በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሩጫውን በጽናት ሩጡ

ሩጫውን በጽናት ሩጡ

ሩጫውን በጽናት ሩጡ

“ከፊታችን የሚጠብቀንን ሩጫ በጽናት እንሩጥ።”​—ዕብ. 12:1

1, 2. ሐዋርያው ጳውሎስ የክርስትናን ሕይወት ከምን ጋር አመሳስሎታል?

በየዓመቱ በብዙ ቦታዎች የማራቶን ውድድር ይካሄዳል። ታዋቂ የሆኑት ሯጮች ወደ ውድድሩ የሚገቡት አንድ ዓላማ ይዘው ሲሆን ይህም ማሸነፍ ነው። በውድድሩ የሚካፈሉት አብዛኞቹ ሯጮች ግን ማሸነፍ እንደማይችሉ ያውቃሉ። ለእነሱ ሩጫውን ማጠናቀቃቸው በራሱ ትልቅ ነገር ነው።

2 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የክርስትና ሕይወት ከሩጫ ውድድር ጋር ተመሳስሏል። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ በጥንቷ ቆሮንቶስ ይኖሩ ለነበሩት የእምነት ባልንጀሮቹ በጻፈው የመጀመሪያ ደብዳቤ ላይ ይህን ሐሳብ አንስቶ ነበር። እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “በሩጫ ውድድር ሁሉም እንደሚሮጡ፣ ሽልማቱን ግን የሚያገኘው አንዱ ብቻ እንደሆነ አታውቁም? እናንተም ሽልማቱን እንድታገኙ በዚሁ ሁኔታ ሩጡ።”​—1 ቆሮ. 9:24

3. ጳውሎስ በውድድሩ የሚያሸንፈው አንዱ ሯጭ ብቻ እንደሆነ የተናገረው ለምንድን ነው?

3 ጳውሎስ፣ ከእነዚህ ክርስቲያኖች መካከል የሕይወትን ሽልማት የሚያገኘው አንዱ ብቻ እንደሆነና ሌሎቹ የሚሮጡት በከንቱ መሆኑን መግለጹ ነበር? በፍጹም! በውድድር ላይ የሚካፈሉ ሯጮች የማሸነፍ ግብ ይዘው በደንብ የሚለማመዱ ከመሆኑም በላይ በውድድሩ ላይ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። ጳውሎስ የእምነት ባልንጀሮቹም የዘላለም ሕይወት ለማግኘት በሚያደርጉት ሩጫ ላይ ብርቱ ጥረት እንዲያደርጉ ፈልጎ ነበር። እንዲህ ከሆነ የሕይወትን ሽልማት የማግኘት ተስፋ ይኖራቸዋል። አዎ፣ ክርስቲያኖች በሚካፈሉበት የሩጫ ውድድር ላይ ውድድሩን ያጠናቀቁ ሁሉ ሽልማቱን ያገኛሉ።

4. ከፊታችን የሚጠብቀንን ሩጫ በተመለከተ የትኞቹን ነገሮች መመርመር ያስፈልገናል?

4 ይህ የሚያበረታታ ሐሳብ ቢሆንም በዛሬው ጊዜ ለሕይወት በሚደረገው ሩጫ የሚካፈሉ ሁሉ በቁም ነገር ሊያስቡበት የሚገባ ነጥብም ይዟል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም የምናገኘው ሽልማት ወደ ሰማይ መሄድም ሆነ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ መኖር ከምንም ነገር ጋር ሊወዳደር አይችልም። እውነት ነው፣ ውድድሩ ረጅም ከመሆኑም በላይ አድካሚ ነው፤ ደግሞም በመንገዱ ላይ በርካታ እንቅፋቶች፣ ትኩረት የሚከፋፍሉ ነገሮች እንዲሁም አደገኛ ሁኔታዎች አሉ። (ማቴ. 7:13, 14) የሚያሳዝነው አንዳንዶች በውድድሩ ላይ ፍጥነታቸውን ቀንሰዋል፣ ዝለዋል ወይም ከነጭራሹ ውድድሩን አቋርጠው ወጥተዋል። ለሕይወት በሚደረገው ሩጫ ላይ የሚያጋጥሙት ወጥመዶችና አደጋዎች ምንድን ናቸው? ከእነዚህ ነገሮች ራስህን መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው? ውድድሩን በማጠናቀቅ አሸናፊ ለመሆን ምን ማድረግ ትችላለህ?

