በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አብረን ሐሴት እናድርግ!

አብረን ሐሴት እናድርግ!

አብረን ሐሴት እናድርግ!

ደስተኛ መሆን ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል። ብዙዎች፣ ከሌሎች ጋር መንፈስን የሚያድስ ውይይት ማድረግ የማይቻል ነገር እንደሆነ ይሰማቸዋል። በተለይ በትልልቅ ከተሞች ውስጥ የሚታየው ዘመናዊው የአኗኗር ዘይቤ ሰዎች በራሳቸው ሕይወት ላይ ብቻ እንዲያተኩሩና የብቸኝነት ሕይወት እንዲመሩ ያደርጋቸዋል።

የሳይኮባዮሎጂ ፕሮፌሰር የሆኑት አልቤርቶ ኦሊቬሪኦ “ብቸኝነት በጣም የተለመደ ነገር ሆኗል” በማለት ተናግረዋል። አክለውም እንዲህ ብለዋል፦ “በትልልቅ ከተሞች ውስጥ ያለው የአኗኗር ዘይቤ ብቸኝነትን እንደሚያባብስ ምንም ጥርጥር የለውም። እንዲህ ያለው አኗኗር ብዙውን ጊዜ ስለ ሥራ ባልደረባችን፣ ስለ ጎረቤታችን ወይም በአካባቢያችን ባለው የገበያ ማዕከል ውስጥ ስለሚሠራው ገንዘብ ተቀባይ ሕይወት እንዳናስብ ያደርገናል።” እንዲህ ዓይነት የብቸኝነት አኗኗር ብዙውን ጊዜ የመንፈስ ጭንቀት ያስከትላል።

በክርስቲያኖች መካከል የሚታየው መንፈስና ያሉበት ሁኔታ ግን ከዚህ የተለየ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ” ሲል ጽፏል። (1 ተሰ. 5:16) አብረን የምንደሰትባቸውና ሐሴት የምናደርግባቸው ብዙ ምክንያቶች አሉን። ሉዓላዊውን አምላክ ይሖዋን እናመልካለን፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን የእውነት መልእክት መረዳት ችለናል፤ የመዳንና የዘላለም ሕይወት ተስፋ አለን እንዲሁም ሌሎች እነዚህን በረከቶች እንዲያገኙ መርዳት እንችላለን።​—መዝ. 106:4, 5፤ ኤር. 15:16፤ ሮም 12:12

መደሰትና ከሌሎች ጋር አብሮ ሐሴት ማድረግ የእውነተኛ ክርስቲያኖች መለያ ናቸው። በመሆኑም ሐዋርያው ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ለሚገኙት ክርስቲያኖች እንደሚከተለው ብሎ መጻፉ የሚያስገርም አይደለም፦ “ደስ ይለኛል፤ እንዲሁም ከሁላችሁም ጋር ሐሴት አደርጋለሁ። እንግዲህ እናንተም ልክ እንደዚሁ ተደሰቱ፤ ከእኔም ጋር ሐሴት አድርጉ።” (ፊልጵ. 2:17, 18) ጳውሎስ በዚህ አጭር ሐሳብ ውስጥ ደስተኛ ስለመሆንና ሐሴት ስለማድረግ ሁለት ጊዜ ጠቅሷል።

እርግጥ ነው፣ ክርስቲያኖች ራስን የማግለል ዝንባሌን ማስወገድ አለባቸው። ራሱን የሚያገልል ማንም ሰው ከእምነት ባልንጀሮቹ ጋር መደሰት አይችልም። ታዲያ ጳውሎስ፣ ከወንድሞቻችን ጋር ‘በጌታ መደሰታችንን እንድንቀጥል’ የሰጠውን ማበረታቻ ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?​—ፊልጵ. 3:1

ከእምነት ባልንጀሮቻችሁ ጋር ደስ ይበላችሁ

ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ለሚገኙት ክርስቲያኖች ደብዳቤ የጻፈው በስብከቱ ሥራው ምክንያት በሮም ታስሮ በነበረበት ወቅት ሳይሆን አይቀርም። (ፊልጵ. 1:7፤ 4:22) በእስር ላይ መሆኑ ግን ለአገልግሎቱ የነበረውን ቅንዓት አላቀዘቀዘበትም። ከዚህ በተቃራኒ አቅሙ የፈቀደውን ያህል ይሖዋን በተሟላ መንገድ በማገልገሉና “እንደ መጠጥ መሥዋዕት [መፍሰስ]” በመቻሉ ደስተኛ ነበር። (ፊልጵ. 2:17) የጳውሎስ አመለካከት ደስታ አንድ ሰው ባለበት ሁኔታ ላይ የተመካ እንዳልሆነ ያሳያል። በእስር ላይ የነበረ ቢሆንም እንኳ “ወደፊትም . . . መደሰቴን እቀጥላለሁ” ብሏል።​—ፊልጵ. 1:18

