በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ታሪካዊ ስብሰባ

ታሪካዊ ስብሰባ

ታሪካዊ ስብሰባ

“የዛሬው ስብሰባ ሲያበቃ ‘ከቲኦክራሲያዊ ክንውኖች አንጻር ይህ ዓመታዊ ስብሰባ በእርግጥም ታሪካዊ ነበር!’ ማለታችሁ አይቀርም።” የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ስቲቨን ሌት በዚህ የመግቢያ ሐሳብ በመጠቀም አድማጮች ፕሮግራሙን በጉጉት እንዲጠባበቁ አነሳሳቸው። ዎች ታወር ባይብል ኤንድ ትራክት ሶሳይቲ ኦቭ ፔንሲልቬንያ ጥቅምት 2, 2010 በጀርሲ ሲቲ፣ ኒው ጀርሲ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ባለው የይሖዋ ምሥክሮች የትልልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ ውስጥ ለ126ኛ ጊዜ ባደረገው ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተሰብሳቢዎች ተገኝተዋል። ከዚህ ታሪካዊ ስብሰባ ጎላ ያሉ ገጽታዎች መካከል እስቲ አንዳንዶቹን እንመልከት።

ወንድም ስቲቨን ሌት ያቀረበው የመክፈቻ ንግግር፣ በሕዝቅኤል መጽሐፍ ላይ የተገለጸውን በሰማይ የሚገኘውን የይሖዋ ሠረገላ ጥሩ አድርጎ የሚያብራራ ነበር። ይህ ግዙፍና አስደናቂ የሆነ ሠረገላ ሙሉ በሙሉ በይሖዋ አመራር ሥር የሆነውን የአምላክ ድርጅት ያመለክታል። መንፈሳዊ ፍጡራንን ያቀፈው የዚህ ድርጅት ሰማያዊ ክፍል በብርሃን ፍጥነት ማለትም ይሖዋ በሚያስብበት ፍጥነት እንደሚጓዝ ወንድም ሌት ገልጿል። የይሖዋ አምላክ ድርጅት ምድራዊ ክፍልም እንዲሁ በጉዞ ላይ ነው። ወንድም ሌት፣ በቅርብ ዓመታት ውስጥ በአምላክ ድርጅት ምድራዊ ክፍል ውስጥ የተፈጸሙ በርካታ አስደሳች ክንውኖችን ጠቅሷል።

ለምሳሌ ያህል፣ በርካታ ቅርንጫፍ ቢሮዎች በተወሰኑ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ሥር እንዲታቀፉ እየተደረጉ ነው፤ ይህ መሆኑ ቀደም ሲል በእነዚህ አገሮች ውስጥ በቤቴል ያገለግሉ የነበሩት በርካታ ወንድሞችና እህቶች በስብከቱ ሥራ ላይ እንዲያተኩሩ ያስችላል። ወንድም ሌት ታማኝና ልባም ባሪያን የሚወክለው የበላይ አካል፣ ታማኝ ብቻ ሳይሆን ብልኅ ወይም ልባም ሆኖ መሥራቱን እንዲቀጥል ተሰብሳቢዎቹ እንዲጸልዩ አበረታታቸው።​—ማቴ. 24:45-47

የሚያበረታቱ ሪፖርቶችና አስደሳች ቃለ ምልልሶች

የሄይቲ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ታብ ሃንስበርገር፣ ጥር 12, 2010 የተከሰተውና በዚያች አገር የ300,000 ገደማ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው የመሬት መናወጥ ስላስከተለው ጉዳት የሚገልጽ የሚያሳዝን ሪፖርት አቀረበ። በዚያች አገር የሚገኙት ቀሳውስት፣ እምነት የለሽ የሆኑትን ሰዎች አምላክ እንደቀጣቸውና ለጥሩ ሰዎች ግን ጥበቃ እንዳደረገላቸው ይናገሩ እንደነበር ወንድም ሃንስበርገር ገልጿል። ይሁን እንጂ በመሬት መናወጡ ሳቢያ አንድ ወኅኒ ቤት ሲፈርስ በሺዎች የሚቆጠሩ ወንጀለኞች ነፃ ወጥተዋል። በዚህ ሁኔታ ግራ የተጋቡ በርካታ ቅን ልብ ያላቸው የሄይቲ ነዋሪዎች፣ ያለንበት ጊዜ በመከራ የተሞላው ለምን እንደሆነ እውነቱን በማወቃቸው ተጽናንተዋል። ወንድም ሃንስበርገር፣ በአደጋው ሳቢያ ሚስቱን ያጣ ታማኝ የሆነ አንድ የሄይቲ ወንድም እንደሚከተለው እንዳለ ገልጿል፦ “አሁንም ድረስ በሐዘን አነባለሁ። ሐዘኔ መቼ እንደሚወጣልኝ አላውቅም፤ ሆኖም የይሖዋን ድርጅት ፍቅር በማግኘቴ ደስተኛ ነኝ። ተስፋ አለኝ፤ ይህን ተስፋዬን ለሌሎች ለማካፈል ቁርጥ ውሳኔ አድርጌያለሁ።”