ለማሸነፍ ጽናት ያስፈልጋል

5. ጳውሎስ በ⁠ዕብራውያን 12:1 ላይ ስለ ውድድር ምን ብሏል?

5 ጳውሎስ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ለሚገኙት ዕብራውያን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ስለ አትሌቲክስ ጨዋታዎች ወይም ውድድሮች በድጋሚ ጠቅሷል። (ዕብራውያን 12:1ን አንብብ።) ሐዋርያው፣ ሰዎች በዚህ ውድድር የሚካፈሉበትን ምክንያት ብቻ ሳይሆን በውድድሩ አሸናፊ ለመሆን ምን ማድረግ እንደሚያስፈልግም ተናግሯል። ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ከጻፈው ምክር ምን ትምህርት ማግኘት እንደምንችል ከመመርመራችን በፊት ይህን ደብዳቤ ለመጻፍ የተነሳሳበትን ምክንያትና አንባቢዎቹን ምን እንዲያደርጉ እንዳበረታታቸው እንመልከት።

6. ክርስቲያኖች ከሃይማኖት መሪዎች ምን ዓይነት ጫና ይደርስባቸው ነበር?

6 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች በተለይም በኢየሩሳሌምና በይሁዳ የሚኖሩት ብዙ መከራና ችግር ያጋጥማቸው ነበር። በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ተደማጭነት የነበራቸው የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች በክርስቲያኖች ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳድሩ ነበር። ከዚህ ቀደም እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች፣ ኢየሱስ ክርስቶስን በመንግሥት ላይ ዓመፅ ይቀሰቅሳል ብለው በመክሰስ እንደ ወንጀለኛ ተቆጥሮ እንዲገደል አድርገዋል። በዚህ ጊዜም ቢሆን በተቃውሟቸው ገፍተውበት ነበር። በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት ከተከናወነው ተአምር ብዙም ሳይቆይ የሃይማኖት መሪዎቹ በክርስቲያኖች ላይ በተደጋጋሚ ጊዜያት ዛቻዎችና ጥቃቶች እንደሰነዘሩ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ እናነባለን። ይህ ሁኔታ ታማኝ የሆኑትን ክርስቲያኖች ሕይወት አስቸጋሪ አድርጎባቸው መሆን አለበት።​—ሥራ 4:1-3፤ 5:17, 18፤ 6:8-12፤ 7:59፤ 8:1, 3

7. ጳውሎስ የጻፈላቸው ክርስቲያኖች የሚኖሩበት ዘመን አስቸጋሪ እንዲሆን ያደረገው ምን ነበር?

7 በተጨማሪም እነዚህ ክርስቲያኖች የሚኖሩት የአይሁድ ሥርዓት ሊጠፋ በተቃረበበት ጊዜ ነበር። ኢየሱስ ታማኝ ባልሆነው የአይሁድ ብሔር ላይ ጥፋት እንደሚመጣ ነግሯቸው ነበር። በተጨማሪም ጥፋቱ ከመምጣቱ በፊት ስለሚከናወኑት ሁኔታዎችና ከጥፋቱ ለመትረፍ ሊወስዷቸው ስለሚገቡ እርምጃዎች ለተከታዮቹ በዝርዝር ነግሯቸዋል። (ሉቃስ 21:20-22ን አንብብ።) ታዲያ ተከታዮቹ ምን ማድረግ ነበረባቸው? ኢየሱስ እንዲህ የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፦ “ከልክ በላይ በመብላትና በመጠጣት፣ እንዲሁም ስለ ኑሮ በመጨነቅ ልባችሁ ሸክም እንዳይበዛበት ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ አለዚያ ያ ቀን ድንገት ሳታስቡት . . . ይመጣባችኋል።”​—ሉቃስ 21:34, 35

