በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢንተርኔት​—ዓለም አቀፉን የመረጃ መረብ በጥበብ መጠቀም

ኢንተርኔት​—ዓለም አቀፉን የመረጃ መረብ በጥበብ መጠቀም

ኢንተርኔት​—ዓለም አቀፉን የመረጃ መረብ በጥበብ መጠቀም

ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት የማተሚያ መሣሪያ መፈልሰፉ ሰዎች እርስ በርስ ሐሳብ በሚለዋወጡበት መንገድ ላይ ትልቅ ለውጥ አምጥቶ ነበር። በዘመናችንም ኢንተርኔት መፈልሰፉ ተመሳሳይ ለውጥ አስከትሏል። ይህ ጠቃሚ መሣሪያ ዓለም አቀፍ የመረጃ መረብ የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን እንዲህ ተብሎ መጠራቱም የተገባ ነው። በዚህ ዓለም አቀፍ የመረጃ መረብ አማካኝነት ስለተለያዩ ርዕሶች የሚገልጹ መረጃዎችን፣ አኃዞችንና ሐሳቦችን ማግኘት ይቻላል።

ሐሳብ የመለዋወጥ ችሎታ ከፈጣሪያችን ያገኘነው ግሩም ስጦታ ነው። ይህ ስጦታ ለሌሎች አመለካከታችንን ለመግለጽና መረጃዎችን ለማካፈል ያስችለናል። ከሰው ልጆች ጋር የሐሳብ ልውውጥ በማድረግ ረገድ ቅድሚያውን የወሰደው ይሖዋ ሲሆን ትርጉም ያለው ሕይወት ለመምራት የሚያስችል ግልጽና የማያሻማ መረጃም ሰጥቷቸዋል። (ዘፍ. 1:28-30) ይሁንና በሰው ልጆች ታሪክ መጀመሪያ ላይ እንደታየው ሐሳብ የመለዋወጥ ስጦታ ተገቢ ባልሆነ መንገድ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል። ሰይጣን ለሔዋን ፈጽሞ ከእውነት የራቀ መረጃ ሰጥቷት ነበር። እሷም ሰይጣን ያላትን ተቀብላ ለአዳም አስተላለፈች፤ አዳም በዚህ ላይ ተመሥርቶ የወሰደው እርምጃ የሰው ልጆችን በመከራ አዘቅት ውስጥ ዘፍቋቸዋል።​—ዘፍ. 3:1-6፤ ሮም 5:12

ኢንተርኔትን ስለ መጠቀምስ ምን ማለት ይቻላል? ኢንተርኔት አስፈላጊ መረጃዎችን ሊያቀርብልን፣ ጊዜያችንን ሊቆጥብልንና ሌሎች ጠቃሚ የሆኑ አገልግሎቶችን ሊሰጠን ቢችልም በሌላ በኩል ደግሞ የተሳሳተ መረጃ ሊሰጠን፣ ጊዜያችንን ሊያባክንብንና ሥነ ምግባራዊ አቋማችንን ሊያበላሽብን ይችላል። እንግዲያው ይህን ዓለም አቀፍ የመረጃ መረብ በጥበብ ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

መረጃ​—አስተማማኝ ወይስ የተዛባ?

በኢንተርኔት ላይ የሚገኘው መረጃ ሁሉ ትክክለኛና ጠቃሚ ነው ብለህ ፈጽሞ ማሰብ የለብህም። መረጃ ለማግኘት የሚረዱን ድረ ገጾች፣ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ማንኛውንም ዓይነት እንጉዳይ ከሚለቅሙ ሠራተኞች ጋር ሊመሳሰሉ ይችላሉ፤ እነዚህ ሰዎች የሚበላውን እንጉዳይ መርዛማ ከሆነው ሳይለዩ ያገኙትን ሁሉ በመልቀም በአንድ ቅርጫት ውስጥ ከከተቱ በኋላ እንድትበላ ቢያቀርቡልህ እንጉዳዮቹን በጥንቃቄ ሳትለይ ሁሉንም ዝም ብለህ ትመገባለህ? እንዲህ እንደማታደርግ የታወቀ ነው! መረጃ ለመፈለግ የሚያገለግሉ የኢንተርኔት ድረ ገጾች በርካታ ኮምፒውተሮችን በመጠቀም ጠቃሚ ከሆነው አንስቶ እጅግ መጥፎ እስከሚባለው ድረስ ሁሉንም መረጃዎች ሰብስበው ከያዙ በቢሊዮን ከሚቆጠሩ ድረ ገጾች ላይ የተወሰዱ መረጃዎችን ያቀርባሉ። አእምሯችን በተሳሳተ መረጃ እንዳይበከል አስተዋዮች በመሆን ስንዴውን ከእንክርዳዱ መለየት ያስፈልገናል።