በአሁኑ ጊዜ የብሩክሊን ቤቴል ቤተሰብ አባል የሆነው ወንድም ማርክ ሳንደርሰን ስለ ፊሊፒንስ ሪፖርት አቀረበ። ቀደም ሲል የፊሊፒንስ የቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አባል የነበረው ወንድም ሳንደርሰን በዚያ አገር በመንግሥቱ አስፋፊዎች ቁጥር ረገድ ለ32ተኛ ጊዜ በተከታታይ ጭማሪ እንደተገኘና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ቁጥር ከአስፋፊዎች ቁጥር በእጅጉ እንደሚበልጥ ሲናገር ፊቱ ላይ ታላቅ ደስታ ይነበብ ነበር። ወንድም ሳንደርሰን፣ ሚጌል ስለተባሉ የልጅ ልጃቸው ስለተገደሉባቸው ወንድም ተናገረ። ሚጌል፣ ነፍሰ ገዳዩ ለፍርድ እንዲቀርብና ወኅኒ እንዲወርድ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። ከጊዜ በኋላ ሚጌል በእስር ቤት ውስጥ ሲያገለግሉ የልጅ ልጃቸውን ከገደለው ሰው ጋር ተገናኙ። ሚጌል ይህን ሰው ሲያገኙት በጣም ቢረበሹም በእርጋታና በደግነት አነጋገሩት። ውሎ አድሮም ይህን ሰው ያስጠኑት ሲሆን ግለሰቡም እድገት ማድረግና ለይሖዋ ፍቅር ማዳበር ጀመረ። በአሁኑ ጊዜ ይህ ሰው ተጠምቋል። ሚጌል የዚህ ሰው የቅርብ ወዳጅ ሲሆኑ የእስራት ጊዜው እንዲያጥርለት ለማድረግ እየጣሩ ነው። *

ቀጣዩ የፕሮግራሙ ክፍል ቃለ ምልልስ ሲሆን ይህን ያቀረበው ቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶችን በሚከታተለው ክፍል ውስጥ አስተማሪ የሆነው ማርክ ኑሜር ነው። ወንድም ኑሜር፣ ለሦስት ባለትዳሮች ይኸውም ለአሊክስ ራይንሙለርና ለባለቤቱ ሣራ፣ ለዴቪድ ሼፈርና ለባለቤቱ ክሪስተ እንዲሁም ለሮበርት ሲራንኮና ለባለቤቱ ኬትረ ቃለ ምልልስ አደረገላቸው። በኅትመት ኮሚቴ ውስጥ ረዳት ሆኖ የሚሠራው ወንድም አሊክስ ራይንሙለር፣ በካናዳ አቅኚ በነበረበት ወቅት እውነትን የራሱ ያደረገው እንዴት እንደሆነ ተናገረ፤ በዚያ ወቅት የ15 ዓመት ልጅ የነበረ ሲሆን ብዙውን ጊዜ የሚያገለግለው ብቻውን ነበር። ወንድም ራይንሙለር በቤቴል ውስጥ ትልቅ ተጽዕኖ ያሳደረበት ማን እንደሆነ ሲጠየቅ ሦስት ታማኝ ወንድሞችን የጠቀሰ ሲሆን እያንዳንዳቸው በመንፈሳዊ እድገት እንዲያደርግ እንዴት እንደረዱትም ተናግሯል። ባለቤቱ ሣራ ደግሞ በእምነቷ ምክንያት ለአሥርተ ዓመታት በቻይና ከታሰረች እህት ጋር የነበራትን ወዳጅነት ጠቅሳለች። በተጨማሪም እህት ሣራ በጸሎት አማካኝነት በይሖዋ ላይ መታመንን እንደተማረች ገልጻለች።