በፊልጵስዩስ የነበረውን ጉባኤ ያቋቋመው ጳውሎስ በመሆኑ በዚያ ለነበሩት ወንድሞች ልዩ ፍቅር ነበረው። ይሖዋን በማገልገል ስላገኘው ደስታ ቢነግራቸው እነሱም እንደሚበረታቱ ያውቅ ነበር። በመሆኑም እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እንግዲህ ወንድሞች፣ በእኔ ላይ የደረሱት ነገሮች ለምሥራቹ እንቅፋት ከመሆን ይልቅ ይበልጥ እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ እንዳደረጉ እንድታውቁ እወዳለሁ፤ በመሆኑም ከክርስቶስ ጋር በተያያዘ መታሰሬ በንጉሠ ነገሥቱ የክብር ዘብ ሁሉና በቀሩትም ሁሉ ዘንድ በይፋ ታውቋል።” (ፊልጵ. 1:12, 13) ጳውሎስ ከወንድሞቹ ጋር ለመደሰትና ሐሴት ለማድረግ ሲል ከተጠቀመባቸው መንገዶች አንዱ ይህን የሚያበረታታ ተሞክሮ ለእነሱ መናገሩ ነበር። በፊልጵስዩስ የነበሩት ክርስቲያኖችም ከጳውሎስ ጋር ተደስተው መሆን አለበት። እርግጥ ነው፣ ከእሱ ጋር ለመደሰት እንዲችሉ ጳውሎስ ባጋጠመው ነገር ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ የእሱን ምሳሌ መከተል ነበረባቸው። (ፊልጵ. 1:14፤ 3:17) ከዚህም በተጨማሪ የፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች ጳውሎስን ሁልጊዜ በጸሎታቸው ማሰብ እንዲሁም በተቻላቸው መጠን እሱን መርዳትና መደገፋቸውን መቀጠል ይችሉ ነበር።​—ፊልጵ. 1:19፤ 4:14-16

እኛስ የጳውሎስ ዓይነት የደስተኝነት መንፈስ እናሳያለን? በሕይወታችንና በክርስቲያናዊ አገልግሎታችን የሚያጋጥሙንን ሁኔታዎችና እነዚህ ነገሮች ያሏቸውን መልካም ገጽታዎች ለማሰብ እንጥራለን? ከወንድሞቻችን ጋር በምንሆንበት ጊዜ በስብከቱ ሥራችን ስላገኘናቸው አስደሳች ነገሮች ማንሳታችን ጥሩ ነው። ይህን ለማድረግ በጣም አስገራሚ የሆነ ተሞክሮ ማግኘት አያስፈልገንም። ውጤታማ የሆነ አንድ የመግቢያ ሐሳብ በመጠቀም ወይም ምክንያታዊ የሆኑ ነጥቦችን በማቅረብ ሰዎች ለመንግሥቱ መልእክት ፍላጎት እንዲያድርባቸው መርዳት ችለን ይሆናል። ምናልባትም ከቤቱ ባለቤት ጋር በአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ ጥሩ ውይይት አድርገን ሊሆን ይችላል። አሊያም ደግሞ በአገልግሎት ክልላችን ውስጥ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች መሆናችንን መገንዘባቸው በራሱ ግሩም ምሥክርነት ለመስጠት አስችሎን ይሆናል። እንዲህ ያሉ ተሞክሮዎችን መለዋወጣችን አብረን መደሰት ከምንችልባቸው መንገዶች አንዱ ነው።

ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች የስብከቱን ሥራ ለማከናወን ሲሉ የተለያዩ መሥዋዕቶችን ከፍለዋል አሁንም እየከፈሉ ነው። አቅኚዎች፣ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች፣ ቤቴላውያን፣ ሚስዮናውያንና ዓለም አቀፍ አገልጋዮች ሙሉ ጊዜያቸውን ለአምላክ አገልግሎት የሰጡ ሲሆን በዚህም ደስታ ያገኛሉ። እኛስ በዚህ እንደሰታለን? ከእነሱ ጋር ሐሴት እናደርጋለን? እንግዲያው ‘ለአምላክ መንግሥት አብረው ለሚሠሩት’ ለእነዚህ ውድ ወንድሞቻችን ያለንን አድናቆት እናሳይ። (ቆላ. 4:11) በጉባኤ ስብሰባዎች እንዲሁም በትላልቅ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አብረናቸው ስንገኝ ሞቅ ባለ መንገድ እናበረታታቸው። በተጨማሪም ቅንዓታቸውን መኮረጅ እንችላለን። ከዚህም ሌላ እንግዳ ተቀባዮች በመሆን ምናልባትም ቤታችን ምግብ በመጋበዝ ተሞክሯቸውንና የሚናገሯቸውን የሚያንጹ ሐሳቦች ለማዳመጥ “አጋጣሚ” መፍጠር እንችላለን።​—ፊልጵ. 4:10