8. አንዳንድ ክርስቲያኖች ፍጥነታቸውን እንዲቀንሱ ወይም ዝለው ሩጫውን እንዲያቆሙ ያደረጋቸው ምን ሊሆን ይችላል?

8 ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ደብዳቤ በጻፈበት ወቅት ኢየሱስ ከላይ ያለውን ማስጠንቀቂያ ከሰጠ ወደ 30 የሚጠጉ ዓመታት አልፈው ነበር። ይህ ማስጠንቀቂያ ከተሰጠ በርካታ ዓመታት ማለፋቸው በእነዚህ ክርስቲያኖች ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድሮ ይሆን? አንዳንዶች በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው በሚያጋጥሟቸው ጫናዎችና ትኩረታቸውን በሚከፋፍሉ ነገሮች በመሸነፋቸው መንፈሳዊ እድገት ማድረግ ስላልቻሉ ጠንካሮች አልነበሩም። (ዕብ. 5:11-14) ሌሎች ክርስቲያኖች በዙሪያቸው እንደነበሩት እንደ አብዛኞቹ አይሁዳውያን ዓይነት አካሄድ ቢከተሉ ሕይወት ቀላል እንደሚሆንላቸው ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል። ምናልባትም እነዚህ ክርስቲያኖች፣ ‘አይሁዳውያኑ አምላክን ሙሉ በሙሉ አልተዉትም፤ በተወሰነ መጠንም ቢሆን ሕግጋቱን እየጠበቁ ነው’ ብለው ሳያስቡ አልቀሩም። አንዳንዶቹ ደግሞ የሙሴን ሕግና የአይሁዳውያንን ልማድ መጠበቅን የሚያበረታቱ የጉባኤው አባላት በሚያሳድሩት ተጽዕኖ አሊያም በፍርሃት ተሸንፈው ሊሆን ይችላል። ታዲያ ጳውሎስ ክርስቲያን ወንድሞቹን በመንፈሳዊ ንቁ ሆነው እንዲቀጥሉና በሩጫው እንዲጸኑ ማበረታታት የሚችለው እንዴት ነው?

9, 10. (ሀ) በ⁠ዕብራውያን ምዕራፍ 10 መደምደሚያ አካባቢ ጳውሎስ ምን ማበረታቻ ሰጥቷል? (ለ) ጳውሎስ የጥንቶቹ ምሥክሮች በእምነት ስላከናወኗቸው ተግባሮች የጻፈው ለምንድን ነው?

9 ጳውሎስ የዕብራውያንን ክርስቲያኖች በአምላክ መንፈስ መሪነት ያበረታታበት መንገድ ትኩረት የሚስብ ነው። በ⁠ዕብራውያን ምዕራፍ 10 ላይ “ሕጉ ወደፊት ለሚመጡት መልካም ነገሮች ጥላ” እንደሆነ የገለጸ ሲሆን የክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ያለውን ጥቅም በግልጽ አብራርቷል። በምዕራፉ መደምደሚያ አካባቢ ጳውሎስ አንባቢዎቹን እንደሚከተለው በማለት አሳስቧቸዋል፦ “የአምላክን ፈቃድ ከፈጸማችሁ በኋላ የተስፋውን ቃል ፍጻሜ ማግኘት እንድትችሉ መጽናት ያስፈልጋችኋል። ምክንያቱም ‘ለጥቂት ጊዜ ነው’ እንጂ ‘የሚመጣው እሱ ይመጣል፤ ደግሞም አይዘገይም።’”​—ዕብ. 10:1, 36, 37