በ1993 አንድ የታወቀ መጽሔት ኮምፒውተር ላይ የሚሠሩ ሁለት ውሾችን የሚያሳይ የካርቱን ሥዕል ይዞ ወጥቶ ነበር። በሥዕሉ ላይ አንዱ ውሻ ለሌላኛው “ኢንተርኔት ላይ እኮ ውሻ መሆንህን ማንም አያውቅም” እንዳለው የሚገልጽ ሐሳብ ሰፍሯል። በኢንተርኔት ላይ እውነተኛ ማንነታቸውን ደብቀው እንደሚቀርቡ ግለሰቦች ሁሉ ሰይጣንም ከረጅም ዘመን በፊት በእባብ ተመስሎ ወደ ሔዋን በመቅረብ እንደ አምላክ መሆን እንደምትችል ነግሯት ነበር። በዛሬው ጊዜ ኢንተርኔት መጠቀም የሚችል ማንኛውም ሰው ማንነቱን እንኳ ሳያሳውቅ ራሱን ሊቅ አድርጎ ሊያቀርብ ይችላል። ማንም ሰው የፈለገውን ሐሳብ፣ መረጃና አስተያየት ከመስጠት እንዲሁም ምስሎችን ከማውጣት የሚያግደው ነገር የለም።

ኢንተርኔት በምትጠቀምበት ጊዜ እንደ ሔዋን እንዳትታለል ተጠንቀቅ። ያገኘኸውን መረጃ በጥንቃቄ መመርመርና መገምገም ይኖርብሃል። መረጃውን ትክክለኛ እንደሆነ አድርገህ ከመቀበልህ በፊት ራስህን እንደሚከተለው እያልክ ጠይቅ፦ (1) ይህን ርዕስ የጻፈው ማን ነው? ግለሰቡ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን የሙያ ማረጋገጫ አለው? (2) ይህ ርዕስ የተጻፈው ለምንድን ነው? የጸሐፊው ዓላማ ምንድን ነው? ያቀረበው ሐሳብ ወደ አንድ ወገን ያደላ ነው? (3) መረጃውን ያገኘው ከየት ነው? ያቀረበውን መረጃ ትክክለኛነት ማረጋገጥ እንዲቻል ምንጮቹን ጠቅሷል? (4) መረጃው ጊዜ ያለፈበት ይሆን? በመጀመሪያው መቶ ዘመን ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የሰጠው ምክር በዛሬውም ጊዜ ተግባራዊ ሊሆን ይችላል። ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ቅዱስ የሆነውን ነገር ከሚጻረሩ ከንቱ ንግግሮችና በውሸት ‘እውቀት’ ተብለው ከሚጠሩ እርስ በርሳቸው ከሚቃረኑ ሐሳቦች በመራቅ በአደራ የተሰጠህን ነገር ጠብቅ።”​—1 ጢሞ. 6:20

ጊዜ ይቆጥባል ወይስ ያባክናል?

ኢንተርኔትን በጥበብ የምንጠቀምበት ከሆነ ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንንና ገንዘባችንን እንደሚቆጥብልን ጥርጥር የለውም። የምንፈልጋቸውን ነገሮች ቤታችን ሆነን በቀላሉ መግዛት እንችላለን። እንዲሁም ዋጋ ለማወዳደር ስለሚያስችለን ገንዘብ ይቆጥብልናል። በኢንተርኔት አማካኝነት የሚሰጠው የባንክ አገልግሎት የብዙዎችን ሕይወት ቀላል አድርጎላቸዋል፤ ከገንዘብ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ከቤታችን ሳንወጣ በፈለግነው ጊዜ ማከናወን እንችላለን። ጉዞ ለማድረግ ስናቅድ፣ የጉዞ ቲኬት ማግኘትንና የምናርፍበትን ቦታ አስቀድመን ማመቻቸትን ጨምሮ ተስማሚና ወጪ የሚቀንስ ፕሮግራም ማውጣት ቀላል እንዲሆንልን ያደርጋል። ስልክ ቁጥሮችንና አድራሻዎችን እንዲሁም የምንፈልግበት ቦታ ለመድረስ ስለሚያስችሉን የተለያዩ መንገዶች የሚገልጹ መረጃዎችን ሳንቸገር ማግኘት እንችላለን። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮዎች ጊዜ፣ የሰው ኃይልና ገንዘብ ለመቆጠብ ሲሉ ኢንተርኔት በሚሰጣቸው በእነዚህ አገልግሎቶች ይጠቀማሉ።