በትምህርት ኮሚቴ ውስጥ ረዳት ሆኖ የሚያገለግለው ወንድም ዴቪድ ሼፈር እናቱ የነበራትን ጠንካራ እምነት አድንቆ ተናግሯል፤ አክሎም ወጣት በነበረበት ጊዜ ረዳት አቅኚ ሆኖ እንዲያገለግል የረዱትን ዛፍ በመቁረጥ የሚተዳደሩ ወንድሞች ጠቅሷል። ባለቤቱ ክሪስተ ደግሞ ኢየሱስ የሰጠውን ምክር ተግባራዊ በማድረግ “በትንሽ ነገር ታማኝ” የሆኑ በዕድሜ የገፉ የቤቴል ቤተሰብ አባላት ስላሳደሩባት በጎ ተጽዕኖ ሞቅ ባለ ስሜት ገልጻለች።​—ሉቃስ 16:10

የጽሑፍ ዝግጅት ኮሚቴን በመርዳት ላይ የሚገኘው ወንድም ሮበርት ሲራንኮ ስለ አራቱም አያቶቹ ተናገረ፤ አያቶቹ የሃንጋሪ ተወላጆች ሲሆኑ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ነበሩ። በ1950ዎቹ በተካሄዱት ትልልቅ ስብሰባዎች ላይ በልጅነቱ በተገኘበት ወቅት የይሖዋ ድርጅት እሱ ከነበረበት ጉባኤ ይበልጥ በጣም ሰፊ መሆኑን ሲገነዘብ ተደንቆ እንደነበር ተናገረ። ባለቤቱ ኬትረ ደግሞ ክህደትና ሌሎች ችግሮች በነበሩበት ጉባኤ ውስጥ አቅኚ ሆና ስታገለግል የታማኝነትን አስፈላጊነት እንዴት እንደተገነዘበች ገለጸች። እነዚህን ችግሮች ተቋቁማ የጸናች ሲሆን ከጊዜ በኋላ ልዩ አቅኚ ሆና እንድታገለግል በተመደበችበት ጉባኤ ውስጥ የተመለከተችው አንድነት ልቧን እንደነካው ተናግራለች።

ቀጥሎም ወንድም ማንፍሬድ ቶናክ ስለ ኢትዮጵያ ሪፖርት አቀረበ። ኢትዮጵያ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰች አገር ስትሆን በአሁኑ ጊዜ በዚህች አገር ከ9,000 በላይ የምሥራቹ አስፋፊዎች አሉ። አብዛኞቹ የሚኖሩት በዋና ከተማዋ በአዲስ አበባና በአቅራቢያዋ ነው። ስለሆነም ራቅ ያሉ አካባቢዎች የበለጠ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። ርቀው በሚገኙ አካባቢዎች ለሚኖሩ ሰዎች ምሥራቹን ለማድረስ ሲባል በሌሎች አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የይሖዋ ምሥክሮች ለተወሰነ ጊዜ ወደ አገራቸው ተመልሰው እንዲሰብኩ ግብዣ ቀርቦላቸዋል። ብዙዎች ይህን ግብዣ ተቀብለው በመምጣት በአገሪቱ የሚገኙ ወንድሞችን ያበረታቱ ከመሆኑም ሌላ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች አግኝተዋል።

ከፕሮግራሙ ጎላ ያሉ ገጽታዎች አንዱ በሩሲያ ስለሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮችና በፍርድ ቤት ስላደረጉት ትግል የሚገልጽ ሲምፖዚየም ነበር። የሩሲያ ቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም አውሊስ ቤርግዳል የይሖዋ ምሥክሮች በሩሲያ በተለይ ደግሞ በሞስኮ ስለደረሰባቸው ስደት ተረከ። በዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ቢሮ የሕግ ክፍል ውስጥ የሚሠራው ወንድም ፊሊፕ ብረምሊ፣ በቅርብ ወራት ውስጥ የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የቀረቡትን ዘጠኝ ክሶች ከሰማ በኋላ ስለተገኙት አስደሳች ውጤቶች ተናገረ። ፍርድ ቤቱ ዘጠኙም ክሶች መሠረተ ቢስ እንደሆኑ በአንድ ድምፅ የወሰነ ከመሆኑም ሌላ አንዳንዶቹ ክሶች ተቀባይነት የሌላቸው ለምን እንደሆነ በዝርዝር አብራርቷል። የፍርድ ቤቱ ውሳኔ የሚያስገኘው ውጤት ወደፊት የሚታይ ቢሆንም በሌሎች አገሮች ከሚሰነዘሩብን ክሶች ጋር በተያያዘ ሊጠቅመን እንደሚችል ወንድም ብረምሊ ገልጿል።