10 ጳውሎስ በ⁠ዕብራውያን ምዕራፍ 11 ላይ በአምላክ ላይ እውነተኛ እምነት ማሳደር ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ጥሩ አድርጎ አብራርቷል። ይህንንም በምሳሌ ለማስረዳት በጥንት ዘመን የኖሩ የእምነት ሰዎችን ጠቅሷል። ጳውሎስ ስለ እምነት መናገር ያስፈለገው ለምን ነበር? ሐዋርያው፣ ክርስቲያን ባልንጀሮቹ በእምነታቸው ምክንያት ድፍረት የተሞላበት እርምጃ መውሰድና መጽናት እንደሚያስፈልጋቸው ሊገነዘቡ እንደሚገባ ያውቅ ነበር። በጥንት ዘመን የኖሩት እነዚያ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች የተዉት ግሩም ምሳሌ፣ የዕብራውያን ክርስቲያኖች ያለባቸውን መከራና ችግር ለመቋቋም እንዲችሉ ብርታት ይሰጣቸዋል። በመሆኑም ጳውሎስ እነዚያ የጥንት ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች በእምነት ያከናወኗቸውን ተግባራት ከዘረዘረ በኋላ እንዲህ ብሏል፦ “እጅግ ታላቅ የምሥክሮች ደመና በዙሪያችን ስላለልን እኛም ማንኛውንም ሸክምና በቀላሉ ተብትቦ የሚይዘንን ኃጢአት ከላያችን ጥለን ከፊታችን የሚጠብቀንን ሩጫ በጽናት እንሩጥ።”​—ዕብ. 12:1

“የምሥክሮች ደመና”

11. “ታላቅ የምሥክሮች ደመና” ስለተባሉት የአምላክ አገልጋዮች ማሰባችን እንዴት ሊጠቅመን ይችላል?

11 “ታላቅ የምሥክሮች ደመና” የተባሉት ውድድሩን ለማየት አሊያም የሚወዱት ሯጭ ወይም ቡድን ሲያሸንፍ ለመመልከት ብቻ የተሰበሰቡ ተመልካቾች ወይም ደጋፊዎች አይደሉም። ከዚህ ይልቅ እነሱ ራሳቸው በውድድሩ የሚሳተፉ ሯጮች ናቸው። እነዚህ የአምላክ አገልጋዮች ሩጫውን በተሳካ ሁኔታ አጠናቅቀዋል። አሁን በሕይወት ባይኖሩም አዲስ ተወዳዳሪዎችን ሊያበረታቱ እንደሚችሉ ልምድ ያላቸው ሯጮች ተደርገው ሊቆጠሩ ይችላሉ። አንድ አዲስ ሯጭ ታዋቂ የሆኑ ሯጮች በዙሪያው እንዳሉ ወይም እየተመለከቱት እንደሆነ ቢያውቅ ምን ሊሰማው እንደሚችል ገምት። አቅሙ የሚፈቅደውን ሁሉ ለማድረግ እንዲያውም ከሌላው ጊዜ የተሻለ ውጤት ለማምጣት አይነሳሳም? እነዚህ የጥንት ምሥክሮች እንዲህ ያለው ምሳሌያዊ ውድድር ምንም ያህል አድካሚ ቢሆን ማሸነፍ እንደሚቻል ማስረጃ ናቸው። በመሆኑም በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት የዕብራውያን ክርስቲያኖች፣ “የምሥክሮች ደመና” የተባሉት የጥንት የአምላክ አገልጋዮች የተዉትን ምሳሌ በአእምሯቸው መያዛቸው ደፋሮች እንዲሆኑና ‘ሩጫውን በጽናት እንዲሮጡ’ ይረዳቸዋል፤ እኛም እንዲህ ማድረግ እንችላለን።

12. ጳውሎስ የጠቀሳቸው ምሳሌዎች የሚጠቅሙን እንዴት ነው?

