚለውን ትንቢትም እንመልከት። በቁጥር 10 ላይም ከዚህ ትንቢት ጋር ተመሳሳይ የሆነ ሐሳብ እናገኛለን። እነዚህን ሁለት ጥቅሶች እንደ ሁለት የተለያዩ ትንቢቶች አድርገን ልንወስዳቸው ይገባል? ወይስ በድጋሚ እንደተገለጸ አንድ ትንቢት አድርገን እንመለከታቸዋለን? በኢሳይያስ ምዕራፍ 53 እና በኢሳይያስ ምዕራፍ 11 ላይ ካሉት ትንቢቶች ጋር በተያያዘ የምንደርስበት መደምደሚያ ስለ መሲሑ በሚናገሩት ትንቢቶች ብዛት ላይ ለውጥ እንደሚያመጣ ግልጽ ነው።
እንግዲያው በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙት ስለ መሲሑ የሚናገሩ ትንቢቶች አጠቃላይ ቁጥር ይህ ነው ብለን በእርግጠኝነት መናገር አንችልም። የይሖዋ ድርጅት ስለ ኢየሱስ የሚናገሩ በርካታ ትንቢቶችንና ፍጻሜያቸውን የሚያሳዩ ዝርዝሮችን አውጥቷል። * እነዚህን ዝርዝሮች በግልና በቤተሰብ ጥናታችን እንዲሁም በአገልግሎታችን ልንጠቀምባቸው እንችላለን። እንዲሁም ይሖዋ የተናገረው ነገር ምንጊዜም እንደሚፈጸም ያለንን እምነት ያጠናክሩልናል። ከዚህም በተጨማሪ ስለ መሲሑ የሚናገሩት በርካታ ትንቢቶች ቁጥራቸው ምንም ያህል ይሁን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ መሲሕ ለመሆኑ ጠንካራ ማስረጃ ይሰጡናል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.7 ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 1 ገጽ 1223፤ ጥራዝ 2 ገጽ 387፤ ‘ቅዱስ መጽሐፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈና ጠቃሚ ነው’ (እንግሊዝኛ) ገጽ 343-344፤ ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? ገጽ 200