ያም ሆኖ ኢንተርኔት ጎጂ ጎኖችም አሉት። ከእነዚህም መካከል አንዱ ጊዜ የሚያባክን መሆኑ ነው። ኢንተርኔት ለአንዳንዶች ጠቃሚ መሣሪያ ከመሆን ይልቅ ቀልብ የሚስብ መጫወቻ ሆኗል። እነዚህ ሰዎች ጌም በመጫወት፣ ዕቃ በመሸመት፣ ከሌሎች ጋር በማውራት፣ መልእክቶችን በመላላክ እንዲሁም መረጃዎችን በመፈለግና የተለያዩ ድረ ገጾችን በመቃኘት ይህ ነው የማይባል ጊዜ ያጠፋሉ። ውሎ አድሮም ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ይኸውም ከቤተሰባቸው፣ ከጓደኞቻቸውና ከጉባኤ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ችላ ማለት ይጀምራሉ። እንዲያውም በኢንተርኔት መጠቀም ሱስ ሊሆንባቸው ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ በ2010 በወጣ ጥናት መሠረት በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ከሚገኙ ኮሪያውያን መካከል 18.4 በመቶ የሚያህሉት የኢንተርኔት ሱሰኞች እንደሆኑ ይገመታል። ጀርመናውያን ተመራማሪዎች እንደገለጹት “የትዳር አጋሮቻቸው [በኢንተርኔት] ሱስ መጠመዳቸውን አስመልክተው ቅሬታ የሚያሰሙ ሴቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ” መጥቷል። አንዲት ሴት፣ ባለቤቷ ከኢንተርኔት መላቀቅ ስላቃተው ባሕርይው ተቀይሮ ፈጽሞ ሌላ ሰው እንደሆነባትና በዚህም ሳቢያ ትዳራቸው እንደፈረሰ በምሬት ተናግራለች።

አንድ የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ፣ የኢንተርኔት ሱሰኛ እንደሆነ ከገለጸ ግለሰብ ደብዳቤ ደርሶት ነበር። ይህ ሰው አንዳንድ ጊዜ በቀን ውስጥ ኢንተርኔት በመጠቀም አሥር ሰዓት ያህል ያሳልፍ ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “መጀመሪያ ላይ ምንም ችግር ያለው አይመስልም ነበር። . . . እያደር ግን ከስብሰባ መቅረት የጀመርኩ ሲሆን መጸለይም አቆምኩ።” ግለሰቡ ስብሰባዎች ላይ የሚገኘው ሳይዘጋጅ ከመሆኑም ሌላ እዚያም እያለ የሚያስበው ቤት ሄዶ ኢንተርኔት ስለመጠቀሙ ነበር። ደስ የሚለው ግን የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ ሁኔታውን ለማስተካከል እርምጃ ወስዷል። እኛም በኢንተርኔት መጠቀም ሱስ እንዳይሆንብን እንጠንቀቅ።

መረጃ​—ጠቃሚ ወይስ ጎጂ?

አንደኛ ተሰሎንቄ 5:21, 22 እንዲህ ይላል፦ “ሁሉንም ነገር መርምሩ፤ መልካም የሆነውን አጥብቃችሁ ያዙ። ከማንኛውም ዓይነት ክፋት ራቁ።” ኢንተርኔት ላይ የምናገኘው መረጃ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለውና ከላቁ የሥነ ምግባር መሥፈርቶቹ ጋር የሚስማማ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልገናል። እንዲሁም ከሥነ ምግባር አንጻር አጠያያቂና ለክርስቲያኖች የማይገባ አለመሆኑን መገምገም ይኖርብናል። በተለይ በኢንተርኔት የሚታዩ የብልግና ምስሎች በጣም ተስፋፍተዋል፤ በመሆኑም ካልተጠነቀቅን በቀላሉ በዚህ ወጥመድ ልንወድቅ እንችላለን።