12 ጳውሎስ የጠቀሳቸው በርካታ የአምላክ አገልጋዮች ሁኔታ ከእኛ ጋር ተመሳሳይ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ኖኅ ይኖር የነበረው ከጥፋት ውኃ በፊት የነበረው ዓለም ሊጠፋ በተቃረበበት ዘመን ነበር። እኛም የምንኖረው በዚህ ሥርዓት መደምደሚያ ላይ ነው። አብርሃምና ሣራ እውነተኛውን አምላክ ለማምለክ የትውልድ አገራቸውን ትተው እንዲወጡ የተነገራቸው ሲሆን ይሖዋ የሰጣቸውን ተስፋ ፍጻሜ ይጠባበቁ ነበር። እኛም የይሖዋን ሞገስና እሱ ያዘጋጀልንን በረከቶች ማግኘት እንድንችል ራሳችንን እንድንክድ ማበረታቻ ተሰጥቶናል። ሙሴ ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት አስፈሪ የሆነውን ምድረ በዳ ማቋረጥ ነበረበት። እኛም ሊጠፋ የተቃረበውን ይህን ሥርዓት አቋርጠን ቃል ወደተገባልን አዲስ ዓለም ለመግባት እየተጓዝን ነው። በእርግጥም እነዚህ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ያሳለፉትን ሕይወት፣ ያጋጠሟቸውን አስደሳችና አሳዛኝ ሁኔታዎች እንዲሁም ጠንካራና ደካማ ጎናቸውን መመርመራችን የተገባ ነው።​—ሮም 15:4፤ 1 ቆሮ. 10:11

ሩጫውን ለማጠናቀቅ የረዳቸው ምንድን ነው?

13. ኖኅ ምን አስቸጋሪ ሁኔታዎች አጋጥመውት ነበር? ለመቋቋም የረዳውስ ምንድን ነው?

13 እነዚህ የይሖዋ አገልጋዮች ጸንተው ውድድሩን ለማጠናቀቅ እንዲችሉ የረዳቸው ምንድን ነው? ጳውሎስ ስለ ኖኅ የጻፈውን ሐሳብ ልብ በል። (ዕብራውያን 11:7ን አንብብ።) ‘ሕያዋን ፍጡራንን ሁሉ የሚያጠፋው የጥፋት ውሃ’ ኖኅ ከዚያ ቀድሞ ‘ያላየው’ ነገር ነበር። (ዘፍ. 6:17) የጥፋት ውሃው ከዚያ በፊት ፈጽሞ ታይቶ የማያውቅ እንግዳ ነገር ነበር። ያም ሆኖ ኖኅ እንዲህ ያለው ነገር የማይመስል እንዲያውም ጨርሶ ሊሆን የማይችል እንደሆነ አድርጎ አላሰበም። ለምን? ምክንያቱም ይሖዋ የተናገረውን ሁሉ እንደሚፈጽም እምነት ነበረው። ኖኅ እንዲሠራ የተጠየቀው ነገር በጣም አስቸጋሪ እንደሆነ አልተሰማውም። ከዚህ ይልቅ ልክ አምላክ ‘እንዳዘዘው አድርጓል።’ (ዘፍ. 6:22) ኖኅ መርከብ መሥራት፣ እንስሳቱን መሰብሰብ፣ ለሰዎችና ለእንስሳት የሚሆን ምግብ በመርከቡ ውስጥ ማከማቸት፣ የማስጠንቀቂያ መልእክት መስበክ እንዲሁም የቤተሰቡን መንፈሳዊነት መጠበቅ እንደነበረበት ስናስብ ሁሉን ነገር ልክ አምላክ ‘እንዳዘዘው ማድረግ’ ቀላል እንዳልነበረ መረዳት አያዳግትም። ያም ሆኖ ኖኅ እምነትና ጽናት ማሳየቱ የራሱንም ሆነ የቤተሰቡን ሕይወት ለማትረፍና በረከት ለማግኘት አስችሎታል።

14. አብርሃምና ሣራ ምን ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በጽናት መወጣት አስፈልጓቸዋል? እኛስ ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን?