በመከራ ውስጥ ካሉት ጋር ደስ ይበላችሁ

ጳውሎስ የደረሰበትን ስደት በጽናት ማሳለፉና መከራዎችን መቋቋሙ ለይሖዋ ታማኝ ሆኖ ለመቀጠል የወሰደውን ቁርጥ አቋም አጠናክሮለታል። (ቆላ. 1:24፤ ያዕ. 1:2, 3) ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ያሉት ወንድሞቹ ተመሳሳይ ፈተናዎች ሊያጋጥሟቸው እንደሚችሉና የእሱ መጽናት እንደሚያበረታታቸው ማወቁ ከእነሱ ጋር ለመደሰት ብሎም ሐሴት ለማድረግ አስችሎታል። ከዚህም የተነሳ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እናንተ በክርስቶስ እንድታምኑ ብቻ ሳይሆን ለእሱ ስትሉ መከራ እንድትቀበሉም መብት ተሰጥቷችኋል። በመሆኑም በእኔ ሁኔታ ያያችሁትንና አሁንም እያደረግኩት እንዳለ የሰማችሁትን ያንኑ ትግል እናንተም እያደረጋችሁ ነው።”​—ፊልጵ. 1:29, 30

ዛሬም ቢሆን ክርስቲያኖች በስብከቱ ሥራቸው የተነሳ ስደት ይደርስባቸዋል። አንዳንድ ጊዜ ይህ ተቃውሞ የኃይል ድርጊት የታከለበት ሲሆን ብዙውን ጊዜ ግን ተቃውሞው የሚመጣው በረቀቀ መንገድ ነው። ከሃዲዎች የሐሰት ክሶችን ሊሰነዝሩብን፣ የቤተሰባችን አባላት ሊቃወሙን እንዲሁም የሥራ ባልደረቦቻችን ወይም አብረውን የሚማሩት ልጆች ሊያሾፉብን ይችላሉ። ኢየሱስ እነዚህ ፈተናዎች ሊያስደንቁንም ሆነ ተስፋ ሊያስቆርጡን እንደማይገባ እንዲያውም ለመደሰት ምክንያት እንደሚሆኑን ተናግሯል። እንዲህ ብሎ ነበር፦ “በእኔ ምክንያት ሰዎች ሲነቅፏችሁ፣ ስደት ሲያደርሱባችሁና ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲያስወሩባችሁ ደስተኞች ናችሁ። በሰማያት ያለው ሽልማታችሁ ታላቅ ስለሆነ ሐሴት አድርጉ፣ በደስታም ፈንጥዙ።”​—ማቴ. 5:11, 12

በአንዳንድ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ወንድሞቻችን ከባድ ስደት እየደረሰባቸው እንዳለ ስንሰማ ልንደናገጥም ሆነ በፍርሃት ልንርድ አይገባም። ከዚህ ይልቅ በመጽናታቸው ልንደሰት ይገባል። ይሖዋ፣ እምነታቸውን ጠብቀው መኖርና መጽናት እንዲችሉ እንዲረዳቸው ልንጸልይላቸው እንችላለን። (ፊልጵ. 1:3, 4) እነዚህን ውድ ወንድሞቻችንን ለመርዳት ብዙም ማድረግ የምንችለው ነገር ባይኖርም በጉባኤያችን ውስጥ መከራ እየደረሰባቸው ያሉትን መርዳት እንችላለን። ለእነዚህ ወንድሞች ትኩረት በመስጠት ልንደግፋቸው እንችላለን። አልፎ አልፎ በቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማችን ላይ እንዲገኙ በመጋበዝ፣ በአገልግሎት አብረናቸው በመካፈል እንዲሁም አብረናቸው በመዝናናት ከእነሱ ጋር ለመደሰት የሚያስችሉንን አጋጣሚዎች መፍጠር እንችላለን።

በእርግጥም አብረን ለመደሰት የሚያስችሉን ብዙ ምክንያቶች አሉን! ይህ ዓለም ራሳችንን እንድናገልል የሚያሳድርብንን ተጽዕኖ በመቋቋም ከወንድሞቻችን ጋር አብረን መደሰታችንን እንቀጥል። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ጉባኤው ፍቅርና አንድነት እንዲኖረው አስተዋጽኦ ከማበርከት በተጨማሪ ከክርስቲያናዊው የወንድማማች ማኅበር የተሟላ ጥቅም ማግኘት እንችላለን። (ፊልጵ. 2:1, 2) አዎን፣ ጳውሎስ እንዳለው “ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ። ደግሜ እላለሁ ደስ ይበላችሁ!”​—ፊልጵ. 4:4

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Globe: Courtesy of Replogle Globes