በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

መጽሐፍ ቅዱስን ሳነብ ካገኘሁት አንድ ሐሳብ ወይም በግል ከገጠመኝ ችግር ጋር በተያያዘ ጥያቄ ቢፈጠርብኝ ምን ማድረግ ይኖርብኛል?

ምሳሌ 2:1-5 እያንዳንዳችን የመለየት ጥበብንና ማስተዋልን ‘እንደ ተሸሸገ ሀብት አጥብቀን እንድንሻ’ ያበረታታናል። ይህም ለተፈጠሩብን ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘትም ሆነ ያጋጠመንን የግል ችግር ለመፍታት ትጋት የተሞላበት ምርምር ማድረግ እንዳለብን ይጠቁማል። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም የተባለው መጽሐፍ ከገጽ 33 እስከ 38 ላይ “ታማኝና ልባም ባሪያ” ያዘጋጃቸውን መሣሪያዎች በመጠቀም ‘ምርምር ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ’ ያብራራል። (ማቴ. 24:45) በገጽ 36 ላይ የመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች ማውጫን እንዴት መጠቀም እንደምንችል ተብራርቷል፤ ማውጫው የርዕሰ ጉዳይ ማውጫና የጥቅስ ማውጫ ተብሎ ለሁለት ተከፍሏል። ይህም ቁልፍ ቃላትን ወይም ጥቅሶችን በመጠቀም የምንፈልገውን ርዕሰ ጉዳይ ለማግኘት ያስችለናል፤ በርዕሰ ጉዳዩ ሥር ደግሞ የተለያዩ የማመሳከሪያ ጽሑፎችን ማግኘት እንችላለን። ለጥያቄህ መልስ ለማግኘት ወይም የሚያስፈልግህን መመሪያ ለማግኘት በትዕግሥት ምርምር ማድረግ ይኖርብሃል። ‘የተሸሸገን ሀብት’ እየፈለግህ እንደሆነ አስታውስ፤ ይህ ደግሞ ጊዜና ጥረት ይጠይቃል።

እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ርዕሰ ጉዳዮችና ጥቅሶች በጽሑፎቻችን ላይ በግልጽ አልተብራሩ ይሆናል። በጽሑፎቻችን ላይ አንድን ጥቅስ የሚያብራራ ሐሳብ ብናሰፍርም እንኳ አንተ ላነሳኸው ጥያቄ መልስ ላይሆን ይችላል። በተጨማሪም በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ እያንዳንዱ ዝርዝር ጉዳይ ስላልሰፈረ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ጥያቄ ሊያስነሱ ይችላሉ። በመሆኑም ለሚነሱብን ጥያቄዎች ሁሉ ወዲያውኑ መልስ ላናገኝ እንችላለን። እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥመን መልስ ሊገኝላቸው ለማይችሉ ነገሮች ግምታዊ ሐሳብ ከመሰንዘር መቆጠብ ይኖርብናል፤ ምክንያቱም ይህ ‘እምነትን የሚያጠናክሩ ከአምላክ የሚገኙ ነገሮች ለሌሎች እንዲዳረሱ ከማድረግ ይልቅ እርባና ቢስ ጥያቄዎችን’ በማስነሳት እንድንከራከር ሊያደርገን ይችላል። (1 ጢሞ. 1:4፤ 2 ጢሞ. 2:23፤ ቲቶ 3:9) ቅርንጫፍ ቢሮውም ሆነ ዋናው መሥሪያ ቤት ከዚህ በፊት በጽሑፎቻችን ላይ ላልወጡ እንዲህ ለመሰሉ ጥያቄዎች በሙሉ ማብራሪያና መልስ ሊሰጥ አይችልም። መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወታችንን ለመምራት የሚያስችሉ በቂ መረጃዎችን የያዘ በመሆኑ ልንደሰት ይገባናል፤ ይሁን እንጂ ይህ መጽሐፍ ዝርዝር ማብራሪያዎችን አለመያዙ በአምላክ ላይ ጠንካራ እምነት እንዳለን ለማሳየት አጋጣሚ ይሰጠናል።​—ወደ ይሖዋ ቅረብ የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 185 እስከ 187 ተመልከት።

አንተን ስላሳሰበህ ነገር የቻልከውን ያህል ምርምር ብታደርግም የሚያስፈልግህን መመሪያ ወይም የመፍትሔ ሐሳብ ማግኘት ባትችልስ? ጉዳዩን በተመለከተ በመንፈሳዊ የጎለመሰ የእምነት ባልንጀራህን ምናልባትም ከጉባኤያችሁ ሽማግሌዎች አንዱን ቀርበህ ከማነጋገር ወደኋላ አትበል። እነዚህ ሰዎች ጥሩ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ያላቸው ሲሆን በክርስቲያናዊ አኗኗርም ተሞክሮ አካብተዋል። የገጠመህን ችግር በተመለከተ ምክር መጠየቅ ብትፈልግ ወይም አንድ ዓይነት ውሳኔ ማድረግ ቢያስፈልግህ ሽማግሌዎች አንተንም ሆነ ያለህበትን ሁኔታ ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ሚዛናዊነት የሚንጸባረቅበት ምክር ሊለግሱህ ይችላሉ። በተጨማሪም ይሖዋ ‘ጥበብንና ማስተዋልን’ ስለሚሰጥ ያሳሰበህን ነገር ለይተህ በመጥቀስ ወደ እሱ መጸለይንና በመንፈስ ቅዱሱ አማካኝነት አመራር እንዲሰጥህ መጠየቅን ፈጽሞ መርሳት የለብህም።​—ምሳሌ 2:6፤ ሉቃስ 11:13