14 ጳውሎስ በዙሪያችን እንዳሉ ከገለጻቸው “የምሥክሮች ደመና” መካከል ቀጥሎ የጠቀሰው አብርሃምንና ሣራን ነው። እነዚህ ሰዎች የተመቻቸ ሕይወት ይመሩ ከነበሩበት ከዑር የተፈናቀሉ ሲሆን ምን ዓይነት ሕይወት እንደሚጠብቃቸው እርግጠኞች አልነበሩም። በአስቸጋሪ ጊዜያት የማይናወጥ እምነት በማሳየትና በመታዘዝ ረገድ ግሩም ምሳሌ ይሆኑናል። አብርሃም ከእውነተኛው አምልኮ ጋር በተያያዘ በፈቃደኝነት ከከፈላቸው መሥዋዕቶች አንጻር “በእምነታቸው የተነሳ እንደ ጻድቃን ለተቆጠሩት ሁሉ አባት” ተብሎ መጠራቱ የተገባ ነው። (ሮም 4:11) ጳውሎስ ደብዳቤውን የጻፈላቸው ሰዎች ስለ አብርሃም ሕይወት በደንብ ያውቁ ስለነበር እዚህ ላይ የጠቀሰው ጎላ ብለው የሚታዩትን ነጥቦች ብቻ ነው። ይሁንና ጳውሎስ በእነዚህ ነጥቦች ላይ ተመሥርቶ የሚከተለውን ትልቅ ቁም ነገር ያዘለ ትምህርት ሰጥቷል፦ “እነዚህ ሁሉ [አብርሃምና ቤተሰቡን ጨምሮ] የተስፋውን ቃል ፍጻሜ ባያገኙም እምነታቸውን እንደጠበቁ ሞቱ፤ ሆኖም ከሩቅ አይተው በደስታ ተቀበሉት፤ በምድሩም ላይ እንግዶችና ጊዜያዊ ነዋሪዎች መሆናቸውን በይፋ ተናገሩ።” (ዕብ. 11:13) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው እነዚህ የአምላክ አገልጋዮች በይሖዋ ላይ ያላቸው እምነትና በግለሰብ ደረጃ ከእሱ ጋር የመሠረቱት ዝምድና ሩጫውን በጽናት እንዲሮጡ ረድቷቸዋል።

15. ሙሴ በሕይወቱ ውስጥ ለውጥ እንዲያደርግ ያነሳሳው ምንድን ነው?

15 “የምሥክሮች ደመና” ከተባሉት መካከል የተጠቀሰው ሌላው ምሳሌ የሚሆን የአምላክ አገልጋይ ደግሞ ሙሴ ነው። ሙሴ የተንደላቀቀና በሰዎች ዘንድ ክብር ሊያስገኝለት የሚችለውን ሕይወት ትቶ “ከአምላክ ሕዝብ ጋር መንገላታትን [መርጧል]።” እንዲህ እንዲያደርግ ያነሳሳው ምንድን ነው? ጳውሎስ “የሚከፈለውን ወሮታ በትኩረት በመመልከቱ . . . የማይታየውን እንደሚያየው አድርጎ በጽናት ቀጥሏል” በማለት መልሱን ሰጥቶናል። (ዕብራውያን 11:24-27ን አንብብ።) ሙሴ “በኃጢአት [የሚገኝ] ጊዜያዊ ደስታ” ትኩረቱን እንዲሰርቅበት አልፈቀደም። አምላክና እሱ የሰጣቸው ተስፋዎች እውን ሆነውለት ስለነበር አስገራሚ ድፍረትና ጽናት ማሳየት ችሏል። እንዲሁም ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል እስራኤላውያንን ከግብፅ አውጥቶ ወደ ተስፋይቱ ምድር መርቷቸዋል።

16. ሙሴ ወደ ተስፋይቱ ምድር እንደማይገባ ሲነገረው በሐዘን ያልተዋጠው ለምንድን ነው?