ከዚህ አስደሳች ዜና በኋላ የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ከቀረጥ ጋር በተያያዘ በፈረንሳይ መንግሥትና በይሖዋ ምሥክሮች መካከል ያለውን ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ክርክር ለመመልከት መስማማቱን ወንድም ሌት አስታወቀ። ከፍተኛ ተደማጭነት ያለው ይህ ፍርድ ቤት ከቀረቡለት ጉዳዮች መካከል የሚያየው ጥቂቶቹን ብቻ ነው። የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት እስከ ዛሬ ድረስ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የተያያዙ 39 ጉዳዮችን የተመለከተ ሲሆን በ37ቱ ላይ ለእኛ ፈርዶልናል። ወንድም ሌት ሁሉም የአምላክ ሕዝቦች ለፍርድ ቤቱ የቀረቡትን ጉዳዮች አስመልክተው ወደ ይሖዋ አምላክ እንዲጸልዩ አበረታታቸው።

የመጨረሻውን ሪፖርት ያቀረበው የጉባኤ ሽማግሌዎች ትምህርት ቤት አስተማሪ የሆነው ወንድም ሪቻርድ ሞርለን ነበር። ስለ ትምህርት ቤቱ በግለት የገለጸ ከመሆኑም ሌላ በትምህርት ቤቱ የተካፈሉት ሽማግሌዎች አድናቆታቸውን እንደገለጹ ተናግሯል።

የበላይ አካል አባላት የሰጧቸው ሌሎች ንግግሮች

የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ጋይ ፒርስ ‘የይሖዋን ስም መጠጊያችሁ አድርጉት’ በሚለው የ2011 የዓመት ጥቅስ ላይ ያተኮረ ሞቅ ያለ ንግግር አቀረበ። (ሶፎ. 3:12 NW) ያለንበት ዘመን ከብዙ አቅጣጫዎች ስናየው ለይሖዋ ሕዝቦች አስደሳች ቢሆንም ወሳኝ ጊዜም እንደሆነ ገለጸ። ታላቁ የይሖዋ ቀን ቀርቧል፤ ይሁንና አሁንም ቢሆን ሰዎች የሐሰት ሃይማኖትን፣ የፖለቲካ ተቋማትን፣ ቁሳዊ ሀብትንና የመሳሰሉትን መጠጊያ የሚያደርጉ ሲሆን አንዳንዶች ደግሞ ከእውነታው ለመሸሽ ይሞክራሉ። እውነተኛ መጠጊያ ለማግኘት የይሖዋን ስም መጥራት ይኸውም ይህ ስም የሚወክለውን አካል ማወቅ፣ በጥልቅ ማክበር፣ በእሱ መታመንና በሙሉ ነፍሳችን እሱን መውደድ ይኖርብናል።

በመቀጠልም የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ዴቪድ ስፕሌን “ወደ አምላክ እረፍት ገብታችኋል?” በሚል ጭብጥ ትኩረት የሚስብ ንግግር አቀረበ። ወንድም ስፕሌን፣ የአምላክ እረፍት ሥራ የማይሠራበት ጊዜ እንዳልሆነ ጠቁሟል፤ ምክንያቱም ይሖዋና ልጁ፣ ከሰው ልጆች ጋር በተያያዘ የአምላክን ዓላማ በተሳካ ሁኔታ ከዳር ለማድረስ በዚህ ምሳሌያዊ የእረፍት ቀን ‘እየሠሩ’ ናቸው። (ዮሐ. 5:17) ታዲያ ወደ አምላክ እረፍት መግባት የምንችለው እንዴት ነው? ወደ እረፍቱ ለመግባት ኃጢአት ከመሥራት መቆጠብ እንዲሁም በክርስቶስ ኢየሱስና በቤዛዊ መሥዋዕቱ ላይ እምነት ማሳደር ብቻ በቂ አይደለም። እምነት እንዳለን በተግባር ማሳየትና አኗኗራችን ከአምላክ ዓላማ ጋር የሚስማማ መሆን ይኖርበታል፤ ከዚህ ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ ለመመላለስ የምንችለውን ሁሉ ማድረግ ይገባናል። አንዳንድ ጊዜ ይህን ማድረግ አስቸጋሪ ሊሆን ቢችልም የይሖዋ ድርጅት የሚሰጠንን ምክር መቀበልና ከመመሪያው ጋር መተባበር ይኖርብናል። ወንድም ስፕሌን፣ ተሰብሳቢዎቹ ወደ አምላክ እረፍት ለመግባት የተቻላቸውን ሁሉ እንዲያደርጉ አበረታቷል።