‘በኢንተርኔት ላይ የምመለከተውን ነገር የትዳር ጓደኛዬ፣ ወላጆቼ ወይም ክርስቲያን ወንድሞቼ ቢመጡ እንዳያዩብኝ ለመደበቅ እሞክራለሁ?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን ጥሩ ነው። መልሳችን አዎ ከሆነ ሌሎች አብረውን በሚሆኑበት ጊዜ ብቻ ኢንተርኔት ለመጠቀም መወሰናችን ተገቢ ይሆናል። እርግጥ ነው፣ ኢንተርኔት ከሰዎች ጋር ሐሳብ በምንለዋወጥበትና ዕቃዎችን በምንገበይበት መንገድ ላይ ለውጥ አምጥቷል። በሌላ በኩል ደግሞ ‘በልባችን እንድናመነዝር’ የሚያደርግ አዲስ መንገድ ከፍቷል።​—ማቴ. 5:27, 28

ያገኘሁትን መረጃ ለሌሎች ላስተላልፈው?

ኢንተርኔት መጠቀም መረጃዎችን ማግኘትን ብቻ ሳይሆን ይህን መረጃ ለሌሎች ማሰራጨትንም ይጨምራል። መረጃ የመቀበልና ለሌሎች የማስተላለፍ ነፃነት ያለን ቢሆንም መረጃው ትክክለኛና ከሥነ ምግባር አንጻር ንጹሕ መሆኑን የማረጋገጥ ኃላፊነት አለብን። የምንጽፈው አሊያም ከሌሎች ተቀብለን የምናስተላልፈው መረጃ ትክክል ስለመሆኑ አፋችንን ሞልተን መናገር እንችላለን? መረጃውን ለሌሎች አሳልፈን ለመስጠት ተፈቅዶልናል? * መረጃው ጠቃሚና የሚያንጽ ነው? ይህን መረጃ የምናስተላልፍበት ዓላማ ምንድን ነው? እንዲህ የምናደርገው ሌሎችን ለማስደመም ብለን ነው?

በአግባቡ ከተጠቀምንበት ኢሜይል እጅግ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ በመረጃዎች ብዛት እንድንጨናነቅ ሊያደርገን ይችላል። የሰማነውን አዲስ ወሬ ወይም ፍሬ ቢስ የሆነ ነገር ሁሉ ለምናውቃቸው ሰዎች በሙሉ በመላክ ጊዜያቸውን የሚሻማ ድርጊት እንፈጽማለን? አንድን መልእክት ከመላካችን በፊት ይህን ለማድረግ የተነሳሳንበትን ምክንያት ቆም ብለን ማሰብ አይኖርብንም? መልእክቱን የምንልክበት ዓላማ ምንድን ነው? ቀደም ባሉት ጊዜያት ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ ያጋጠሟቸውን አዳዲስ ነገሮች ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጆቻቸው ለማካፈል ደብዳቤ ይጽፉ ነበር። ኢሜይል ስንልክስ ዓላማችን ይህ ሊሆን አይገባውም? ትክክለኛነቱን ማረጋገጥ የማንችለውን መረጃ ለሌሎች ለምን እናስተላልፋለን?

እንግዲያው ከኢንተርኔት ጋር በተያያዘ ውሳኔያችን ምን ሊሆን ይገባል? በኢንተርኔት ፈጽሞ መጠቀም የለብንም ማለት ነው? አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ማድረጉ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። ቀደም ብሎ የተጠቀሰው የኢንተርኔት ሱስ የተጠናወተው ግለሰብ ለዓመታት ሲታገለው ከቆየው ከዚህ ሱስ ለመላቀቅ ሲል እንዲህ ማድረግ አስፈልጎት ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ ‘የመለየት ችሎታ እንዲጋርደንና ማስተዋል እንዲጠብቀን’ እስከፈቀድን ድረስ ኢንተርኔት ጠቃሚ ሊሆንልን ይችላል።​—ምሳሌ 2:10, 11

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.17 ይህ ከፎቶግራፍም ጋር በተያያዘ ይሠራል። ባነሳናቸው ፎቶግራፎች ላይ ያሉትን ሰዎች ስምና አድራሻ መግለጽ ይቅርና ፎቶግራፎቹን ለብዙ ሰዎች ማሰራጨት በራሱ ተገቢ አይደለም።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በተዛባ መረጃ ምክንያት ሊደርስብህ ከሚችለው ጉዳት ራስህን መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው?

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድን መልእክት ከመላካችን በፊት ልናስብበት የሚገባው ነገር ምንድን ነው?