16 ልክ እንደ አብርሃም ሙሴም አምላክ የሰጠው ተስፋ በሕይወት ዘመኑ ሲፈጸም አልተመለከተም። እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ሊገቡ በተቃረቡበት ወቅት ይሖዋ ለሙሴ “ምድሪቱን ከሩቅ ሆነህ ታያታለህ እንጂ፣ ለእስራኤል ሕዝብ ወደምሰጣት ምድር አትገባም” ብሎት ነበር። ይህ የሆነው ሙሴና አሮን ዓመፀኛ በሆነው ሕዝብ ተበሳጭተው ‘በመሪባ ውሃ አጠገብ በአምላክ ላይ መታመናቸውን በእስራኤላውያን ፊት ስላጐደሉ’ ነበር። (ዘዳ. 32:51, 52) ታዲያ ሙሴ በሐዘን ተውጦ ወይም ተማርሮ ነበር? በፍጹም። ሙሴ፣ እስራኤላውያንን የባረካቸው ሲሆን በንግግሩ መደምደሚያ ላይ እንዲህ ብሏል፦ “እስራኤል ሆይ፤ አንተ ቡሩክ ነህ፤ እግዚአብሔር ያዳነው ሕዝብ፣ እንዳንተ ያለ ማን አለ? እርሱ ጋሻህና ረዳትህ፣ የክብርህም ሰይፍ ነው።”​—ዘዳ. 33:29

ምን ትምህርት እናገኛለን?

17, 18. (ሀ) ለሕይወት የምናደርገውን ሩጫ በተመለከተ “የምሥክሮች ደመና” ከተባሉት ምን ትምህርት እናገኛለን? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?

17 በዙሪያችን ካሉት “የምሥክሮች ደመና” መካከል የአንዳንዶቹን ምሳሌ መመርመራችን ሩጫውን እስከ መጨረሻ ለመሮጥ እንድንችል በአምላክና እሱ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ ጽኑ እምነት ማሳደር እንዳለብን እንድንገነዘብ ረድቶናል። (ዕብ. 11:6) እምነት አንዳንድ ጊዜ ብቻ የምናንጸባርቀው ባሕርይ ሳይሆን በአኗኗራችን ሁሉ መታየት ያለበት ነገር ነው። እምነት ከሌላቸው ሰዎች በተቃራኒ የይሖዋ አገልጋዮች የወደፊቱን ጊዜ አሻግረው መመልከት ይችላሉ። “የማይታየውን” ማየት ስለምንችል ሩጫውን በጽናት መሮጥ እንችላለን።​—2 ቆሮ. 5:7

18 ክርስቲያኖች የሚካፈሉበት የሩጫ ውድድር ቀላል አይደለም። ያም ሆኖ ውድድሩን በተሳካ ሁኔታ ማጠናቀቅ እንችላለን። ይህን ለማድረግ የሚረዱንን ተጨማሪ ሐሳቦች በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንመለከታለን።

ልታብራራ ትችላለህ?

• ጳውሎስ ስለ ጥንቶቹ ታማኝ ምሥክሮች በዝርዝር የጻፈው ለምን ነበር?

• “የምሥክሮች ደመና በዙሪያችን” እንዳሉ አድርገን ማሰባችን በጽናት እንድንሮጥ የሚያበረታታን እንዴት ነው?

• እንደ ኖኅ፣ አብርሃም፣ ሣራ እና ሙሴ ያሉትን ታማኝ ምሥክሮች ታሪክ በመመርመርህ ምን ትምህርት አግኝተሃል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አብርሃምና ሣራ በዑር የነበራቸውን የተመቻቸ ሕይወት ትተው ለመሄድ ፈቃደኞች ነበሩ