“ወደፊት ምን እንጠብቃለን?” የሚለውን የመጨረሻውን ንግግር ያቀረበው የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም አንቶኒ ሞሪስ ነበር። ወንድም ሞሪስ፣ አድማጮቹ የጥድፊያ ስሜት እንዲኖራቸው በሚያበረታታና አባታዊ ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ ባቀረበው በዚህ ንግግር ላይ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች በሙሉ በጉጉት የሚጠብቋቸውን ትንቢታዊ ክንውኖች ጠቀሰ። ከእነዚህም መካከል “ሰላምና ደኅንነት ሆነ!” የሚለው አዋጅ እንዲሁም የሐሰት ሃይማኖት መጥፋት ይገኙበታል። (1 ተሰ. 5:2, 3፤ ራእይ 17:15-17) ወንድም ሞሪስ እንደነዚህ ያሉ ትንቢቶች እስካልተፈጸሙ ድረስ አንዳንድ የዜና ዘገባዎችን ስንሰማ “አርማጌዶን መጣ” ብለን ማሰብ እንደሌለብን አስጠንቅቋል። ከዚህ ይልቅ በ⁠ሚክያስ 7:7 ላይ እንደተገለጸው ደስተኞች ሆነን በትዕግሥት እንድንጠብቅ አበረታቷል። ከዚህም በተጨማሪ ወታደሮች ወደ ተፋፋመ ጦርነት ሲገቡ እንደሚያደርጉት ሁሉ እኛም ከበላይ አካሉ ጋር ተቀራርበን እንድንጓዝ አሳስቧል። ወንድም ሞሪስ “እግዚአብሔርን ተስፋ የምታደርጉ ሁሉ፤ በርቱ፤ ልባችሁም ይጽና” በማለት ንግግሩን ደምድሟል።​—መዝ. 31:24

በመጨረሻም አንዳንድ አስደሳች የሆኑ ታሪካዊ ማስታወቂያዎች ተነገሩ። የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ጄፍሪ ጃክሰን፣ እንግሊዝኛ ማንበብ ለሚከብዳቸው አንባቢዎች ሲባል ቀለል ባለ እንግሊዝኛ የሚዘጋጅ የመጠበቂያ ግንብ የጥናት እትም ለሙከራ ያህል ለማውጣት እንደታቀደ ተናገረ። ከዚያም ወንድም ስቲቨን ሌት፣ በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ ለአውራጃ የበላይ ተመልካቾችና ለሚስቶቻቸው እረኝነት የሚደረግበት ዝግጅት እንደሚኖር አስታወቀ። በተጨማሪም የአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ከዚህ በኋላ ለነጠላ ወንድሞች የተዘጋጀ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ተብሎ እንደሚጠራ ገለጸ። በቅርቡ ደግሞ ከዚህ ትምህርት ቤት በተጨማሪ ለባለትዳሮች የተዘጋጀ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ይከፈታል። ይህ ትምህርት ቤት፣ ባለትዳሮች በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ይበልጥ መሥራት እንዲችሉ ተጨማሪ ሥልጠና ይሰጣቸዋል። ወንድም ሌት፣ የተጓዥ የበላይ ተመልካቾችና የሚስቶቻቸው ትምህርት ቤት እንዲሁም የቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አባላትና የሚስቶቻቸው ትምህርት ቤት በፓተርሰን በየዓመቱ ለሁለት ጊዜ እንደሚካሄድ ማስታወቂያ ተናገረ፤ ከዚህ ቀደም በዚህ ትምህርት ቤት የተካፈሉ ወንድሞች በድጋሚ እንዲካፈሉ ዝግጅት ተደርጓል።

በስብሰባው መደምደሚያ ላይ ለረጅም ጊዜ የቆየ የበላይ አካል አባል የሆነው የ97 ዓመቱ ወንድም ጆን ባር ትሕትና የሚንጸባረቅበት፣ ከልብ የመነጨና ስሜት የሚነካ ጸሎት አቀረበ። * ፕሮግራሙ ሲያበቃ ተሰብሳቢዎቹ በሙሉ ይህ በእርግጥም ታሪካዊ ቀን እንደሆነ ተሰምቷቸው ነበር።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.7 የ2011 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ (እንግሊዝኛ) ገጽ 62, 63⁠ን ተመልከት።

^ አን.20 ወንድም ጆን ባር ታኅሣሥ 4, 2010 ምድራዊ ሕይወቱን አጠናቅቋል።

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ተሰብሳቢዎቹ በሙሉ በቃለ ምልልሶቹ ተደስተዋል

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ይሖዋ በኢትዮጵያ ያለውን የስብከት ሥራ ባርኮታል